የአምላክ ቃል የብርታት ምንጭ ሆኖልሃል?
የአምላክ ቃል የብርታት ምንጭ ሆኖልሃል?
የሚያጋጥሙህን ችግሮች የምትወጣው እንዴት ነው? ኢየሱስ ሰይጣን ያደረሰበትን ፈተና ሊቋቋም የቻለው ከጉዳዩ ጋር የሚስማማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማስታወሱ ነበር። (ማቴዎስ 4:1-11) በተመሳሳይም ንጉሥ ዳዊት ችግሮች ባጋጠሙት ጊዜ የአምላክ ቃል ምን ያህል እንዳጽናናው ሲናገር “የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት” ብሏል።—መዝሙር 94:19
እኛም ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን አንድ የምንወደውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማስታወሳችን ሊያጽናናን ወይም ሊያበረታታን ይችላል። ለምሳሌ ያህል የ89 ዓመት አረጋዊ የሆኑት ሬክስ ከ1931 ጀምሮ የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ሆነው አገልግለዋል። ሆኖም “ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ አንድ ልዩ ሥራ ሲሰጠኝ ብዙ ጊዜ ለዚህ ኃላፊነት እንደማልበቃ ሆኖ ይሰማኝ ነበር” በማለት ስሜታቸውን ገልጸዋል። ታዲያ እንዲህ ያለውን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም የቻሉት እንዴት ነው? “በምሳሌ 3:5 ላይ የሚገኘውን በጣም የምወደውን ጥቅስ አስታውሳለሁ፤ ጥቅሱ ‘በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ’ ይላል። በዚህ ጥቅስ ላይ ማሰላሰሌና ምክሩን በተግባር ለማዋል መጣሬ የተሰጠኝን ኃላፊነት በሚገባ እንድወጣ ረድቶኛል።”
ትንንሽ ልጆችም እንኳን የሚያስታውሱት ጥቅስ ቢኖር ይጠቀማሉ። የስድስት ዓመቱ ጃክ በጣም የሚወደው ጥቅስ ማቴዎስ 24:14 እንደሆነ ይናገራል። ይህ ጥቅስ ከወላጆቹ ጋር በስብከቱ ሥራ እንዲካፈል ይገፋፋዋል። “ቅዳሜ ቅዳሜ ከእማማ፣ ከአባባና ከእህቴ ጋር ወደ አገልግሎት መሄድ ያስደስተኛል” ሲል ተናግሯል።
ልክ እንደ ኢየሱስ አንተም በእምነትህ ላይ የተሰነዘረ ቀጥተኛ ፈተና ያጋጥምሃል? እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ ፊልጵስዩስ 4:13ን ለማስታወስ ብትሞክር ትጠቀማለህ። እንደ ንጉሥ ዳዊት አንተም “ጭንቀት” ይሰማሃል? ፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ያለብህን ጭንቀት እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ለይሖዋ የምታቀርበው አገልግሎት ከንቱ እንደሆነ ይሰማሃል? ከሆነ 1 ቆሮንቶስ 15:58 ላይ የሚገኘው ሐሳብ የብርታት ምንጭ ይሆንሃል።
ካለንበት ሁኔታ ጋር የሚስማሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በማስታወስ ከአምላክ ቃል ብርታት ማግኘት እንችላለን። (ዕብራውያን 4:12) እንደነዚህ ያሉ ጥቅሶች የብርታት ምንጭ ሊሆኑን እንዲሁም ሊያጽናኑን ይችላሉ።—ሮሜ 15:4