በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ሲፈጸም

የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ሲፈጸም

የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ሲፈጸም

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፤ እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት ያስተማራቸው ከአባቱ ጋር በሰማይ ሲኖር ካካበተው ተሞክሮ በመነሳት ነበር። (ማቴዎስ 6:10፤ ዮሐንስ 1:18፤ 3:13፤ 8:42) ሰው ከመሆኑ በፊት ባሳለፈው ሕይወት በሰማይም ሆነ በምድር ማንኛውም ነገር ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ይፈጸም በነበረበት ዘመን ኖሯል። እነዚያ ጊዜያት ሁሉም ነገር በተሳካ ሁኔታ የሚፈጸምባቸው የደስታ ጊዜያት ነበሩ።—ምሳሌ 8:27-31

አምላክ በመጀመሪያ የፈጠረው መንፈሳዊ ፍጥረታትን ማለትም ‘ለቃሉ የሚታዘዙትን ኀያላን መላእክቱን’ ነበር። እነዚህ መላእክት ድሮም ሆነ አሁን ‘ፈቃዱን የሚፈጽሙ አገልጋዮቹ’ ናቸው። (መዝሙር 103:20, 21) እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ፈቃድ አላቸው? አዎን፣ ለዚህም ነው ምድር ስትመሠረት እነዚህ ‘መላእክት እልል’ ያሉት። (ኢዮብ 38:7) ይህ እልልታቸው በአምላክ ፈቃድ መደሰታቸውንና በዓላማው መስማማታቸውን ያሳያል።

አምላክ ምድርን ከፈጠረና ለሰው ልጅ መኖሪያ እንድትሆን ካዘጋጃት በኋላ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ፈጠረ። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 1) ይህስ ውዳሴ የሚገባው ነበር? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ” ይላል። አዎን፣ እንከን የለሽ ፍጹም ሥራ ነበር።—ዘፍጥረት 1:31

አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችንና ለዘሮቻቸው ምን ዓላማ ነበረው? አምላክ ለእነርሱ በጣም ጥሩ ዓላማ እንደነበረው ዘፍጥረት 1:28 እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “እግዚአብሔርም፣ ‘ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው’ ብሎ ባረካቸው።” የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችንም ሆኑ ከእነርሱ የሚወለዱት ልጆች ይህንን አስደሳች ኃላፊነት ለመወጣት ለዘላለም መኖር ነበረባቸው። አሳዛኝ አደጋ፣ የፍትሕ መጓደል፣ ሐዘን ወይም ሞት እንደሚያጋጥማቸው የሚጠቁም ምንም ነገር አልነበረም።

በዚህ ወቅት የአምላክ ፈቃድ በሰማይም ሆነ በምድር ይፈጸም ነበር። ከፈቃዱ ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሁሉ ከፍተኛ ደስታ ያገኙ ነበር። ታዲያ ምን ችግር ተፈጠረ?

በአምላክ ፈቃድ ላይ ያልተጠበቀ ተቃውሞ ተነሳ። እርግጥ ይህ ተቃውሞ መፍትሔ የሌለው አልነበረም። ቢሆንም አምላክ የሰው ዘርን በሚመለከት ስላለው ዓላማ ብዙ ውዝግብ የሚያስነሳ ለዘመናት የዘለቀ ስቃይና መከራ አስከትሏል። ሁላችንም ብንሆን የዚህ መከራና ስቃይ ሰለባ ነን። ይሁን እንጂ ተቃውሞው ምን ነበር?

በዓመፁ ወቅት የአምላክ ፈቃድ ምን ነበር?

ከአምላክ መንፈሳዊ ልጆች አንዱ አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ፈቃድ በማሰናከል የራሱን ጥቅም ለማራመድ የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ተመለከተ። ይህ መንፈሳዊ ፍጡር ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ባወጣና ባወረደ መጠን ሐሳቡን እየወደደውና ሊሳካ እንደሚችል እየታየው ሄደ። (ያዕቆብ 1:14, 15) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አምላክን ችላ ብለው እርሱን እንዲያዳምጡት ማድረግ ከቻለ አምላክ አማራጭ ስለማይኖረው ለእርሱ ሉዓላዊ አገዛዝ እውቅና ለመስጠት ይገደዳል ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። አምላክ እርምጃ ቢወስድባቸው ዓላማው እንደከሸፈ ስለሚያሳይ በሕይወት እንደሚተዋቸው አስቦ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እነርሱን ከማጥፋት ይልቅ ሰብዓዊ ፍጥረታቱ ለሚታዘዙለት መንፈሳዊ ልጁ ሥልጣን እውቅና በመስጠት በዓላማው ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ይገደዳል። በእርግጥም ይህ ዓመጸኛ መልአክ ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ማለትም ተቃዋሚ ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው።—ኢዮብ 1:6

ሰይጣን ይህን ሕልሙን እውን ለማድረግ ሔዋንን ቀርቦ አነጋገራት። ‘መሞት እንኳን አትሞቱም፤ መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ’ በማለት የአምላክን ፈቃድ ችላ ብላ ራሷን በራሷ እንድትመራ አግባባት። (ዘፍጥረት 3:1-5) ሔዋን ሰይጣን ያቀረበላት ሐሳብ ነጻነት የሚያቀዳጃት የመሰላት ሲሆን ሕይወቷን በተሻለ መንገድ ለመምራት የሚያስችል አማራጭ ሆኖ ታያት። ከዚያም ባሏን እንዲተባበራት አሳመነችው።—ዘፍጥረት 3:6

ይህ የአዳምና የሔዋን ፈቃድ እንጂ የአምላክ ፈቃድ አልነበረም። እናም የከፋ መዘዝ ማስከተሉ አልቀረም። መጀመሪያውኑም ቢሆን አምላክ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ሞት እንደሚያስከትልባቸው ነግሯቸው ነበር። (ዘፍጥረት 3:3) አዳምና ሔዋን ከአምላክ አመራር ውጪ በተሳካ ሁኔታ እንዲኖሩ ተደርገው አልተፈጠሩም። (ኤርምያስ 10:23) በተጨማሪም ፍጽምናቸውን የሚያጡ ሲሆን ለልጆቻቸውም አለፍጽምናንና ሞትን ያስተላልፋሉ። (ሮሜ 5:12) ሰይጣን እነዚህን ሁሉ መጥፎ ውጤቶች ሊያስቀር አይችልም።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች አምላክ ለሰው ዘርና ለምድር የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ወይም ፈቃድ አስለውጠውታል? በፍጹም። (ኢሳይያስ 55:9-11) ሆኖም የሚከተሉትን መልስ የሚያሻቸው ወሳኝ ጥያቄዎች አስነስተዋል:- የሰው ልጅ ሰይጣን እንዳለው ‘መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ መሆን’ ይችላል? በሌላ አባባል በቂ ጊዜ ቢሰጠን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ትክክልና ስህተት እንዲሁም ጠቃሚና ጎጂ የሆነውን በራሳችን መለየት እንችላለን? አምላክ የሚገዛበት መንገድ ከሁሉም የተሻለ ከመሆኑ አኳያ ሙሉ በሙሉ ልንታዘዝለት ይገባል? ከፈቃዱ ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምተን መኖርስ ይኖርብናል? እነዚህን ጥያቄዎች ምን ብለህ ትመልሳለህ?

የማሰብ ችሎታ ባላቸው ፍጥረታት ሁሉ ፊት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያለው አማራጭ አንድ ብቻ ነው። ይኸውም ራሳቸውን በራሳቸው ለመምራት ለፈለጉት ሰዎች ነጻነት ሰጥቶ ይሳካላቸው እንደሆነና እንዳልሆነ እንዲታይ ማድረግ ነው። እነርሱን ማጥፋቱ ለተነሳው ጥያቄ መልስ አያስገኝም። የሰው ልጅ ለተወሰነ ጊዜ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር መፍቀድ ውጤቱ በግልጽ እንዲታይ ስለሚያደርግ ለጥያቄው መልስ ማስገኘት ይችላል። አምላክ ልጆች እንደምትወልድ ለሴቲቱ በነገራት ጊዜ ጉዳዩን በዚህ መልክ ሊፈታው እንዳሰበ ጠቁሟል። በዚህም ምክንያት ሰብዓዊው ቤተሰብ ሊኖር ችሏል። አምላክ ይህን ዓይነት ውሳኔ በማድረጉ እኛም በሕይወት ለመትረፍ ችለናል።—ዘፍጥረት 3:16, 20

እንዲህ ሲባል ግን አምላክ የሰው ልጆችንና ዓመጸኛውን መልአክ እንዳሻቸው እንዲሆኑ ፈቅዶላቸዋል ማለት አይደለም። አምላክ ሉዓላዊነቱን አሳልፎ አልሰጠም፤ ዓላማውንም ፈጽሞ አልተወውም። (መዝሙር 83:18) የዓመጹ ጠንሳሽ ከጊዜ በኋላ እንደሚቀጠቀጥና ዓመጹ ያስከተለው መጥፎ ውጤት ሙሉ በሙሉ እንደሚስተካከል አስቀድሞ ሲናገር ይህን ግልጽ አድርጓል። (ዘፍጥረት 3:15) ስለዚህ ገና ከጅምሩ ሰብዓዊው ቤተሰብ ከመከራ እፎይ የሚልበት ጊዜ እንደሚመጣ ቃል ተገብቶለት ነበር።

እስከዚያው ድረስ ግን የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችንም ሆኑ ወደፊት የሚወለዱት ልጆቻቸው ከአምላክ አገዛዝ ርቀዋል። አምላክ ውሳኔያቸው የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት በሙሉ ለማስቀረት ከፈለገ በእያንዳንዱ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ፈቃዱን እንዲፈጽሙ ማስገደድ ይሆንበታል። ይህ ደግሞ ራሳቸውን በራሳቸው መምራት ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ አያስችልም።

እርግጥ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ የአምላክን አገዛዝ ሊመርጡ ይችላሉ። በጊዜያችን አምላክ ለሰዎች ያለውን ፈቃድ ተምረው ከዚያ ጋር ተስማምተው ለመኖር የተቻላቸውን ያህል ጥረት ማድረግ ይችላሉ። (መዝሙር 143:10) ሆኖም የሰው ልጅ ራሱን በራሱ የመምራቱ ጉዳይ እልባት እስካላገኘ ድረስ ከችግሮች ሊያመልጡ አይችሉም።

ሰዎች የራሳቸውን ምርጫ ማድረጋቸው የሚያስከትለው ውጤት የታየው ገና ከጅምሩ ነበር። የሰብዓዊው ቤተሰብ የበኩር ልጅ የነበረው ቃየን “የእርሱ ሥራ ክፉ፣ የወንድሙ ግን ጽድቅ ስለነበረ” ወንድሙን አቤልን ገደለው። (1 ዮሐንስ 3:12) አምላክ መጀመሪያውኑ ድርጊቱን እንዳይፈጽም ቃየንን ማስጠንቀቁና በኋላም መቅጣቱ የአቤል መሞት የእርሱ ፈቃድ እንዳልነበር ያሳያል። (ዘፍጥረት 4:3-12) ቃየን ሰይጣን ያመነጨውን ራስን በራስ የመምራት ሐሳብ ለመከተል የመረጠ ሲሆን በዚህም “የክፉው ወገን” መሆኑን አሳይቷል። ሌሎችም ቢሆን ያደረጉት ነገር ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው።

የሰው ልጅ በምድር ላይ መኖር ከጀመረ ከ1,500 ዓመታት በኋላ “ምድር በእግዚአብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች፤ በዐመፅም ተሞላች።” (ዘፍጥረት 6:11) ምድር እንዳትበላሽ ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልግ ነበር። አምላክ ዓለም አቀፋዊ የውኃ ጥፋት በማምጣት ክፉዎችን ያጠፋ ሲሆን ጻድቅ የነበረው አንድ ቤተሰብ ማለትም ኖኅና ሚስቱ እንዲሁም ልጆቹና ሚስቶቻቸው በሕይወት እንዲተርፉ አድርጓል። (ዘፍጥረት 7:1) ሁላችንም የእነርሱ ልጆች ነን።

ከዚያ ወዲህ ባለው የሰው ልጆች ታሪክ አምላክ ፈቃዱን ለማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ መመሪያ ሲሰጥ ቆይቷል። የእርሱን መመሪያ ለማግኘት ለሚሹ ሁሉ እንዲሆን ታማኝ የሆኑ ሰዎችን በመንፈሱ አነሳስቶ ቃሉን እንዲጽፉ አድርጓል። ይህ ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በፍቅር ተነሳስቶ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከእርሱ ጋር ዝምድና እንዲመሠርቱ አልፎ ተርፎም ወዳጆቹ እንዲሆኑ ፈቅዶላቸዋል። (ኢሳይያስ 41:8) እንዲሁም የሰው ልጆች ከአምላክ ተለይተው ባሳለፏቸው በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ከባድ መከራዎች ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ኃይል ይሰጣቸዋል። (መዝሙር 46:1፤ ፊልጵስዩስ 4:13) ለዚህ ሁሉ ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል!

የአምላክ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል

አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ፈቃድ እስካሁን ባከናወናቸው ነገሮች ብቻ የተወሰነ አይደለም። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጴጥሮስ “እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን” በማለት ተናግሯል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ ምሳሌያዊ አባባል አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ እንደሚመሠረትና በዚህ ኅብረተሰብ ላይ የሚገዛ አዲስ መንግሥት እንደሚቋቋም ያመለክታል።

ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ በማለት በማያሻማ አነጋገር ጽፏል:- “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስ . . . መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (ዳንኤል 2:44) ይህ ትንቢት በጊዜያችን ያለው ሊስተካከል የማይችል ሥርዓት እንደሚያበቃለትና በአምላክ መንግሥት እንደሚተካ ያሳያል። ይህ ምንኛ የሚያስደስት ዜና ነው! በጊዜያችን ያለው ዓለም በዓመጽ እንዲሞላ ያደረጉትና የምድራችንን ህልውና ዳግመኛ ስጋት ላይ የጣሉት ጦርነቶችና የራስ ወዳድነት ድርጊቶች ወደፊት የተረሱ ይሆናሉ።

እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት:- “የምትለው ሁሉ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና [“የመገኘትህና፣ NW] የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” በማለት ለኢየሱስ ጥያቄ አቅርበውለት ነበር። ኢየሱስ ከሰጣቸው መልሶች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል:- “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:3, 14

ይህ የስብከት ሥራ በምድር ዙሪያ እየተከናወነ እንዳለ ዓለም የሚያውቀው ነው። አንተም በምትኖርበት አካባቢ ይህ ሥራ ሲከናወን ሳትመለከት አትቀርም። ቻርልስ ሳሙኤል ብራደን የተባሉ ፕሮፌሰር ዚስ ኦልሶ ብሊቭ (እነዚህም ያምናሉ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ምሥክርነት በመስጠት ሥራቸው መላውን ምድር ቃል በቃል አዳርሰዋል። የመንግሥቱን ምሥራች በማሰራጨት ረገድ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚያክል ቅንዓትና ጽናት ያሳየ አንድም ሃይማኖታዊ ቡድን የለም።” የይሖዋ ምሥክሮች ከ230 በሚበልጡ አገሮች ወደ 400 በሚጠጉ ቋንቋዎች ምሥራቹን በትጋት በማወጅ ላይ ናቸው። አስቀድሞ በትንቢት የተነገረለት ይህ ሥራ ዓለም አቀፋዊ በሆነ መልኩ የአሁኑን ያህል ተከናውኖ አያውቅም። የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን የሚያስወግድበት ጊዜ እንደቀረበ ከሚጠቁሙት በርካታ ማስረጃዎች መካከል አንዱ ይህ ነው።

ኢየሱስ በጊዜያችን እንደሚሰበክ የተናገረው መንግሥት በናሙና ጸሎቱ ላይ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለን እንድንጸልይለት ያስተማረን መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:10) አዎን፣ አምላክ ለሰው ዘርና ለምድር ያለውን ዓላማና ፈቃድ ለማስፈጸም የሚጠቀመው በዚህ መንግሥት ነው።

እንዲህ ስንል ምን ማለታችን ነው? መልሱን በራእይ 21:3ና 4 ላይ እናገኛለን:- “ደግሞም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ ‘እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።’” ከዚያ በኋላ የአምላክ ፈቃድ በሰማይም ሆነ በምድር በተሟላ ሁኔታ ይፈጸማል። a አንተስ ከዚህ በረከት ተካፋይ ለመሆን አትፈልግም?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስለ አምላክ መንግሥት ይበልጥ ለማወቅ ከፈለግክ በአቅራቢያህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልገህ አግኝ ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 2 ላይ ከተዘረዘሩት አድራሻዎች በአንዱ ጻፍ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአምላክ ፈቃድ ውጭ ራስን በራስ ለመምራት መሞከር አሳዛኝ መከራ አስከትሏል