በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአምላክ ክብር የሚሰጡ የተባረኩ ናቸው

ለአምላክ ክብር የሚሰጡ የተባረኩ ናቸው

ለአምላክ ክብር የሚሰጡ የተባረኩ ናቸው

“መጥተው በፊትህ ይሰግዳሉ፤ ለስምህም ክብር ይሰጣሉ።”—መዝሙር 86:9

1. ግዑዝ ፍጥረታት ከሚያደርጉት በላቀ ሁኔታ እኛ ለአምላክ ክብር መስጠት የምንችልባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

 ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎቹ ሁሉ ሊያወድሱት የሚገባ አምላክ ነው። ግዑዝ የሆኑ የፍጥረት ሥራዎቹ ክብር የሚሰጡት ያለ ድምፅ ሲሆን እኛ ግን የማመዛዘን፣ የመረዳት፣ የማድነቅና የማምለክ ችሎታ አለን። ስለዚህም መዝሙራዊው “ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል ይበል! ለስሙ ክብር ዘምሩ፤ ውዳሴውንም አድምቁ!” ሲል የተናገረው ለእኛ ነው።—መዝሙር 66:1, 2

2. ለአምላክ ክብር ስጡ ለሚለው ትእዛዝ ምላሽ የሰጡት እነማን ናቸው? ለምንስ?

2 አብዛኞቹ የሰው ልጆች የአምላክን ሕልውና ለመቀበል ወይም ለእርሱ ክብር ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም። ይሁን እንጂ በ235 አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ በፈጠራቸው ነገሮች አማካኝነት ‘የማይታየው ባሕሪውን’ ማየታቸውንና ፍጥረት ያለ ድምፅ የሚሰጠውን ምሥክርነት ‘መስማታቸውን’ በተግባር አሳይተዋል። (ሮሜ 1:20፤ መዝሙር 19:2, 3) መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ይሖዋን ማወቅና ማፍቀርም ችለዋል። መዝሙር 86:9, 10 ይህን ትንቢት ይዟል:- “ጌታ ሆይ፤ አንተ የሠራሃቸው ሕዝቦች ሁሉ፣ መጥተው በፊትህ ይሰግዳሉ፤ ለስምህም ክብር ይሰጣሉ፤ አንተ ታላቅ ነህና፤ ታምራትም ትሠራለህ፤ አንተ ብቻህን አምላክ ነህ።”

3. ‘እጅግ ብዙ ሰዎች’ አምላክን ‘ቀንና ሌሊት የሚያገለግሉት’ እንዴት ነው?

3 በተመሳሳይ ራእይ 7:9, 15 “እጅግ ብዙ” የሆኑ አምላኪዎች “[አምላክን] ቀንና ሌሊት በመቅደሱ ያገለግሉታል” ሲል ይገልጻል። አምላክ አገልጋዮቹ ቃል በቃል ያለ ምንም ፋታ እንዲያወድሱት ይጠብቅባቸዋል ማለት ሳይሆን አምላኪዎቹ በዓለም ዙሪያ እንደሚገኙ መግለጹ ነው። ስለዚህ በአንዳንድ አገሮች ሲመሽ በሌላው የዓለም ክፍል የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች ግን በትጋት ይሰብካሉ። ከዚህም የተነሳ ለይሖዋ ክብር በሚሰጡ ሰዎች ላይ ፀሐይ ፈጽሞ አትጠልቅም ሊባል ይችላል። በቅርቡ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ” ድምፁን አስተባብሮ ይሖዋን ያወድሳል። (መዝሙር 150:6) እስከዚያ ድረስ ግን ለአምላክ ክብር ለመስጠት በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ እንችላለን? ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ? እንዲሁም ለአምላክ ክብር የሚሰጡ ሰዎች ምን በረከት ተዘጋጅቶላቸዋል? መልሱን ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ ከእስራኤል ነገዶች መካከል አንዱ ስለሆነው ስለ ጋድ ነገድ የሚናገረውን ዘገባ እስቲ እንመርምር።

በጥንት ዘመን የተከሰተ አስቸጋሪ ሁኔታ

4. የጋድ ነገድ ምን አስቸጋሪ ሁኔታ ተደቅኖበት ነበር?

4 ከእስራኤል ነገዶች መካከል የሆኑት የጋድ ሰዎች ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚገኘው ለከብት ርቢ ምቹ የሆነው መሬት እንዲሰጣቸው ጠየቁ። (ዘኍልቁ 32:1-5) ይሁን እንጂ በዚያ አካባቢ መኖር ከባድ ችግሮችን መጋፈጥ ይጠይቃል። በስተ ምዕራብ በኩል ለሚሰፍሩት ነገዶች የዮርዳኖስ ወንዝ ተገን በመሆን ወታደራዊ ወረራን የሚመክት የተፈጥሮ አጥር ይሆናቸዋል። (ኢያሱ 3:13-17) ይሁን እንጂ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን አገር በተመለከተ በጆርጅ አዳም ስሚዝ የተዘጋጀው ዘ ሂስቶሪካል ጂኦግራፊ ኦቭ ዘ ሆሊ ላንድ እንዲህ ይላል:- “ታላቁ የአረብ ምድር አምባ ምንም መሰናክል የሌለው የተንጣለለ ሜዳ ነው። ከዚህም የተነሳ ባለፉት ዘመናት በሙሉ ቦታውን ረሃብተኛ የሆኑ ዘላኖች ይወርሩት የነበረ ሲሆን አንዳንዶቹም ግጦሽ ፍለጋ በየዓመቱ አምባው ላይ ይሰፍራሉ።”

5. ያዕቆብ የጋድ ነገድ ጥቃት ሲሰነዘርበት አጸፋ እንዲመልስ ያበረታታው እንዴት ነው?

5 የጋድ ነገድ በየጊዜው የሚካሄድበትን ወረራ መቋቋም የሚችለው እንዴት ነው? ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ቅድመ አያታቸው ያዕቆብ መሞቻው ተቃርቦ በነበረበት ጊዜ “ጋድን ወራሪዎች አደጋ ይጥሉበታል፤ እርሱ ግን ዱካቸውን ተከታትሎ ብድሩን ይመልሳል” የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 49:19) ላይ ላዩን ሲታይ ያዕቆብ መጥፎ ትንቢት የተናገረ ሊመስል ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የጋድ ነገድ በአጸፋው ጥቃት እንዲሰነዝር የተሰጠ መመሪያ መሆኑ ነው። የጋድ ነገድ እንዲህ ካደረገ የጠላቶቹን ዱካ ተከታትሎ እንደሚያሳድዳቸውና ወራሪዎቹ እፍረት ተከናንበው እንደሚሸሹ ያዕቆብ አረጋግጦለታል።

ከአምልኮታችን ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙን ችግሮች

6, 7. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች የሚያጋጥማቸው ሁኔታ የጋድ ነገድ ካጋጠመው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ የሆነው እንዴት ነው?

6 የጋድ ነገድ እንዳጋጠመው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም የሰይጣን ሥርዓት የሚያመጣው መከራና ጭንቀት ይደርስባቸዋል። እነዚህን ሁኔታዎች ከመጋፈጥ የሚያስጥለን ተአምራዊ ጥበቃ አናገኝም። (ኢዮብ 1:10-12) አብዛኞቻችን ትምህርት፣ ሥራና ልጆች ማሳደግ የሚያስከትልብንን ሸክም ተቋቁመን ለመኖር እንገደዳለን። በግለሰብ ደረጃ ወይም ከስሜት ጋር በተያያዘ ያሉብን ችግሮች ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደሉም። አንዳንዶች ያለባቸውን ‘የሥጋ መውጊያ’ ማለትም ከባድ የአካል ጉዳት ወይም የጤና መታወክ ችለው ለመኖር ይገደዳሉ። (2 ቆሮንቶስ 12:7-10) ሌሎች ደግሞ አልረባም በሚል ስሜት ይደቆሳሉ። ዕድሜ መግፋት የሚያስከትለው “የጭንቀት ጊዜ” አረጋውያን ክርስቲያኖች ብርቱ በነበሩበት ወቅት ያደርጉ እንደነበረው ይሖዋን ማገልገል እንዳይችሉ ያግዳቸዋል።—መክብብ 12:1

7 ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ “ተጋድሎአችን . . . በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋር” እንደሆነ አሳስቦናል። (ኤፌሶን 6:12) ሰይጣንና አጋንንቱ የሚያስፋፉት ‘የዓለም መንፈስ’ ማለትም የዓመፀኝነት መንፈስና የሥነ ምግባር ርኩሰት ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 2:12፤ ኤፌሶን 2:2, 3) አምላክን ይፈራ እንደነበረው እንደ ሎጥ እኛም በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች በሚያደርጉትና በሚናገሩት ሥነ ምግባር የጎደለው ነገር እንጨነቅ ይሆናል። (2 ጴጥሮስ 2:7) ከዚህ በተጨማሪ ሰይጣን ከሚሰነዝርብን ቀጥተኛ ጥቃት ማምለጥ አንችልም። ሰይጣን ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው በያዙ’ በቅቡዓን ክርስቲያኖች ቀሪ አባላት ላይ ጦርነት አውጆአል። (ራእይ 12:17) እንዲሁም የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ሰይጣን በእገዳና በስደት መልክ ጥቃት ይሰነዝርባቸዋል።—ዮሐንስ 10:16

እጅ መስጠት ወይስ አጸፋ መመለስ?

8. ሰይጣን ለሚሰነዝርብን ጥቃት ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? ለምንስ?

8 ሰይጣን ለሚሰነዝርብን ጥቃት ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? በጥንት ዘመን እንደነበረው የጋድ ነገድ ሁሉ እኛም በመንፈሳዊ ጠንካራ መሆንና አምላክ የሚሰጠንን መመሪያ ተከትለን አጸፋ መመለስ ይኖርብናል። የሚያሳዝነው ግን፣ አንዳንዶች በኑሮ ጭንቀት ተውጠው መንፈሳዊ ኃላፊነቶቻቸውን ችላ በማለት እጅ ሰጥተዋል። (ማቴዎስ 13:20-22) አንድ ወንድም በጉባኤያቸው የተሰብሳቢዎች ቁጥር ዝቅተኛ የሆነበትን ምክንያት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ወንድሞች የዛሉ ይመስላል። ሁሉም ከልክ በላይ ይጨነቃሉ።” እርግጥ በዛሬው ጊዜ ሰዎች እንዲዝሉ የሚያደርጓቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። በመሆኑም አንድ ክርስቲያን ለአምላክ የሚያቀርበውን አምልኮ እንደ ተጨማሪ ሸክም ወይም ከባድ ግዴታ አድርጎ ሊመለከተው ይችላል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ትክክል ነው?

9. የክርስቶስን ቀንበር መሸከም ዕረፍት የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ የሕይወት ጫና በጣም ከብዷቸው ለነበረው የዚያን ዘመን ሰዎች ምን እንዳላቸው ተመልከት:- “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ።” ኢየሱስ እንዲህ ሲል አንድ ሰው ለአምላክ የሚያቀርበውን አገልግሎት ቢያቆም ዕረፍት ያገኛል ማለቱ ነው? እንዲያውም ኢየሱስ “ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” ብሏል። ቀንበር አንድ ሰው ወይም እንስሳ ከባድ ዕቃ እንዲሸከም የሚያስችለው ከእንጨት ወይም ከብረት የሚሠራ መሣሪያ ነው። ታዲያ የትኛውም ሰው ቢሆን እንዲህ ዓይነት ቀንበር ለመሸከም ፈቃደኛ የሚሆንበት ምን ምክንያት አለ? ድሮውንም ‘ሸክም ከብዶብን’ የለ? ይህ እውነት ቢሆንም የግሪክኛው ጥቅስ ‘ቀንበሬን አብራችሁኝ ተሸከሙ’ ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። እስቲ አስበው ኢየሱስ ሸክማችንን ለመጋራት ሐሳብ አቅርቦልናል! ሸክሙን ብቻችንን መሸከም የለብንም።—ማቴዎስ 9:36፤ 11:28, 29፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7

10. ለአምላክ ክብር ለመስጠት የምናደርገው ጥረት ምን ያስገኝልናል?

10 የደቀ መዝሙርነትን ቀንበር በምንሸከምበት ጊዜ ሰይጣንን እንደተቃወምነው ይቆጠራል። ያዕቆብ 4:7 “ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል” የሚል ተስፋ ይሰጣል። እንዲህ ሲባል ግን ዲያብሎስን መቃወም ቀላል ነው ማለት አይደለም። አምላክን ማገልገል ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። (ሉቃስ 13:24) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ መዝሙር 126:5 ላይ “በእንባ የሚዘሩ፣ በእልልታ ያጭዳሉ” የሚል ተስፋ ይዟል። አዎን፣ የምናመልከው አምላክ አመስጋኝ ነው። ‘ከልብ ለሚሹት ዋጋ የሚሰጥ’ ሲሆን ክብር የሚሰጡትን ደግሞ ይባርካቸዋል።—ዕብራውያን 11:6

የመንግሥቱ ሰባኪ በመሆን ለአምላክ ክብር መስጠት

11. አገልግሎት ሰይጣን ለሚሰነዝርብን ጥቃት መከታ ሆኖ የሚያገለግለን እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ “ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል። የስብከቱ ሥራ ለአምላክ ‘የምስጋና መሥዋዕት’ የምናቀርብበት ዋነኛ መንገድ ነው። (ማቴዎስ 28:19፤ ዕብራውያን 13:15) “በሰላም ወንጌል ዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ” ተብሎ የተገለጸው ትጥቅ የሰይጣንን ጥቃት ከምንከላከልበት “ሙሉ የጦር ዕቃ” መካከል መጓደል የሌለበት አንደኛው ክፍል ነው። (ኤፌሶን 6:11-15) መስክ አገልግሎት ወጥተን አምላክን ማወደስ እምነታችንን የምንገነባበት ግሩም መንገድ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:13) አእምሯችን አፍራሽ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዳያተኩር ለማድረግ ይረዳናል። (ፊልጵስዩስ 4:8) በመስክ አገልግሎት መሳተፍ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር የሚያንጽ ወዳጅነት እንዲኖረን ያስችለናል።

12, 13. አዘውትሮ በአገልግሎት መሳተፍ ቤተሰቦችን እንዴት ሊጠቅም ይችላል? በምሳሌ አስረዳ።

12 ከዚህ በተጨማሪ የስብከቱ ሥራ ቤተሰቦች የሚታነጹበት እንቅስቃሴ ሊሆን ይችላል። ልጆች መዝናናት እንደሚያስፈልጋቸው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ቤተሰቡ አንድ ላይ ሆኖ በአገልግሎት የሚያሳልፈው ጊዜ አሰልቺ መሆን አይኖርበትም። ወላጆች ልጆቻቸው በስብከቱ ሥራ ውጤታማ እንዲሆኑ በማሰልጠን አገልግሎቱን እንዲወዱት ማድረግ ይችላሉ። ልጆች በደንብ የሚችሉትን ነገር መሥራት ያስደስታቸው የለ? ወላጆች ሚዛናዊ ሆነው ልጆቻቸው ከአቅማቸው በላይ እንዲሠሩ ባለማስገደድ ከአገልግሎት ደስታ እንዲያገኙ ሊረዷቸው ይችላሉ።—ዘፍጥረት 33:13, 14

13 ከዚህ በተጨማሪ አንድ ላይ ሆኖ አምላክን የሚያወድስ ቤተሰብ የጠበቀ ወዳጅነት ይኖረዋል። አማኝ ያልሆነው ባሏ ከአምስት ልጆች ጋር ጥሏት የሄደውን የአንዲት እህት ሁኔታ ተመልከት። በዚህ ጊዜ ወደ ሥራው ዓለም መግባትና ለልጆቿ የሚያስፈልገውን ሥጋዊ ነገር ማሟላት ግድ ሆነባት። የልጆቿን መንፈሳዊ ፍላጎት የማሟላቱን ጉዳይ ችላ እስክትል ድረስ በሥራ ተወጥራ ይሆን? እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “መጽሐፍ ቅዱስንና በዚያ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በትጋት አጠና የነበረ ሲሆን የተማርኩትን በሥራ ለማዋል ጥረት አደርጋለሁ። ልጆቹን ወደ ስብሰባም ሆነ ከቤት ወደ ቤት ለማገልገል ሁልጊዜ እወስዳቸዋለሁ። ታዲያ ጥረቴ ምን አስገኘልኝ? አምስቱም ልጆቼ ተጠምቀዋል።” እናንተም በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ማድረጋችሁ ልጆቻችሁን “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” ለማሳደግ በምታደርጉት ጥረት ሊረዳችሁ ይችላል።—ኤፌሶን 6:4

14. (ሀ) ወጣቶች በትምህርት ቤት ለአምላክ ክብር መስጠት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ወጣቶች ‘በወንጌል እንዳያፍሩ’ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

14 ወጣቶች በምትኖሩበት አገር ውስጥ በትምህርት ቤት መመሥከር በሕግ የታገደ ካልሆነ በዚህ ረገድ ለአምላክ ክብር ትሰጣላችሁ ወይስ የሰው ፍርሃት ዝም እንድትሉ ያደርጋችኋል? (ምሳሌ 29:25) በፖርቶ ሪኮ የምትኖር የይሖዋ ምሥክር የሆነች አንዲት የ13 ዓመት ልጅ እንዲህ ብላለች:- “የምሰብከው እውነት መሆኑን ስለማውቅ ትምህርት ቤት ውስጥ መመሥከር አሳፍሮኝ አያውቅም። ክፍል ውስጥ አጋጣሚ ባገኘሁ ቁጥር እጄን አውጥቼ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩትን ነገር እናገራለሁ። ትርፍ ጊዜ ሳገኝ ደግሞ ወደ ቤተ መጻሕፍት ሄጄ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች የተባለውን መጽሐፍ አነብባለሁ።” a ይሖዋ ጥረቷን ባርኮላታል? እንዲህ ትላለች:- “አንዳንድ ጊዜ የክፍል ጓደኞቼ ጥያቄ ይጠይቁኛል፤ መጽሐፉን እንዳመጣላቸው የሚጠይቁኝም አሉ።” በዚህ ረገድ ወደኋላ ትል ከነበረ በግል ጥናት በመትጋት “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ” በእርግጠኝነት ማወቅ ሊያስፈልግህ ይችላል። (ሮሜ 12:2) ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርከው ነገር እውነት መሆኑን በእርግጠኝነት ካመንክ ‘በወንጌል አታፍርም።’—ሮሜ 1:16

ለአገልግሎት ‘የተከፈተ በር’

15, 16. አንዳንድ ክርስቲያኖች የገቡበት “ታላቅ የሥራ በር” ምንድን ነው? ምን በረከቶችስ አግኝተዋል?

15 ሐዋርያው ጳውሎስ “ታላቅ የሥራ በር” የተከፈተለት መሆኑን ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 16:9) የአንተ ሁኔታ ሥራ በሞላበት በር እንድትገባ ይፈቅድልህ ይሆን? ለምሳሌ ያህል የዘወትር ወይም ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል በስብከቱ ሥራ በየወሩ 70 ወይም 50 ሰዓት ማሳለፍ ይጠይቃል። አቅኚዎች በታማኝነት የሚያከናውኑትን አገልግሎት ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው በአድናቆት እንደሚመለከቱት የታወቀ ነው። ይሁንና በአገልግሎት ሰፋ ያለ ሰዓት ማሳለፋቸው ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው የተሻሉ እንደሆኑ እንዲሰማቸው አያደርግም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “ከቁጥር የማንገባ አገልጋዮች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን ተግባር ፈጽመናል” በማለት እንድናሳየው ያበረታታንን ባሕርይ ያዳብራሉ።—ሉቃስ 17:10

16 አቅኚነት ራስ መግዛት፣ በፕሮግራም መመራትና መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆን ይጠይቃል። የሚያስገኘው በረከት ግን ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይደለም። በወጣትነት ዕድሜ ላይ የምትገኘው ታሚካ የተባለች አቅኚ እንዲህ ብላለች:- “የአምላክን የእውነት ቃል በትክክል መጠቀም መቻል ትልቅ በረከት ነው። አቅኚ ከሆናችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ የመጠቀም ሰፊ አጋጣሚ ይኖራችኋል። ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል ለእያንዳንዱ ሰው የሚስማማ ጥቅስ ወዲያውኑ ትዝ ይለኛል።” (2 ጢሞቴዎስ 2:15) ማይከ የተባለች አቅኚ እንዲህ ትላለች:- “እውነት የሰዎችን ሕይወት እንዴት እንደሚለውጥ ማየት ሌላው አስደሳች በረከት ነው።” በተመሳሳይ ማቲው የተባለ ወጣት “አንድ ሰው ወደ እውነት ሲመጣ ማየት” አስደሳች መሆኑን ከመግለጹም በተጨማሪ “ይህን ሊተካ የሚችል አስደሳች ሥራ የለም” ሲል ተናግሯል።

17. አንዲት እህት ለአቅኚነት የነበራትን የተሳሳተ አመለካከት ያሸነፈችው እንዴት ነው?

17 አቅኚ በመሆን በበሩ መግባት ትችል እንደሆነ ማየት ትፈልጋለህ? ምናልባት ፍላጎቱ ቢኖርህም ብቁ እንዳልሆንክ ይሰማህ ይሆናል። ኬንያተ የተባለች ወጣት እህት “ለአቅኚነት ጥሩ አመለካከት አልነበረኝም” ስትል በግልጽ ተናግራለች። “እችለዋለሁ የሚል ሐሳብ አልነበረኝም። መግቢያ እንዴት እንደምዘጋጅ ወይም ጥቅስ ጠቅሼ እንዴት ማስረዳት እንደምችል አላውቅም ነበር።” ሆኖም ሽማግሌዎች አብራት የምታገለግል ጎልማሳ እህት መደቡላት። ኬንያተ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “ከእርሷ ጋር ማገልገል በጣም ያስደስታል። አቅኚ የመሆን ፍላጎት ያሳደረብኝ ያ ነው።” አንተም የተወሰነ ማበረታቻና ሥልጠና ብታገኝ አቅኚ የመሆን ፍላጎት ያድርብህ ይሆናል።

18. ሚስዮናዊ የሆኑ ክርስቲያኖች ምን በረከት ሊያገኙ ይችላሉ?

18 አቅኚነት ለሌሎች የአገልግሎት መብቶች መሸጋገሪያ ሊሆንም ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አቅኚነት አንዳንድ ባልና ሚስት በሚስዮናዊነት ውጭ አገር ሄዶ ለማገልገል የሚሰጠውን ሥልጠና ለማግኘት ብቃቱን እንዲያሟሉ ያስችላቸዋል። ሚስዮናውያን የማያውቁትን አገር ምናልባትም ደግሞ አዲስ ቋንቋ፣ ባሕልና ምግብ መልመድ ይኖርባቸዋል። ሆኖም ከአገልግሎት የሚገኘው ደስታ እነዚህን ችግሮች ከቁጥር እንዳይገቡ ያደርጋቸዋል። ሜክሲኮ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በሚስዮናዊነት ያገለገሉት እህት ሚልድረድ እንዲህ ይላሉ:- “ሚስዮናዊ ለመሆን ባደረግሁት ውሳኔ ተቆጭቼ አላውቅም። ከልጅነቴ አንስቶ ስመኘው የነበረ ነገር ነው።” እኚህ እህት ምን በረከት አግኝተዋል? “አገሬ እያለሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማግኘት በጣም እቸገር ነበር። እዚህ ግን አራት የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼ በአንድ ጊዜ አገልግሎት የጀመሩበት ወቅት አጋጥሞኛል!”

19, 20. የቤቴል አገልግሎት፣ ዓለም አቀፍ አገልግሎትና የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለብዙዎች በረከት ያስገኘላቸው እንዴት ነው?

19 በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ማለትም በቤቴል የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶችም ብዙ በረከት ያገኛሉ። በጀርመን የሚያገለግለው ስቬን የተባለ ወጣት ወንድም በቤቴል ስለሚያከናውነው ሥራ እንዲህ ብሏል:- “የምሠራው ሥራ ዘላቂ ጥቅም እንዳለው ይሰማኛል። ያለኝን ሙያ በዓለም ውስጥ ልጠቀምበት እችል ነበር። እንዲህ ማድረግ ግን ከስሮ ሊዘጋ በተቃረበ ባንክ ውስጥ ገንዘብ ከማጠራቀም ተለይቶ አይታይም።” እርግጥ ያለ ደሞዝ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኖ ማገልገል መሥዋዕት መክፈል ይጠይቃል። ይሁንና ስቬን እንዲህ ይላል:- “ከሥራ በኋላ ወደ ቤት ስትሄዱ የሠራችሁት ሥራ ሁሉ ለይሖዋ ብላችሁ ያደረጋችሁት መሆኑን ታውቃላችሁ። ይህ ደግሞ ከፍተኛ እርካታ ያስገኝላችኋል።”

20 አንዳንድ ወንድሞች ዓለም አቀፍ አገልጋዮች በመሆን ከአገራቸው ውጪ በቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ላይ የመሥራት መብት አግኝተዋል። በስምንት አገሮች ውስጥ በግንባታ ሥራ የተሳተፉ አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “እዚህ ያገኘናቸው ወንድሞች በጣም የሚወደዱ ናቸው። ከእነርሱ መለየት በጣም ይከብዳል፤ እንዲያውም መለየት የሚያስከትለው ሐዘን ሲደርስብን ይህ ለስምንተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። እጅግ አስደሳች ጊዜ አሳልፈናል!” ሌላው የአገልግሎት በር ደግሞ የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሲሆን በዚህ ትምህርት ቤት ብቃቱን ያሟሉ ነጠላ ወንድሞች መንፈሳዊ ሥልጠና ያገኛሉ። ከትምህርት ቤቱ የተመረቀ አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንዲህ ለመሰለው ድንቅ ትምህርት ቤት የተሰማኝን አመስጋኝነት ምን ብዬ እንደምገልጽላችሁ አላውቅም። ሰዎችን ለማሰልጠን ይህን ያህል ጥረት የሚያደርግ ሌላ የትኛው ድርጅት ነው?”

21. ለአምላክ ከሚያቀርቡት አገልግሎት ጋር በተያያዘ በሁሉም ክርስቲያኖች ፊት የተደቀነው ፈታኝ ሁኔታ ምንድን ነው?

21 አዎን፣ ክፍት የሆኑ በርካታ የአገልግሎት በሮች አሉ። እርግጥ አብዛኞቻችን ቤቴል ገብተን ወይም ውጭ አገር ሄደን ማገልገል እንደማንችል የታወቀ ነው። ኢየሱስ እንኳ ክርስቲያኖች ካሉበት የተለያየ ሁኔታ አንጻር የሚያፈሩት “ፍሬ” መጠን እንደሚለያይ ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:23) በመሆኑም ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን በሁላችንም ፊት የተደቀነው ፈተና ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን አቅማችን የፈቀደውን ያህል የመሥራቱ ጉዳይ ነው። ሁኔታችን በሚፈቅድልን መጠን በይሖዋ አገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ በማድረግ ለይሖዋ ክብር እንሰጣለን እንዲሁም ይሖዋ በእኛ እንደሚደሰት እርግጠኛ መሆን እንችላለን። በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም የሚኖሩትን የኢተልን ሁኔታ ተመልከት። በተቋሙ ውስጥ አብረዋቸው ለሚኖሩ ሰዎች ምንጊዜም ይሰብካሉ፤ እንዲሁም በስልክ ምሥክርነት ይሰጣሉ። የአቅም ገደብ ቢኖርባቸውም በአገልግሎት የሙሉ ነፍስ ተሳትፎ ያደርጋሉ።—ማቴዎስ 22:37

22. (ሀ) ለአምላክ ክብር መስጠት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? (ለ) ከፊታችን ምን ዓይነት አስደሳች ወቅት ይጠብቀናል?

22 ሆኖም የስብከቱ ሥራ ለይሖዋ ክብር ከምንሰጥባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ብቻ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤትና በቤታችን ስንሆን በባሕርያችንም ሆነ በአለባበሳችን ምሳሌ በመሆን የይሖዋን ልብ እናስደስታለን። (ምሳሌ 27:11) ምሳሌ 28:20 “ታማኝ ሰው እጅግ ይባረካል” የሚል ተስፋ ይሰጣል። በመሆኑም ብዙ በረከት እንደምናጭድ ስለምናውቅ ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት ‘ብዙ መዝራት’ ይኖርብናል። (2 ቆሮንቶስ 9:6) በዚህ ከቀጠልን “እስትንፋስ ያለው ሁሉ” ለይሖዋ የሚገባውን ክብር በሚሰጥበት አስደሳች ወቅት በሕይወት የመኖር መብት እናገኛለን!—መዝሙር 150:6

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለው መጽሐፍ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ነው።

ታስታውሳለህ?

• የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን “ቀንና ሌሊት” የሚያገለግሉት እንዴት ነው?

• የጋድ ነገድ ያጋጠመው ችግር ምንድን ነበር? ይህስ በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች ምን ትምህርት ይዟል?

• አገልግሎት ሰይጣን ከሚሰነዝርብን ጥቃት ከለላ የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

• አንዳንዶች የገቡበት ‘ክፍት በር’ ምንድን ነው? ምን በረከቶችስ አግኝተዋል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጋድ ነገድ ወራሪ ኃይሎችን እንደተዋጋ ሁሉ ክርስቲያኖችም ሰይጣን የሚሰነዝርባቸውን ጥቃት መመከት ይገባቸዋል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሌሎች ጋር ማገልገላችን የሚያንጽ ወዳጅነት እንድናገኝ ያስችለናል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አቅኚነት እንደሚከተሉት ላሉ የአገልግሎት መብቶች መሸጋገሪያ ሊሆን ይችላል:-

1. ዓለም አቀፍ አገልግሎት

2. የቤቴል አገልግሎት

3. የሚስዮናዊነት አገልግሎት