በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አረጋውያን—በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው

አረጋውያን—በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው

አረጋውያን—በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው

“በእግዚአብሔር ቤት ተተክለዋል። . . . ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ።”—መዝሙር 92:13, 14

1. ብዙ ሰዎች ለአረጋውያን ምን አመለካከት አላቸው?

 ይሖዋ በዕድሜ የገፉትን ጨምሮ ታማኝ አገልጋዮቹን ሁሉ ይወዳል። ይሁን እንጂ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በየዓመቱ በግምት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ አረጋውያን ግፍ ይፈጸምባቸዋል ወይም ችላ ይባላሉ። ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ተመሳሳይ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በአረጋውያን ላይ የሚፈጸመው በደል ዓለም አቀፋዊ ይዘት አለው። አንድ ድርጅት እንደገለጸው የችግሩ መንስኤ “አረጋውያን እምብዛም አይጠቅሙም፣ ምርታማም አይደሉም እንዲሁም በሌሎች ላይ ጥገኛ ናቸው የሚለው አመለካከት በብዙዎች ዘንድ እየተስፋፋ መሄዱ” ነው።

2. (ሀ) ይሖዋ በዕድሜ የገፉ አገልጋዮቹን የሚመለከተው እንዴት ነው? (ለ) በመዝሙር 92:12-15 ላይ ምን ልብ የሚነካ ሐሳብ እናገኛለን?

2 ይሖዋ አምላክ በዕድሜ የገፉ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደ ውድ ሀብት ይመለከታቸዋል። እርሱ የሚመለከተው የአቅማችንን ውስንነት ሳይሆን ‘ውስጣዊ ሰውነታችንን’ ማለትም መንፈሳዊ ሁኔታችንን ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:16) በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚከተለውን ልብ የሚነካ ሐሳብ እናገኛለን “ጻድቃን እንደ ዘንባባ ይንሰራፋሉ፤ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ይንዠረገጋሉ። በእግዚአብሔር ቤት ተተክለዋል፤ በአምላካችንም አደባባይ ይንሰራፋሉ። ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ፤ እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ። ‘እግዚአብሔር ትክክለኛ ነው፤ እርሱ ዐለቴ ነው፤ በእርሱ ዘንድ እንከን የለም’ ይላሉ።” (መዝሙር 92:12-15) እነዚህን ቁጥሮች መመርመራችን አረጋውያን ለመላው የወንድማማች ማኅበር ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉባቸውን አንዳንድ ገጽታዎች እንድንገነዘብ ይረዳናል።

“ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ”

3. (ሀ) ጻድቃን በዘንባባ ዛፍ የተመሰሉት ለምንድን ነው? (ለ) አረጋውያን ‘ባረጁ ጊዜም እንኳ ማፍራት’ የሚችሉት እንዴት ነው?

3 መዝሙራዊው ጻድቃንን ‘በአምላካችን አደባባይ በተተከሉ’ የዘንባባ ዛፎች መስሏቸዋል። እነዚህ ዛፎች ‘ባረጁ ጊዜም እንኳ ፍሬ ማፍራታቸውን ይቀጥላሉ።’ ይህ የሚያበረታታ ሐሳብ ነው ቢባል አትስማሙም? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ ግርማ ሞገስ የተላበሱና ቀጥ ብለው ያደጉ የዘንባባ ዛፎችን በየቦታው ማየት የተለመደ ነበር። እነዚህ ዛፎች ለዓይን ማራኪ ከመሆናቸውም በላይ ብዙ ፍሬ ያፈራሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከመቶ ዓመት በላይ ሆኗቸውም እንኳ ማፍራታቸውን ይቀጥላሉ። a እናንተም በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ሥር በመስደድ ‘በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ ማፍራታችሁን’ መቀጠል ትችላላችሁ።—ቆላስይስ 1:10

4, 5. (ሀ) ክርስቲያኖች ምን አስፈላጊ ፍሬ ማፍራት ይኖርባቸዋል? (ለ) በእርጅና ዘመናቸው “የከንፈሮችን ፍሬ” እንዳፈሩ የሚገልጹ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ጥቀስ።

4 ይሖዋ፣ ክርስቲያኖች “የከንፈሮችን ፍሬ” እንዲያፈሩ ይኸውም እርሱንና ዓላማውን የሚያወድሱ ቃላትን እንዲናገሩ ይጠብቅባቸዋል። (ዕብራውያን 13:15) ይህ ለእናንተ ለአረጋውያንም ይሠራል? እንደሚሠራ ምንም ጥያቄ የለውም።

5 መጽሐፍ ቅዱስ ዕድሜያቸው ቢገፋም ስለ ይሖዋ ስምና ስለ ዓላማዎቹ በድፍረት ስለ መሰከሩ አገልጋዮቹ የሚናገሩ ታሪኮችን ይዟል። ይሖዋ ሙሴን ነቢይና ወኪል አድርጎ በላከው ጊዜ ዕድሜው ‘ከሰባ ዓመት’ በላይ ነበር። (መዝሙር 90:10፤ ዘፀአት 4:10-17) ነቢዩ ዳንኤል ዕድሜው መግፋቱ ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነት በድፍረት እንዳይመሰክር አላገደውም። ቤልሻዛር በግድግዳ ላይ የተጻፈውን የእጅ ጽሑፍ እንዲተረጉምለት በጠየቀው ወቅት ዳንኤል ዕድሜው በ90ዎቹ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። (ዳንኤል ምዕራፍ 5) አረጋዊ ስለ ነበረው ስለ ሐዋርያው ዮሐንስስ ምን ለማለት ይቻላል? በታማኝነት ባሳለፈው ሕይወቱ መገባደጃ ላይ ‘ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ በመመሥከሩ’ ምክንያት ፍጥሞ በምትባል ትንሽ ደሴት ታስሮ ነበር። (ራእይ 1:9) እናንተም በእርጅና ዘመናቸው ‘የከንፈር ፍሬዎችን’ ሲያፈሩ የነበሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ በርካታ ሰዎችን እንደምታስታውሱ ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ሳሙኤል 8:1, 10፤ 12:2፤ 1 ነገሥት 14:4, 5፤ ሉቃስ 1:7, 67-79፤ 2:22-32

6. ይሖዋ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ‘ሽማግሌዎችን’ ትንቢት ለመናገር የተጠቀመባቸው እንዴት ነው?

6 ሐዋርያው ጴጥሮስ ዕብራዊ ነቢይ የነበረውን ኢዩኤልን ጠቅሶ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመጨረሻው ቀን፣ መንፈሴን [‘ሽማግሌዎችን’ ጨምሮ] በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ . . . እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:17, 18፤ ኢዩኤል 2:28) በዚህ መሠረት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋ ዓላማዎቹን ለማወጅ በዕድሜ የገፉ ቅቡዓንንና ‘ሌሎች በጎችን’ ሲጠቀም ቆይቷል። (ዮሐንስ 10:16) ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የመንግሥቱን ፍሬ ለአሥርተ ዓመታት በታማኝነት ሲያፈሩ ቆይተዋል።

7. አረጋውያን የአቅም ገደብ ቢኖርባቸውም የመንግሥቱን ፍሬ ማፍራታቸውን እንዳላቋረጡ የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።

7 በ1941 የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ የሆኑትን ሶንያ የተባሉ አረጋዊት እህት እንመልከት። እኚህ እህት ሥር የሰደደ ሕመም የነበረባቸው ቢሆንም በቤታቸው ውስጥ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኑ ነበር። ሶንያ እንዲህ ብለዋል “ምሥራቹን መስበክ የሕይወቴ ክፍል ነው። እንዲያውም ሕይወቴ ነው ማለት እችላለሁ። አገልግሎት ማቆም አልፈልግም።” በቅርቡ ሶንያ እና እህታቸው ኦሊቭ በአንድ ሆስፒታል ተራ መጠበቂያ ክፍል ውስጥ ላገኟት ለሞት በሚያደርስ በሽታ ለተያዘች ጃኔት ለተባለች ሴት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የተስፋ መልእክት ነገሯት። አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነችው የጃኔት እናት ለልጅዋ በተደረገው ፍቅራዊ አሳቢነት በጣም በመደሰቷ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ የተቀበለች ሲሆን አሁን ጥሩ እድገት እያደረገች ነው። እናንተስ የመንግሥቱን ፍሬ ለማፍራት እንዲህ ያለውን አጋጣሚ በሚገባ ትጠቀሙበታላችሁ?

8. አረጋዊው ካሌብ በይሖዋ እንደሚታመን ያሳየው እንዴት ነው? በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ምሳሌውን መኮረጅ የሚችሉትስ እንዴት ነው?

8 በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች የአቅም ገደብ ቢኖርባቸውም መንግሥቱን በድፍረት መስበካቸውን በመቀጠል ከሙሴ ጋር በምድረ በዳ ለአሥርተ ዓመታት አብሮ የተጓዘውን ታማኝ እስራኤላዊ የካሌብን ምሳሌ ይከተላሉ። ካሌብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን በተሻገረ ጊዜ 79 ዓመቱ ነበር። በድል ላይ ድል እየተቀዳጀ ወደፊት ይገሰግስ በነበረው የእስራኤል ሠራዊት ውስጥ ለስድስት ዓመታት ከተዋጋ በኋላ ግዳጄን ተወጥቻለሁ ብሎ ሊያርፍ ይችል ነበር። ከዚህ ይልቅ በይሁዳ ተራራማ አካባቢ ዔናቃውያን የሚባሉት በጣም ግዙፍ ሰዎች ይኖሩባቸው የነበሩትን ‘ታላላቅና የተመሸጉ ከተሞች’ በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ራሱን በድፍረት አቀረበ። የይሖዋ እርዳታ ያልተለየው ካሌብ ‘ልክ ይሖዋ እንዳለው አሳድዶ አወጣቸው።’ (ኢያሱ 14:9-14፤ 15:13, 14) በእርጅና ዘመናችሁ የመንግሥቱን ፍሬ ማፍራታችሁን በምትቀጥሉበት ጊዜ ይሖዋ ከካሌብ ጋር እንደነበረው ሁሉ ከእናንተም ጋር እንደሚሆን እርግጠኞች ሁኑ። ታማኝነታችሁን ጠብቃችሁ የምትኖሩ ከሆነ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ርስት ይሰጣችኋል።—ኢሳይያስ 40:29-31፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

“እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ”

9, 10. በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች በእምነት ጤናሞች መሆንና መንፈሳዊ ጥንካሬያቸውን ጠብቀው መኖር የሚችሉት እንዴት ነው? (በገጽ 13 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

9 መዝሙራዊው በዕድሜ የገፉ የይሖዋ አገልጋዮች ፍሬያማ መሆናቸውን ለመግለጽ እንዲህ በማለት ዘምሯል “ጻድቃን እንደ ዘንባባ ይንሰራፋሉ፤ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ይንዠረገጋሉ። ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ፤ እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ።”—መዝሙር 92:12, 14

10 ዕድሜያችሁ እየገፋ ቢሄድም እንኳ መንፈሳዊ ጥንካሬያችሁን ጠብቃችሁ መኖር የምትችሉት እንዴት ነው? የዘንባባ ዛፍ ከዓመት እስከ ዓመት ውበቱን ጠብቆ መኖሩ የተመካው ምንጊዜም የማይነጥፍ ንጹሕ ውኃ በማግኘቱ ላይ ነው። በተመሳሳይ እናንተም የአምላክን ቃል በማጥናትና ከድርጅቱ ጋር በመተባበር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የእውነት ውኃ መጠጣት ትችላላችሁ። (መዝሙር 1:1-3፤ ኤርምያስ 17:7, 8) መንፈሳዊ ጥንካሬያችሁ በእምነት ባልንጀሮቻችሁ ዘንድ እንደ ውድ ሀብት እንድትታዩ ያደርጋችኋል። የዚህን እውነተኝነት ለማየት አረጋዊ ሊቀ ካህን የነበረውን የዮዳሄን ታሪክ እንመልከት።

11, 12. (ሀ) ዮዳሄ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ውስጥ ምን ጠቃሚ ሚና ተጫውቷል? (ለ) የነበረውን ተሰሚነት እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት የተጠቀመበትስ እንዴት ነው?

11 የሥልጣን ጥመኛ የነበረችው ንግሥት ጎቶልያ የልጅ ልጆቿን አጥፍታ ይሁዳን በቁጥጥሯ ሥር ባደረገች ጊዜ ዮዳሄ ዕድሜው ከመቶ ዓመት በላይ ሳይሆን አይቀርም። አረጋዊው ዮዳሄ ምን ሊያደርግ ይችላል? እርሱና ሚስቱ ኢዮአስ የተባለውን ከጭፍጨፋው የተረፈ ብቸኛ ንጉሣዊ ወራሽ ለስድስት ዓመታት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሸሸጉት። ከዚያም ዮዳሄ ባልተጠበቀ ሁኔታ የሰባት ዓመቱ ኢዮአስ ንጉሥ መሆኑን በማወጅ ጎቶልያን አስገደላት።—2 ዜና መዋዕል 22:10-12፤ 23:1-3, 15, 21

12 ዮዳሄ የንጉሡ ጠባቂ መሆኑ ያስገኘለትን ተሰሚነት እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት ተጠቀመበት። “እርሱ ራሱ፣ ሕዝቡና ንጉሡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሚሆኑ ቃል ኪዳን ገባ።” ሕዝቡ በዮዳሄ ትእዛዝ የሐሰት አምላክ የሆነውን የበአልን ቤት ከማፍረሱም በላይ መሠዊያውንና ጣዖቱን እንዲሁም ካህኑን አስወገደ። በተጨማሪም ኢዮአስ የቤተ መቅደሱን አገልግሎት እንደገና ያስጀመረውና እጅግ አስፈላጊ የነበረው እድሳት እንዲከናወን ያደረገው በዮዳሄ ትእዛዝ ነበር። “ካህኑ ዮዳሄ ያስተምረው በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ኢዮአስ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ።” (2 ዜና መዋዕል 23:11, 16-19፤ 24:11-14፤ 2 ነገሥት 12:2) ዮዳሄ ‘በእስራኤል ውስጥ ለእግዚአብሔርና ለቤተ መቅደሱ መልካም ስለሠራ’ በ130 ዓመቱ በሞተ ጊዜ ልዩ አክብሮት ተሰጥቶት በነገሥታት መቃብር እንዲቀበር ተደርጓል።—2 ዜና መዋዕል 24:15, 16

13. በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ‘ለእውነተኛው አምላክና ለቤቱ መልካም መሥራት’ የሚችሉት እንዴት ነው?

13 ምናልባት ጤና ማጣት ወይም ሌሎች ሁኔታዎች እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት የምታደርጉትን ጥረት ይገድቡባችሁ ይሆናል። ያም ሆኖ ግን ‘ለእውነተኛው አምላክና ለቤቱ መልካም መሥራት’ ትችላላችሁ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና ተሳትፎ በማድረግ እንዲሁም አመቺ በሚሆንባቸው ጊዜያት ሁሉ በመስክ አገልግሎት በመካፈል ለይሖዋ መንፈሳዊ ቤት ያላችሁን ቅንዓት ማሳየት ትችላላችሁ። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በፈቃደኝነት መቀበላችሁና ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ እንዲሁም ጉባኤውን በታማኝነት መደገፋችሁ ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ጥንካሬ አስተዋጽኦ ያበረክታል። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) የእምነት ባልንጀሮቻችሁንም “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ” ልታነቃቁ ትችላላችሁ። (ዕብራውያን 10:24, 25፤ ፊልሞና 8, 9) እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ የምታደርጉ ከሆነ ለሌሎች በረከት ትሆናላችሁ “አረጋውያን ጭምቶች፣ የተከበሩ፣ ራሳቸውን የሚገዙና በእምነት፣ በፍቅርና በትዕግሥት ጤናማነት ያላቸው እንዲሆኑ ምከራቸው። እንዲሁም አሮጊቶች በአኗኗራቸው የተከበሩ እንዲሆኑ፣ በጎ የሆነውን የሚያስተምሩ እንጂ የሰው ስም የሚያጠፉ ወይም በወይን ጠጅ ሱስ የተጠመዱ እንዳይሆኑ አስተምራቸው።”—ቲቶ 2:2-4

14. ሽማግሌ ሆነው ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ክርስቲያኖች እውነተኛውን አምልኮ በማስፋፋት ረገድ ምን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ?

14 ለበርካታ ዓመታት በጉባኤ ሽማግሌነት አገልግለሃል? ለዓመታት በጉባኤ ሽማግሌነት ያገለገሉ አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ይመክራሉ “በረጅም ዓመታት ውስጥ ያካበትከውን ተሞክሮ በልግሥና ተጠቀምበት። ለሌሎች ኃላፊነት ስጥ እንዲሁም ለመማር ፈቃደኛ ለሆኑ ተሞክሮህን አካፍል። . . . ምን ልዩ ችሎታ እንዳላቸው ለማስተዋል ሞክር። ይህን ችሎታቸውን እንዲያሰፉና እንዲያዳብሩ በመርዳት ለወደፊቱ ጊዜ ጥሩ መሠረት ጣል።” (ዘዳግም 3:27, 28) ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እያደገ በመጣው የመንግሥቱ ስብከት ሥራ የምታደርገው ጉልህ ተሳትፎ ለሌሎች ክርስቲያን ወንድሞችህ ብዙ በረከት ያስገኛል።

‘ይሖዋ ትክክል እንደሆነ ተናገሩ’

15. አረጋውያን ክርስቲያኖች ‘ይሖዋ ትክክል እንደሆነ መናገር’ የሚችሉት እንዴት ነው?

15 በዕድሜ የገፉ የአምላክ አገልጋዮች ‘ይሖዋ ትክክል እንደሆነ የመናገር’ ኃላፊነታቸውን በደስታ ይወጣሉ። አረጋውያን ክርስቲያኖች ከሆናችሁ ሌሎች ከምትናገሩትና ከምታደርጉት ነገር ይሖዋ ‘እንከን የሌለው ዐለታችሁ እንደሆነ’ ሊገነዘቡ ይችላሉ። (መዝሙር 92:15) የዘንባባ ዛፍ ወደር ስለሌላቸው የፈጣሪ ባሕርያት ያለ ድምፅ ይመሠክራል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ለሚገኙ ሌሎች ክርስቲያኖች ስለ እርሱ እንድትመሠክሩ ልዩ መብት ሰጥቷችኋል። (ዘዳግም 32:7፤ መዝሙር 71:17, 18፤ ኢዩኤል 1:2, 3) እንዲህ ማድረጋችሁ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

16. ‘አምላክ ትክክል መሆኑን መናገር’ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳየው የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ነው?

16 የእስራኤል መሪ የነበረው ኢያሱ “በጣም አርጅቶ፣ ዕድሜውም ገፍቶ” በነበረበት ወቅት አምላክ ያደረገላቸውን መልካም ነገሮች እንዲያስታውሱ ለመንገር “እስራኤልን ሁሉ አለቆቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ፈራጆቻቸውንና ሹማምታቸውን በሙሉ ጠርቶ” ነበር። ከዚያም “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ. . . ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል” አላቸው። (ኢያሱ 23:1, 2, 14) ለጊዜውም ቢሆን እነዚህ ቃላት ሕዝቡ ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን የነበረውን ቁርጠኝነት አጠናክሮለታል። ይሁን እንጂ ኢያሱ ከሞተ በኋላ “እግዚአብሔርንም ሆነ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ። . . . እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ የበአል አማልክትንም አመለኩ።”—መሳፍንት 2:8-11

17. ይሖዋ በዘመናችን ለሕዝቦቹ ምን አድርጎላቸዋል?

17 በዛሬው ጊዜ ያለው የክርስቲያን ጉባኤ ታማኝነት በዕድሜ የገፉ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ለሕዝቡ ስላደረጋቸው “ታላላቅ ነገሮች” በሚሰጡት ምሥክርነት ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። ሆኖም ስለ እነዚህ ነገሮች የሚገልጹ ታሪኮችን ከእነርሱ አንደበት ስንሰማ በይሖዋና እርሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ይጠናከራል። (መሳፍንት 2:7፤ 2 ጴጥሮስ 1:16-19) በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የቆየህ ከሆንህ በምትኖርበት አካባቢ ወይም አገር የነበሩት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር በጣም ጥቂት የነበረበትን ወይም በስብከቱ ሥራ ላይ ከባድ ተቃውሞ የተነሳበትን ጊዜ ታስታውስ ይሆናል። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይሖዋ አንዳንድ እንቅፋቶችን አስወግዶ የአስፋፊዎች ቁጥር “በፍጥነት” እንዲያድግ ሲያደርግ የማየት አጋጣሚ አግኝተሃል። (ኢሳይያስ 54:17፤ 60:22) ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የነበረው ግንዛቤ እየጠራ ሲሄድና የአምላክ ምድራዊ ድርጅት ደረጃ በደረጃ ማስተካከያዎችን ሲያደርግ ተመልክተሃል። (ምሳሌ 4:18፤ ኢሳይያስ 60:17) ይሖዋ ስላደረገልህ መልካም ነገሮች የሚገልጹ ተሞክሮዎችን በመናገር ሌሎችን ማነጽ ትፈልጋለህ? እንዲህ ማድረግህ መላውን የወንድማማች ማኅበር እንደሚያበረታና እንደሚያጠናክር ምንም ጥርጥር የለውም!

18. (ሀ) ‘ይሖዋ ትክክል መሆኑን መናገር’ ከዓመታት በኋላ የሚያስገኘውን ውጤት የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር። (ለ) አንተ በግልህ ይሖዋ ትክክል መሆኑን በተሞክሮ ያየኸው እንዴት ነው?

18 በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤና አመራር ያገኘህባቸው ጊዜያት የሉም? (መዝሙር 37:25፤ ማቴዎስ 6:33፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) ማርታ የሚባሉ አንዲት አረጋዊት እህት “ምንም ነገር ቢከሰት ፈጽሞ ይሖዋን አትተዉ። እርሱ ይደግፋችኋል” በማለት ሌሎችን የማበረታታት ልማድ ነበራቸው። በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የተጠመቁ ቶልሚና የተባሉ የማርታ ጥናት ከዚህ ምክር በእጅጉ ተጠቅመዋል። ቶልሚና እንዲህ ይላሉ “ባለቤቴን በሞት ባጣሁ ጊዜ በጣም ተስፋ ቆርጬ ነበር። ይሁን አንጂ እነዚህ ቃላት ፈጽሞ ከስብሰባ ላለመቅረት ቁርጥ ውሳኔ እንዳደርግ ረድተውኛል። ይሖዋም መጽናት እንድችል አበርትቶኛል።” እህት ቶልሚናም መጽሐፍ ቅዱስን ለሚያስጠኗቸው ሰዎች ይህንኑ ምክር ሲሰጡ ቆይተዋል። በእርግጥም፣ ማበረታቻ በመስጠትና ይሖዋ ያደረጋቸውን መልካም ነገሮች በመናገር የእምነት ባልንጀሮቻችሁን እምነት በእጅጉ መገንባት ትችላላችሁ።

ይሖዋ ታማኝ የሆኑ አረጋውያንን እንደ ውድ ሀብት ይመለከታቸዋል

19, 20. (ሀ) ይሖዋ አረጋውያን አገልጋዮቹ የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚመለከተው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

19 በውለታ ቢስነቱ የሚታወቀው ይህ ዓለም ለአረጋውያን የሚሰጠው ግምት በጣም አነስተኛ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) ቢያስታውሳቸው እንኳ ብዙውን ጊዜ ድሮ ባከናወኗቸው ነገሮች ይኸውም በቀድሞ ማንነታቸው እንጂ አሁን እያከናወኑ ባሉት ነገር አይደለም። በአንጻሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም” ይላል። (ዕብራውያን 6:10) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ አምላክ ባለፉት ዘመናት በታማኝነት ያደረጋችሁትን ሁሉ ያስታውሳል። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ በማከናወን ላላችሁት ነገር ትልቅ ግምት ይሰጣል። አዎን፣ ይሖዋ ታማኝ የሆኑ አረጋውያንን ፍሬያማ፣ በመንፈሳዊ ጤናሞችና ጠንካራ ክርስቲያኖች እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸዋል። ለታላቅ ኃይሉ ሕያው ምሥክሮች ናቸው።—ፊልጵስዩስ 4:13

20 በዓለም አቀፉ የክርስቲያን ወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችንና እህቶችን በይሖዋ ዓይን ትመለከታቸዋለህ? ከሆነ ለእነርሱ ያለህን ፍቅር ለማሳየት መገፋፋትህ አይቀርም። (1 ዮሐንስ 3:18) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ፍቅራችንን በተግባር ማሳየት የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከዘንባባ ዛፍ የሚገኘው እያንዳንዱ የተምር ዘለላ በሺህ የሚቆጠሩ ፍሬዎችን የሚይዝ ሲሆን 8 ኪሎ ግራም ወይም ከዚያ በላይ ሊመዝን ይችላል። በአንድ ጸሐፊ ግምት መሠረት “እያንዳንዱ ፍሬ የሚያፈራ [የዘንባባ] ዛፍ በሕይወት ዘመኑ ከሁለት እስከ ሦስት ቶን የሚያህል የተምር ምርት ለባለቤቱ ይሰጣል።”

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• አረጋውያን ‘ፍሬ የሚያፈሩት’ እንዴት ነው?

• በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆኑ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ውድ ሀብት ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?

• በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ‘ይሖዋ ትክክል መሆኑን መናገር’ የሚችሉት እንዴት ነው?

• ይሖዋ ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉትን እንደ ውድ ሀብት የሚያያቸው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በእምነት ጤናሞች ሆነው እንዲኖሩ የረዳቸው ምንድን ነው?

ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ክርስቲያኖች በእምነት ጤናሞች እንዲሆኑና መንፈሳዊ ጥንካሬያቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ የረዳቸው ምንድን ነው? እስቲ አንዳንዶቹ የሚሉትን እንስማ

“ከይሖዋ ጋር በመሠረትነው ዝምድና ላይ የሚያተኩሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማንበቡ በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙውን ጊዜ ማታ ማታ መዝሙር 23 እና 91ን በቃሌ እወጣቸዋለሁ።”—ኦሊቭ፣ በ1930 የተጠመቁ እህት።

“ሁልጊዜ በጥምቀት ንግግር ላይ የምገኝ ከመሆኑም በላይ እኔ ራሴ የምጠመቅ ያህል ንግግሩን በጥሞና አዳምጣለሁ። ራሴን ስወስን የገባሁትን ቃል ሁልጊዜ ማስታወሴ ታማኝነቴን ጠብቄ እንድኖር ከረዱኝ ወሳኝ ነገሮች አንዱ ነው።”—ሃሪ፣ በ1946 የተጠመቁ ወንድም።

“ይሖዋ እንዲረዳን፣ እንዲጠብቀንና እንዲባርከን እየለመንን በየዕለቱ መጸለያችን በጣም አስፈላጊ ነው። ‘በመንገዳችን ሁሉ እርሱን ማወቅ’ ይኖርብናል።” (ምሳሌ 3:5, 6)—አንቶኒዮ፣ በ1951 የተጠመቁ ወንድም።

“ለረጅም ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ያገለገሉና አሁንም በማገልገል ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖችን ተሞክሮ መስማቴ ለይሖዋ ታማኝ ሆኜ ለመኖር ያደረግሁትን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልኛል።”—ጆአን፣ በ1954 የተጠመቁ እህት።

“ለራሳችን ከልክ በላይ ግምት መስጠት ተገቢ አይደለም። አለን የምንለው ነገር ሁሉ የይሖዋ የጸጋ ስጦታ ነው። እንዲህ ያለ አመለካከት መያዛችን እስከ መጨረሻው ለመጽናት የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ምግብ ለማግኘት ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ዞር እንድንል ይረዳናል።”—አርሊን፣ በ1954 የተጠመቁ እህት።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አረጋውያን የመንግሥቱን ፍሬዎች ያፈራሉ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆኑ አረጋውያን ውድ ሀብት ናቸው