ዓይነ ሥውር ሳለሁ ማየት ቻልኩ!
የሕይወት ታሪክ
ዓይነ ሥውር ሳለሁ ማየት ቻልኩ!
ኤጎን ሃውሰር እንደተናገረው
ለሁለት ወራት ያህል ዓይኔ ከታወረ በኋላ ሕይወቴን ሙሉ ችላ ብዬው የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ማየት ቻልኩ።
ከሰባት አሥርተ ዓመታት በላይ ያሳለፍኩትን ሕይወት መለስ ብዬ ሳስብ እርካታ ይሰማኛል። በሕይወቴ ውስጥ አንድ ነገር የመለወጥ አጋጣሚ ቢኖረኝ ግን ስለ ይሖዋ ቀደም ብዬ አውቄ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር።
በአርጀንቲና እና በብራዚል መካከል በምትገኘው በኡራጓይ በ1927 ተወለድኩ። የአቮካዶ ቅርጽ ያላት ይህቺ አገር በአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ በርካታ ኪሎ ሜትሮች የሚሸፍን ውብ መልክአ ምድር አላት። ከአገሪቱ ዜጎች አብዛኞቹ የጣልያንና የስፔይን ፈላሻዎች ዝርያ ሲሆኑ ወላጆቼ ግን የሃንጋሪ ተወላጆች ናቸው። ያደግሁት ኑሯቸው ዝቅተኛ ቢሆንም ተቀራርበው የሚኖሩ ሰዎች ባሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። በራችንን መቆለፍም ሆነ መስኮታችንን መቀርቀር አያስፈልገንም ነበር። በመካከላችን የዘር ጥላቻ አልነበረም። የባዕድ አገር ሰዎችም ሆኑ የአገሩ ተወላጆች እንዲሁም ጥቁሮችና ነጮች ሁላችንም ተስማምተን እንኖር ነበር።
ወላጆቼ አጥባቂ ካቶሊኮች ነበሩ፤ እኔም 10 ዓመት ሲሆነኝ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማገልገል ጀመርኩ። ካደግሁ በኋላ በአቅራቢያችን ባለው ደብር ውስጥ መሥራት የጀመርኩ ሲሆን ለሃገረ ስብከቱ ጳጳስ አማካሪ የሆነው ቡድን አባል ነበርኩ። በሕክምና መስክ ለመሰማራት ስለመረጥኩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቬኔዙዌላ ውስጥ ባዘጋጀችው ሴሚናር ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩ። እኔ ያለሁበት ቡድን በማሕጸን ሕክምና ላይ የተሰማሩ ዶክተሮችን ያቀፈ በመሆኑ ቡድናችን በወቅቱ ገበያ ላይ በዋሉት የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች ዙሪያ ጥናት እንዲያካሂድ ተመደበ።
የሕክምና ተማሪ ሳለሁ ያደረብኝ ስሜት
የሕክምና ተማሪ ሆኜ ስለ ሰው ልጅ አካል በማጠናበት ጊዜ ጥበብ የተንጸባረቀበት አፈጣጠሩ ያስደምመኝ ነበር። ለአብነት ያህል፣ ሰውነታችን ከባድ ቁስል
ካጋጠመው በኋላ እንደገና ማገገም መቻሉ ያስደንቀኝ ነበር፤ ጉበታችን ወይም አንዳንድ የጎድን አጥንቶቻችን በከፊል ተቆርጠው ከወጡ በኋላም እንኳ እንደገና ወደ ቀድሞው መጠናቸው መመለስ ይችላሉ።በዚሁ ጊዜ፣ ከባድ አደጋ የደረሰባቸው ብዙ ሰዎች ለሕክምና ሲመጡ እመለከት ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ደም በመውሰዳቸው ምክንያት ሲሞቱ ያሳዝነኝ ነበር። ደም በመውሰዳቸው በተፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ ዘመዶቻቸውን በሞት ላጡ ሰዎች ስለ ሁኔታው መንገር ምን ያህል ከባድ እንደነበረ እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ አልጠፋም፤ አብዛኛውን ጊዜ ዘመዶቻቸው የሞቱት ደም ስለተሰጣቸው መሆኑ አይነገራቸውም። ከዚህ ይልቅ ሌሎች ምክንያቶች ይሰጧቸዋል። ይህ ከሆነ በርካታ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ደም መስጠትን በተመለከተ ጥሩ ስሜት እንዳልነበረኝ እስከ አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል፤ በመጨረሻም ይህ የሕክምና ዘዴ አንድ ዓይነት ችግር አለበት ወደሚለው መደምደሚያ ደረስኩ። ይሖዋ ስለ ደም ቅድስና ያወጣውን ሕግ ያን ጊዜ አውቄ ቢሆን ኖሮ ይህንን አሠራር በተመለከተ ጥርጣሬ ያደረብኝ ለምን እንደሆነ ይገባኝ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 15:19, 20
ሰዎችን መርዳት የሚያስገኘው እርካታ
ከጊዜ በኋላ በቀዶ ሕክምና መስክ ተሰማራሁና በሳንታ ሉሲያ በሚገኝ ሆስፒታል ዲሬክተር ሆንኩ። ከዚህም በላይ በናሽናል ኢንስቲትዩት ኦቭ ባዮሎጂካል ሳይንስ ውስጥ እሠራ ነበር። በሙያዬ በጣም እረካ ነበር። ሕመምተኞች ከበሽታቸው እንዲያገግሙ ከመርዳትም በላይ በተደጋጋሚ ጊዜያት የሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ችያለሁ፤ እናቶችንም አዋልድ ነበር። ቀደም ሲል ከገጠመኝ ነገር የተነሳ ሕክምና ሳደርግ ደም መስጠት አልፈልግም ነበር፤ በዚህ ዓይነት በሺዎች የሚቆጠሩ ቀዶ ሕክምናዎች አከናውኛለሁ። ከሰውነታችን ደም ሲፈስስ ሁኔታው ከተቀደደ በርሜል ከሚንጠባጠብ ውኃ ጋር ሊመሳሰል ይችላል የሚል አመለካከት ነበረኝ። ብቸኛው ትክክለኛ መፍትሔ ቀዳዳውን መድፈን እንጂ በርሜሉን መሙላት አይደለም።
የይሖዋ ምሥክሮችን ማከም
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተዋወቅሁት በ1960ዎቹ ዓመታት ሲሆን ይህም የሆነው ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ እኔ ወደምሠራበት ሆስፒታል ሲመጡ ነበር። መርሴቴስ ጎንዛሌዝ የተባለች አንዲት አቅኚ (የሙሉ ጊዜ አገልጋይ) ያጋጠማትን ችግር መቼም አልረሳውም። የደሟ መጠን በጣም ወርዶ ስለነበር በዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል የሚሠሩት ዶክተሮች እንደማትተርፍ ተሰምቷቸው ቀዶ ሕክምና ሊያደርጉላት ፈቃደኛ አልሆኑም። ደም ይፈሳት የነበረ ቢሆንም በምሠራበት ሆስፒታል ውስጥ ቀዶ ሕክምና አደረግንላት። ቀዶ ሕክምናው በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን እርሷም በቅርቡ በ86 ዓመቷ እስካረፈችበት ጊዜ ድረስ ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በአቅኚነት ስታገለግል ቆይታለች።
ምሥክሮቹ ሆስፒታል የተኙ ክርስቲያን ወንድሞቻቸውን ሲያስታምሙ የሚያሳዩት ፍቅርና አሳቢነት ሁልጊዜም ያስገርመኝ ነበር። ታካሚዎችን እየዞርኩ በምጎበኝበት ጊዜ ስለ እምነታቸው ሲናገሩ መስማት ያስደስተኝ የነበረ ሲሆን የሚሰጡኝን ጽሑፎችም እወስድ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሐኪማቸው ከመሆን አልፌ መንፈሳዊ ወንድማቸው እሆናለሁ ብዬ ግን ጨርሶ አላሰበኩም።
ቢያትሪስ የተባለች የአንድ ታካሚዬን ልጅ ሳገባ ደግሞ ከምሥክሮቹ ጋር ያለኝ ዝምድና ተጠናከረ። አብዛኞቹ የቤተሰቧ አባላት የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን ከተጋባን በኋላ እርሷም ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። በሌላ በኩል ደግሞ፣ እኔ በሥራዬ ሙሉ በሙሉ ተጠምጄ የነበረ ከመሆኑም በላይ በሕክምናው መስክ ታዋቂ ሆኜ ነበር። በሕይወቴ ሁሉ ነገር የተሳካልኝ መስሎኝ ነበር። ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር መከራ ይገጥመኛል ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም።
የጤና እክል አጋጠመኝ
አንድ የቀዶ ሕክምና ባለሞያ በሕይወቱ ውስጥ ሊያጋጥሙት ከሚችሉት ነገሮች ሁሉ የከፋው የዓይኑን ብርሃን ማጣት ነው። ይህ ሁኔታ በእኔ ላይ ደረሰ። በድንገት የሬቲና መቀደድ አጋጠመኝና ሁለቱም ዓይኖቼ ታወሩ! እንደገና ማየት መቻሌን ማወቅ የምችልበት መንገድ አልነበረም። ቀዶ ሕክምና ከተደረገልኝ በኋላ ሁለቱም ዓይኖቼ በፋሻ ታስረው መተኛቴ በመንፈስ ጭንቀት እንድዋጥ አደረገኝ። የዋጋ ቢስነትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ስላደረብኝ ሕይወቴን ለማጥፋት ወሰንኩ። ሆስፒታሉ ውስጥ የተኛሁት አራተኛ ፎቅ ላይ ስለነበር ከአልጋዬ ተነስቼ ግድግዳውን እየዳበስኩ መስኮቱን ለማግኘት ሞከርኩ። ከፎቁ ላይ ተወርውሬ ሕይወቴን ላጠፋ አስቤ ነበር። ሆኖም የሄድኩት ወደ ኮሪደሩ ስለነበር አንዲት ነርስ አገኘችኝና ወደ አልጋዬ መለሰችኝ።
በድጋሚ እንደዚህ ለማድረግ አልሞከርኩም። ይሁን እንጂ የዓይኔን ብርሃን ማጣቴ የመንፈስ ጭንቀት እንዲያድርብኝና ግልፍተኛ እንድሆን አደረገኝ። በዚህ ወቅት፣ እንደገና ማየት ከቻልኩ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር እንደማነብበው ለአምላክ ቃል ገባሁ። እያደር የዓይኔ ብርሃን በከፊል ተመለሰና ማንበብ ቻልኩ። ሆኖም የቀዶ ሕክምና ባለሞያ ሆኜ መቀጠል አልቻልኩም። ያም ቢሆን በኡራጓይ የሚነገር አንድ የተለመደ አባባል በሕይወቴ ሲፈጸም ተመልክቻለሁ። “ኖ ሃይ ማል ካ ፖር በየን ኖ ቬንጋ” ይኸውም “አንድ ነገር የቱንም ያህል መጥፎ ቢሆን መልካም ጎን አያጣም” ይባላል። ብዙም ሳይቆይ የዚህን አባባል እውነተኝነት ተመለከትሁ።
መጥፎ ጅምር
በትላልቅ ፊደላት የተዘጋጀውን ዘ ጀሩሳሌም ባይብል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለመግዛት እያሰብሁ ሳለ የይሖዋ ምሥክሮች ዋጋው ከዚያ የሚቀንስ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳላቸው አወቅሁ። አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱሱን እቤቴ ድረስ ሊያመጣልኝ ፈቃደኛ መሆኑን ነገረኝ። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት መጽሐፍ ቅዱሱን ይዞልኝ መጣ። ባለቤቴ በሩን ከፍታ እያነጋገረችው ሳለ እኔ ከውስጥ ሆኜ የመጽሐፍ ቅዱሱን ሒሳብ ከከፈለችው ሁለተኛ ወደ ቤታችን የሚያስመጣ ምንም ጉዳይ ስለሌለው እንዲሄድ በኃይለ ቃል ተናገርኩት፤ እርሱም ወዲያውኑ ቤቱን ጥሎ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ ይኸው ሰው በሕይወቴ ላይ የጎላ ለውጥ እንደሚያመጣ አላወቅሁም ነበር።
አንድ ቀን ለባለቤቴ አንድ ነገር ለማድረግ ቃል ገብቼ መፈጸም ሳልችል ቀረሁ። ጥፋቴን ለማካካስና እርሷን ለማስደሰት ስል በዓመት አንድ ጊዜ ወደሚከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል አብሬያት እንደምሄድ ነገርኳት። ቀኑ ሲደርስ ቃሌን አስታውሼ አብሬያት ወደ በዓሉ ሄድኩ። በበዓሉ ላይ የተመለከትኩት ወዳጃዊ መንፈስና የተደረገልኝ ደግነት የተንጸባረቀበት አቀባበል ልቤን ነካው። ንግግሩን ያቀረበው አክብሮት በጎደለው መንገድ ከቤቴ ያባረርኩት ወጣት መሆኑን ስመለከት ደግሞ ይበልጥ ተገረምኩ። ንግግሩ በጥልቅ የነካኝ ሲሆን ከዚህ ቀደም ስላመናጨቅሁት በጣም አዘንኩ። ይህንን ሰው ልክሰው የምችለው እንዴት ነው?
እራት እንድትጋብዘው ባለቤቴን ጠየቅኋት፤ እርሷ ግን “አንተ ብትጋብዘው የተሻለ አይመስልህም? እዚሁ ቆይ፣ እርሱ ራሱ መጥቶ ያናግረናል” አለችኝ። አልተሳሳተችም፤ ያለንበት ድረስ መጥቶ ሰላም ያለን ሲሆን ያቀረብንለትን የእራት ግብዣም በደስታ ተቀበለ።
እራት በጋበዝነው ምሽት ያደረግነው ውይይት በሕይወቴ ውስጥ ብዙ ለውጦች ለማድረግ አነሳሳኝ። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት a የተባለውን መጽሐፍ አሳየኝ፤ እኔም የይሖዋ ምሥክር የሆኑ የተለያዩ ሕመምተኞች በሆስፒታሉ ውስጥ የሰጡኝን የዚሁ መጽሐፍ ስድስት ቅጂዎች አሳየሁት። ሆኖም መጽሐፉን አንብቤው አላውቅም ነበር። እራት እየበላንና ከዚያም በኋላ ምሽቱን ሁሉ ብዙ ጥያቄዎች የጠየቅሁት ሲሆን እርሱም በመጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም ሁሉንም ጥያቄዎቼን መለሰልኝ። ውይይታችን ከእኩለ ሌሊት በኋላም ቀጠለ። በመጨረሻም እውነት በተባለው መጽሐፍ ተጠቅመን መጽሐፍ ቅዱስን እንድናጠና ሐሳብ አቀረበልኝ። በሦስት ወራት ውስጥ ይህንን መጽሐፍ አጥንተን ጨረስንና “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች!” የአምላክ መንግሥት ትገዛለች!* የተባለውን መጽሐፍ አጠናን። ከዚያም ሕይወቴን ለይሖዋ ወሰንኩና ተጠመቅሁ።
ያደረብኝ የከንቱነት ስሜት ተወገደልኝ
ዓይኖቼ መታወራቸው እስከዚያ ጊዜ ድረስ ችላ ብዬው ለነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ‘የልቤ ዓይኖች’ ኤፌሶን 1:18) ይሖዋንና ፍቅራዊ ዓላማውን ማወቄ መላ ሕይወቴን ለወጠው። እንደገና ጠቃሚ እንደሆንኩ ተሰማኝ፤ ደስታዬም ተመለሰልኝ። በአሁኑ ወቅት ሰዎችን በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ በመርዳት በዚህ ሥርዓት ውስጥ ለተወሰኑ ዓመታት ሕይወታቸውን እንዴት ማራዘም እንደሚችሉ አሳያቸዋለሁ እንዲሁም በአዲሱ ሥርዓት ዘላለማዊ ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባቸው አስተምራቸዋለሁ።
እንዲከፈቱ መንገድ ጠረገ! (በሕክምናው መስክ የሚደረጉ እድገቶችን እከታተላለሁ፤ ደም መውሰድ በሚያስከትላቸው አደጋዎች፣ አማራጭ በሆኑ የሕክምና ዘዴዎች፣ በሕመምተኞች መብት እንዲሁም ባዮኤቲክስ ተብሎ በሚታወቀው የሕክምና ሥነ ምግባር መስክ ጥናት አድርጌያለሁ። በሕክምና ዙሪያ በሚደረጉ ሴሚናሮች ላይ እነዚህን ርዕሶች አስመልክቶ ንግግር እንዳቀርብ ስጋበዝ በጥናቴ ያገኘሁትን ውጤት በአካባቢያችን ለሚኖሩ የሕክምና ባለሞያዎች የማካፈል አጋጣሚ አግኝቻለሁ። በ1994 በሪዮ ዴ ጄኔሮ፣ ብራዚል ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምናን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገ ስብሰባ ላይ ተገኘሁና ደም የሚፈስሳቸውን ሕመምተኞች እንዴት ማከም እንደሚቻል ንግግር አቀረብሁ። በንግግሬ ላይ ካቀረብሁት ሐሳብ ከፊሉ “ዩና ፕሮፕዌስታ:- ኢስትራቴክያስ ፓራ ኢል ትራታሚየንቶ ዲ ላስ ኤሞራኪያስ” (“የደም መፍሰስን ለማስቆም የሚረዱ ዘዴዎች”) በሚል ርዕስ ሄሞቴራፒያ በተባለው የሕክምና መጽሔት ላይ ባወጣሁት ጽሑፍ ውስጥ ይገኛል።
ተጽዕኖ ቢደረግብኝም በአቋሜ ጸናሁ
የሕክምና ሙያዬን በጀመርኩበት ወቅት ደም በመስጠት የሚከናወነውን ሕክምና እንድጠራጠር ምክንያት የሆነኝ በሳይንሱ መስክ ያካበትሁት እውቀት ነበር። እኔ ራሴ ታምሜ ሆስፒታል ስተኛ ግን ዶክተሮች የሚያደርጉብኝን ከፍተኛ ተጽዕኖ ተቋቁሜ ከደም መራቅ ቀላል እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ከባድ የልብ ሕመም አጋጥሞኝ ሕክምና ለማድረግ ሆስፒታል በገባሁበት ወቅት ለአንድ የቀዶ ሕክምና ባለሞያ አቋሜን ለማስረዳት ከሁለት ሰዓት በላይ ፈጅቶብኛል። ዶክተሩ በጣም የምቀርባቸው ወዳጆቼ ልጅ ስለነበረ ደም መውሰድ ሕይወቴን ሊያተርፍልኝ እንደሚችል ከተሰማው ስሞት ዝም ብሎ እንደማይመለከት ነገረኝ። ሐኪሙ በእኔ አመለካከት ባይስማማም አቋሜን እንዲረዳልኝና እንዲያከብርልኝ እንዲረዳው በልቤ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። በመጨረሻ ዶክተሩ ፍላጎቴን ለማክበር ተስማማ።
በሌላ ጊዜ ደግሞ ከፕሮስቴት ዕጢ አካባቢ አንድ ትልቅ እብጠት ለማስወገድ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አስፈለገኝ። ደም ይፈሰኝ ነበር። አሁንም ደም የማልወስድበትን ምክንያት ማስረዳት ነበረብኝ፤ ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው ደሜ ቢፈስስም የሕክምና ቡድኑ አቋሜን አከበረልኝ።
የአመለካከት ለውጥ
ኢንተርናሽናል አሶሲዬሽን ኦቭ ባዮኤቲክስ የተባለው ማኅበር አባል እንደመሆኔ መጠን የሕክምና ባለሞያዎችና የሕግ ባለ ሥልጣናት የሕመምተኞችን መብት በተመለከተ የአመለካከት ለውጥ ሲያደርጉ በመመልከቴ ተደስቻለሁ። ዶክተሮች ታካሚውን እነርሱ የተሻለ በመሰላቸው መንገድ ለማከም ከመሞከር ይልቅ ሕመምተኛው ስለሚሰጠው ሕክምና በቂ መረጃ ተሰጥቶት በራሱ የመወሰን መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ እያመኑ ነው። በአሁኑ ጊዜ ሕመምተኞች የሚሰጣቸውን ሕክምና እንዲመርጡ መፍቀድ ጀምረዋል። የይሖዋ ምሥክሮችም ሕክምና ሊሰጣቸው የማይገባ አክራሪዎች እንደሆኑ ተደርገው መቆጠራቸው እየቀረ ነው። ከዚህ ይልቅ ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ያላቸውና መብታቸው ሊከበርላቸው የሚገባ ታካሚዎች ተደርገው ይታያሉ። በሕክምና ዙሪያ በሚደረጉ ሴሚናሮች እንዲሁም በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ ታዋቂ የሆኑ ፕሮፌሰሮች እንደሚከተሉት ያሉ አስተያየቶች ሲሰጡ ተደምጠዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ላደረጉት ጥረት ምስጋና ይግባቸውና አሁን . . . መገንዘብ ችለናል።” “ከምሥክሮቹ . . . ተምረናል” እንዲሁም “ለውጥ እንድናደርግ አስተምረውናል።”
ሕይወት ከሌለ ነጻነትና ክብር ዋጋ ስለማይኖራቸው ሕይወት ከምንም ነገር በላይ ከፍተኛ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ
ይነገር ነበር። አሁን ግን ከዚህ ላቅ ያለና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ ያለ አመለካከት አለ:- እያንዳንዱ ሰው በመብቶቹ የማዘዝ ነፃነት ያለው ከመሆኑም በላይ ከመብቶቹ መካከል የትኛው ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ መወሰን የሚችለው እርሱ ብቻ ነው። በዚህ መሠረት ክብር፣ የመምረጥ ነፃነትና ሃይማኖታዊ እምነቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል። ሕመምተኛው ጤንነቱን በተመለከተ የራሱን ውሳኔ የማድረግ መብት አለው። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት በርካታ ዶክተሮች በዚህ ረገድ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል።ቤተሰቤ የሚያደርግልኝ ያልተቋረጠ ድጋፍ በይሖዋ አገልግሎት ጠቃሚ ድርሻ እንዳበረክት እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ እንዳገለግል አስችሎኛል። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ስለ ይሖዋ በወጣትነቴ አለማወቄ በጣም ይቆጨኛል። ያም ሆኖ፣ “ታምሜአለሁ” የሚል ሰው በማይኖርበት በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የመኖርን አስደሳች ተስፋ እንዳውቅ ዓይኖቼን ስለከፈተልኝ ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ።—ኢሳይያስ 33:24 b
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
b ወንድም ኤጎን ሃውሰር ይህ ተሞክሮ በመዘጋጀት ላይ እያለ በሞት አንቀላፍቷል። እስከ ዕለተ ሞቱ ታማኝነቱን የጠበቀ ሲሆን አስተማማኝ ተስፋ እንዳለው ማወቃችን ያስደስተናል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ በሳንታ ሉሲያ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ስሠራ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1995 ከባለቤቴ ከቢያትሪስ ጋር