በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ረጅምና አስደሳች ሕይወት የመኖር ምሥጢር

ረጅምና አስደሳች ሕይወት የመኖር ምሥጢር

ረጅምና አስደሳች ሕይወት የመኖር ምሥጢር

‘ማንም ሰው ቢሆን በዕድሜ እያደገ መሄድ ይፈልጋል፤ ማንም ግን ማርጀት አይፈልግም’ የሚል አባባል አለ። ብዙ ሰዎች የጡረታ ዕድሜያቸው ሲቃረብ ወደፊት ሰፊ ጊዜ እንደሚያገኙና ኃላፊነት እንደሚቀነስላቸው ተስፋ ያደርጋሉ። ሆኖም ዓላማ የለሽና ለማኅበረሰቡ ምንም የማይጠቅሙ እንዳይሆኑ ይፈራሉ። እንዲሁም ብቸኝነቱ፣ ደስታ ማጣቱና የጤንነታቸው ማሽቆልቆልም ያሳስባቸዋል።

ታዲያ ደስተኛ ሕይወት ለመኖር ምሥጢሩ ምንድን ነው? አረጋውያንም ሆኑ ወጣቶች ጥሩ ጓደኞችና አፍቃሪ ቤተሰብ ካላቸው ደስተኛ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ አንድን በዕድሜ የገፋ ሰው ደስተኛ የሚያደርገው ሌሎች ለእርሱ የሚያደርጉለት ነገር ብቻ አይደለም። የበለጠ ቦታ ያለው እርሱ ራሱ ለሌሎች ሊያደርገው የሚችለው ነገር ነው።

በዕድሜ በገፉ 423 ጥንዶች ላይ ረዘም ላለ ጊዜ የተካሄደ አንድ ጥናት “ለሌሎች ሰዎች ጠቃሚ ነገር ማከናወን ሕይወታችንን ለማራዘም አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ” ይጠቁማል። ጥናቱን ያካሄደችው ስቴፋኒ ብራውን እንዲህ ትላለች:- “ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ይበልጥ ጠቃሚ የሚያደርገው ከግንኙነቱ የምናተርፈው ሳይሆን እኛ ለሌሎች የምንሰጠው ነገር ነው።” መስጠት ሲባል ሌሎችን በቤት ውስጥ ሥራ መርዳትን፣ ልጆችን መንከባከብን፣ መላላክንና፣ በመጓጓዣ መርዳትን እንዲሁም የልቡን አውጥቶ መናገር የሚፈልግን ሰው ማዳመጥን የሚጨምር ሊሆን ይችላል።

የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ ኢየሱስ ክርስቶስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ብሎ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ረጅምና ደስተኛ ሕይወት የመኖር ምሥጢሩ በባንክ ብዙ ገንዘብ ማጠራቀም፣ እርጅናን ለመከላከል የሚሰጡ ሕክምናዎችን መከታተል ወይም የአመጋገብ ለውጥ ማድረግ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጠመድ እንዲሁም ጊዜንና ጉልበትን የሌሎችን ሕይወት አስደሳች ለማድረግ ማዋል ናቸው።

ሆኖም እርጅናን፣ ሕመምንና ሞትን ለማስቀረት ከዚህ የበለጠ ነገር ይጠይቃል። እነዚህን ችግሮች ሊያስወግድ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ሕመም የሚወገድ ሲሆን ከዚያ ወዲያ ‘ሞት አይኖርም።’ (ራእይ 21:3, 4፤ ኢሳይያስ 33:24) እንዲያውም ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ይኖራሉ። (ሉቃስ 23:43) የይሖዋ ምሥክሮች ረጅምና ደስተኛ ሕይወት ለመኖር የሚያስችለውን ይህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምሥጢር ለሰዎች ለማካፈል ፈቃደኞች ናቸው።