በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አረጋውያንን መንከባከብ—ክርስቲያናዊ ኃላፊነት ነው

አረጋውያንን መንከባከብ—ክርስቲያናዊ ኃላፊነት ነው

አረጋውያንን መንከባከብ—ክርስቲያናዊ ኃላፊነት ነው

“እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣ የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ።”—ኢሳይያስ 46:4

1, 2. ሰማያዊ አባታችን የሚያደርገው እንክብካቤ ከሰብዓዊ ወላጆች የሚለየው በምንድን ነው?

 አፍቃሪ ወላጆች ልጆቻቸውን ከሕፃንነታቸው አንስቶ ጉርምስና ዕድሜ ላይ እስከሚደርሱበት ጊዜ ድረስ እየተንከባከቡ ያሳድጓቸዋል። ልጆቹ አድገው የራሳቸውን ጎጆ ከመሠረቱ በኋላም እንኳ ወላጆቻቸው ፍቅራዊ እንክብካቤና ድጋፍ ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ።

2 ወላጆች ለልጆቻቸው ማድረግ የሚፈልጉትን ሁሉ ለማድረግ አቅም የሌላቸው ቢሆንም ሰማያዊ አባታችን ምንጊዜም ለታማኝ አገልጋዮቹ ፍቅራዊ እንክብካቤና ድጋፍ ማድረግ ይችላል። ይሖዋ ጥንት ስለነበሩት ምርጥ ሕዝቦቹ ሲናገር “እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣ የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ” ብሏል። (ኢሳይያስ 46:4) እነዚህ ቃላት በዕድሜ ለገፉ ክርስቲያኖች ምንኛ የሚያበረታቱ ናቸው! ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን አይተዋቸውም። እንዲያውም በሕይወታቸው ሁሉ ሌላው ቀርቶ በእርጅና ዘመናቸውም እንኳ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያደርግላቸው፣ እንደሚደግፋቸውና እንደሚመራቸው ቃል ገብቷል።—መዝሙር 48:14

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ለአረጋውያን ፍቅራዊ እንክብካቤ በማድረግ ረገድ የይሖዋን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? (ኤፌሶን 5:1, 2) ልጆች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችና ሌሎች ክርስቲያኖች በዕድሜ ለገፉ የዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር አባላት አሳቢነት ማሳየት የሚችሉባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

የልጆች ኃላፊነት

4. ክርስቲያን የሆኑ ልጆች ለወላጆቻቸው ምን ኃላፊነት አለባቸው?

4 “አባትህንና እናትህን አክብር።” (ኤፌሶን 6:2፤ ዘፀአት 20:12) ሐዋርያው ጳውሎስ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በወሰዳቸው በእነዚህ አጭር ሆኖም ከፍተኛ ትርጉም ያዘሉ ቃላት አማካኝነት ልጆች ለወላጆቻቸው ምን ኃላፊነት እንዳለባቸው አስታውሷቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ቃላት ወላጆችን ከመንከባከብ ጋር ምን ግንኙነት አላቸው? ከቅድመ ክርስትና በፊት የተፈጸመን አንድ ታሪክ መመልከታችን የዚህን ጥያቄ መልስ እንድናገኝ ይረዳናል።

5. (ሀ) ዮሴፍ ልጅ መሆኑ ያስከተለበትን ኃላፊነት እንዳልዘነጋ የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) ወላጆቻችንን ማክበር ሲባል ምን ማለት ነው? በዚህ ረገድ ዮሴፍ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?

5 ዮሴፍ ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ከአረጋዊ አባቱ ከያዕቆብ ተለይቶ ኖሯል። ይሁን እንጂ፣ ዮሴፍ ለያዕቆብ የነበረው የልጅነት ፍቅር እንዳልቀዘቀዘ ግልጽ ነው። እንዲያውም ለወንድሞቹ እውነተኛ ማንነቱን በገለጠላቸው ጊዜ “ለመሆኑ አባቴ እስካሁን በሕይወት አለ?” በማለት ጠይቋቸዋል። (ዘፍጥረት 43:7, 27፤ 45:3) በዚያን ጊዜ በከነዓን ምድር ረሃብ ገብቶ ስለነበር ዮሴፍ እንዲህ ሲል ወደ አባቱ መልእክት ላከ “ሳትዘገይ ወደ እኔ ና። . . . በአቅራቢያዬ በጌሤም ትኖራለህ። . . . የሚያስፈልጋችሁን እኔ እሰጣችኋለሁ።” (ዘፍጥረት 45:9-11፤ 47:12) አዎን፣ በዕድሜ የገፉ ወላጆችን ማክበር ለእነርሱ ጥበቃ ማድረግንና ራሳቸውን መርዳት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን መስጠትን ይጨምራል። (1 ሳሙኤል 22:1-4፤ ዮሐንስ 19:25-27) ዮሴፍ ይህን ኃላፊነት በደስታ ተቀብሏል።

6. ዮሴፍ ለአባቱ የነበረውን እውነተኛ ፍቅር የገለጸው እንዴት ነበር? የእርሱን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለውስ እንዴት ነው?

6 ዮሴፍ ይሖዋ ስለባረከው በግብፅ ከፍተኛ ሀብትና ሥልጣን ከነበራቸው ሰዎች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል። (ዘፍጥረት 41:40) ይሁን እንጂ ትልቅ ቦታ ላይ ስላለ የ130 ዓመት አባቱን ማክበር እንደማይጠበቅበት ወይም ለእርሱ የሚሆን ጊዜ እንደሌለው ሆኖ አልተሰማውም። ያዕቆብ (ወይም እስራኤል) ወደ እርሱ እየመጣ እንደሆነ ሲሰማ “ዮሴፍ ሠረገላውን አዘጋጅቶ፤ አባቱን እስራኤልን ለመቀበል ወደ ጌሤም አመራ። ዮሴፍ አባቱ ዘንድ እንደ ደረሰ፣ ዐንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ለረጅም ጊዜ አለቀሰ።” (ዘፍጥረት 46:28, 29) እንዲህ ያለው አቀባበል ከተለመደው የአክብሮት መግለጫ የበለጠ ነበር። ዮሴፍ አረጋዊ አባቱን በጣም ይወደው ስለነበር ፍቅሩን ለመግለጽ አላፈረም። እኛስ በዕድሜ የገፉ ወላጆች ካሉን ፍቅራችንን ያለምንም ይሉኝታ እንገልጽላቸዋለን?

7. ያዕቆብ በከነዓን ለመቀበር የፈለገው ለምን ነበር?

7 ያዕቆብ ለይሖዋ የነበረው ፍቅር እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ አልቀዘቀዘም። (ዕብራውያን 11:21) አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ስለነበረው አስከሬኑ በከነዓን እንዲቀበር ጠየቀ። ዮሴፍ ከፍተኛ ወጪና ጉልበት የሚጠይቅ ቢሆንም አባቱ የጠየቀውን በማድረግ አክብሮታል።—ዘፍጥረት 47:29-31፤ 50:7-14

8. (ሀ) በዕድሜ የገፉ ወላጆቻችንን እንድንንከባከብ የሚገፋፋን ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በዕድሜ የገፉ ወላጆቹን ለመንከባከብ ምን አደረገ? (በገጽ 17 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)

8 ዮሴፍ አባቱን እንዲንከባከብ የገፋፋው ምን ነበር? ለወለደውና ተንከባክቦ ላሳደገው አባቱ የነበረው ፍቅር እንዲሁም የእርሱን ውለታ ለመመለስ የነበረው ፍላጎት ከግምት መግባት ያለባቸው ምክንያቶች ቢሆኑም ይሖዋን የማስደሰት ልባዊ ምኞት እንደነበረው አያጠራጥርም። እኛም ተመሳሳይ ፍላጎት ሊያድርብን ይገባል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል “አንዲት መበለት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሯት፣ እነዚህ ልጆች የራሳቸውን ቤተ ሰብ በመርዳትና ለወላጆቻቸውም ብድራትን በመመለስ ከሁሉ በፊት እምነታቸውን በተግባር ለማሳየት መማር ይገባቸዋል፤ ይህ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነውና።” (1 ጢሞቴዎስ 5:4) በእርግጥም ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንብን ለይሖዋ ያለን ፍቅርና አክብሮታዊ ፍርሃት በዕድሜ የገፉ ወላጆቻችንን እንድንንከባከብ ይገፋፋናል። a

የጉባኤ ሽማግሌዎች አሳቢነታቸውን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

9. ይሖዋ አረጋዊ ክርስቲያኖችን ጨምሮ መንጋውን ለመጠበቅ ማንን ሾሟል?

9 ረጅም ዕድሜ የኖረው ያዕቆብ በሕይወቱ ማገባደጃ ላይ “ለእኔም እስከ ዛሬ ድረስ በዘመኔ ሁሉ እረኛ የሆነኝ አምላክ” በማለት ስለ ይሖዋ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 48:15) ዛሬም ይሖዋ “የእረኞች አለቃ” በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር ባሉ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ወይም ሽማግሌዎች አማካኝነት ምድራዊ አገልጋዮቹን ይጠብቃል። (1 ጴጥሮስ 5:2-4) የበላይ ተመልካቾች በዕድሜ ለገፉ የመንጋው አባላት አሳቢነት በማሳየት ረገድ የይሖዋን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?

10. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖችን ለመርዳት ምን ዝግጅት ተደርጎ ነበር? (በገጽ 19 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

10 የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያት ችግር ላይ ለወደቁ መበለቶች ‘በየዕለቱ የሚከናወነውን የምግብ እደላ’ የሚከታተሉ “በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው የተመሰከረላቸውን ሰባት ሰዎች” ሾመው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 6:1-6) በኋላም ጳውሎስ ቁሳዊ እርዳታ ከሚደረግላቸው ክርስቲያኖች ዝርዝር ውስጥ ምሳሌ የሚሆኑ በዕድሜ የገፉ መበለቶችን እንዲጨምር የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግል የነበረውን ጢሞቴዎስን አሳስቦት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 5:3, 9, 10) ዛሬም በተመሳሳይ የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በዕድሜ ለገፉ ክርስቲያኖች ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት በፈቃደኝነት ዝግጅት ያደርጋሉ። ሆኖም፣ በዕድሜ ለገፉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች አሳቢነት ማሳየት ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠይቃል።

11. ኢየሱስ በመዋጮ ሣጥን ውስጥ አነስተኛ ገንዘብ ስለከተተችው ድኻ መበለት ምን አለ?

11 ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ በቤተ መቅደሱ ተቀምጦ “ብዙ ሰዎች ስጦታቸውን ወደ ቤተ መቅደሱ ገንዘብ ማስቀመጫ ሣጥን ሲያስገቡ ይመለከት” ጀመር። በዚያ ጊዜ አንዲት አረጋዊት ሴት ትኩረቱን ሳበችው። ዘገባው “አንዲት ምስኪን መበለት ግን ከአንድ ሳንቲም የማይበልጡ ሁለት የናስ ቤሳዎች አስገባች” ይላል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህቺ ድኻ መበለት ሣጥኑ ውስጥ ከጣሉት ከሌሎቹ የበለጠ አስገባች። እነዚህ ሁሉ ከተረፈው ሀብታቸው ሰጡ፤ እርሷ ግን በድኽነት ዐቅሟ ያላትን ሁሉ አውጥታ ለመኖሪያ የሚሆናትን እንዳለ ሰጠች።” (ማርቆስ 12:41-44) በገንዘብ ደረጃ ከታየ መበለቷ የጣለችው አነስተኛ ነው፤ ሆኖም ኢየሱስ በሰማይ የሚኖረው አባቱ በሙሉ ነፍስ የቀረበን የፍቅር መግለጫ ምን ያህል በአድናቆት እንደሚመለከት ያውቅ ነበር። ድኻዋ መበለት ዕድሜዋ የቱንም ያህል የገፋ ቢሆን ኢየሱስ ያደረገችውን አቅልሎ አልተመለከተውም።

12. ሽማግሌዎች በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ያላቸውን አድናቆት መግለጽ የሚችሉት እንዴት ነው?

12 እንደ ኢየሱስ ሁሉ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችም አረጋውያን እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ጥረት አቅልለው አይመለከቱትም። ሽማግሌዎች፣ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች በመስክ አገልግሎትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስለሚያደርጉት ተሳትፎ እንዲሁም በጉባኤው ላይ ስለሚያሳድሩት በጎ ተጽዕኖና ስለጽናታቸው ሊያመሰግኗቸው ይችላሉ። ከልብ የመነጨ ማበረታቻ አረጋውያን በሚያቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ‘የሚመኩበት ነገር እንዲያገኙ’ ሊረዳቸው ይችላል። ይህም ራሳቸውን ከሌሎች ክርስቲያኖች ወይም እነርሱ ራሳቸው በፊት ያደርጉት ከነበረው ጋር እያወዳደሩ ተስፋ እንዳይቆርጡ ይረዳቸዋል።—ገላትያ 6:4

13. ሽማግሌዎች በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ካላቸው ተሰጥኦና ተሞክሮ መጠቀም የሚችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

13 የጉባኤ ሽማግሌዎች በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ካላቸው ተሞክሮና ተሰጥኦ በመጠቀም ለጉባኤው ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ እንዲሰማቸው ማድረግ ይችላሉ። ምሳሌ የሚሆኑ አረጋውያን አልፎ አልፎ በሠርቶ ማሳያዎች ወይም በቃለ ምልልሶች እንዲካፈሉ ማድረግ ይቻላል። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ “ልጆቻቸውን በእውነት ቤት ካሳደጉ አረጋዊ ወንድም ወይም እህት ጋር ቃለ ምልልስ ሳደርግ አድማጮች ትኩረት ሰጥተው ይከታተላሉ” በማለት ተናግሯል። በሌላ ጉባኤ ያሉ ሽማግሌዎች ደግሞ አንዲት የ71 ዓመት አቅኚ እህት ሌሎች የመንግሥቱ አስፋፊዎች በመስክ አገልግሎት አዘውታሪ እንዲሆኑ በመርዳት ረገድ ስኬታማ እንደነበሩ ገልጸዋል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስንና የዕለት ጥቅስ ማንበብን እንዲሁም ባነበቡት ላይ ማሰላሰልን የመሳሰሉትን “መሠረታዊ” ነገሮች እንዲያደርጉ አበረታተዋቸዋል።

14. በአንድ ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች በዕድሜ ለገፉ ሌላ ሽማግሌ ያላቸውን አድናቆት የገለጹት እንዴት ነበር?

14 ከዚህም በላይ ሽማግሌዎች በዕድሜ የገፉ ሌሎች የበላይ ተመልካቾች የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ በአድናቆት ይመለከታሉ። ለተወሰኑ አሥርተ ዓመታት ሽማግሌ ሆነው ያገለገሉ በ70ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ዦዜ የተባሉ ወንድም በቅርቡ ከባድ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸው ነበር። ለማገገም ረጅም ጊዜ ስለሚወስድባቸው ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆነው የማገልገል መብታቸውን ለመተው አሰቡ። ዦዜ እንዲህ ይላሉ “ሽማግሌዎቹ የሰጡኝ መልስ በጣም ነበር ያስደነቀኝ። ሐሳቤን ከመቀበል ይልቅ ኃላፊነቴን ለመወጣት ምን ተግባራዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገኝ ጠየቁኝ።” በዕድሜ ከእርሳቸው የሚያንስ ሽማግሌ እንዲረዳቸው ስለተደረገ በሰብሳቢ የበላይ ተመልካችነት በደስታ ማገልገላቸውን የቀጠሉ ሲሆን ይህም ለጉባኤው በረከት አምጥቷል። አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል “ወንድሞች ዦዜ በሽማግሌነት ለሚያከናውኑት ሥራ ከፍተኛ አድናቆት አለው። የካበተ ተሞክሮ ስላላቸውና ለእምነት ምሳሌ በመሆናቸው ጉባኤው ይወዳቸዋል እንዲሁም ያከብራቸዋል። ለጉባኤያችን በረከት ናቸው።”

እርስ በርስ መተሳሰብ

15. ሁሉም ክርስቲያኖች በመካከላቸው ለሚገኙ አረጋውያን ደኅንነት ማሰብ የሚገባቸው ለምንድን ነው?

15 ለአረጋውያን ማሰብ ያለባቸው ልጆቻቸውና ኃላፊነት ያለባቸው ሽማግሌዎች ብቻ አይደሉም። ጳውሎስ ክርስቲያን ጉባኤን ከሰው አካል ጋር በማወዳደር እንዲህ ሲል ጽፏል “እግዚአብሔር ግን የአካል ብልቶችን አንድ ላይ አገጣጥሞ ክብር ለሚጎድላቸው የበለጠ ክብር ሰጥቶአቸዋል፤ ይህንም ያደረገው በአካል ብልቶች መካከል መለያየት ሳይኖር፣ እርስ በርሳቸው እኩል እንዲተሳሰቡ ነው።” (1 ቆሮንቶስ 12:24, 25) አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ሁሉም [የሰውነት] ክፍሎች አንዳቸው ለሌላው ደኅንነት እንዲያስቡ ነው” በማለት አስቀምጦታል። (ኖክስ) የክርስቲያን ጉባኤ በተቀናጀ መልኩ መሥራት እንዲችል አረጋውያንን ጨምሮ እያንዳንዱ የጉባኤ አባል ለሌሎች ክርስቲያኖች ደኅንነት ማሰብ ይኖርበታል።—ገላትያ 6:2

16. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ለአረጋውያን አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለአረጋውያን አሳቢነት እንድናሳይ የሚያስችሉ ግሩም አጋጣሚዎችን ይፈጥሩልናል። (ፊልጵስዩስ 2:4፤ ዕብራውያን 10:24, 25) በእነዚህ አጋጣሚዎች ጊዜ ወስደን ከእነርሱ ጋር እንጫወታለን? ስለ ጤንነታቸው መጠየቃችን እንዳለ ሆኖ አንድ የሚያንጽ ተሞክሮ ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ በመንገር “መንፈሳዊ ስጦታ” ልናካፍላቸው እንችላለን? አንዳንድ አረጋውያን እንደልብ መንቀሳቀስ ስለሚቸግራቸው እነርሱ ወደ እኛ እንዲመጡ ከመጠበቅ ይልቅ እኛ ወደ እነርሱ ብንሄድ ጥሩ ይሆናል። የመስማት ችግር ካለባቸው ረጋ ብለን ጥርት ባለ ሁኔታ መናገር ያስፈልገን ይሆናል። እንዲሁም “እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” ከተፈለገ በዕድሜ የገፉት ወንድም ወይም እህት የሚሉትን በጥሞና ማዳመጥ ይገባናል።—ሮሜ 1:11, 12

17. ከቤት መውጣት ለማይችሉ አረጋውያን ክርስቲያኖች አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

17 አንዳንድ አረጋውያን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ባይችሉስ? ያዕቆብ 1:27 “ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳት” የእኛ ኃላፊነት እንደሆነ ይጠቁማል። እዚህ ላይ “መርዳት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንዱ ትርጉም “መጎብኘት” ነው። (የሐዋርያት ሥራ 15:36) አረጋውያን ሄደን ስንጠይቃቸው በጣም እንደሚደሰቱ ጥርጥር የለውም! ‘ሽማግሌ’ የነበረው ጳውሎስ በ65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ በሮም በታሰረበት ወቅት ብቻውን ነበር። የአገልግሎት ባልደረባው የነበረውን ጢሞቴዎስን ለማየት ስለናፈቀ “በቶሎ ወደ እኔ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ” በማለት ጽፎለታል። (ፊልሞና 9፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:3, 4፤ 4:9) አንዳንድ አረጋውያን ቃል በቃል እስረኞች ባይሆኑም በጤና ችግሮች ምክንያት ከቤት መውጣት አይችሉም። እነርሱም ‘በተቻለን መጠን ቶሎ ሄደን ብንጠይቃቸው’ ደስ እንደሚላቸው የታወቀ ነው። ታዲያ ሄደን እንጠይቃቸዋለን?

18. አረጋውያንን መጠየቃችን ምን ጠቃሚ ውጤት ይኖረዋል?

18 አንድን መንፈሳዊ የሆኑ አረጋዊ ወንድም ወይም እህት ሄዶ መጠየቅ የሚያስገኘውን ጥቅም ፈጽሞ አቅልላችሁ አትመልከቱ። ሄኔሲፎሩ የሚባል አንድ ክርስቲያን ሮም ሳለ ጳውሎስን ፈልጎ ያገኘው ሲሆን ከዚያ በኋላም ለረጅም ጊዜ ‘የዕረፍት ምንጭ ሆኖለት’ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 1:16, 17 የ1954 ትርጉም) አንዲት አረጋዊት እህት እንዲህ ይላሉ “ከወጣቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተኛል። ይበልጥ የሚያስደስተኝ ደግሞ እንደ ቤተሰባቸው አባል አድርገው ስለሚይዙኝ ነው። መንፈሴን በእጅጉ ያነቃቃልኛል።” አንዲት ሌላ አረጋዊት እህት ደግሞ እንዲህ ብለዋል “አንድ ሰው ካርድ ሲልክልኝ፣ ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን ስልክ ደውሎ ሲያነጋግረኝ ወይም ቤቴ መጥቶ ሲያጫውተኝ በጣም ደስ ይለኛል። እንደ ንጹሕ አየር መንፈሴን ያድስልኛል።”

ይሖዋ ለአረጋውያን የሚያስቡትን መልሶ ይክሳቸዋል

19. አረጋውያንን መንከባከብ ምን በረከቶች ያስገኛል?

19 አረጋውያንን መንከባከብ ብዙ በረከቶችን ያስገኛል። ከአረጋውያን ጋር መቀራረብ እንዲሁም ያላቸውን እውቀትና ተሞክሮ መቅሰም መቻል በራሱ መብት ነው። አረጋውያንን የሚንከባከቡ ሰዎች በመስጠት የሚገኘውን ደስታ የሚያገኙ ከመሆኑም በላይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣታቸው እርካታና ውስጣዊ ሰላም ያገኛሉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ከዚህም በላይ አረጋውያንን የሚንከባከቡ ሰዎች በእርጅና ዘመናችን ጧሪ እናጣለን ብለው አይፈሩም። የአምላክ ቃል “ለጋስ ይበለጽጋል፤ ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል” የሚል ዋስትና ይሰጠናል።—ምሳሌ 11:25

20, 21. ይሖዋ አረጋውያንን ለሚንከባከቡ ሰዎች ያለው አመለካከት ምንድን ነው? ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?

20 ይሖዋ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን አረጋዊ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን የሚንከባከቡ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ልጆች፣ የበላይ ተመልካቾችንና ሌሎች ክርስቲያኖችን መልሶ ይክሳል። እንዲህ ያለው መንፈስ “ለድኻ የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ ስላደረገውም ተግባር ዋጋ ይከፍለዋል” ከሚለው ምሳሌ ጋር የሚስማማ ነው። (ምሳሌ 19:17) በፍቅር ተገፋፍተን ለችግረኞች ወይም ለድኾች ቸርነት የምናደርግ ከሆነ አምላክ እንዲህ ያለውን ቸርነት ለእርሱ እንደተሰጠ ብድር ስለሚቆጥረው አትረፍርፎ ይባርከናል። በተጨማሪም የእምነት ባልንጀሮቻችን ለሆኑት አረጋውያን ፍቅራዊ አሳቢነት በማሳየታችን ወሮታውን ይከፍለናል። ከእነዚህ አረጋውያን መካከል ብዙዎቹ ‘በዚህ ዓለም ድኾች ቢሆኑም በእምነት ባለጸጋ’ ናቸው።—ያዕቆብ 2:5

21 የይሖዋ በረከት እጅግ የተትረፈረፈ ነው! በረከቱ የዘላለም ሕይወትንም ይጨምራል። አብዛኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች ከአዳም የወረስነው ኃጢአት ውጤቶች በማይኖሩበትና ታማኝ የሆኑ አረጋውያን የወጣትነት ጥንካሬያቸውን መልሰው በሚያገኙበት ምድራዊ ገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (ራእይ 21:3-5) ያንን በረከት የምናገኝበት ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አረጋውያንን የመንከባከብ ክርስቲያናዊ ኃላፊነታችንን መወጣታችንን እንቀጥል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አረጋዊ ወላጆችን እንዴት መንከባከብ እንደሚቻል ተግባራዊ ሐሳብ ለማግኘት የየካቲት 8, 1994 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 3-10 ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ልጆች አረጋዊ ወላጆቻቸውን ማክበር የሚችሉት እንዴት ነው?

• የጉባኤ ሽማግሌዎች በዕድሜ ለገፉ የመንጋው አባላት አድናቆታቸውን መግለጽ የሚችሉት እንዴት ነው?

• ሌሎች ክርስቲያኖች ለአረጋውያን አሳቢነት ለማሳየት ምን ማድረግ ይችላሉ?

• በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖችን መንከባከብ ምን በረከቶች ያስገኛል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ወላጆቹ እርዳታ ባስፈለጋቸው ጊዜ

ፊሊፕ በ1999 አባቱ በጠና መታመማቸውን በሰማ ጊዜ ላይቤሪያ ውስጥ ፈቃደኛ የግንባታ ሠራተኛ ሆኖ ያገለግል ነበር። እናቱ ብቻቸውን ችግሩን መቋቋም እንደማይችሉ ስለተረዳ አባቱ የሕክምና እርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ወደ ቤተሰቦቹ ለመመለስ ወሰነ።

ፊሊፕ “ውሳኔው ቀላል አልነበረም፤ ሆኖም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ግዴታዬ ወላጆቼን መንከባከብ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር” በማለት ተናግሯል። በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ወላጆቹ ይበልጥ ተስማሚ ወደሆነ ቤት እንዲዛወሩ ያደረገ ሲሆን በአካባቢው በሚኖሩ ክርስቲያኖች እርዳታ ቤቱን ለአባቱ ሁኔታ እንዲመች አንዳንድ ማስተካከያዎችን አደረገለት።

በዚህም ምክንያት የፊሊፕ እናት ከባድ የጤና ችግር ያጋጠማቸውን አባቱን ለማስታመም ሁኔታው ተመቻቸላቸው። በቅርቡ ፊሊፕ መቄዶንያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኖ እንዲሠራ የቀረበለትን ግብዣ ተቀብሏል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሚያስፈልጋቸውን ነገር አድርገውላቸዋል

በአውስትራሊያ አዳ የሚባሉ አንዲት የ85 ዓመት ክርስቲያን በጤና ችግር ምክንያት ከቤት መውጣት ባቃታቸው ጊዜ የጉባኤው ሽማግሌዎች እርሳቸውን ለመርዳት አንዳንድ ዝግጅቶች አደረጉ። ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው የተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች እንዲረዷቸው ፕሮግራም አወጡ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በጽዳት፣ በአጠባ፣ ምግብ በማብሰልና በመላላክ በደስታ እንክብካቤ አድርገውላቸዋል።

አዳን ለመርዳት ፕሮግራም ከወጣ ወደ 10 የሚጠጉ ዓመታት አልፈዋል። እስከአሁን ከ30 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች አዳን በመንከባከቡ ሥራ ተካፍለዋል። አሁንም ሄደው የሚጠይቋቸው ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ያነብቡላቸዋል፣ በጉባኤው ውስጥ ስላሉ ወንድሞችና እህቶች መንፈሳዊ እድገት ያጫውቷቸዋል እንዲሁም ዘወትር አብረዋቸው ይጸልያሉ።

በጉባኤው ውስጥ የሚገኝ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል “ለአዳ እንክብካቤ የሚያደርጉ ወንድሞችና እህቶች እርሳቸውን መርዳቱን እንደ መብት ይቆጥሩታል። ብዙዎቹ አዳ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሲያከናውኑ በነበረው የታማኝነት አገልግሎት በጣም የተነኩ ሲሆን እርሳቸውን ችላ ማለቱ ለእነርሱ የማይታሰብ ነገር ነው።”

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በዕድሜ ለገፉ ወላጆቻችን ፍቅራችንን በግልጽ እናሳያቸዋለን?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የጉባኤው አባላት በሙሉ በዕድሜ ለገፉ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ያላቸውን ፍቅር መግለጽ ይችላሉ