በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍጥረት የአምላክን ክብር ያውጃል!

ፍጥረት የአምላክን ክብር ያውጃል!

ፍጥረት የአምላክን ክብር ያውጃል!

“ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ።”—መዝሙር 19:1

1, 2. (ሀ) ሰዎች የአምላክን ክብር በቀጥታ ማየት የማይችሉት ለምንድን ነው? (ለ) ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች ለአምላክ ክብር የሰጡት እንዴት ነው?

 “ማንም እኔን አይቶ መኖር ስለማይችል፣ ፊቴን ማየት አትችልም” ሲል ይሖዋ ለሙሴ ማስጠንቀቂያ ሰጠው። (ዘፀአት 33:20) ሰዎች ደካማ ሥጋ ለባሽ በመሆናቸው የአምላክን ክብር በቀጥታ ካዩ ለሞት ይዳረጋሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ ይሖዋን በክብራማ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ በራእይ ብቻ እንዲመለከት የተደረገው በዚህ ምክንያት ነው።—ራእይ 4:1-3

2 ከዚህ በተቃራኒ ታማኝ የሆኑ መንፈሳዊ ፍጥረታት የይሖዋን ፊት ማየት ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል ዮሐንስ በራእይ ሰማይ ላይ የተመለከታቸው 144,000ዎቹን የሚወክሉ “ሃያ አራት ሽማግሌዎች” ይገኙበታል። (ራእይ 4:4፤ 14:1-3) የአምላክን ክብር ሲያዩ ምን ተሰማቸው? ራእይ 4:11 እንደሚናገረው “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና” በማለት አውጀዋል።

“ማመካኛ የላቸውም”

3, 4. (ሀ) በአምላክ ማመን ከሳይንስ ጋር ይቃረናል ሊባል የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት አንዳንዶች በአምላክ የማያምኑት ለምንድን ነው?

3 ለአምላክ ክብር ለመስጠት ስሜትህ ያነሳሳሃል? አብዛኞቹ የሰው ልጆች ለአምላክ ክብር አይሰጡም፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ሕልውናውን ይክዳሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ የስነ ፈለክ ተመራማሪ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ለእኛ ሲል ጣልቃ በመግባት አጽናፈ ዓለምን ግሩም አድርጎ ያዘጋጀልን አምላክ ነው እንዴ? . . . ይሄማ ቀልድ ነው። በእኔ እምነት እንደዚያ ብሎ ማሰብ ከእውነት የራቀ ነው። . . . አምላክ ነው የፈጠረው የሚለው አባባል አጥጋቢ መልስ ሊሆን አይችልም።”

4 ሳይንሳዊ ምርምር ገደብ አለው፤ ሰዎች በቀጥታ ሊያዩት ወይም ሊያጠኑት በሚችሉት ነገር ላይ ብቻ የተወሰነ ነው። ከዚህ ውጪ ግን ከንድፈ ሐሳብ ወይም ከመላ ምት አልፎ አይሄድም። “እግዚአብሔር መንፈስ” ስለሆነ ሳይንሳዊ ዘዴዎችን ተጠቅሞ እርሱን መመርመር አይቻልም። (ዮሐንስ 4:24) በመሆኑም በአምላክ ማመን ከሳይንስ ጋር ይቃረናል ብሎ መናገር እንደ ድፍረት ይቆጠራል። የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ሳይንቲስቱ ቪንሰንት ዊገልዝወርዝ ሳይንሳዊ ምርምር በራሱ “ሃይማኖታዊ ስልት” ነው ሲሉ ገልጸዋል። እንዴት? “በግዑዙ ዓለም ላይ የሚታዩ ክስተቶች ‘የተፈጥሮ ሕጎች’ ውጤት ናቸው በሚለው ጽኑ እምነት ላይ የተመሠረተ ነው።” ታዲያ አንድ ሰው በአምላክ አላምንም ሲል አንዱን ትቶ በሌላ ማመኑ አይደል? በአንዳንድ ሁኔታዎች እንደሚታየው በአምላክ አለማመን እውነታውን ላለመቀበል ሆን ተብሎ የሚደረግ ክህደት ነው። መዝሙራዊው “ክፉ ሰው ከትዕቢቱ የተነሣ እግዚአብሔርን አይፈልግም፤ በሐሳቡም ሁሉ አምላክ የለም” ሲል ጽፏል።—መዝሙር 10:4

5. ሰዎች በአምላክ ላለማመን ማመካኛ የላቸውም የምንለው ለምንድን ነው?

5 በአምላክ መኖር እንድናምን የሚያስችሉ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ማስረጃዎች ስላሉ በአምላክ ማመን ጭፍን እምነት አይደለም። (ዕብራውያን 11:1) የስነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት አለን ሰንዴጅ እንዲህ ብለዋል:- “በሥርዓት የተደራጀው [አጽናፈ ዓለም] የተገኘው በፍንዳታ ነው ብሎ መቀበል በጣም ይከብደኛል። ሥርዓትና መልክ እንዲኖረው ያደረገ አንድ ነገር መኖር አለበት። ለእኔ አምላክ እንቆቅልሽ ነው፤ ይሁንና አስደናቂ የሆነው ፍጥረት ሊገኝ የቻለው አምላክ በመኖሩ ነው።” ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ላሉ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል፤ ስለዚህ [በአምላክ መኖር የማያምኑ] ሰዎች ማመካኛ የላቸውም።” (ሮሜ 1:20) “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ” በተለይ ደግሞ የአምላክን መኖር መገንዘብ የሚችሉ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ኃይል ያለው ፈጣሪና አምልኮ ሊሰጠው የሚገባ አምላክ መኖሩ በግልጽ ታይቷል። በመሆኑም የአምላክን ክብር አምኖ መቀበል የተሳናቸው ሰዎች ማመካኛ የላቸውም። ይሁን እንጂ ፍጥረት ምን ማስረጃ ይዟል?

አጽናፈ ዓለም የአምላክን ክብር ያውጃል

6, 7. (ሀ) ሰማያት የአምላክን ክብር የሚያውጁት እንዴት ነው? (ለ) ሰማያት ‘ድምፃቸውን’ ያስተጋቡት ለምን ዓላማ ነው?

6 መዝሙር 19:1 “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ” በማለት መልስ ይሰጣል። “ጠፈር” ወይም ህዋ ውስጥ ብርሃን ፈንጥቀው የሚታዩት ከዋክብትና ፕላኔቶች ታላቅ ክብር ያለው አምላክ ስለመኖሩ የማይካድ ማስረጃ እንደሚያቀርቡ ዳዊት ተገንዝቧል። በመቀጠልም “ቀን ለሌላው ቀን ይናገራል፤ ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀትን ይገልጣል” ብሏል። (መዝሙር 19:2) ቀን በቀን እንዲሁም ሌሊት በሌሊት በተተካ ቁጥር ሰማያት የአምላክን ጥበብና የመፍጠር ችሎታውን ይገልጣሉ። ይህም ሰማያት ለአምላክ የውዳሴ ቃል ‘የተናገሩ’ ያህል ነው።

7 ይሁን እንጂ ይህን ምሥክርነት ለመስማት አስተዋይ መሆን ያስፈልጋል። “ንግግር የለም፤ ቃል የለም፤ ድምፃቸው በጆሮ የሚሰማ አይደለም።” ሆኖም ሰማያት ያለ ድምፅ የሚሰጡት ምሥክርነት በጣም አሳማኝ ነው። “ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፤ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ይወጣል።” (መዝሙር 19:3, 4) ሰማያት ምሥክርነታቸው ከምድር ጫፍ እስከ ምድር ጫፍ እንዲሰማ ድምፃቸውን አስተጋብተዋል ሊባል ይችላል።

8, 9. ፀሐይን በተመለከተ ያሉት አንዳንድ አስደናቂ ሐሳቦች ምንድን ናቸው?

8 ከዚህ በመቀጠል ዳዊት ይሖዋ ስለፈጠረው ሌላ አስደናቂ ነገር ገልጿል:- “እርሱ በሰማያት ለፀሓይ ድንኳን ተክሎአል፤ ፀሓይም ከእልፍኙ እንደሚወጣ ሙሽራ ይወጣል፤ ወደ ግቡም እንደሚሮጥ ብርቱ ሰው ደስ ይለዋል። መውጫው ከሰማያት ዳርቻ ነው፤ ዑደቱም እስከ ሌላኛው ዳርቻ ነው፤ ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም።”—መዝሙር 19:4-6

9 ፀሐይ ከሌሎች ከዋክብት ጋር ስትታይ መጠኗ መካከለኛ ነው። ሆኖም አስደናቂ ኮከብ ከመሆኗ የተነሳ በዙሪያዋ የሚሽከረከሩት ፕላኔቶች ከእርሷ አንጻር ሲታዩ ኢምንት ይመስላሉ። አንድ ምንጭ የፀሐይ ክብደት “2 ቢሊዮን ሲባዛ በቢሊዮን ሲባዛ በቢሊዮን ቶን” እንደሆነ ገልጿል። ይህም እኛ ካለንበት ሥርዓተ ፀሐይ መጠነ ቁስ ውስጥ 99.9 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል! ፀሐይ ያላት የስበት ኀይል 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ምድር ከፀሐይ ሳትርቅም ሆነ ወደ ፀሐይ ሳትቀርብ ምኅዋሯን ጠብቃ እንድትዞር ያስችላታል። ፀሐይ ከምታመነጨው ኃይል ውስጥ ወደ ፕላኔታችን የሚደርሰው ከሁለት ቢሊዮን አንድ እጅ ብቻ ነው። ይሁንና ይህ መጠን በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር ለማስቻል በቂ ነው።

10. (ሀ) ፀሐይ ወደ ‘ድንኳንዋ’ የምትገባውና ከዚያ የምትወጣው እንዴት ነው? (ለ) ፀሐይ እንደ “ብርቱ ሰው” የምትሮጠው እንዴት ነው?

10 መዝሙራዊው ፀሐይን በቀን ከአንዱ አድማስ ወደ ሌላው እንደሚሮጥና ሲመሽ ደግሞ ‘ድንኳኑ’ ውስጥ እንደሚገባ “ብርቱ ሰው” አድርጎ ይገልጻታል። ይህች ግዙፍ ኮከብ ከአድማስ ባሻገር ስትጠልቅ፣ ምድር ሆኖ ለሚያያት ሰው ለእረፍት ወደ “ድንኳን” የምትገባ፤ ጎህ ሲቀድ ደግሞ “ከእልፍኙ እንደሚወጣ ሙሽራ” በድንገት ቦግ ብላ የምትወጣ ትመስላለች። ዳዊት እረኛ ስለነበር ማታ ማታ በጣም እንደሚቀዘቅዝ ያውቃል። (ዘፍጥረት 31:40) የፀሐይ ጨረር እርሱንም ሆነ አካባቢውን ወዲያውኑ እንደሚያሞቅም ትዝ ይለዋል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ፀሐይ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የምታደርገው “ጉዞ” ታክቷት አያውቅም፤ እንዲያውም እንደ “ብርቱ ሰው” ጉዞውን ለመድገም ምንጊዜም ዝግጁ ነች።

አስደናቂ የሆኑት ከዋክብትና ጋላክሲዎች

11, 12. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ከዋክብትን በባሕር ዳር ካለ አሸዋ ጋር አመሳስሎ መግለጹ ምን ትርጉም ይዟል? (ለ) አጽናፈ ዓለም ምን ያህል ስፋት እንዳለው ይገመታል?

11 ዳዊት በባዶ ዓይኑ ማየት የሚችለው በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ከዋክብት ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ በቅርቡ በተካሄደ አንድ ጥናት መሠረት ዘመናዊ ቴሌስኮፖችን በመጠቀም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ 70 ሴክስቲሊዮን ከዋክብት (7ና 22 ዜሮዎች) ማየት ተችሏል! ይሖዋ የከዋክብትን ብዛት ‘በባሕር ዳር ካለ አሸዋ’ ጋር አያይዞ ሲገልጽ በጣም ብዙ መሆናቸውን ጠቁሟል።—ዘፍጥረት 22:17

12 ከበርካታ ዓመታት በፊት የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች “ምንነቱን ለመለየት የሚያስቸግር ሆኖም ደብዛዛ የብርሃን ነጸብራቅ የሚፈነጥቁ፣ መጠናቸው አነስተኛ የሆነ አካላት” መኖራቸውን አይተዋል። ሳይንቲስቶች እነዚህ “ክብ ቅርጽ ያላቸው አንጸባራቂ አካላት” ፍኖተ ሐሊብ በሚባለው በእኛ ጋላክሲ ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ ገምተው ነበር። ክብ ቅርጽ ካላቸው አንጸባራቂ አካላት መካከል በጣም ቅርብ የሆነው አንድሮሜዳ፣ ወደ ሁለት ሚሊዮን የብርሃን ዓመታት ገደማ ርቆ የሚገኝ ራሱን የቻለ ጋላክሲ መሆኑ በ1924 ታወቀ! በአሁኑ ጊዜ ሳይንቲስቶች በሺዎችና አንዳንድ ጊዜም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብት ያቀፉ ከመቶ ቢሊዮን በላይ ጋላክሲዎች እንዳሉ ይገምታሉ። ይሖዋ ግን “የከዋክብትን ብዛት ያውቃል፤ እያንዳንዱንም በስሙ ይጠራዋል።”—መዝሙር 147:4

13. (ሀ) የተለያዩ ኀብረ ከዋክብት ምን አስደናቂ ባሕርይ ይታይባቸዋል? (ለ) ሳይንቲስቶች “የሰማያትን ሥርዐት” እንደማያውቁ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?

13 ይሖዋ ኢዮብን “ፕልያዲስ የተባሉትን ውብ ከዋክብት ልትለጉም፣ ወይም የኦርዮንን ማሰሪያ ልትፈታ ትችላለህን?” ሲል ጠይቆታል። (ኢዮብ 38:31) አንድ ላይ ተሰብስበው የተወሰነ ቅርጽ የሚሠሩ ከዋክብት ኅብረ ኮከብ ተብለው ይጠራሉ። በከዋክብቱ መካከል ከፍተኛ ርቀት ሊኖር ቢችልም ከምድር ሆኖ ሲታዩ ቋሚ ቦታ ያላቸው ይመስላሉ። ቦታቸው በትክክል ስለሚታወቅ እነዚህ ከዋክብት “ለመርከበኞች፣ ለጠፈርተኞችና ኮከቦችን ለይቶ ለማወቅ ጠቃሚ አቅጣጫ ጠቋሚዎች” ናቸው። (ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና) ሆኖም የተለያዩ የከዋክብት ስብስቦችን አንድ ላይ ‘አስሮ’ የያዛቸው ምን እንደሆነ በትክክል የሚያውቅ ሰው የለም። አዎን፣ ሳይንቲስቶች ኢዮብ 38:33 ላይ ለሚገኘው “የሰማያትን ሥርዐት ታውቃለህ?” ለሚለው ጥያቄ እስካሁን ድረስ መልስ አላገኙም።

14. ብርሃን የሚሰራጭበት መንገድ አይታወቅም የሚባለው እንዴት ነው?

14 ሳይንቲስቶች ለኢዮብ ለቀረበለት ‘መብረቅ [“ብርሃን፣” የ1954 ትርጉም] ወደሚሰራጭበት ቦታ የሚያደርሰው መንገድ የትኛው ነው?’ ለሚለው ጥያቄም መለስ የላቸውም። (ኢዮብ 38:24) አንድ ጸሐፊ ስለ ብርሃን የቀረበውን ይህን ጥያቄ “ከባድ ዘመናዊ የሳይንስ ጥያቄ” ብለውታል። ከዚህ በተቃራኒ አንዳንድ የግሪክ ፈላስፎች ብርሃን የሚመነጨው ከሰው ዓይን እንደሆነ ያምኑ ነበር። ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በፊት ደግሞ ሳይንቲስቶች ብርሃን ጥቃቅን ቅንጣቶች አሉት የሚል አስተሳሰብ ይዘው ነበር። ሌሎች ደግሞ በሞገድ መልክ ይጓዛል ብለው አስበዋል። በዛሬው ጊዜ ሳይንቲስቶች ብርሃን ሞገድም፣ ቅንጣትም ነው ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ የብርሃን ባሕርይና ‘የሚሰራጭበት መንገድ’ በትክክል አይታወቅም።

15. ስለ ሰማያት ስናስብ እኛም እንደ ዳዊት ምን ሊሰማን ይገባል?

15 አንድ ሰው በእነዚህ ነጥቦች ላይ ካሰበ በኋላ የመዝሙራዊው ዳዊት ዓይነት ስሜት ማንጸባረቁ አይቀርም:- “የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?”—መዝሙር 8:3, 4

ምድርና በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታት የይሖዋን ክብር ያውጃሉ

16, 17. ‘በጥልቅ ውሆች’ ውስጥ ያሉ ፍጥረታት ይሖዋን የሚያወድሱት እንዴት ነው?

16 መዝሙር 148 ፍጥረት የአምላክን ክብር የሚያውጅባቸውን ሌሎች መንገዶች ይዘረዝራል። ቁጥር 7 እንዲህ ይላል:- “የባሕር ውስጥ ግዙፍ ፍጥረትና ጥልቅ ውሆች ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት።” አዎን፣ “ጥልቅ ውሆች” ውስጥ የአምላክን ጥበብና ኃይል የሚያንጸባርቁ በጣም ብዙ አስደናቂ ፍጥረታት አሉ። ብሉ ዌል የሚባለው ዓሣ ነባሪ በአማካይ 120 ቶን የሚመዝን ሲሆን ይህም 30 ዝሆኖች ያህል ይመዝናል ማለት ነው! ልቡ ብቻ ከ450 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ከመሆኑም ሌላ በመላ ሰውነቱ ውስጥ 6,400 ኪሎ ግራም ያህል ደም ማሰራጨት ይችላል! እነዚህ ግዙፍ የባሕር ፍጥረታት ውኃ ውስጥ ሲጓዙ ቀርፋፋ ናቸው? በፍጹም። ዩሮፒያን ሰቴሽን ባይካች ካምፔይን የተባለ አንድ ድርጅት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በከፍተኛ ፍጥነት “ውቅያኖሶች ውስጥ ይጓዛሉ።” “አንድ ብሉ ዌል በ10 ወራት ውስጥ ከ16,000 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዙን” በሳተላይት በተቀረጸ ፊልም ማየት ተችሏል።

17 ቦትልኖዝድ ዶልፊን በአብዛኛው 45 ሜትር ጠልቆ መግባት የሚችል ሲሆን እስከዛሬ ከተመዘገበው ሁሉ ከፍተኛው ጥልቀት ግን 547 ሜትር ነው። ይህ ዓሣ ያን ያህል ርቀት ጠልቆም ለሞት የማይዳረገው እንዴት ነው? ወደ ታች ጠልቆ ሲገባ የልብ ምቱ ይቀንሳል፤ እንዲሁም በሰውነቱ ውስጥ ያለው ደም ወደ ልቡ፣ ሳምባዎቹና አንጎሉ ይሄዳል። ከዚህ በተጨማሪ የሰውነቱ ጡንቻዎች ኦክስጅን መያዝ የሚችል ኬሚካል አላቸው። አቆስጣና ስፐርም ዌል የሚባለው ዓሣ ነባሪ ደግሞ ከዚያም በላይ ውቅያኖስ ውስጥ ጠልቀው የመግባት ችሎታ አላቸው። ዲስከቨር የተባለ አንድ መጽሔት “የውኃውን ግፊት ለመቋቋም ከመታገል ይልቅ በግፊቱ ኃይል ሳምባቸው ሙሉ በሙሉ እንዲኮማተር ያደርጋሉ” ብሏል። የሚያስፈልጋቸውን አብዛኛውን ኦክስጅን በጡንቻዎቻቸው ውስጥ ያጠራቅማሉ። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው እነዚህ ፍጥረታት ሁሉን ቻይ አምላክ ላለው ጥበብ ሕያው ማስረጃ ናቸው!

18. ውቅያኖስ የይሖዋን ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

18 ውቅያኖስ በራሱ የይሖዋን ጥበብ ያንጸባርቃል። ሳይንቲፊክ አሜሪካን እንዲህ ይላል:- “ከውቅያኖስ ውኃ እስከ 100 ሜትር ድረስ ባለው ጥልቀት የሚገኘው እያንዳንዱ የውኃ ጠብታ በአጉሊ መነጽር ብቻ የሚታዩ ፋይቶፕላንክተን የሚባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ተንሳፋፊ ዕፅዋት ይዟል።” ይህ “በዓይን የማይታይ ጫካ” ብዙ ቢሊዮን ቶን የሚመዝን ካርቦን ዳይኦክሳይድ በማስወገድ የምንተነፍሰውን አየር ያጸዳል። ከምንተነፍሰው ኦክስጅን ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የምናገኘው ከፋይቶፕላንክተን ነው።

19. እሳትና በረዶ የይሖዋን ፈቃድ የሚፈጽሙት እንዴት ነው?

19 መዝሙር 148:8 “እሳትና በረዶ፣ ዐመዳይና ጭጋግ፣ ትእዛዙንም የሚፈጽም ዐውሎ ነፋስ” ይላል። አዎን፣ ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ግዑዝ በሆኑ የተፈጥሮ ኃይሎችም ይጠቀማል። እሳትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ባለፉት አሥርተ ዓመታት ሰደድ እሳት አውዳሚ እንደሆነ ብቻ ተደርጎ ነበር የሚታየው። በአሁኑ ጊዜ ግን ተመራማሪዎች እሳት ያረጁ ወይም የሞቱ ዛፎችን በማስወገድ፣ በርካታ ዘሮች እንዲበቅሉ በማድረግ፣ አፈር ለምነቱን መልሶ እንዲያገኝ በማስቻልና የሰደድ እሳትን ድግግሞሽ በመቀነስ ለተፈጥሮ ሃብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በረዶም ቢሆን አፈሩን በማራስና በማዳበር፣ ወንዞች እንዲሞሉ በማድረግ እንዲሁም ዕፅዋትና እንስሳት ከቅዝቃዜ የተነሳ እንዳይሞቱ በመከላከል ጠቃሚ ድርሻ ያበረክታል።

20. ተራሮችና ዛፎች የሰው ልጆችን የሚጠቅሙት እንዴት ነው?

20 መዝሙር 148:9 “ተራሮችና ኰረብቶች ሁሉ፣ የፍሬ ዛፎችና ዝግቦች ሁሉ” በማለት ተጨማሪ ነገሮች ይጠቅሳል። ግዙፍ የሆኑ ተራሮች ይሖዋ ታላቅ ኃይል እንዳለው ይመሠክራሉ። (መዝሙር 65:6) ሆኖም የሚያከናውኑት ጠቃሚ ሥራም አለ። በበርን ስዊዘርላንድ የሚገኘው የጂኦግራፊ ተቋም ያወጣው ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “የዓለማችን ታላላቅ ወንዞች በሙሉ የሚፈልቁት ከተራሮች ነው። ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ ውሃ የሚያገኘው በተራሮች ውስጥ ከሚከማቸው ንጹሕ ውሃ ነው . . . እነዚህ ‘የውሃ ማማዎች’ ለሰው ልጆች ሕልውና እጅግ ወሳኝ ናቸው።” በየቦታው የሚገኝ ዛፍ እንኳ ሳይቀር ለሠሪው ክብር ያስገኛል። የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ባወጣው አንድ ሪፖርት ላይ እንዲህ ብሏል:- ዛፎች “በየትኛውም አገር ለሚኖሩ ሰዎች ደኅንነት አስፈላጊ ናቸው . . . በርካታ የዛፍ ዝርያዎች እንደ አጣና፣ ፍራፍሬ፣ የቅባት እህል፣ ዕጣንና ሙጫ የመሳሰሉ ምርቶችን በማስገኘት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያበረክታሉ። በዓለም ዙሪያ 2 ቢሊዮን የሚያክሉ ሰዎች ምግብ ለማብሰልና ሙቀት ለማግኘት የሚጠቀሙት በእንጨት ነው።”

21. አንድ ቅጠል ሠሪ እንዳለው የሚያሳየው እንዴት ነው?

21 የዛፍ አፈጣጠር በራሱ ጥበበኛ ፈጣሪ ለመኖሩ ማስረጃ ይሰጣል። ቅጠልን እንውሰድ፤ ከውጭ በኩል ቅጠሉ እንዳይጠወልግ የሚከላከል ቅባትነት ያለው ሽፋን አለው። ከዚህ ሽፋን ስር በላይኛው የቅጠሉ ክፍል ክሎሮፕላስት ያላቸው አንድ ላይ የተከማቹ ሕዋሳት ይገኛሉ። እነዚህ ሕዋሳት ከፀሐይ ብርሃን ኃይል የሚወስድ ክሎሮፊል የሚባል ንጥረ ነገር አላቸው። ፎቶሲንተሲስ በሚባል ሂደት አማካኝነት ቅጠሎች “ምግብ አምራች ፋብሪካ” ሆነው ያገለግላሉ። በዛፎቹ ሥሮች አማካኝነት ውሃ ከተሳበ በኋላ ውስብስብ በሆነ “የቧንቧ መሥመር” በኩል ለቅጠሎቹ ይዳረሳል። በቅጠሉ ጀርባ ያሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ጥቃቅን “መቆጣጠሪያዎች” (ስቶማታ ይባላሉ) የሚከፈቱና የሚዘጉ ሲሆን በዚህ መንገድ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ያስገባሉ። ከፀሐይ ብርሃን በሚገኘው ኃይል አማካኝነት ውሃና ካርቦን ዳይኦክሳይድ ተዋህደው ካርቦሃይድሬት ይዘጋጃል። ከዚህ በኋላ ተክሉ ራሱ ያዘጋጀውን ምግብ ይመገባል። ሆኖም ይህ “ፋብሪካ” ድምፅ አልባ ከመሆኑም በላይ የአካባቢ ብክለት አያስከትልም። እንዲያውም አካባቢውን ከማቆሸሽ ይልቅ ዛፉ የሚያመነጨው ተረፈ ምርት ኦክስጅን ነው!

22, 23. (ሀ) አንዳንድ ወፎችና እንስሳት ምን ዓይነት አስደናቂ ችሎታ አላቸው? (ለ) መልስ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ተጨማሪ ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?

22 መዝሙር 148:10 “የዱር አራዊትና የቤት እንስሳት ሁሉ፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና የሚበሩ ወፎችም” ይላል። ብዙ እንስሳትና ሰማይ ላይ የሚበርሩ ፍጥረታት አስገራሚ ችሎታ አላቸው። በላይሳን የሚገኘው አልባጥሮስ የሚባለው ትልቅ የባሕር ወፍ ብዙ ርቀት መብረር ይችላል (በአንድ ወቅት በ90 ቀናት ውስጥ ብቻ 40,000 ኪሎ ሜትር በርሯል።) ብላክፖል ዋርብለር የምትባለው ወፍ ከሰሜን ወደ ደቡብ አሜሪካ በምታደርገው ጉዞ ምንም ሳታርፍ ከ80 ሰዓታት በላይ ትበርራለች። ግመል ውሃ የማጠራቀም ችሎታ ስላለው ሳይጠማው ለበርካታ ቀናት ሊቆይ ይችላል። ውሃውን የሚያጠራቅመው በተለምዶ እንደሚታሰበው በሻኛው ውስጥ ሳይሆን በምግብ መፍጫ የሰውነቱ ክፍሎች ውስጥ ነው። መሐንዲሶች ለማሽኖችና ለአዳዲስ መሣሪያዎች ንድፍ ለማውጣት እንስሳትን በጥንቃቄ የሚያጠኑ መሆናቸው ምንም አይገርምም። ጸሐፊዋ ጌይል ክሊር “በደንብ የሚሠራ . . . እንዲሁም በአካባቢ ላይ ብክለት የማያስከትል መሣሪያ መፈልሰፍ ከፈለጋችሁ ተፈጥሮን በማየት ናሙና የሚሆን ጥሩ ነገር ማግኘት ትችላላችሁ” ብለዋል።

23 አዎን፣ ፍጥረት የአምላክን ክብር በሚገባ ያውጃል! በከዋክብት ከተሞላው ሰማይ አንስቶ እስከ ዕፅዋትና እንስሳት ድረስ እያንዳንዱ የፍጥረት ሥራ በተለያየ መንገድ ፈጣሪን ያወድሳል። በዚህ ረገድ እኛስ ምን ማድረግ እንችላለን? እንደ ፍጥረት ሥራዎች ሁሉ እኛም አምላክን ማወደስ የምንችለው እንዴት ነው?

ታስታውሳለህ?

• በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች ማመካኛ የላቸውም የምንለው ለምንድን ነው?

• ከዋክብትና ፕላኔቶች ለአምላክ ክብር የሚያመጡት እንዴት ነው?

• የባሕር ውስጥና የምድር ላይ እንስሳት አፍቃሪ አምላክ ለመኖሩ ማስረጃ የሚሆኑት እንዴት ነው?

• ግዑዝ የተፈጥሮ ኃይሎች የይሖዋን ፈቃድ የሚፈጽሙት እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳይንቲስቶች እስካሁን ድረስ የተደረሰባቸው ከዋክብት ብዛት 70 ሴክስቲሊዮን እንደሚሆን ገምተዋል!

[ምንጭ]

Frank Zullo

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቦትልኖዝድ ዶልፊን

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የበረዶ ቅንጣት

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የላይሳን አልባጥሮስ ጫጩት

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]

snowcrystals.net