በሜክሲኮ ለሚኖሩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር
በሜክሲኮ ለሚኖሩ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር
ሐዋርያው ጳውሎስ የጉዞ ባልደረቦቹን በአቴንስ ይጠባበቅ በነበረበት ወቅት አጋጣሚውን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ተጠቅሞበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ዘገባ “በገበያ ስፍራ ዕለት ዕለት ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይነጋገር ነበር” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 17:17) ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ ሲጓዝ በውሃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሴት መደበኛ ባልሆነ መንገድ ምሥራቹን ሰብኳል። (ዮሐንስ 4:3-26) አንተስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ የምታገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ትጠቀማለህ?
በሜክሲኮ የሚገኘው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ መስክ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለሚደረገው ምሥክርነት የተመቸ ነው። ቱሪስቶች የመዝናኛ ቦታዎችን ይጎበኛሉ፣ አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይመጣሉ እንዲሁም ጡረታ የወጡ የውጭ ሀገር ዜጎች የመናፈሻ ቦታዎችንና ምግብ ቤቶችን ያዘወትራሉ። እንግሊዝኛ መናገር የሚችሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ከእነዚህ ሰዎች ጋር ውይይት በመክፈት ረገድ የተዋጣላቸው ሆነዋል። እንዲያውም የውጭ አገር ሰው የሚመስል ወይም እንግሊዝኛ መናገር የሚችል ሰው ካገኙ አጋጣሚውን ለመጠቀም ንቁ ናቸው። እስቲ እንዴት ውይይት እንደሚከፍቱ እንመልከት።
በሜክሲኮ የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች መስክ ውስጥ የሚያገለግሉ ከውጭ አገር የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ እነርሱ ከውጭ የመጣ ሰው ሲያገኙ ብዙውን ጊዜ በቀጥታ ሄደው ይተዋወቁትና ከየት አገር እንደመጣ ይጠይቁታል። አብዛኛውን ጊዜ ግለሰቡ በሜክሲኮ ምን እያደረጉ እንዳለ ምሥክሮቹን መጠየቁ ስለማይቀር ስለ ክርስቲያናዊ እምነታቸው ለመናገር የሚያስችል አጋጣሚ ያገኛሉ። ለምሳሌ ለእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ምሥራቹን የሚሰብኩ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት በዋሃካ የምታገለግለው ግሎሪያ በዚህ ዘዴ ተጠቅሞ ውይይት መክፈት በጣም ቀላል ሆኖ አግኝታዋለች። በከተማው አደባባይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስትመሠክር ቆይታ ወደ ቤቷ ስትመለስ ከእንግሊዝ አገር የመጡ ባልና ሚስት አስቆሟት። ከዚያም ሴትየዋ:- “በዋሃካ አውራ ጎዳናዎች ላይ ጥቁር ሴት ሳይ ዓይኔን ማመን አልቻልኩም” አለቻት። ግሎሪያ በሴትየዋ አባባል ቅር ከመሰኘት ይልቅ ሳቀች። ከዚያም ወደ ሜክሲኮ ለምን እንደመጣች ማውራት ጀመሩ። ሴትየዋ ቡና ለመጠጣት ወደ ቤታቸው እንድትመጣ ግሎሪያን ጋበዘቻት። የሚገናኙበትን ቀን ቀጠሮ ከያዙ በኋላ ግሎሪያ የመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ልትሰጣት ስትል ሴትየዋ በአምላክ መኖር እንደማታምን በመናገር ጽሑፎቹን አልቀበልም አለች። ግሎሪያም በአምላክ መኖር አናምንም ከሚሉ ሰዎች ጋር መነጋገር እንደሚያስደስታት ከጠቀሰችላት በኋላ “የአምልኮ ቦታዎች ያስፈልጉናልን?” በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያላትን አመለካከት ለመስማት እንደምትፈልግ ነገረቻት። ሴትየዋም “ልታሳምኚኝ ከቻልሽ አንድ ትልቅ ነገር አከናውነሻል ማለት ነው” አለቻትና ጽሑፉን ተቀበለቻት። በቀጠሯቸው ቀን ቡና እየጠጡ ረዘም ላለ ሰዓት ተወያዩ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባልና ሚስቱ ወደ እንግሊዝ የሄዱ ሲሆን ከግሎሪያ ጋር በኤሌክትሮኒክ የመልእክት መለዋወጫ መሣሪያ (e-mail) መገናኘታቸውን ቀጥለዋል።
ግሎሪያ የማስተርስ ዲግሪዋን ለማጠናቀቅ የአገሪቱ ተወላጅ ከሆኑ ሴቶች ጋር በዋሃካ በፈቃደኛ ሠራተኛነት ከምትሠራ ሳሮን ከተባለች ከዋሽንግተን ዲሲ የመጣች ተማሪ ጋርም ውይይት ለመክፈት ችላ ነበር። ግሎሪያ ለመልካም ጥረቷ ካመሰገነቻት በኋላ ወደ ሜክሲኮ የመጣችው ለምን እንደሆነ ነገረቻት። ከዚያም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም አምላክ ለድሆች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሰው ዘር ለማድረግ ስላቀደው ነገር ግሩም ውይይት አደረጉ። ሳሮን በዩናይትድ ስቴትስ በነበረችበት ወቅት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ፈጽሞ ተነጋግራ የማታውቅ ሆኖ ሳለ በሜክሲኮ መጀመሪያ ካገኘቻቸው ሰዎች መካከል አንዷ የይሖዋ ምሥክር መሆኗ እንዳስገረማት ተናገረች። መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ የተቀበለች ከመሆኑም በላይ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምራለች።
በርካታ የውጭ አገር ሰዎች የገነትነት ውበት ያለው አካባቢ ፍለጋ በሜክሲኮ የባሕር ዳርቻዎች ወዳሉት መዝናኛዎች ይመጣሉ። ሎረል ይህን ሁኔታ በአካፑልኮ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ውይይት ለመክፈት የተጠቀመችበት ሲሆን አካፑልኮ ከመጡበት አካባቢ ይልቅ የገነትነት ውበት ያለው መሆን አለመሆኑን እንዲሁም በጣም የወደዱት ምኑን እንደሆነ ትጠይቃቸዋለች። ከዚያም በቅርቡ መላው ምድር ገነት እንደሚሆን ትነግራቸዋለች። በአንድ የእንስሳት ሐኪም ቢሮ ውስጥ በዚህ አቀራረብ ተጠቅማ ያነጋገረቻት ካናዳዊት ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራለች። አንተስ በምትኖርበት አካባቢ እንዲህ ዓይነቱ አቀራረብ ውጤታማ ይሆን?
‘በጎዳና ላይ እና በየአደባባዩ’
ብዙውን ጊዜ በጎዳና እና በአደባባይ ላይ “እንግሊዝኛ መናገር ትችላለህ?” ብሎ በመጠየቅ ብቻ ውይይት መክፈት ይቻላል። አብዛኞቹ የሜክሲኮ ተወላጆች በሥራቸው ጠባይ ወይም በዩናይትድ ስቴትስ በመኖራቸው ምክንያት እንግሊዝኛ መናገር የሚችሉ ናቸው።
የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንድ ባልና ሚስት በአንዲት ነርስ በሚገፋ ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ወደ ተቀመጡ አረጋዊት ሴት ቀርበው እንግሊዝኛ መናገር ይችሉ እንደሆነ ጠየቋቸው። ሴትየዋ ለብዙ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ስለኖሩ መናገር እንደሚችሉ መለሱላቸው። ከዚህ በፊት ደርሷቸው የማያውቁትን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ተቀበሉና ስማቸው ኮንስዌሎ እንደሆነ ከነገሯቸው በኋላ አድራሻቸውንም ሰጧቸው። ባልና ሚስቱ ከአራት ቀናት በኋላ በአድራሻው ሲሄዱ ኮንስዌሎ የሚኖሩት በካቶሊክ መነኮሳት በሚተዳደር የአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ እንደሆነ አወቁ። መጀመሪያ ላይ ኮንስዌሎን ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። መነኮሳቱ ስለተጠራጠሩ ኮንስዌሎ ሊያነጋግሯቸው እንደማይችሉ በመንገር ሊመልሷቸው ሞከሩ። ቢሆንም ባልና ሚስቱ ለሰላምታ እንደመጡ ለኮንስዌሎ እንዲነግሩላቸው መነኮሳቱን አጥብቀው ጠየቋቸው። ኮንስዌሎ ባልና ሚስቱ ወደ ቤት እንዲገቡ አደረጉ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የ86 ዓመት ባልቴት የሆኑት እኚህ ሴት ከመነኮሳቱ አፍራሽ አስተያየት ቢሰነዘርባቸውም መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት በማጥናት ላይ ይገኛሉ። በአንዳንድ ስብሰባዎች ላይም ተገኝተዋል።
ምሳሌ 1:20 “ጥበብ በጎዳና ላይ ጮኻ ትጣራለች፤ በየአደባባዩ ድምፅዋን ከፍ ታደርጋለች” ይላል። ይህ በሳን ሚጌል ዴ አየንዴ አደባባይ እንዴት እንደተፈጸመ ተመልከት። አንድ ቀን ማለዳ ራልፍ በአግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረን በመካከለኛው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሰው ቀረበና አነጋገረው። ራልፍ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ሲሰጠው ሰውየው በጣም ስለተገረመ ታሪኩን ነገረው።
ሰውየው በቬትናም የተዋጋ የቀድሞ ወታደር ሲሆን በግዳጅ ላይ በነበረበት ወቅት ብዙ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሲሞቱ ማየቱ ባስከተለበት የስሜት ቀውስ የተነሳ ለአእምሮ መታወክ ተዳርጎ ነበር። በዚህም ምክንያት ከግንባር ወደ ጦር ሰፈሩ ተላከና ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚላክ የወታደሮች
አስከሬን እያጠበ የማዘጋጀት ሥራ ተሰጠው። ይህ ከሆነ 30 ዓመታት ቢያልፉም አሁንም በአስፈሪ ቅዠትና በፍርሃት ስሜት ይሰቃይ ነበር። የዚያን ዕለት ጠዋት በአደባባዩ ላይ ተቀምጦ እርዳታ ለማግኘት ወደ አምላክ እየጸለየ ነበር።ይህ የቀድሞ ወታደር ጽሑፎችን ከመውሰዱም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ እንዲገኝ የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ። በስብሰባ ላይ ከተገኘ በኋላ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ በቆየባቸው ሁለት ሰዓታት ውስጥ በ30 ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ውስጣዊ ሰላም እንዳገኘ ተናግሯል። ይህ ሰው በሳን ሚጌል ዴ አየንዴ የቆየው ለጥቂት ሳምንታት ብቻ ቢሆንም ለበርካታ ጊዜያት መጽሐፍ ቅዱስን ያጠና ሲሆን ወደ መኖሪያ አካባቢው እስኪመለስ ድረስ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቷል። በሄደበት አካባቢም ጥናቱን እንዲቀጥል ዝግጅት ተደርጎለታል።
በሥራ ቦታና በትምህርት ቤት መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር
በሥራ ቦታህ የይሖዋ ምሥክር መሆንህን ታሳውቃለህ? ለእረፍት ለመጡ ሰዎች ቤቶችን የሚያከራየው አድሪያን በሥራ ቦታው የይሖዋ ምሥክር መሆኑን አሳውቆ ነበር። ይህ ያስገኘውን ውጤት የሥራ ባልደረባው ጁዲ ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “የዛሬ ሦስት ዓመት የይሖዋ ምሥክር እንደምሆን ብትነግሩኝ ‘ሞቼ ነው ወይስ በቁሜ!’ እላችሁ ነበር። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ወሰንኩ። ‘ማንበብ ስለምወድ ያን ያህል አይከብደኝም’ ብዬ አስቤ ነበር። ሆኖም ስድስት ገጽ ገደማ እንኳን ሳላነብብ የሚረዳኝ ሰው እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። ወደ አእምሮዬ የመጣው ብቸኛው ሊረዳኝ የሚችል ሰው የሥራ ባልደረባዬ የሆነው አድሪያን ነበር። በመሥሪያ ቤታችን ያለው ጨዋ ሰው እርሱ ብቻ ስለሆነ ከእሱ ጋር ማውራት ያስደስተኛል።” አድሪያን ካቲ ከተባለች እጮኛው ጋር መጥቶ ጥያቄዎቿን በሙሉ እንደሚመልስላት ነገራት። ጁዲ ከካቲ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረች ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆናለች።
በትምህርት ቤትስ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ይቻላል? የስፓንኛ ቋንቋ የሚማሩ ሁለት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አንድ ቀን በትልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከክፍል ቀሩ። በቀጣዩ ክፍለ ጊዜ ከክፍል የቀሩበትን ምክንያት በስፓንኛ ቋንቋ እንዲናገሩ ተጠየቁ። እነርሱም የስፓንኛ ቋንቋ እውቀታቸው በፈቀደላቸው መጠን ምሥክርነቱን ለመስጠት አጋጣሚውን ተጠቀሙበት። ሲልቪያ የምትባለው መምህራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ትንቢቶች ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ነበራት። በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት የተስማማች ሲሆን አሁን የምሥራቹ አስፋፊ ናት። ከቤተሰቧ አባላት ውስጥም ብዙዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ይገኛሉ። ሲልቪያ “ሕይወቴን ሙሉ ስፈልገው የነበረውን ነገር ነው ያገኘሁት” በማለት ተናግራለች። አዎን፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ጥሩ ውጤት ያስገኛል።
ሌሎች አጋጣሚዎችን መጠቀም
እንግዳ ተቀባይ መሆን ምሥክርነቱን ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጥራል። በሳን ካርሎስ፣ ሶናራ የሚኖሩ ጂም እና ጌይል የተባሉ ባልና ሚስት ይህ እውነት መሆኑን ከራሳቸው ተሞክሮ ተገንዝበዋል። ጠዋት በ12:00 ላይ ውሾቻቸውን የሚያንሸራሽሩ አንዲት ሴት በግቢያቸው ውበት ስለተማረኩ ከቤታቸው ፊት ቆመው መመልከት ጀመሩ። ጂም እና ጌይል ወደ ቤት ገብተው ቡና እንዲጠጡ ጋበዟቸው። ከዚያም ስለ ይሖዋና የዘላለም ሕይወት
እንድናገኝ ስላዘጋጀልን ተስፋ ነገሯቸው። ሴትየዋ ስለዚህ ተስፋ የሰሙት በ60 ዓመት ዕድሜያቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል።አድሪንም ከዚህ በፊት የማታውቃቸውን ሰዎች በደግነት ትይዛቸዋለች። በካንኩን በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ እየተመገበች ሳለ አንድ ልጅ ወደ እርሷ ቀረበና የመጣችው ከካናዳ እንደሆነ ጠየቃት። ከካናዳ መምጣትዋን ስትነግረው እሱና እናቱ ስለ ካናዳውያን የትምህርት ቤት ሪፖርት በመጻፍ ላይ የነበረችውን እህቱን ለመርዳት መረጃ እያሰባሰቡ እንደሆነ ነገራት። እንግሊዝኛ መናገር የምትችለው እናቱ አድሪን አጠገብ መጥታ ተቀመጠችና ስለ ካናዳውያን ጥያቄዎች ትጠይቃት ጀመር። አድሪን ጥያቄዎቿን ሁሉ በትዕግሥት መለሰችላት። ከዚያም “ከካናዳ ወደዚህ የመጣሁበት ዋነኛ ምክንያት ግን ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲማሩ ለመርዳት ነው። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መማር ትፈልጊያለሽ?” በማለት ጠየቀቻት። ሴትየዋም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ መሆንዋን ገለጸችላት። ቤተ ክርስቲያኗን ጥላ የወጣችው ከአሥር ዓመታት በፊት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን በራሷ ለማጥናት ጥረት ስታደርግ ነበር። ለአድሪን የስልክ ቁጥሯንና አድራሻዋን የሰጠቻት ሲሆን አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመሩ።
“እንጀራህን በውሃ ላይ ጣል”
በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች መናገር የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት እምብዛም አጋጣሚ ያላገኙ ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰሙ መንገድ ይከፍታል። ሴዋታኔኮ በምትባለው የወደብ ከተማ ሰው በሚበዛበት በአንድ ካፊቴሪያ ውስጥ አንዲት እህት መቀመጫ ያጡ ሁለት የውጭ አገር ሰዎችን አብረዋት እንዲቀመጡ ጋበዘቻቸው። እነዚህ ባልና ሚስት ለሰባት ዓመታት ከቦታ ቦታ በጀልባ ሲዘዋወሩ ነበር። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት እንደሌላቸው ለእህት ነገሯት። በሌላ ጊዜ ይህቺ እህት ባልና ሚስቱን ለመጠየቅ ወደ ጀልባቸው ሄደችና ወደ ቤቷ እንዲመጡ ጋበዘቻቸው። ከ20 የሚበልጡ መጽሔቶችንና 5 ጽሑፎችን የወሰዱ ሲሆን በሚቀጥለው በሚያርፉበት ወደብ የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልገው እንደሚያገኙ ቃል ገብተውላታል።
ጄፍ እና ዴብ የተባሉ የይሖዋ ምሥክሮች በካንኩን በአንድ የገበያ ማዕከል በሚገኝ የምግብ አዳራሽ ውስጥ አንዲት ቆንጅዬ ሕፃን ልጅ የያዙ ሰዎች ተመለከቱ። የምታምር ልጅ እንዳለቻቸው ለሕፃኗ ወላጆች ሲነግሯቸው ወላጆቿ አብረዋቸው ተቀምጠው ፒሳ እንዲበሉ ጋበዟቸው። ቤተሰቡ የመጣው ከሕንድ ሲሆን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሰምተውም ሆነ ጽሑፎቻችንን አይተው አያውቁም ነበር። በመጨረሻ ሲሄዱ በርካታ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ጽሑፎችን ወስደዋል።
ጄፍ በዩካታን የባሕር ጠረፍ አጠገብ በምትገኝ አንዲት ደሴት ላይም ተመሳሳይ ተሞክሮ ያጋጠመው ሲሆን ይህኛው ደግሞ አዲስ ከተጋቡ ቻይናውያን ባልና ሚስት ጋር ነበር። ፎቶ እንዲያነሳቸው ሲጠይቁት ጄፍ በፈቃደኝነት አነሳቸው። ከዚያም ባለፉት 12 ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ቢኖሩም የይሖዋ ምሥክሮችን አይተውም ሆነ ስለ እነርሱ ሲወራ ሰምተው እንደማያውቁ ተረዳ። ደስ የሚል ውይይት ያደረጉ ሲሆን ወደ አገራቸው ሲመለሱ የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልገው እንዲያገኙ ጄፍ አበረታቷቸዋል።
በምትኖርበት አካባቢ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር አጋጣሚ የሚፈጥርልህ ልዩ ክንውን ይኖር ይሆናል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የሜክሲኮ አቻቸውን በእርሻ ቦታቸው ለመጎብኘት ሲመጡ ስለ ሁኔታው ለመዘገብ ከዓለም ዙሪያ በርካታ ሪፖርተሮች ተሰባስበው ነበር። አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ በእንግሊዝኛ ለመስበክ አሰበ። ያገኙት ውጤት አስደሳች ነበር። ለምሳሌ አንድ የዜና ዘጋቢ በኮሶቮና በኩዌት የተደረጉትን ጨምሮ በርካታ ጦርነቶችን የዘገበ ሲሆን አንድ የሥራ ባልደረባው ከታጣቂ በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ያለፈው ዓይኑ እያየ ነበር። ስለ ትንሣኤ ተስፋ ሲሰማ ዓይኖቹ እንባ አቅርረው ሕይወት ዓላማ እንዳለው እንዲያውቅ ስለረዳው አምላክን አመስግኗል። እነዚህን ባልና ሚስት ምሥክሮች ዳግመኛ ባያገኛቸውም ከመጽሐፍ ቅዱስ የነገሩት ምሥራች ምንጊዜም ከአእምሮው እንደማይጠፋ ነግሯቸዋል።
እነዚህ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት በዚህ መንገድ መመሥከር ብዙ ጊዜ ውጤቱ ላይታወቅ ይችላል። ይሁን እንጂ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “እንጀራህን በውሃ ላይ ጣል፤ ከብዙ ቀን በኋላ መልሰህ ታገኘዋለህና” ብሏል። አክሎም “ጠዋት ላይ ዘርህን ዝራ፤ ማታም ላይ እጅህ ሥራ አይፍታ፤ ይህ ወይም ያ፣ ወይም ሁለቱ መልካም ይሁኑ፣ የቱ እንደሚያፈራ አታውቅምና” በማለት ተናግሯል። (መክብብ 11:1, 6) አዎን፣ ጳውሎስና ኢየሱስ እንዲሁም በሜክሲኮ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መስክ ውስጥ የሚያገለግሉት ምሥክሮች እንዳደረጉት አንተም ‘እንጀራህን በብዙ ውሃዎች ላይ ጣል፤’ ‘ዘርህንም አትረፍርፈህ ዝራ።’