በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በላይቤሪያ ጦርነት ቢኖርም ጭማሪ ተገኝቷል

በላይቤሪያ ጦርነት ቢኖርም ጭማሪ ተገኝቷል

በላይቤሪያ ጦርነት ቢኖርም ጭማሪ ተገኝቷል

ላይቤሪያ ከአሥር ለሚበልጡ ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ቆይታለች። በ2003 አጋማሽ ላይ ዓማፅያኑ ዋና ከተማዋን ሞንሮቪያን ተቆጣጠሩ። አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች በተደጋጋሚ ጊዜያት ቤታቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገድደዋል። ብዙ ጊዜም ንብረታቸው ይዘረፍባቸው ነበር።

የሚያሳዝነው በዋና ከተማዋ በተካሄደው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህም መካከል ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች (አንድ ወንድምና አንዲት እህት) ይገኙበታል። ሌሎች ወንድሞች ችግሩን እንዴት ተወጡት? እነርሱን ለመርዳትስ ምን ተደርጓል?

ለተቸገሩት እርዳታ ማቅረብ

ጦርነቱ በሚካሄድበት ጊዜ ሁሉ በላይቤሪያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ችግር ላይ የወደቁት ወንድሞች እርዳታ የሚያገኙበት ዝግጅት አድርጓል። ምግብ፣ መሠረታዊ የሆኑ የቤት ዕቃዎችና የሕክምና ቁሳቁሶች ያቀርብ ነበር። ዓማፅያኑ የወደቡን አካባቢ በተቆጣጠሩበት ወቅት የምግብ ችግር ተከሰተ። ቅርንጫፍ ቢሮው ይህ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ስለነበር በከተማው ውስጥ ወደሚገኙ የመንግሥት አዳራሾች ለሸሹት ሁለት ሺህ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማቅረብ ችሏል። ወንድሞች ወደቡ እንደገና እስከሚከፈትበት ጊዜ ድረስ እንዲያቆያቸው ለማድረግ ያለውን ምግብ እያመጣጠኑ ያከፋፍሉ ነበር። በቤልጅየምና በሴራሊዮን የሚገኙት ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሕክምና ቁሳቁሶችን በአውሮፕላን ሲልኩ የብሪታንያና የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ደግሞ ልብስ ላኩ።

ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም ወንድሞቻችን ደስተኞች ከመሆናቸውም በላይ ብሩሕ አመለካከት ነበራቸው። ሦስት ጊዜ ቤቱን ጥሎ ለመሸሽ የተገደደ አንድ ወንድም የሰጠው አስተያየት የብዙዎቹን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። “የምንሰብከው እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር አይደል? ያለነው በመጨረሻው ቀን ውስጥ ነው” ብሏል።

ሰዎች ለምሥራቹ የሰጡት ምላሽ

በአገሪቱ በአጠቃላይ ብጥብጥ ቢነግስም የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ ግሩም ውጤት እያገኙ ነው። በጥር 2003፣ 3,879 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ሲገኝ በየካቲት ደግሞ ምሥክሮቹ 15,227 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መርተዋል።

ሰዎች ለምሥራቹ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣሉ። በአገሪቱ ደቡብ ምሥራቅ ከሚገኝ መንደር የተገኘ ተሞክሮ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። አንድ ጉባኤ ቀደም ሲል ይሰበሰቡበት ከነበረው ቦታ በእግር የአምስት ሰዓት መንገድ ርቆ በሚገኝ በዋን በተባለ ትልቅ መንደር ውስጥ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ያቅዳል። ወንድሞች የመንደሩን ነዋሪዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ከመጋበዛቸው በፊት የበዋንን ከንቲባ ጋበዙት። ከንቲባው ጥሪው ሲደርሰው መጽሐፍ ቅዱሱን ይዞ ወደ መንደሩ ነዋሪዎች በመሄድ በግብዣ ወረቀቱ ላይ የሚገኘውን ጥቅስ እያነበበ በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ አበረታታቸው። አስፋፊዎቹ ወደ መንደሩ ሲሄዱ ሥራቸው ተጠናቅቆ ጠበቃቸው! ከንቲባው ከልጆቹና ከሁለት ሚስቶቹ ጋር በመሆን በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኘ። በበዓሉ ላይ በአጠቃላይ 27 ሰዎች ተገኝተው ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከንቲባው ከሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ወጥቶ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረ ሲሆን ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ የሚሆን መሬት ሰጥቷል።

የአመለካከት ለውጥ

የአንዳንድ ተቃዋሚዎችን አመለካከት በመለወጥ ረገድ የወንድሞቻችን መልካም ባሕርይም አስተዋጽኦ አድርጓል። ኦፖኩ የተባለውን ሰው እንደ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ልዩ አቅኚ በስብከቱ ሥራ ላይ እያለ ያገኘውና መጠበቂያ ግንብ እንዲወስድ ጋበዘው። ኦፖኩ በመጽሔቱ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ ቢማርከውም ገንዘብ አልነበረውም። አቅኚው እንደማይከፈልበት ከነገረው በኋላ መጽሔቱን ሰጠውና ሌላ ጊዜ ለመገናኘት ቀጠሮ ያዙ። በድጋሚ ሲገናኙ ኦፖኩ አቅኚውን “በሃርፐር ከተማ የሚገኙ አብዛኞቹ የእናንተ ሰዎች ያውቁኛል። ልጆቻችሁን ከትምህርት ቤት አባርር ነበር! አንተስ ከዚህ በፊት አታውቀኝም?” ሲል ጠየቀው። ከዚያም በከተማው ውስጥ በሚገኘው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዲሬክተር እያለ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ለባንዲራ ሰላምታ ባለመስጠታቸው ያስቸግራቸው እንደነበረ ነገረው።

ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮችን ክርስቲያናዊ ፍቅር የተመለከተባቸው ሦስት አጋጣሚዎች አመለካከቱን እንደገና እንዲመረምር አነሳሱት። በመጀመሪያ፣ ምሥክሮቹ በጠና የታመመ አንድ መንፈሳዊ ወንድማቸውን ሲንከባከቡ ተመለከተ። እንዲያውም ይህ ወንድማቸው ወደ ጎረቤት አገር ሄዶ እንዲታከም ዝግጅት አደረጉለት። ኦፖኩ የታመመው ወንድም በይሖዋ ምሥክሮች መካከል “ትልቅ ቦታ ያለው ሰው” እንደሆነ አስቦ ነበር፤ ሆኖም ምሥክሩ የተለየ ቦታ እንደሌለው አወቀ። ሁለተኛ፣ በ1990ዎቹ ዓመታት ኦፖኩ በኮት ዲቩዋር ስደተኛ ሆኖ ይኖር ነበር። አንድ ቀን ውኃ ይጠማውና ለመግዛት ወደ አንድ ወጣት ይሄዳል። ወጣቱ ለኦፖኩ የሚመልስለት ዝርዝር ብር ስላልነበረው ውኃውን በነፃ ሰጠው። ለኦፖኩ ውኃውን ሲሰጠው “እንደ እኔና እንደ አንተ ያሉ ሰዎች ገንዘብ ሳያስፈልግ መገበያየት የሚችሉበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልሃል?” ብሎ ጠየቀው። ኦፖኩ ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆን አለበት ሲል አሰበ፤ ወጣቱም ግምቱ ትክክል እንደሆነ አረጋገጠለት። ኦፖኩ ይህ ወንድም ያሳየው ለጋስነትና ደግነት አስደነቀው። በመጨረሻም ልዩ አቅኚው አለምንም ክፍያ መጽሔቱን ሊሰጠው ፈቃደኛ በመሆኑ ኦፖኩ ስለ ምሥክሮቹ ያለው አመለካከት የተሳሳተ እንደሆነና አስተሳሰቡን መለወጥ እንዳለበት ተገነዘበ። መንፈሳዊ እድገት በማድረግ አሁን ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኗል።

በላይቤሪያ ያሉት ወንድሞች አሁንም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያጋጠሟቸው ቢሆንም በአምላክ በመታመን በእርሱ መንግሥት ግዛት ሥር የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጸውን የምሥራች በታማኝነት ይሰብካሉ። ይሖዋም በትጋት ያከናወኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር ፈጽሞ አይረሳውም።—ዕብራውያን 6:10

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሞንሮቪያ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጦርነቱ ወቅት የይሖዋ ሕዝቦች ችግር ላይ ለወደቁት ወንድሞቻቸው መንፈሳዊና ሥጋዊ እርዳታ አድርገዋል