የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ዘኁልቁ 25:9 ዝሙት በመፈጸማቸው ምክንያት በአንድ ቀን የተገደሉት እስራኤላውያን 24,000 እንደሆኑ ሲናገር 1 ቆሮንቶስ 10:8 ግን 23,000 መሆናቸውን የሚገልጸው ለምንድን ነው?
በሁለቱ ጥቅሶች ላይ የቁጥር ልዩነት የተፈጠረበትን ምክንያት ከተለያየ አቅጣጫ መግለጽ ይቻላል። ትክክለኛው አኃዝ በ23,000 እና በ24,000 መካከል ሊሆንና ቁጥሩን ሙሉ ለማድረግ ተጨምሮበት ወይም ከቁጥሩ ላይ ተቀንሶ ይሆናል ብለን በቀላሉ መግለጽ እንችላለን።
ሌላውን አማራጭ ደግሞ ተመልከት። ሐዋርያው ጳውሎስ በሰጢም የነበሩትን እስራኤላውያን ታሪክ ጠቅሶ የተናገረው ልቅ በሆነው የሕዝቡ አኗኗር በምትታወቀው በጥንቷ ቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ እንዲሆናቸው ነው። “ከእነርሱ አንዳንዶቹ ዝሙት ፈጽመው በአንድ ቀን ሀያ ሦስት ሺህ ሰው እንደ ረገፈ፣ እኛም ዝሙት አንፈጽም” ሲል ጽፏል። ጳውሎስ ዝሙት በመፈጸማቸው ምክንያት በቀጥታ ይሖዋ የገደላቸውን ብቻ ለይቶ ሲጠቅስ ቁጥራቸው 23,000 መሆኑን ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 10:8
ይሁን እንጂ ዘኁልቁ ምዕራፍ 25 “እስራኤል የፌጎርን በኣል በማምለክ ተባበረ፤ የእግዚአብሔርም ቁጣ በላዩ ነደደ” በማለት ይገልጻል። ከዚያም ይሖዋ “የሕዝቡን አለቆች ሁሉ” እንዲገድላቸው ሙሴን አዘዘው። ሙሴም ይሖዋ የሰጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለእስራኤል ዳኞች መመሪያ ሰጣቸው። በመጨረሻ ፊንሐስ አንዲት ምድያማዊት ሴት ወደ ሠፈሩ ይዞ የመጣን እስራኤላዊ ለመግደል ፈጣን እርምጃ በመውሰዱ ‘መቅሠፍቱ ተከለከለ።’ ዘገባው “በመቅሠፍቱ የሞተው ሰው ቁጥር ሃያ አራት ሺህ ደርሶ ነበር” በማለት ይደመደማል።—ዘኍልቊ 25:1-9
ዘኁልቁ ላይ የተጠቀሰው ቁጥር በዳኞቹ የተገደሉትን “የሕዝቡን አለቆች” እና በቀጥታ በይሖዋ የተቀሠፉትን ሰዎች እንደሚያጠቃልል ግልጽ ነው። በዳኞቹ እጅ የተገደሉት የሕዝቡ አለቆች አንድ ሺህ ሊደርሱ ይችላሉ፤ ይህም ቁጥሩን ወደ 24,000 ከፍ ያደርገዋል። እነዚህ አለቆች ወይም የዓመፁ ቆስቋሾች ዝሙት የፈጸሙ፣ በበዓሉ ላይ የተገኙ አሊያም በእነዚህ ድርጊቶች ለተካፈሉት ድጋፍ የሰጡ ሆኑም አልሆኑ ‘የፌጎርን በኣል በማምለክ ተባባሪ’ በመሆናቸው ጥፋተኞች ሆነው ተገኝተዋል።
‘መተባበር’ የሚለውን ቃል በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ላይ ማብራሪያ የሚሰጥ አንድ ጽሑፍ “ከአንድ ሰው ጋር ቁርኝት መፍጠር” የሚል ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ገልጿል። እስራኤላውያን ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሕዝቦች ቢሆኑም ‘የፌጎርን በኣል በማምለክ ተባባሪ’ ሆነው በመገኘታቸው ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ዝምድና አበላሽተዋል። ከ700 ዓመታት ገደማ በኋላ ይሖዋ በነቢዩ ሆሴዕ አማካኝነት እስራኤላውያንን በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “ወደ ብዔልፌጎር በመጡ ጊዜ . . . ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ራሳቸውን ለዩ፤ እንደ ወደዱትም ጣዖት የረከሱ ሆኑ።” (ሆሴዕ 9:10) እንደዚህ ያደረጉ ሁሉ መለኮታዊ ቅጣት ይገባቸው ነበር። በመሆኑም ሙሴ እስራኤላውያንን “እግዚአብሔር በብዔልፌጎር ላይ ምን እንዳደረገ በዐይናችሁ አይታችኋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከመካከላችሁ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሁሉ አጥፍቶአቸዋል” በማለት አስታውሷቸዋል።—ዘዳግም 4:3