በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን ይኖርብሃል?

የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን ይኖርብሃል?

የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን ይኖርብሃል?

‘በአምላክ ለማመን የግድ የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል መሆን ወይም አዘውትሬ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አያስፈልገኝም!’ ብዙ ሰዎች የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል መሆንን በተመለከተ እንደዚህ ይሰማቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ከአምላክ ጋር ይበልጥ እንደተቀራረቡ የሚሰማቸው በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ ሲገኙ ሳይሆን ወጣ ብለው ተፈጥሮን ሲመለከቱ እንደሆነ ይናገራሉ። በአምላክ ለማመን የአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን ወይም ድርጅት አባል መሆን አያስፈልግም የሚለው አመለካከት ዛሬ በብዙዎች ዘንድ ተስፋፍቶ ይገኛል።

ሌሎች ደግሞ ከዚህ የተለየ አመለካከት አላቸው። የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል መሆንና ቤተ ክርስቲያን መሄድ በጣም አስፈላጊ ነው በማለት ይሟገታሉ። እንግዲያው የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም የሚለው ጥያቄ ስለ ሃይማኖት ጥናት የሚያካሂዱ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን ግለሰብ የሚያሳስብ ነው። ያም ሆነ ይህ ጉዳዩ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና የሚነካ በመሆኑ እርሱ ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት ለማወቅ መሞከሩ ተገቢ አይሆንም? ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚሰጠው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን?

አምላክ በጥንት ጊዜ ከሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት

ከ4,400 ዓመታት ገደማ በፊት መላዋ ምድር በከባድ ጎርፍ ተጥለቅልቃ ነበር። እንዲህ ያለው ክስተት ከሰዎች አእምሮ በቀላሉ የሚጠፋ ባለመሆኑ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሕዝቦች ስለ ጥፋት ውኃው የሚገልጽ አፈ ታሪክ አላቸው። እነዚህ ታሪኮች በአንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የሚለያዩ ቢሆንም ከጥፋቱ የተረፉት ጥቂት ሰዎችና እንስሳት መሆናቸውን የሚገልጸውን ዘገባ ጨምሮ በአብዛኛው ይመሳሰላሉ።

እነዚህ ሰዎች ከጥፋቱ መትረፍ የቻሉት እንዲያው በአጋጣሚ ነበር? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሁኔታው ከዚህ የተለየ እንደሆነ ይገልጻል። አምላክ ጥፋት እንደሚመጣ የተናገረው ለእያንዳንዱ ሰው እንዳልሆነ ልብ ልንል ይገባል። ከዚህ ይልቅ የጥፋት ውኃ እንደሚመጣ ለኖኅ የነገረው ሲሆን እርሱ ደግሞ በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች አስጠንቅቋቸዋል።—ዘፍጥረት 6:13-16፤ 2 ጴጥሮስ 2:5

በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ከጥፋት መትረፋቸው የተመካው አንድነት ካለው ከዚህ ቡድን ጋር በመተባበራቸውና አምላክ ለኖኅ የሰጠውን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆናቸው ላይ ነው። መርከቡ ውስጥ ገብተው ከጥፋቱ የተረፉት እንስሳት እንኳ ከዚህ ቡድን ተነጥለው መትረፍ አይችሉም ነበር። ምክንያቱም እንስሳቱ ከምድር ገጽ እንዳይጠፉ ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርግ ዝርዝር መመሪያዎች የተሰጡት ለኖኅ ነበር።—ዘፍጥረት 6:17 እስከ 7:8

ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ፣ የኖኅ ልጅ የሆነው የሴም ዘሮች በግብጽ በባርነት ቀንበር ሥር ወደቁ። የአምላክ ዓላማ ይህንን ሕዝብ ነፃ ማውጣትና ለቅድመ አያታቸው ለአብርሃም ተስፋ ወደ ሰጠው ምድር ማስገባት ነበር። በዚህም ጊዜ ቢሆን ይህንን ዓላማውን የገለጸው ለእያንዳንዱ ግለሰብ ሳይሆን መሪ እንዲሆኑ ለመረጣቸው ለሙሴና ለወንድሙ ለአሮን ነው። (ዘፀአት 3:7-10፤ 4:27-31) በባርነት ቀንበር ተይዘው የነበሩት እነዚህ ሰዎች በአንድነት ሆነው ከግብጽ ነፃ ከወጡ በኋላ በሲና ተራራ ግርጌ ሰፈሩ፤ በዚያም የአምላክ ሕግ የተሰጣቸው ሲሆን በብሔር መልክም ተደራጁ።—ዘፀአት 19:1-6

እያንዳንዱ እስራኤላዊ አምላክ ካቋቋመው ቡድን ጋር ባይተባበርና በቡድኑ ላይ የተሾሙት መሪዎች የሚሰጡትን መመሪያ ባይከተል ኖሮ ከግብጽ ነፃ ሊወጣ አይችልም ነበር። አንዳንድ ግብጻውያንም የአምላክን ሞገስ ካገኘው ከዚህ ቡድን ጋር እንዲቀላቀሉ ተፈቅዶላቸዋል። እነዚህ ሰዎች እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ አብረዋቸው በመውጣታቸው የአምላክን በረከት ማግኘት ችለዋል።—ዘፀአት 12:37, 38

ከዚያም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ የስብከት እንቅስቃሴውን ሲጀምር ደቀ መዛሙርት የሚሆኑት ሰዎች ሰበሰበ። በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዳቸው የሚያስፈልጋቸውን ፍቅራዊ አሳቢነት ቢያሳያቸውም በቡድን መልክ ያስተምራቸውና አብሯቸው ይሠራ ነበር። ለአሥራ አንዱ ታማኝ ሐዋርያት “እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 22:28, 29) ቆየት ብሎም የአምላክ መንፈስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የወረደው አንድ ላይ ተሰባስበው እያሉ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 2:1-4

እነዚህ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ባለፉት ዘመናት ሁሉ አምላክ ሕዝቦቹ በቡድን መልክ እንዲደራጁ ያደርግ ነበር። እንደ ኖኅ፣ ሙሴና ኢየሱስ የመሳሰሉትን ጥቂት ሰዎችም ቢሆን በግለሰብ ደረጃ መመሪያ የሰጣቸው በቡድን መልክ ለተደራጁት አገልጋዮቹ መልእክት ለማስተላለፍ ነው። ዛሬም ቢሆን አምላክ ከአገልጋዮቹ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ከዚህ የተለየ ይሆናል ብለን እንድናስብ የሚያደርገን ምክንያት የለም። ይህ ሲባል ግን የማንኛውም ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል መሆኑ ብቻ በቂ ነው? የሚል ጥያቄ ይነሳል። በሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ወሳኝ ጥያቄ ላይ እንወያያለን።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጥንት ጀምሮ አምላክ አገልጋዮቹ በቡድን መልክ እንዲደራጁ ያደርግ ነበር