በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሕይወታችሁ የሚያጋጥሟችሁን ለውጦች ለመቋቋም በአምላክ መንፈስ ታመኑ

በሕይወታችሁ የሚያጋጥሟችሁን ለውጦች ለመቋቋም በአምላክ መንፈስ ታመኑ

በሕይወታችሁ የሚያጋጥሟችሁን ለውጦች ለመቋቋም በአምላክ መንፈስ ታመኑ

“በአምላክ ፊት ሞገስ ለማግኘት ትጋ።”—2 ጢሞቴዎስ 2:15 NW

1. በመንፈሳዊ ደህንነታችን ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ለውጦች የትኞቹ ናቸው?

 በዙሪያችን ባለው ዓለም ውስጥ ሁልጊዜ ለውጥ ይታያል። በሳይንስና በቴክኖሎጂ መስክ አስደናቂ የሆነ እድገት ተመዝግቧል፤ በዚያው መጠን ደግሞ የሥነ ምግባር ደንቦች በጣም እያሽቆለቆሉ መጥተዋል። በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ክርስቲያኖች ከአምላክ ርቆ ያለውን የዚህን ዓለም መንፈስ መቋቋም አለባቸው። ይሁን እንጂ ዓለም እንደሚለወጠው ሁሉ እኛም በብዙ መንገዶች እንለወጣለን። ከልጅነት ወደ ጉልምስና እንሸጋገራለን። ገንዘብ ልናገኝ ወይም ልናጣ፣ ጤንነታችን ሊያሽቆለቁል እንዲሁም ወዳጆች ልናፈራ ወይም በሞት ልናጣ እንችላለን። እነዚህን የመሳሰሉ አብዛኞቹ ለውጦች ከቁጥጥራችን ውጪ ከመሆናቸውም ሌላ በመንፈሳዊ ደህንነታችን ላይ አዳዲስና ከባድ ፈተናዎች ሊጋርጡብን ይችላሉ።

2. ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ምን ዓይነት ለውጦች አይቷል?

2 የእሴይ ልጅ፣ የዳዊትን ያህል በሕይወታቸው ውስጥ ብዙ ለውጦችን ያስተናገዱ ሰዎች ቢኖሩ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ተራ ሰው የነበረው ዳዊት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከእረኝነት ተነስቶ በአገሩ የታወቀ ጀግና ለመሆን በቅቷል። ከጊዜ በኋላ፣ ቅንዓት ያደረበት አንድ ንጉሥ እንደ እንስሳ ስላሳደደው ከቦታ ቦታ እየኮበለለ ለመኖር ተገደደ። ከዚያም ዳዊት የንግሥና ሥልጣን ያዘ እንዲሁም በርካታ ድሎችን ተቀዳጀ። ከባድ ኃጢአት መሥራት የሚያስከትለውን አስከፊ መዘዝ ቀመሰ። በቤተሰቡ ውስጥ አሳዛኝ መከራና መከፋፈል አጋጠመው። ሀብት አካበተ፣ ሸመገለ፤ እርጅናም አጎሳቆለው። ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ብዙ ለውጦች ቢያጋጥሙትም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በይሖዋና በመንፈሱ ላይ ትምክህትና እምነት አሳድሯል። “በአምላክ ፊት ሞገስ ለማግኘት” አቅሙ የፈቀደለትን ሁሉ አድርጓል፤ አምላክም ባርኮታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15 NW) ያለንበት ሁኔታ ከዳዊት የተለየ ቢሆንም በሕይወቱ ያጋጠሙትን ሁኔታዎች ከተቋቋመበት መንገድ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። እርሱ የተወው ምሳሌ በሕይወታችን ውስጥ ለውጦች ሲያጋጥሙን እንዴት ከአምላክ መንፈስ እርዳታ ማግኘት እንደምንችል እንድንገነዘብ ይረዳናል።

ዳዊት ትሕትና በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል

3, 4. እረኛ የነበረው ዳዊት በአገሩ የታወቀ ሰው ለመሆን የበቃው እንዴት ነው?

3 ዳዊት ልጅ እያለ በቤተሰቡ ውስጥም እንኳ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ሰው አልነበረም። ነቢዩ ሳሙኤል ወደ ቤተ ልሔም በመጣበት ወቅት የዳዊት አባት ከስምንት ወንዶች ልጆቹ መካከል ሰባቱን በፊቱ አቀረባቸው። የሁሉም ታናሽ የሆነው ዳዊት መስክ ላይ በጎች እየጠበቀ ነበር። ሆኖም ይሖዋ የወደፊቱ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው እርሱን ነበር። ዳዊት ካለበት ቦታ ተጠርቶ መጣ። ከዚያ ቀጥሎ የተፈጸመውን ሁኔታ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ በማለት ይገልጻል “ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ።” (1 ሳሙኤል 16:12, 13) ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በይሖዋ መንፈስ ታምኗል።

4 ይህ እረኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገሩ የታወቀ ሰው ሊሆን ነው። የንጉሡ አገልጋይ እንዲሆንና ሙዚቃ እንዲጫወትለት ተጠራ። የውጊያ ልምድ ያላቸው የእስራኤል ወታደሮች ለመግጠም የፈሩትን ጎልያድ የተባለውን ኃይለኛና ግዙፍ ወታደር ገደለ። ዳዊት የሠራዊቱ አዛዥ ከሆነ በኋላ ፍልስጥኤማውያንን ድል ነሳ። በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅነት አተረፈ፤ በዘፈንም አሞገሱት። የንጉሥ ሳኦል አገልጋይ የሆነ ሰው ቀደም ሲል ስለ ወጣቱ ዳዊት ‘መልካም አድርጎ በገና መደርደር ይችላል’ ከማለቱም ሌላ “ጀግናና ተዋጊ ነው፤ በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” ብሏል።—1 ሳሙኤል 16:18፤ 17:23, 24, 45-51፤ 18:5-7

5. ዳዊት እንዲታበይ ሊያደርገው የሚችል ምን ሁኔታ ነበረው? ሆኖም እንዲህ ዓይነት መንፈስ እንዳላደረበት እንዴት ማወቅ እንችላለን?

5 ዝነኛ፣ መልከ መልካም፣ በዕድሜ ለጋ፣ አንደበተ ርቱዕ የሆነውና ጥሩ የሙዚቃ ችሎታ፣ ወታደራዊ ጥበብና መለኮታዊ ሞገስ የነበረው ዳዊት በማንኛውም መስክ የተዋጣለት ሰው ነበር ማለት ይቻላል። ዳዊት ካሉት ችሎታዎች የተነሳ ሊታበይ ይችል ነበር። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ባሕርይ አላንጸባረቀም። ንጉሥ ሳኦል ልጁን ሊድርለት ሐሳብ ሲያቀርብለት ዳዊት የሰጠውን መልስ ተመልከት። ከልብ በመነጨ የትሕትና ስሜት “የንጉሥ ዐማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ቤተ ሰቤም ሆነ የአባቴ ጐሣስ በእስራኤል ዘንድ ምንድን ነው?” አለ። (1 ሳሙኤል 18:18) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር በዚህ ጥቅስ ላይ ሐሳብ ሲሰጡ እንዲህ ብለው ጽፈዋል “ዳዊት እንዲህ ብሎ ሲናገር የራሱ ማንነትም ሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ቦታ እንዲሁም የትውልድ ሐረጉ የንጉሡ አማች የመሆን ክብር ለማግኘት እንደማያበቃው መናገሩ ነበር።”

6. ትሕትና ማዳበር ያለብን ለምንድን ነው?

6 ዳዊት ትሑት እንዲሆን ያስቻለው ይሖዋ ፍጽምና ከሚጎድላቸው ሰዎች በማንኛውም መንገድ እጅግ የላቀ መሆኑን መገንዘቡ ነበር። አምላክ ለሰዎች ትኩረት የሚሰጥ መሆኑ እንኳ ዳዊትን በጣም አስገርሞታል። (መዝሙር 144:3) ከዚህ በተጨማሪ ምንም ዓይነት ክብር ቢኖረው ይህን ሊያገኝ የቻለው ይሖዋ ራሱን ዝቅ አድርጎ በትሕትና ስለረዳው፣ ስለጠበቀውና ስለተንከባከበው መሆኑን ተገንዝቧል። (መዝሙር 18:35) ይህ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ይዞልናል! ያሉን ተሰጥኦዎችና የአገልግሎት መብቶች እንዲሁም ያከናወንናቸው ነገሮች ሊያስታብዩን አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ያልተቀበልኸው የራስህ የሆነ ነገር ምን አለ? ከተቀበልህ ታዲያ፣ እንዳልተቀበልህ ለምን ትመካለህ?” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 4:7) የአምላክን ቅዱስ መንፈስና የእርሱን ሞገስ ማግኘት ከፈለግን የትሕትና ባሕርይ ማዳበርና ምንጊዜም በትሕትና መመላለስ ይኖርብናል።—ያዕቆብ 4:6

“አትበቀሉ”

7. ዳዊት ሳኦልን መግደል የሚችልበት ምን አጋጣሚ አግኝቶ ነበር?

7 ዳዊት ታዋቂ ሰው መሆኑ የትዕቢት መንፈስ ባያሳድርበትም የአምላክ መንፈስ በራቀው በንጉሥ ሳኦል ላይ ግን ለግድያ የሚያነሳሳ የምቀኝነት ስሜት አሳድሮበታል። ዳዊት የሠራው ጥፋት ባይኖርም ሕይወቱን ለማዳን ሸሽቶ በበረሃ ለመኖር ተገደደ። ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን በሄደበት ሁሉ እያሳደደው በነበረበት በአንድ ወቅት ዳዊትና ግብረ አበሮቹ ዋሻው ውስጥ መደበቃቸውን ሳያውቅ ወደዚያ ገባ። ከዳዊት ጋር ያሉት ሰዎች የአምላክ እጅ ያለበት በሚመስለው በዚህ አጋጣሚ ተጠቅሞ ሳኦልን እንዲገድለው ጎተጎቱት። ሰዎቹ ጨለማ ውስጥ ሆነው “እግዚአብሔር፣ ‘የወደድኸውን ታደርግበት ዘንድ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ’ ብሎ ለአንተ የተናገረው ቀን ዛሬ ነው” ብለው ለዳዊት በሹክሹክታ ሲነግሩት በዓይነ ሕሊናችን ማየት እንችላለን።—1 ሳሙኤል 24:2-6

8. ዳዊት የበቀል እርምጃ ከመውሰድ የተቆጠበው ለምን ነበር?

8 ዳዊት በሳኦል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ፈቃደኛ አልሆነም። እምነትና ትዕግሥት በማሳየት ጉዳዩን በይሖዋ እጅ ለመተው መርጧል። ንጉሡ ከዋሻው ወጥቶ ከሄደ በኋላ ዳዊት ተጣርቶ እንዲህ አለው “እግዚአብሔር በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ። ክፉ ስላደረግህብኝ እግዚአብሔር ይበቀልህ እንጂ፣ እጄስ በአንተ ላይ አትሆንም።” (1 ሳሙኤል 24:12) ምንም እንኳ ሳኦል ጥፋተኛ መሆኑን ዳዊት ቢያውቅም በገዛ እጁ አልተበቀለውም እንዲሁም የስድብ ቃል አልሰነዘረበትም ወይም ከኋላው ክፉ ቃል አልተናገረም። በሌሎች በርካታ አጋጣሚዎችም ዳዊት በገዛ እጁ የበቀል እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቧል። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ለጉዳዩ መፍትሄ እንዲያመጣ በእርሱ ተማምኗል።—1 ሳሙኤል 25:32-34፤ 26:10, 11

9. ተቃውሞ ወይም ስደት ሲደርስብን መበቀል የሌለብን ለምንድን ነው?

9 እንደ ዳዊት ሁሉ አንተም አስቸጋሪ ሁኔታ ሊያጋጥምህ ይችላል። ምናልባት አብረውህ ከሚማሩት ልጆች፣ ከሥራ ባልደረቦችህ፣ ከቤተሰብህ አባላት ወይም እምነትህን ከማይጋሩ ሌሎች ሰዎች ተቃውሞ ወይም ስደት ይደርስብህ ይሆናል። በዚህ ጊዜ የበቀል እርምጃ አትውሰድ። ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት እንዲረዳህ ጠይቅ፤ በትዕግሥትም ተጠባበቅ። የሚቃወሙህ ሰዎች በመልካም ጠባይህ ተደንቀው እምነትህን ሊቀበሉ ይችሉ ይሆናል። (1 ጴጥሮስ 3:1) ያም ሆነ ይህ ይሖዋ ሁኔታህን እንደሚያይና እርሱ በወሰነው ጊዜ አንድ ነገር እንደሚያደርግ እርግጠኛ ሁን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል “ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቁጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።”—ሮሜ 12:19

“ምክሬን አድምጡ”

10. ዳዊት ኃጢአት ሊፈጽም የቻለው እንዴት ነው? ኃጢአቱን ለመሸፋፈንስ ምን አደረገ?

10 በርካታ ዓመታት አለፉ፤ ዳዊት ስመ ጥር የሆነ ተወዳጅ ንጉሥ ለመሆን በቃ። በሕይወት ዘመኑ የላቀ ታማኝነት ያሳየና ይሖዋን ለማወደስ ግሩም መዝሙሮች የጻፈ ሰው መሆኑ ከባድ ኃጢአት ሊፈጽም አይችልም የሚል ስሜት ያሳድርብን ይሆናል። ሆኖም ከባድ ኃጢአት ላይ ወድቋል። አንድ ቀን ንጉሡ ሰገነቱ ላይ ሆኖ አንዲት ቆንጆ ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ ከዚያም ማንነቷን አጠያየቀ። ዳዊት ሴትየዋ ጦር ሜዳ ላይ ያለው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ መሆኗን ካወቀ በኋላ አስጠራትና ከእርሷ ጋር አመነዘረ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማርገዟን ሰማ። ጉዳዩ ይፋ ቢወጣ ለከፍተኛ ቅሌት ሊዳረግ ነው! በሙሴ ሕግ መሠረት ምንዝር በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነበር። ንጉሡ የሠራው ኃጢአት ተሸፋፍኖ ሊቀር እንደሚችል ሳያስብ አልቀረም። በመሆኑም ወደ ጦር ሠራዊቱ መልእክት ልኮ ኦርዮ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲላክ ትእዛዝ አስተላለፈ። ዳዊት፣ ኦርዮ ከቤርሳቤህ ጋር ያድራል ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር፤ ሆኖም ያሰበው ሳይሳካ ቀረ። ዳዊት አጣብቂኝ ውስጥ በመግባቱ ለጦር ሠራዊቱ አዛዥ ለኢዮአብ የሚሰጥ ደብዳቤ አስይዞ ኦርዮን ወደ ጦር ሜዳ መልሶ ላከው። በደብዳቤው መሠረት ኢዮአብ ኦርዮን ሊገደል በሚችልበት ቦታ ላይ ማሰለፍ አለበት። ኢዮአብ እንደተባለው አደረገ፤ ኦርዮም ተገደለ። ቤርሳቤህ በወጉ መሠረት ሐዘን የምትቀመጥበትን ጊዜ ከፈጸመች በኋላ ዳዊት ሚስቱ አደረጋት።—2 ሳሙኤል 11:1-27

11. ናታን ለዳዊት የነገረው ታሪክ ምንድን ነው? ዳዊትስ ምን ምላሽ ሰጠ?

11 ዘዴው የሰመረለት ቢመስልም እንኳ ዳዊት ያደረገው ነገር ሁሉ በይሖዋ ፊት የተገለጠ መሆኑን ማወቅ ነበረበት። (ዕብራውያን 4:13) ወራቶች አልፈው በመጨረሻ ሕፃኑ ተወለደ። ከዚያም ነቢዩ ናታን ከአምላክ በተቀበለው መመሪያ መሠረት ዳዊትን ሊያነጋግረው ሄደ። ነቢዩ ብዙ በጎች ያሉት ባለጠጋ ከአንድ ድሃ ላይ የሚወዳትን አንዲት በግ ቀምቶ እንዳረዳት የሚገልጽ ታሪክ ነገረው። ዳዊት ታሪኩን ሲሰማ በተፈጸመው ግፍ በጣም ተናደደ፤ ሆኖም ቅኔው አልገባውም ነበር። ዳዊት በባለጠጋው ላይ ወዲያውኑ ፍርድ በየነ። በከፍተኛ የቁጣ ስሜት ናታንን “ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል!” አለው።—2 ሳሙኤል 12:1-6

12. ይሖዋ በዳዊት ላይ ያስተላለፈው ፍርድ ምንድን ነው?

12 ነቢዩ “ያ ሰው አንተ ነህ” አለው። ዳዊት የፈረደው በራሱ ላይ ነበር። ዳዊት ያደረበት ቁጣ ጠፍቶ ወዲያውኑ ከፍተኛ የሐፍረትና የጸጸት ስሜት እንደተሰማው አያጠራጥርም። ናታን፣ ይሖዋ ያስተላለፈበትን ፍርድ ሲነግረው በድንጋጤ ተውጦ አዳመጠ። አንድም የማጽናኛ ወይም የማበረታቻ ቃል አላመጣለትም። ዳዊት ክፉ ነገር በመሥራት የይሖዋን ቃል አቃሏል። ኦርዮን በጠላት ሰይፍ አስገድሎ የለም? እንግዲያው ከዳዊት ቤት ሰይፍ አይርቅም። የኦርዮን ሚስት በድብቅ ወስዶ የለም? እርሱም ተመሳሳይ የሆነ ክፉ ነገር በስውር ሳይሆን በገሃድ ይደርስበታል።—2 ሳሙኤል 12:7-12

13. ዳዊት፣ ይሖዋ ለሰጠው ተግሣጽ ምን ምላሽ ሰጠ?

13 ደግነቱ ዳዊት ጥፋቱን አምኖ ተቀብሏል። በነቢዩ ናታን ላይ በቁጣ አልደነፋም። ጥፋቱን በሌሎች ላይ አላላከከም ወይም ደግሞ ሰበብ አስባብ አልደረደረም። ዳዊት የፈጸመው ኃጢአት ሲነገረው “እግዚአብሔርን በጣም በድያለሁ” በማለት ጥፋቱን አምኗል። (2 ሳሙኤል 12:13) መዝሙር 51 የተሰማው የበደለኛነት ስሜት ያስከተለበትን ሥቃይና ያደረበትን ከባድ ጸጸት ይገልጻል። “ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ” በማለት ይሖዋን ተማጽኗል። ይሖዋ ከምሕረቱ የተነሳ፣ በፈጸመው ኃጢአት “የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ” እንደማይንቅ እምነት ነበረው። (መዝሙር 51:11, 17) ዳዊት በአምላክ መንፈስ መታመኑን ቀጥሏል። ይሖዋ ኃጢአቱ ካስከተለበት ከባድ መዘዝ ዳዊትን ባያስጥለውም ይቅርታ ግን አድርጎለታል።

14. ይሖዋ ሲገሥጸን ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?

14 ሁላችንም ፍጽምና የሚጎድለን ከመሆኑም ሌላ ኃጢአት እንሠራለን። (ሮሜ 3:23) አንዳንድ ጊዜ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ እኛም ከባድ ኃጢአት እንፈጽም ይሆናል። አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹን እንደሚገሥጽ ሁሉ ይሖዋም እርሱን ማገልገል ለሚፈልጉ ሰዎች ምክር ይሰጣቸዋል። ተግሣጽ ጠቃሚ ቢሆንም ለመቀበል ይከብዳል። አንዳንድ ጊዜም ‘ለሐዘን’ ይዳርጋል። (ዕብራውያን 12:6, 11) ሆኖም የሚሰጠንን ‘ምክር የምናዳምጥ’ ከሆነ ከይሖዋ ጋር እርቅ ልንፈጥር እንችላለን። (ምሳሌ 8:33) የይሖዋን መንፈስ ላለማጣት ተግሣጽን መቀበልና የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።

አስተማማኝነት በሌለው ሀብት ተስፋ አታድርጉ

15. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች ሀብታቸውን የሚጠቀሙበት እንዴት ነው? (ለ) ዳዊት በሀብቱ ምን የማድረግ ፍላጎት ነበረው?

15 ዳዊት ታዋቂ ሰው እንደነበረ ወይም ከሀብታም ቤተሰብ እንደተወለደ የሚጠቁም ምንም ነገር የለም። ሆኖም በንግሥና ዘመኑ ከፍተኛ ሀብት አፍርቷል። እንደሚታወቀው ብዙዎች ያገኙትን ገንዘብ ያከማቻሉ፣ በዚያ ላይ በስግብግብነት መጨመር ይፈልጋሉ ወይም በራስ ወዳድነት ይጠቀሙበታል። ሌሎች ደግሞ ገንዘባቸውን ለራሳቸው ክብር ለማግኘት ያውሉታል። (ማቴዎስ 6:2) ዳዊት ሀብቱን የተጠቀመበት ለየት ባለ መንገድ ነው። በሀብቱ ይሖዋን የማክበር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ዳዊት በወቅቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ ‘በድንኳን የነበረው’ የይሖዋ ታቦት የሚቀመጥበት ቤተ መቅደስ የመገንባት ፍላጎት እንዳለው ለናታን ነግሮታል። ይሖዋ በዳዊት ሐሳብ የተደሰተ ቢሆንም ቤተ መቅደሱን የሚገነባው ግን ልጁ ሰሎሞን እንደሚሆን በነቢዩ ናታን አማካኝነት ነገረው።—2 ሳሙኤል 7:1, 2, 12, 13

16. ዳዊት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ ምን ዝግጅት አድርጓል?

16 ዳዊት ለዚህ ታላቅ የግንባታ ሥራ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች አከማችቷል፤ ሰሎሞንንም እንዲህ ብሎታል “ለእግዚአብሔር ቤት እንዲሆንም አንድ ሺህ መክሊት ወርቅ፣ አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፣ ከብዛቱ የተነሣ ሊመዘን የማይቻል ናስና ብረት ለማዘጋጀት በተቻለኝ ሁሉ ጥሬአለሁ። በተረፈ አንተ ጨምርበት።” ካለው የግል ሀብት ውስጥ 3,000 መክሊት ወርቅና 7,000 መክሊት ብር ሰጥቷል። a (1 ዜና መዋዕል 22:14፤ 29:3, 4) ዳዊት እንዲህ በልግስና የሰጠው ሰዎች እንዲያዩለት ብሎ ሳይሆን በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት ስለነበረውና ለእርሱ ያደረ በመሆኑ ነው። የሀብቱ ምንጭ ማን እንደሆነ ስለተገነዘበ ይሖዋን “ሁሉ የተገኘው ከአንተ ነው፤ ለአንተም የሰጠንህ ከእጅህ የተቀበልነውን ብቻ ነው” ብሎታል። (1 ዜና መዋዕል 29:14) ዳዊት የነበረው የልግስና መንፈስ ንጹሑን አምልኮ ለመደገፍ የቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ አነሳስቶታል።

17. 1 ጢሞቴዎስ 6:17-19 ላይ የሚገኘው ምክር ባለጠጋም ሆኑ ድሃ ለሆኑ ሰዎች የሚጠቅመው እንዴት ነው?

17 በተመሳሳይ እኛም ሀብታችንን ጥሩ ነገር ለመሥራት እንጠቀምበት። ቁሳዊ ሀብት እያሳደድን ከመኖር ይልቅ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት መጣራችን የተሻለ ነው። እንዲህ ማድረጋችን እውነተኛ ጥበብና ደስታ ያስገኝልናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል “በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት እንዳይታበዩ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። መልካም እንዲሠሩ፣ ቸሮችና ለማካፈል ፈቃደኞች የሆኑ እንዲሆኑ እዘዛቸው። በዚህ ዐይነት እውነተኛ የሆነውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳቸው ያከማቻሉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:17-19) የኢኮኖሚ ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን በአምላክ መንፈስ እንታመን እንዲሁም “በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም” የሚያደርገንን የሕይወት ጎዳና እንከተል። (ሉቃስ 12:21) በሰማይ በሚኖረው አፍቃሪ አባታችን ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘት የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር የለም።

የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ጣሩ

18. ዳዊት ለክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ የተወላቸው በምን መንገድ ነው?

18 ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ጥረት አድርጓል። “ማረኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ማረኝ፤ ነፍሴ አንተን መጠጊያ አድርጋለችና” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 57:1) በይሖዋ መታመኑ ጠቅሞታል። ዳዊት ሸመገለ፣ ‘ዕድሜውም ገፋ።’ (1 ዜና መዋዕል 23:1) ዳዊት ከባድ ጥፋቶች የሠራ ቢሆንም የሚደነቅ እምነት ካሳዩ በርካታ ምሥክሮች መካከል እንደ አንዱ ይቆጠራል።—ዕብራውያን 11:32

19. የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ራሳችንን ማቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?

19 በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ለውጦች ሲያጋጥሙህ ይሖዋ ዳዊትን እንደረዳው፣ እንዳበረታውና እንዳረመው ሁሉ አንተንም በተመሳሳይ መንገድ ሊረዳህ እንደሚችል አስታውስ። ሐዋርያው ጳውሎስም እንደ ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ብዙ ለውጦች አይቷል። ይሁንና እርሱም በአምላክ መንፈስ በመታመኑ በታማኝነት መጽናት ችሏል። “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:12, 13) በይሖዋ የምንታመን ከሆነ የተሳካ ሕይወት እንድናገኝ ይረዳናል። ይሖዋ መጨረሻችን ያማረ እንዲሆን ይፈልጋል። የሚነግረንን የምንሰማና ወደ እርሱ የምንቀርብ ከሆነ የእርሱን ፈቃድ ማድረግ እንድንችል ኃይል ይሰጠናል። በአምላክ መንፈስ መታመናችንን ከቀጠልን አሁንም ሆነ ለዘላለም ‘የአምላክን ሞገስ ማግኘት’ እንችላለን።—2 ጢሞቴዎስ 2:15 NW

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ዳዊት የሰጠው መዋጮ ዛሬ ባለው የዋጋ ተመን መሠረት ከ1,200,000,000 የአሜሪካ ዶላር ይበልጣል።

መልስህ ምንድን ነው?

• ከኩራት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

• በገዛ እጃችን መበቀል የሌለብን ለምንድን ነው?

• ለተግሣጽ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

• በሀብት ሳይሆን በአምላክ መታመን ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት በአምላክ መንፈስ የታመነ ከመሆኑም ሌላ መለኮታዊ ሞገስ ለማግኘት ጥረት አድርጓል። አንተም እንዲሁ እያደረግህ ነው?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ሁሉ የተገኘው ከአንተ ነው፤ ለአንተም የሰጠንህ ከእጅህ የተቀበልነውን ብቻ ነው”