የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እየሆነ ነውን?
የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እየሆነ ነውን?
“ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፤ እንዲሁ በምድር ትሁን።”—ማቴዎስ 6:10
ሁልዮ እና ክርስቲና ዓይናቸው እያየ አራቱ ልጆቻቸው በሚሰቀጥጥ ሁኔታ በእሳት ተቃጥለው ሞቱ። መንገድ ዳር ያቆሙት መኪናቸው ሰክሮ ሲያሽከረክር በነበረ ሹፌር ተገጭቶ በእሳት እየጋየ ነበር። አምስተኛ ልጃቸው ማርቆስ ከአደጋው በሕይወት የተረፈ ቢሆንም ሰውነቱ ክፉኛ በእሳት በመለብለቡ ገጽታው ሊስተካከል በማይችል ሁኔታ ተበላሽቷል። ይህ አደጋ ሲደርስበት ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበር። በከባድ ሐዘን የተደቆሰው አባቱ “መልካምም ሆነ መጥፎ፣ ማንኛውም ነገር ቢደርስብን የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል” በማለት ራሱንና ቤተሰቡን አጽናና።
ብዙዎች እንዲህ ያለውን አሳዛኝ አደጋ በተመለከተ የሚኖራቸው አስተሳሰብ ከሁልዮ የተለየ አይደለም። ‘አምላክ ሁሉን ቻይና ለእያንዳንዳችን የሚያስብልን ከሆነ እንዴት እንደሆነ ባይገባንም እንኳን የደረሰብን መከራ በሆነ መንገድ የሚጠቅመን መሆን አለበት’ ብለው ያስባሉ። አንተስ በዚህ ሐሳብ ትስማማለህ?
ጥሩም ይሁን መጥፎ ማንኛውም ነገር በሰዎች ላይ የሚደርሰው በአምላክ ፈቃድ ነው የሚለው አመለካከት በአብዛኛው የተመሠረተው ‘አቡነ ዘበሰማያት’ ተብሎ በሚጠራው የጌታ ጸሎት ውስጥ በሚገኙት ከላይ በተጠቀሱት ቃላት ነው። አንዳንድ ሰዎች ‘የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እየተፈጸመ እስከሆነ ድረስ “ፈቃድህ በምድር ላይ ትሁን” ብለን ስንጸልይ በምድር ላይ የሚፈጸመው ሁሉ የእርሱ ፈቃድ ነው እያልን ነው’ ብለው ይከራከራሉ።
ብዙዎች በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። ለእነርሱ እንዲህ ያለው አመለካከት አምላክን ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ ስሜት ግድ የሌለው ያስመስለዋል። ‘አፍቃሪ የሆነ አምላክ በንጹሐን ሰዎች ላይ አሰቃቂ የሆነ ነገር እንዲደርስ እንዴት ሊፈቅድ ይችላል? ሊያስተምረን የሚፈልገው ነገር ቢኖር እንኳን በዚህ መንገድ ምን ሊያስተምረን ይችላል?’ ብለው ይጠይቃሉ። ምናልባት አንተም እንደዚህ ይሰማህ ይሆናል።
የኢየሱስ ወንድም የነበረው ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ይህን በሚመለከት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ማንም ሲፈተን፣ ‘እግዚአብሔር ፈተነኝ’ አይበል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) ክፋትን የሚያመጣው አምላክ አይደለም። ስለሆነም በጊዜያችን በምድር ላይ ከሚከሰቱት ነገሮች መካከል የአምላክ ፈቃድ የሆኑት ሁሉም እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወንድ ፈቃድ፣ ስለ አሕዛብ ፈቃድ አልፎ ተርፎም ስለ ዲያብሎስ ፈቃድ ይናገራል። (ዮሐንስ 1:13፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:26፤ 1 ጴጥሮስ 4:3 የ1954 ትርጉም) በሁልዮና በክርስቲና ቤተሰብ ላይ የደረሰው አሳዛኝ ሁኔታ በሰማይ የሚኖረው የአፍቃሪው አባት ፈቃድ ሊሆን አይችልም ቢባል አትስማማም?
ታዲያ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ‘ፈቃድህ በምድር ይሁን’ ብለው እንዲጸልዩ ሲያስተምራቸው ምን ማለቱ ነበር? እንዲያው አምላክ በአንዳንድ ጉዳዮች ጣልቃ እንዲገባ የቀረበ ልመና ነው ወይስ ሁላችንም በተስፋ የምንጠብቀውን የተሻለና የላቀ ለውጥ እንዲመጣ እንድንጸልይ እያስተማረን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚል እስቲ እንመርምር።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
መኪና:- Dominique Faget-STF/AFP/Getty Images; ሕፃን:- FAO photo/B. Imevbore