በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥላቻ በነገሠበት ዓለም ደግነት ለማሳየት መጣር

ጥላቻ በነገሠበት ዓለም ደግነት ለማሳየት መጣር

ጥላቻ በነገሠበት ዓለም ደግነት ለማሳየት መጣር

“ሰው የሚመኘው ጽኑ ፍቅር [“ፍቅራዊ ደግነት፣” Nw] ነው።”—ምሳሌ 19:22

1. ደግነት ማሳየት አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው?

 ደግ እንደሆንክ ይሰማሃል? እንደዚያ የሚሰማህ ከሆነ በዚህ ዓለም ውስጥ መኖር አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል። እርግጥ ነው፣ ደግነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ከመንፈስ ፍሬዎች’ አንዱ እንደሆነ ተገልጿል። ሆኖም ክርስቲያን ነን በሚሉ አገሮች ውስጥ እንኳን ደግነትን ማሳየት ይህን ያህል ከባድ የሆነው ለምንድን ነው? (ገላትያ 5:22 NW) ቀደም ሲል በነበረው ርዕስ ውስጥ እንደተገለጸው ሐዋርያው ዮሐንስ መላው ዓለም በክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ማለትም በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ የጻፈው ሐሳብ የዚህን ጥያቄ መልስ በከፊል ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 5:19) ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” ሲል ጠርቶታል። (ዮሐንስ 14:30) በመሆኑም ይህ ዓለም በጭካኔ ባሕርይው የሚታወቀውን ዓመጸኛ ገዥውን የመምሰል ዝንባሌ አለው።—ኤፌሶን 2:2

2. ደግነት እንዳናሳይ እንቅፋት ሊሆኑብን የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

2 ሌሎች ሰዎች ማለትም ጎረቤቶቻችን፣ የማናውቃቸው ሰዎች አልፎ ተርፎም ወዳጆቻችንና የቤተሰብ አባሎቻችን የሚፈጽሙብን ደግነት የጎደለው ድርጊት ሕይወታችንን በእጅጉ ይነካዋል። ተገቢ ያልሆነ ነገር ከሚፈጽሙ፣ እርስ በርሳቸው ከሚጯጯኹና ከሚሰዳደቡ ሰዎች ጋር አብሮ መዋል የሚያስከትለው ውጥረት እንድናዝን ሊያደርገን ይችላል። እንዲህ ያለው ደግነት የጎደለው ተግባር እኛም የጥላቻ መንፈስ እንዲያድርብን በማድረግ ክፉውን በክፉ እንድንመልስ ያነሳሳን ይሆናል። ይህ ደግሞ በመንፈሳዊና በአካላዊ ጤንነታችን ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል።—ሮሜ 12:17

3. ሰዎች ደግነት ለማሳየት ያላቸውን ፍላጎት ፈታኝ የሚያደርጉባቸው ምን ችግሮች ያጋጥሟቸዋል?

3 በዓለም ላይ የሚታዩ አስጨናቂ ሁኔታዎችም እንዲሁ ደግነት ለማሳየት የምናደርገውን ጥረት አስቸጋሪ ሊያደርጉብን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አሸባሪዎች የሚሰነዝሯቸው ጥቃቶችና ማስፈራሪያዎች እንዲሁም የተለያዩ ቡድኖች ባዮሎጂያዊ ወይም የኑክሌር መሣሪያዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ የሚለው ስጋት የሰውን ልጅ ሕይወት ውጥረት የነገሠበት አድርጎታል። በተጨማሪም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቂ ምግብ፣ መጠለያ፣ ልብስና ሕክምና ስለማያገኙ ለድህነት ተዳርገዋል። ሁኔታዎች ተስፋ የሌላቸው በሚመስሉበት ጊዜ ደግነት ማሳየት ተፈታታኝ ይሆናል።—መክብብ 7:7 የ1954 ትርጉም

4. አንዳንዶች ለሌሎች ደግነት ማሳየትን በሚመለከት ምን የተሳሳተ አመለካከት ሊያድርባቸው ይችላል?

4 አንድ ሰው ደግነት ማሳየት ይህን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንዳልሆነ እንዲያውም የድክመት ምልክት እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። በተለይ ደግሞ ሌሎች ስለ ስሜቱ ሳይጨነቁ የሚያደርጉት ነገር እንደተበደለ እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል። (መዝሙር 73:2-9) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “የለዘበ መልስ ቁጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቁጣን ይጭራል” የሚል ተገቢ መመሪያ ይዞልናል። (ምሳሌ 15:1) ደግነትና ገርነት (ልዝብ መሆን) እርስ በርስ ተዛማጅነት ያላቸው የመንፈስ ፍሬዎች ሲሆኑ አስቸጋሪ ወይም ፈታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ በእጅጉ ይረዱናል።

5. ደግነት ማሳየት አስፈላጊ የሆነባቸው አንዳንድ የሕይወት ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?

5 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የመንፈስ ፍሬዎችን ማፍራታችን አስፈላጊ ነው፤ በመሆኑም ከእነዚህ መካከል አንዱን ባሕርይ ይኸውም ደግነትን እንዴት ማሳየት እንደምንችል መመርመራችን ተገቢ ነው። ጥላቻ በነገሠበት በዚህ ዓለም ውስጥ ደግነት ማሳየት ይቻላል? የሚቻል ከሆነስ በተለይ አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የሰይጣንን ተጽዕኖ ተቋቁመን ደግነት ማንጸባረቅ እንደምንችል የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? በቤተሰብ ውስጥ፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በአገልግሎት ላይ፣ ለጎረቤቶቻችን እንዲሁም ለእምነት ባልንጀሮቻችን እንዴት ደግነት ማሳየት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።

በቤተሰብ ውስጥ ደግነት ማሳየት

6. በቤተሰብ ውስጥ ደግነት ማሳየት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዴትስ ማሳየት ይቻላል?

6 የይሖዋን በረከትና አመራር ለማግኘት የመንፈስ ፍሬዎችን ሙሉ በሙሉ ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ኤፌሶን 4:32 NW) የቤተሰብ አባላት እርስ በርሳቸው ደግነት ማሳየት የሚችሉባቸውን መንገዶች እስቲ እንመልከት። ባልና ሚስት በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ እርስ በርሳቸው እንዲሁም ከልጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ደግነትና አሳቢነት ማሳየት ይኖርባቸዋል። (ኤፌሶን 5:28-33፤ 6:1, 2) የቤተሰብ አባላት እርስ በርስ የሚነጋገሩበት መንገድ እንዲህ ያለውን ደግነት የሚያንጸባርቅ መሆን ያለበት ሲሆን ልጆች ወላጆቻቸውን ማክበር፣ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን በተገቢው ሁኔታ መያዝ ይኖርባቸዋል። ሁሉም ለማመስገን የፈጠኑ፣ ለመኮነን ግን የዘገዩ መሆን ይገባቸዋል።

7, 8. (ሀ) በቤተሰብ ውስጥ ደግነት ለማሳየት የምንፈልግ ከሆነ ምን ዓይነት ባሕርያትን ማስወገድ ይኖርብናል? (ለ) ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለጠንካራ የቤተሰብ ትስስር አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው? (ሐ) በቤተሰብህ ውስጥ ደግነት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

7 ለቤተሰባችን አባላት ደግነት ማሳየት ሐዋርያው ጳውሎስ “ቁጣን፣ ንዴትን፣ ስድብን፣ ሐሜትንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ” በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ መከተልን ይጨምራል። ክርስቲያን ቤተሰቦች ምንጊዜም አክብሮት ባለው መንገድ መነጋገር ይኖርባቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለጠንካራና ሰላም ለሰፈነበት ቤተሰብ ወሳኝ ነው። በቤተሰብ ውስጥ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በክርክሩ ለመርታት ከመጣር ይልቅ ችግሩን በመፍታት ውጥረቱን ለማርገብ ሞክሩ። ደስተኛ የቤተሰብ አባላት አንዳቸው ለሌላው ደግነትና አሳቢነት ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።—ቆላስይስ 3:8, 12-14

8 ደግነት ከቅን አስተሳሰብ የሚመነጭ ባሕርይ ስለሆነ ለሌሎች መልካም እንድናደርግ ይገፋፋናል። ስለሆነም ለሌሎች የቤተሰባችን አባላት የምንጠቅም እንዲሁም አሳቢና ተባባሪ መሆን እንፈልጋለን። በቤተሰብ ውስጥ የደግነት ባሕርይ ጎልቶ እንዲታይ የግልም ሆነ የቡድን ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። እንዲህ ማድረግ የአምላክን በረከት የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ በጉባኤም ሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ ደግ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ያስከብራል።—1 ጴጥሮስ 2:12

በሥራ ቦታ ደግነት ማሳየት

9, 10. በሥራ ቦታ ሊያጋጥሙ የሚችሉ አንዳንድ ችግሮች ምንድን ናቸው? በደግነት እንዴት ልንፈታቸው እንደምንችል ተናገር።

9 አንድ ክርስቲያን በሥራ ቦታው በየዕለቱ የሚያጋጥመው ሁኔታ ለሥራ ባልደረቦቹ ደግነት እንዳያሳይ እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል። በሠራተኞች መካከል በሚፈጠር የፉክክር መንፈስ የተነሳ አንድ ሠራተኛ በተንኮል የሥራ ባልደረባውን በአሠሪው ፊት በማሳጣት ከሥራው እንዲባረር ሊያደርገው ይችላል። (መክብብ 4:4 የ1954 ትርጉም) እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ደግነት ማሳየት ቀላል አይሆንም። ይሁን እንጂ አንድ የይሖዋ አገልጋይ ምንጊዜም ትክክለኛው እርምጃ ደግ የሆነውን ነገር ማድረግ እንደሆነ ተገንዝቦ አስቸጋሪ ባሕርይ ያላቸውን ባልደረቦቹን በመልካም ለማሸነፍ የቻለውን ያህል መጣር ይኖርበታል። አሳቢነትን ማሳየት በዚህ ረገድ ይረዳን ይሆናል። የሥራ ባልደረባህ ወይም ከቤተሰቡ አባላት መካከል አንዱ ከታመመ በአሳቢነት ስሜት ስለሁኔታው ልትጠይቀው ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ አመለካከቱን እንዲለውጥ ሊያደርገው ይችላል። አዎን፣ ክርስቲያኖች በበኩላቸው ሰላምና ስምምነት እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ አለባቸው። አንዳንድ ጊዜ አሳቢነትን የሚገልጹ ቃላትን መናገር ችግሩን ለማሻሻል ይረዳል።

10 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሠራተኞቹ የግል አመለካከቶቹን እንዲቀበሉ የሚፈልግ አንድ አሠሪ ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው እንቅስቃሴዎች ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ በዓላት እንዲካፈሉ ያስገድዳቸው ይሆናል። አንድ ክርስቲያን ሕሊናው ይህን እንዲያደርግ ስለማይፈቅድለት ከአሠሪው ጋር አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። በዚህ ወቅት የአሠሪውን ፈቃድ ማድረጉ ስህተት እንደሆነ ለማሳመን ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ መግባቱ ጥሩ አይሆንም። ደግሞም እምነታችንን የማይጋሩ ሰዎች በእነዚህ ድርጊቶች መካፈሉ ስህተት እንደሆነ ላይታያቸው ይችላል። (1 ጴጥሮስ 2:21-23) ምናልባት አንተ በግልህ የማትካፈልበትን ምክንያት በደግነት ማስረዳት ትችል ይሆናል። ለሚሰነዘርብህ የሽሙጥ አነጋገር ፈጽሞ አጸፋ አትመልስ። አንድ ክርስቲያን በሮሜ 12:18 ላይ የሚገኘውን “ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚለውን ግሩም ምክር መከተሉ ጥሩ ነው።

በትምህርት ቤት ደግነት ማሳየት

11. ወጣቶች አብረዋቸው ለሚማሩ ተማሪዎች ደግነት በማሳየት ረገድ ምን ፈተና ይገጥማቸዋል?

11 ልጆች አብረዋቸው ለሚማሩ ተማሪዎች ደግነት ማሳየት ፈታኝ ሊሆንባቸው ይችላል። ልጆች በክፍል ተማሪዎቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይፈልጋሉ። አንዳንድ ልጆች የሌሎች ተማሪዎችን ትኩረት ለመሳብ ሲሉ ሌሎችን በማስፈራራትና በማንገላታት ጉልበተኞች ለመሆን ይጥራሉ። (ማቴዎስ 20:25) ሌሎች ደግሞ በትምህርት፣ በስፖርት ወይም በሌሎች መስኮች ልቀው በመታየት ሌሎችን ለማስደመም ይፈልጋሉ። ከሌሎች ልቀው እንዲታዩ የሚያደርጋቸው ስለሚመስላቸው በክፍል ጓደኞቻቸውና በሌሎች ተማሪዎች ላይ ጉራቸውን በመንዛት ደግነት የጎደለው ባሕርይ ያሳያሉ። አንድ ወጣት ክርስቲያን እንደነዚህ ያሉ ተማሪዎችን እንዳይመስል መጠንቀቅ ይኖርበታል። (ማቴዎስ 20:26, 27) ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው” በማለት የጻፈ ሲሆን ይህ ዓይነቱ ፍቅር “አይመካም፤ አይታበይም።” በመሆኑም አንድ ክርስቲያን አብረውት ከሚማሩት ተማሪዎች ጋር ባለው ግንኙነት ቅዱሳን ጽሑፎች የያዙትን መመሪያ መከተል ይኖርበታል እንጂ ደግነት የጎደለው ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን መጥፎ ምሳሌ መኮረጅ አይገባውም።—1 ቆሮንቶስ 13:4

12. (ሀ) ወጣቶች ለአስተማሪዎቻቸው ደግነት ማሳየት አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ወጣቶች ደግነት የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽሙ ተጽዕኖ ሲደረግባቸው በማን መተማመን ይችላሉ?

12 ወጣቶች ከአስተማሪዎቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነትም ደግነት ማሳየት ይኖርባቸዋል። በርካታ ተማሪዎች አስተማሪዎቻቸውን ማበሳጨት ያስደስታቸዋል። የትምህርት ቤቱን ሕጎች በሚያስጥሱ እንቅስቃሴዎች በመካፈል ለአስተማሪዎቻቸው አክብሮት እንደሌላቸው ማሳየታቸውን እንደ ሥልጣኔ ይቆጥሩታል። ሌሎችን በማስፈራራት እንዲተባበሯቸው ያደርጋሉ። አንድ ወጣት ክርስቲያን ለመተባበር ፈቃደኛ ካልሆነ ሊፌዝበትና ድብደባ ሊፈጸምበት ይችላል። አንድ ተማሪ እስከ ትምህርት ዘመኑ መገባደጃ ድረስ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲደርስበት ደግነት ለማሳየት የነበረውን ቁርጥ አቋም ሊፈትንበት ይችላል። ይሁን እንጂ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አትዘንጉ። አስቸጋሪ በሆኑት በእነዚያ ጊዜያት ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንደሚረዳችሁ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ።—መዝሙር 37:28

ለጎረቤቶች ደግነት ማሳየት

13-15. ለጎረቤቶቻችን ደግነት እንዳናሳይ እንቅፋት ሊሆኑብን የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው? እነዚህን እንቅፋቶች ማሸነፍ የምንችለውስ እንዴት ነው?

13 የምትኖረው በራስህ ቤትም ይሁን በአፓርታማ ውስጥ ወይም በሌላ በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ለጎረቤቶችህ በምን መንገዶች ደግነት ማሳየትና አሳቢነትህን መግለጽ እንደምትችል ማሰብ ትችላለህ። ይህም ቢሆን ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው።

14 ጎረቤቶችህ በዘርህ፣ በዜግነትህ ወይም በሃይማኖትህ ምክንያት ቢጠሉህስ? አንዳንድ ጊዜ ጨዋነት የጎደለው ምግባር ቢያሳዩህ ወይም ከነጭራሹ ችላ ቢሉህስ? የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ በተቻለህ መጠን ደግነት ማሳየትህ ጠቃሚ ነው። ደግነት በማሳየት ረገድ ምሳሌ ለሚሆነው ለይሖዋ ክብር የምታመጣ ከሌሎች የተለየህ ሰው ትሆናለህ። ጎረቤትህ በምታሳየው ደግነት ተነክቶ መቼ የአመለካከት ለውጥ ሊያደርግ እንደሚችል አታውቅም። እንዲያውም እርሱ ራሱ የይሖዋ አምላኪ ሊሆን ይችላል።—1 ጴጥሮስ 2:12

15 ደግነት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት የመንፈስ ፍሬዎችን እያፈሩ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል ባሕርይ በማንጸባረቅ ነው። ጎረቤቶችህ ይህን ማስተዋላቸው አይቀርም። አንዳንድ ጊዜ ለጎረቤትህ መልካም ነገር ልታደርግለት ትችል ይሆናል። ደግነት ማሳየት ሲባል ለሌሎች ደህንነት ልባዊ አሳቢነት ማሳየት ማለት እንደሆነ አስታውስ።—1 ጴጥሮስ 3:8-12

በአገልግሎት ላይ ደግነት ማሳየት

16, 17. (ሀ) በአገልግሎት ላይ ደግነት ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ደግነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ላይ ሰዎችን በቤታቸው፣ በሚሠሩበት ቦታና በአደባባይ አግኝተን ለማነጋገር በምናደርገው ልባዊ ጥረት ደግነት ማንጸባረቅ ይኖርብናል። ምንጊዜም ደግ የሆነው የይሖዋ ወኪሎች መሆናችንን መዘንጋት አይኖርብንም።—ዘፀአት 34:6 NW

17 በአገልግሎት ላይ ደግነት ማሳየት የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ለምሳሌ ያህል፣ በመንገድ ላይ ምሥክርነት በምትሰጥበት ጊዜ መልእክትህን አጭር በማድረግና አሳቢ በመሆን ደግነት ማሳየት ትችላለህ። የእግረኞች መተላለፊያ ብዙውን ጊዜ ሰው ስለሚበዛበት መንገድ እንዳትዘጋ ጥንቃቄ አድርግ። በንግድ አካባቢ በምታገለግልበት ጊዜም የሱቅ ባለቤቶች ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ እንደሚኖርባቸው በማስታወስ መልእክትህን አጭር በማድረግ ደግነት ማሳየት ትችላለህ።

18. በአገልግሎት ላይ ደግነት በማሳየት ረገድ ማስተዋል ምን ሚና ይጫወታል?

18 ከቤት ወደ ቤት በምታገለግልበት ጊዜም አስተዋይ ሁን። በተለይ የአየሩ ጠባይ መጥፎ ከሆነ በአንድ ሰው ቤት ወይም በር ላይ ብዙ አትቆይ። አንድ ሰው ትዕግሥቱ እያለቀ ወይም እየተናደደ ሲሄድ ማስተዋል ትችላለህ? ምናልባት አንተ በምትኖርበት አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች የአገልግሎት ክልላቸውን ቶሎ ቶሎ ይሸፍኑ ይሆናል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ ሁልጊዜ ደግ በመሆንና አቀራረብህን ወዳጃዊ በማድረግ የተለየ አሳቢነት አሳይ። (ምሳሌ 17:14) የምታነጋግረው ሰው የዚያን ዕለት ሊያነጋግርህ ያልፈለገበትን ምክንያት ተረዳለት። ሌሎች ወንድሞች ወይም እህቶች በቅርቡ ያንን ቤት ማንኳኳታቸው እንደማይቀር አስታውስ። የሚቆጣ ሰው ካጋጠመህ ደግነት ለማሳየት የተለየ ጥረት አድርግ። ጮክ ብለህ አትናገር ወይም አትኮሳተር፤ ከዚህ ይልቅ ረጋ ብለህ ተናገር። ደግ የሆነ ክርስቲያን የቤቱ ባለቤት ጭቅጭቅ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ ነገር አይናገርም። (ማቴዎስ 10:11-14) ግለሰቡ አንድ ቀን ለምሥራቹ ጆሮ ይሰጥ ይሆናል።

በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ደግነት ማሳየት

19, 20. በጉባኤ ውስጥ ደግነት ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ደግነት ማሳየት የሚቻለውስ እንዴት ነው?

19 ለእምነት ባልንጀሮቻችን ደግነት ማሳየትም ቢሆን በጣም አስፈላጊ ነው። (ዕብራውያን 13:1) የዓለም አቀፉ ወንድማማች ማኅበር አባላት በመሆናችን እርስ በርስ ባለን ግንኙነት ደግነት ማሳየታችን ጠቃሚ ነው።

20 አንድ ጉባኤ አንድን የመንግሥት አዳራሽ ከአንድ ወይም ከዚያ በላይ ከሆኑ ጉባኤዎች ጋር በጋራ የሚጠቀም ከሆነ የሌሎች ጉባኤ አባላትን በአክብሮት በመያዝ ከእነርሱ ጋር ባለው ግንኙነት ደግነት ማሳየት አስፈላጊ ነው። የስብሰባ ሰዓትን፣ ጽዳትንና ጥገናን ስለመሳሰሉ አስፈላጊ ጉዳዮች በምትነጋገሩበት ጊዜ በመካከላችሁ የፉክክር መንፈስ ካለ ተባብሮ መሥራትን አስቸጋሪ ሊያደርግባችሁ ይችላል። አንዳንድ የአመለካከት ልዩነቶች ቢኖሩባችሁ እንኳ ደግና አሳቢ ሁኑ። በዚህ መንገድ ደግነት ጎልቶ የሚታይ ሲሆን ይሖዋም ይህን ባሕርይ ለማሳየት ያደረጋችሁትን ጥረት ይባርከዋል።

ደግነት ማሳየታችሁን ቀጥሉ

21, 22. ከቆላስይስ 3:12 ጋር በሚስማማ መንገድ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?

21 ደግነት እያንዳንዱን የሕይወታችንን ክፍል የሚነካ ሁሉን አቀፍ ባሕርይ ነው። በመሆኑም የክርስቲያናዊ ባሕርያችን ዓብይ ክፍል ልናደርገው ይገባል። ለሌሎች ደግነት የማሳየትን ልማድ ማዳበር ይኖርብናል።

22 ሁላችንም በየዕለቱ ለሌሎቸ ደግነት በማሳየት “የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን [“ደግነትን፣”]፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ” የሚሉትን የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት በግለሰብ ደረጃ ተግባራዊ እናድርግ።—ቆላስይስ 3:12

ታስታውሳለህ?

• አንድ ክርስቲያን ደግነት እንዳያሳይ እንቅፋት የሚሆኑበት ነገሮች ምንድን ናቸው?

• በቤተሰብ ውስጥ ደግነት ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ እንዲሁም ለጎረቤቶቻችን ደግነት ማሳየትን አስቸጋሪ የሚያደርጉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

• ክርስቲያኖች በአገልግሎት ላይ ደግነት ማሳየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ደግነት ማሳየቱ አንድነትና ትብብር እንዲሰፍን ያደርጋል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የሥራ ባልደረባህ ወይም ከቤተሰቡ አባላት መካከል አንዱ ሲታመም ደግነት ማሳየት ትችላለህ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ቢፌዝባቸውም በታማኝነት ደግነት የሚያሳዩ አገልጋዮቹን ይደግፋቸዋል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጎረቤትን በችግር ጊዜ መርዳት የደግነት መግለጫ ነው