በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እየተለወጠ ያለው ዓለም የሚያንጸባርቀው መንፈስ እንዳይጋባባችሁ ተጠንቀቁ

እየተለወጠ ያለው ዓለም የሚያንጸባርቀው መንፈስ እንዳይጋባባችሁ ተጠንቀቁ

እየተለወጠ ያለው ዓለም የሚያንጸባርቀው መንፈስ እንዳይጋባባችሁ ተጠንቀቁ

“ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።”—1 ቆሮንቶስ 2:12

1. ሔዋን የተታለለችው በምን መንገዶች ነው?

 “እባብ አሳሳተኝ።” (ዘፍጥረት 3:13) የመጀመሪያዋ ሴት ሔዋን በይሖዋ አምላክ ላይ ያመፀችበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ለማስረዳት ሞከረች። የተናገረችው ነገር ትክክል ቢሆንም ለሠራችው ጥፋት ግን ማስተባበያ ሊሆን አይችልም። ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የተታለለችው ሔዋን ናት’ ሲል በመንፈስ ተመርቶ ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 2:14) በአምላክ ላይ ዓምፃ ከተከለከለው ፍሬ ብትበላ እንደ አምላክ ልትሆን እንደምትችል ስላሰበች እጠቀማለሁ የሚል የተሳሳተ እምነት አደረባት። ያታለላት ማን እንደሆነም አላወቀችም ነበር። እባቡ የሰይጣን ዲያብሎስ አፈ ቀላጤ እንደነበር አልተገነዘበችም።—ዘፍጥረት 3:1-6

2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ሰይጣን ሰዎችን እያሳሳተ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ‘የዓለም መንፈስ’ ምንድን ነው? ቀጥሎ የሚብራሩት ጥያቄዎችስ የትኞቹ ናቸው?

2 ከአዳምና ከሔዋን ጊዜ አንስቶ ሰይጣን ሰዎችን ማታለሉን ቀጥሏል። እንዲያውም ‘ዓለምን ሁሉ እያሳተ ነው።’ (ራእይ 12:9) የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ተመሳሳይ ናቸው። ከዚያ በኋላ ቃል በቃል በእባብ ተጠቅሞ ባያውቅም እንኳ አሁንም ማንነቱን ይደብቃል። ሰይጣን የመዝናኛውን ኢንዱስትሪ፣ መገናኛ ብዙሐንንና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም ሰዎች አምላክ የሚሰጠው ፍቅራዊ መመሪያ እንደማያስፈልጋቸው ወይም እንደማይጠቅማቸው በማሳመን ያታልላቸዋል። ዲያብሎስ ሰዎችን ለማታለል የሚያካሂደው ዘመቻ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የማመፅ ዝንባሌ እንዲይዙ አድርጓቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሁኔታ ‘የዓለም መንፈስ’ በማለት ይጠራዋል። (1 ቆሮንቶስ 2:12) ይህ መንፈስ አምላክን የማያውቁ ሰዎች ባላቸው እምነት፣ አመለካከትና ባሕርይ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህ መንፈስ የሚንጸባረቀው በምን መንገዶች ነው? ጎጂ ተጽዕኖውን መቋቋም የምንችለውስ እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።

የሥነ ምግባር ደንቦች እየተሸረሸሩ መጥተዋል

3. በዚህ ዘመን ‘የዓለም መንፈስ’ በጣም እየተስፋፋ ያለው ለምንድን ነው?

3 በዚህ ዘመን ‘የዓለም መንፈስ’ በጣም እየተስፋፋ መጥቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) የሥነ ምግባር ደንቦች እየተሸረሸሩ መሆናቸውን ሳታስተውል አትቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሆነበትን ምክንያት ይገልጻል። በ1914 የአምላክን መንግሥት መቋቋም ተከትሎ በሰማይ ጦርነት ፈነዳ። ሰይጣንና አጋንንቱ በጦርነቱ ተሸንፈው ወደ ምድር ተጣሉ። ሰይጣን በዚህ ተቆጥቶ በዓለም ዙሪያ የሚያካሂደውን የማሳት ዘመቻ አጠናከረ። (ራእይ 12:1-9, 12, 17) ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ማንኛውንም ሰው፣ “ቢቻል የተመረጡትን ለማሳት” ጥረት ያደርጋል። (ማቴዎስ 24:24) የአምላክ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ዒላማው ያነጣጠረው በእኛ ላይ ነው። የይሖዋን ሞገስና የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን እንድናጣ መንፈሳዊነታችንን ለማጥፋት ይፍጨረጨራል።

4. የይሖዋ አገልጋዮች ለመጽሐፍ ቅዱስ ምን አመለካከት አላቸው? ዓለም ለመጽሐፉ ያለው አመለካከትስ ምንድን ነው?

4 ሰይጣን ስለ አፍቃሪ ፈጣሪያችን እውቀት የምናገኝበትን ውድ መጽሐፍ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን ተቀባይነት ለማሳጣት ጥረት ያደርጋል። የይሖዋ አገልጋዮች ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ያላቸው ከመሆኑም በላይ እንደ ውድ ሀብት ይቆጥሩታል። መጽሐፉ የሰው ቃል ሳይሆን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል መሆኑን እናውቃለን። (1 ተሰሎንቄ 2:13፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) የሰይጣን ዓለም ግን መጽሐፉን አቅልለን እንድንመለከተው ይፈልጋል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስን የሚያንቋሽሽ አንድ መጽሐፍ በመቅድሙ ላይ እንዲህ ይላል “መጽሐፍ ቅዱስን ‘ቅዱስ’ ሊያስብለው የሚችል አንድም ነገር የለም፤ ‘የአምላክ ቃል’ ነው ሊባልም አይችልም። የተጻፈው በአምላክ መንፈስ በተመሩ ቅዱሳን ሳይሆን የሥልጣን ጥመኛ በሆኑ ቀሳውስት ነው።” እንዲህ ዓይነት አባባሎችን የሚቀበሉ ሰዎች አምላክን በመረጡት መንገድ ማምለክ፣ ካልፈለጉ ደግሞ ጭራሹን አለማምለክ መብታቸው እንደሆነ የሚነገራቸውን የተሳሳተ ትምህርት አምነው ይቀበላሉ።—ምሳሌ 14:12

5. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀሙ ሃይማኖቶችን በተመለከተ አንድ ደራሲ ምን አስተያየት ሰጥተዋል? (ለ) አንዳንድ ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው አባባሎች መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገራቸው ሐሳቦች ጋር የሚቃረኑት እንዴት ነው? (በሚቀጥለው ገጽ ላይ የሚገኘውን ሣጥን ጨምር።)

5 መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚሰነዘረው ጥቃት በተጨማሪ መጽሐፉ መመሪያችን ነው የሚሉ ሰዎች የሚታይባቸው ሃይማኖታዊ ግብዝነት መጽሐፍ ቅዱስን በጥብቅ የሚከተለውን ሃይማኖት ጨምሮ ማንኛውም ሃይማኖት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ ከመገናኛ ብዙሐንም ሆነ ከምሑራን ጥቃት ይሰነዘርበታል። አንድ ደራሲ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል “ሰዎች በሕብረተሰቡ መካከል ተስፋፍቶ ለሚገኘው የአይሁድና የክርስትና እምነት በጎ አመለካከት የላቸውም። የእነዚህን ሃይማኖቶች መልካም ጎን እንይ ብንል የብዙዎችን ቀልብ የሚስበው ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ መሆናቸው ነው። መጥፎ ጎናቸውን እንይ ከተባለ ደግሞ የአስተሳሰብ ብስለትን የሚገድቡና ሳይንሳዊ እድገትን የሚያጓትቱ ጊዜ ያለፈባቸው አመለካከቶች ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ለእነዚህ ሃይማኖቶች የነበረው ንቀት ወደ ፌዝና ግልጽ ጥላቻ ተቀይሯል።” በአብዛኛው እንዲህ ዓይነቱ ጥላቻ የሚመነጨው የአምላክን ሕልውና ከሚክዱና “ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ” ከሆነ ሰዎች ነው።—ሮሜ 1:20-22

6. ዓለም አምላክ ለሚያወግዛቸው የፆታ ድርጊቶች ምን አመለካከት አለው?

6 በመሆኑም ሰዎች ከአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጣም እየራቁ መሄዳቸው ምንም አያስገርምም። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶም “ነውር” እንደሆነ ይገልጻል። (ሮሜ 1:26, 27) ከዚህ በተጨማሪ ዝሙትና ምንዝር የሚፈጽሙ ሰዎች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9) ይሁን እንጂ በበርካታ አገሮች ውስጥ እነዚህ ድርጊቶች ተቀባይነት ያላቸው እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩ ከመሆኑም ሌላ በመጻሕፍት፣ በመጽሔቶች፣ በዘፈኖች፣ በፊልሞችና በቴሌቪዥን ትርዒቶች ላይ እንደ ጥሩ ነገር ተደርገው ይቀርባሉ። እነዚህን ድርጊቶች የሚያወግዙ ሰዎች ጠባብ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ነቃፊዎችና ኋላ ቀር እንደሆኑ ይታያሉ። ዓለም አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የአሳቢነት መግለጫ አድርጎ ከማየት ይልቅ የግል ነፃነትና ደስታ ጠር እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸዋል።—ምሳሌ 17:15፤ ይሁዳ 4

7. ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

7 የምንኖርበት ዓለም አምላክን መቃወሙን ስለገፋበት የራሳችንን ዝንባሌና የሥነ ምግባር ደንቦች መመርመራችን ጥበብ ነው። ከይሖዋ አስተሳሰብና የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ቀስ በቀስ እየራቅን እንዳንሄድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሳችንን በጸሎትና በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን ‘ከተወሰኑ ዓመታት በፊት እጸየፈው የነበረውን ነገር አሁን አስደሳች እንደሆነ አድርጌ እየተመለከትኩ ነው? አምላክ የሚያወግዛቸውን ድርጊቶች አቅልዬ መመልከት ጀምሬያለሁ? ከዚህ ቀደም ለመንፈሳዊ ጉዳዮች እሰጥ የነበረው ትኩረት እየቀነሰ መጥቷል? አኗኗሬ ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በሕይወቴ ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንደሚይዙ ያሳያል? (ማቴዎስ 6:33) እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች በማንሳት ራሳችንን መመርመራችን የዓለምን መንፈስ እንድንቋቋም ይረዳናል።

“ስተን እንዳንወድቅ”

8. አንድ ሰው ከይሖዋ ሊርቅ የሚችለው እንዴት ነው?

8 ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ “ከሰማነው ነገር ስተን እንዳንወድቅ፣ ለሰማነው ነገር አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባናል” ሲል ጽፎላቸዋል። (ዕብራውያን 2:1) አቅጣጫውን የሳተ መርከብ የሚፈለገው ቦታ ላይ መድረስ አይችልም። ካፒቴኑ ንፋሱንና የውኃውን ሞገድ በንቃት ካልተከታተለ መርከቧ ሳይታወቅ ወደቡን አልፋ የባሕሩ ዳርቻ ላይ ካለ ዓለት ጋር ልትላተም ትችላለች። በተመሳሳይ እኛም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ውድ እውነቶች በትኩረት የማንከታተል ከሆነ በቀላሉ ከይሖዋ ልንርቅና መንፈሳዊ ኪሳራ ሊደርስብን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ኪሳራ ምን እንደሚያስከትል ለማየት የግድ ከእውነት መውጣት አያስፈልገንም። እንዲያውም ይሖዋን በድንገትና ሆን ብለው የሚተዉ ብዙዎች አይደሉም። አብዛኛውን ጊዜ ለአምላክ ቃል ትኩረት እንዳይሰጡ በሚያደርጋቸው ነገር ቀስ በቀስ ይጠላለፋሉ። ደህና ናቸው ተብሎ ሲታሰብ ኃጢአት ፈጽመው ይገኛሉ። እንቅልፍ እንደወሰደው ካፒቴን ሁሉ እነዚህ ግለሰቦችም ከእንቅልፋቸው የሚነቁት ቆይተው ነው።

9. ይሖዋ ሰሎሞንን በምን መንገዶች ባርኮታል?

9 የሰሎሞንን ሕይወት ተመልከት። ይሖዋ በእስራኤል ላይ አነገሠው፣ ቤተ መቅደሱን እንዲገነባ ፈቀደለት፤ በተጨማሪም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እንዲጽፍ በመንፈሱ መራው። ይሖዋ ከአንዴም ሁለቴ ያነጋገረው ከመሆኑም ሌላ ዝና፣ ሀብትና ሰላማዊ የንግሥና ዘመን ሰጠው። ከዚህ ሁሉ በላይ ይሖዋ ከፍተኛ ጥበብ በመስጠት ሰሎሞንን ባርኮታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል “አምላክ ለሰሎሞን ጥበብንና እጅግ ታላቅ ማስተዋልን እንዲሁም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋትን ሰጠው። የሰሎሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በጣም የላቀ ከግብፅም ጥበብ ሁሉ የበለጠ ነበር።” (1 ነገሥት 4:21, 29, 30፤ 11:9) አንድ ሰው ከሰሎሞን የተሻለ ለይሖዋ ታማኝ የሚሆን ማንም ሊገኝ አይችልም ብሎ ያስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሰሎሞን የክህደት ጎዳናን ተከትሏል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

10. ሰሎሞን የትኛውን መመሪያ ሳይታዘዝ ቀርቷል? ይህስ ምን አስከተለበት?

10 ሰሎሞን የአምላክን ሕግ ጠንቅቆ ያውቅና ይረዳ ነበር። በእስራኤል ላይ ለሚነግሡ ሰዎች ለተሰጡት መመሪያዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም። ከመመሪያዎቹ መካከል አንደኛው ‘ንጉሡ ልቡ እንዳይስት ብዙ ሚስቶችን አያግባ’ ይላል። (ዘዳግም 17:14, 17) ይህ ግልጽ መመሪያ እያለም ሰሎሞን ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች ነበሩት። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ጣዖት አምላኪዎች ነበሩ። ሰሎሞን ይህን ያህል ብዛት ያላቸው ሚስቶች ያገባበትን ምክንያትም ሆነ እንዲህ ለማድረግ ምን ሰበብ እንዳቀረበ የምናውቀው ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ አምላክ ያወጣውን ግልጽ መመሪያ መጣሱን እናያለን። ከዚህም የተነሳ ይሖዋ የተናገረው ማስጠንቀቂያ ደረሰበት። ‘የሰሎሞን ሚስቶች ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት’ ተብሎ ተጽፏል። (1 ነገሥት 11:3, 4) ቀስ በቀስ የነበረውን መለኮታዊ ጥበብ እያጣ ሄደ፤ አቅጣጫውንም ሳተ። ከጊዜ በኋላ ሰሎሞን አምላክን ለመታዘዝና ለማስደሰት በነበረው ፍላጎት ፋንታ አረማዊ ሚስቶቹን የማስደሰት ፍላጎት አደረበት። ቀደም ሲል “ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው፤ ለሚንቁኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችል ዘንድ” የሚሉትን ቃላት የጻፈው ሰሎሞን እንዴት ያለ አሳዛኝ ውድቀት ደረሰበት!—ምሳሌ 27:11

የዓለም መንፈስ ኃይለኛ ነው

11. አእምሯችንን የምንመግበው ነገር በአስተሳሰባችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

11 እውነትን ስለምናውቅ የዓለም ተጽዕኖ አስተሳሰባችንን ሊቀይረው አይችልም ብሎ ማሰብ አደገኛ መሆኑን ሰሎሞን ከደረሰበት ሁኔታ መማር እንችላለን። ሥጋዊ ምግብ በአካላችን ላይ አንድ ዓይነት ለውጥ እንደሚያመጣ ሁሉ አእምሯችንን የምንመግበው ምግብም በአስተሳሰባችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። አእምሯችንን የምንመግበው ነገር አስተሳሰባችንንና ዝንባሌያችንን ይቀርጻል። በዓለማችን ላይ ያሉ የንግድ ድርጅቶች ይህን ስለሚገነዘቡ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያወጣሉ። ማስታወቂያዎች የተጠቃሚውን ጉጉትና ፍላጎት ለማነሳሳት ስሜት የሚቀሰቅሱ አባባሎችንና ሥዕሎችን ይጠቀማሉ። በተጨማሪም የማስታወቂያ አዘጋጆች፣ ሰዎች አንድን ማስታወቂያ አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ መመልከታቸው ዕቃውን ለመግዛት እንደማያነሳሳቸው ያውቃሉ። ሆኖም ሰዎች ማስታወቂያውን ደጋግመው መመልከታቸው ዕቃውን የመግዛት ፍላጎት ያሳድርባቸዋል። የንግድ ማስታወቂያ ሽያጭ ለማስፋፋት ይረዳል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ ለማስታወቂያ ገንዘብ የሚያወጣ ባልኖረ ነበር። የንግድ ማስታወቂያ በሕዝቡ አስተሳሰብና ዝንባሌ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።

12. (ሀ) ሰይጣን በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች በተጽዕኖው ሊሸነፉ እንደሚችሉ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

12 እንደ አንድ የማስታወቂያ አዘጋጅ ሁሉ ሰይጣንም ውሎ አድሮ ሰዎች የእርሱን አስተሳሰብ እንዲቀበሉ ማሳመን እንደሚችል ስለሚያውቅ የእርሱ መንገድ አስደሳች መስሎ እንዲታይ ለማድረግ ይጥራል። ሰይጣን በመዝናኛው መስክና በሌሎች መንገዶች ሰዎችን አታልሎ መልካሙን ክፉ፣ ክፉውን መልካም ብለው እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል። (ኢሳይያስ 5:20) አንዳንድ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ጭምር ሰይጣን የሚያዛምተውን የተሳሳተ መረጃ አምነው ተቀብለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል “በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች እምነትን ክደው አታላይ መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት እንደሚከተሉ መንፈስ በግልጥ ይናገራል። እንዲህ ያለው ትምህርት የሚመጣው ኅሊናቸው በጋለ ብረት የተጠበሰ ያህል ከደነዘዘባቸው ግብዝ ውሸተኞች ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 4:1, 2፤ ኤርምያስ 6:15

13. መጥፎ ጓደኝነት ምንድን ነው? የጓደኛ ምርጫችን ምን ተጽዕኖ ያሳድርብናል?

13 ማናችንም ብንሆን የዓለም መንፈስ አይነካኝም ልንል አንችልም። የሰይጣን ሥርዓት ንፋስና ማዕበል በጣም ኃይለኛ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አትሳቱ፤ ’መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል’” የሚል ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጠናል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) መጥፎ ጓደኝነት የዓለምን መንፈስ የሚያንጸባርቅ ማንኛውንም ነገር ወይም ማንኛውንም ሰው ሊጨምር ብሎም በጉባኤ ውስጥ ሊታይ ይችላል። መጥፎ ጓደኝነት ምንም ጉዳት ሊያስከትልብን አይችልም የምንል ከሆነ ጥሩ ጓደኝነትም ምንም ሊጠቅመን አይችልም የማለት ያህል ይሆንብናል። ይህ ምንኛ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው! “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጒዳት ያገኘዋል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ጉዳዩን በግልጽ አስቀምጦታል።—ምሳሌ 13:20

14. የዓለምን መንፈስ መቋቋም የምንችለው ምን በማድረግ ነው?

14 የዓለምን መንፈስ ለመቋቋም ይሖዋን ከሚያገለግሉ ጥበበኛ ሰዎች ጋር መቀራረብ ይኖርብናል። እምነታችን እንዲጠናከር በሚያስችሉ ነገሮች አእምሯችንን መሙላት ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል “እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና፣ እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።” (ፊልጵስዩስ 4:8) ክፉና ደጉን የመለየት ችሎታ ያለን እንደመሆናችን መጠን ማሰብ የምንፈልጋቸውን ነገሮች መምረጥ እንችላለን። ምንጊዜም ቢሆን ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚያስችሉንን ነገሮች ለማሰብ እንምረጥ።

የአምላክ መንፈስ የበለጠ ኃይል አለው

15. በጥንቷ ቆሮንቶስ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች በከተማዋ ከነበሩ ሰዎች የተለዩ የሆኑት እንዴት ነው?

15 በዓለም መንፈስ ተታልለው ከሚወሰዱ ሰዎች በተለየ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚመሩት በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ነው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበረው ጉባኤ እንዲህ ሲል ጽፏል “ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ነው።” (1 ቆሮንቶስ 2:12) የጥንቷ ቆሮንቶስ የዓለም መንፈስ የነገሠባት ከተማ ነበረች። አብዛኞቹ የከተማዋ ነዋሪዎች አስጸያፊ ሥነ ምግባር ስለነበራቸው “ቆሮንቶሳዊነት” የሚለው ቃል “ብልግና መፈጸም” የሚል ትርጉም ይዟል። ሰይጣን የሰዎቹን አእምሮ አሳውሮ ነበር። በመሆኑም ስለ እውነተኛው አምላክ የነበራቸው ግንዛቤ በጣም ትንሽ ሲሆን አንዳንዶቹም ምንም እውቀት አልነበራቸውም። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሆኖም ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት አንዳንድ የቆሮንቶስ ሰዎች ዓይናቸው እንዲገለጥ በማድረግ የእውነትን እውቀት እንዲያገኙ አስቻላቸው። መንፈሱ በሕይወታቸው ውስጥ ጉልህ ለውጦች እንዲያደርጉ በማነሳሳትና በመምራት የእርሱን ሞገስና በረከት እንዲያገኙ ረዳቸው። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) የዓለም መንፈስ ጠንካራ ቢሆንም የይሖዋ መንፈስ ግን ከዚያ ይበልጥ ጠንካራ ነበር።

16. የአምላክን መንፈስ ለማግኘትና መልሰን ላለማጣት ምን ማድረግ እንችላለን?

16 ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ አቻ የሌለው ብርቱ ኃይል ሲሆን ይሖዋም በእምነት ለሚጠይቁት ሁሉ ምንም ሳይቆጥብ በነጻ ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 11:13) ይሁን እንጂ የአምላክን መንፈስ ለማግኘት የዓለምን መንፈስ በመቋቋም ብቻ መወሰን የለብንም። መንፈሳችን ማለትም አስተሳሰባችን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የተስማማ እንዲሆን በየጊዜው ቃሉን ማጥናትና በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግም አለብን። እንዲህ ካደረግን ሰይጣን መንፈሳዊነታችንን ለማጥፋት የሚጠቀምበትን ማንኛውንም ዘዴ መቋቋም እንድንችል ይሖዋ ያበረታናል።

17. ሎጥ ያጋጠመው ሁኔታ ማጽናኛ ሊሆነን የሚችለው እንዴት ነው?

17 ክርስቲያኖች የዓለም ክፍል ባይሆኑም እንኳ የሚኖሩት በዓለም ውስጥ ነው። (ዮሐንስ 17:11, 16) በሥራም ሆነ በጉርብትና የምንገናኛቸው ሰዎች ለአምላክና ለመመሪያዎቹ ፍቅር የሌላቸው ሊሆኑ ስለሚችሉ ማናችንም ብንሆን ከዓለም መንፈስ ሙሉ በሙሉ መራቅ አንችልም። አብረውት የሚኖሩት የሰዶም ሰዎች በሚፈጽሙት የዓመፅ ድርጊት ‘ይሣቀቅ’ ብሎም ይሠቃይ እንደነበረው እንደ ሎጥ ይሰማናል? (2 ጴጥሮስ 2:7, 8) እንዲህ የሚሰማን ከሆነ መጽናኛ ማግኘት የምንችልበት ዝግጅት አለ። ይሖዋ ሎጥን ጠብቆታል እንዲሁም አድኖታል፤ ለእኛም ተመሳሳይ ነገር ሊያደርግልን ይችላል። አፍቃሪው አባታችን ያለንበትን ሁኔታ የሚመለከትና የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ መንፈሳዊነታችንን መጠበቅ እንድንችል አስፈላጊውን እርዳታና ኃይል ሊሰጠን ይችላል። (መዝሙር 33:18, 19) በእርሱ የምንመካና የምንታመን እንዲሁም ወደ እርሱ የምንጸልይ ከሆነ ያለንበት ሁኔታ የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን የዓለምን መንፈስ እንድንቋቋም ይረዳናል።—ኢሳይያስ 41:10

18. ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ከፍ አድርገን መመልከት ያለብን ለምንድን ነው?

18 የምንኖረው ከአምላክ በራቀና ሰይጣን ባሳወረው ዓለም ውስጥ ቢሆንም የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን እውነትን በማወቃችን ተባርከናል። በመሆኑም ዓለም ያላገኘው ደስታና ሰላም አለን። (ኢሳይያስ 57:20, 21፤ ገላትያ 5:22) የዚህ ዓለም መንፈስ በማይኖርበት ገነት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ያለንን ግሩም ተስፋ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ስለዚህ ከአምላክ ጋር ያለንን ውድ ዝምድና አጥብቀን እንያዝ። እንዲሁም በመንፈሳዊ እንድንወሰድ የሚያደርገንን ማንኛውንም ዝንባሌ ለማስወገድ ንቁ እንሁን። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንቅረብ፤ እርሱም የዓለምን መንፈስ እንድንቋቋም ይረዳናል።—ያዕቆብ 4:7, 8

ልታብራራ ትችላለህ?

• ሰይጣን ሰዎችን የሚያታልለውና የሚያስተው በምን መንገዶች ነው?

• ከይሖዋ እንዳንርቅ መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

• የዓለም መንፈስ ኃይለኛ መሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን?

• የአምላክን መንፈስ ለማግኘትና መልሰን ላለማጣት ምን ማድረግ አለብን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ግራፍ/ሰንጠረዥ]

በዓለም ጥበብና በአምላክ ጥበብ መካከል ያለው ልዩነት

ፍጹም እውነት የለም—እውነት እንደየሰዉ አመለካከት ይለያያል።

‘የአምላክ ቃል እውነት ነው።’—ዮሐንስ 17:17

ክፉና ደጉን ለመለየት ስሜትህ የሚነግርህን ስማ።

“የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም።”—ኤርምያስ 17:9

ያሻህን አድርግ።

“[ሰው] አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ።”—ኤርምያስ 10:23

ሀብት የደስታ ቁልፍ ነው።

“የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 6:10

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰሎሞን ከእውነተኛው አምልኮ ስቶ የሐሰት አማልክትን ማምለክ ጀምሯል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰይጣን እንደ አንድ የማስታወቂያ አዘጋጅ የዓለምን መንፈስ ያስፋፋል። መንፈሱን እየተቋቋምክ ነው?