የአውሬውን ማንነትና የምልክቱን ትርጉም መረዳት
የአውሬውን ማንነትና የምልክቱን ትርጉም መረዳት
እንቆቅልሽ መፍታት ትወድዳለህ? መልሱን ለማግኘት እንዲረዳህ በመጀመሪያ ፍንጭ የሚሰጡ አንዳንድ ነገሮችን ለማግኘት ትሞክራለህ። አምላክ በመንፈስ አነሳሽነት ባስጻፈው ቃሉ አማካኝነት ራእይ ምዕራፍ 13 ላይ የተጠቀሰው ለአውሬው የተሰጠው 666 የሚለውን ቁጥር፣ ስም ወይም ምልክት መረዳት የምንችልበትን ፍንጭ ሰጥቶናል።
በዚህ ርዕስ ውስጥ የአውሬውን ምልክት ትርጉም ለማወቅ እንድንችል ፍንጭ የሚሰጡንን አራት ቁልፍ ነጥቦች እንመለከታለን። (1) የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞች የሚሰጡት እንዴት እንደሆነ፣ (2) አውሬው ምን እንደሆነ፣ (3) 666 “የሰው ቁጥር” መባሉ ምን ትርጉም እንዳለው እና (4) 6 ቁጥር የያዘውን ትርጉምና ቁጥሩ ሦስት ጊዜ የተደገመው ማለትም 600 ሲደመር 60 ሲደመር 6 ወይም 666 ተብሎ የተጻፈው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።—ራእይ 13:18
የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞች ትርጉም አዘል ፍቺ አላቸው
የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞች በተለይ አምላክ ያወጣቸው በሚሆኑበት ጊዜ በአብዛኛው ትርጉም አዘል ናቸው። ለምሳሌ ያህል አብራም ከአብራኩ ብዙ ነገዶች ስለሚወጡ አምላክ ስሙን አብርሃም ብሎ ለወጠው፤ ትርጉሙም “የብዙ ሕዝቦች አባት” ማለት ነው። (ዘፍጥረት 17:5) አምላክ፣ ማርያም ከጊዜ በኋላ የምትወልደውን ልጅ ኢየሱስ ብለው እንዲጠሩት ለእሷና ለዮሴፍ የነገራቸው ሲሆን ስሙ ይሖዋ አዳኝ ነው የሚል ትርጉም አለው። (ማቴዎስ 1:21 የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት፤ ሉቃስ 1:31) ከዚህ ትርጉም አዘል ስም ጋር በሚስማማ መንገድ ይሖዋ በኢየሱስ አገልግሎትና መሥዋዕታዊ ሞት አማካኝነት መዳን የምናገኝበትን ዝግጅት አድርጎልናል።—ዮሐንስ 3:16
በዚህ መሠረት 666 የሚለው አምላክ ያወጣው ስም አውሬው ምን ባሕርይ እንዳለው የሚያመለክት መግለጫ መሆን አለበት። የአውሬውን ባሕርያት መረዳት እንድንችል የአውሬውን ማንነት መገንዘብና የሚያከናውናቸውን ነገሮች ማወቅ አለብን።
የአውሬው ማንነት ታወቀ
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዳንኤል መጽሐፍ የምሳሌያዊዎቹን አውሬዎች ትርጉም ማወቅ እንድንችል ብርሃን ይፈነጥቅልናል። ምዕራፍ 7 ስለ “‘አራት ታላላቅ አራዊት’” ማለትም ስለ አንበሳ፣ ድብ፣ ነብርና ታላላቅ ጥርሶች ስላሉት የሚያስፈራ አውሬ ዝርዝር መግለጫ ይዟል። (ዳንኤል 7:2-7) ዳንኤል እነዚህ አራዊት በጣም ሰፊ ግዛት የሚኖራቸው ተራ በተራ የሚነሡ “መንግሥታት” መሆናቸውን አሳውቆናል።—ዳንኤል 7:17, 23
ራእይ 13:1, 2 ላይ የተጠቀሰውን አውሬ በተመለከተ ዚ ኢንተርፕሬተርስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንዲህ ሲል ገልጿል:- “[አውሬው] ዳንኤል ባየው ራእይ ላይ የተጠቀሱት አራቱ አራዊት ያላቸውን ባሕርያት አጠቃልሎ ይዟል . . . በመሆኑም [በራእይ ላይ የተጠቀሰው] ይህ የመጀመሪያው አውሬ የአምላክ ጠላት የሆኑትን በዓለም ላይ ያሉትን የፖለቲካ አገዛዞች በሙሉ ይወክላል።” ራእይ 13:7 ላይ የሚገኘው “በነገድ፣ በወገን፣ በቋንቋና በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው” የሚለው መግለጫ ይህን አባባል ያረጋግጣል። a
መጽሐፍ ቅዱስ ሰብዓዊ አገዛዝን ለመግለጽ አራዊትን ምሳሌ አድርጎ የሚጠቀመው ለምንድን ነው? ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል። አንደኛው ምክንያት ባለፉት መቶ ዘመናት መንግሥታት እንደ አራዊት ደም በማፍሰስ ያስመዘገቡት ታሪክ ነው። የታሪክ ምሑራን የሆኑት መክብብ 8:9) ሁለተኛው ምክንያት ‘ዘንዶው [ሰይጣን] የራሱን ኀይልና የራሱን ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን ለአውሬው የሰጠው’ መሆኑ ነው። (ራእይ 12:9፤ 13:2) ከዚህም የተነሳ ሰብዓዊ አገዛዝ ዲያብሎስ ያቋቋመው ተቋም በመሆኑ የእርሱን ዘንዶ መሰል የአውሬነት ባሕርይ ያንጸባርቃል።—ዮሐንስ 8:44፤ ኤፌሶን 6:12
ዊል እና ኤሪየል ዱራንት “ዓለማችን ከጦርነት ያረፈችበት ወቅት የለም። ሥልጣኔና ዲሞክራሲ በሰፈነበት በዚህ ዘመን እንኳ ጦርነት ፈጽሞ ጋብ አላለም” በማለት ጽፈዋል። “ሰው ሰውን ለመጉዳት ገዥ” ይሆናል መባሉ ምንኛ ትክክል ነው! (እንዲህ ሲባል ግን እያንዳንዱ ሰብዓዊ ገዥ በቀጥታ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ነው ማለት አይደለም። እርግጥ ሰብዓዊ መንግሥታት በኅብረተሰቡ ውስጥ ሥርዓት በማስፈን “የእግዚአብሔር አገልጋይ” ሆነው የሚሠሩበት ሁኔታ አለ፤ ይህ ባይሆን ኖሮ ሥርዓት አልበኝነት በነገሠ ነበር። እንዲያውም አንዳንድ መሪዎች መሠረታዊ ከሆኑ ሰብዓዊ መብቶች በተጨማሪ በእውነተኛው አምልኮ የመሳተፍ መብትን አስከብረዋል፤ ሰይጣን ግን በዚህ አይደሰትም። (ሮሜ 13:3, 4፤ ዕዝራ 7:11-27፤ የሐዋርያት ሥራ 13:7) ይሁንና ዲያብሎስ በዚህ ዓለም ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ የትኛውም ግለሰብ ወይም ሰብዓዊ ተቋም ለሰዎች ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ማምጣት አልቻለም። b—ዮሐንስ 12:31
“የሰው ቁጥር”
666 ምን ትርጉም እንዳለው እንድናውቅ የሚያስችለን ሦስተኛው ፍንጭ ቁጥሩ “የሰው ቁጥር” መሆኑ ነው። በአውሬው ላይ ሥልጣን ያለው ሰይጣን እንጂ ሰው ባለመሆኑ ይህ አባባል አንድን ግለሰብ የሚያመለክት ሊሆን አይችልም። (ሉቃስ 4:5, 6፤ 1 ዮሐንስ 5:19፤ ራእይ 13:2, 18) ከዚህ ይልቅ አውሬው “የሰው ቁጥር” ወይም ምልክት ያለው መሆኑ መንፈስ ወይም አጋንንት ሳይሆን የሰው ተፈጥሮ ያለውና ከዚህም የተነሳ ሰዎች ያላቸውን አንዳንድ ባሕርያት የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ያሳያል። እነዚህ ባሕርያት ምንድን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም [ሰዎች] ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” የሚል መልስ ይሰጣል። (ሮሜ 3:23) በመሆኑም አውሬው “የሰው ቁጥር” ያለው መሆኑ መንግሥታት፣ የኃጢአትና የአለፍጽምና ምልክት የሆነውን ሰው የሚገኝበትን የረከሰ ሁኔታ እንደሚያንጸባርቁ ያሳያል።
ታሪክ ለዚህ ምሥክር ነው። የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲህ ብለዋል:- “በዚህ ዓለም ላይ የተነሳ የትኛውም ሥልጣኔ በመጨረሻ ወድቋል። ታሪክ ሳይሳኩ የቀሩ ጥረቶች፣ ሳይፈጸሙ የቀሩ ውጥኖች የሚወሱበት መድረክ ነው . . . በመሆኑም አንድ የታሪክ ምሑር ሁኔታዎች አሳዛኝ መደምደሚያ እንደሚኖራቸው አምኖ መቀበል አለበት።” ኪሲንገር የሰነዘሩት ሐሳብ “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል” መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው መሠረታዊ እውነት ትክክል መሆኑን ያሳያል።—ኤርምያስ 10:23
የአውሬውን ማንነት ካወቅንና አምላክ እንዴት እንደሚመለከተው ከተረዳን፣ ቀጥሎ የእንቆቅልሹ የመጨረሻ ክፍል የሆነውን ስድስት ቁጥርና ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ መጻፉ (666) ማለትም 600 ሲደመር 60 ሲደመር 6 ምን ማለት እንደሆነ መመርመር እንችላለን።
ስድስት ሦስት ጊዜ የተጻፈው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ቁጥሮች ምሳሌያዊ ትርጉም አላቸው። ለምሳሌ ያህል ሰባት ቁጥር በአምላክ ዓይን ሙሉ ወይም ፍጹም የሆነን ነገር ለማመልከት ይሠራበታል። አምላክ የፍጥረት ሥራዎቹን ያከናወነበት ሳምንት፣ ሰባት ‘ቀናት’ ማለትም ለረጅም ጊዜ የዘለቁ ዘመናትን የያዘ ሲሆን በዚህ ወቅት በምድር ላይ መሥራት የፈለገውን ነገር ሙሉ በሙሉ ሠርቶ አጠናቅቋል። (ዘፍጥረት 1:3 እስከ 2:3) የአምላክ “ቃል . . . ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ” ብር ተደርጎ የተገለጸ ሲሆን ይህም ፈጽሞ የጠራ መሆኑን ያሳያል። (መዝሙር 12:6፤ ምሳሌ 30:5, 6) ለምጻም የነበረው ንዕማን ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሰባት ጊዜ እንዲታጠብ ተነግሮታል፤ ይህን በማድረጉም የተሟላ ፈውስ አግኝቷል።—2 ነገሥት 5:10, 14
ስድስት ቁጥር ከሰባት በአንድ ያንሳል፤ ታዲያ በአምላክ ዓይን ጉድለት ወይም እንከን ያለበትን ነገር ለማመልከት የሚያስችል ተስማሚ ምሳሌ አይደለም? በእርግጥ ነው! (1 ዜና መዋዕል 20:6, 7) ከዚህም በላይ ስድስት ሦስት ጊዜ መደጋገሙ (666) አንድ ነገር ከፍጽምና በጣም የራቀ መሆኑን አጉልቶ ያሳያል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው 666 “የሰው ቁጥር” መሆኑ ይህ መደምደሚያ ትክክል መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም አውሬው ያስመዘገበው ታሪክ፣ “የሰው ቁጥር” ያለው መሆኑ እንዲሁም 666 የሚለው ቁጥር በራሱ፣ በይሖዋ ዓይን ሲታይ ከፍተኛ ጉድለት ያለበትና ደካማ መሆኑን ያሳያል የሚል ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያስችለናል።
አውሬው ያሉበት ጉድለቶች የተገለጸበት ሁኔታ ለጥንቷ ባቢሎን ንጉሥ ለብልጣሶር የተነገረውን ነገር ያስታውሰናል። ይሖዋ በነቢዩ ዳንኤል አማካኝነት ለንጉሡ ይህን መልእክት ልኮለታል:- “በሚዛን ተመዘንህ፤ ቀለህም ተገኘህ።” ብልጣሶር በዚያው ሌሊት ተገደለ፤ ኃያሉ የባቢሎን መንግሥትም ወደቀ። (ዳንኤል 5:27, 30) በተመሳሳይ አምላክ የፖለቲካውን ሥርዓት በሚወክለው አውሬና ምልክቱን በተቀበሉ ሰዎች ላይ የሚያስተላልፈው ፍርድ የአውሬውንና የደጋፊዎቹን ጥፋት ያመለክታል። በዚህ ጊዜ ግን አምላክ ከዚህ ምድር ላይ የሚያስወግደው አንድን የፖለቲካ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም የሰብዓዊ አገዛዝ ርዝራዥ ጭምር ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 19:19, 20) በመሆኑም ለሞት የሚዳርገውን የአውሬውን ቁጥር አለመቀበላችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
የቁጥሩ ትርጉም ታወቀ
ራእይ መጽሐፍ ላይ 666 የሚለው ቁጥር ከተገለጸ በኋላ ቀጥሎ የተጠቀሱት 144,000ዎቹ ሲሆኑ እነርሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ስምና የአባቱ የይሖዋ ስም በግምባራቸው ላይ ተጽፎባቸዋል። እነዚህን ስሞች የተሸከሙ ሰዎች የይሖዋና የልጁ ወገን መሆናቸውን ያሳያሉ፤ ስለ እነርሱም በልበ ሙሉነት ይመሠክራሉ። በተመሳሳይም የአውሬው ቁጥር ያላቸው ሰዎች የአውሬው አገልጋዮች ሉቃስ 20:25፤ ራእይ 13:4, 8፤ 14:1) እንዴት? ተስፋቸውን ለጣሉበትና መዳን ያስገኝልናል ብለው ለሚያምኑበት ለፖለቲካ ተቋም፣ ለሚጠቀምባቸው አርማዎችና ለወታደራዊ ኃይሉ አምልኮ አከል ክብር በመስጠት ነው። ለእውነተኛው አምላክ የሚያቀርቡት አምልኮ ከቃል ያለፈ አይደለም።
መሆናቸውን በግልጽ ያሳያሉ። በመሆኑም ምልክቱ የተደረገው ቀኝ እጅ ላይም ሆነ ግምባር ላይ ምልክቱ ያለበት ሰው በዚህ ዓለም ላይ ላሉ አውሬ መሰል የፖለቲካ ሥርዓቶች ከአምልኮ የማይተናነስ ድጋፍ እንደሚሰጥ የሚያሳይ ምሳሌያዊ መግለጫ ነው። ምልክቱን የተቀበሉ ሰዎች ለአምላክ የሚገባውን “ለቄሳር” ይሰጣሉ። (ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ይሰጣል:- “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ። መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።” (መዝሙር 146:3, 4) ይህን ጥበብ ያዘለ ምክር የሚከተሉ ክርስቲያኖች መንግሥታት የሰጡትን ተስፋ መፈጸም ሲያቅታቸው ወይም ከፍተኛ አድናቆት ያተረፉ መሪዎች በድንገት ከቦታቸው ሲወርዱ ግራ አይጋቡም።—ምሳሌ 1:33
እንዲህ ሲባል ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ችግር ዝም ብለው ይመለከታሉ ማለት አይደለም። እንዲያውም የአምላክ መንግሥት ወኪል በመሆናቸው ይህ መንግሥት የሰው ልጆችን ችግር የሚያስወግደው ብቸኛው መስተዳድር መሆኑን በትጋት ያውጃሉ።—ማቴዎስ 24:14
የአምላክ መንግሥት—ብቸኛው የሰው ልጆች ተስፋ
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የስብከቱ ዋነኛ ጭብጥ የአምላክ መንግሥት ነበር። (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ላይ (አንዳንድ ጊዜ የጌታ ጸሎት ይባላል) ተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና ፈቃዱም በምድር ላይ እንዲሆን መጸለይ እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ መንግሥት በሰማይ ሆኖ በመላው ምድር ላይ የሚገዛ መስተዳድር ነው። ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማይ” ብሎ የጠራው በዚህ ምክንያት ነው።—ማቴዎስ 11:12
ወደፊት ተገዢዎቹ ለሚሆኑት ሰዎች ከሞተው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ የዚህ መንግሥት ንጉሥ ለመሆን የተሻለ ብቃት ያለው ማን አለ? (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዮሐንስ 3:16) በአሁኑ ጊዜ ኃያል መንፈሳዊ አካል የሆነው ይህ ፍጹም ገዥ በቅርቡ አውሬውን፣ ነገሥታቱንና ሠራዊቶቻቸውን “በዲን ወደሚቃጠለው የእሳት ባህር” ውስጥ ይጥላቸዋል። ይህም ፍጹም ጥፋትን የሚያመለክት ምሳሌያዊ መግለጫ ነው። ይሁንና ነገሩ በዚህ አያበቃም። ኢየሱስ ሰይጣንንም ያስወግደዋል፤ ይህ ማንኛውም ሰው ሊያደርገው የሚችለው ነገር አይደለም።—ራእይ 11:15፤ 19:16, 19-21፤ 20:2, 10
የአምላክ መንግሥት ታዛዥ ለሆኑ ዜጎቹ በሙሉ ሰላም ያሰፍንላቸዋል። (መዝሙር 37:11, 29፤ 46:8, 9) ሐዘን፣ ሥቃይና ሞት እንኳ ሳይቀር ይወገዳሉ። የአውሬውን ምልክት የማይቀበሉ ሰዎች እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ይጠብቃቸዋል!—ራእይ 21:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የእነዚህን ጥቅሶች ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 28 ተመልከት።
b እውነተኛ ክርስቲያኖች ሰብዓዊ አገዛዝ በአመዛኙ የአውሬነት ባሕርይ እንዳለው የሚገነዘቡ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ በሚያዘው መሠረት “በሥልጣን ላሉት ሹማምንት” ይገዛሉ። (ሮሜ 13:1) ይሁን እንጂ የመንግሥት ሹማምንት የአምላክን ሕግ የሚጻረር ነገር እንዲያደርጉ ሲያዟቸው “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚል መልስ ይሰጣሉ።—የሐዋርያት ሥራ 5:29
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የ666ን ትርጉም ለማወቅ የሚያስችሉ ፍንጮች
1. በአብርሃም፣ በኢየሱስና በሌሎች በርካታ ሰዎች ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞች አብዛኛውን ጊዜ ስለ ግለሰቡ ባሕርያትና አኗኗር አንዳንድ ነገሮችን ይገልጻሉ። በተመሳሳይ የአውሬው ስም ማለትም ቁጥሩ ባሕርያቱን ይወክላል።
2. የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱት አራዊት በቅደም ተከተል የተነሱ ሰብዓዊ መንግሥታትን ወይም አገሮችን ያመለክታሉ። ራእይ 13:1, 2 ላይ የተገለጸው የተለያዩ ገጽታዎችን ያካተተው አውሬ ሰይጣን የሾመውንና የሚቆጣጠረውን ዓለም አቀፉን የፖለቲካ ሥርዓት ያመለክታል።
3. አውሬው “የሰው ቁጥር” ያለው መሆኑ ከአጋንንት ጋር ሳይሆን ከሰው ጋር ዝምድና ያለው ተቋም መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም ሰዎች ከኃጢአትና ከአለፍጽምና የተነሳ ያሉባቸውን ጉድለቶች ያንጸባርቃል።
4. በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ ሙሉ ወይም ፍጹም መሆንን ከሚያመለክተው ከሰባት የሚያንሰው ስድስት ቁጥር በአምላክ ዓይን ከፍጽምና የራቀን ነገር ያመለክታል። 666 በሚለው ምልክት ላይ ስድስት ቁጥር ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ መጻፉ ጉድለቱን አጉልቶ ያሳያል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በረሃብ የተጠቃ ሕፃን:- UNITED NATIONS/Photo by F. GRIFFING
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
666 የሚለው ቁጥር በግልጽ እንደሚያሳየው ሰብዓዊ አገዛዝ ከንቱ መሆኑ ተረጋግጧል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ፍጹም አገዛዝ ያሰፍናል