በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያለህበት ሁኔታ ሕይወትህን እንዲቆጣጠር አትፍቀድ

ያለህበት ሁኔታ ሕይወትህን እንዲቆጣጠር አትፍቀድ

ያለህበት ሁኔታ ሕይወትህን እንዲቆጣጠር አትፍቀድ

በዚህ ‘አስጨናቂ ዘመን’ አስከፊ ሁኔታዎችና ችግሮች የዕለት ተዕለት የሕይወት ገጠመኞቻችን ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) አንዳንድ ችግሮች ጊዜያዊና ቀስ በቀስ የሚወገዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎቹ ግን ለወራት ብሎም ለዓመታት ሊዘልቁ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ብዙዎች “የልቤ መከራ በዝቶአል፤ ከጭንቀቴ ገላግለኝ” በማለት ወደ ይሖዋ እንደጮኸው እንደ መዝሙራዊው ዳዊት ይሰማቸዋል።—መዝሙር 25:17

አንተስ ከአቅም በላይ ከሆኑ ችግሮች ጋር እየታገልህ ነው? ከሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታና ማበረታቻ ማግኘት ትችላለህ። የደረሱባቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በመቋቋም ረገድ የተሳካላቸው ሁለት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ያሳለፉትን ሕይወት እስቲ እንመልከት። እነዚህ ሰዎች ዮሴፍና ዳዊት ናቸው። መከራ ሲደርስባቸው ምን እንዳደረጉ በመመርመር እኛም ተመሳሳይ ችግሮች ሲያጋጥሙን እንዴት መቋቋም እንደምንችል የሚያሳዩ ጠቃሚ ትምህርቶችን ልናገኝ እንችላለን።

አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል

ዮሴፍ 17 ዓመት ሲሆነው ከገዛ ቤተሰቡ ከባድ ችግር አጋጥሞት ነበር። ታላላቅ ወንድሞቹ አባታቸው ያዕቆብ “ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው መሆኑን” አስተዋሉ። በዚህም የተነሳ “ዮሴፍን ጠሉት፤ በቅን አንደበትም ሊያናግሩት አልቻሉም።” (ዘፍጥረት 37:4) ይህ ሁኔታ በዮሴፍ ላይ ምን ያህል ጭንቀትና ውጥረት ፈጥሮበት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ውሎ አድሮ የዮሴፍ ወንድሞች ጥላቻቸው እየተባባሰ ከመምጣቱ የተነሳ ለባርነት ሸጡት።—ዘፍጥረት 37:26-33

ዮሴፍ በግብፅ በባርነት ሳለ የጌታው ሚስት ከእርሷ ጋር እንዲባልግ የምታሳድርበትን ተጽእኖ ለመቋቋም ተገድዷል። ዮሴፍ ፈቃደኛ አለመሆኑ ስላበሳጫት አስገድዶ ሊደፍራት እንደሞከረ በማስመሰል በሐሰት የከሰሰችው ሲሆን ጌታውም “እስር ቤት አስገባው።” በዚህም ምክንያት “እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤ በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ።” (ዘፍጥረት 39:7-20፤ መዝሙር 105:17, 18) እንዴት ያለ አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር! ዮሴፍ የቤተሰቡን አባላት ጨምሮ ሌሎች ባደረሱበት በደል ምክንያት ለ13 ዓመታት ያህል በባርነትና በእስር ኖሯል።—ዘፍጥረት 37:2፤ 41:46

በጥንቷ እስራኤል ይኖር የነበረው ዳዊትም ገና በወጣትነቱ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር። ንጉሥ ሳኦል እንደ እንስሳ ያድነው ስለነበር ለበርካታ ዓመታት በስደት ለመኖር ተገዷል። የዳዊት ሕይወት በአደጋ ላይ ወድቆ ነበር። በአንድ ወቅት ምግብ ፍለጋ ወደ ካህኑ ወደ አቢሜሌክ ሄደ። (1 ሳሙኤል 21:1-7) አቢሜሌክ ዳዊትን እንደረዳው ሲሰማ ሳኦል አቢሜሌክን ጨምሮ ሁሉም ካህናት ከነቤተሰቦቻቸው እንዲገደሉ አዘዘ። (1 ሳሙኤል 22:12-19) ዳዊት በእርሱ ምክንያት እንዲህ ያለ አሳዛኝ ሁኔታ በመከሰቱ ምን ያህል ሊያዝን እንደሚችል መገመት አያዳግትህም።

ዮሴፍና ዳዊት ለበርካታ ዓመታት ያሳለፉትን መከራና የደረሰባቸውን በደል አስብ። እነርሱ ያጋጠሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዴት እንደተወጡ በመመርመር እኛም ጠቃሚ ትምህርቶች ልናገኝ እንችላለን። እነዚህ ሰዎች ግሩም ምሳሌ የሚሆኑባቸውን ሦስት መንገዶች እንመልከት።

ቂም ከመያዝና ጥላቻን ከማሳደር ተቆጠብ

በመጀመሪያ ደረጃ፣ እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ቂም ከመያዝና ጥላቻ ከማሳደር ተቆጥበዋል። ዮሴፍ በወኅኒ ቤት ሳለ ወንድሞቹ ለባርነት በመሸጥ ስለፈጸሙበት በደል በማብሰልሰል አንድ ቀን ቢያገኛቸው እንዴት አድርጎ እንደሚበቀላቸው ሊያስብ ይችል ነበር። ዮሴፍ እንዲህ ያለ መጥፎ ሐሳብ እንዳላደረበት እንዴት እናውቃለን? እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ የመጡትን ወንድሞቹን ለመበቀል አጋጣሚውን ባገኘ ጊዜ ምን እንደተሰማው ተመልከት። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “[ዮሴፍ] ከፊታቸውም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ከዚያም . . . በስልቻዎቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው፤ ብሩንም በያንዳንዱ ሰው ስልቻ ውስጥ መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጉዞአቸው ስንቅ እንዲያሲዟቸው ዮሴፍ [ለአገልጋዮቹ] ትእዛዝ ሰጠ።” ከጊዜ በኋላ አባታቸውን ወደ ግብፅ እንዲያመጡ ወንድሞቹን በላካቸው ጊዜ “መንገድ ላይ እንዳትጣሉ” በማለት አሳሰባቸው። ዮሴፍ ጥላቻና የበቀል ስሜት ሕይወቱን እንዲመርዝበት እንዳልፈቀደ በቃልም ሆነ በድርጊት አሳይቷል።—ዘፍጥረት 42:24, 25፤ 45:24

በተመሳሳይ ዳዊት በንጉሥ ሳኦል ላይ ቂም አልያዘም። ሳኦልን ለመግደል የሚያስችሉ ሁለት አጋጣሚዎች አግኝቶ ነበር። በእነዚህ ጊዜያት ወታደሮቹ እንዲገድለው ቢያበረታቱትም ዳዊት ግን እንዲህ አለ:- “እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ከማድረግና እግዚአብሔር የቀባው ስለ ሆነም እጄን በእርሱ ላይ ከማንሣት እግዚአብሔር ይጠብቀኝ።” ዳዊት “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ራሱ ይቀስፈዋል፤ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፤ ወይም በጦርነት ይሞታል” ብሎ ለወታደሮቹ በመንገር ጉዳዩን ለይሖዋ ትቶታል። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ሳኦልና የሳኦል ልጅ ዮናታን ሲሞቱ የሐዘን እንጉርጉሮ ተቀኝቶላቸዋል። እንደ ዮሴፍ ሁሉ ዳዊትም የበቀል ስሜት እንዲያሸንፈው አልፈቀደም።—1 ሳሙኤል 24:3-6፤ 26:7-13፤ 2 ሳሙኤል 1:17-27

እኛስ በተፈጸመብን በደል የተነሳ ችግር ላይ ስንወድቅ ቂም እንይዛለን? ጥላቻስ ያድርብናል? እንዲህ ዓይነት ስሜት በቀላሉ ሊያድርብን ይችላል። ስሜታችንን መቆጣጠር ካልቻልን ከተፈጸመብን በደል ይልቅ በውስጣችን የተፈጠረው ጥላቻና የበቀል ስሜት ይበልጥ ሊጎዳን ይችላል። (ኤፌሶን 4:26, 27) ሌሎች እንዳይበድሉን ማድረግ ባንችልም እንኳ ስሜታችንን መቆጣጠር እንችላለን። ይሖዋ ችግሩን እርሱ በፈቀደው ጊዜ እንደሚፈታው ካመንን ቂም ከመያዝም ሆነ ጥላቻን ከማሳደር መቆጠብ ቀላል ይሆንልናል።—ሮሜ 12:17-19

አጋጣሚውን ለበጎ ተጠቀምበት

ከዮሴፍና ከዳዊት ተሞክሮ ልናገኘው የምንችለው ሁለተኛው ትምህርት ደግሞ ያጋጠመን ችግር የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንን ከማከናወን እንዲያግደን አለመፍቀድ ነው። አእምሯችን ምንም ለውጥ በማናመጣበት ጉዳይ ከመያዙ የተነሳ ማድረግ የምንችለው ነገር እንኳ ላይታየን ይችላል። እንደዚያ ከሆነ ያለንበት ሁኔታ ሕይወታችንን ተቆጣጥሯል ማለት ነው። ዮሴፍ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችል ነበር። እርሱ ግን ያጋጠመውን ሁኔታ ለበጎ ተጠቅሞበታል። ዮሴፍ በባርነት ባገለገለባቸው ዓመታት “[በጌታው] ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው።” ዮሴፍ እስር ቤት በነበረበትም ጊዜ ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል። ይሖዋ ስለባረከውና እርሱም ትጉ ስለነበረ “የወኅኒው አዛዥ ዮሴፍን የእስረኞች ሁሉ አለቃ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ላለውም ነገር ሁሉ ኀላፊ ሆነ።”—ዘፍጥረት 39:4, 21-23

ዳዊትም በስደት በኖረባቸው ዓመታት ሁሉ የሚያጋጥመውን ሁኔታ ለበጎ ይጠቀምበት ነበር። እርሱና ወታደሮቹ በፋራን ምድረ በዳ በኖሩበት ወቅት የናባልን መንጋ ከሽፍታ ጠብቀውለታል። ከናባል እረኞች መካከል አንዱ “ቀንም ሆነ ሌሊት በዙሪያችን ዐጥር ሆነውን ነበር” በማለት ተናግሯል። (1 ሳሙኤል 25:16) ከጊዜ በኋላም በጺቅላግ በነበረበት ወቅት በደቡብ በኩል የእስራኤል ጠላቶች ይዘዋቸው የነበሩትን ከተሞች በማስለቀቅ የይሁዳን ድንበር አስከብሯል።—1 ሳሙኤል 27:8፤ 1 ዜና መዋዕል 12:20-22

እኛስ ያለንበትን ሁኔታ ለበጎ ለመጠቀም ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ይኖርብን ይሆን? እንዲህ ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆንብን ቢችልም እንኳ ሊሳካልን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ያሳለፈውን ሕይወት በሚመለከት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን . . . ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብም፣ ባገኝም ሆነ ባጣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ።” ጳውሎስ ለሕይወት እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲያዳብር የረዳው ምንድን ነው? ምንጊዜም በይሖዋ መተማመኑ ነው። ይህንንም “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” በማለት ገልጾታል።—ፊልጵስዩስ 4:11-13

ይሖዋን በትዕግሥት ተጠባበቅ

ከዮሴፍና ከዳዊት ተሞክሮ የምናገኘው ሦስተኛው ትምህርት ደግሞ ያለንበትን ሁኔታ ለመለወጥ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ መንገድ ከመጠቀም ይልቅ ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ምንም የማይጐድላችሁ ፍጹማንና ምሉአን እንድትሆኑ ትዕግሥት ሥራውን ይፈጽም” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 1:4) ትዕግሥት ‘ሥራውን እንዲፈጽም’ ከፈለግን ከችግሩ ቶሎ ለመገላገል ስንል ቅዱስ ጽሑፋዊ ወዳልሆኑ መንገዶች ዞር ከማለት ይልቅ እስከመጨረሻው መጽናት ይኖርብናል። በዚህ መንገድ እምነታችን የሚፈተንና የሚጣራ ከመሆኑም በላይ ጥንካሬው ይታያል። ዮሴፍና ዳዊት እንዲህ ያለ ትዕግሥት አሳይተዋል። ይሖዋን ሊያሳዝን በሚችል መንገድ ለችግሩ የራሳቸውን መፍትሔ ለማምጣት አልሞከሩም። ከዚህ ይልቅ ያጋጠማቸውን ሁኔታ ለመቀበል ጥረት አድርገዋል። ይሖዋን በትዕግሥት የጠበቁ ሲሆን እንዲህ በማድረጋቸውም በእጅጉ ተባርከዋል! ይሖዋ ዮሴፍንም ሆነ ዳዊትን ሕዝቦቹን ነጻ ለማውጣትና ለመምራት ተጠቅሞባቸዋል።—ዘፍጥረት 41:39-41፤ 45:5፤ 2 ሳሙኤል 5:4, 5

እኛም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ መፍትሔዎችን እንድንሞክር የሚፈትኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ እስከ አሁን ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ባለማግኘትህ አዝነሃል? ከሆነ ይሖዋ ‘በጌታ ብቻ’ እንድታገባ የሰጠውን ትእዛዝ እንድትጥስ ከሚያደርግ ከማንኛውም ፈታኝ ሁኔታ ራቅ። (1 ቆሮንቶስ 7:39) በትዳርህ ውስጥ አንዳንድ ችግሮች አጋጥመውሃል? ተለያይቶ መኖርንና ፍቺን በሚያበረታታው በዚህ ዓለም መንፈስ ተጽእኖ ከምትሸነፍ ይልቅ ችግሩን ከትዳር ጓደኛህ ጋር ለመፍታት ጥረት አድርግ። (ሚልክያስ 2:16፤ ኤፌሶን 5:21-33) በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ቤተሰብህን ማስተዳደር አስቸጋሪ ሆኖብሃል? ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ ገንዘብ ለማግኘት አጠያያቂ ወይም ሕገ ወጥ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ከመሳተፍ መቆጠብንም ይጨምራል። (መዝሙር 37:25፤ ዕብራውያን 13:18) አዎን፣ ሁላችንም ያለንበትን ሁኔታ ለበጎ ለመጠቀም መትጋትና የይሖዋን በረከት ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህን በምናደርግበት ጊዜ ይሖዋን በትዕግሥት በመጠባበቅ ትክክለኛውን መፍትሔ ማግኘት ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን።—ሚክያስ 7:7

ይሖዋ ይደግፍሃል

ዮሴፍንና ዳዊትን የመሳሰሉ ሰዎች ያጋጠሟቸውን አሳዛኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዴት እንደተቋቋሙ በሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ ማሰላሰላችን በእኛ ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ታሪካቸው ጥቂት ገጾችን ብቻ የሚሸፍን ቢሆንም ያሳለፉት መከራ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ነው። እንዲህ እያልህ ራስህን ጠይቅ:- ‘እንደነዚህ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ያጋጠሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው የኖሩት እንዴት ነበር? ደስታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ የረዳቸው ምንድን ነው? የትኞቹን ባሕርያት ማፍራት አስፈልጓቸዋል?’

ከዚህም በላይ በዚህ ዘመን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች በመከራ ወቅት ስላሳዩት ጽናት የሚናገሩ ታሪኮችን በማንበብ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 5:9) መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በየዓመቱ በርካታ የሕይወት ታሪኮችን ይዘው ይወጣሉ። ስለ ታማኝ ክርስቲያኖች የሚገልጹ ታሪኮችን ታነብባለህ? በታሪኮቹስ ላይ ታሰላስላለህ? በተጨማሪም በእያንዳንዳችን ጉባኤ አስከፊ ሁኔታ ደርሶባቸው በታማኝነት የጸኑ ወንድሞችና እህቶች አሉ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር እነርሱን ቀርበህ በማጫወት ትምህርት ለመቅሰም ትሞክራለህ?—ዕብራውያን 10:24, 25

አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ ይሖዋ እንደሚያስብልህና እንደሚደግፍህ እርግጠኛ ሁን። (1 ጴጥሮስ 5:6-10) ያለህበት ሁኔታ ሕይወትህን እንዲቆጣጠር ላለመፍቀድ ከፍተኛ ጥረት አድርግ። ቂም ባለመያዝ፣ ያለህበትን ሁኔታ ለበጎ በመጠቀም እንዲሁም ለትክክለኛው መፍትሔ ይሖዋን በትዕግሥት በመጠባበቅ የዮሴፍን፣ የዳዊትንና የሌሎች ክርስቲያኖችን ምሳሌ ኮርጅ። በጸሎትና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈል ወደ ይሖዋ ቅረብ። በዚህ መንገድ በአስቸጋሪ ጊዜያት እንኳ ደስታ ልታገኝ ትችላለህ።—መዝሙር 34:8

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮሴፍ ያጋጠሙትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለበጎ ተጠቅሞባቸዋል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት ለችግሮቹ መፍትሔ ለማግኘት ይሖዋን በትዕግሥት ተጠባብቋል