በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እርዳታ ለማግኘት ወደ መላእክት መጸለይ ይኖርብናል?

እርዳታ ለማግኘት ወደ መላእክት መጸለይ ይኖርብናል?

እርዳታ ለማግኘት ወደ መላእክት መጸለይ ይኖርብናል?

መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ መላእክት እንዲረዱን መጸለያችን ተገቢ ነው? ብዙዎች እንደዚያ ይሰማቸዋል። እንዲያውም ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “አንድ ሰው . . . ወደ መላእክት መጸለይ ይችላል . . . ይህን የሚያደርገው ግን በአምላክ ፊት እንዲያማልዱት ብቻ ብሎ ነው።” ታዲያ መላእክት እንዲያማልዱን ወደ እነርሱ መጸለይ ይኖርብናል?

የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ከሆኑት መላእክት መካከል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስም የተጠቀሱት ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነርሱም ሚካኤልና ገብርኤል ናቸው። (ዳንኤል 8:16፤ 12:1፤ ሉቃስ 1:26፤ ይሁዳ 9) እነዚህ ስሞች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው መገኘታቸው እያንዳንዱ መልአክ ስም ያለው ራሱን የቻለ መንፈሳዊ አካል እንጂ አካል የሌለው ኃይል እንዳልሆነ እንድንገነዘብ ያስችለናል። ሆኖም አንዳንድ መላእክት ስማቸውን ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ለምሳሌ ያህል ያዕቆብ ወደ እርሱ የመጣው መልአክ ስሙን እንዲነግረው በጠየቀ ጊዜ መልአኩ ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። (ዘፍጥረት 32:29፤ መሳፍንት 13:17, 18) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመላእክት ስም በዝርዝር ተጽፎ አይገኝም። ይህም የሆነበት ምክንያት ሰዎች ከሚገባው በላይ ትኩረት እንዳይሰጧቸው ለማድረግ ነው።

መላእክት ከሚያከናውኑት ሥራ መካከል አንዱ የአምላክን መልእክት ለሰዎች ማድረስ ነው። እንዲያውም “መልአክ” ተብለው የተተረጎሙት የመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ቃል በቃል “መልእክተኛ” የሚል ትርጉም አላቸው። ይሁን እንጂ መላእክት ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት ወደ ልዑል አምላክ ዙፋን ለማቅረብ አማላጅ ሆነው የማገልገል መብት የላቸውም። አምላክ ወደ እርሱ ጸሎት መቅረብ ያለበት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንደሆነ ተናግሯል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ “አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል” ብሏል።—ዮሐንስ 15:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5

ይሖዋ አምላክ በተገቢው መንገድ ወደ እርሱ ከጸለይን እኛን ለመስማት ጊዜ አያጣም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ዋስትና ይሰጣል:- “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።”—መዝሙር 145:18