በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች መልካም ማድረግ

ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች መልካም ማድረግ

ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች መልካም ማድረግ

ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ” በማለት አሳስቦናል። (ገላትያ 6:10) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች ሁሉ በተለይም ለእምነት አጋሮቻቸው መልካም በማድረግ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ለማዋል ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ። ይህ በችግር ጊዜያት ከአንዴም ብዙ ጊዜ ታይቷል። እስቲ በሦስት አገሮች የተፈጸሙ የቅርብ ጊዜ ምሳሌዎችን እንመልከት።

በታኅሣሥ 2002፣ ጉዋም በሰዓት ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ በሚምዘገዘግ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተመታች። በርካታ ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን አንዳንዶቹም ሙሉ በሙሉ ፈራረሱ። በጉዋም አቅራቢያ የሚገኙ ጉባኤዎች በአደጋው በጣም የተጠቁትን የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች ለመርዳት ፍርስራሹን በማጽዳት የሚያግዙ ቡድኖችን በአፋጣኝ አደራጁ። የጉዋም ቅርንጫፍ ቢሮ የፈራረሱ ቤቶችን ለመጠገን የሚያስፈልገውን የቁሳቁስና የሰው ኃይል እርዳታ ያቀረበ ከመሆኑም በላይ የሃዋይ ቅርንጫፍ ቢሮም ድጋፍ ሰጥቷል። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ አንድ የአናጺዎች ቡድን በመልሶ ግንባታው ሥራ ለመርዳት ከሃዋይ የመጣ ሲሆን አንዳንድ የአካባቢው ወንድሞችም እነርሱን ለማገዝ ከሥራቸው እረፍት ወሰዱ። በሥራው ላይ የታየው አስደሳች የትብብር መንፈስም ለአካባቢው ኅብረተሰብ ግሩም ምሥክርነት ሰጥቷል።

በማያንማር፣ በማንዳሌይ ከተማ ዳርቻ ላይ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ አቅራቢያ እሳት ተነሳ። እሳቱ ከተነሳበት አካባቢ ብዙም ሳይርቅ የአንዲት ጉባኤ መምጣት ያቆመች እህትና የቤተሰብዋ መኖሪያ ይገኝ ነበር። ነፋሱ ወደ ቤቷ አቅጣጫ ይነፍስ ስለነበር እህት ወደ አዳራሹ ሮጣ ሄዳ እርዳታ ጠየቀች። በወቅቱ አዳራሹ እየታደሰ ስለነበር በርካታ ወንድሞች በዚያ ነበሩ። እህት በዚያ አካባቢ እንደምትኖር ስላላወቁ ሲያገኟት ተደነቁ። ከዚያም ወንድሞች በፍጥነት በመረባረብ የቤተሰቡን ንብረት ከእሳቱ ማሸሽ ጀመሩ። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ባለቤቷ ስለ እሳቱ ሰምቶ በፍጥነት ሲመጣ ወንድሞች ቤተሰቡን እየረዷቸው ደረሰ። በዚህ በጣም ተገርሞ ወንድሞችን ያመሰገነ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ሌቦች እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎችን ስለሚጠቀሙ ንብረቱ ከዘረፋ በመዳኑ ተደሰተ። ወንድሞች ባደረጉት ደግነት የተነሳ እህትና ወንድ ልጅዋ ዳግመኛ ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ለመቀራረብ የተነሳሱ ሲሆን አሁን በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ።

ባለፈው የአገልግሎት ዓመት በሞዛምቢክ በተከሰተው ድርቅና የሰብል መበላሸት ሳቢያ በርካታ ሰዎች ለረሃብ ተዳርገው ነበር። የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ቢሮ ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ለተቸገሩት ሰዎች ምግብ አቀረበ። ምግብ ይከፋፈል የነበረው በመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ከጉባኤ ስብሰባ በኋላ ነበር። አንዲት ነጠላ እህት “ከስብሰባው በኋላ ወደ ቤት ስንመለስ ለልጆቼ የምሰጠው ምግብ ስላልነበረኝ ወደ ጉባኤ ስመጣ በጣም አዝኜ ነበር” ብላለች። ወንድሞች ያደረጉላት ፍቅራዊ እርዳታ ወዲያውኑ መንፈሷን ያነቃቃላት ሲሆን “ልክ ትንሣኤ ያገኘሁ ያህል ነው የተሰማኝ!” ብላለች።

ከዚህ በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች አጽናኝና ተስፋ ሰጪ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለሰዎች በማካፈል በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘መልካም ያደርጋሉ።’ ከረጅም ጊዜ በፊት ‘[አምላካዊ ጥበብን] የሚያዳምጥ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤ ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል’ በማለት እንደተናገረው እንደ ጠቢቡ ሰሎሞን ዓይነት እምነት አላቸው።—ምሳሌ 1:33

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1, 2. በሞዛምቢክ ለተቸገሩ ሰዎች ምግብ ሲከፋፈል

3, 4. ጉዋምን የመታት አውሎ ነፋስ በርካታ ቤቶችን አፈራርሷል

[ምንጭ]

በስተ ግራ ልጁ Andrea Booher/FEMA News Photo፤ ከላይ ሴትየዋ AP Photo/Pacific Daily News, Masako Watanabe