በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ወንዞች በእጃቸው ያጨብጭቡ”

“ወንዞች በእጃቸው ያጨብጭቡ”

ዕጹብ ድንቅ የሆኑት የይሖዋ ፍጥረታት

“ወንዞች በእጃቸው ያጨብጭቡ”

የምድርን ካርታ ስትመለከት በአብዛኞቹ ቦታዎች ላይ እየተጥመዘመዙ የሚሄዱ ቀጫጭን መሥመሮችን ታያለህ። እነዚህ መሥመሮች አውላላ ሜዳዎችን፣ በረሃዎችንና በሣር የተሸፈኑ አካባቢዎችን ያቋርጣሉ። እንዲሁም ሸለቆዎችን፣ ገደላማ ቦታዎችንና ደኖችን እየሰነጠቁ ያልፋሉ። (ዕንባቆም 3:9) እነዚህ መሥመሮች በፕላኔታችን ላይ ላለው ሕይወት የደም ሥር የሆኑት ወንዞች ናቸው። ወንዞች የምድር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ላለው ጥበብና ኃይል ሕያው ምሥክር ናቸው። እነሱን ስንመለከት “ወንዞች በእጃቸው ያጨብጭቡ፤ ተራሮችም በአንድነት ይዘምሩ፤ እነዚህ በእግዚአብሔር ፊት ይዘምሩ” በማለት እንዳዜመው መዝሙራዊ ይሰማናል።—መዝሙር 98:8, 9 a

ወንዞች ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር የቅርብ ትስስር አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ከኤድን ከሚወጣ ወንዝ ተከፍለው በተለያየ አቅጣጫ ስለሚሄዱ አራት ትላልቅ ወንዞች ይናገራል። (ዘፍጥረት 2:10-14) ቀደምት ከሚባሉት ሥልጣኔዎች መካከል አንዱ የተገኘው በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙት በጤግሮስና በኤፍራጥስ ወንዞች አቅራቢያ ባሉት ለም ሸለቆዎች ውስጥ ነው። በቻይና የሚገኘው የሁዋንግ ወንዝ፣ በደቡባዊ እስያ ያሉት የጋንጅስና የኢንዱስ ወንዞች እንዲሁም በግብፅ የሚገኘው የናይል ወንዝ የታላላቅ ሥልጣኔዎች መነሻ ናቸው።

ከዚህ አኳያ የሰው ልጅ በየቦታው የሚገኙትን ወንዞች ውበትና ኃይል ሲመለከት በአድናቆት መደመሙ አያስገርምም። በግብፅ የሚገኘው የናይል ወንዝ 6,670 ኪሎ ሜትር ገደማ ይጓዛል። የዓለማችን ትልቁ ወንዝ የሚለው መጠሪያ የተሰጠው በደቡብ አሜሪካ ለሚገኘው ለአማዞን ነው። ለአንዳንድ ወንዞች ግርማ ሞገስ የሚሰጣቸው መጠናቸው ሲሆን በጃፓን እንደሚገኘው ፈጣኑ የቶኔ ወንዝ ያሉ ትናንሽ ወንዞችም የራሳቸው የሆነ ውበት አላቸው።

ወንዝ እንዲፈስስ የሚያደርገው ምንድን ነው? በአጭሩ የስበት ሕግ ነው። የስበት ሕግ ውኃ ከከፍታ ቦታዎች ወደ ዝቅተኛ ቦታዎች እንዲፈስስ የሚያደርግ ሲሆን ይህም በአንዳንድ ቦታዎች እንደ ነጎድጓድ የሚያስገመግሙ ፏፏቴዎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ኃይልና ግርማ ሞገስ ስላላቸው ስለ እነዚህ ፏፏቴዎች ሲናገር እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ ወንዞች ከፍ አደረጉ፤ ወንዞች ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ፤ ወንዞች የሚያስገመግም ማዕበላቸውን ከፍ አደረጉ።”—መዝሙር 93:3

ይሖዋ ፈሪሃ አምላክ የነበረውን ኢዮብን “ለዝናብ መውረጃን . . . ያበጀ ማን ነው?” ሲል ጠይቆት ነበር። (ኢዮብ 38:25) አዎን፣ ይህ ሁሉ ውኃ የሚመጣው ከየት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ የውኃ ኡደት ተብሎ ከሚጠራው ውስብስብ ሥርዓት ጋር የተያያዘ ነው። በምድር ላይ የሚገኘው ውኃ በፀሐይና በስበት ኃይል አማካኝነት በአንድ የማያቋርጥ ኡደት ውስጥ ይጓዛል። ውኃ ሲተን በከባቢው አየር ውስጥ ወደ ላይ ይነሳል። ከዚያም ቀስ በቀስ ሲቀዘቅዝ ወደ ጉምነት ይለወጥና ደመና ይፈጥራል። ከዚያም በዝናብ ወይም በበረዶ መልክ ወደ ምድር ይመለሳል። አብዛኛው ውኃ የሚከማቸው በውቅያኖሶች፣ በሐይቆች፣ በወንዞች፣ በዋልታዎች ላይ በሚገኙ በረዷማ ቦታዎችና በከርሰ ምድር ውስጥ እንዲሁም በግግር በረዶ መልክ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ አስገራሚ ኡደት ሲናገር “ወንዞች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈሳሉ፤ ባሕሩ ግን ፈጽሞ አይሞላም፤ ወንዞች ወደ መጡበት ስፍራ፣ ወደዚያ እንደ ገና ይመለሳሉ” ይላል። (መክብብ 1:7) ይሄን የመሰለውን የማያቋርጥ ኡደት ሊያስጀምር የሚችለው ለጥበቡና ለፍቅራዊ አሳቢነቱ ወደር የሌለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። እንዲህ ዓይነቱ በእጅጉ የረቀቀ ንድፍ ስለ አምላክ ምን ይነግረናል? ታላቅ ጥበብና ፍቅራዊ አሳቢነት ያለው አምላክ መሆኑን ያስገነዝበናል!—መዝሙር 104:13-15, 24, 25፤ ምሳሌ 3:19, 20

ወንዞች መጠናቸው የቱንም ያህል ትልቅ ቢሆንና ቁጥራቸውም ቢበዛ ከዓለማችን ንጹሕ ውኃ ውስጥ የሚይዙት በጣም ጥቂቱን ነው። ቢሆንም ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው። ዋተር የተባለው መጽሐፍ “ውኃን ማግኘትና በተወሰነ መጠንም ቢሆን መቆጣጠር ካልተቻለ በጣም ቀላሉንም ሆነ የተወሳሰበውን የሰው ልጅ ፍላጎት ማሟላት የማይቻል ነው” ይላል። “የሰው ልጅ ለዚህ እውነታ የሰጠው ምላሽ በሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ ትልቁን ቦታ ይይዛል።”

ወንዞች በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የሰውን ልጅ የውኃ ጥም ለማርካትና ጓሮውን ለማልማት አገልግለዋል። በበርካታ ወንዞች ግራና ቀኝ የሚገኘው ለም አፈር ሰብል ለማምረት ተስማሚ ነው። የይሖዋ አገልጋዮች ስለሚያገኙት በረከት በሚናገር ሐሳብ ውስጥ ይህ እንዴት እንደተገለጸ ተመልከት:- “ያዕቆብ ሆይ፤ ድንኳኖችህ፣ እስራኤል ሆይ፤ ማደሪያዎችህ እንዴት ያማሩ ናቸው! እንደ ሸለቆዎች፣ በወንዝ ዳር እንዳሉም የአትክልት ስፍራዎች ተዘርግተዋል፤ በእግዚአብሔር እንደ ተተከሉ ሬቶች፣ በውሃም አጠገብ እንዳሉ ዝግባዎች ናቸው።” (ዘኍልቍ 24:5, 6) ከዚህም በተጨማሪ ወንዞች በስዕሉ ላይ እንደምታያቸው ያሉትን እንደ ዳክዬና ቀበሮ የመሳሰሉ እንስሳት በሕይወት ለማቆየት ይረዳሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ስለ ወንዞች ብዙ እያወቅን በሄድን መጠን ይሖዋን ለማመስገን የዚያኑ ያህል እንገፋፋለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በ2004 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ግንቦትና ሰኔ ላይ ያሉትን ሥዕሎች ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በአርጀንቲናና በብራዚል ድንበር ላይ የሚገኘው የኢግዋሱ ፏፏቴ በዓለማችን ላይ ከሚገኙት ፏፏቴዎች ሁሉ በስፋቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሲሆን ከአንደኛው ጫፉ እስከሌላኛው ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት አለው። ተፈጥሯዊ ውበቱ ባልተለየው ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ የሚገኘው ይህ ፏፏቴ ወደ 300 የሚጠጉ ትናንሽ ፏፏቴዎችን ይዟል። በዝናብ ወቅት ከኢግዋሱ ፏፏቴ ላይ በእያንዳንዱ ሴኮንድ ቁልቁል የሚወረወረው ውኃ 10,000 ኪዩቢክ ሜትር ገደማ ይሆናል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጃፓን የሚገኘው የቶኔ ወንዝ