ለሰዎች በሥራ ቦታቸው መመሥከር
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ለሰዎች በሥራ ቦታቸው መመሥከር
ማቴዎስ፣ ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የተባሉትን ሐዋርያት ምን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ? ኢየሱስ ሁሉንም የጠራቸው በሥራ ገበታቸው ላይ እያሉ ነበር። “ኑ፣ ተከተሉኝ” በማለት ሲጋብዛቸው ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ዓሣ እያጠመዱ የነበረ ሲሆን ማቴዎስ ደግሞ በቀረጥ መሰብሰቢያ ቢሮው ነበር።—ማቴዎስ 4:18-21፤ 9:9
ወደ ሥራ ቦታቸው ሄዶ ለሰዎች መመሥከር ጥሩ ውጤቶች ሊያስገኝ ይችላል። በጃፓን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን በመገንዘባቸው በቅርቡ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል የተቀናጀ ጥረት አድርገው ነበር። ምን ውጤት አገኙ? በጥቂት ወራት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ተመላልሶ መጠየቆች ያደረጉ ሲሆን ወደ 250 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀምረዋል። ቀጥሎ የቀረቡትን ተሞክሮዎች ተመልከት።
በቶኪዮ የሚኖር የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለአንድ የምግብ ቤት ኃላፊ መሠከረለት፤ ግለሰቡ ከ30 ዓመታት በፊት ተማሪ እያለ አንድ የይሖዋ ምሥክር አነጋግሮት ነበር። ኃላፊው በዚያን ጊዜ ከሰማው ነገር አብዛኛውን ባይረዳውም መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎት አድሮበት ነበር። አሁን ፍላጎቱ እንደገና ስለተነሳሳ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። a ከዚህም በላይ ሁልጊዜ ማታ ማታ ከመተኛቱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመረ።
አንዲት ልዩ አቅኚ ወደ አንድ ቢሮ በመሄድ ሥራ አስኪያጁን ለማነጋገር ጠየቀች። ሥራ አስኪያጁን ማግኘት ባትችልም ስልኩን ያነሳችው ወጣት “እኔን ልታነጋግሪኝ ትፈልጊያለሽ?” አለቻት። በስልክ አጠር ያለ ውይይት ካደረጉ በኋላ ወጣቷ ወደ እንግዳ መቀበያው ቦታ መጣችና መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ፍላጎት እንዳላት ነገረቻት። ልዩ አቅኚዋ መጽሐፍ ቅዱስ ልታመጣላት በቀጠሮ ተለያዩ። ወጣቷ ጠዋት ሥራ ከመግባቷ በፊት በቢሮዋ አቅራቢያ በሚገኝ መናፈሻ ውስጥ ማጥናት ጀምረዋል።
በሌላ ቢሮ ውስጥ የሚሠራ ሰው የሥራ ባልደረባው ከአንድ የይሖዋ ምሥክር መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ከተቀበለች በኋላ ምሥክሩ እንደወጣ መጽሔቶቹን ስትጥላቸው ተመለከተ። ሰውየው ወደ ቤቱ ሲመለስ፣ የይሖዋ ምሥክር ለሆነችው ባለቤቱ ስለሁኔታው ከነገራት በኋላ እርሱ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ለትንሽ ጊዜ ያዳምጥ እንደነበረ ገለጸ። እንዲህ ሲል የሰማችው ሴት ልጁ አባቷ በሚሠራበት አካባቢ ለሚያገለግል አንድ ምሥክር ጉዳዩን አጫወተችው። ምሥክሩም ጊዜ ሳያጠፋ ባልየው ወደሚገኝበት ቢሮ ሄደና ከእርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ሰውየው እሁድ ዕለት በሚደረገው ስብሰባ ላይ አዘውትሮ መገኘት ጀመረ።
ለሰዎች በሥራ ቦታቸው መመሥከር ሌሎች ጥቅሞችም አሉት። በጃፓን የሚገኙት አብዛኞቹ አስፋፊዎች በሱቆች፣ በፋብሪካዎችና በቢሮዎች አካባቢ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ጥሩ ችሎታ አዳብረዋል። ከዚህም በላይ በዚህ መንገድ ምሥክርነት መሰጠቱ ጉባኤ መምጣት አቁመው የነበሩ በርካታ ወንድሞችና እህቶችን ለማግኘትና ጥናት ለማስጀመር አስችሏል። በዚህም አስደናቂ ውጤት ተገኝቷል። በማዕከላዊ ቶኪዮ የሚገኝ አንድ ጉባኤ በቅርቡ 108 ጥናቶች እንደተመሩ ሪፖርት አድርጓል፤ ይህም ባለፈው ዓመት ሪፖርት ከተደረገው ከእጥፍ በላይ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።