በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትኛውን ሃይማኖት መምረጥ ይኖርብሃል?

የትኛውን ሃይማኖት መምረጥ ይኖርብሃል?

የትኛውን ሃይማኖት መምረጥ ይኖርብሃል?

‘የተለያዩ ሃይማኖቶች ወደ አንድ ቦታ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸው። ደግሞስ አምላክ አንድ ብቻ አይደል?’ የአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን አባል መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ቢያምኑም አንድ ሰው የየትኛውም ሃይማኖት አባል ቢሆን ለውጥ እንደማያመጣ የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች በዚህ አባባል ይስማማሉ።

በእርግጥም ሁሉን ቻይ የሆነው እውነተኛ አምላክ አንድ ብቻ በመሆኑ ላይ ላዩን ሲታይ ይህ አመለካከት ምክንያታዊ ሊመስል ይችላል። (ኢሳይያስ 44:6፤ ዮሐንስ 17:3፤ 1 ቆሮንቶስ 8:5, 6) ይሁን እንጂ እውነተኛውን አምላክ እናገለግላለን በሚሉት በርካታ ሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል ያሉት ልዩነቶችና እርስ በርስ የሚጋጩ ትምህርቶች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። በሃይማኖታዊ ሥርዓቶቻቸው፣ በእምነቶቻቸው፣ በትምህርቶቻቸውና ከተከታዮቻቸው በሚጠብቁት ብቃት ረገድ የጎላ ልዩነት አላቸው። እነዚህ ልዩነቶች በጣም ሰፊ በመሆናቸው የአንድ ሃይማኖት ወይም ቡድን አባላት የሌሎችን ትምህርት አሊያም እምነት መረዳት ወይም መቀበል በጣም ይከብዳቸዋል።

በሌላ በኩል ኢየሱስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል” ብሏል። (ዮሐንስ 4:24) ስለ አምላክ ማንነት፣ ስለ ዓላማዎቹ እንዲሁም እንዲቀርብለት ስለሚፈልገው አምልኮ እርስ በርስ የሚጋጩ የተለያዩ አመለካከቶች ይዞ አምላክን በእውነት ማምለክ ይቻላል? ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በየትኛውም መንገድ ብናመልከው ይቀበለናል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው?

እውነተኛ ክርስቲያኖች—ጥንትና ዛሬ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ስለ አንዳንድ ጉዳዮች የተለያየ አመለካከት የያዙበት ወቅት ነበር። ለአብነት ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏል:- “ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ከቀሎዔ ቤተ ሰብ ሰምቻለሁ፤ ነገሩም እንዲህ ነው፤ ከእናንተ አንዱ፣ ‘እኔ የጳውሎስ ነኝ’ ሲል፣ ሌላው፣ ‘እኔ የአጵሎስ ነኝ’ ይላል፤ ደግሞም አንዱ፣ ‘እኔ የኬፋ ነኝ’ ሲል፣ ሌላው ደግሞ፣ ‘እኔስ የክርስቶስ ነኝ’ ይላል።”—1 ቆሮንቶስ 1:11, 12

ጳውሎስ እነዚህን ልዩነቶች አቅልሎ ተመለከታቸው? እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን መንገድ ተከትሎ መዳን ለማግኘት እየጣረ ነበር? በፍጹም! ጳውሎስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል:- “ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ መለያየት እንዳይኖር፣ አንድ ልብ፣ አንድ ሐሳብ እንዲኖራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም እንድትስማሙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።”—1 ቆሮንቶስ 1:10

በእርግጥ ሰውን በማስገደድ የአምልኮ አንድነት ማስገኘት አይቻልም። አንድነት ሊኖር የሚችለው ሰዎች በልዩነቶቻቸው ላይ ጥንቃቄ የታከለበት ምርምር አድርገው ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ መድረስ ሲችሉና በዚህም ሲስማሙ ብቻ ነው። ስለዚህ ጳውሎስ የገለጸው ዓይነት አንድነት እንዲኖር የአምላክን ቃል በግላችን ማጥናት እንዲሁም ቃሉን በተግባር የማዋል ልባዊ ፍላጎት መኮትኮት ይኖርብናል። ታዲያ በአሁኑ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት አንድነት ሊኖር ይችላል? ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ከጥንት ጊዜ አንስቶ አምላክ ሕዝቦቹ በቡድን መልክ እንዲደራጁ ያደርግ ነበር። በዛሬው ጊዜ ይህንን ቡድን ለይቶ ማወቅ ይቻላል?

የትክክለኛው ሃይማኖት አባል መሆን የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

መዝሙራዊው ዳዊት በአንድ ወቅት “እግዚአብሔር ሆይ፤ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰው ኰረብታህስ ማን መኖር ይችላል?” የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር። ይህ የእኛንም ትኩረት የሚስብ ጥያቄ እንደሆነ ግልጽ ነው። ዳዊት “አካሄዱ ንጹሕ የሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ፤ ከልቡ እውነትን የሚናገር” በማለት መልሱን ሰጥቷል። (መዝሙር 15:1, 2) መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል መረዳት አምላክ ያወጣቸውን እነዚህን ብቃቶች የሚያሟላውን ሃይማኖት ለይቶ ለማወቅ ያስችላል። ከዚያም የዚህ ቡድን አባል በመሆን አምላክን በአንድነት እንዲሁም “በመንፈስና በእውነት” ከሚያመልኩት ሰዎች ጋር የሚያንጽ ወዳጅነት መመሥረት ይቻላል።

የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ እንኳ አንድነት ሊኖር እንደሚችል አሳይተዋል፤ የአምልኮ አንድነት አላቸው እንዲሁም በቡድን መልክ ተባብረው ይሠራሉ። አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች ቀደም ሲል የተለያዩ ሃይማኖቶችና ጎሳዎች አባላት ነበሩ። ሌሎቹ ደግሞ አምላክ የለም ወይም ስለ እርሱ ማወቅ አይቻልም ብለው ያምኑ የነበሩ ሰዎች ናቸው። ለሃይማኖት እምብዛም ግድ ያልነበራቸው ሰዎችም አሁን የይሖዋ ምሥክር ሆነዋል። ከእነዚህ ሁሉ የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ባህሎችና ፍልስፍናዎች የተሰባሰቡ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ፈጽሞ የማይታይ የአምልኮ አንድነት ማግኘት ችለዋል።

እንደዚህ ላለው የአምልኮ አንድነት መሠረቱ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎችን በማስገደድ አንድ ዓይነት እርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ እንደማይቻል ያውቃሉ። ሆኖም ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የማበረታታት መብት በማግኘታቸው ይደሰታሉ፤ በዚህ መንገድ ሌሎች ከአምልኮ ጋር በተያያዘ ለሚያደርጓቸው ምርጫዎች መሠረት የሚሆን አስተማማኝ መመሪያ እንዲያገኙ ይረዷቸዋል። ይህም ብዙ ሰዎች አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ ከሚያስገኛቸው በረከቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል።

በዛሬው ጊዜ ጎጂ በሆኑ ተጽዕኖዎችና ማባበያዎች የመሸነፍ ሰፊ አደጋ ስላለ ትክክለኛውን ሃይማኖት መምረጡ በጣም አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል” እንዲሁም “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” ይላል። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) ከእውነተኛዎቹ የአምላክ አገልጋዮች ጋር መተባበር ጥበቃ ያስገኛል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቶናል:- “እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።” (ዕብራውያን 10:24, 25) በመንፈሳዊ ወንድምና እህት የሆኑ እውነተኛ ወዳጆች በአምላክ ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እርስ በርስ በፍቅር መረዳዳታቸው በእርግጥም ታላቅ በረከት ነው!

የኦትማር ታሪክ ይህ እውነት መሆኑን ያረጋግጥልናል። በጀርመን በካቶሊክ ቤተሰብ ውስጥ ቢያድግም በኋላ ላይ ግን ቤተ ክርስቲያን መሄድ አቆመ። “ቤተ ክርስቲያን መሄዴ የነበረብኝን የባዶነት ስሜት ሊያስወግድልኝ አልቻለም” ብሏል። ያም ሆኖ በአምላክ ያምን ነበር። በዚህ መሃል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘ እንዲሁም እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች እንደሆኑ አመነ። የይሖዋ ምሥክር መሆን አስፈላጊ እንደሆነም ተገነዘበ። አሁን እንዲህ ይላል:- “ዓለም አቀፋዊ የሆነ ድርጅት አባል መሆኔ የአእምሮ ሰላምና መረጋጋት አስገኝቶልኛል። [የይሖዋ ምሥክሮች] በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠውን ነገር ይኸውም ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዳገኝ ደረጃ በደረጃ እየረዱኝ ነው።”

ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የቀረበ ግብዣ

ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ሰዎች አንድ ሥራ ለማከናወን በየፊናቸው ጥረት ከሚያደርጉ ይልቅ በቡድን መልክ ተባብረው ቢንቀሳቀሱ የተሻለ ውጤት ማግኘት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከተከታዮቹ ሊለይ ሲል የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር:- “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።” (ማቴዎስ 28:19, 20) አንድ ዓይነት አመራር ወይም ድርጅት ሳይኖር እንደዚህ ያለውን ሥራ አጥጋቢ በሆነ መልኩ ማከናወን እንዴት ይቻላል? አንድ ሰው አምላክን ብቻውን ለማገልገል የሚሞክር ከሆነ ይህንን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ እንዴት መፈጸም ይችላል?

ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች 91,933,280 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው የተዘጋጁ መጽሐፎች፣ ቡክሌቶችና ብሮሹሮች እንዲሁም 697,603,247 መጽሔቶች ያሰራጩ ሲሆን በ235 አገሮችና ደሴቶች ለሚኖሩ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን ቃል ሰብከዋል። አንድነት ያላቸው ሰዎች በሚገባ ተደራጅተው በቡድን መልክ የሚያከናውኑት ሥራ በግለሰብ ደረጃ ከሚደረግ ጥረት በጣም የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ከዚህ መመልከት ይቻላል!

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከማሰራጨትም በተጨማሪ ሰዎች አምላክ ስለሚፈልግባቸው ነገር ጥልቅ እውቀት እንዲኖራቸው ለመርዳት ሲሉ መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ ያስተምራሉ። ባለፈው ዓመት በየሳምንቱ በአማካይ 5,726,509 የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በግለሰብ ደረጃ አሊያም በቡድን መልክ መርተዋል። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምልኮን በተመለከተ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችላቸው አስተማማኝ መሠረት እንዲያገኙ ረድቷቸዋል። አንተም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈሩትን መለኮታዊ ብቃቶች እንድትማር እንጋብዝሃለን። ይህንን መሠረት በማድረግ የራስህን ምርጫ ማድረግ ትችላለህ።—ኤፌሶን 4:13፤ ፊልጵስዩስ 1:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:20፤ 2 ጴጥሮስ 3:18

አምላክን ለማስደሰት ከፈለግህ የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን የግድ ያስፈልግሃል፤ ይህ ሲባል ግን የማንኛውም ሃይማኖታዊ ቡድን ወይም ድርጅት አባል መሆን ማለት አይደለም። ሃይማኖትን በተመለከተ የምታደርገው ምርጫ እውነተኝነታቸው ባልተረጋገጠ ትምህርቶች ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሲነገር በሰማኸው ነገር ላይ ሳይሆን በትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። (ምሳሌ 16:25) እውነተኛው ሃይማኖት ሊያሟላቸው ስለሚገባው ብቃቶች ተማር። ከዚያም የተማርከውን አንተ ከምታምነው ነገር ጋር በማወዳደር በዚያ መሠረት ምርጫ አድርግ።—ዘዳግም 30:19

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች የሚኖሩት በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ቢሆንም አንድነት አላቸው