በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትናንሽ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረጋችን የተትረፈረፈ በረከት አስገኝቶልናል

ትናንሽ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረጋችን የተትረፈረፈ በረከት አስገኝቶልናል

የሕይወት ታሪክ

ትናንሽ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረጋችን የተትረፈረፈ በረከት አስገኝቶልናል

ጆርጅ እና አን አልጀን እንደተናገሩት

እኔና ባለቤቴ “አስተማሪ” በማለት ፋንታ “አይጥ” እንላለን ብለን በእውናችንም ሆነ በሕልማችን አስበን አናውቅም ነበር። ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች ከመጡ ሰዎች ጋር ለመነጋገር ስንል ለየት ባለ መንገድ የሚጻፉ ፊደላት ያሉትን ቋንቋ በ60ዎቹ ዕድሜያችን እንማራለን የሚል ሐሳብም አልነበረንም። ያም ሆኖ በ1980ዎቹ መገባደጃ ላይ እኔና አን እንዲህ አድርገናል። በሕይወታችን ውስጥ ትናንሽ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረጋችን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኘልን እንዴት እንደሆነ እንንገራችሁ።

ቤተሰቦቼ አርመኖች ሲሆኑ የአርመን ቤተ ክርስቲያን አባላት ነበርን። አን ደግሞ ካቶሊክ ነበረች። በ1950 ስንጋባ አንዳችን የሌላውን ሃይማኖታዊ አመለካከት ችለን ለመኖር ተስማማን። በወቅቱ እኔ 27 ዓመቴ፣ አን ደግሞ 24 ዓመቷ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኒው ጀርሲ፣ ጀርሲ ሲቲ ውስጥ የደረቅ እጥበት አገልግሎት የምሰጥበት ለአራት ዓመታት ያህል የሠራሁበት ሱቅ ነበረኝ። ከተጋባን በኋላ ሱቁ በሚገኝበት ሕንፃ ላይ መኖር ጀመርን።

በ1955 በሚድልታውን፣ ኒው ጀርሲ ውስጥ ሦስት መኝታ ቤት ያለው የሚያምር ቤት ገዛን። ቤቱ ሱቄ ከሚገኝበት ቦታ 60 ኪሎ ሜትር ገደማ ይርቃል። በሳምንት ውስጥ ስድስት ቀን የምሠራ ሲሆን ሁልጊዜ ወደ ቤት የምመለሰው አምሽቼ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመገናኘት የምችልበት ብቸኛው አጋጣሚ አልፎ አልፎ ወደ ሱቄ መጥተው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ሲሰጡኝ ብቻ ነበር። ጽሑፎቹን በከፍተኛ ጉጉት አነባቸዋለሁ። ምንም እንኳ ሥራዬ ጊዜዬንና ሐሳቤን በሙሉ ተቆጣጥሮት የነበረ ቢሆንም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮት አደረብኝ።

ብዙም ሳይቆይ፣ ከሱቅ ወደ ቤት በምመላለስበት ሰዓት ላይ ደብልዩ ቢ ቢ አር የተባለው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሬዲዮ ጣቢያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን እንደሚያስተላልፍ አወቅሁ። ንግግሮቹን በትኩረት ማዳመጤ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት ስላሳደረብኝ የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንዲያነጋግሩኝ ጠየቅሁ። በኅዳር ወር፣ 1957 ጆርጅ ብላንተን የተባለ ሰው ወደ ቤቴ እየመጣ ያስጠናኝ ጀመር።

ቤተሰባችን በእውነተኛው አምልኮ አንድ ሆነ

አን ስለጉዳዩ ምን ተሰማት? እስቲ ራሷ ትናገር።

“መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንደጀመረ ሳውቅ አጥብቄ ተቃወምኩት። ጆርጅ ሲያጠና በጣም እረብሻቸው ስለነበረ ሌላ ቦታ ለማጥናት ወሰነ፤ በዚህ ዓይነት ለስምንት ወራት ያህል አጠና። በዚህ ጊዜ ውስጥ ጆርጅ እሁድ እሁድ በመንግሥት አዳራሹ በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረ። ያለውን አንድ የእረፍት ቀን ለስብሰባ ሲያውለው ስመለከት ጉዳዩን በቁም ነገር እንደያዘው ገባኝ። እንዲያውም ከበፊቱ በተሻለ የባልነትና የአባትነት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ስመለከት አመለካከቴ እየተቀየረ መጣ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የሳሎኑን ጠረጴዛ ሳጸዳ ማንም የማያየኝ ከሆነ ጆርጅ ሁልጊዜ ጠረጴዛው ላይ የሚያስቀምጠውን ንቁ! መጽሔት አንስቼ አነብብ ነበር። በሌላ ጊዜ ደግሞ ጆርጅ በቀጥታ ከሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶች ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሆኖም ስለ ፈጣሪ የሚናገሩ በንቁ! መጽሔት ላይ የወጡ ርዕሶችን ያነብልኝ ነበር።

“አንድ ምሽት ባለቤቴ ከወንድም ብላንተን ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ሄዶ እያለ ሁለት ዓመት የሆነው ልጃችን ጆርጅ አልጋዬ አጠገብ ያለው ጠረጴዛ ላይ ያስቀመጠውን ጽሑፍ አንስቼ መመልከት ጀመርኩ። ጽሑፉ ሙታን ምን ተስፋ እንዳላቸው የሚናገር ነው። ድክም ብሎኝ የነበረ ቢሆንም በቅርቡ አያቴን በሞት በማጣቴ በጣም አዝኜ ስለነበር አነበብኩት። ሙታን በሆነ ቦታ እየተቃጠሉ እንዳልሆነና ወደፊት በትንሣኤ አማካኝነት እንደገና ሕይወት እንደሚያገኙ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም። ብዙም ሳይቆይ ጋደም ካልኩበት ተነስቼ አልጋዬ ላይ ተቀመጥኩና በከፍተኛ ጉጉት ማንበቤን ቀጠልኩ፤ ጆርጅ ከጥናቱ ሲመለስ ላሳየው የምፈልጋቸውን ነጥቦች አሠመርኩባቸው።

“ባለቤቴ ወደ ቤት ሲመለስ እኔ መሆኔን እስኪጠራጠር ድረስ አመለካከቴ ተለውጦ ነበር። ወደ ጥናቱ ሲሄድ እየተቃወምኩት የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ባወቅኋቸው አስደናቂ እውነቶች ፍንድቅድቅ ብዬ ነበር! ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስንወያይ እኩለ ሌሊት አለፈ። ጆርጅ አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ አብራራልኝ። እኔም በጥናቱ ላይ እንድገኝ እቤት ማጥናት ይችል እንደሆነ የዚያኑ ዕለት ጠየቅሁት።

“ወንድም ብላንተን ልጆቻችንም በጥናቱ ላይ እንዲገኙ ሐሳብ አቀረበ። ገና የሁለትና የአራት ዓመት ልጆች በመሆናቸው አብረውን ለማጥናት እንደሚከብዳቸው ተሰምቶን ነበር። ሆኖም ወንድም ብላንተን “ይሰሙና . . . ይማሩ ዘንድ፣ . . . ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችን . . . ሰብስብ” የሚለውን የዘዳግም 31:12ን ጥቅስ አሳየን። ሐሳቡን በመቀበል ልጆቹ በጥናቱ ላይ እንዲገኙና መልስም ጭምር እንዲሰጡ አደረግን። አስቀድመን አብረን የምንዘጋጅ ቢሆንም በጥናቱ ላይ ግን መልሱን አንነግራቸውም ነበር። እንዲህ ማድረጋችን ልጆቹ እውነትን የራሳቸው እንዲያደርጉት አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይሰማናል። ቤተሰባችን በመንፈሳዊ እንዲያድግ ወንድም ብላንተን ላደረገልን እርዳታ ምን ጊዜም አመስጋኞች ነን።”

መሥዋዕት መክፈል የሚጠይቁ ፈታኝ ሁኔታዎች

መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ ማጥናት ስንጀምር አዳዲስ ፈተናዎች ተጋረጡብን። ሱቄ ከቤታችን በጣም ስለሚርቅ አብዛኛውን ጊዜ ማታ ከ3:00 ሰዓት በፊት እቤት አልደርስም። በዚህም ምክንያት በሳምንቱ ቀናት በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ባልችልም እሁድ እሁድ ግን እሄድ ነበር። በዚህ ወቅት አን በሁሉም ስብሰባዎች ላይ የምትገኝ ሲሆን ፈጣን እድገት እያደረገች ነበር። እኔም በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና ትርጉም ያለው የቤተሰብ ጥናት ለመምራት ፈለግሁ። ለዚህም አንዳንድ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። በመሆኑም አንዳንድ ደንበኞቼን ሊያሳጣኝ ቢችልም እንኳ በሥራ ቦታዬ የማሳልፈውን ሰዓት ለመቀነስ ወሰንኩ።

ይህን ማስተካከያ ማድረጋችን ጠቅሞናል። የቤተሰብ ጥናታችንን በመንግሥት አዳራሹ ከሚደረጉት አምስት ሳምንታዊ ስብሰባዎች ባልተናነሰ መልኩ በቁም ነገር እንመለከተው ስለነበር ስድስተኛው ስብሰባችን ብለን ሰየምነው። በመሆኑም ለቤተሰብ ጥናታችን ቋሚ ቀንና ሰዓት መደብንና ረቡዕ ዕለት ማታ በ2:00 ሰዓት ማድረግ ጀመርን። አንዳንድ ጊዜ ከእራት በኋላ የተመገብንባቸውን ዕቃዎች አጣጥበን ስንጨርስ ከመካከላችን አንዱ “‘የስብሰባ’ ሰዓት እየደረሰ ነው!” ይላል። ከዘገየሁ አን ጥናቱን ጀምራ ትቆየኝና እኔ ስመጣ እቀጥላለሁ።

በቤተሰብ መልክ አንድነታችንን ጠብቀንና ጠንካራ ሆነን እንድንኖር የረዳን ሌላው ነገር ማለዳ ላይ የዕለቱን ጥቅስ አብረን ማንበባችን ነው። ሆኖም ሁላችንም ከእንቅልፋችን የምንነሳው በተለያየ ሰዓት በመሆኑ ይህንን ማድረግ አስቸግሮን ነበር። በጉዳዩ ላይ ከተወያየን በኋላ ሁላችንም በተመሳሳይ ሰዓት ተነስተን 12:30 ላይ ቁርሳችንን ለመብላትና የዕለቱን ጥቅስ ለማንበብ ወሰንን። እንዲህ በማድረጋችን በጣም ተጠቅመናል። ልጆቻችን ሲያድጉ ቤቴል ለመግባት ወሰኑ። በየዕለቱ የምናደርጋቸው እነዚህ ውይይቶች ለልጆቻችን መንፈሳዊነት አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይሰማናል።

ከተጠመቅን በኋላ ያገኘናቸው መብቶች ተጨማሪ መሥዋዕቶችን ጠየቁብን

በ1962 ተጠመቅሁ። ለቤተሰቤ ቅርብ ሆኜ ይሖዋን በአንድነት ማገልገል እንድንችል ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ስል፣ ለ21 ዓመታት ሳንቀሳቅሰው የቆየሁትን ድርጅቴን ሸጥኩና በምንኖርበት አካባቢ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። ይህ እርምጃ የተትረፈረፈ በረከት እንድናገኝ መንገድ ከፈተ። ሁላችንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ግብ አወጣን። በ1970ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የበኩር ልጃችን ኤድዋርድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ወይም የዘወትር አቅኚ ሲሆን ይህ ግባችን ፈር መያዝ ጀመረ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሁለተኛው ልጃችን ጆርጅ አቅኚ ሆነ፤ ብዙም ሳይቆይ አንም በዚሁ አገልግሎት መካፈል ጀመረች። ሦስቱም በመስክ አገልግሎት ያገኟቸውን ተሞክሮዎች ስለሚነግሩኝ በጣም እበረታታ ነበር። ሁላችንም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እንድንሆን ኑሯችንን እንዴት ማቅለል እንደምንችል በቤተሰብ መልክ ከተወያየን በኋላ ቤታችንን ለመሸጥ ወሰንን። ለ18 ዓመታት የኖርንበትና ልጆቻችንንም ያሳደግንበት ቤት በመሆኑ በጣም እንወድደው ነበር። ሆኖም ቤቱን ለመሸጥ ያደረግነውን ውሳኔ ይሖዋ ባርኮታል።

በ1972 ኤድዋርድ በ1974 ደግሞ ጆርጅ በቤቴል እንዲያገለግሉ ተጋበዙ። እኔና አን ልጆቻችን ቢናፍቁንም ትዳር መሥርተውና ልጆች ወልደው አጠገባችን ቢኖሩ የተሻለ ይሆን ነበር ብለን አናስብም። ከዚህ ይልቅ ልጆቻችን በቤቴል ይሖዋን እያገለገሉ በመሆናቸው ደስተኞች ነን። a በምሳሌ 23:15 ላይ በሚገኘው “ልጄ ሆይ፤ ልብህ ጠቢብ ቢሆን፣ የእኔም ልብ ሐሤት ያደርጋል” በሚለው ሐሳብ እንስማማለን።

ልዩ አቅኚዎች ሆንን

ሁለቱም ልጆቻችን ቤቴል ከገቡ በኋላም በአቅኚነት ማገልገላችንን ቀጠልን። ከዚያም በ1975 በክሊንተን ካውንቲ፣ ኢሊኖይ በሚገኝ ገለልተኛ ክልል ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል የሚጋብዝ ደብዳቤ ደረሰን። ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነገር ነበር! ይህንን ምድብ ከተቀበልን ኒው ዮርክ የሚኖሩትን ልጆቻችንን ቶሎ ቶሎ ለመጠየቅ አመቺ የሆነውንና ወዳጆቻችንና ዘመዶቻችን የሚገኙበትን ኒው ጀርሲን ለቅቀን መሄድ ይኖርብናል ማለት ነው። ሆኖም በዚያ ቦታ እንድናገለግል የመደበን ይሖዋ እንደሆነ በማሰብ የሚያስፈልገውን መሥዋዕት ከፈልን፤ ይህም አዳዲስ በረከቶችን አስገኘልን።

በተመደብንበት ገለልተኛ ክልል ለብዙ ወራት ካገለገልን በኋላ በካርላይል ኢሊኖይ በሚገኝ የሕዝብ አዳራሽ ስብሰባ ማድረግ ጀመርን። ሆኖም ቋሚ የሆነ የመሰብሰቢያ ቦታ ያስፈልገን ነበር። በአካባቢው የሚኖር አንድ ወንድምና ባለቤቱ አንዲት በጣም አነስተኛ የሆነች ጎጆ አገኙና ተከራየነው። ጎጆውንና መጸዳጃ ቤቱን ካጸዳን በኋላ አነስ ያለ የመሰብሰቢያ ቦታ ሆነ። በዚህ ቦታ የነበረ አንድ ፈረስ ትዝ ይለናል። በስብሰባው ላይ ምን እንደሚከናወን ለማየት የፈለገ ይመስል አብዛኛውን ጊዜ ጭንቅላቱን በመስኮቱ በኩል ብቅ አድርጎ ይመለከተን ነበር።

ከጊዜ በኋላ ካርላይል የተባለ ጉባኤ ተቋቋመ፤ በዚህ ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻላችን ደስተኞች ነን። በዚህ ገለልተኛ ክልል ለማገልገል የመጡ ስቲቭ እና ካረል ቶምፕሰን የተባሉ ወጣት ባልና ሚስት አቅኚዎች ያግዙን ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት በዚያ ቦታ ለበርካታ ዓመታት የቆዩ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ከጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተመርቀው በምሥራቅ አፍሪካ በሚስዮናዊነት እንዲያገለግሉ ተመደቡ፤ በዚያም በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እያገለገሉ ነው።

ብዙም ሳይቆይ ትንሿ የመሰብሰቢያ ቦታችን ስለጠበበችን ሰፋ ያለ አዳራሽ አስፈለገን። ከዚህ ቀደም ቦታ ያገኙልን ወንድምና ባለቤቱ ለመንግሥት አዳራሽ ይበልጥ ተስማሚ የሆነ ቦታ በመግዛት ለችግሩ መፍትሔ አስገኙ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ በካርላይል አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ተሠርቶ በተወሰነበት ወቅት ፕሮግራሙ ላይ እንድንገኝ ስንጋበዝ በጣም ተደሰትን! የውሰናውን ንግግር የማቅረብ መብት አግኝቼ ነበር። በዚያ ምድብ በቆየንባቸው ጊዜያት ግሩም ተሞክሮ ያካበትን ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ባርኮናል።

አዲስ የሥራ መስክ ተከፈተልን

በ1979 በሃሪሰን፣ ኒው ጀርሲ እንድናገለግል ተመደብን። በዚህ ቦታ ለ12 ዓመታት ያህል ያገለገልን ሲሆን በዚያ ጊዜ ውስጥ አንዲት ቻይናዊት ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመርን። ይህም ሌሎች በርካታ ቻይናውያንን ለማስጠናት መንገድ ከፈተ። በዚህ መሃል በአካባቢያችን በሺዎች የሚቆጠሩ ቻይናውያን ተማሪዎችና ቤተሰቦች እንደሚኖሩ አወቅን። በዚህም ምክንያት የቻይናን ቋንቋ እንድንማር ማበረታቻ ተሰጠን። ይህ ቋንቋውን ለማጥናት በየቀኑ ጊዜ መመደብ የሚጠይቅ ቢሆንም በአካባቢያችን ለሚገኙ በርካታ ቻይናውያን አስደሳች የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት አስችሎናል።

በእነዚያ ዓመታት (በተለይ ቻይንኛ ለመናገር ስንሞክር) በርካታ አስቂኝ ሁኔታዎች አጋጥመውናል። አንድ ቀን አን ራሷን ለቤቱ ባለቤት ስታስተዋውቅ የመጽሐፍ ቅዱስ “አስተማሪ” እንደሆነች ለመናገር ብላ የመጽሐፍ ቅዱስ “አይጥ” መሆኗን ነገረቻት። ቃላቶቹ በጣም ይመሳሰላሉ። የቤቱ ባለቤትም ፈገግ ብላ “ከአሁን ቀደም ከመጽሐፍ ቅዱስ አይጥ ጋር ተነጋግሬ አላውቅም፤ እባክዎ ይግቡ” አለቻት። አሁንም ቢሆን ቋንቋውን ለመቻል እየታገልን ነው።

ቆየት ብሎም ኒው ጀርሲ ውስጥ የቻይንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በሚኖሩበት ሌላ ክልል እንድናገለግል ተመደብን። ከዚያ ደግሞ ከተቋቋመ ሦስት ዓመታት ያስቆጠረ የቻይንኛ ተናጋሪዎች ቡድን በሚገኝበት በቦስተን፣ ማሳቹሴትስ እንድናገለግል ተጋበዝን። ላለፉት ሰባት ዓመታት ይህንን ቡድን የመርዳት መብት በማግኘታችንና በጥር 1, 2003 ጉባኤ ሲሆን በመመልከታችን በጣም ተደስተናል።

የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ያስገኘልን በረከት

በሚልክያስ 3:10 ላይ ይሖዋ ስጦታቸውንና መሥዋዕታቸውን ወደ ቤቱ እንዲያመጡና የተትረፈረፈ በረከቱን እንዲያገኙ ለሕዝቡ ግብዣ አቅርቧል። በጣም የምወደውን ሥራዬን ተውኩ። እንዲሁም እጅግ የምንወደውን ቤታችንን ሸጥን። ሌሎች ነገሮችንም እንዲሁ መሥዋዕት አድርገናል። ሆኖም ካገኘነው በረከት ጋር ሲወዳደር የከፈልናቸው መሥዋዕቶች ከቁጥር የሚገቡ አይደሉም።

በእርግጥም ይሖዋ እጅግ አትረፍርፎ ባርኮናል! ልጆቻችን በእውነት ውስጥ ሲመላለሱ በማየታችን እርካታ አግኝተናል፤ ሙሉ ጊዜያችንን ሕይወት አድን በሆነው አገልግሎት በማሳለፋችን እንደሰታለን እንዲሁም ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች በመስጠት ሲንከባከበን ተመልክተናል። በእውነትም ትናንሽ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረጋችን የተትረፈረፈ በረከት አስገኝቶልናል!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኤድዋርድና ባለቤቱ ኮኒ በፓተርሰን፣ ጆርጅና ባለቤቱ ግሬስ ደግሞ በብሩክሊን ቤቴል በታማኝነት እያገለገሉ ነው።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሎይስና ጆርጅ ብላንተን ከአን ጋር፣ በ1991

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰኔ 4, 1983 የተወሰነው በካርላይል የሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሁን ጉባኤ ከሆነው በቦስተን ከሚገኘው የቻይንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቡድን ጋር

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከኤድዋርድ፣ ኮኒ፣ ጆርጅና ግሬስ ጋር