በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕያው የሆነው አምላክ የሚሰጠውን መመሪያ ተከተል

ሕያው የሆነው አምላክ የሚሰጠውን መመሪያ ተከተል

ሕያው የሆነው አምላክ የሚሰጠውን መመሪያ ተከተል

“ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር [ተመለሱ]።”—የሐዋርያት ሥራ 14:15

1, 2. ይሖዋ “ሕያው አምላክ” መሆኑን መቀበል ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

 ሐዋርያው ጳውሎስና በርናባስ ልስጥራን ውስጥ አንድን ሰው ከፈወሱ በኋላ ጳውሎስ ሁኔታውን ይመለከቱ ለነበሩ ሰዎች እንዲህ አላቸው:- “እኛም እኮ እንደ እናንተው ሰዎች ነን። እናንተም ደግሞ ከዚህ ከንቱ ነገር ርቃችሁ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር እንድትመለሱ ወንጌልን እንሰብክላችኋለን።”—የሐዋርያት ሥራ 14:15

2 በእርግጥም ይሖዋ በድን ጣዖት ሳይሆን “ሕያው አምላክ” ነው። (ኤርምያስ 10:10፤ 1 ተሰሎንቄ 1:9, 10) እርሱ ራሱ ሕያው ከመሆኑ ባሻገር የሕይወት ምንጭ ነው። “ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ” የሚሰጠው እርሱ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 17:25) አሁንም ሆነ ወደፊት ተደስተን እንድንኖር ይፈልጋል። ጳውሎስ፣ አምላክ “ዝናብን ከሰማይ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠቱ፣ ደግሞም ልባችሁን በመብልና በደስታ በማርካቱ መልካምን በማድረግ ራሱን ያለ ምስክር አልተወም” በማለት አክሎ ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 14:17

3. አምላክ በሚሰጠው መመሪያ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

3 አምላክ የሚያስብልን መሆኑ በሚሰጠን መመሪያ እንድንተማመን ይገፋፋናል። (መዝሙር 147:8፤ ማቴዎስ 5:45) አንዳንድ ሰዎች አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ካልገባቸው ወይም ነጻነታቸውን የሚነፍግ መስሎ ከታያቸው መመሪያውን መከተል አይፈልጉ ይሆናል። ያም ሆኖ ግን ይሖዋ በሚሰጠው መመሪያ መተማመን ጠቃሚ መሆኑ ታይቷል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- አንድ እስራኤላዊ በድን እንዳይነካ የሚያዘው ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ባይገባውም እንኳ ትእዛዙን በማክበር ይጠቀማል። በመጀመሪያ ደረጃ ታዛዥ መሆኑ ሕያው ወደሆነው አምላክ እንዲቀርብ የሚረዳው ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በበሽታ ከመያዝ ይጠበቃል።—ዘሌዋውያን 5:2፤ 11:24

4, 5. (ሀ) ከክርስትና ዘመን በፊት ይሖዋ ደምን በሚመለከት ምን መመሪያ ሰጥቶ ነበር? (ለ) አምላክ ደምን በሚመለከት የሰጠው መመሪያ በክርስቲያኖችም ላይ እንደሚሠራ እንዴት እናውቃለን?

4 አምላክ ደምን በሚመለከት የሰጠው መመሪያም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። አምላክ፣ ሰዎች ደም መብላትም ሆነ መጠጣት እንደማይኖርባቸው ለኖኅ ነግሮት ነበር። ከዚያም በሕጉ ውስጥ ደም ጥቅም ላይ መዋል የሚኖርበት ኀጢአትን ለማስተስረይ በመሰዊያ ላይ በመቅረብ ብቻ እንደሆነ አስታወቀ። አምላክ በእነዚህ መመሪያዎች አማካኝነት ደም ለሚሰጠው የላቀ ጥቅም ይኸውም በኢየሱስ ቤዛ አማካኝነት ሰዎችን ለማዳን የሚያስችል መሠረት ጥሏል። (ዕብራውያን 9:14) አዎን፣ የአምላክ መመሪያዎች እርሱ ስለ ሕይወታችንና ስለ ደኅንነታችን እንደሚያስብ ያሳያሉ። አዳም ክላርክ የተባሉ የ19ኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ዘፍጥረት 9:4ን በሚመለከት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች [ለኖኅ የተሰጠውን] ይህን ትእዛዝ አሁን ድረስ በጥብቅ ይከተላሉ . . . ደም ለዓለም ኀጢአት የሚፈሰውን ደም ያመለክት ስለነበር ሕጉ ደም መብላትን ፈጽሞ ይከለክል ነበር። እንዲሁም በወንጌል ዘመን ለኀጢአት ስርየት የፈሰሰውን ደም እንደሚወክል ስለሚታመን ፈጽሞ አይበላም ነበር።”

5 እኚህ ምሑር በኢየሱስ ሕይወት ላይ ስለሚያተኩረው ወንጌል ወይም ምሥራች መናገራቸው ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ አምላክ፣ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ልጁ ደሙን በማፍሰስ ለእኛ እንዲሞት ወደ ምድር መላኩን ይጨምራል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 5:8, 9) ምሑሩ የሰጡት ሐሳብ የክርስቶስ ተከታዮች ከደም እንዲርቁ ተሰጥቷቸው የነበረውን ትእዛዝም ያካትታል።

6. ደምን በሚመለከት ለክርስቲያኖች ምን መመሪያዎች ተሰጥተዋቸው ነበር? ለምንስ?

6 አምላክ ለእስራኤላውያን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጎች ሰጥቷቸው እንደነበር የታወቀ ነው። ከኢየሱስ ሞት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እነዚያን ሁሉ ሕጎች የመጠበቅ ግዴታ አልነበረባቸውም። (ሮሜ 7:4, 6፤ ቆላስይስ 2:13, 14, 17፤ ዕብራውያን 8:6, 13) ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ አንደኛውን መሠረታዊ ግዴታ ይኸውም የወንዶች ግዝረትን በሚመለከት ጥያቄ ተነሳ። የክርስቶስ ደም የሚያስገኘውን ጥቅም የሚፈልጉ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች በሕጉ ሥር መሆናቸውን ለማሳየት መገረዝ ይኖርባቸዋል? በ49 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የአስተዳደር አካሉ በዚህ ጥያቄ ላይ ውይይት አደረገ። (የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15) ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በአምላክ መንፈስ ተመርተው ግዝረት ከሕጉ ጋር እንደተሻረ ውሳኔ አስተላለፉ። የሆነ ሆኖ ክርስቲያኖች አንዳንዶቹን መለኮታዊ ትእዛዛት እንዲያከብሩ ይጠበቅባቸው ነበር። የአስተዳደር አካሉ ለጉባኤዎች በላከው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ከእነዚህ አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ፣ ለመንፈስ ቅዱስም ለእኛም መልካም መስሎ ታይቶናል፤ ይኸውም:- ለጣዖት ከተሠዋ ነገር፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከዝሙት ርኩሰት እንድትርቁ ነው። ከእነዚህ ዐይነት ነገሮች ብትርቁ ለእናንተ መልካም ነው።”—የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29

7. ክርስቲያኖች ‘ከደም መራቃቸው’ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

7 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ የአስተዳደር አካሉ ‘ከደም መራቅ’ ከዝሙትና ከጣዖት አምልኮ የመራቅን ያህል በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ይህ ደግሞ ደምን በሚመለከት የተሰጠው መመሪያ ከባድ ጉዳይ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ጣዖት ያመለኩና የጾታ ብልግና የፈጸሙ ክርስቲያኖች ንስሐ ካልገቡ በስተቀር “የእግዚአብሔርን መንግሥት” አይወርሱም፤ እንዲያውም “ዕጣ ፈንታቸው . . . ሁለተኛው ሞት ነው።” (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:8፤ 22:15) አምላክ የደም ቅድስናን በሚመለከት የሰጠውን መመሪያ ችላ ማለት ዘላለማዊ ሞት ያስከትላል። በአንጻሩ ደግሞ ለኢየሱስ መሥዋዕት አክብሮት ማሳየት የዘላለም ሕይወት ያስገኛል። ይህ ንጽጽር ልብ ሊባል የሚገባው ነው።

8. የጥንት ክርስቲያኖች አምላክ ደምን በሚመለከት የሰጠውን መመሪያ አክብደው ይመለከቱት እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?

8 የጥንት ክርስቲያኖች አምላክ ደምን በሚመለከት የሰጠውን መመሪያ የተረዱት እንዴት ነበር? ምንስ እርምጃ ወስደዋል? ክላርክ “በወንጌል ዘመን [ደም] ለኀጢአት ስርየት የፈሰሰውን ደም እንደሚወክል ስለሚታመን ፈጽሞ አይበላም ነበር” በማለት የሰጡትን አስተያየት አስታውስ። የጥንት ክርስቲያኖች ጉዳዩን አክብደው ይመለከቱት እንደነበር ታሪክ ያረጋግጥልናል። ተርቱሊያን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ከክፉ ወንጀለኞች . . . የሚፈሰውን ትኩስ ደም ተስገብግበው የሚልፉትንና ከሚጥል በሽታቸው ለመፈወስ ቀድተው የሚወስዱትን ሰዎች ተመልከቱ።” እንዲህ ያደርጉ ከነበሩት አረማውያን በተቃራኒ ክርስቲያኖች “የእንስሳትን ደም እንኳ በምግባቸው ውስጥ አይጨምሩም። . . . ክርስቲያኖችን ለመፈተን በደም የተሞላ ቋሊማ ስጧቸው። በሕጋቸው ፈጽሞ ያልተፈቀደ መሆኑን ታረጋግጣላችሁ” በማለት ተርቱሊያን ተናግሯል። አዎን፣ ክርስቲያኖች እንደሚገደሉ ማስፈራሪያ ቢሰነዘርባቸው እንኳ ደም አይበሉም። የአምላክን መመሪያ ያን ያህል አክብደው ይመለከቱት ነበር።

9. ከደም መራቅ በቀጥታ አለመብላትን ብቻ ሳይሆን ምንን ይጨምራል?

9 አንዳንዶች የአስተዳደር አካሉ ክርስቲያኖች ደም በቀጥታ እንዳይበሉ ወይም እንዳይጠጡ አሊያም ሥጋን ከነደሙ ወይም ደም የተቀላቀለበት ምግብ እንዳይበሉ ብቻ እንደከለከለ ይሰማቸው ይሆናል። እርግጥ ነው፣ አምላክ ለኖኅ የሰጠው ትእዛዝ የያዘው ዋነኛ ትርጉም ይህ ነበር። እንዲሁም የሐዋርያት ድንጋጌ ክርስቲያኖች “ታንቆ የሞተ ከብት” ይኸውም ደም ያለበት ሥጋ ‘ከመብላት ራሳቸውን እንዲጠብቁ’ የሚያዝ ነበር። (ዘፍጥረት 9:3, 4፤ የሐዋርያት ሥራ 21:25) ይሁን እንጂ የጥንት ክርስቲያኖች ከዚህም የበለጠ ትርጉም እንደነበረው ያውቁ ነበር። ደም ለመድኃኒትነት ጥቅም ላይ የዋለባቸው ጊዜያት ነበሩ። ተርቱሊያን አንዳንድ አረማውያን ከሚጥል በሽታ ለመዳን ሲሉ ትኩስ ደም ይጠጡ እንደነበር ተናግሯል። ደም በሽታን ለማዳን ወይም የተሻለ ጤንነት ለማግኘት ጥቅም ላይ የዋለባቸው ሌሎች መንገዶችም ይኖሩ ይሆናል። በመሆኑም ክርስቲያኖች ከደም መራቃቸው “ለመድኃኒትነት” አለመውሰድንም ይጨምር ነበር። ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም እንኳ ከዚህ አቋማቸው ፍንክች አላሉም።

ደም ለሕክምና ሲውል

10. በሕክምና መስክ ደም ጥቅም ላይ የሚውልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ይህስ ምን ጥያቄ ያስነሳል?

10 በዛሬው ጊዜ ደምን ለሕክምና መጠቀም በጣም የተለመደ ነው። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ደም ከለጋሾች ተወስዶ ይቀመጥና ለበሽተኞች ምናልባትም ለጦር ሜዳ ቁስለኞች ሙሉው ደም ይሰጥ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ተመራማሪዎች ደምን በዋና ዋና ክፍሎች መለያየት እንደሚቻል ተገነዘቡ። ስለዚህ ለአንድ ቁስለኛ ፕላዝማ ለሌላው ደግሞ ቀይ የደም ሴሎችን በመስጠት ከለጋሾች የተገኘውን ደም ለብዙ ታካሚዎች ማዳረስ ቻሉ። በመስኩ በተደረገ ተጨማሪ ጥናት ፕላዝማን ከመሳሰሉ ዋና ዋና የደም ክፍሎች ብዙ ክፍልፋዮችን ማውጣት የተቻለ ሲሆን ይህም ደሙን የበለጠ ቁጥር ላላቸው ታካሚዎች ለማዳረስ አስችሏል። ተጨማሪ የደም ክፍልፋዮችን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት የቀጠለ ሲሆን አዲስ የተገኙ የደም ክፍልፋዮች ጥቅም ላይ መዋላቸው በየጊዜው ይዘገባል። አንድ ክርስቲያን የደም ክፍልፋዮችን ለሕክምና መጠቀምን በሚመለከት ምን አመለካከት ሊኖረው ይገባል? ደም ላለመውሰድ ቁርጥ አቋም ቢይዝም ዶክተሩ አንድን ዋና የደም ክፍል ምናልባትም ቀይ የደም ሴሎችን እንዲወስድ ይገፋፋው ይሆናል። ወይም ደግሞ ሕክምና የሚደረግለት ከዋና ዋናዎቹ የደም ክፍሎች በተወሰደ ክፍልፋይ ሊሆን ይችላል። አንድ የአምላክ አገልጋይ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ደም ቅዱስ እንደሆነና ሙሉ በሙሉ ሕይወት አድን የሆነው የክርስቶስ ደም መሆኑን ሳይዘነጋ ውሳኔ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?

11. የይሖዋ ምሥክሮች ከረጅም ዓመታት በፊት አንስቶ ደምን በሚመለከት ምን አቋም ይዘዋል?

11 ከበርካታ ዓመታት በፊት የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ያላቸውን አቋም በግልጽ አሳውቀዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን (ኅዳር 27, 1981) በተባለው መጽሔት ላይ የታተመ አንድ ጽሑፍ አዘጋጅተው ነበር። (ይህ ጽሑፍ ደም ሕይወትህን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው? በተሰኘው ብሮሹር ገጽ 27-9 ላይ እንደገና ታትሟል።) a ጽሑፉ ከዘፍጥረት፣ ከዘሌዋውያንና ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፎች ላይ ጠቅሶ እንዲህ ብሏል:- “እነዚህ ጥቅሶች የተጻፉት ከሕክምና አንፃር ባይሆንም ሙሉ ደም፣ የታመቁ ቀይ የደም ሕዋሳት፣ ፕላዝማ፣ ነጭ የደም ሕዋሳትና ፕሌትሌት መውሰድን የሚከለክሉ ጥቅሶች እንደሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ያምናሉ።” ኢመርጀንሲ ኬር የተባለው የ2001 መማሪያ መጽሐፍ “ኮምፖዚሽን ኦቭ ዘ ብለድ” (የደም ቅንብር) በሚል ርዕስ ሥር “ደም ፕላዝማ፣ ቀይና ነጭ የደም ሕዋሳት እንዲሁም አርጊ ሕዋስ ደም (platelets) የተባሉ ዋና ዋና ክፍሎች ውሁድ ነው” ብሏል። በመሆኑም የሕክምናው መስክ ከደረሰበት ከዚህ ሐቅ በመነሳት የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉውን ደምም ይሁን አራቱን ዋና ዋና ክፍሎች ለመውሰድ ፈቃደኞች አይደሉም።

12. (ሀ) ከዋና ዋና የደም ክፍሎች የተወሰዱ ክፍልፋዮችን በሚመለከት ምን አቋም እንዳለን ተገልጿል? (ለ) ይህን በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ ከየት ማግኘት ይቻላል?

12 የሕክምና መጽሔቱ ቀጥሎ እንዲህ ይላል:- “የምሥክሮቹ ሃይማኖታዊ ግንዛቤ [ከደም ክፍልፋዮች የሚቀመሙ] እንደ አልቡሚንና ኢምዩን ግሎቡሊን የመሰሉትን ንጥረ ነገሮችና ሂሞፊልያ የተባለ የደም አለመርጋት ችግር ላለባቸው ሰዎች የሚሰጡትን መድኃኒቶች ሙሉ በሙሉ አይከለክልም። እነዚህን መውሰድና አለመውሰድ በእያንዳንዱ ግለሰብ ምሥክር ይወሰናል።” ከ1981 ጀምሮ በርካታ ክፍልፋዮች (ከአራቱ ዋና ዋና የደም ክፍሎች የሚወሰዱ ንጥረ ነገሮች) ተቀምመው ጥቅም ላይ ውለዋል። በመሆኑም የሰኔ 15, 2000 መጠበቂያ ግንብ “የአንባብያን ጥያቄዎች” በሚለው ርዕስ ሥር ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጠቃሚ መረጃዎችን ይዞ ወጥቷል። በአሁኑ ጊዜ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንባቢያንን ለመጥቀም ሲባል የጥያቄው መልስ በዚህ መጽሔት ገጽ 29-31 ላይ በድጋሚ እንዲታተም ተደርጓል። ርዕሰ ጉዳዩ ዝርዝር ሐሳቦችንና ምክንያታዊ ማብራሪያዎችን የያዘ ቢሆንም ዋና ዋና ነጥቦቹ በ1981 ከቀረበው ጋር ተመሳሳይ ናቸው።

ኅሊናህ ምን ሚና አለው?

13, 14. (ሀ) ኅሊና ምንድን ነው? ከደም ጋር በተያያዘስ ምን ቦታ አለው? (ለ) አምላክ ሥጋ መብላትን በሚመለከት ለእስራኤላውያን ምን መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር? ሆኖም ምን ጥያቄዎች ተነስተው ሊሆን ይችላል?

13 የአንባቢያን ጥያቄዎች በሚለው ርዕስ ሥር የቀረቡት ሐሳቦች በኅሊና መወሰን የሚኖርባቸው ጉዳዮች ናቸው። ለምን? ክርስቲያኖች የአምላክን መመሪያ መከተል አስፈላጊ መሆኑ ቢሰማቸውም አንዳንድ ጊዜ በግል ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ጉዳዮች ያጋጥሟቸዋል። በእነዚህ ወቅቶች ኅሊናቸውን መጠቀም ይኖርባቸዋል። ኅሊና ብዙውን ጊዜ ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አመዛዝኖ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል የተፈጥሮ ስጦታ ነው። (ሮሜ 2:14, 15) ይሁን እንጂ የአንድ ሰው ኅሊና ከሌላው እንደሚለይ የታወቀ ነው። b መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንዶች ‘ደካማ ኅሊና’ እንዳላቸው መናገሩ ጠንካራ ኅሊና ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን ይጠቁማል። (1 ቆሮንቶስ 8:12) ክርስቲያኖች የአምላክን ፈቃድ በመማር፣ አስተሳሰቡን በመገንዘብ እንዲሁም ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ረገድ ያላቸው የእድገት ደረጃ የተለያየ ነው። ይህን ጉዳይ አይሁዳውያን ሥጋን ከመብላት ጋር በተያያዘ በውስጣቸው ሊፈጠሩባቸው የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሳት በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል።

14 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን መመሪያ የሚታዘዝ ሰው ደም ያለበትን ሥጋ እንደማይበላ በግልጽ ይናገራል። ይህ መመሪያ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ እስራኤላውያን ወታደሮች ተቻኩለው ሥጋውን ከነደሙ በበሉ ጊዜ ከባድ በደል ወይም ኀጢአት እንደሠሩ ተነግሯቸዋል። (ዘዳግም 12:15, 16፤ 1 ሳሙኤል 14:31-35) የሆነ ሆኖ አንዳንድ ጥያቄዎች ተነስተው ሊሆን ይችላል። አንድ እስራኤላዊ በግ በሚያርድበት ጊዜ ደሙ ቶሎ እንዲፈስ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? የበጉን የኋላ እግሮች አስሮ ማንጠልጠል ያስፈልገዋል? ከሆነስ ለምን ያህል ጊዜ? ከብቱ ትልቅ ቢሆንስ ምን ማድረግ ይችላል? ደሙ ከፈሰሰ በኋላም እንኳ የተወሰነ ደም ሥጋው ውስጥ ሊቀር ይችላል። እንዲህ ያለ ሥጋ መብላት ይኖርበታል? እንዲህ ያለውን ውሳኔ ማድረግ የሚኖርበት ማን ነው?

15. አንዳንድ አይሁዳውያን ሥጋ መብላትን በሚመለከት የተለያዩ ውሳኔዎችን ያደረጉት እንዴት ነው? ይሁንና አምላክ የሰጠው ትእዛዝ ምን ነበር?

15 አንድ ቀናተኛ አይሁዳዊ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች አጋጥመውታል እንበል። አንድ ሌላ አይሁዳዊ ለጣዖት የተሠዋ ሊሆን ይችላል በሚል ስሜት ከገበያ የተገዛ ሥጋ ላለመብላት ሊወስን እንደሚችለው ሁሉ እርሱም ጭራሽ ከገበያ ሥጋ አለመግዛቱ የተሻለ እንደሆነ ይሰማው ይሆናል። ሌሎች አይሁዳውያን ደግሞ ሥጋ የሚበሉት ደሙን ለማስወገድ የተለያዩ ሥርዓቶችን ከተከተሉ በኋላ ሊሆን ይችላል። c (ማቴዎስ 23:23, 24) እንዲህ ስላለው የተለያየ አቋም አንተ ምን ይሰማሃል? ከዚህም በላይ አምላክ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መመሪያ ስላልሰጠ አይሁዳውያኑ ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ረቢዎችን መጠየቅ ያስፈልጋቸው ይሆን? በአይሁድ እምነት ውስጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ የተለመደ ቢሆንም ይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎቹ ደምን በሚመለከት ዝርዝር ጉዳዮችን ጠይቀው እንዲረዱ ባለማዘዙ ደስ ሊለን ይገባል። አምላክ ንጹሕ የሆኑ እንስሳትን ስለማረድና ደሙን ስለማፍሰስ መሠረታዊ መመሪያ እንጂ ዝርዝር ሕጎችን አልሰጠም።—ዮሐንስ 8:32

16. አንዳንድ ክርስቲያኖች ከዋና ዋና የደም ክፍሎች በሚገኙ ክፍልፋዮች የሚሠሩ መድኃኒቶችን በመውሰድ ረገድ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

16 በአንቀጽ 11 እና 12 ላይ እንደተገለጸው የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉውን ደም እንዲሁም ፕላዝማ፣ ቀይ የደም ሴሎች፣ ነጭ የደም ሴሎችና አርጊ ሕዋስ ደም የተባሉትን አራት ዋና ዋና የደም ክፍሎች አይወስዱም። የደም እዥን ከመሳሰሉ ዋና ዋና የደም ክፍሎች የሚቀመሙና አንድን በሽታ ለማዳን ወይም የእባብን መርዝ ለማርከስ የሚረዱ ፀረ እንግዳ አካላት (antibodies) ያሉባቸውን የደም ክፍልፋዮች መውሰድን በሚመለከትስ ምን ለማለት ይቻላል? (ገጽ 30 አንቀጽ 4ን ተመልከት።) አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ እነዚህ ጥቃቅን ክፍልፋዮች ደም ሊባሉ ስለማይችሉ ‘ከደም ራቁ’ በሚለው ትእዛዝ ውስጥ አይጠቃለሉም የሚል አቋም አላቸው። (የሐዋርያት ሥራ 15:29፤ 21:25፤ ገጽ 31 አንቀጽ 1) ይህ የራሳቸው ኃላፊነት ነው። ሌሎች ደግሞ ከዋና ዋና የደም ክፍሎች የሚወሰዱ ጥቃቅን ክፍልፋዮችን ጨምሮ ከደም (ከእንስሳም ሆነ ከሰው) የሚገኝን ማንኛውንም ነገር ለመውሰድ ኅሊናቸው አልፈቀደላቸውም። d በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች በሽታን ለማዳን ወይም የእባብ መርዝን ለማርከስ ከፕላዝማ ፕሮቲን ተቀምመው በመርፌ የሚሰጡ መድኃኒቶችን ለመውሰድ ፈቃደኛ ሲሆኑ ጥቃቅን ክፍልፋዮችን ግን መውሰድ አይፈልጉም። ከዚህም በላይ ከአራቱ የደም ዋና ዋና ክፍሎች የሚወሰዱ አንዳንድ ክፍልፋዮች ያላቸው ጥቅም ዋና ዋና የደም ክፍሎች ከሚሰጡት ጥቅም ጋር ተመሳሳይ በመሆኑና በሰውነት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ሚና ስለሚጫወቱ በርካታ ክርስቲያኖች እነዚህን መውሰዱ ተገቢ እንደማይሆን ተሰምቷቸዋል።

17. (ሀ) የደም ክፍልፋዮችን ስለመውሰድ ጥያቄዎች ሲያጋጥሙን ኅሊናችን ሊመራን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን ማድረግ ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?

17 እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ኅሊናን በሚመለከት የሚናገረውን ተግባራዊ ማድረጋችን ጠቃሚ ነው። የመጀመሪያው እርምጃ የአምላክ ቃል ምን እንደሚል መመርመርና ኅሊናህን በዚያ ለመቅረጽ ጥረት ማድረግ ነው። ይህም ሌላ ሰው እንዲወስንልህ ከመጠየቅ ይልቅ አምላክ ከሰጠው መመሪያ ጋር የሚስማማ ውሳኔ እንድታደርግ ይረዳሃል። (መዝሙር 25:4, 5) አንዳንዶች የደም ክፍልፋዮች መውሰድን በሚመለከት ‘ይህ ለኅሊና የተተወ ስለሆነ የሚያስከትለው ችግር የለም’ የሚል ሐሳብ አላቸው። እንዲህ ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም። አንድ ነገር ለኅሊና የተተወ ነው ሲባል ችግር የማያስከትል ተራ ጉዳይ ነው ማለት አይደለም። ከባድ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ከእኛ የተለየ ኅሊና ያላቸውን ሰዎች ሊጎዳ ይችላል። ጳውሎስ፣ ምናልባት ለጣዖት ከታረደ በኋላ ለገበያ የቀረበ ሥጋን በሚመለከት ከሰጠው ምክር ይህን መገንዘብ እንችላለን። አንድ ክርስቲያን የሌሎችን ‘ደካማ ኅሊና እንዳያቆስል’ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ሌሎችን ካሰናከለ ‘ክርስቶስ የሞተለትን ወንድሙን በማጥፋት’ ክርስቶስን ሊበድል ይችላል። በመሆኑም፣ ጥቃቅን የደም ክፍልፋዮችን መውሰድ አለመውሰድ ለእያንዳንዱ ኅሊና የተተወ ቢሆንም እንደነዚህ ያሉ ውሳኔዎች በጣም ታስቦባቸው ሊደረጉ ይገባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 8:8, 11-13፤ 10:25-31

18. አንድ ክርስቲያን ከደም ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን ሲያደርግ ኅሊናው እንዳይደነዝዝ መጠንቀቅ የሚችለው እንዴት ነው?

18 ደምን በሚመለከት የሚደረገው ውሳኔ ከባድ እንደሆነ የሚያሳይ ሌላም ነጥብ አለ። ይህም የምታደርገው ውሳኔ አንተን ሊነካ የሚችል መሆኑ ነው። የደም ክፍልፋይ ለመውሰድ በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ኅሊናህ የማይፈቅድልህ ከሆነ ቸል ልትለው አይገባም። ወይም ሌሎች “ብዙዎች ስለሚወስዱ አንተም ብትወስድ ምንም ችግር የለውም” ስላሉህ ብቻ ኅሊናህን መጣስ አይኖርብህም። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ኅሊናቸውን ችላ በማለታቸው ስለደነዘዘ ሲዋሹ ወይም ሌሎች መጥፎ ነገሮችን ሲሠሩ እንደማይቆረቁራቸው አትዘንጋ። ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳይደርስባቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።—2 ሳሙኤል 24:10፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1, 2

19. ከደም ጋር የተያያዙ የሕክምና ጉዳዮችን በሚመለከት ውሳኔ ስናደርግ ለምን ነገር የላቀ ቦታ መስጠት ይኖርብናል?

19 በገጽ 29-31 ላይ በድጋሚ የወጣው ማብራሪያ በማጠቃለያው ላይ “የሰዎች አመለካከትና የሚወስዱት ማስተዋል የተሞላበት ውሳኔ ሊለያይ መቻሉ ጉዳዩ ክብደት የሌለው ተራ ነገር ነው ማለት ነውን?” የሚል ጥያቄ ያነሳና “እንደዚያ ማለት አይቻልም። እንዲያውም አሳሳቢ ጉዳይ ነው” በማለት መልስ ይሰጣል። ይህ ሊሆን የቻለው ‘ሕያው ከሆነው አምላክ’ ጋር ያለህን ዝምድና ስለሚነካብህ ነው። የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝልህ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም አማካኝነት ከእርሱ ጋር የመሠረትከው ዝምድና ነው። አምላክ በደም አማካኝነት ሕይወት የማዳን ዓላማ ስላለው አንተም ለደም ከፍተኛ አክብሮት ይኑርህ። ጳውሎስ እንደሚከተለው ማለቱ የተገባ ነው:- “በዓለም ላይ ያለ ተስፋና ያለ እግዚአብሔር እንደ ነበራችሁ አስታውሱ። አሁን ግን እናንተ ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል።”—ኤፌሶን 2:12, 13

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

b በአንድ ወቅት ጳውሎስና ሌሎች አራት ክርስቲያኖች ሥርዓቱ በሚጠይቀው መሠረት ራሳቸውን ለማንጻት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደው ነበር። በወቅቱ ሕጉ በእነርሱ ላይ የማይሠራ ቢሆንም ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ያሉ ሽማግሌዎች የሰጡትን ምክር ተከትሏል። (የሐዋርያት ሥራ 21:23-25) ይሁን እንጂ አንዳንድ ክርስቲያኖች ወደ ቤተ መቅደስ መግባት እንደሌለባቸው ወይም እንዲህ ያለውን ሥርዓት መከተል እንደማይገባቸው ተሰምቷቸው ይሆናል። በዚያ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም የሰዎች ኅሊና ይለያያል።

c ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ ሥጋን “የማንጻት ሥርዓት” በሚመለከት “የተወሳሰቡና ዝርዝር” ደንቦችን ይዟል። መጽሐፉ ሥጋው በውኃ ውስጥ ምን ያህል መዘፍዘፍ እንደሚኖርበት፣ በመክተፊያ ላይ እንዴት ማንጠፍጠፍ እንደሚቻል፣ ሥጋው ስለሚታሽበት የጨው ዓይነት እንዲሁም በቀዝቃዛ ውኃ ምን ያህል ጊዜ መታጠብ እንደሚኖርበት ዝርዝር መመሪያዎችን ይጠቅሳል።

d በአብዛኛው፣ በመርፌ በሚሰጡ አንዳንድ መድኃኒቶች ውስጥ ያሉ ዋና ዋና ንጥረ ነገሮች ከደም የተወሰዱ አይደሉም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ አልቡሚንን የመሳሰሉ የደም ክፍልፋዮች በመጠኑ ይጨመሩባቸዋል።—የጥቅምት 1, 1994 መጠበቂያ ግንብየአንባብያን ጥያቄዎች” የሚለውን ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• አምላክ ደምን በሚመለከት ለኖኅ፣ ለእስራኤላውያንና ለክርስቲያኖች ምን መመሪያ ሰጥቶ ነበር?

• ደምን በሚመለከት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ለማድረግ ፈጽሞ ፈቃደኛ አይሆኑም?

• ከዋና ዋና የደም ክፍሎች የወጡ ጥቃቅን ክፍልፋዮችን መውሰድ ለኅሊና የተተወው እንዴት ነው? ይህስ ምን ማለት አይደለም?

• ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ ከአምላክ ጋር ለመሠረትነው ዝምድና የላቀ ቦታ መስጠት የሚገባን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ግራፍ/ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ደምን በተመለከተ ያላቸው መሠረታዊ አቋም

ሙሉ ደም

መወሰድ የሌለባቸው

ቀይ የደም ሕዋሳት

ነጭ የደም ሕዋሳት

አርጊ ሕዋስ ደም (Platelets)

ፕላዝማ (እዥ)

ለኅሊና የተተዉ

ከቀይ የደም ሕዋሳት የሚገኙ ክፍልፋዮች

ከነጭ የደም ሕዋሳት የሚገኙ ክፍልፋዮች

ከአርጊ ሕዋስ ደም የተገኙ ክፍልፋዮች

የፕላዝማ ክፍልፋዮች

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአስተዳደር አካሉ ክርስቲያኖች ‘ከደም መራቅ’ እንደሚገባቸው ወስኗል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የደም ክፍልፋዮችን በሚመለከት ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ ኅሊናህ የሚልህን ስማ