በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወጣቶች፣ ለወደፊቱ ጊዜ መሠረት እየጣላችሁ ነው?

ወጣቶች፣ ለወደፊቱ ጊዜ መሠረት እየጣላችሁ ነው?

ወጣቶች፣ ለወደፊቱ ጊዜ መሠረት እየጣላችሁ ነው?

“ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም።”—ኤርምያስ 29:11 የ1954 ትርጉም

1, 2. ሰዎች ለወጣትነት ምን የተለያየ አመለካከት አላቸው?

 በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ወጣትነት አስደሳች የዕድሜ ክልል እንደሆነ ያምናሉ። ወጣት እያሉ የነበራቸው ጉልበትና ከፍተኛ የተነሳሽነት ስሜት ትዝ ይላቸዋል። ከኃላፊነት ነፃ የነበሩበት፣ አብዛኛውን ጊዜ በጨዋታ ያሳለፉበት እንዲሁም ከፊታቸው ብዙ ነገር የመሥራት አጋጣሚ ተከፍቶላቸው የነበረበት ወቅት ጥሩ ትዝታ ጥሎባቸው አልፏል።

2 በወጣትነት ዕድሜ ላይ የምትገኙት ደግሞ ከዚህ የተለየ አመለካከት ይኖራችሁ ይሆናል። ወጣትነት የሚያስከትላቸውን ስሜታዊና አካላዊ ለውጦች እንዴት እንደምትወጡ ግራ ሊገባችሁ ይችላል። ትምህርት ቤት ውስጥ እኩዮቻችሁ ከባድ ተጽዕኖ ያሳድሩባችሁ ይሆናል። ዕፅ ላለመውሰድ፣ የአልኮል መጠጥ ላለመጠጣት እንዲሁም የሥነ ምግባር ብልግና ላለመፈጸም ከባድ ትግል ማድረግ ሊጠይቅባችሁ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ብዙዎቻችሁ የገለልተኝነት ጥያቄ ወይም ከእምነታችሁ ጋር የተያያዘ ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ያጋጥማችኋል። አዎን፣ ወጣትነት ፈታኝ ወቅት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ወጣትነት በርካታ አጋጣሚዎች የሚከፈቱበት ወቅትም ነው። ጥያቄው፣ በእነዚህ አጋጣሚዎች ምን ታደርጋላችሁ? የሚል ነው።

በወጣትነትህ ተደሰት

3. ሰሎሞን ለወጣቶች የሰጠው ምክርና ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?

3 በዕድሜ የበሰሉ ሰዎች ወጣትነት አጭር መሆኑን ሊነግሩህ ይችላሉ፤ ደግሞም ትክክል ናቸው። ወጣትነት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያልፋል። ኋላ እንዳይቆጭህ በወጣትነትህ ተደሰት! ይህን ምክር የሰጠው ንጉሥ ሰሎሞን ነው። “አንተ ወጣት በወጣትነትህ ጊዜ ደስ ይበልህ፤ በወጣትነትህም ዘመን ልብህ ደስ ያሰኝህ፤ የልብህን መንገድ፣ ዐይንህ የሚያየውንም ሁሉ ተከተል” ሲል ጽፏል። ይሁን እንጂ ሰሎሞን ለወጣቶች ማስጠንቀቂያም ሰጥቷል “ጭንቀትን ከልብህ አርቅ፤ ክፉ ነገርንም ከሰውነትህ አስወግድ።” በተጨማሪም “ወጣትነትና ጉብዝና ከንቱ ናቸው” ብሏል።—መክብብ 11:9, 10

4, 5. ወጣቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰባቸው የሚጠቅማቸው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

4 ሰሎሞን ምን ማለቱ እንደሆነ ገብቶሃል? ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ውድ ዋጋ የሚያወጣ ስጦታ ምናልባትም የገንዘብ ውርስ ሊሆን ይችላል ያገኘ አንድ ወጣት አስብ። ገንዘቡን ምን ያደርግበታል? ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ እንደጠቀሰው አባካኝ ልጅ ገንዘቡን ደስታ በማሳደድ ያባክን ይሆናል። (ሉቃስ 15:11-23) ሆኖም ገንዘቡ ሲያልቅ ምን ይሰማዋል? ግድ የለሽ መሆኑ ለቁጭት እንደሚዳርገው የታወቀ ነው! በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛውን ገንዘብ ጥሩ ነገር ላይ በማዋል ወደፊት ሊጠቅመው በሚችል መንገድ ተጠቀመበት ብለን እናስብ። የኋላ ኋላ ከገንዘቡ ትርፍ ማግኘት ሲጀምር በስጦታ ያገኘውን ገንዘብ በሙሉ በወጣትነት ዕድሜው ስላልተምነሸነሸበት የሚቆጭ ይመስልሃል? በፍጹም አይቆጭም!

5 የወጣትነት ዕድሜህን ከአምላክ እንዳገኘኸው ስጦታ አድርገህ ልትቆጥረው ይገባል። ታዲያ እንዴት ትጠቀምበታለህ? ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምንም ሳታስብ ነጋ ጠባ ደስታ በማሳደድ የወጣትነት ጉልበትህን ልትጨርስ ትችላለህ። ወጣትነትህን በዚህ መንገድ ከተጠቀምክበት “ወጣትነትና ጉብዝና” በእርግጥ “ከንቱ” ይሆኑብሃል። የወጣትነት ዕድሜህን ከፊትህ ለሚጠብቅህ ጊዜ ለመዘጋጀት ብትጠቀምበት ምንኛ የተሻለ ነው!

6. (ሀ) ሰሎሞን ለወጣቶች መመሪያ የያዘ ምን ምክር ሰጥቷል? (ለ) ይሖዋ ወጣቶች ምን እንዲያገኙ ይፈልጋል? አንድ ወጣት ከዚህ ጥቅም ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው?

6 ሰሎሞን “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” በማለት ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ እንድትጠቀምበት የሚያስችል መሠረታዊ ሥርዓት ተናግሯል። (መክብብ 12:1) ሰሎሞን የሰጠው ይህ ምክር ለስኬት የሚያበቃ ቁልፍ ሐሳብ ይዟል፤ ይሖዋን ስማ፣ ፈቃዱንም ፈጽም። ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን ሊያደርግላቸው የፈለገውን ነገር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም።” (ኤርምያስ 29:11 የ1954 ትርጉም) ይሖዋ ለአንተም “ፍጻሜና ተስፋ” ሊሰጥህ ይፈልጋል። በተግባርም ሆነ በሐሳብ እንዲሁም በምታደርገው ውሳኔ እርሱን የምታስብ ከሆነ ፍጻሜህና ተስፋህ ያማረ ይሆናል።—ራእይ 7:16, 17፤ 21:3, 4

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ”

7, 8. አንድ ወጣት ወደ አምላክ መቅረብ የሚችለው እንዴት ነው?

7 ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” የሚል ማሳሰቢያ በመስጠት ይሖዋን እንድናስብ አበረታቶናል። (ያዕቆብ 4:8) ይሖዋ አምልኮና ውዳሴ የሚገባው የሁሉ ነገር ፈጣሪና በሰማይ የሚኖር ሉዓላዊ ገዥ ነው። (ራእይ 4:11) ሆኖም ወደ እርሱ ከቀረብን እርሱም ወደ እኛ ይቀርባል። ይህን የመሰለ ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያሳይ መሆኑ አያስደስትም?—ማቴዎስ 22:37

8 ወደ ይሖዋ መቅረብ የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ “ከማመስገን ጋር ነቅታችሁ በትጋት ጸልዩ” ብሏል። (ቆላስይስ 4:2) በሌላ አባባል የጸሎት ልማድ አዳብሩ ማለት ነው። አባትህ ወይም የጉባኤው አባል የሆነ አንድ ክርስቲያን አንተን ወክሎ ከጸለየ በኋላ አሜን በማለት ብቻ ረክተህ አትኑር። ውስጣዊ ሐሳብህንና ስሜትህን ሳትደብቅ የምታስበውን፣ የምትጨነቅበትን ነገር ወይም ያሉብህን ችግሮች ለይሖዋ ነግረኸዋል? ለሰው መንገር የሚያሳፍርህን ጉዳይ ለእርሱ ነግረኸው ታውቃለህ? ውስጣዊ ስሜታችንን ሳንደብቅ በጸሎት የልባችንን ገልጠን መናገራችን የአእምሮ ሰላም ያስገኝልናል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ወደ ይሖዋ እንድንቀርብና እርሱም ወደ እኛ እየቀረበ እንደሆነ እንዲሰማን ያደርገናል።

9. አንድ ወጣት ይሖዋን መስማት የሚችለው እንዴት ነው?

9 ወደ ይሖዋ መቅረብ የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። ይህም “ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል፤ በመጨረሻም ጠቢብ ትሆናለህ” በሚሉት በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉ ቃላት ተገልጿል። (ምሳሌ 19:20) አዎን፣ ይሖዋን የምትሰማና የምትታዘዝ ከሆነ ለወደፊቱ ጊዜ መሠረት እየጣልክ ነው። ይሖዋን እንደምትሰማ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ዘወትር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንደምትገኝና የሚቀርቡትን ትምህርቶች እንደምታዳምጥ የታወቀ ነው። እንዲሁም በቤተሰባችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ በመገኘት ‘አባትህንና እናትህን እንደምታከብር’ ታሳያለህ። (ኤፌሶን 6:1, 2፤ ዕብራውያን 10:24, 25) እንዲህ ማድረግህ የሚያስመሰግን ነው። ሆኖም ለስብሰባ ለመዘጋጀት፣ አዘውትሮ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብና ምርምር ለማድረግ ‘ዘመኑን በሚገባ እየዋጀህ’ ነው? “እንደ ጥበበኞች” መኖር እንድትችል ያነበብከውን ነገር በሥራ ለማዋል ጥረት ታደርጋለህ? (ኤፌሶን 5:15-17፤ መዝሙር 1:1-3) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ወደ ይሖዋ እየቀረብክ ነው ማለት ይቻላል።

10, 11. ወጣቶች ይሖዋን የሚሰሙ ከሆነ ምን የላቀ በረከት ያገኛሉ?

10 የምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊ በመክፈቻዎቹ ቃላት ላይ የመጽሐፉን ዓላማ ሲገልጽ “ጥበብንና ተግሣጽን ለመቀበል፤ ጥልቅ ሐሳብ የሚገልጡ ቃላትን ለማስተዋል፤ ጽድቅን፣ ፍትሕንና ሚዛናዊ ብያኔን በማድረግ፣ የተገራ ጠቢብ ልቦናን ለማግኘት፤ ብስለት ለሌላቸው አስተዋይነትን፣ በዕድሜ ለጋ ለሆኑት ዕውቀትንና ልባምነትን ለመስጠት” እንደሆነ ተናግሯል። (ምሳሌ 1:1-4) በመሆኑም በምሳሌ መጽሐፍም ሆነ በሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የሚገኘውን ትምህርት ስታነብና በተግባር ስታውል ጽድቅንና ሚዛናዊ ብያኔን የምታዳብር ከመሆኑም በላይ ይሖዋም ወደ እርሱ እንድትቀርብ ያስችልሃል። (መዝሙር 15:1-5) ፍትሕ፣ ብስለት፣ ዕውቀትና ልባምነት ይበልጥ ባዳበርክ መጠን ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታህም ይሻሻላል።

11 አንድ ወጣት በዚህ ረገድ ጥበበኛ እንዲሆን መጠበቅ ምክንያታዊነት የጎደለው አስተሳሰብ ነው? በጥበብ የሚመላለሱ ብዙ ወጣት ክርስቲያኖች ስላሉ እንደዚያ ማለት አይቻልም። እንዲያውም ሌሎች በአክብሮት ያዩአቸዋል፤ ‘ወጣትነታቸውንም ማንም አይንቅም።’ (1 ጢሞቴዎስ 4:12) ወላጆቻቸው በእነርሱ መኩራታቸው ተገቢ ነው፤ ይሖዋም ልቡን እንደሚያስደስቱ ተናግሯል። (ምሳሌ 27:11) ምንም አንኳ ወጣት ቢሆኑ “ንጹሐንን ልብ በል፤ ቅኑንም አስተውል፤ የሰላም ሰው ተስፋ አለውና” የሚሉት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቃላት ለእነርሱም ተፈጻሚ እንደሚሆኑ እርግጠኛ መሆን ይችላሉ።—መዝሙር 37:37

ጥሩ ምርጫ አድርግ

12. ወጣቶች ማድረግ ካሉባቸው ወሳኝ ምርጫዎች መካከል አንደኛው ምንድን ነው? በዚህ ረገድ የሚያደርጉት ምርጫ በወደፊቱ ሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚኖረው ለምንድን ነው?

12 አንድ ሰው በወጣትነት ዕድሜው በርካታ ምርጫዎች ከፊቱ ይደቀናሉ፤ አንዳንዶቹም በሕይወቱ ላይ ዘላቂ ተጽዕኖ ሊኖራቸው ይችላል። በአሁኑ ጊዜ የምታደርጋቸው አንዳንድ ምርጫዎች የወደፊት ሕይወትህንም ይነካሉ። ጥበብ የተሞላባቸው ምርጫዎች አስደሳችና የተሳካ ሕይወት ያስገኛሉ። ጥበብ የጎደላቸው ውሳኔዎች ደግሞ የወደፊት ሕይወትህን ሊያበላሹብህ ይችላሉ። የዚህን ትክክለኛነት ለማየት በሕይወትህ የምታደርጋቸውን ሁለት ምርጫዎች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የመጀመሪያው ጓደኛ አድርገህ የምትመርጠው ማንን ነው? የሚል ነው። ይህ አሳሳቢ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ አንድ ምሳሌ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጉዳት ያገኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) በሌላ አባባል ውሎ አድሮ አብረናቸው የምንውለውን ሰዎች መምሰላችን አይቀርም፤ ወይ ጠቢብ አሊያም ተላላ እንሆናለን። የትኛውን መሆን ትፈልጋለህ?

13, 14. (ሀ) ባልንጀርነት ከሰዎች ጋር ካለን ቀጥተኛ ግንኙነት ሌላ ምንን ይጨምራል? (ለ) ወጣቶች ምን ስህተት ላለመፈጸም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል?

13 ባልንጀርነት ሲባል ወደ አእምሮህ የሚመጣው ነገር ከሰዎች ጋር ያለህ ግንኙነት ይሆናል። አልተሳሳትክም፤ ሆኖም ይህ ብቻ አይደለም። ቴሌቪዥን ስትመለከት፣ ሙዚቃ ስታዳምጥ፣ ልብ ወለድ መጽሐፍ ስታነብብ፣ ፊልም ስታይ ወይም በኢንተርኔት ላይ የሚቀርቡ አንዳንድ መረጃዎችን ስታነብብ ከሰዎች ጋር ቅርርብ እንደፈጠርክ ይቆጠራል። እንዲህ ዓይነቱ ቅርርብ ዓመፅንና የሥነ ምግባር ብልግናን የሚያበረታታ ከሆነ ወይም ዕፅ መውሰድን፣ ስካርን ወይም ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚቃረኑ ሌሎች ነገሮች ማድረግን የሚያደፋፍር ከሆነ በአኗኗሩ የይሖዋን መኖር እንደማይቀበል ከሚያሳይ “ሞኝ” ሰው ጋር ተቀራርበሃል ማለት ይቻላል።—መዝሙር 14:1

14 በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስለምትገኝና በጉባኤ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ስለምታደርግ ጭካኔ የተሞላባቸው ፊልሞች ብታይ ወይም ለጆሮ የሚጥሙ ቢሆኑም መጥፎ ግጥም ያላቸው ሙዚቃዎች ብታዳምጥ ምንም እንደማትሆን ታስብ ይሆናል። ኢንተርኔት ላይ እርቃንን የሚያሳዩ ሥዕሎች የሚቀርብበት ድህረ ገጽ ለአንድ አፍታ አየት ብታደርግ ምንም ጉዳት እንደማያስከትልብህ ይሰማህ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ አንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እንደማያዋጣ ገልጿል! “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) የሚያሳዝነው፣ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ ብዙ ወጣት ክርስቲያኖች መጥፎ ጓደኝነት በመመሥረታቸው መልካም ጠባያቸው ተበላሽቷል። በመሆኑም ከእንዲህ ዓይነቱ ጓደኝነት ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። እንዲህ በማድረግ የጳውሎስን ምክር እንደምትከተል ማሳየት ትችላለህ “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።”—ሮሜ 12:2

15. ወጣቶች ምርጫ ለማድረግ የሚገደዱበት ሁለተኛው ጉዳይ ምንድን ነው? በዚህ ረገድ አንዳንድ ጊዜ ምን ዓይነት ግፊት ይደረግባቸዋል?

15 ትምህርት ከጨረስህ በኋላ ደግሞ በሕይወትህ ምን እንደምታደርግ ለመወሰን የምትገደድበት ጊዜ ይመጣል። ይህ ከፊትህ የተደቀነው ሁለተኛ ምርጫ ነው። የምትኖረው ሥራ የማግኘት አጋጣሚው ጠባብ በሆነበት አገር ውስጥ ከሆነ ጥሩ ሥራ ካጋጠመህ እንዳያመልጥህ ትቻኮል ይሆናል። ያለኸው በበለጸገ አገር ውስጥ ከሆነ ደግሞ ብዙ ምርጫ ሊኖርህና አንዳንዶቹም በጣም ፈታኝ ሊሆኑብህ ይችላሉ። አስተማሪዎችህና ወላጆችህ ላንተ በማሰብ ጥሩ ደሞዝ ሊያስገኝልህ ምናልባትም ባለጠጋ ሊያደርግህ የሚችል ሥራ እንድትይዝ ይገፋፉህ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ሥራ ለማግኘት የሚያስፈልገው ሥልጠና ይሖዋን በማገልገል የምታሳልፈውን ጊዜ ሊገድብብህ ይችላል።

16, 17. አንድ ወጣት ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲይዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንዴት ሊረዱት እንደሚችሉ አብራራ።

16 ውሳኔ ከማድረግህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ ጥረት አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ችለን የመኖር ግዴታ ስላለብን መተዳደሪያ ለማግኘት እንድንሠራ ያበረታታናል። (2 ተሰሎንቄ 3:10-12) ይሁንና ጉዳዩ በዚህ ብቻ አያበቃም። ቀጥሎ የቀረቡትን ጥቅሶች እንድታነብና አንድ ወጣት ሥራ ሲመርጥ ሚዛናዊ እንዲሆን እንዴት ሊረዱት እንደሚችሉ እንድታስብባቸው እናበረታታሃለን ምሳሌ 30:8, 9፤ መክብብ 7:11, 12፤ ማቴዎስ 6:33፤ 1 ቆሮንቶስ 7:31፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10። እነዚህን ጥቅሶች ካነበብክ በኋላ ይሖዋ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አመለካከት ግልጽ ሆኖልሃል?

17 ተቀጥረን የምንሠራውን ሥራ ለይሖዋ ከምናቀርበው አገልግሎት አስበልጠን ማየት የለብንም። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትህን ካጠናቀቅህ በኋላ ሥራ ማግኘት የምትችል ከሆነ ጥሩ ነው። ተጨማሪ ሥልጠና መውሰድ የሚኖርብህ ከሆነ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ከወላጆችህ ጋር መማከሩ አስፈላጊ ነው። ይሁንና “ከሁሉ የሚሻለውን” ማለትም መንፈሳዊ ነገሮችን ፈጽሞ ችላ ማለት የለብህም። (ፊልጵስዩስ 1:9, 10) የኤርምያስ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ የፈጸመውን ስህተት ላለመድገም ተጠንቀቅ። ለተሰጠው የአገልግሎት መብት የነበረውን አድናቆት በማጣቱ ‘ለራሱ ታላቅ ነገርን መሻት’ ጀመረ። (ኤርምያስ 45:5) በዚህ ዓለም ላይ ያለ ማንኛውም “ታላቅ ነገር” ወደ ይሖዋ ይበልጥ ሊያቀርበው ወይም በኢየሩሳሌም ላይ ከሚደርሰው ጥፋት ሊያድነው እንደማይችል ዘንግቶ ነበር። ይህ ምክር ለእኛም ጠቃሚ ነው።

መንፈሳዊ ነገሮችን ከፍ አድርገህ ተመልከት

18, 19. (ሀ) በአካባቢህ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ምን ዓይነት ችግር ደርሶባቸዋል? ለእነርሱ ምን ዓይነት ስሜት ሊኖርህ ይገባል? (ለ) አብዛኞቹ ሰዎች በመንፈሳዊ እንደተራቡ የማይሰማቸው ለምንድን ነው?

18 በቴሌቪዥን ወይም በጋዜጣ ላይ በረሐብ የተጠቁ ልጆች አይተህ ታውቃለህ? እነርሱን ስታይ አዝነህላቸው እንደሚሆን የታወቀ ነው። በአካባቢህ ለሚኖሩ ሰዎች ተመሳሳይ የአዘኔታ ስሜት ታሳያለህ? ልታዝንላቸው የሚገባው ለምንድን ነው? አብዛኞቹ እየተራቡ ስለሆነ ነው። አሞጽ በትንቢት የተናገረው ረሐብ አጥቅቷቸዋል “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በምድር ላይ ረሐብን የምሰድበት ዘመን ይመጣል፤ ይኸውም የእግዚአብሔርን ቃል የመስማት ረሐብ እንጂ፣ እንጀራን የመራብ ወይም ውሃን የመጠማት አይደለም።’”—አሞጽ 8:11

19 እርግጥ፣ መንፈሳዊ ረሐብ ያጠቃቸው አብዛኞቹ ሰዎች “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ” አይደሉም። (ማቴዎስ 5:3 NW) ብዙ ሰዎች በመንፈሳዊ እንደተራቡ አይሰማቸውም። እንዲያውም አንዳንዶቹ በደንብ እንደተመገቡ ሊሰማቸው ይችላል። ሆኖም አንዲህ እንዲሰማቸው የሚያደርገው ፍቅረ ነዋይን፣ ሳይንሳዊ መላምቶችን፣ ሥነ ምግባርን በተመለከተ የሚሰጡ አስተያየቶችንና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችን ጨምሮ ከንቱ የሆነውን “የዓለምን ጥበብ” ስለሚመገቡ ነው። አንዳንዶች ዘመናዊ “ጥበብ” የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ጊዜ ያለፈበት የሚያደርገው ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ ‘ዓለም በገዛ ጥበብዋ እግዚአብሔርን ማወቅ ተስኗታል።’ የዓለም ጥበብ ወደ አምላክ እንድትቀርብ አይረዳህም። የዓለም ጥበብ ‘በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት’ ነው።—1 ቆሮንቶስ 1:20, 21፤ 3:19

20. ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎችን ለመምሰል መጣር ምን ጉዳት ያስከትላል?

20 በረሐብ የተጠቁትን የእነዚያን ልጆች ፎቶ ስታይ አንተም እንደ እነርሱ ለመሆን ምኞት አድሮብህ ያውቃል? አታደርገውም! ሆኖም በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ አንዳንድ ወጣቶች በዙሪያቸው እንዳሉት በመንፈሳዊ የተራቡ ሰዎች መሆን እንደሚፈልጉ አሳይተዋል። እነዚህ ወጣቶች በዓለም ያሉ እኩዮቻቸው ምንም ጭንቀት እንደሌለባቸውና ደስተኛ እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ይሆናል። በዓለም ያሉት ወጣቶች ከይሖዋ የራቁ መሆናቸውን ዘንግተዋል። (ኤፌሶን 4:17, 18) በተጨማሪም መንፈሳዊ ረሐብ የሚያስከትለውን ጉዳት ማስታወስ ተስኗቸዋል። ከእነዚህም መካከል ያልተፈለገ እርግዝና እንዲሁም የሥነ ምግባር ብልግና፣ ማጨስ፣ ስካርና ዕፅ መውሰድ በአካልና በስሜት ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት አንዳንዶቹ ናቸው። መንፈሳዊ ረሐብ የዓመፀኝነት መንፈስ፣ ሥር የሰደደ የባዶነት ስሜትና ዓላማ የሌለው ሕይወት ያስከትላል።

21. ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎች ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ከመከተል መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

21 ስለዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ይሖዋን ከማያመልኩ ልጆች ጋር በምትሆንበት ጊዜ የእነርሱ አስተሳሰብ እንዲቀርጽህ አትፍቀድ። (2 ቆሮንቶስ 4:18) አንዳንዶች ስለ መንፈሳዊ ነገሮች አንኳስሰው ይናገሩ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ በመገናኛ ብዙሐን የሥነ ምግባር ብልግና መፈጸም፣ መስከር፣ መጥፎ ቃላት መናገር ምንም ስህተት እንደሌለው የሚያስመስል የረቀቀ ፕሮፓጋንዳ ሊቀርብ ይችላል። ይህን ተጽዕኖ ተቋቋም። “እምነትና በጎ ኅሊና” ካላቸው ሰዎች ጋር ዘወትር መገናኘትህን ቀጥል። ‘ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጋ ሁን።’ (1 ጢሞቴዎስ 1:19፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58) በጉባኤ ስብሰባና በመስክ አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ አድርግ። ተማሪ እያለህ አልፎ አልፎ ረዳት አቅኚ ሆነህ አገልግል። በዚህ መንገድ መንፈሳዊ አቋምህን አጠናክር፤ እንዲህ ካደረግህ ሚዛንህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ።—2 ጢሞቴዎስ 4:5

22, 23. (ሀ) አንድ ወጣት ክርስቲያን የሚያደርጋቸውን ውሳኔዎች ሌሎች ለመረዳት የሚከብዳቸው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ወጣቶች ምን እንዲያደርጉ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል?

22 መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያለህ ወጣት መሆንህ ሌሎች ለመረዳት የሚከብዳቸውን ውሳኔዎች እንድታደርግ እንደሚያነሳሳህ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወጣት ክርስቲያን የሙዚቃ መሣሪያ ጥሩ አድርጎ የመጫወት ችሎታ ያለውና በሁሉም ትምህርት የላቀ ውጤት የሚያስመዘግብ ተማሪ ነበር። ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በመረጠው ሙያ ማለትም በሙሉ ጊዜ ወንጌላዊነት ወይም በአቅኚነት መሠማራት እንዲችል ከአባቱ ጋር መስተዋት በማጽዳት ሥራ መሳተፍ ጀመረ። አስተማሪዎቹ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ያደረገበት ምክንያት ሊገባቸው አልቻለም። ሆኖም አንተ ከይሖዋ ጋር ተቀራርበህ የምትኖር ከሆነ ይህ ወጣት እንዲህ ያደረገበት ምክንያት እንደሚገባህ እርግጠኞች ነን።

23 በወጣትነት ዕድሜህ ባሉህ ውድ ሀብቶች ምን ብታደርግ እንደሚሻል ስታስብ ‘እውነተኛ የሆነውን ሕይወት ማግኘት እንድትችል ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራስህ አከማች።’ (1 ጢሞቴዎስ 6:19) በወጣትነት ዕድሜህም ሆነ በቀሪው የሕይወት ዘመንህ ሁሉ ‘ፈጣሪህን ለማሰብ’ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። የወደፊቱ ጊዜ የተሳካልህ እንዲሆን መሠረት መጣል የምትችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፤ ይህም የዘላለም ሕይወት ያስገኝልሃል።

ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰሃል?

• ወጣቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ዕቅድ ሲያወጡ የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ማስታወሳቸው ይጠቅማቸዋል?

• አንድ ወጣት ‘ወደ እግዚአብሔር መቅረብ’ የሚችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

• አንድ ወጣት የወደፊት ሕይወቱን የሚነኩበት አንዳንድ ውሳኔዎች ምንድን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሥጋዊ ፍላጎቶች የወጣትነት ጉልበትህንና ተነሳሽነትህን እንዲያሟጥጡብህ ትፈቅዳለህ?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥበበኛ የሆኑ ወጣት ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እይታቸው የጠራ እንዲሆን ያደርጋሉ