ቀሳውስት ፖለቲካ መስበክ ይገባቸዋል?
ቀሳውስት ፖለቲካ መስበክ ይገባቸዋል?
“በፖለቲካዊ ጉዳዮች መሳተፍ ድሆችን ሊጠቅም እንደሚችል አንድ ካናዳዊ ሊቀ ጳጳስ ለተሳላሚዎች ገለጹ። . . . የፖለቲካው ሥርዓት ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ባይመስልም እንኳ ‘ለድሆች ፍትሕ ለማስፈን ስንል [በፖለቲካዊ ጉዳዮች] መሳተፍ ይኖርብናል።’”—ካቶሊክ ኒውስ
የሃይማኖት መሪዎች በፖለቲካ ጉዳዮች መካፈል ተገቢ እንደሆነ ሲናገሩ መሰማታቸውም ሆነ የፖለቲካ ሥልጣን መያዛቸው የተለመደ ሆኗል። አንዳንዶች ፖለቲካዊ ተሐድሶ ለማምጣት ጥረት አድርገዋል። ሌሎች ደግሞ የዘር መድልዎና ባርነት እንዲወገድ ለማድረግ ሲሉ ባካሄዷቸው ዘመቻዎች በአድናቆት ይታወሳሉ።
ያም ሆኖ በርካታ ምዕመናን ቄሶቻቸው በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ መግባታቸው አያስደስታቸውም። ክርስቺያን ሴንቸሪ የተባለው መጽሔት ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ የሚሰጥ ሃይማኖታዊ ትምህርትን አስመልክቶ ባወጣው ርዕስ ላይ “ቀሳውስቶቻቸው በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ መግባታቸው ተገቢ ስለመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ጥያቄ የሚያነሱት የፕሮቴስታንት ምዕመናን ናቸው” ብሏል። አብዛኞቹ የሃይማኖት ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ በመሆኑ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ መግባት እንደሌለበት ይሰማቸዋል።
ይህ ጉዳይ የተሻለ ዓለም ለማየት የሚናፍቁ ሰዎችን ትኩረት የሚስቡ ጥያቄዎች ያስነሳል። የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች ፖለቲካዊ ተሐድሶ ሊያመጡ ይችላሉ? a በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ የተሻለ መንግሥትና የተሻለ ዓለም ለማምጣት አምላክ የሚጠቀምበት መንገድ ነው? ክርስትና ሲመሠረት ዓላማው የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር ነበር?
ቀሳውስት በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ መግባት የጀመሩት እንዴት ነው?
ሄንሪ ቻድዊክ የተባሉት የታሪክ ምሑር ዚ ኧርሊ ቸርች በተባለው መጽሐፍ ላይ የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ የሚታወቀው “በዓለም ላይ ሥልጣን ለመያዝ የማይፈልግ በመሆኑ” እንደነበረ ተናግረዋል። “ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ የሆነ፣ ሰላማዊና በጦርነት የማይካፈል ኅብረተሰብ” ነበር። የክርስትና ታሪክ የተባለው መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) እንዲህ ይላል፦ “ክርስቲያኖች ከመካከላቸው ማናቸውም ቢሆኑ ፖለቲካዊ ሥልጣን ሊይዙ እንደማይገባ በጽኑ ያምኑ ነበር። . . . እስከ ሦስተኛው መቶ ዘመን መባቻ ድረስ በነበረው የክርስትና ልማድ መሠረት፣ በሕዝብ አስተዳደር ሥራ የሚሳተፍ አንድ ሰው ክርስቲያን መሆን ከፈለገ ሥራውን እንዲለቅቅ ይጠበቅበት እንደነበር ሂፖሊተስ ተናግሯል።” ውሎ አድሮ ግን የሥልጣን ጥመኛ የሆኑ ሰዎች በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ የአመራር ቦታ ያዙና ለራሳቸው የማዕረግ ስሞች ይሰጡ ጀመር። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) አንዳንዶች የሃይማኖት መሪዎች በመሆን ሳይወሰኑ የፖለቲካ መሪዎችም መሆን ፈለጉ። የሮም መስተዳደር በድንገት ሲለወጥ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ምኞታቸውን ለማሳካት የሚያስችል አጋጣሚ ተከፈተላቸው።
በ312 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አረማዊው የሮም ንጉሠ
ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ነን ለሚሉ ሰዎች ቀና አመለካከት ያሳይ ጀመረ። የሚያስገርመው የቤተ ክርስቲያኗ ጳጳሳት ከአረማዊው ንጉሠ ነገሥት ለሚያገኟቸው መብቶች ሲሉ ከእርሱ ጋር ለመስማማት ፈቃደኞች ነበሩ። ሄንሪ ቻድዊክ “ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ቤተ ክርስቲያኗ ወሳኝ በሆኑ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ረገድ ይበልጥ ተሰሚነት እያገኘች መጣች” በማለት ጽፈዋል። ቀሳውስት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ መግባታቸው ምን አስከተለ?ፖለቲካ በሃይማኖት መሪዎች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ
አምላክ የሃይማኖት መሪዎች በፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዲሳተፉ ይፈልጋል የሚለውን ሐሳብ ያስፋፋው አውጉስቲን የተባለ ተደማጭነት የነበረው የአምስተኛው መቶ ዘመን የካቶሊክ ሃይማኖት ምሑር ነው። ቤተ ክርስቲያኗ ብሔራትን በመምራት ለዓለም ሰላም ታመጣለች ብሎ ያስብ ነበር። ሆኖም የታሪክ ምሑር የሆኑት ኸርበርት ጆርጅ ዌልስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ከአምስተኛው እስከ አስራ አምስተኛው መቶ ዘመን ያለው የአውሮፓ ታሪክ፣ በአምላክ የሚመራ ዓለም አቀፋዊ መንግሥት ይኖራል የሚለው ታላቅ ጽንሰ ሐሳብ ተግባራዊ ሊሆን አለመቻሉን አሳይቷል።” ሕዝበ ክርስትና በመላው ዓለም ቀርቶ በአውሮፓ ውስጥ ብቻ እንኳ ሰላም ማስፈን አልቻለችም። ክርስትና በብዙዎች ዘንድ የነበረውን ተቀባይነት አጥቷል። ችግሩ ምን ላይ ነበር?
ክርስትናን እንደሚሰብኩ የሚናገሩ አብዛኞቹ ሰዎች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ የሚገቡት በበጎ ዓላማ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን በመጥፎ ድርጊቶች መካፈል ይጀምራሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ሰባኪና ተርጓሚ የሆነው ማርቲን ሉተር በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ ባካሄደው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ይታወቃል። የቤተ ክርስቲያኗን መሠረተ ትምህርቶች በድፍረት መቃወሙ ፖለቲካዊ ዓላማ ይዘው ዓመፅ በሚያነሳሱ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅነት አተረፈለት። ሉተርም በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ሐሳብ መስጠት ሲጀምር በብዙኃኑ ዘንድ የነበረውን ከበሬታ አጣ። መጀመሪያ፣ ጨቋኝ በሆኑ መሳፍንት ላይ ያመፁትን ጭሰኞች ይደግፍ ነበር። ቆየት ብሎ ዓመፁ አረመኔያዊ ደም መፋሰስ ሲያስከትል ደግሞ መሳፍንቱን እርምጃ እንዲወስዱ ያበረታታቸው ጀመር። ይህም በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች እልቂት ምክንያት ሆነ። ጭሰኞቹ ሉተርን እንደ ከሃዲ ቢቆጥሩት የሚያስገርም አይደለም። ሉተር መሳፍንቱም በበኩላቸው የካቶሊክ እምነት ተከታይ በነበረው ንጉሠ ነገሥት ላይ እንዲያምፁ ቅስቀሳ አድርጓል። እንዲያውም ፕሮቴስታንቶች ተብለው የተጠሩት የሉተር ተከታዮች እምነቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ፖለቲካዊ ንቅናቄ ማድረግ ጀምረው ነበር። ሉተር ሥልጣን መያዙ ምን ተጽዕኖ አሳደረበት? አቋሙን አበላሸበት። ለአብነት ያህል፣ መጀመሪያ ላይ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹን በኃይል በማሳመን አይስማማም ነበር፤ በኋላ ግን የፖለቲካ ሥልጣን ያላቸው ወዳጆቹ የሕፃናት ጥምቀትን የሚቃወሙ ሰዎችን በእሳት አቃጥለው እንዲገድሉ አነሳስቷል።
ጆን ካልቪን በጀኔቫ የታወቀ የሃይማኖት መሪ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ በፖለቲካው ዓለም ከፍተኛ ተደማጭነት አተረፈ። ሚካኤል ሰርቪተስ ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንደሌለው ሲያብራራ ካልቪን ፖለቲካዊ ተደማጭነቱን በመጠቀም ሰርቪተስ በእንጨት ላይ ተቃጥሎ እንዲገደል ግፊት አድርጓል። ካልቪን ከኢየሱስ ትምህርት ምንኛ ርቆ ነበር!
እነዚህ ሰዎች በ1 ዮሐንስ 5:19 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር ነው’ እንደሚል ሳይዘነጉ አልቀሩም። እውነተኛ ፍላጎታቸው በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካ ሥርዓት ማሻሻል ነበር? ወይስ ትኩረታቸውን የሳበው ሥልጣን መያዛቸውና ባለሥልጣን የሆኑ ወዳጆች ማፍራት መቻላቸው ነው? በዚህም ሆነ በዚያ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነው ያዕቆብ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ ሊሉ ይገባ ነበር፦ “ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላት መሆን እንደሆነ አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” (ያዕቆብ 4:4) ያዕቆብ፣ ኢየሱስ ስለተከታዮቹ ሲናገር “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ፣ እነርሱም ከዓለም [አይደሉም]” እንዳለ ያውቅ ነበር።—ዮሐንስ 17:14
ብዙዎች፣ ክርስቲያኖች በዓለም ላይ በሚፈጸመው ክፋት መካፈል እንደሌለባቸው ቢገነዘቡም ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ በመሆን ሙሉ በሙሉ ‘ከዓለም አለመሆናቸውን’ ግን ይቃወማሉ። እንደዚህ ያለው የገለልተኝነት አቋም ክርስቲያኖች ለሌሎች ያላቸውን ፍቅር በተግባር እንዳያሳዩ ያግዳቸዋል ብለው ይናገራሉ። የሃይማኖት መሪዎች ሙስናንና የፍትሕ መጓደልን በመዋጋት ረገድ ሐሳባቸውን ሊገልጹና የጎላ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል የሚል እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ገለልተኛ አቋም እንድንይዝ የሰጠው ትምህርት ለሌሎች አሳቢነት እንዳናሳይ ያግደናል? አንድ ክርስቲያን በአንድ በኩል ሰዎችን ከሚከፋፍሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎችን መርዳት ይችላል? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ፖለቲካ የአንድ አገር መንግሥት የሚያከናውናቸው ተግባሮች፣ በተለይም ሥልጣን ላይ ያሉ አሊያም ሥልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች የሚያደርጉት ሽኩቻ ወይም ግብግብ የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀሳውስት ፖለቲካዊ ሥልጣን ለማግኘት ሲሉ እንደ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ካሉት መሪዎች ጋር ስምምነት ፈጥረዋል
[ምንጭ]
Musée du Louvre, Paris
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታዋቂ የሆኑ የሃይማኖት መሪዎች በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ የገቡት ለምንድን ነው?
አውጉስቲን
ሉተር
ካልቪን
[ምንጭ]
አውጉስቲን፦ ICCD Photo; ካልቪን፦ ዘ ሂስትሪ ኦቭ ፕሮቴስታንቲዝም (ጥራዝ ሁለት) ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ በሆልባይን የተሠራ ሥዕል