ርብቃ—ፈሪሃ አምላክ ያላት የተግባር ሴት
ርብቃ—ፈሪሃ አምላክ ያላት የተግባር ሴት
ለልጅህ ሚስት የምትመርጥለት አንተ ነህ እንበል? ምን ዓይነት ሴት ትመርጥለታለህ? የትኞቹን ብቃቶች እንድታሟላ ትፈልጋለህ? መልከ ቀና፣ አስተዋይ፣ ደግና ታታሪ የሆነች ሴት ነው የምትፈልግለት? ወይስ እንድታሟላው የምትፈልገው ሌላ ብቃት አለ?
አብርሃም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ገጥሞት ነበር። በልጁ በይስሐቅ በኩል ዘሮቹ እንደሚባረኩ ይሖዋ ቃል የገባለት ቢሆንም አብርሃም በዚህ ወቅት አርጅቶ የነበረ ሲሆን ልጁ ይስሐቅ ደግሞ ገና አላገባም ነበር። (ዘፍጥረት 12:1-3, 7፤ 17:19፤ 22:17, 18፤ 24:1) ይስሐቅ ከይሖዋ በረከቶች የሚካፈለው ከወደፊት ሚስቱና ከልጆቻቸው ጋር ስለነበር አብርሃም ለልጁ ተስማሚ ሚስት ለማግኘት ዝግጅት አደረገ። ይህቺ ሴት ከሁሉም በላይ የይሖዋ አገልጋይ መሆን ይኖርባታል። አብርሃም በሚኖርበት በከነዓን ይሖዋን የምታመልክ ሴት ማግኘት ስለማይቻል ከሌላ ቦታ መፈለግ ነበረበት። በመጨረሻም ርብቃ የተባለች ሴት የይስሐቅ ሚስት እንድትሆን ተመረጠች። ርብቃ የተገኘችው እንዴት ነበር? ደግሞስ መንፈሳዊ ሴት ነበረች? የእርሷን ታሪክ በመመርመር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
ብቃቱን የምታሟላ ሴት ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ
አብርሃም ይሖዋን ከሚያመልኩት ዘመዶቹ ለይስሐቅ ሚስት እንዲያመጣለት ከአገልጋዮቹ መካከል በዕድሜ ትልቅ የሆነውን (ምናልባትም ኤሊዔዘርን ሳይሆን አይቀርም) ርቆ ወደሚገኘው ወደ መስጴጦምያ ላከው። ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ስለሆነ ለይስሐቅ ከነዓናዊት ሚስት እንዳያመጣለት ኤሊዔዘርን አስምሎት ነበር። አብርሃም ለሁኔታው ከፍተኛ ክብደት በመስጠቱ አድናቆት ሊቸረው ይገባል።—ዘፍጥረት 24:2-10
ኤሊዔዘር የአብርሃም ዘመዶች ወደሚኖሩበት ከተማ ከደረሰ በኋላ አሥሩን ግመሎቹን ወደ ውሃ ጉድጓድ ይዟቸው መጣ። ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር! ጊዜው አመሻሹ ላይ ነበር። ኤሊዔዘር እንዲህ በማለት ወደ ይሖዋ ጸሎት አቀረበ:- “እነሆ፤ እኔ በዚህ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዪቱ ሴቶች ልጆች ውሃ ለመቅዳት ወደዚህ ይመጣሉ። እንግዲህ ‘እንስራሽን አውርጂና ውሃ አጠጪኝ’ ስላት፣ ‘እንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም ላጠጣልህ’ የምትለኝ ቆንጆ እርሷ ለባሪያህ ለይስሐቅ የመረጥካት ትሁን።”—በአካባቢው የምትኖር ማንኛዋም ሴት አንድ የተጠማ ግመል እስከ 100 ሊትር የሚደርስ ውሃ ሊጠጣ እንደሚችል ሳታውቅ አትቀርም። ስለዚህ አሥር ግመሎችን ማጠጣት በጣም ከባድ ሥራ እንደሆነ ትገነዘባለች። አንዲት ሴት ሌሎች ቆመው ከማየት በቀር ምንም ሳይረዷት ብቻዋን ይህን ሥራ ማከናወኗ ጠንካራ፣ ትዕግሥተኛ፣ ትሑት እንዲሁም ለሰውና ለእንስሳ የምታዝን መሆኗን ያሳያል።
ታዲያ የጸሎቱ መልስ ምን ሆነ? “እርሱም ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ፣ እነሆ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች። እርሷም ከአብርሃም ወንድም ከናኮርና ከሚስቱ ከሚልካ የተወለደው የባቱኤል ልጅ ነበረች። ልጃገረዲቱ እጅግ ውብና . . . ድንግል ነበረች። ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ በእንስራዋ ሞልታ ተመለሰች። አገልጋዩም ወደ እርሷ ፈጥኖ ቀረበና፣ ‘እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ’ አላት። እርሷም፣ ‘ጌታዬ፤ ጠጣ’ አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ወደ እጅዋ አውርዳ አጠጣችው።”—ዘፍጥረት 24:15-18
ርብቃ ብቃቱን ታሟላ ይሆን?
ርብቃ የአብርሃም የወንድሙ የልጅ ልጅ ስትሆን ከውበቷ በተጨማሪ መልካም ምግባር ያላት ሴት ነበረች። አንድን እንግዳ ሰው ለማነጋገር ወደኋላ የማትል ብትሆንም በጣም የምታውቀው ይመስል ከልክ በላይ ለመቅረብም አልደፈረችም። ኤሊዔዘር ውሃ እንድትሰጠው በጠየቃት ጊዜ ለመስጠት አላመነታችም። ውሃ መስጠት ለማንም ሰው የሚደረግ የደግነት ተግባር ስለሆነ ይህ የሚጠበቅ ነበር። ይሁን እንጂ ርብቃ፣ ኤሊዔዘር በጸሎቱ ላይ
የጠቀሰውን ሁለተኛ ብቃት ታሟላ ይሆን?ርብቃ “ጌታዬ፤ ጠጣ” ብላ በዚያ አላበቃችም። “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውሃ እቀዳላቸዋለሁ” አለችው። ከሚጠበቅባት በላይ ለማድረግ ራሷን በፈቃደኝነት አቅርባለች። “ፈጥናም በእንስራው ውስጥ የነበረውን ውሃ በገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ እየሮጠች ከጉድጓዱ ውሃ እያመላለሰች ግመሎቹ እስኪበቃቸው ድረስ አጠጣቻቸው።” ሥራውን የምታከናውነው በከፍተኛ ቅልጥፍና ነበር። ታሪኩ እንደሚለው በዚህ ጊዜ ሁሉ አገልጋዩ “ልጂቱን በአንክሮ ይከታተል ነበር።”—ዘፍጥረት 24:19-21
ኤሊዔዘር ወጣቷ የአብርሃም ዘመድ መሆኗን ሲገነዘብ ተንበርክኮ ይሖዋን አመሰገነ። ከዚያም በአባቷ ቤት ለእርሱና አብረውት ላሉት ሰዎች የሚሆን ማደሪያ ይኖር እንደሆነ ጠየቃት። ርብቃም በቂ ማደሪያ እንዳለ ነገረችውና እንግዳ መምጣቱን ለመንገር ወደ ቤት ሮጠች።—ዘፍጥረት 24:22-28
የርብቃ ወንድም ላባ እና አባቷ ባቱኤል ኤሊዔዘር ያጋጠመውን ሁኔታ ሲሰሙ አምላክ ይመራው እንደነበር አስተዋሉ። ይህም ርብቃ የይስሐቅ ሚስት እንድትሆን መመረጧን የሚያረጋግጥ ነበር። “ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር እንደተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁነው” አሉት። ርብቃስ ምን ተሰምቷት ይሆን? ወዲያውኑ ለመሄድ ፈቃደኛ እንደሆነች ስትጠየቅ በዕብራይስጥ በአንድ ቃል “አዎን፤ እሄዳለሁ” ብላ መለሰች። ርብቃ ይህን የጋብቻ ጥያቄ ለመቀበል የሚያስገድዳት ምንም ነገር አልነበረም። አብርሃም ‘ሴቲቱ አብራው ለመምጣት ፈቃደኛ ካልሆነች’ ከመሃላው ነጻ እንደሚሆን ለኤሊዔዘር ሲነግረው ይህንን ግልጽ አድርጓል። ይሁን እንጂ ርብቃ ራሷ በጉዳዩ የአምላክ እጅ እንዳለበት ተገንዝባ ነበር። ስለሆነም ከዚህ በፊት አይታው የማታውቀውን ሰው ለማግባት ጊዜ ሳታጠፋ ቤተሰቧን ተሰናብታ ጉዞ ጀመረች። ርብቃ የወሰደችው ይህ ድፍረት የሚጠይቅ ውሳኔ እምነት እንዳላት የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በእርግጥም ለይስሐቅ ሚስት እንድትሆን ዘፍጥረት 24:29-59
መመረጧ ተገቢ ነበር።—ርብቃ ከይስሐቅ ጋር ስትገናኝ የራስነት ሥልጣኑን እንደምታከብር ለማሳየት ፊቷን በዓይነ ርግብ ሸፈነች። ይስሐቅ ሚስቱ አድርጎ የወሰዳት ሲሆን በነበሯት ግሩም ባሕርያት የተነሳ በጣም ወደዳት።—ዘፍጥረት 24:62-67
መንትዮቹ ልጆች
ርብቃ ለ19 ዓመታት ያህል ልጆች አልወለደችም። የኋላ ኋላ ግን መንትያ ልጆች ጸነሰች። ልጆቹ በማሕፀኗ ውስጥ እየተጋፉ ስላስቸገሯት አምላክ እንዲረዳት እስከ መጸለይ ደርሳ ነበር። እኛም በሕይወታችን ውስጥ ከባድ ችግር ሲያጋጥመን ወደ ይሖዋ ልንጸልይ እንችላለን። ይሖዋ የርብቃን ጸሎት ሰምቶ ያጽናናት ሲሆን የሁለት ሕዝቦች እናት እንደምትሆንና ‘ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ እንደሚሆን’ ነግሯታል።—ዘፍጥረት 25:20-26
ርብቃ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብን ይበልጥ እንድትወደው ያደረጋት ከላይ ያለውን ስለተባለች ብቻ ላይሆን ይችላል። የልጆቹ ባሕርይ ፈጽሞ የተለያየ ነበር። ያዕቆብ “ጭምት” ሲሆን ዔሳው ግን አምላክ የገባላቸውን ቃል ለመውረስ የሚያስችለውን የብኩርናውን መብት ለያዕቆብ በአንድ ምግብ የሸጠ ለመንፈሳዊ ነገሮች ደንታ የሌለው ሰው ነበር። ዔሳው ሁለት ኬጢያውያን ሴቶች ማግባቱም ለመንፈሳዊ እሴቶች ንቀት እንደነበረው የሚያሳይ ሲሆን ይህ ድርጊቱም ወላጆቹን በጣም ያሳዝናቸው ነበር።—ዘፍጥረት 25:27-34፤ 26:34, 35
ያዕቆብ በረከት እንዲያገኝ የተደረገ ጥረት
ዔሳው ለያዕቆብ መገዛት እንዳለበት ይስሐቅ ያውቅ እንደሆነና እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። የሆነ ሆኖ ርብቃም ሆነች ያዕቆብ በረከቱ የሚገባው ለእርሱ እንደሆነ ያውቁ ነበር። ይስሐቅ እንስሳ አድኖ ምግብ ሠርቶ ካመጣለት እንደሚባርከው ለዔሳው ሲነግረው ርብቃ ስትሰማ ጊዜ ሳታጠፋ አንድ ነገር ለማድረግ ተነሳች። ከወጣትነቷ ጀምሮ የምትታወቅበት ቆራጥነትና ቅንዓት አሁንም አልተለያትም ነበር። ያዕቆብን ሁለት የፍየል ጠቦቶች እንዲያመጣላት ‘አዘዘችው’ [የ1954 ትርጉም]። ባሏ የሚወደውን ምግብ ልታዘጋጅለትና ያዕቆብ በረከቱን ለማግኘት ዔሳውን መስሎ ወደ ይስሐቅ እንዲገባ አስባ ነበር። ያዕቆብ ሐሳቧን ተቃወመ። አባቱ እንዳታለሉት ሲያውቅ እንዳይረግመው ፈርቶ ነበር። ቢሆንም ርብቃ “ልጄ ሆይ፤ የአንተ ርግማን በኔ ላይ ይድረስ፤ ግድ የለህም” በማለት አደፋፈረችው። ከዚያም ምግቡን አዘጋጀችና ያዕቆብን ከዔሳው ጋር አመሳስላ ወደ ባሏ ላከችው።—ዘፍጥረት 27:1-17
ርብቃ እንደዚህ ያደረገችው ለምን እንደሆነ በታሪኩ ላይ አልተጠቀሰም። ብዙዎች በዚህ ድርጊቷ ይኮንኗታል። ሆኖም ይህ ተግባሯ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተወገዘ ከመሆኑም በላይ ይስሐቅም በረከቱን የወሰደው ያዕቆብ መሆኑን ሲያውቅ አልኮነናትም። እንዲያውም ያዕቆብን ጨምሮ ባርኮታል። (ዘፍጥረት 27:29፤ 28:3, 4) ርብቃ ይሖዋ ልጆቿን አስመልክቶ የተናገረውን ታውቃለች። ስለሆነም እንዲህ ያደረገችው ያዕቆብ ለእርሱ የሚገባውን በረከት እንዲያገኝ ብላ ነበር። ይህም ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እንደሆነ አያጠራጥርም።—ሮሜ 9:6-13
ያዕቆብ ወደ ካራን ተላከ
ከዚያም ርብቃ የወንድሙ ቁጣ እስኪበርድ ያዕቆብ ከአካባቢው ዞር እንዲል በማድረግ የዔሳውን እቅድ አጨናገፈችበት። ሐሳቡን ለይስሐቅ ብታማክረውም ዔሳው በወንድሙ ላይ ቂም መያዙን ከማንሳት ተቆጥባለች። ያዕቆብ ከከነዓናውያን ሴቶች ሚስት ያገባል የሚል ስጋት እንዳደረባት አስመስላ ለይስሐቅ በዘዴ ነገረችው። ያዕቆብ ከነዓናዊ ሚስት ሊያገባ ይችላል የሚለው ፍርሃቷ ብቻውን ይስሐቅን ለማሳመን በቂ ነበር። በመሆኑም ይስሐቅ ያዕቆብን ጠርቶ ከከነዓናውያን ሴቶች እንዳያገባ ከነገረው በኋላ ወደ ርብቃ ቤተሰቦች ሄዶ አምላክን የምትፈራ ሴት እንዲፈልግ ላከው። ርብቃና ያዕቆብ ከዚያ በኋላ ዳግመኛ እንደተገናኙ የሚጠቁም ምንም ነገር የለም። ሆኖም የወሰደችው እርምጃ ወደፊት ለሚመሠረተው የእስራኤል ብሔር ትልቅ በረከት አስገኝቷል።—ዘፍጥረት 27:43 እስከ 28:2
እስከ አሁን ስለ ርብቃ የተመለከትነው ሁሉ እንድናደንቃት ያደርገናል። በጣም የተዋበች ሴት ብትሆንም እውነተኛው ውበቷ ግን አምላክን የምትፈራ ሴት መሆኗ ነበር። አብርሃም ምራቱ እንድትሆን የሚፈልገው እንዲህ ዓይነቷን ሴት ነበር። ርብቃ አብርሃም ካሰበው በላይ ሌሎች በርካታ መልካም ባሕርያትም ነበሯት። መለኮታዊ መመሪያ ለመከተል የነበራት እምነትና ድፍረት፣ ቅንዓቷ፣ ልኳን የምታውቅ ሴት መሆኗና ሞቅ ያለ እንግዳ ተቀባይነቷ ሁሉም ክርስቲያን ሴቶች ሊኮርጁት የሚገባ ነው። ይሖዋም ጥሩ ምሳሌ ከምትሆን ሴት የሚፈልገው እነዚህን ባሕርያት ነው።