በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንዳችሁ ሌላውን አበርቱ

አንዳችሁ ሌላውን አበርቱ

አንዳችሁ ሌላውን አበርቱ

“የብርታት ምንጭ የሆኑልኝ እነዚህ ናቸው።”—ቆላስይስ 4:11 Nw

1, 2. አደጋ ሊያስከትልባቸው ቢችልም የጳውሎስ ጓደኞች እስር ቤት ድረስ ሄደው የጠየቁት ለምን ነበር?

 አንድ ጓደኛህ በእስር እየማቀቀ ያለው ያለ ጥፋቱ ቢሆንም እንኳ የእንዲህ ዓይነት ሰው ወዳጅ መሆን ለችግር ሊዳርግ ይችላል። የእስር ቤቱ ኃላፊዎች በጥርጣሬ ዓይን ያዩህ እንዲሁም ወንጀል እንዳትፈጽም በመፍራት የምታደርገውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ይከታተሉ ይሆናል። በዚህም ምክንያት ከጓደኛህ ጋር በየጊዜው መገናኘትና እርሱን እስር ቤት ሄዶ መጠየቅ ድፍረት ይጠይቅብሃል።

2 ሆኖም ከ1,900 ዓመታት ገደማ በፊት አንዳንድ የሐዋርያው ጳውሎስ ጓደኞች ያደረጉት ነገር ከዚህ የተለየ አይደለም። አስፈላጊውን ማጽናኛና ማበረታቻ እንዲሁም መንፈሳዊ ማጠናከሪያ ለመስጠት የታሰረበት ቦታ ድረስ ሄደው ጳውሎስን ከመጠየቅ ወደኋላ አላሉም። እነዚህ ታማኝ ጓደኞቹ እነማን ነበሩ? እንዲሁም ካሳዩት ድፍረት፣ ታማኝነትና የወዳጅነት መንፈስ ምን ትምህርት እናገኛለን?—ምሳሌ 17:17

“የብርታት ምንጭ”

3, 4. (ሀ) አምስቱ የጳውሎስ ጓደኞች እነማን ናቸው? ለእርሱስ ምን አድርገውለታል? (ለ) “የብርታት ምንጭ” ሲባል ምን ማለት ነው?

3 እስቲ በ60 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ የተፈጸመውን ነገር እንመልከት። ሐዋርያው ጳውሎስ ሁከት አስነስቷል በሚል የሐሰት ክስ ተወንጅሎ ሮም ውስጥ በእስር ላይ ይገኛል። (የሐዋርያት ሥራ 24:5፤ 25:11, 12) ጳውሎስ ከጎኑ የቆሙ አምስት ክርስቲያኖችን በስም ጠቅሶ ተናግሯል ከእስያ አውራጃ የመጣው የጳውሎስ የግል መልእክተኛና ‘በጌታም አብሮት ሎሌ የሆነው’ ቲኪቆስ፤ ከቆላስይስ የመጣው ‘ታማኝና ተወዳጅ ወንድም’ አናሲሞስ፤ ከተሰሎንቄ የመጣው የመቄዶንያ ሰውና በአንድ ወቅት ከጳውሎስ ጋር ‘አብሮ ታስሮ የነበረው’ አርስጥሮኮስ፤ ከጳውሎስ ጋር በሚስዮናዊነት ያገለገለው የበርናባስ የአክስት ልጅና በስሙ የተሰየመ ወንጌል የጻፈው ማርቆስ፤ እንዲሁም “ለእግዚአብሔር መንግሥት” ከጳውሎስ ጋር አብረውት ከሚሠሩት መካከል አንዱ የሆነው ኢዮስጦስ። ጳውሎስ እነዚህን አምስት ሰዎች በተመለከተ “የብርታት ምንጭ የሆኑልኝ እነዚህ ናቸው” [NW] ብሏል።—ቆላስይስ 4:7-11

4 ጳውሎስ ታማኝ ጓደኞቹ ስለሰጡት እርዳታ ሲናገር በጣም ገላጭ የሆነ አባባል ተጠቅሟል። የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል (ፓሪጎሪያ) “የብርታት ምንጭ” ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን ይህ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ነው። ቃሉ ሰፊ ትርጉም ያለው ከመሆኑም ሌላ አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራበት ከሕክምና ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ነው። a ‘ማጽናናት፣ መርዳት፣ ማበረታታት ወይም ማሳረፍ’ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ማበረታቻ ያስፈልገው ነበር፤ እነዚህ አምስት ወንድሞችም አስፈላጊውን እርዳታ ሰጥተውታል።

ጳውሎስ ‘ማበረታቻ’ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

5. ጳውሎስ ሐዋርያ ቢሆንም እንኳ ምን አስፈልጎት ነበር? ማናችንም ብንሆን አልፎ አልፎ ምን መፈለጋችን አይቀርም?

5 አንዳንዶች ጳውሎስ ሐዋርያ ስለሆነ ማበረታቻ ያስፈልገዋል ብለው አያስቡ ይሆናል፤ ይሁንና ማበረታቻ አስፈልጎታል። ጳውሎስ በተደጋጋሚ ጥቃት ተፈጽሞበታል፤ ‘ብዙ ጊዜ ተገርፏል፣ ብዙ ጊዜ ለሞት ተቃርቧል፣’ ሌሎች መከራዎችም ደርሰውበታል። ይሁንና ጠንካራ እምነት ስለነበረው ይህን ሁሉ በጽናት ተወጥቷል። (2 ቆሮንቶስ 11:23-27) የሆነ ሆኖ ጳውሎስ ሥጋ ለባሽ ነበር፤ ማንኛውም ሰው ቢሆን ደግሞ በአንድ ወቅት ላይ ማጽናኛ ለማግኘትና እምነቱ እንዲጠናከር የሌሎችን እርዳታ መፈለጉ አይቀርም። ኢየሱስ እንኳ ሳይቀር ማጽናኛ የፈለገበት ወቅት ነበር። ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት በጌቴሴማኒ እያለ አንድ መልአክ መጥቶ ‘አበረታቶታል።’—ሉቃስ 22:43

6, 7. (ሀ) ሮም ውስጥ ጳውሎስን ያሳዘኑት እነማን ነበሩ? ያጽናኑትስ? (ለ) የጳውሎስ መንፈሳዊ ወንድሞች ምን ዓይነት ድጋፍ በመስጠት “የብርታት ምንጭ” መሆናቸውን አስመስክረዋል?

6 ጳውሎስም ማበረታቻ የፈለገበት ወቅት ነበር። እስረኛ ሆኖ ሮም ሲደርስ ወገኖቹ የሆኑ ሰዎች በጥሩ ሁኔታ አልተቀበሉትም። በጥቅሉ ሲታይ እነዚህ አይሁዶች የመንግሥቱን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የአይሁድ መሪዎች የታሰረበት ቦታ ድረስ መጥተው ጳውሎስን ካነጋገሩት በኋላ “አንዳንዶቹ እርሱ የሚለውን አምነው ተቀበሉ፤ ሌሎቹ ግን አላመኑበትም፤ እርስ በርሳቸውም አልተስማሙም” በማለት የሐዋርያት ሥራ ዘገባ ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 28:17, 24, 25) እነዚህ ሰዎች ይሖዋ ላሳያቸው ታላቅ ደግነት አመስጋኝ ሳይሆኑ መቅረታቸው ጳውሎስን ምንኛ አሳዝኖት ይሆን! በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰማው ጥልቅ ሐዘን ከጥቂት ዓመታት በፊት በሮም ለሚገኘው ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በግልጽ ታይቷል “ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት በልቤ አለ። ለወገኖቼ ስል ስለ ወንድሞቼ [ስለ አይሁዶች] እኔ ራሴ የተረገምሁና ከክርስቶስም ተለይቼ የተጣልሁ እንድሆን እንኳ እወድ ነበር።” (ሮሜ 9:2, 3) ይሁንና ሮም ውስጥ ያገኛቸው ታማኝና እውነተኛ ወዳጆች ያሳዩት ድፍረትና ፍቅር አጽናንቶታል። እነዚህ እውነተኛ መንፈሳዊ ወንድሞቹ ነበሩ።

7 እነዚህ አምስት ወንድሞች የብርታት ምንጭ የሆኑለት እንዴት ነው? ጳውሎስ እስረኛ መሆኑ ከእርሱ እንዲሸሹ አላደረጋቸውም። ከዚህ ይልቅ እስር ላይ በመሆኑ ምክንያት ሊያደርጋቸው ያልቻላቸውን ሥራዎች በማከናወን ለጳውሎስ በፈቃደኝነትና በፍቅር አንዳንድ ነገሮች አድርገውለታል። ለምሳሌ ያህል መልእክተኛ በመሆን የጳውሎስን ደብዳቤዎችና የቃል መመሪያዎች ለተለያዩ ጉባኤዎች አድርሰዋል፤ እንዲሁም በሮምም ሆነ በሌሎች አገሮች ስላሉ ወንድሞች ደኅንነት የሚያበረታቱ ሪፖርቶች አምጥተውለታል። እንደ ክረምት ልብስ፣ የብራና ጥቅልሎችና የመጻፊያ መሣሪያዎች የመሳሰሉ አስፈላጊ ዕቃዎችንም ይዘውለት መጥተዋል። (ኤፌሶን 6:21, 22፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:11-13) እነዚህ ጠቃሚ ተግባሮች በእስር ላይ የነበረውን ሐዋርያ ያጠናከሩትና ያበረታቱት በመሆኑ እርሱም ጉባኤዎችን ጨምሮ ለሌሎች “የብርታት ምንጭ” መሆን ችሏል።—ሮሜ 1:11, 12

“የብርታት ምንጭ” መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

8. ጳውሎስ ‘የሚያበረታው ሰው’ እንደሚፈልግ በትሕትና አምኖ መቀበሉ ለእኛ ምን ትምህርት ይዟል?

8 ስለ ጳውሎስና ስለ አምስት የሥራ ባልደረቦቹ ከሚናገረው ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? እስቲ በአንድ ነጥብ ላይ ትኩረት እናድርግ ሌሎች መከራ ሲያጋጥማቸው እነርሱን ለመርዳት ከጎናቸው መቆም ድፍረትና የራስን ጥቅም መሠዋት ይጠይቃል። በተጨማሪም እኛም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን እርዳታ እንደምንፈልግ ማሳወቅ ትሕትና ይጠይቅብናል። ጳውሎስ እርዳታ እንደሚያስፈልገው በግልጽ ከመናገሩም በላይ የተሰጠውን እርዳታ በደስታ ተቀብሏል፤ የረዱትን ሰዎችም አመስግኗል። ከሌሎች እርዳታ መቀበል የደካማነት ምልክት እንደሆነ ወይም እንደ ውርደት አድርጎ አልቆጠረውም። እኛም የእርሱ ዓይነት አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል። የሌሎች ማበረታቻ አያስፈልገኝም ብሎ መናገር ከሰው የተለየ ብርታት አለኝ ከማለት ተለይቶ አይታይም። ፍጹም የሆነ ሰው እንኳ አንዳንድ ጊዜ እርዳታ ለማግኘት መለመን እንዳለበት ከኢየሱስ ምሳሌ ማየት እንደሚቻል አስታውስ።—ዕብራውያን 5:7

9, 10. አንድ ሰው እርዳታ እንደሚያስፈልገው በግልጽ መናገሩ ምን መልካም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል? ይህስ በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ባሉ ወንድሞች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል?

9 የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ወንድሞች የአቅም ገደብ እንዳለባቸውና የሌሎች ድጋፍ የግድ እንደሚያስፈልጋቸው አምነው መቀበላቸው ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። (ያዕቆብ 3:2) እንዲህ የመሰለው ግልጽነት ኃላፊነት ባላቸውና በጉባኤ ውስጥ ላለው ሥልጣን በሚገዙ ወንድሞች መካከል ያለውን አንድነት ያጠናክራል፤ ሞቅ ያለና መፈራራት የሌለበት የሐሳብ ግንኙነት እንዲሰፍንም ያደርጋል። ከሌሎች እርዳታ ለማግኘት ፈቃደኛ የሚሆኑ ወንድሞች የሚያሳዩት ትሕትና በተመሳሳይ ሁኔታ ሥር ለሚገኙ ለሌሎች ሕያው ምሳሌ ይሆንላቸዋል። የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ወንድሞች ሰብዓዊ ድካም እንዳለባቸውና ሊቀረቡ የሚችሉ መሆናቸውን ያሳያል።—መክብብ 7:20

10 ለምሳሌ ያህል ልጆች፣ ወላጆቻቸው ትንንሽ በነበሩበት ጊዜ እነርሱ የሚያጋጥሟቸው ዓይነት ችግሮችና ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸው እንደነበር ማወቃቸው ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን እርዳታ ለመቀበል ይበልጥ ፈቃደኞች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። (ቆላስይስ 3:21) ይህም በወላጅና በልጅ መካከል ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል። ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ማካፈል የሚቻል ከመሆኑም በላይ ልጆች የሚነገራቸውን በደስታ ይቀበላሉ። (ኤፌሶን 6:4) በተመሳሳይ የጉባኤ አባሎች ሽማግሌዎችም የተለያዩ ችግሮች እንዲሁም ስጋት ላይ የሚጥሏቸውና የሚያስጨንቋቸው ነገሮች እንደሚያጋጥሟቸው ሲገነዘቡ ሽማግሌዎች የሚሰጧቸውን እርዳታ ለመቀበል ይበልጥ ፈቃደኛ ይሆናሉ። (ሮሜ 12:3፤ 1 ጴጥሮስ 5:3) በመካከላቸው ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት የሚፈጠር ከመሆኑም ሌላ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ማካፈልና የወንድሞችን እምነት ማጠናከር ይቻላል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው ዛሬ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1

11. በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ‘ማበረታቻ’ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

11 በሕይወታችን ውስጥ አልፎ አልፎ አስጨናቂ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙን ሲሆን በዚህ ረገድ የምንኖርበት ቦታ፣ ማንነታችን ወይም ዕድሜያችን የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። ይህ የዚህ ዓለም አንድ ገጽታ ነው። (ራእይ 12:12) በአካልና በስሜት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እነዚህን የመሳሰሉ ሁኔታዎች የእምነታችንን ጥራት ይፈትናሉ። በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በቤተሰብ ወይም በጉባኤ ውስጥ ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። የጤና መታወክ ወይም ከዚህ በፊት በሕይወታችን ያጋጠመን አሳዛኝ ነገር ለጭንቀት ሊዳርገን ይችላል። የትዳር ጓደኛችን፣ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ወይም ወዳጃችን በቃልና በድርጊት ቢያበረታታን ምንኛ እንጽናናለን! በሚቆጠቁጥ የሰውነታችን ክፍል ላይ ዘይት የፈሰሰልን ያህል ይሰማናል! ስለዚህ አንድ ወንድምህ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ካስተዋልክ አበረታታው። ወይም ደግሞ አንድ ያስጨነቀህ ችግር ካለ በመንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንድሞች እንዲረዱህ ጠይቅ።—ያዕቆብ 5:14, 15

ጉባኤው እርዳታ ማበርከት የሚችልበት መንገድ

12. በጉባኤ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ሰው ወንድሞቹን ለማበረታታት ምን ማድረግ ይችላል?

12 ወጣቶችን ጨምሮ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ ሌሎችን ለማበረታታት ማድረግ የሚችሉት ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ በጉባኤና በመስክ አገልግሎት ስብሰባ ላይ አዘውትረህ መገኘትህ የሌሎች እምነት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ በጽናት መቀጠልህ ለይሖዋ ያለህን ታማኝነት የሚያረጋግጥ ከመሆኑም ሌላ ችግሮች እያሉብህም በመንፈሳዊ ንቁ መሆንህን ያሳያል። (ኤፌሶን 6:18) በአቋምህ መጽናትህ ሌሎችን ሊያበረታታ ይችላል።—ያዕቆብ 2:18

13. አንዳንዶች አገልግሎት ያቆሙት ለምን ሊሆን ይችላል? እነርሱን ለመርዳትስ ምን ማድረግ ይቻላል?

13 አንዳንድ ጊዜ የኑሮ ጫናዎች ወይም ሌሎች ችግሮች አንዳንዶች በአገልግሎት የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲቀንሱ ወይም እስከ ጭራሹ እንዲያቆሙ ሊያደርጋቸው ይችላል። (ማርቆስ 4:18, 19) አገልግሎት ያቆመ ክርስቲያን ወደ ጉባኤ ስብሰባ አይመጣ ይሆናል። ሆኖም እነዚህ ወንድሞች አሁንም ለአምላክ ፍቅር ሊኖራቸው ይችላል። እምነታቸው እንዲጠናከር ምን ማድረግ ይቻላል? ሽማግሌዎች እነዚህን ወንድሞች ሄደው በመጠየቅ በደግነት ሊረዷቸው ይችላሉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ሌሎች የጉባኤው አባላትም እርዳታ እንዲሰጡ ሊጠየቁ ይችላሉ። በፍቅር ተነሳስተው የሚያደርጉት እርዳታ በእምነት የደከሙት ክርስቲያኖች እንዲያንሰራሩ የሚረዳ ትክክለኛው መድኃኒት ሊሆን ይችላል።

14, 15. ጳውሎስ ሌሎችን ስለማበረታታት ምን ምክር ሰጥቷል? አንድ ጉባኤ የጳውሎስን ምክር በተግባር ያዋለው እንዴት ነው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ ‘ያዘኑትን ነፍሳት እንድናጽናና፣ የደከሙትን እንድንረዳ’ ያበረታታናል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) እነዚህ ‘ያዘኑ ነፍሳት’ ወኔ እንዳጡና የተደቀኑባቸውን ችግሮች ያለ ሌሎች እርዳታ መወጣት እንደማይችሉ ይሰማቸው ይሆናል። የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ አንተ ልትሰጣቸው ትችላለህ? ‘የደከመውን መርዳት’ የሚለው ሐረግ ደካማውን “አጥብቆ መያዝ” ወይም ከእርሱ ጋር “መጣበቅ” ተብሎ ተተርጉሟል። ይሖዋ በጎቹን በሙሉ ይንከባከባቸዋል እንዲሁም ይወዳቸዋል። ዋጋ እንደሌላቸው አድርጎ አይቆጥራቸውም፤ አንዳቸውም እንዲጠፉም አይፈልግም። በመንፈሳዊ የደከሙት እስኪጠነክሩ ድረስ ጉባኤው ‘አጥብቆ እንዲይዛቸው’ መርዳት ትችላለህ?—ዕብራውያን 2:1

15 አንድ ሽማግሌ ለስድስት ዓመታት ከጉባኤ የራቁ አንድ ባልና ሚስትን ቤታቸው ሄዶ ጠየቃቸው። ሽማግሌው እንዲህ ብሎ ጽፏል “የጉባኤው አባላት በሙሉ ያሳዩአቸው ደግነትና ፍቅራዊ አሳቢነት በጥልቅ ስለነካቸው ወደ መንጋው ለመመለስ ተገፋፍተዋል።” እህት የጉባኤው አባላት መጥተው ስለጠየቋት ምን ተሰማት? እንዲህ ትላለች “በመንፈሳዊ እንድናንሰራራ የረዳን ነገር ሊጠይቁን የመጡ ወንድሞችም ሆኑ አብረዋቸው የሚመጡት እህቶች እኛን የመተቸት ወይም የመንቀፍ ዝንባሌ ያልነበራቸው መሆኑ ነው። ከዚህ ይልቅ አሳቢነት ያሳዩን ከመሆኑም ሌላ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ ሰጥተውናል።”

16. ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን ክርስቲያኖች በማንኛውም ጊዜ መርዳት የሚችለው ማን ነው?

16 በእርግጥም፣ አፍቃሪ የሆነ ክርስቲያን ሌሎችን መርዳት ያስደስተዋል። በሕይወታችን ውስጥ ሁኔታዎች ሲለወጡ እኛ ራሳችን ሌሎች ወንድሞች ከሚሰጡን ማበረታቻ ተጠቃሚ ልንሆን እንችላለን። ሆኖም ችግር ላይ በወደቅንበት ወቅት እርዳታ ሊሰጠን የሚችል ሰው የሚታጣበት ጊዜ ሊፈጠር እንደሚችል መጠበቅ ይኖርብናል። ይሁንና በማንኛውም ጊዜ የሚገኝና ለመርዳት ፈቃደኛ የሆነ አንድ የብርታት ምንጭ አለ፤ እርሱም ይሖዋ አምላክ ነው።—መዝሙር 27:10

ይሖዋ—ታላቁ የብርታት ምንጭ

17, 18. ይሖዋ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ያበረታው በምን መንገዶች ነው?

17 ኢየሱስ ተሰቅሎ እያለ “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ!” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮዃል። (ሉቃስ 23:46) ከዚያም በሞት አንቀላፋ። ይህ ከመሆኑ ከተወሰኑ ሰዓታት በፊት ተይዞ በታሰረበት ወቅት የቅርብ ወዳጆቹ በፍርሃት ጥለውት ሸሽተው ነበር። (ማቴዎስ 26:56) ኢየሱስ ከአጠገቡ ማንም ባልነበረበት ሰዓት ማበረታቻ ማግኘት የሚችልበት ብቸኛው ምንጭ በሰማይ የሚኖረው አባቱ ነበር። ደግሞም በይሖዋ መታመኑ ጠቅሞታል። ኢየሱስ ለአባቱ ታማኝ መሆኑ ይሖዋም እርሱን በታማኝነት እንዲረዳው አድርጎታል።—መዝሙር 18:25፤ ዕብራውያን 3:2

18 ይሖዋ፣ ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ታማኝነቱን መጠበቅ እንዲችል አስፈላጊውን እርዳታ ሰጥቶታል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት በውኃ ተጠምቆ እንደወጣ አባቱ ደስ እንደሚሰኝበትና እንደሚወድደው ሲናገር ሰምቷል። ኢየሱስ እርዳታ ባስፈለገው ጊዜ ይሖዋ እንዲያበረታቱት መላእክት ልኮለታል። ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ማብቂያ ላይ ከሁሉ የከፋው ፈተና በደረሰበት ወቅት ያቀረበውን ልመናና ምልጃ ይሖዋ ሰምቶለታል። ይህ ሁሉ ለኢየሱስ የብርታት ምንጭ እንደሆነለት የታወቀ ነው።—ማርቆስ 1:11, 13፤ ሉቃስ 22:43

19, 20. ይሖዋ በችግራችን ጊዜ ሊያበረታን እንደሚችል እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

19 ይሖዋ ለእኛም የብርታት ምንጭ መሆን ይፈልጋል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) የታላቅ ኃይልና ብርታት ሁሉ ትክክለኛ ምንጭ የሆነው ይሖዋ ችግር ላይ ስንወድቅ ሊረዳን ይችላል። (ኢሳይያስ 40:26) ጦርነት፣ ድኅነት፣ በሽታ፣ ሞት ወይም የራሳችን አለፍጽምና ከፍተኛ ጭንቀት ሊያስከትልብን ይችላል። በሕይወታችን የሚያጋጥሙን ፈተናዎች እንደ ‘ኀያል ጠላት’ እንደበረቱብን ሲሰማን ይሖዋ ብርታትና ኃይል ሊሆነን ይችላል። (መዝሙር 18:17፤ ዘፀአት 15:2) ቅዱስ መንፈሱ እኛን ለመርዳት የሚጠቀምበት ኃይለኛ መሣሪያ ነው። ይሖዋ፣ ‘እንደ ንስር በክንፍ መውጣት’ እንዲችል በመንፈሱ አማካኝነት “ለደከመው ብርታት” መስጠት ይችላል።—ኢሳይያስ 40:29, 31

20 የአምላክ መንፈስ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ኃይል ነው። ጳውሎስ “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” ብሏል። አዎን፣ በሰማይ የሚኖረው አፍቃሪ አባታችን በቅርቡ እውን በሚሆነው፣ ቃል በገባልን ገነት ውስጥ “ሁሉን ነገር አዲስ” እስከሚያደርግበት ጊዜ ድረስ የሚያጋጥሙንን ከባድ ችግሮች ሁሉ በጽናት መወጣት እንድንችል “እጅግ ታላቅ ኀይል” ይሰጠናል።—ፊልጵስዩስ 4:13፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ራእይ 21:4, 5

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በደብልዩ ኢ ቫይን የተዘጋጀው ቫይንስ ኮምፕሊት ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ የተባለው መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል “ቃሉ [ፓሪጎሪያ] በግስ መልክ ሲቀመጥ የመቆጥቆጥ ስሜት የሚያስታግሱ መድኃኒቶችን ያመለክታል።”

ታስታውሳለህ?

• በሮም የነበሩ ወንድሞች ለጳውሎስ “የብርታት ምንጭ” የሆኑለት እንዴት ነው?

• በጉባኤ ውስጥ “የብርታት ምንጭ” መሆን የምንችለው በምን መንገዶች ነው?

• ይሖዋ ታላቅ የብርታት ምንጭ የሚሆንልን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በታማኝነት ከጎኑ በመቆም፣ ማበረታቻ በመስጠትና የሚያስፈልጉትን ነገሮች በማድረግ ወንድሞች ለጳውሎስ “የብርታት ምንጭ” መሆናቸውን አስመስክረዋል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎች መንጋውን በማበረታታት ግንባር ቀደም ይሆናሉ