በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-

ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች እንደነበሩት የትኛው ማስረጃ ያሳያል?

መጽሐፍ ቅዱስ በማቴዎስ 13:55, 56 እና በማርቆስ 6:3 ላይ ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች እንደነበሩት ይናገራል። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የሚገኘው አዴልፎስ የሚለው የግሪክኛ ቃል “ሥጋዊ ወይም ሕጋዊ ዝምድናን ለማመልከት” የሚሠራበት ሲሆን “በእናትና በአባት ወይም በአንዳቸው በኩል ሥጋዊ ወንድም መሆንን ያመለክታል።” (ዘ ካቶሊክ ቢብሊካል ኳርተርሊ፣ ጥር 1992)—12/15, ገጽ 3

በጊዜያችን የምንመለከተው የትኛውን አዲስ የጦርነት ገጽታ ነው? ለዚህስ ዋነኛ መንስዔ የሆነው ምንድን ነው?

በቅርብ ዓመታት የሰው ዘርን ክፉኛ እያሰቃዩ ያሉት የአንድ አገር ዜጎች በሆኑ ተቃራኒ አንጃዎች መካከል የሚካሄዱ የእርስ በርስ ጦርነቶች ናቸው። የዘርና የጎሳ ጥላቻ፣ የሃይማኖት ልዩነት፣ የፍትሕ መዛባትና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በዋነኝነት የሚጠቀሱ መንስዔዎች ናቸው። ሌላው መንስዔ ደግሞ ለሥልጣንና ለገንዘብ መስገብገብ ነው።—1/1, ገጽ 3-4

ኢየሱስ የናሙና ጸሎቱን ያስተማረው ክርስቲያኖች ቃል በቃል እንዲደግሙት አስቦ እንዳልነበር እንዴት ማወቅ እንችላለን?

ኢየሱስ የናሙና ጸሎቱን ያስተማረው በተራራ ስብከቱ ላይ ነበር። ከ18 ወራት ገደማ በኋላ የጸሎቱን ዋና ዋና ነጥቦች በድጋሚ ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:9-13፤ ሉቃስ 11:1-4) በዚህ ወቅት ኢየሱስ ጸሎቱን ቃል በቃል አለመድገሙ ክርስቲያኖች በቃላቸው አጥንተውት ሙሉ በሙሉ እንዲደግሙት አስቦ እንዳልነበር ያሳያል።—2/1, ገጽ 8

ከጥፋት ውኃ በኋላ ኖኅ የላካት ርግብ ወደ መርከቡ ይዛው የመጣችውን የወይራ ቅጠል ያገኘችው ከየት ነበር?

የጥፋት ውኃው የነበረውን የጨው ይዘትም ሆነ የሙቀት መጠን ማወቅ አንችልም። ይሁን እንጂ የወይራ ዛፍ ከተቆረጠም በኋላ ዳግመኛ ሊያቆጠቁጥ እንደሚችል ይታወቃል። በመሆኑም አንዳንድ ዛፎች ከጥፋት ውኃው ተርፈው እንደገና አቆጥቁጠው ሊሆን ይችላል።—2/15, ገጽ 31

በናይጄሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ቢያፍራ በወታደሮች ተከብባ በነበረበት ጊዜ በአካባቢው የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች መንፈሳዊ ምግብ ያገኙት እንዴት ነው?

ሁለት የመንግሥት ሠራተኞች አንደኛው በአውሮፓ ሌላው ደግሞ ቢያፍራ በሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ተሰጣቸው። እነዚህ ሁለት ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። እነዚህ ሁለት ምሥክሮች ከባድ ችግር ሊያስከትልባቸው የሚችል ቢሆንም እንኳ ወደ ቢያፍራ መንፈሳዊ ምግብ ለማስገባት ፈቃደኞች በመሆን ጦርነቱ በ1970 እስካበቃበት ጊዜ ድረስ በዚህ ወሳኝ ዝግጅት አማካኝነት ወንድሞችን ሲረዱ ቆይተዋል።—3/1, ገጽ 27

የዌስትፋሊያ የሰላም ስምምነት ምን ውጤት አስገኝቷል? ሃይማኖት ለጦርነቱ ምክንያት የሆነው እንዴት ነበር?

በሃይማኖታዊ ተሃድሶው የተነሳ የቅዱስ ሮማ ግዛት ካቶሊክ፣ ሉተራንና ካልቪኒስት ተብሎ ለሦስት ተከፈለ። በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የፕሮቴስታንት ኅብረትና የካቶሊክ ማኅበር ተመሠረተ። ከዚያም በቦሔሚያ ሃይማኖታዊ ግጭት ተቀሰቀሰና ቀስ በቀስ እየሰፋ ሄዶ ዓለም አቀፋዊ የበላይነትን ለማግኘት የሚደረግ ትግል ሆነ። የካቶሊክና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆኑ መሪዎች የፖለቲካ የበላይነትና የንግድ ጥቅም ለማግኘት መሽቀዳደም ጀመሩ። በመጨረሻም በጀርመን፣ የዌስትፋሊያ አውራጃ የሰላም ድርድር ተጀመረ። ከአምስት ዓመታት በኋላ በ1648 የዌስትፋሊያ የሰላም ስምምነት የተፈረመ ሲሆን ይህም የሠላሳው ዓመት ጦርነት ማብቃቱንና ሉዓላዊ መንግሥታትን የያዘችው ዘመናዊ አውሮፓ መመሥረቷን ያበሰረ ነበር።—3/15, ገጽ 20-3

“የአውሬው” ምልክት ወይም ስም የሆነው የ666 ትርጉም ምንድን ነው?

ይህ ምልክት የተጠቀሰው በራእይ 13:16-18 ላይ ነው። አውሬው ሰብዓዊ አገዛዝን የሚያመለክት ሲሆን “የሰው ቁጥር” ያለው መሆኑ መንግሥታት ሰው የሚገኝበትን የረከሰ ሁኔታ እንደሚያንጸባርቁ ያሳያል። ቁጥሩ 6 ሲደመር 60 ሲደመር 600 መሆኑ አውሬው በአምላክ ዓይን ጉድለት ወይም እንከን ያለበትን ነገር እንደሚያመለክት ያሳያል። ምልክቱ ያለባቸው ሰዎች ለፖለቲካው ተቋም ከአምልኮ የማይተናነስ ድጋፍ ይሰጣሉ፤ ወይም መዳን ያስገኝልናል ብለው ይተማመኑበታል።—4/1, ገጽ 4-7