በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በ1 ሳሙኤል 19:12, 13 ላይ ያለው ዘገባ እንደሚያመለክተው ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ የነበረው ዳዊት ሚስቱ ሜልኮል ተራፊም ወይም ጣዖት እንዲኖራት የፈቀደው ለምንድን ነው?

በቅድሚያ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ታሪክ በአጭሩ እንመልከት። የዳዊት ሚስት ሜልኮል፣ ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን ለመግደል እንዳሰበ ስትሰማ ፈጣን እርምጃ ወሰደች። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አሾልካ አወረደችው፣ እርሱም ሸሽቶ አመለጠ። ከዚያም ሜልኮል የጣዖት ምስል [“ተራፊምን፣” የ1954 ትርጉም] [የሰው ቅርጽና መጠን ያለው መሆኑን ከሁኔታው መረዳት ይቻላል] ወስዳ በዐልጋው ላይ አጋደመችው፤ በራስጌውም የፍየል ጠጉር አኖረች፤ በልብስም ሸፈነችው።” የሳኦል መልእክተኞች ዳዊትን ለመያዝ ሲመጡ ሜልኮል “ታሞአል” አለቻቸው። ይህ ዘዴዋ ለዳዊት ማምለጥ የሚችልበት በቂ ጊዜ ሰጥቶታል።—1 ሳሙኤል 19:11-16

አርኪዮሎጂያዊ ግኝቶች በጥንት ጊዜያት ተራፊም ለሃይማኖታዊ ዓላማ ብቻ ሳይሆን ከሕግ ጋር በተያያዘም ይሠራበት እንደነበር ይጠቁማሉ። በዛሬው ጊዜ የባለቤትነት ሰነድና በጽሑፍ የሰፈረ ኑዛዜ የውርስ መብትን ለማረጋገጥ እንደሚያገለግሉ ሁሉ በጥንት ጊዜም ተራፊም ለዚህ ዓላማ ይውል ነበር። በአንዳንድ ሁኔታዎች አንድ አማች ተራፊም መያዙ የሚስቱ አባት ሲሞት ንብረቱን ለመውረስ ያስችለው ነበር። ይህ ከዚያ ቀደም ብሎ በተከሰተ ታሪክ ላይ ራሔል የአባቷን ተራፊሞች የወሰደችበትንና እርሱም ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት ያደረገበትን ምክንያት ለመገንዘብ ያስችለናል። በወቅቱ የራሔል ባል የነበረው ያዕቆብ ሚስቱ ያደረገችውን አላወቀም ነበር።—ዘፍጥረት 31:14-34

እስራኤላውያን በብሔር መልክ ሲደራጁ አሥርቱ ትእዛዛት የተሰጧቸው ሲሆን ሁለተኛው ትእዛዝ ጣዖት መሥራትን ለይቶ የሚከለክል ነበር። (ዘፀአት 20:4, 5) ከጊዜ በኋላ ነቢዩ ሳሙኤል ይህንን ሕግ በተዘዋዋሪ በመጥቀስ ለንጉሥ ሳኦል “ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፣ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው” ብሎት ነበር። (1 ሳሙኤል 15:23 የ1954 ትርጉም) ከዚህ አኳያ ተራፊም በእስራኤል ውስጥ ከውርስ ጋር በተያያዘ ይሠራበት ነበር ለማለት አይቻልም። ቢሆንም ጥንታዊ የሆነው ተራፊምን የማምለክ አጉል ልማድ በአንዳንድ እስራኤላውያን ቤተሰቦች ዘንድ የቀጠለ ይመስላል። (መሳፍንት 17:5, 6፤ 2 ነገሥት 23:24) ሜልኮል የተራፊም ምስል ያላት መሆኑ ልብዋ ሙሉ በሙሉ ከይሖዋ ጋር እንዳልነበር ይጠቁማል። ዳዊት ግን ስለ ተራፊሙ የሚያውቀው ነገር ላይኖር ይችላል፤ ወይም ሜልኮል የንጉሥ ሳኦል ልጅ ስለነበረች አልከለከላትም ይሆናል።

ዳዊት በፍጹም ልቡ ይሖዋን ያመልክ እንደነበር ከሚከተለው አነጋገሩ መረዳት ይቻላል:- “እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ምስጋናውም ብዙ ነው፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ የሚገባው ነው። የአሕዛብ ሁሉ አማልክት ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።”—1 ዜና መዋዕል 16:25, 26

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ ሁለተኛው በሥዕሉ ላይ እንደሚታዩት ያሉትን የተራፊም ጣዖታት መሥራትን ይከለክላል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1859 ከታተመው ዘ ሆሊ ላንድ የተባለ መጽሐፍ ጥራዝ ሁለት የተወሰደ