በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጨለማ እስር ቤት ወደ ስዊስ ተራሮች

ከጨለማ እስር ቤት ወደ ስዊስ ተራሮች

የሕይወት ታሪክ

ከጨለማ እስር ቤት ወደ ስዊስ ተራሮች

ሎታር ቫልተር እንደተናገረው

ኮሚኒስት በነበረችው ምሥራቅ ጀርመን በሚገኙ ጨለማ እስር ቤቶች ውስጥ በቀላሉ የማይገፉ ሦስት ዓመታት ካሳለፍኩ በኋላ የነጻነት አየር የምተነፍስበትና አፍቃሪ ከሆነው ቤተሰቤ ጋር የምቀላቀልበት ቀን እስኪደርስ በጣም ጓጉቼ ነበር።

ይሁን እንጂ በስድስት ዓመቱ ልጄ በዮሐንስ ፊት ላይ የተመለከትኩት የግራ መጋባት ስሜት ፈጽሞ ያልጠበቅኩት ነገር ሆነብኝ። በእስር ላይ በቆየሁባቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ አንድም ጊዜ ስላላየኝ እንግዳ ሆንኩበት።

እኔ ግን ከልጄ በተለየ መልኩ አፍቃሪ ከሆኑት ወላጆቼ ሳልለይ ነበር ያደግሁት። በ1928 ጀርመን ውስጥ ኬምኒትስ በምትባል ከተማ የተወለድኩ ሲሆን ቤተሰባችን እርስ በርሱ ይቀራረብ ነበር። አባቴ በሃይማኖት ላይ የነበረውን ቅሬታ ከመናገር ወደኋላ የሚል ሰው አልነበረም። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የገና በዓል በሚከበርበት ዕለት በአንደኛው ወገን የተሰለፉ “ክርስቲያን” ወታደሮች ከሌላው ወገን ወታደሮች ጋር “እንኳን አደረሳችሁ” ከተባባሉ በኋላ በማግሥቱ እርስ በርስ መገዳደላቸውን ይቀጥሉ እንደነበር ያስታውሳል። አባቴ የሃይማኖትን ያህል ግብዝነት የሚታይበት ቦታ እንደሌለ ይሰማው ነበር።

ያደረብኝ ግራ መጋባት ተወግዶ የእምነት ሰው ሆንኩ

ደስ የሚለው ግን እኔ እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ አጋጥሞኝ አያውቅም። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃ የ17 ዓመት ልጅ ስለነበርኩ ለውትድርና ሳልመለመል ለጥቂት አመለጥኩ። ያም ሆኖ ግን ‘ሰዎች እርስ በርሳቸው የሚገዳደሉት ለምንድን ነው? ማንን ማመን እችላለሁ? እውነተኛ ደኅንነት ማግኘት የምችለው ከየት ነው?’ እንደሚሉት ያሉ እረፍት የሚነሱ ጥያቄዎች ያስጨንቁኝ ነበር። እኛ እንኖርባት የነበረችው ምሥራቅ ጀርመን በሶቪዬት ቁጥጥር ሥር ወደቀች። በአውዳሚው ጦርነት ተሰላችተው የነበሩ ሰዎች ፍትሕ፣ እኩልነት፣ አንድነትና ሰላማዊ ግንኙነት በሚሉት የኮሚኒዝም መርሆዎች ተማርከው ነበር። ይዋል ይደር እንጂ ከእነዚህ ቅን ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በእጅጉ ግራ መጋባታቸው የማይቀር ነው። ይህ የሚሆነው ግን በሃይማኖት ሳይሆን በፖለቲካ ነው።

የይሖዋ ምሥክር የነበረች አንዲት አክስቴ ስለ እምነቷ የነገረችኝ ለጥያቄዎቼ አጥጋቢ መልስ ስፈልግ በነበረበት ወቅት ላይ ነበር። በዚያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ ሰጥታኝ ነበር። ይህን ጽሑፍ ማንበቤ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ማቴዎስ ምዕራፍ 24ን በሙሉ እንዳነብ አነሳሳኝ። መጽሐፉ የምንኖረው ‘በዓለም መጨረሻ’ ላይ ስለመሆኑና የሰው ልጅ ችግሮች ዋነኛው መንስዔ ማን እንደሆነ በሚሰጠው ምክንያታዊና አሳማኝ ማብራሪያ በጣም ተገረምኩ።—ማቴዎስ 24:3፤ ራእይ 12:9

ብዙም ሳይቆይ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ሌሎች ጽሑፎችን ያገኘሁ ሲሆን እነዚህን ጽሑፎች በጉጉት ሳነብብ በጣም ስፈልገው የነበረውን እውነት እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ። ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 በሰማይ መንገሡንና ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ለመባረክ ሲል በቅርቡ አምላካዊ አክብሮት የሌላቸውን ሰዎች እንደሚያስወግድ ሳውቅ በጣም ተገረምኩ። አዲስ የሆነብኝ ሌላው ነገር ደግሞ ስለ ቤዛው ያገኘሁት ግልጽ እውቀት ነበር። ይህም ይሖዋ አምላክ ይቅር እንዲለኝ ወደ እርሱ ልባዊ ጸሎት እንዳቀርብ ረድቶኛል። ከዚህም በላይ በያዕቆብ 4:8 ላይ በሚገኘው “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በሚለው በደግነት የቀረበ ግብዣ ልቤ በእጅጉ ተነክቷል።

ለወላጆቼና ለእህቴ ስለ አዲሱ እምነቴ በጋለ ስሜት እነግራቸው የነበረ ቢሆንም መጀመሪያ ላይ የምላቸውን ለመቀበል አልፈለጉም ነበር። ሆኖም ይህ ሁኔታ ኬምኒትስ አካባቢ በቁጥር አነስተኛ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የነበረኝን ፍላጎት አላቀዘቀዘውም። የሚገርመው ደግሞ ወላጆቼና እህቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘሁበት በዚህ ስብሰባ ላይ አብረውኝ ተገኝተው ነበር! ይህ የሆነው በ1945/46 የክረምት ወራት ሲሆን ከጊዜ በኋላ እኛ በምንኖርበት በሃርታኡ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ሲቋቋም ቤተሰቦቼ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው መገኘት ጀመሩ።

“ገና ሕፃን ልጅ ነኝ”

ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መማሬ እንዲሁም ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር አዘውትሬ መሰብሰቤ ሕይወቴን ለይሖዋ እንድወስን የረዳኝ ሲሆን ግንቦት 25, 1946 ተጠመቅሁ። በጣም ያስደሰተኝ ደግሞ የቤተሰቤ አባላት መንፈሳዊ እድገት አድርገው ከጊዜ በኋላ ሦስቱም ታማኝ የይሖዋ ምሥክር መሆናቸው ነው። እህቴ አሁንም ኬምኒትስ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ይሖዋን በቅንዓት በማገልገል ላይ ትገኛለች። እናቴ በ1965 አባቴ ደግሞ በ1986 እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል።

ከተጠመቅሁ ከስድስት ወራት በኋላ ልዩ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ‘አመቺ በሆነውም ሆነ ባልሆነው ጊዜ’ ይሖዋን የማገልገል የዕድሜ ልክ ሥራ የጀመርኩት በዚህ ጊዜ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 4:2) ብዙም ሳይቆይ ሌሎች የአገልግሎት መብቶች ተከፈቱልኝ። በምሥራቅ ጀርመን ርቆ በሚገኝ አንድ አካባቢ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ያስፈልጉ ነበር። እኔና አንድ ወንድም እዚያ እንድንመደብ አመለከትን። ሆኖም እንዲህ ላለው ኃላፊነት ተሞክሮም ሆነ ጉልምስና እንደሚጎድለኝ ተሰምቶኝ ነበር። ዕድሜዬ ገና 18 ዓመት ስለነበር “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝና” እንዳለው እንደ ኤርምያስ ተሰምቶኝ ነበር። (ኤርምያስ 1:6) ብቃት እንደሚጎድለኝ ይሰማኝ የነበረ ቢሆንም ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ሄደን እንድናገለግል በደግነት ጠየቁን። በመሆኑም በብራንደንበርግ ግዛት በምትገኝ በልጽክ በምትባል ትንሽ ከተማ ተመደብን።

በዚያ የአገልግሎት ክልል መስበክ በጣም አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም ጠቃሚ ትምህርቶች አስገኝቶልኛል። ከጊዜ በኋላ በርካታ ነጋዴ ሴቶች የመንግሥቱን መልእክት ተቀብለው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። የአካባቢው ሕዝብ ባሕሉን የሚያጠብቅና አዳዲስ ነገሮች በጥርጣሬ ዓይን የሚመለከት ቢሆንም እንዲህ ያለውን እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አላሉም። የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ቀሳውስት በስብከት እንቅስቃሴያችን ምክንያት አምርረው ይቃወሙንና ስማችንን ለማጥፋት በሐሰት ይወነጅሉን ነበር። ሆኖም በይሖዋ አመራርና ጥበቃ በመተማመን ፍላጎት ያላቸው በርካታ ሰዎች እውነትን እንዲቀበሉ ለመርዳት ችለናል።

የስደት ዳመና አንዣበበ

በ1948 የተለያዩ በረከቶች ያገኘሁ ሲሆን ያልተጠበቁ ችግሮችም አጋጥመውኛል። በመጀመሪያ በቱሪንጂያ፣ ሩደልሽታት ከተማ በአቅኚነት እንዳገለግል ተመደብኩ። እዚያም ከበርካታ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ጋር የተዋወቅሁ ከመሆኑም በላይ ከእነርሱ ጋር አስደሳች ጊዜ አሳልፌአለሁ። በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ደግሞ በዓይነቱ ልዩ የሆነ በረከት አገኘሁ። በኬምኒትስ ጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ የማውቃትን ኤሪካ ኡልማን የተባለች ታማኝና ቀናተኛ ወጣት አገባሁ። የትውልድ ከተማዬ በሆነችው በሃርታኡ አንድ ላይ አቅኚ ሆነን ማገልገል ጀመርን። ይሁን እንጂ ኤሪካ ከጊዜ በኋላ በጤናና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል አልቻለችም።

ወቅቱ ለይሖዋ ምሥክሮች በጣም አስቸጋሪ ነበር። የኬምኒትስ የሠራተኛ ደኅንነት ጉዳይ መሥሪያ ቤት የስብከት ሥራዬን አቋርጬ የሙሉ ቀን ሰብዓዊ ሥራ እንድይዝ ለማስገደድ የራሽን ካርድ ከለከለኝ። ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የእኔን ጉዳይ በማንሳት ከመንግሥት ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት ሞከሩ። ሙከራቸው ያልተሳካ ከመሆኑም በላይ ሰኔ 23, 1950 መቀጫ እንድከፍል ወይም ለአንድ ወር እንድታሰር ተፈረደብኝ። ይግባኝ ጠይቀን ነበር፤ ሆኖም ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኙን ውድቅ ስላደረገብን እስር ቤት ገባሁ።

ይህ ሁኔታ እየተጠናከረ የመጣውን የስደት ዳመና የሚያመላክት ነበር። አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መስከረም 1950 በመገናኛ ብዙሐን ስማችንን የሚያጠፋ ዘገባ ከቀረበ በኋላ የኮሚኒስቱ መንግሥት በሥራዎቻችን ላይ እገዳ ጣለ። ፈጣን እድገት በማድረጋችንና በገለልተኝነት አቋማችን ምክንያት ‘በሃይማኖት ስም “አጠያያቂ እንቅስቃሴ” በማድረግ ለምዕራባውያን የሚሰልል አደገኛ ድርጅት’ ተብለን ተወነጀልን። እገዳው በተጣለበት ዕለት እኔ እስር ቤት እንዳለሁ ባለቤቴ ዮሐንስ የተባለውን ልጃችንን ወለደች። የደኅንነት አባላት አዋላጅዋ ብትቃወማቸውም በኃይል ገብተው ይህን ውንጀላቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለማግኘት ቤታችንን በረበሩ። እርግጥ ምንም አላገኙም። ዳሩ ምን ያደርጋል ከጊዜ በኋላ ወደ ጉባኤያችን ሰላይ ለማስገባት ያደረጉት ሙከራ ተሳክቶላቸው ጥቅምት 1953 ኃላፊነት ያለን ወንድሞች በሙሉ ተያዝን።

ጨለማ ክፍል ውስጥ ታሰርኩ

ጥፋተኞች ናቸው ተብለን ከሦስት እስከ ስድስት ዓመት የሚደርስ እስራት ከተፈረደብን በኋላ በርካታ ወንድሞቻችን ወደታሰሩበት ዝዊካው ውስጥ በኡስተሽቲን ሕንፃ ሥር ወደሚገኝ የታፈገ ጨለማ እስር ቤት ተላክን። የእስር ቤቱ ሁኔታ በጣም ዘግናኝ ቢሆንም ከጎለመሱ ወንድሞች ጋር መገናኘታችን በእርግጥ የሚያስደስት ነበር። ነጻነት ቢነፈገንም መንፈሳዊ ምግብ እናገኝ ነበር። በመንግሥት የተጠላንና እገዳ የተጣለብን ቢሆንም መጠበቂያ ግንብ በድብቅ ወደ እስር ቤቱ ገብቶ ክፍላችን ድረስ ይመጣልን ነበር! እንዴት?

በከሰል ማውጫዎች ውስጥ ለመሥራት ከውጭ የሚመጡ የይሖዋ ምሥክሮች ከመካከላችን እዚያ እንዲሠሩ ከተመደቡ አንዳንድ ወንድሞች ጋር ስለሚገናኙ መጽሔት ይሰጧቸው ነበር። እነዚህ ወንድሞች መጽሔቶቹን ወደ ወኅኒ ቤቱ በድብቅ አስገብተው በጣም የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ምግብ በብልሃት ለእያንዳንዳችን ያስተላልፉልን ነበር። በዚህ መንገድ የይሖዋን እንክብካቤና አመራር ለማግኘት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ!

በ1954 መገባደጃ ላይ በአስከፊነቱ ወደሚታወቀው በቶርጋው ወደሚገኝ ወኅኒ ቤት ተዛወርን። እዚያ የነበሩ ወንድሞች እኛን በማግኘታቸው በጣም ተደሰቱ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ መንፈሳዊ ጥንካሬያቸውን ጠብቀው መኖር የቻሉት ከቆዩ መጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የሚያስታውሱትን አንስተው በመወያየት ነበር። በቅርብ የወጡ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለማግኘት በጣም ጓጉተው ነበር! በዝዊካው ያጠናናቸውን አስፈላጊ ትምህርቶች የማካፈሉ ኃላፊነት በእኛ ላይ ወድቆ ነበር። ይሁን እንጂ ወደ ሥራ ስንሄድ እርስ በርስ እንዳናወራ በጥብቅ ተከልክለን እያለ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ወንድሞች ምን ማድረግ እንደምንችል ጠቃሚ ሐሳብ ያካፈሉን ሲሆን የይሖዋ ብርቱ እጅ ጥበቃ ያደርግልን ነበር። ይህ ሁኔታ በነጻነት ጊዜ እንዲሁም አጋጣሚው በተገኘበት ጊዜ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናትና ማሰላሰል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስተምሮናል።

ከባድ ውሳኔዎችን ያደረግንበት ወቅት

በይሖዋ እርዳታ ጸንተን ለመኖር ቻልን። በጣም የሚያስገርመው በ1956 መጨረሻ ላይ ብዙዎቻችን ምሕረት ተደረገልን። ከወኅኒ ቤቱ ስንወጣ የተሰማንን ደስታ በቃላት መግለጽ ያስቸግራል! በዚያን ጊዜ ልጄ ስድስት ዓመት ሞልቶት የነበረ ሲሆን ባለቤቴን ማግኘቴና ልጃችንን በማሳደጉ ሥራ መካፈል መቻሌ በጣም አስደስቶኝ ነበር። ለጊዜውም ቢሆን ዮሐንስ እንግዳ ስለሆንኩበት አይቀርበኝም ነበር፤ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ በመካከላችን የጠበቀ ግንኙነት ተፈጠረ።

በምሥራቅ ጀርመን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በወቅቱ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ነበሩ። በክርስቲያናዊ አገልግሎታችንና በገለልተኝነት አቋማችን ምክንያት እየጨመረ የመጣው ጥላቻ ምንጊዜም በፍርሃት እንድንኖር አስገድዶናል። ሕይወታችን በአደጋና በጭንቀት የተሞላ ከመሆኑ የተነሳ ተሰላችተን ነበር። በመሆኑም እኔና ኤሪካ ጉዳዩን በጸሎት ካሰብንበት በኋላ በስጋት ከምናልቅ ሁኔታው ሻል ወደሚልበት አካባቢ መዛወር እንደሚኖርብን ተሰማን። ይሖዋን ለማገልገልና መንፈሳዊ ግቦችን ለማውጣት የሚያስችል ነጻነት ለማግኘት ፈለግን።

በ1957 የጸደይ ወራት ወደ ስቱትጋርት፣ ምዕራብ ጀርመን የመሄድ አጋጣሚ አገኘን። እዚያ በነጻነት መስበክ የሚቻል ሲሆን ከወንድሞቻችን ጋር እንደልብ መሰብሰብ ቻልን። የተደረገልን ፍቅራዊ ድጋፍ ከጠበቅነው በላይ ነበር። በሄደልፊንጀን በሚገኝ ጉባኤ ሰባት ዓመት አሳለፍን። በእነዚህ ዓመታት ልጃችን ትምህርት የጀመረ ከመሆኑም በላይ በመንፈሳዊ ጥሩ እድገት አድርጓል። በመስከረም 1962 በቪስባደን በተደረገው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት የመካፈል መብት አግኝቻለሁ። እዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት የጀርመንኛ ተናጋሪ ክልል ከቤተሰቤ ጋር እንድዛወር ማበረታቻ ተሰጠኝ። ክልሉ አንዳንድ የጀርመን ግዛቶችንና ስዊዘርላንድን የሚጨምር ነበር።

ወደ ስዊስ ተራሮች አመራን

በዚህም ምክንያት በ1963 ወደ ስዊዘርላንድ ሄድን። እዚያም በስዊስ ተራሮች ማዕከላዊ ክፍል ውብ በሆነው የሉሴርኔ ሃይቅ አካባቢ በብሩነን ከተማ በሚገኝ አነስተኛ አስፋፊዎች ባሉበት ጉባኤ እንድናገለግል ተመደብን። እዚያ መሄዳችን ገነት የገባን ያህል ነበር። በአካባቢው የሚነገረውን የስዊስ ጀርመንኛ፣ የአኗኗር ዘይቤውንና የሕዝቡን አስተሳሰብ መልመድ አስፈልጎናል። ይሁንና ሰላም ወዳድ በሆኑ ሰዎች መካከል መሥራቱንና ለእነርሱ መስበኩን ወደነዋል። በብሩነን 14 ዓመት የቆየን ሲሆን ልጃችንም እዚያ አደገ።

በ1977 በ50 ዓመቴ ገደማ ቱን በሚገኘው የስዊስ ቤቴል እንድናገለግል ግብዣ ቀረበልን። እዚያ ማገልገሉን እንደ ልዩ መብት ስለምንቆጥረው ግብዣውን በከፍተኛ አድናቆት ተቀበልን። እኔና ባለቤቴ ቤቴል ውስጥ ለዘጠኝ ዓመታት ያገለገልን ሲሆን እነዚያ ዓመታት በክርስቲያናዊ ሕይወታችን እንዲሁም በመንፈሳዊ እድገታችን ውስጥ ልዩ ትርጉም አላቸው። በተጨማሪም በቱን ከተማና በአካባቢዋ ከሚኖሩ አስፋፊዎች ጋር የማገልገል አጋጣሚ አግኝተናል። በእርግጥም የይሖዋ ‘ድንቅ ሥራ’ የሆኑትን አናታቸው በበረዶ የተሸፈኑ ግዙፍ የበርኒዝ ተራሮች እያዩ ማገልገል እጅግ የሚያስደስት ነው።—መዝሙር 9:1

እንደገና ተቀየርን

በ1986 መጀመሪያ አካባቢ ደግሞ ወደ ሌላ አካባቢ ተቀየርን። በስዊዘርላንድ ምሥራቃዊ ክፍል ቡኽስ በተባለ ጉባኤ ሥር በሚገኝ ሰፊ የአገልግሎት ክልል ውስጥ በልዩ አቅኚነት እንድናገለግል ተመደብን። በዚህም ጊዜ ሌላ የአኗኗር ዘይቤ መልመድ ጠይቆብናል። ይሁን እንጂ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ቦታ ሁሉ ይሖዋን ለማገልገል ካለን ፍላጎት የተነሳ ይህን አዲስ ምድብ የተቀበልን ሲሆን የእርሱን በረከት አግኝተንበታል። አልፎ አልፎ፣ ጉባኤዎችን በመጎብኘትና በማበረታታት ተተኪ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜም ሠርቻለሁ። በዚህ አካባቢ ለ18 ዓመት የኖርን ሲሆን በአካባቢው በመስበክ በርካታ አስደሳች ተሞክሮዎች አግኝተናል። ቡኽስ የሚገኘው ጉባኤ እድገት ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከአምስት ዓመት በፊት ለይሖዋ አገልግሎት በተወሰነ የሚያምር መንግሥት አዳራሽ ውስጥ እንሰበሰባለን።

ይሖዋ ይህ ነው የማይባል እንክብካቤ አድርጎልናል። አብዛኛውን ዕድሜያችንን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አሳልፈናል፤ ሆኖም አንዳች ነገር ጎድሎብን አያውቅም። ልጃችን፣ ሚስቱና ልጆቻቸው እንዲሁም የልጆቻቸው ቤተሰቦች በይሖዋ መንገድ በታማኝነት ሲሄዱ ማየታችን እርካታና ደስታ አስገኝቶልናል።

ያለፉትን ዓመታት መለስ ብዬ ስመለከት በእርግጥም ይሖዋን ‘አመቺ በሆነውም ሆነ ባልሆነው ጊዜ’ እንዳገለገልን ይሰማኛል። ክርስቲያናዊ አገልግሎቴን ለማከናወን ባደረግሁት ጥረት በኮሚኒስቶች ጨለማ እስር ቤት ታስሬያለሁ። ዕጹብ ድንቅ ወደሆኑት የስዊስ ተራሮች የሄድኩትም ለዚሁ ነው። እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ ባሳለፍነው ሕይወት ለአፍታ እንኳ ተጸጽተን አናውቅም።

በተደጋጋሚ የደረሰባቸውን ስደት በጽናት ተቋቁመዋል

ምሥራቅ ጀርመን ተብላ በምትታወቀው በቀድሞዋ ጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ እገዳ ተጥሎባቸው ነበር። መዛግብት እንደሚያሳዩት ከ5,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቲያናዊ አገልግሎታቸውና በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው ካምፖች እንዲሁም ወደ ማቆያ ማዕከሎች እንዲገቡ ተገድደዋል።—ኢሳይያስ 2:4

ከእነዚህ ምሥክሮች መካከል አንዳንዶቹ ‘የሁለት መንግሥታት የጥቃት ሰለባዎች’ ተብለው ተገልጸዋል። ከእነዚህ መካከል 325 የሚያህሉት በናዚ የማጎሪያ ካምፖችና እስር ቤቶች ታስረዋል። ከዚያም በ1950ዎቹ ዓመታት ሽታዚ በተሰኘው የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ታድነው በመያዝ እንዲታሰሩ ተደርጓል። እንዲያውም አንዳንድ እስር ቤቶች በሁለቱም ሥርዓቶች ግልጋሎት ላይ ውለዋል፤ በመጀመሪያ ለናዚ ከዚያም ለኮሚኒስቶች።

የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ ስደት በደረሰባቸው በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት ማለትም ከ1950 እስከ 1961 በአጠቃላይ 60 ወንዶችና ሴቶች በደረሰባቸው እንግልት፣ በረሃብ፣ በበሽታና በእርጅና እዚያው እስር ቤት ሳሉ ለህልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል። አሥራ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ዕድሜ ይፍታህ ተፈርዶባቸው የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ቅጣቱ ወደ 15 ዓመት ተቀንሶላቸዋል።

በአሁኑ ጊዜ፣ በርሊን በሚገኘው የቀድሞው የምሥራቅ ጀርመን የደኅንነት ዋና መሥሪያ ቤት በዚያች አገር በሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የደረሰውን የ40 ዓመት ስደት የሚያሳይ ቋሚ ኤግዚቢሽን አለ። በዚያ የሚታዩት ፎቶግራፎችና የግለሰቦች ታሪክ እነዚህ ምሥክሮች እንደ እሳት በሚፋጅ የመከራ ወቅት ላሳዩት ድፍረትና መንፈሳዊ ጥንካሬ ሕያው ምሥክር ናቸው።

[በገጽ 24,25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ምሥራቅ ጀርመን

ሩደልሽታት

በልጽክ

ቶርጋው

ኬምኒትስ

ዝዊካው

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዝዊካው የሚገኘው የኡስተሽቲን ሕንፃ

[ምንጭ]

Fotosammlung des Stadtarchiv Zwickau, Deutschland

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከኤሪካ ጋር