የጥንት ስፖርቶችና ለአሸናፊዎች ይሰጥ የነበረው ክብር
የጥንት ስፖርቶችና ለአሸናፊዎች ይሰጥ የነበረው ክብር
“ለውድድር የሚዘጋጅ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል።” “በውድድር የሚሳተፍ ሰው፣ የውድድሩን ሕግ ጠብቆ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አያገኝም።”—1 ቆሮንቶስ 9:25፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:5
ሐዋርያው ጳውሎስ የጠቀሳቸው ውድድሮች የጥንቱ ግሪካውያን ሥልጣኔ አንዱ ገጽታ ነበሩ። ታሪክ ስለ እነዚህ ውድድሮችና በውድድሮቹ ላይ ይታይ ስለነበረው መንፈስ ምን የሚለው ነገር አለ?
በቅርቡ በሮም ኮሎሲየም ውስጥ የግሪክ ውድድሮችን አስመልክቶ ኒኬ—ኢል ጆኮ ኤ ላ ቪቶርያ (“ኒኬ—ውድድሮቹና ድሉ”) የተሰኘ ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቶ ነበር። a በኤግዚቢሽኑ ላይ ለእይታ የቀረቡት ነገሮች ከላይ ላነሳነው ጥያቄ መልስ የሚሰጡ ከመሆናቸውም በላይ አንድ ክርስቲያን ስፖርትን በተመለከተ ሊኖረው ስለሚገባው አመለካከት እንድናስብ ያደርጉናል።
ጥንታዊ ልማድ
በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ግሪክ የመጀመሪያዋ አገር አይደለችም። ያም ቢሆን በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ የኖረው ግሪካዊው ገጣሚ ሆሜር፣ በወቅቱ የነበረው ኅብረተሰብ ለወታደራዊ ችሎታና ለአትሌቲክስ ውድድር ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጥ እንዲሁም በጀብደኝነት ስሜትና የውድድር መንፈስ የተዋጠ እንደነበረ ጽፏል። በኤግዚቢሽኑ ላይ እንደተገለጸው የጥንቶቹ
የግሪክ ክብረ በዓላት የጀመሩት በጀግኖች የቀብር ሥርዓት ላይ ለአማልክቱ ክብር ለመስጠት ሲባል በሚከናወን ሃይማኖታዊ ዝግጅት መልክ ነበር። ለአብነት ያህል፣ ኢሊያድ የተባለው አሁን በእጅ ከሚገኙት የግሪክ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ ጥንታዊ የሆነው የሆሜር መጽሐፍ የሚሰጠውን መግለጫ እንመልከት። መጽሐፉ የአኪሊዝ ወዳጆች የሆኑ የታወቁ ጦረኞች በፓትሮክለስ የቀብር ሥርዓት ላይ ትጥቃቸውን ፈትተው በቦክስ፣ በነፃ ትግል፣ በዲስክና ጦር ውርወራ እንዲሁም በሠረገላ እሽቅድምድም በመካፈል ጥንካሬያቸውን ለማሳየት እንደተፎካከሩ ይገልጻል።ከጊዜ በኋላ በመላዋ ግሪክ ተመሳሳይ ክብረ በዓላት መከበር ጀመሩ። የኤግዚቢሽኑ ካታሎግ እንዲህ ይላል:- “እነዚህ ክብረ በዓላት ግሪኮች ለአማልክቶቻቸው ባላቸው ክብር በመነሳሳት፣ ማቆሚያ የሌለውና ብዙውን ጊዜ ጠብ የታከለበት ክርክራቸውን ትተው የፉክክር መንፈሳቸውን ሠላማዊ ለሆነ ሆኖም ከዚያ ባልተናነሰ ከፍተኛ ቦታ ለሚሠጠው የአትሌቲክስ ውድድር ለማዋል አጋጣሚ ከፍተውላቸዋል።”
ከተለያዩ ግዛቶች የመጡ ሰዎች በተወሰኑ የአምልኮ ቦታዎች በየጊዜው በመሰባሰብ ለአማልክቶቻቸው ክብር ለመስጠት የአትሌቲክስ ውድድር የማካሄድ ልማድ አዳበሩ። ከጊዜ በኋላ እንደነዚህ ያሉ አራት ክብረ በዓላት ተወዳጅነት እያተረፉ ሄዱና በመላው ግሪክ ይከበሩ ጀመር፤ ዚየስ ለተባለው አምላክ ክብር የኦሎምፒክና የኒሚያ በዓላት ይከበሩ የነበረ ሲሆን አፖሎና ፖሳይደን ለተባሉት አማልክት ክብር ደግሞ የፒቲየንና የኢስሚየን በዓላት ይከበሩ ነበር። በእነዚህ በዓላት ላይ ከመላው ግሪክ የመጡ ተወዳዳሪዎች ይካፈላሉ። በሥነ ሥርዓቱ ላይ መሥዋዕትና ጸሎት ይቀርብ የነበረ ሲሆን ላቅ ያለ የአትሌቲክስ ወይም የሥነ ጥበብ ችሎታቸውን ለማሳየት ውድድር በማካሄድም አማልክቱን ለማክበር ጥረት ይደረግ ነበር።
በ776 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደጀመረ የሚነገርለት ጥንታዊና በጣም ታዋቂ የሆነው የዚህ ዓይነት ክብረ በዓል ለዚየስ ክብር በየአራት ዓመቱ በኦሎምፒያ ይካሄድ የነበረው ነው። ከዚህ ክብረ በዓል ቀጥሎ ሁለተኛ ቦታ የሚሰጠው የፒቲየን በዓል ነበር። በጥንቱ ዓለም በጣም ታዋቂ በሆነው በዴልፋይ በሚገኘው ቤተ መቅደስ አቅራቢያ ይካሄድ የነበረው ይኸኛው ክብረ በዓልም የአትሌቲክስ ውድድርን ያካትት ነበር። የሥነ ግጥምና የሙዚቃ አምላክ ለሆነው ለአፖሎ ክብር ሲባል ይበልጥ ትኩረት ይደረግ የነበረው በሙዚቃና በጭፈራ ላይ ነው።
ውድድሮቹ ምን ይመስሉ ነበር?
ከዘመናዊው የአትሌቲክስ ውድድር ጋር ሲነጻጸር በግሪክ ይካሄዱ የነበሩት ውድድሮች ቁጥር በጣም አነስተኛ ከመሆኑም በላይ የሚካፈሉት ወንዶች ብቻ ነበሩ። በጥንቱ የኦሎምፒክ ጨዋታ በአብዛኛው ከአሥር በላይ ውድድሮች ተካሂደው አያውቁም። በኮሎሲየሙ ቀርበው የነበሩት ሃውልቶች፣ ቅርጻ ቅርጾችና ከሸክላ በተሠሩ የአበባ ማስቀመጫዎች ላይ ያሉት ሥዕሎች እንዲሁም ሌሎች የሥነ ጥበብ ሥራዎች ምን ዓይነት ውድድሮች ይካሄዱ እንደነበረ ያሳያሉ።
የሩጫ ውድድር የሚካሄድበት ርቀት በሦስት ተከፍሎ ነበር፤ ይኸውም 200 ሜትር ገደማ የሚሆን ርቀት የሚሸፍነው ውድድር፣ ዛሬ ከሚካሄደው የ400 ሜትር ሩጫ ጋር ተመጣጣኝ የሆነው የሁለት ዙር ውድድር እንዲሁም ወደ 4,500 ሜትር ገደማ የሚሸፍነው የረዥም ርቀት ሩጫ ናቸው። አትሌቶቹ የሚወዳደሩትም ሆነ ሥልጠና የሚያካሂዱት ሙሉ በሙሉ እርቃናቸውን ሆነው ነበር። ፔንታትለን በሚባለው ስፖርት የሚካፈሉ ተወዳዳሪዎች በአምስት ዓይነት ውድድሮች የሚሳተፉ ሲሆን እነዚህም ሩጫ፣ የርቀት ዝላይ፣ የዲስክና የጦር ውርወራ እንዲሁም ነፃ ትግል ናቸው። “ነፃ ትግልንና ያለ ጓንት የሚደረግ የቦክስ ግጥሚያን አጣምሮ የያዘ ጭካኔ የተሞላበት ስፖርት” ተብሎ የተገለጸውን ፓንክሬሺየም የተባለ ውድድርና ቦክስን የሚያካትቱ ሌሎች ግጥሚያዎችም ነበሩ። ከዚህም በላይ 1,600 ሜትር ርቀት የሚሸፍን የሠረገላ ውድድር ይካሄድ ነበር፤ ከኋላቸው ክፍት የሆኑት እነዚህ ሠረገላዎች ትንንሽ ጎማዎች ያሏቸው ሲሆን በሁለት ወይም በአራት ውርንጭላዎች አሊያም በትላልቅ ፈረሶች ይጎተታሉ።
የቦክስ ግጥሚያዎቹ በጣም አሰቃቂና አንዳንድ ጊዜም ለሞት የሚዳርጉ ነበሩ። ተጋጣሚዎቹ አደገኛ የሆኑ ብረቶች የተሰኩበት የደረቀ ቆዳ እጃቸው ላይ ያስራሉ። ስትራቶውፎንቴ የተባለ አንድ ቦክሰኛ ከአራት ሰዓታት ግጥሚያ በኋላ የገዛ ፊቱን በመስታወት ተመልክቶ ማወቅ የተሳነው
ለምን እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ጥንታዊ ሃውልቶችና የሥነ ጥበብ ሥራዎች ቦክሰኞች ዘግናኝ በሆነ መልኩ ገጽታቸው ይበላሽ እንደነበረ ይመሰክራሉ።በነፃ ትግል ላይ ተጋጣሚዎቹ መያዝ የሚችሉት ከወገብ በላይ ያለውን የሰውነት ክፍል ብቻ እንደሆነ ሕጉ የሚደነግግ ሲሆን አሸናፊ የሚባለውም ተጋጣሚውን ቀድሞ ሦስት ጊዜ መዘረር የቻለው ነው። ከዚህ በተቃራኒ ፓንክሬሺየም በተባለው ግጥሚያ ተፋላሚዎች የትኛውንም የሰውነት ክፍል መያዝ ይችላሉ። መራገጥ፣ በቡጢ መምታት እንዲሁም መገጣጠሚያዎችን ማውለቅ የሚችሉ ሲሆን ክልክል የሆነው ዓይን ማውጣት፣ መቧጠጥ ወይም መንከስ ብቻ ነበር። የግጥሚያው ዓላማ ተፋላሚውን መሬት ላይ በመጣል እንዳይንቀሳቀስ ማድረግና መሸነፉን እንዲያምን ማስገደድ ነው። አንዳንዶች ይህ ግጥሚያ “በኦሎምፒያ ከሚታዩት [ውድድሮች] ሁሉ ይበልጥ ማራኪ” እንደሆነ ይሰማቸው ነበር።
በ564 ከክርስቶስ ልደት በፊት በኦሎምፒክ የፍጻሜ ውድድር ላይ የተካሄደው የፓንክሬሺየም ግጥሚያ በጥንቱ ዓለም ከተካሄዱት የዚህ ዓይነት ግጥሚያዎች ሁሉ ታዋቂ እንደሆነ ይነገራል። በተጋጣሚው ታንቆ ሊሞት እያጣጣረ የነበረው አራሂኦን የተባለ ሰው በዚያ ሁኔታ ላይ እያለም እንኳ የተጋጣሚውን የእግር ጣት ማውለቅ ችሎ ነበር። ሥቃዩን መቋቋም ያቃተው ተጋጣሚ አራሂኦን ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ መሸነፉን አመነ። በዳኞቹ ውሳኔ መሠረት አሸናፊው የአራሂኦን አስከሬን ነበር!
በሥርዓቱ ላይ ከሚታዩት ውድድሮች ሁሉ የሠረገላ ውድድር የላቀ ግምት ይሰጠው ነበር፤ አሸናፊ የሚባለው ሠረገላውን የነዳው ሰው ሳይሆን የሠረገላውና የፈረሶቹ ባለቤት በመሆኑ ባላባቶቹ ይህን ውድድር በጣም ይወዱታል። በውድድሩ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ከሚደረግባቸው ቦታዎች አንዱ የውድድሩ መነሻ ሲሆን በዚህ ወቅት ሠረገላዎቹ ከመስመራቸው መውጣት የለባቸውም። ከዚያ በበለጠ ትኩረት የሚደረግበት ሌላው ቦታ ደግሞ በእያንዳንዱ ዙር ኩርባዎች ላይ ነው። የውድድሩን ደንብ መጣስ ወይም ስህተት መሥራት አደጋ ሊያስከትል የሚችል ሲሆን ይህም ውድድሩን ይበልጥ ማራኪ ያደርገዋል።
ለአሸናፊዎች የሚሰጠው ሽልማት
ሐዋርያው ጳውሎስ “በሩጫ ውድድር የሚሮጡ ብዙዎች እንደሆኑ፣ ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ እንደ ሆነ አታውቁምን?” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 9:24) ማሸነፍ ብቸኛው አማራጭ ነበር። ሁለተኛና ሦስተኛ የወጡት ተወዳዳሪዎች ምንም ሽልማት አይሰጣቸውም፤ የብርም ሆነ የነሐስ ሜዳልያ አልነበረም። በኤግዚቢሽኑ ላይ እንደተገለጸው “የአትሌቶቹ ዋነኛ ፍላጎት ድል ማድረግ ወይም ‘ናይክ’ ነበር። የአትሌቱን አካላዊም ሆነ ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬ የሚያንጸባርቀውና የአገሩ መኩሪያ የሚያደርገው [ድል ማድረጉ] በመሆኑ ይህ ብቻውን በቂ ነበር።” ከሆሜር መጽሐፍ የተወሰደው “ምንጊዜም ቢሆን ልቆ መገኘትን ተምሬያለሁ” የሚለው ሐረግ በወቅቱ የነበረውን አመለካከት ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል።
በግሪክ በሚካሄዱት ውድድሮች ለአሸናፊው ይሰጥ የነበረው ከቅጠል የተሠራ አክሊል አሸናፊነቱን ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም። ጳውሎስ ይህን አክሊል ‘ዐላፊ ጠፊ’ በማለት ጠርቶታል። (1 ቆሮንቶስ 9:25) ሆኖም ሽልማቱ ለአሸናፊው ተፈጥሮ የለገሰችውን ኃይል ስለሚያመለክት ጥልቅ ትርጉም ነበረው። ሙሉ ትኩረታቸውን በውድድሩ ላይ በማድረግ የሚያገኙት ድል መለኮታዊ ሞገስ እንደማግኘት ተደርጎ ይቆጠራል። በጥንት ዘመን የነበሩ የቅርጻ ቅርጽ ሠራተኞችና ሠዓሊዎች ናይክ የተባለችው ባለ ክንፍ የድል አምላክ በአሸናፊው ላይ አክሊሉን እንደምታኖር ያስቡ እንደነበረ የሚያሳዩ ሥዕሎች በኤግዚቢሽኑ ላይ ቀርበው ነበር። በኦሎምፒያ ማሸነፍ ለአንድ አትሌት በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር።
ለኦሎምፒክ ውድድር አክሊሎች የሚሠሩት በዱር ከሚበቅል የወይራ ቅጠል ነው፤ ለኢስሚየን ውድድር ከጥድ፣ ለፒቲየን ከሎረል ቅጠል እንዲሁም ለኒሚያ ከሾርባ ቅጠል የተሠሩ አክሊሎች ይቀርቡ ነበር። በሌሎች ቦታዎች የውድድሮቹ አዘጋጆች ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ተወዳዳሪዎች
ለመማረክ ሲሉ ገንዘብ ወይም ሌሎች ሽልማቶች ያዘጋጁ ነበር። በኤግዚቢሽኑ ላይ ለእይታ የቀረቡ በርካታ የአበባ ማስቀመጫዎች አቴና ለተባለችው አምላክ ክብር በአቴንስ በተካሄዱ የፓናቲኔእክ ውድድሮች ላይ የተሰጡ ሽልማቶች ነበሩ። እነዚህ ሁለት እጀታ ያላቸው ገንቦዎች በወቅቱ ውድ የሆነ የአቲክ የወይራ ዘይት ተቀምጦባቸው ነበር። ከእነዚህ የአበባ ማስቀመጫዎች አንዱ በአንድ ጎኑ የአቴና ምስል የተሳለበት ሲሆን “በአቴና ስም በተካሄዱ ውድድሮች ላይ የተሰጠ ሽልማት” የሚል ጽሑፍ ሰፍሮበታል። የገንቦው ሌላኛው ወገን አንድ ዓይነት ውድድር፣ በተለይም ተወዳዳሪው ያሸነፈበትን ግጥሚያ የሚያሳይ ሥዕል አለው።ድል አድራጊዎቹ አትሌቶች በትውልድ መንደራቸው ውስጥ እንደ ጀግኖች ይታዩ የነበረ ሲሆን ዝናቸው ከራሳቸው አልፎ ለሚኖሩበት ከተማም ይተርፍ ነበር። አሸናፊዎቹ ሲመለሱ ታላቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል። በግሪኮች ዘንድ የተለመደ ባይሆንም ለአማልክቱ የምስጋና መሥዋዕት እንዲሆን ሲባል ለአሸናፊዎቹ ክብር ሃውልት ይቆምላቸዋል። ከዚህም በላይ ገጣሚዎች ስለ ጀግንነታቸው እያነሱ በዘፈን ያወድሷቸዋል። ከዚያ በኋላም አሸናፊዎች በሕዝባዊ ዝግጅቶች ላይ የከበሬታ ቦታ ይሰጣቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ በሕዝቡ ወጪ ድጎማ ይደረግላቸዋል።
ጂምናዚየሞችና በዚያ የሚሠለጥኑ አትሌቶች
ለአገሪቷ ወታደሮች በማሰልጠን ረገድ የአትሌቲክስ ውድድር የጎላ ድርሻ እንዳለው ይታሰብ ነበር። ሁሉም የግሪክ ከተሞች ለወጣት ወንዶች የቀለምና ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን የሚያካትት የአካል ብቃት ሥልጠና የሚሰጥበት ጂምናዚየም ነበራቸው። ጂምናዚየሞቹ የሚሠሩት ልምምድ ለማድረግ በሚያመቹ ሰፊ ቦታዎች ሲሆን ዙሪያውን እንደ ቤተ መጻሕፍትና የመማሪያ ክፍል ሊያገለግሉ የሚችሉ በረንዳዎች ይኖራሉ። ከማንም በላይ ወደነዚህ ተቋማት አዘውትረው የሚሄዱት ሃብታም ወላጆች ያሏቸው ወጣት ወንዶች ነበሩ፤ እነዚህ ወጣቶች መተዳደሪያ ለማግኘት መሥራት ስለማያስፈልጋቸው ለትምህርት የሚያውሉት ጊዜ ያገኛሉ። በዚህ ቦታ አትሌቶቹ በአሠልጣኞቻቸው እየታገዙ ለበርካታ ሰዓታት ከፍተኛ ልምምድ የሚያደርጉ ሲሆን አሠልጣኞቹም የአትሌቶቹን አመጋገብና ከጾታ ግንኙነት መታቀባቸውን ሳይቀር ይቆጣጠራሉ።
በኮሎሲየሙ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ የጥንቶቹን አትሌቶች የሚያመለክቱ ግሩም ቅርጻ ቅርጾች ቀርበው ነበር፤ ከእነዚህ አብዛኞቹ ሮማውያን ግሪካውያኑ መጀመሪያ የሠሩትን አስመስለው የቀረጿቸው ናቸው። በጥንቱ የግሪክ ዓለም የላቀ አካላዊም ሆነ ሥነ ምግባራዊ አቋም የማይነጣጠሉ እንደሆኑ ይታሰብ የነበረ ከመሆኑም በላይ የዚህ ዓይነት ብቃት የሚኖራቸው የገዥው መደብ አባላት ብቻ ናቸው፤ በመሆኑም የተስተካከለ ቁመና ያላቸው እነዚህ ድል አድራጊ አትሌቶች ፍጹም ተብሎ ለሚታሰበው የሰውነት አቋም መለኪያ እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር። ብዙውን ጊዜ ስታዲየሞችን፣ መታጠቢያ ቤቶችን፣ መኖሪያ ቤቶችንና ቤተ መንግሥቶችን የሚያስውቡትን እነዚህን ቅርጻ ቅርጾች ሮማውያን በሥነ ጥበብ ሥራነታቸው ያደንቋቸው ነበር።
ሮማውያን ምን ጊዜም ቢሆን ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ትርዒት ይስባቸው ነበር፤ በዚህም የተነሳ ሮም ውስጥ ከቀረቡት የግሪክ ውድድሮች ሁሉ ከፍተኛ ተደናቂነት ያተረፉት ቦክስ፣ ነፃ ትግልና ሁለቱን አጣምሮ የያዘው ፓንክሬሺየም የተባለው ግጥሚያ ነበሩ። ሮማውያን እነዚህን ስፖርቶች እንደ ተራ መዝናኛ እንጂ እኩል ችሎታ ባላቸው ተጋጣሚዎች መካከል ብቃታቸውን ለመመዘን እንደሚደረግ ፍልሚያ አልተመለከቷቸውም። ስፖርት ምርጥ ጦረኛ የሆኑ አትሌቶች ብቻ የሚካፈሉበትና ከሚሰጣቸው ሥልጠና ጋር የሚካተት ውድድር መሆኑ ቀረ። ሮማውያን የግሪካውያኑን ውድድር ሰውነታቸውን ከመታጠባቸው በፊት ለጤንነት በሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ተራ የሆነው የኅብረተሰቡ ክፍል በተመልካቾች ፊት በሚያቀርበው እንደ ግላዲያተር ያለ ውድድር በመተካት ደረጃውን አሳነሱት።
ክርስቲያኖች ለውድድሮቹ የነበራቸው አመለካከት
በመጀመሪያ መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ከእነዚህ ውድድሮች እንዲርቁ ካደረጓቸው ነገሮች አንዱ ውድድሮቹ ከአምልኮ ጋር የተዛመዱ መሆናቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖታት ጋር ምን ስምምነት አለው?” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 6:14, 16) ዛሬ ስላሉት ስፖርቶችስ ምን ማለት ይቻላል?
ዘመናዊ ስፖርቶች የሚካሄዱት ለአረማዊ አማልክት ክብር ለመስጠት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ያም ሆኖ አንዳንድ ስፖርቶች በጥንቶቹ ዓለም ከነበረው ሁኔታ ጋር ሊመሳሰል የሚችል ከሃይማኖታዊ ስሜት ያልተለየ መንፈስ ይንጸባረቅባቸው የለም? ከዚህም በላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አንዳንድ አትሌቶች ለማሸነፍ ሲሉ ጤንነታቸውንና ሕይወታቸውን ጭምር ለአደጋ በማጋለጥ ኃይል የሚሰጡ መድኃኒቶችን ይወስዳሉ።
ክርስቲያኖች በስፖርታዊ ውድድሮች ለሚገኝ ስኬት ትልቅ ቦታ አይሰጡም። በአምላክ ፊት የሚያስውቡን ‘ከውስጣዊው ሰው’ የሚመነጩ መንፈሳዊ ባሕርያት ናቸው። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4) በስፖርት የሚካፈሉ ሁሉ የጋለ የፉክክር መንፈስ እንደማያንጸባርቁ ብንገነዘብም አብዛኞቹ ግን እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ እንዳላቸው እናውቃለን። ከእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር መቀራረብ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቁጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ያስችለናል? ደግሞስ እንዲህ ዓይነቱ ቅርርብ “ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት” አይፈጥርም?—ፊልጵስዩስ 2:3፤ ገላትያ 5:19-21
ተጫዋቾች እርስ በርስ በሚነካኩባቸው በብዙዎቹ ዘመናዊ ስፖርቶች ላይ የኃይል ድርጊት ለመፈጸም የሚያስችል አጋጣሚ ይኖራል። እንደዚህ ያሉት ስፖርቶች የሚማርኩት ማንኛውም ሰው በመዝሙር 11:5 ላይ የሰፈሩትን ቃላት ልብ ማለቱ ጥሩ ይሆናል:- “እግዚአብሔር ጻድቁንና ኀጥኡን ይመረምራል፤ ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች።”
የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በተገቢው ቦታ የምናስቀምጠው ከሆነ አስደሳች ሊሆንልን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስም “የአካል ብቃት ልምምድ ለጥቂት ነገር ይጠቅማል” ብሏል። (1 ጢሞቴዎስ 4:7-10) ይሁን እንጂ ጳውሎስ በግሪክ ስለሚካሄዱት ውድድሮች የጠቀሰው ክርስቲያኖች ራስን እንደ መግዛትና ጽናት ያሉትን ባሕርያት ማዳበራቸው ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ለማጉላት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ከምንም ነገር በላይ ለማግኘት ይጥር የነበረው አምላክ የሚሰጠውን “አክሊል” ማለትም የዘላለም ሕይወትን ነው። (1 ቆሮንቶስ 9:24-27፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:12) በዚህ ረገድ ልንከተለው የሚገባ አርአያ ሆኖናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኒኬ የሚለው የግሪክኛ ቃል “ድል” ማለት ነው።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ከግጥሚያ በኋላ
በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የተሠራው ይህ የነሐስ ቅርጽ በጥንት ዘመን ይካሄዱ የነበሩ የቦክስ ግጥሚያዎች ምን ያህል ከባድ ጉዳት ያደርሱ እንደነበረ ያሳያል። በሮም የቀረበው ኤግዚቢሽን ካታሎግ እንደሚገልጸው “አድካሚ በሆነው ግጥሚያ ላይ ቦክሰኛው የደረሰበትን ‘ቁስል፣ በቁስል’ በመመለስ . . . እስከ መጨረሻው መፋለሙ እንደ ጀግና ያስቆጥረዋል።” ካታሎጉ “ከዚህ ቀደም በተደረገው ግጥሚያ ላይ የደረሰበት ጉዳት አሁን ባደረገው ግጥሚያ ይባባሳል” ይላል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሠረገላ ውድድር በጥንት ጊዜ ይካሄዱ ከነበሩት ውድድሮች ሁሉ በጣም ተወዳጅ ነበር
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥንት ሠዓሊዎች ናይክ የተባለችው ባለ ክንፍ የድል አምላክ ለአሸናፊው አክሊል እንደምታደርግለት ያስቡ ነበር