በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አካል እስካልሆነ ድረስ እንዴት ልናሳዝነው እንችላለን?

“ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝኑ” በማለት የጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ ነበር። (ኤፌሶን 4:30) አንዳንዶች እነዚህ ቃላት መንፈስ ቅዱስ አካል መሆኑን እንደሚጠቁሙ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ‘በታማኝና ልባም መጋቢ’ በሚዘጋጁ ጽሑፎች ላይ የጥንት ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን አካል እንደሆነ ወይም ከልዑሉ አምላክ ጋር እኩል የሆነ የሥላሴ ክፍል አድርገው ይመለከቱት እንዳልነበር የሚያሳይ ቅዱስ ጽሑፋዊና ታሪካዊ ማስረጃ በተደጋጋሚ ወጥቷል። a (ሉቃስ 12:42 የ1954 ትርጉም) በመሆኑም ጳውሎስ ከላይ ያለውን የተናገረው መንፈስ ቅዱስን እንደ አንድ አካል አድርጎ በመመልከት አልነበረም።

መንፈስ ቅዱስ በዓይን የማይታይ የአምላክ ኃይል ነው። (ዘፍጥረት 1:2) ዮሐንስ በውኃ እንዳጠመቀ ሁሉ ኢየሱስ ‘በመንፈስ ቅዱስ’ እንደሚያጠምቅ ተነግሮለት ነበር። (ሉቃስ 3:16) በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ 120 ገደማ የሚሆኑ ደቀ መዛሙርት ‘በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ’ ሲሆን አንድ አካል መጥቶ በውስጣቸው እንዳልገባ የታወቀ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 1:5, 8፤ 2:4, 33) እነዚህ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሰማይ የመኖር ተስፋ ያገኙ ከመሆኑም በላይ የአምላክ መንፈስ በታማኝነት እንዲጸኑ ረድቷቸዋል። (ሮሜ 8:14-17፤ 2 ቆሮንቶስ 1:22) ይህ መንፈስ አምላካዊ ፍሬዎች እንዲያፈሩ ያስቻላቸው ሲሆን መለኮታዊ ሞገስ እንዲያጡ ከሚያደርጓቸው ‘የሥጋ ሥራዎች’ እንዲርቁም እገዛ አድርጎላቸዋል።—ገላትያ 5:19-25

በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያለን የአምላክ አገልጋዮች ከሆንን በመንፈስ ቅዱስ አልተቀባንም ማለት ነው። ቢሆንም ሰማያዊ ተስፋ ካላቸው የአምላክ አገልጋዮች በማይተናነስ ሁኔታ የአምላክ መንፈስ ሊኖረን ይችላል። በመሆኑም እኛም የአምላክን መንፈስ ልናሳዝን እንችላለን። እንዴት?

በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፈውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ቸል የምንል ከሆነ አንዳንድ መጥፎ ባሕርያትን ልናዳብር እንችላለን። ይህም በመንፈስ ቅዱስ ላይ ሆን ብለን ኃጢአት እንድንሠራ ሊያደርገን፣ የይሖዋን ሞገስ ሊያሳጣንና ውሎ አድሮ ለጥፋት ሊዳርገን ይችላል። (ማቴዎስ 12:31, 32) ከባድ ኃጢአት አልሠራን ይሆናል፤ ሆኖም የኋላ ኋላ የመንፈስ ቅዱስን አመራር የሚቃረን አካሄድ እንድንከተል የሚያደርጉ ዝንባሌዎችን ማዳበር ጀምረን ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ሁኔታዎች መንፈስ ቅዱስን ልናሳዝን እንችላለን።

ታዲያ መንፈስ ቅዱስን ከማሳዘን መራቅ የምንችለው እንዴት ነው? አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን መቆጣጠር ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ምዕራፍ 4 ላይ ወደ ውሸት፣ ቁጣ፣ ስንፍናና ተገቢ ያልሆነ ንግግር የሚመሩ ዝንባሌዎችን እንድናስወግድ መክሮናል። ‘አዲሱን ሰውነት’ ከለበስን በኋላ ወደ እነዚህ ዓይነት ድርጊቶች ከተመለስን ውጤቱ ምን ይሆናል? በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን ምክር እየጣስን ነው ማለት ነው። በዚህም መንፈስ ቅዱስን እናሳዝናለን።

በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ላይ ደግሞ ጳውሎስ ዝሙት የመፈጸምን ተገቢ ያልሆነ ፍላጎት እንድናስወግድ የሰጠውን ምክር እናገኛለን። በተጨማሪም ጳውሎስ የሚያሳፍር ምግባርንና ጸያፍ ንግግርን እንዲያስወግዱ የእምነት ባልንጀሮቹን አጥብቆ አሳስቧቸዋል። የአምላክን መንፈስ ላለማሳዘን ከፈለግን በመዝናኛ ምርጫችን ረገድ ይህን ምክር ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። ስለ እነዚህ ነገሮች የማውራት፣ የማንበብና በቴሌቪዥን ወይም በሌላ ነገር የመመልከት ፍላጎት ሊያድርብን አይገባም።

እርግጥ ነው፣ በሌሎች መንገዶችም መንፈስ ቅዱስን ልናሳዝን እንችላለን። የይሖዋ መንፈስ በጉባኤ ውስጥ አንድነት እንዲሰፍን በሚያደርግበት ጊዜ እኛ ግን ጎጂ ሐሜት የምናስፋፋ ወይም በጉባኤው ውስጥ መከፋፈል የምንፈጥር ከሆነ መንፈሱን መቃወማችን አይሆንም? በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር እንዳደረጉት ክርስቲያኖች እኛም መንፈሱን ልናሳዝን እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 1:10፤ 3:1-4, 16, 17) በጉባኤ ውስጥ ላሉት በመንፈስ የተቀቡት ወንድሞች አክብሮት የማናሳይ ከሆነም መንፈስ ቅዱስን እናሳዝናለን።—የሐዋርያት ሥራ 20:28፤ ይሁዳ 8

እንግዲያው አስተሳሰባችንና ድርጊታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈረውና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሚንጸባረቀው የመንፈስ ቅዱስ አመራር ጋር የሚስማማ እንደሆነና እንዳልሆነ መመርመራችን ተገቢ ነው። እንዲሁም ‘በመንፈስ ቅዱስ መጸለይ፣’ በሕይወታችን ላይ እንዲሠራ መፍቀድና ምንጊዜም በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ቃሉ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (ይሁዳ 20) መንፈስ ቅዱስን ፈጽሞ ላለማሳዘንና ምንጊዜም በእርሱ በመመራት ለይሖዋ ቅዱስ ስም ክብር ለማምጣት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ሀብታም ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ግመልን በመርፌ ቀዳዳ ከማሾለክ ጋር አወዳድሮታል። ኢየሱስ የተናገረው ስለ እውነተኛ ግመልና የልብስ መስፊያ መርፌ ነበር?

እነዚህን ቃላት የያዙት ሦስቱም ጥቅሶች ተመሳሳይ ሐሳብ አላቸው። ኢየሱስ “ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል” ብሎ ነበር።—ማቴዎስ 19:24፤ ማርቆስ 10:25፤ ሉቃስ 18:25

አንዳንድ የማመሳከሪያ ጽሑፎች “በመርፌ ቀዳዳ” የሚለው ሐረግ ከኢየሩሳሌም ትላልቅ በሮች በአንዱ ላይ ያለውን ትንሽ በር ያመለክታል ይላሉ። ምሽት ላይ ትልቁ በር ከተዘጋ ትንሹ በር የሚከፈት ሲሆን አንድ ግመል ማሳለፍ ይችላል ተብሎ ይታመናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስለዚህ በር መናገሩ ነበር?

እንደዚያ እንዳልሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ኢየሱስ የተናገረው ስለ ልብስ መስፊያ መርፌ ነበር። በአካባቢው ከአጥንትና ከብረት የተሠሩ ጥንታዊ መርፌዎች ስለተገኙ በወቅቱ መርፌ በማንም ሰው ቤት ሊኖር የሚችል ዕቃ ነበር። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በሉቃስ 18:25 ላይ “ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በልብስ መስፊያ መርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል” ስለሚል የኢየሱስን አባባል ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል።

በርካታ የመዝገበ ቃላት አዘጋጆች በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ላይ ባለው ‘የልብስ መስፊያ መርፌ’ የሚል አተረጓጎም ይስማማሉ። በማቴዎስ 19:24ና በማርቆስ 10:25 ላይ የሚገኘው ራፊስ የተባለው የግሪክኛ ቃል “መስፋት” የሚል ትርጉም ካለው ግስ የመጣ ነው። በሉቃስ 18:25 ላይ የሚገኘው የግሪክኛ ቃል (ቬሎኒ) ደግሞ ለቀዶ ሕክምና ጥቅም ላይ የሚውለውን መርፌ ለማመልከት ይሠራበታል። ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ የተባለው መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል:- “‘የመርፌ ቀዳዳ’ ትንሽ በርን ያመለክታል የሚለው አስተሳሰብ ዘመን ያመጣው ነው፤ ጥንት በዚህ መልክ ይሠራበት እንደነበር የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም። ጌታ እንደዚያ ብሎ የተናገረበት ዓላማ ለሰው አስቸጋሪ የሆነን አንድ ነገር ለመግለጽ ሲሆን መርፌው የስፌት መርፌን ሳይሆን ሌላ ነገርን ያመለክታል በማለት የሁኔታውን አስቸጋሪነት ለማቅለል መሞከሩ አስፈላጊ አይደለም።”—1981, ጥራዝ 3, ገጽ 106

አንዳንዶች በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የገባው “ግመል” የሚለው ቃል “ገመድ” ተብሎ መተርጎም አለበት ይላሉ። ገመድን ለማመልከት የሚሠራበት የግሪክኛ ቃል (ካሚሎስ) እና ለግመል የሚሠራበት ቃል (ካሜሎስ) ተመሳሳይ ናቸው። ይሁን እንጂ አሁን በእጅ ባሉ ጥንታዊ የግሪክኛ የብራና ቅጂዎች ላይ (የሳይናይቲክ, የቫቲካን ቁጥር 1209, እና የአሌክሳንድራይን ቅጂዎች) በማቴዎስ 19:24 ላይ የገባው ቃል “ገመድ” የሚለው ሳይሆን “ግመል” ለማለት የሚሠራበት ነው። ማቴዎስ ወንጌሉን በመጀመሪያ የጻፈው በዕብራይስጥ እንደሆነና ወደ ግሪክኛ የተረጎመው ራሱ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል። ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ አሳምሮ ስለሚያውቅ የተጠቀመው ትክክለኛውን ቃል ነበር።

ስለዚህ ኢየሱስ የተናገረው ስለ ስፌት መርፌና ስለ ግመል ነው ማለት ነው። ኢየሱስ ይህን አባባል የተጠቀመው አንድን አስቸጋሪ የሆነ ነገር ለመግለጽ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሀብታም ሰው ፈጽሞ ወደ አምላክ መንግሥት መግባት አይችልም ማለቱ ነበር? አልነበረም። ምክንያቱም አባባሉን መረዳት ያለብን ቃል በቃል አይደለም። ኢየሱስ እዚህ ላይ የተጠቀመው የግነት ዘይቤ ሲሆን ልክ አንድ ግመል በስፌት መርፌ ቀዳዳ ውስጥ ማለፍ እንደማይችል ሁሉ ሀብታም የሆነ ሰውም ሀብቱን የሙጥኝ ካለና በሕይወቱ ውስጥ ለይሖዋ ቀዳሚውን ቦታ ካልሰጠ ወደ አምላክ መንግሥት መግባት እንደማይችል ማመልከቱ ነበር።—ሉቃስ 13:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:17-19

ኢየሱስ ይህን አባባል የተናገረው አንድ ወጣት የሆነ ሀብታም ገዢ የእርሱ ተከታይ ለመሆን የነበረውን ትልቅ አጋጣሚ ለመቀበል ባመነታበት ወቅት ነበር። (ሉቃስ 18:18-24) አንድ ሃብታም ሰው ከመንፈሳዊ ነገሮች ይልቅ ለቁሳዊ ንብረቱ ከፍተኛ ፍቅር ካለው በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ተስፋ ሊያደርግ አይችልም። ቢሆንም ሀብታም የሆኑ አንዳንድ ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ችለዋል። (ማቴዎስ 27:57፤ ሉቃስ 19:2, 9) ስለሆነም ለመንፈሳዊ ፍላጎቱ ንቁ የሆነና መለኮታዊ እርዳታ የሚሻ ሰው አምላክ ካዘጋጀው የመዳን ዝግጅት ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል።—ማቴዎስ 5:3፤ 19:16-26

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን በሥላሴ ማመን ይኖርብሃልን? የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።