እንደ ኤርምያስ ደፋር ሁኑ
እንደ ኤርምያስ ደፋር ሁኑ
“እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ በርታ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።”—መዝሙር 27:14
1. የይሖዋ ምሥክሮች ምን የተትረፈረፈ በረከት አግኝተዋል?
የይሖዋ ምሥክሮች የሚኖሩት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው። (ኢሳይያስ 11:6-9) በዚህ በመከራ በተሞላ ዓለም ከክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ጋር በዓይነቱ ልዩ በሆነ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ አምላክ ጋርም ሆነ እርስ በርሳቸው ሰላማዊ ዝምድና አላቸው። (መዝሙር 29:11፤ ኢሳይያስ 54:13) መንፈሳዊ ገነታቸው ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጥቷል። ‘የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ የሚፈጽሙ’ ሁሉ ይህ መንፈሳዊ ገነት እየሰፋ እንዲሄድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። (ኤፌሶን 6:6) እንዴት? ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው በመኖርና ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ በማስተማር ነው። በዚህ መንገድ በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ከሚገኙት የተትረፈረፉ በረከቶች እንዲካፈሉ ለሰዎች ግብዣ ያቀርባሉ።—ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 15:8
2, 3. እውነተኛ ክርስቲያኖች ጽናት የሚጠይቁ ምን ነገሮችን ይጋፈጣሉ?
2 የምንኖረው መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ቢሆንም መከራ አይደርስብንም ማለት አይደለም። አሁንም አለፍጽምና ተጽዕኖ የሚያሳድርብን ከመሆኑም ሌላ በሽታ፣ እርጅናና ሞት ለሥቃይ ይዳርጉናል። ከዚህም በላይ “በመጨረሻው ዘመን” እንደሚፈጸሙ የተነገሩት ትንቢቶች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ጦርነት፣ ወንጀል፣ በሽታ፣ ረሐብና ሌሎች አስከፊ ችግሮች የሰው ልጆችን በሙሉ ይነካሉ፤ የይሖዋ ምሥክሮችም ከእነዚህ ነፃ አይደሉም።—ማርቆስ 13:3-10፤ ሉቃስ 21:10, 11
3 በተጨማሪም፣ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ መሆናችን ጥበቃ የሚያስገኝልን ቢሆንም ከዚያ ውጪ ያሉ ሰዎች ከባድ ተቃውሞ እንደሚያደርሱብን እናውቃለን። ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ ሲል አስጠንቅቋቸዋል፦ “ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም፤ ዓለም የሚጠላችሁም ስለዚሁ ነው። ‘አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን አሳደውኝ ከሆነ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል።” (ዮሐንስ 15:18-21) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ብዙ ሰዎች ስለ እምነታችን ትክክለኛ ግንዛቤ የላቸውም አሊያም ጠቀሜታው አይታያቸውም። አንዳንዶች ይነቅፉናል፣ ያፌዙብናል ወይም ኢየሱስ እንደተናገረው ይጠሉናል። (ማቴዎስ 10:22) በመገናኛ ብዙሃን ስለ እኛ የተሳሳተ መረጃ በማቅረብና ጥላቻ የተሞላበት ፕሮፓጋንዳ በማናፈስ ስማችንን ለማጉደፍ ብዙ ጥረት ይደረጋል። (መዝሙር 109:1-3) አዎን፣ ሁላችንም ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል፤ አንዳንዶቻችንም ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ታዲያ መጽናት የምንችለው እንዴት ነው?
4. ለመጽናት እርዳታ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?
4 ይሖዋ የእርዳታ እጁን ይዘረጋልናል። መዝሙራዊው “የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል” ሲል በመንፈስ አነሳሽነት ጽፏል። (መዝሙር 34:19፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13) በይሖዋ ሙሉ በሙሉ የምንታመን ከሆነ ማንኛውንም መከራ መቋቋም የምንችልበት ብርታት አንደሚሰጠን አብዛኞቻችን አይተናል። ለእርሱ ያለን ፍቅርና ከፊታችን የሚጠብቀን ደስታ ተስፋ መቁረጥንና ፍርሃትን እንድንዋጋ ይረዳናል። (ዕብራውያን 12:2) በመሆኑም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ጸንተን መቆም እንችላለን።
ኤርምያስ ከአምላክ ቃል ማበረታቻ አግኝቷል
5, 6. (ሀ) ጽናት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑን አንዳንድ እውነተኛ አምላኪዎች እነማን ናቸው? (ለ) ኤርምያስ ነቢይ ሆኖ እንዲያገለግል ሲነገረው ምን ተሰማው?
5 በታሪክ ዘመናት በሙሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ደስታቸውን ጠብቀው ኖረዋል። አንዳንዶቹ የኖሩት ይሖዋ ከሃዲ በሆኑት ላይ እርምጃ በወሰደበት የፍርድ ወቅት ነበር። ኤርምያስና በእርሱ ዘመን የኖሩ አንዳንዶች እንዲሁም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ከታማኝ አምላኪዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህ የታሪክ ዘገባዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈሩት የብርታት ምንጭ እንዲሆኑን ስለሆነ ታሪኮቹን በማጥናት ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (ሮሜ 15:4) ለምሳሌ ያህል የኤርምያስን ሁኔታ ተመልከት።
6 ኤርምያስ ገና በልጅነት ዕድሜው በይሁዳ ነቢይ ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ። ይህ ሥራ እንዲህ የዋዛ አልነበረም። በወቅቱ ብዙዎች የሐሰት አማልክት ተከታዮች ሆነው ነበር። ኤርምያስ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት ንጉሥ የነበረው ኢዮስያስ ንጹሑን አምልኮ በታማኝነት የደገፈ ቢሆንም ከእርሱ በኋላ የመጡት ነገሥታት በሙሉ ግን ከሃዲዎች ነበሩ። ከዚህም በላይ ሕዝቡን እንዲያስተምሩ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ከነበሩት ነቢያትና ካህናት መካከል አብዛኞቹ የእውነት ጠበቆች አልነበሩም። (ኤርምያስ 1:1, 2፤ 6:13፤ 23:11) ታዲያ ኤርምያስ ነቢይ ሆኖ እንዲያገለግል ይሖዋ ሲነግረው ምን ተሰማው? በጣም ፈራ! (ኤርምያስ 1:8, 17) ኤርምያስ በወቅቱ የተሰማውን እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “እኔም፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝና’ አልሁ።”—ኤርምያስ 1:6
7. ኤርምያስ መልእክቱን በሚያውጅበት ክልል ውስጥ ያገኘው ምላሽ ምንድን ነው? እርሱስ ምን አለ?
7 ኤርምያስ መልእክቱን በሚያውጅበት ክልል ውስጥ በአመዛኙ ጥሩ ምላሽ አላገኘም፤ አብዛኛውን ጊዜም ከባድ ተቃውሞ ገጥሞታል። በአንድ ወቅት ካህኑ ጳስኮር ኤርምያስን የመታው ከመሆኑም ሌላ በእግር ግንድ አሳሰረው። ኤርምያስ በወቅቱ የተሰማውን እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ከእንግዲህ የእርሱን [የይሖዋን] ስም አላነሣም፤ በስሙም አልናገርም።” አንተም ተመሳሳይ ስሜት አድሮብህ ሥራውን ለማቆም ያሰብክበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። ኤርምያስ እንዲጸና የረዳው ምን እንደሆነ ተመልከት። “ቃሉ በልቤ እንደ እሳት፣ በዐጥንቴም ውስጥ እንደ ረመጥ ሆነብኝ፤ ዐፍኜ መያዝ አቃተኝ፤ ጨርሶ መቋቋም አልቻልሁም” ብሏል። (ኤርምያስ 20:9) የአምላክ ቃል በአንተም ላይ ተመሳሳይ ስሜት ያሳድራል?
የኤርምያስ ባልደረቦች
8, 9. (ሀ) ነቢዩ ኦርዮ የታየበት ድክመት ምንድን ነው? ይህስ ምን አስከተለበት? (ለ) ባሮክ ተስፋ የቆረጠው ለምን ነበር? አቋሙን አንዲያስተካክል እርዳታ ያገኘውስ እንዴት ነው?
8 ኤርምያስ የነቢይነት ሥራውን የሚያከናውነው ብቻውን አልነበረም። የሥራ ባልደረቦች የነበሩት ሲሆን ይህም አበረታቶት እንደሚሆን ይገመታል። ይሁንና እነዚህ ሰዎች ጥበብ የጎደለው እርምጃ የወሰዱባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል እንደ እርሱ ነቢይ የነበረው ኦርዮ “እንደ ኤርምያስ” ቃል ሁሉ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ስለሚመጣው ጥፋት በትጋት ማስጠንቀቂያ ያውጅ ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሥ ኢዮአቄም፣ ኦርዮ እንዲገደል ትእዛዝ ባስተላለፈ ጊዜ ይህ ነቢይ ፈርቶ ወደ ግብፅ ሸሸ። ሆኖም ከሞት አላመለጠም። የንጉሡ መልእክተኞች ግብፅ ድረስ ሄደው ይዘውት ወደ ኢየሩሳሌም ከመጡ በኋላ ገደሉት። ኤርምያስ ይህን ሲሰማ ምንኛ ደንግጦ ይሆን!—ኤርምያስ 26:20-23
9 ሌላው የኤርምያስ የሥራ ባልደረባ ጸሐፊው ባሮክ ነበር። ባሮክ ለኤርምያስ ጥሩ ረዳት ሆኖለት ነበር፤ አንድ ወቅት ላይ ግን የእርሱም መንፈሳዊ አመለካከት ተዛባ። “እግዚአብሔር በሕመሜ ላይ ሐዘን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ፤ ከልቅሶዬ ብዛት የተነሣ ደክሜያለሁ፤ ዕረፍትም የለኝም” በማለት ማጉረምረም ጀመረ። ባሮክ ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ለመንፈሳዊ ነገሮች የነበረውን አድናቆት አጣ። ይሁንና ይሖዋ በደግነት ጥበብ የተሞላበት ምክር ሰጠው፤ እርሱም አቋሙን አስተካከለ። ከዚያም በኢየሩሳሌም ላይ ከሚመጣው ጥፋት በሕይወት እንደሚተርፍ ዋስትና ተሰጠው። (ኤርምያስ 45:1-5) ባሮክ ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ አቋሙ መመለሱ ኤርምያስን ምንኛ አበረታቶት ይሆን!
ይሖዋ ለአገልጋዩ ድጋፍ ሰጠው
10. ይሖዋ ለኤርምያስ ድጋፍ እንደሚሰጠው ቃል የገባለት ምን በማለት ነው?
10 ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ ኤርምያስን አልተወውም። ይሖዋ የነቢዩን ስሜት የተረዳለት ከመሆኑም በላይ አስፈላጊውን ማበረታቻና ድጋፍ ሰጥቶታል። ለምሳሌ ያህል በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ ኤርምያስ ብቁ እንዳልሆነ በተሰማው ጊዜ ይሖዋ “‘እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራቸው’ ይላል እግዚአብሔር” ብሎት ነበር። ከዚያም፣ ይሖዋ ለነቢዩ የሚያከናውነውን ሥራ ከገለጸለት በኋላ እንዲህ ብሎታል፦ “‘ይዋጉሃል፤ ዳሩ ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም’ ይላል እግዚአብሔር።” (ኤርምያስ 1:8, 19) ምንኛ የሚያበረታታ ቃል ነው! ይሖዋም እንዳለው አድርጓል።
11. ይሖዋ ኤርምያስን እንደሚረዳው የገባውን ቃል እንደጠበቀ እንዴት እናውቃለን?
11 ከዚህም የተነሳ በእግር ግንድ ከታሰረና የሕዝብ መቀለጃ ከሆነ በኋላ ኤርምያስ በልበ ሙሉነት እንዲህ ብሏል፦ “እግዚአብሔር እንደ ኀያል ተዋጊ ከእኔ ጋር ነው፤ ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ እንጂ አያሸንፉም፤ ክፉኛ ይዋረዳሉ እንጂ አይሳካላቸውም።” (ኤርምያስ 20:11) ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት ኤርምያስን ለመግደል ሙከራዎች ቢደረጉም ይሖዋ እርሱን መደገፉን ቀጥሏል። እንዲሁም ያሳድዱት የነበሩትና ማስጠንቀቂያውን ችላ ያሉት ሰዎች ሲገደሉና አንዳንዶቹም ተማርከው ወደ ባቢሎን ሲወሰዱ ኤርምያስ ግን እንደ ባሮክ በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው ጥፋት በሕይወት ተርፎ በነፃነት መኖር ችሏል።
12. ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም መዘንጋት የሌለብን ጉዳይ ምንድን ነው?
12 እንደ ኤርምያስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችም ልዩ ልዩ መከራ ይደርስባቸዋል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ለዚህ መንስኤ ከሚሆኑት ነገሮች መካከል የራሳችን አለፍጽምና፣ ዓለም የሚገኝበት ውጥንቅጡ የወጣ ሁኔታ እንዲሁም ሥራችንን የሚቃወሙ ሰዎች አንዳንዶቹ ናቸው። እንዲህ ዓይነት መከራ ሲደርስብን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊሰማን ይችላል። ኤርምያስ ተሰምቶት እንደነበረው እኛም በአገልግሎቱ መቀጠል ስለመቻላችን ጥርጣሬ ያድርብን ይሆናል። በእርግጥም፣ አልፎ አልፎ ተስፋ መቁረጥ ሊያጋጥመን እንደሚችል መጠበቅ አለብን። ተስፋ መቁረጥ ሲሰማን ለይሖዋ ያለን ፍቅር ጥልቀት ይፈተናል። በመሆኑም ተስፋ መቁረጥ እንደ ኦርዮ ይሖዋን ማገልገላችንን እንድናቆም እንዲያደርገን አንፍቀድ። ከዚህ ይልቅ ኤርምያስን እንምሰል እንዲሁም የይሖዋ ድጋፍ እንደማይለየን ትምክህት ይኑረን።
ተስፋ መቁረጥን መዋጋት የምንችልበት መንገድ
13. የኤርምያስንና የዳዊትን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
13 ኤርምያስ ውስጣዊ ስሜቱን በመግለጽና ብርታት እንዲሰጠው በመለመን ምንጊዜም ከይሖዋ አምላክ ጋር ይነጋገር ነበር። ይህ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ነው። ይሖዋ እንዲያበረታው ይለምን የነበረው ንጉሥ ዳዊትም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃሌን አድምጥ፤ መቃተቴንም ቸል አትበል። ንጉሤና አምላኬ ሆይ፤ ወደ አንተ እጸልያለሁና፣ ድረስልኝ ብዬ ስጮህ ስማኝ።” (መዝሙር 5:1, 2) በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የዳዊት የሕይወት ታሪክ ዳዊት ላቀረበው የእርዳታ ጸሎት ይሖዋ በተደጋጋሚ ምላሽ እንደሰጠው ያሳያል። (መዝሙር 18:1, 2፤ 21:1-5) በተመሳሳይ እኛም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ወይም የተደቀኑብን ችግሮች ከአቅማችን በላይ ሲሆኑብን ወደ ይሖዋ መጸለያችንና የልባችንን መንገራችን በጣም ይረዳናል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ 1 ተሰሎንቄ 5:16-18) ይሖዋ እኛን ከመስማት ወደኋላ አይልም። ከዚህ ይልቅ ‘እንደሚያስብልን’ ቃል ገብቶልናል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ይሁን አንጂ ወደ ይሖዋ ከጸለይን በኋላ እርሱ የሚነግረንን ለመስማት ፈቃደኛ አለመሆን ተገቢ አይደለም።
14. የይሖዋ ቃል በኤርምያስ ላይ ምን ስሜት ፈጥሯል?
14 ይሖዋ እኛን የሚያናግረን እንዴት ነው? አሁንም የኤርምያስን ሁኔታ ተመልከት። ኤርምያስ ነቢይ በመሆኑ ይሖዋ በቀጥታ ሐሳቡን ይገልጽለት ነበር። ኤርምያስ የአምላክ ቃል ያሳደረበትን ስሜት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ቃልህ በተገኘ ጊዜ በላሁት፤ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በስምህ ተጠርቻለሁና፣ ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነልኝ።” (ኤርምያስ 15:16) አዎን፣ ኤርምያስ በአምላክ ስም በመጠራቱ ተደስቷል እንዲሁም ቃሉን እንደ ውድ ሀብት ተመልክቶታል። በመሆኑም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ ኤርምያስም በአደራ የተሰጠውን መልእክት ለማወጅ ጓጉቶ ነበር።—ሮሜ 1:15, 16
15. የይሖዋ ቃል በልባችን እንዲተከል ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ምሥራቹን ከማወጅ ወደኋላ እንዳንል የሚረዳን የትኞቹን ነጥቦች ማስታወሳችን ነው?
15 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ከማንም ጋር በቀጥታ አይነጋገርም። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮልናል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር የምናጠናና በተማርነው ነገር ላይ በጥልቅ የምናሰላስል ከሆነ የአምላክ ቃል “ሐሤትና የልብ ደስታ” ይሆንልናል። እንዲሁም ቃሉን ለሌሎች ለማካፈል ጥረት ስናደርግ በይሖዋ ስም የምንጠራ መሆናችን ያስደስተናል። በዚህ ዓለም ከእኛ ሌላ የይሖዋን ስም የሚያውጅ ሕዝብ እንደሌለ እናስታውስ። በሰማይ የተቋቋመውን የአምላክ መንግሥት ምሥራች የሚያውጁትና ትሑት ለሆኑ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ የሚያስተምሩት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። (ማቴዎስ 28:19, 20) ምንኛ ተባርከናል! ይሖዋ በፍቅር በመነሳሳት ይህን የመሰለ ታላቅ መብት ሰጥቶን እያለ እንዴት ዝም ማለት እንችላለን?
በባልንጀራ ምርጫችን ጠንቃቆች እንሁን
16, 17. ኤርምያስ የጓደኛ ምርጫን በተመለከተ ምን አመለካከት ነበረው? እኛስ የእርሱን አርአያ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
16 ኤርምያስ ደፋር እንዲሆን የረዳውን ሌላም ነገር ጠቅሷል። “ፈንጠዝያ ከሚያደርጉት ጋር አልተቀመጥሁም፤ ከእነርሱም ጋር አልፈነጨሁም፤ እጅህ በላዬ ስለ ነበር፣ በቁጣህ ስለ ሞላኸኝ፣ ለብቻዬ ተቀመጥሁ” ብሏል። (ኤርምያስ 15:17) ኤርምያስ ክፉ ባልንጀሮች መጥፎ ተጽእኖ ከሚያሳድሩበት ይልቅ ብቻውን መሆንን መርጧል። እኛም ብንሆን የእርሱ ዓይነት አመለካከት አለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” ሲል የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ፈጽሞ አንዘነጋም። መልካም ጠባያችን ለረጅም ጊዜ አብሮን የኖረ ቢሆንም እንኳ በዚህ ረገድ ካልተጠነቀቅን ሊበላሽብን ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:33
17 መጥፎ ጓደኝነት አስተሳሰባችን በዓለም መንፈስ እንዲበከል ሊያደርግ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 2:12፤ ኤፌሶን 2:2፤ ያዕቆብ 4:4) ስለዚህ ክፉ ባልንጀሮችን ለይተን ለማወቅና ከእነርሱ ሙሉ በሙሉ ለመራቅ የማስተዋል ችሎታችንን እናሰልጥን። (ዕብራውያን 5:14) በዛሬው ጊዜ ጳውሎስ በምድር ላይ ቢኖር ኖሮ የብልግና ወይም የዓመፅ ፊልሞችን ወይም ስፖርቶችን ለሚያይ አንድ ክርስቲያን ምን ይለው ነበር? ፈጽሞ ከማያውቃቸው ሰዎች ጋር በኢንተርኔት ጓደኝነት ለመሠረተ አንድ ወንድም ምን ምክር ይሰጠው ነበር? ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ስለሌለው ሆኖም የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት ወይም ቴሌቪዥን በመመልከት ብዙ ሰዓት ስለሚያሳልፍ አንድ ክርስቲያን ምን ይሰማው ነበር?—2 ቆሮንቶስ 6:14ለ፤ ኤፌሶን 5:3-5, 15, 16
ከመንፈሳዊው ገነት አትውጡ
18. በመንፈሳዊ ጠንካራ አቋም ይዘን ለመቀጠል ምን ይረዳናል?
18 መንፈሳዊ ገነት ውስጥ በመሆናችን በጣም ደስተኞች ነን። በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ከዚያ ጋር ሊመሳሰል የሚችል አንድም ነገር የለም። አማኝ ያልሆኑ ሰዎች እንኳ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው የሚያሳዩትን ፍቅር፣ አሳቢነትና ደግነት ያደንቃሉ። (ኤፌሶን 4:31, 32) ይሁንና ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተስፋ መቁረጥን መዋጋት ያለብን ዛሬ ነው። ጥሩ ጓደኝነት፣ ጸሎትና ጥሩ የጥናት ልማድ በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድንሆን ይረዳናል። እነዚህ ነገሮች ማንኛውንም ፈተና ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ ታምነን እንድንጋፈጥ ብርታት ይሰጡናል።—2 ቆሮንቶስ 4:7, 8
19, 20. (ሀ) ጸንተን እንድንቀጥል የሚረዳን ምንድን ነው? (ለ) የሚቀጥለው ርዕስ የቀረበው ለእነማን ነው? እነማንን ጭምር ሊጠቅም ይችላል?
19 የምናውጀውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የሚጠሉ ሰዎችን በመፍራት እምነታችን እንዲዳከም ፈጽሞ መፍቀድ የለብንም። ኤርምያስን እንዳሳደዱት ሰዎች ሁሉ ከእኛ ጋር የሚዋጉ ሰዎችም የሚዋጉት አምላክን ነው። ሊያሸንፉን አይችሉም። ከሚቃወሙን ሰዎች እጅግ የላቀ ኃይል ያለው ይሖዋ “እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ በርታ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ” ብሎናል። (መዝሙር 27:14) በሙሉ ልባችን በይሖዋ ላይ ተስፋ በማድረግ መልካም የሆነውን ነገር ከመሥራት ወደኋላ ላለማለት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ተስፋ ሳንቆርጥ ከቀጠልን እንደ ኤርምያስና እንደ ባሮክ መልካም ፍሬ እንደምናጭድ እርግጠኛ እንሁን።—ገላትያ 6:9
20 በርካታ ክርስቲያኖች ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ጋር የማያቋርጥ ትግል ለማድረግ ይገደዳሉ። ወጣቶች ደግሞ በዓይነቱ ለየት ያለ ፈተና ያጋጥማቸዋል። እነርሱም ቢሆኑ ከፊታቸው ግሩም አጋጣሚ ተዘርግቶላቸዋል። የሚቀጥለው ርዕስ በመካከላችን ለሚገኙ ወጣቶች የቀረበ ነው። እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ላሉ ወጣቶች በቃል፣ ምሳሌ በመሆንና በቀጥታ ድጋፍ በመስጠት እርዳታ የማበርከት አጋጣሚ ያላቸውን ወላጆችና በዕድሜ የበሰሉ የጉባኤውን አባላት ሊጠቅም ይችላል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው? እርዳታ መጠየቅ ያለብንስ ከማን ነው?
• ኤርምያስ የተሰጠው ሥራ ከባድ ቢሆንም ተስፋ መቁረጥን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው?
• በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብንኖርም ‘ሐሤትና የልብ ደስታ’ የሚያስገኝልን ምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤርምያስ ነቢይ ለመሆን ዕድሜው እንደማይፈቅድለትና ብቁ እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበር
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤርምያስ ስደት ቢደርስበትም እንኳ ይሖዋ “እንደ ኀያል ተዋጊ” ከእርሱ ጋር እንደሆነ ተገንዝቧል