በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በስጦታ ላገኘኸው ሕይወት ትክክለኛ ግምት ይኑርህ

በስጦታ ላገኘኸው ሕይወት ትክክለኛ ግምት ይኑርህ

በስጦታ ላገኘኸው ሕይወት ትክክለኛ ግምት ይኑርህ

“የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ [ያነጻልናል]።”—ዕብራውያን 9:14

1. ለሕይወት ከፍተኛ ግምት እንደምንሰጥ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

 ለሕይወትህ ዋጋ እንድትተምን ብትጠየቅ ምን ያህል ትገምተዋለህ? ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ሕይወት ከፍተኛ ግምት እንሰጣለን። ለመታከም ወይም በየጊዜው የጤና ምርመራ ለማድረግ ሐኪም ቤት መሄዳችን ይህን ያሳያል። ጥሩ ጤንነት ይዘን መኖር እንፈልጋለን። በዕድሜ የገፉ ወይም የአካል ጉዳተኞች እንኳ በሕይወት መኖርን እንጂ ሞትን አይመርጡም።

2, 3. (ሀ) ምሳሌ 23:22 ምን ግዴታ እንዳለብን ይናገራል? (ለ) ምሳሌ 23:22 ላይ የተጠቀሰው ግዴታ አምላክን መታዘዝን የሚጨምረው እንዴት ነው?

2 ለሕይወት ያለህ ግምት ከሌሎች ጋር ያለህን ግንኙነት ይነካል። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ ቃል “የወለደህን አባትህን አድምጥ፤ እናትህንም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” የሚል ትእዛዝ ይዟል። (ምሳሌ 23:22) ‘ማዳመጥ’ ሲባል ቃላትን መስማት ማለት ብቻ አይደለም፤ ጥቅሱ መስማትና ተግባራዊ ማድረግ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። (ዘፀአት 15:26፤ ዘዳግም 7:12፤ 13:18፤ 15:5፤ ኢያሱ 22:2፤ መዝሙር 81:13) የአምላክ ቃል አባትህንና እናትህን እንድታዳምጥ የሚያዝዘው ለምንድን ነው? በዕድሜ ስለሚበልጡህ ወይም የበለጠ ተሞክሮ ስላላቸው ብቻ አይደለም። ‘የወለዱህ’ እነርሱ ስለሆኑ ልትሰማቸው ይገባል። አንዳንድ ትርጉሞች ይህንን ጥቅስ “ሕይወት የሰጠህን አባትህን አድምጥ” በማለት አስቀምጠውታል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ለሕይወትህ ከፍተኛ ግምት የምትሰጥ ከሆነ የሕይወትህ ምንጭ የሆኑትን አባትህንና እናትህን የማክበር ግዴታ እንዳለብህ ይሰማሃል።

3 እውነተኛ ክርስቲያን ከሆንክ ዋነኛው የሕይወትህ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን እንደምትገነዘብ የታወቀ ነው። ‘ሕያው የሆንከው’ እና የስሜት ሕዋሳት ኖሮህ ‘የምትንቀሳቀሰው’ እንዲሁም አሁን ‘የምትኖረውም’ ሆነ የዘላለም ሕይወትን ጨምሮ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰብ ወይም ማቀድ የቻልከው በእርሱ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 17:28 የ1954 ትርጉምመዝሙር 36:9፤ መክብብ 3:11) ከምሳሌ 23:22 ጋር በሚስማማ መንገድ አምላክ ለሕይወት ያለውን አመለካከት የመረዳትና በዚያም የመመራት ፍላጎት በመያዝ እርሱን በታዛዥነት ‘ማዳመጣችን’ ተገቢ ነው። ከዚህ ሌላ ሕይወትን በተመለከተ የሚሰጡ ግምታዊ ሐሳቦችን የመስማት ፍላጎት ሊኖረን አይገባም።

ለሕይወት አክብሮት ይኑርህ

4. በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ ለሕይወት አክብሮት ማሳየት አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑ የታየው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ ሰዎች ሕይወትን እንዳሻቸው እንዲጠቀሙበት ነጻነት እንዳልሰጣቸው በግልጽ ተናግሯል። በቅናት የበገነው ቃየን የገዛ ወንድሙን የአቤልን ሕይወት አጠፋ። ቃየን ሕይወትን በሚመለከት እንዲህ ያለ ውሳኔ የማድረግ መብት የነበረው ይመስልሃል? ይህ የአምላክን አስተሳሰብ የሚቃረን ድርጊት ነው። ቃየንን ጠርቶ “ምንድነው ያደረግኸው? ስማ! የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል” በማለት ተጠያቂ አድርጎታል። (ዘፍጥረት 4:10) በምድር ላይ የፈሰሰው የአቤል ደም በጭካኔ ያለ ዕድሜው የተቀጨውን ሕይወቱን እንደሚወክል እንዲሁም ለበቀል ወደ አምላክ እንደጮኸ ልብ በል።—ዕብራውያን 12:24

5. (ሀ) አምላክ በኖኅ ዘመን ደምን በተመለከተ ምን ትእዛዝ ሰጠ? ትእዛዙስ በማን ላይ ይሠራል? (ለ) ይህ ትእዛዝ ትልቅ እርምጃ ነው የምንለው ከምን አንጻር ነው?

5 ከጥፋት ውኃ በኋላ የሰው ልጅ ታሪክ በአዲስ መልክ የጀመረ ሲሆን በወቅቱ ስምንት ነፍሳት ብቻ ነበሩ። አምላክ ለመላው የሰው ዘር በሰጠው ትእዛዝ አማካኝነት ስለ ሕይወትና ስለ ደም ምን አመለካከት እንዳለው ተጨማሪ መመሪያ ሰጠ። ሰዎች የእንስሳትን ሥጋ መብላት እንደሚችሉ ቢገልጽም ደምን በተመለከተ ግን የሚከተለውን እገዳ ጣለ “ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፤ ለምለሙን ዕፀዋት እንደ ሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ። ነገር ግን ሕይወቱ፣ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ።” (ዘፍጥረት 9:3, 4) አንዳንድ አይሁዳውያን አምላክ ይህን ሲል ሰዎች እንስሳው በሕይወት እያለ ሥጋውን ወይም ደሙን መብላት አይኖርባቸውም ማለቱ ነው ብለው ማብራሪያ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ አምላክ እዚህ ላይ የከለከለው ሰዎች ደምን ለምግብነት እንዳይጠቀሙ እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ግልጽ ሆኗል። ከዚህም በላይ አምላክ በኖኅ በኩል የሰጠው ትእዛዝ ከደም ጋር በተያያዘ ያለውን ታላቅ ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚያስችል ትልቅ እርምጃ ነው። በዚህ ዓላማ አማካኝነት ሰዎች የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።

6. አምላክ ለሕይወት የሚሰጠውን ግምት በኖኅ በኩል የገለጸው እንዴት ነው?

6 አምላክ ቀጥሎ እንዲህ አለ “ሰውን የገደለ ሁሉ ስለሟቹ ደም ተጠያቂ ነው፤ የሟቹን ሰው ደም ከገዳዩ፣ ከእንስሳም ይሁን ከሰው እሻለሁ። የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ፣ ደሙ በሰው እጅ ይፈሳል፤ በእግዚአብሔር አምሳል፣ እግዚአብሔር ሰውን ሠርቶታልና።” (ዘፍጥረት 9:5, 6) አምላክ የሰውን ደም ከሕይወቱ ለይቶ እንደማያየው ለመላው የሰው ዘር ከተሰጠው ከዚህ ሕግ መረዳት ትችላለህ። ፈጣሪ ለግለሰቡ ሕይወትን የሰጠው ሲሆን በደም የሚወከለውን ይህን ሕይወት ማንም ማጥፋት አይኖርበትም። አንድ ሰው ልክ እንደ ቃየን ሕይወት ቢያጠፋ ፈጣሪ የገዳዩን ሕይወት ‘የመጠየቅ’ መብት አለው።

7. አምላክ ደምን በሚመለከት ለኖኅ ለሰጠው ትእዛዝ ትኩረት መስጠት የሚገባን ለምንድን ነው?

7 አምላክ በዚህ ሕግ አማካኝነት ሰዎች ደምን ያለ አግባብ እንዳይጠቀሙ አዟል። አምላክ ይህን ትእዛዝ የሰጠው ለምን እንደሆነ አስበህ ታውቃለህ? ደምን በሚመለከት እንዲህ ያለ አመለካከት የያዘው ለምንድን ነው? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዋና ትምህርቶች መካከል ከአንዱ ጋር የተያያዘ ነው። በርካታ ሃይማኖቶች ችላ ቢሉትም ይህ ትምህርት ለክርስትና እምነት መሠረት ነው። ታዲያ ይህ ትምህርት ምንድን ነው? ሕይወትህን፣ ውሳኔዎችህንና የምትወስዳቸውን እርምጃዎች የሚነካውስ እንዴት ነው?

ደም ለምን ዓላማ ሊውል ይገባል?

8. ይሖዋ በሕጉ ውስጥ ደምን በሚመለከት ምን እገዳ ጥሏል?

8 ይሖዋ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ ሕይወትንና ደምን በሚመለከት ዝርዝር መመሪያዎችን አስፍሯል። በዚህ መንገድ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚያስችል አንድ ተጨማሪ እርምጃ ወስዷል። ሕጉ ለአምላክ የእህል፣ የዘይትና የወይን ቁርባን እንዲቀርብ ያዝዝ እንደነበር ታውቅ ይሆናል። (ዘሌዋውያን 2:1-4፤ 23:13፤ ዘኍልቍ 15:1-5) የእንስሳት መሥዋዕቶችም ይቀርቡ ነበር። አምላክ እነዚህን በሚመለከት እንዲህ ብሏል “የፍጡር ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ በመሠዊያ ላይ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ደሙን ሰጥቻችኋለሁ፤ ለሰውም ሕይወት ስርየት የሚያስገኝ ደም ነው። ስለዚህ እስራኤላውያንን፣ ‘ከእናንተ ማንም ደም አይብላ . . .’ አልሁ።” ይሖዋ አንድ አዳኝ ወይም ገበሬ አድኖ የያዘውን እንስሳ ለመብላት ደሙን ማፍሰስና በአፈር መሸፈን እንደሚኖርበት ጨምሮ ገልጿል። ምድር የአምላክ እግር ማረፊያ ስለሆነች አንድ ሰው የእንስሳውን ደም መሬት ላይ ማፍሰሱ ሕይወት ወደ ሰጪው የሚመለስ መሆኑን እንደሚያምን ያሳያል።—ዘሌዋውያን 17:11-13፤ ኢሳይያስ 66:1

9. በሕጉ መሠረት ደም የሚያገለግለው ለምን ብቻ ነበር? የዚህስ ዓላማ ምን ነበር?

9 ይህ ሕግ ለእኛ ምንም ትርጉም የሌለው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ብቻ አይደለም። እስራኤላውያን ደም መብላት የተከለከሉት ለምን እንደነበር ገብቶሃል? አምላክ “ስለዚህ እስራኤላውያንን፣ ‘ከእናንተ ማንም ደም አይብላ፤ . . .’ አልሁ” ብሎ ነበር። ታዲያ የተከለከሉበት ምክንያት ምን ነበር? “በመሠዊያ ላይ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ደሙን ሰጥቻችኋለሁ።” አምላክ ሰዎች ደም መብላት እንደሌለባቸው ለኖኅ የነገረው ለምን እንደሆነ ከዚህ ሐሳብ ሳትገነዘብ አትቀርም። ፈጣሪ ደምን ለአንድ ልዩ ዓላማ ይኸውም የብዙዎችን ሕይወት ለማዳን ሊጠቀምበት ስለፈለገ ለደም የላቀ ቦታ ሰጥቷል። ደም ኃጢአትን በማስተስረይ ረገድ ጉልህ ሚና እንዲጫወት ዓላማ ነበረው። በመሆኑም ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት ደም ጥቅም ላይ ይውል የነበረው በመሠዊያው ላይ ብቻ ሲሆን ይህም የእርሱን ምሕረት ለሚሹ እስራኤላውያን ኃጢአት ማስተስረያ ሆኖ እንዲያገለግል ነበር።

10. የእንስሳት ደም የተሟላ የኀጢአት ይቅርታ ማስገኘት የማይችለው ለምንድን ነው? ሆኖም በሕጉ ሥር ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች የትኛውን ሐቅ አስገንዝበዋል?

10 ደምን ለኃጢአት ማስተስረያ መጠቀም በክርስትና እምነት ውስጥም ቦታ ነበረው። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ የመለኮታዊው ሕግ ክፍል ስለነበረው ስለዚህ ሥርዓት ሲናገር “ከጥቂት ነገሮች በስተቀር ሁሉም ነገር በደም መንጻት እንዳለበት ሕጉ ያዛል፤ ደም ሳይፈስ ስርየት የለምና” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 9:22) ጳውሎስ ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች እስራኤላውያንን ከኃጢአት አንጽቶ ፍጹማን እንዳላደረጋቸው በግልጽ ተናግሯል። “እነዚህ መሥዋዕቶች በየዓመቱ ኀጢአትን የሚያስታውሱ ናቸው፤ ምክንያቱም የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኀጢአትን ማስወገድ አይችልም” ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 10:1-4) ያም ሆኖ ግን እነዚህ መሥዋዕቶች ዓላማቸውን አከናውነዋል። እስራኤላውያን ኀጢአተኞች መሆናቸውንና ኀጢአታቸው ሙሉ በሙሉ ይቅር እንዲባልላቸው ከዚያ የበለጠ ነገር እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝበዋቸዋል። ይሁን እንጂ የእንስሳትን ሕይወት የሚወክለው ደም የሰዎችን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ማስተስረይ ካልቻለ ይህን ዓላማ ማሳካት የሚችል ደም ይኖር ይሆን?

ሕይወት ሰጪው ያዘጋጀው መፍትሔ

11. መሥዋዕት ሆኖ ይቀርብ የነበረው የእንስሳት ደም ጥላ እንደነበር እንዴት እናውቃለን?

11 ሕጉ የአምላክን ዓላማ በመፈጸም ረገድ ከፍተኛ ቦታ ላለው ነገር ጥላ ነበር። ጳውሎስ “ታዲያ ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው?” በማለት ከጠየቀ በኋላ እንዲህ ሲል መልስ ሰጥቷል “ሕግ የተጨመረው፣ ከመተላለፍ የተነሣ ተስፋው ያመለከተው ዘር እስኪመጣ ድረስ ነበር፤ ሕጉም የመጣው በመላእክት በኩል፣ በአንድ መካከለኛ [በሙሴ] እጅ ነበር።” (ገላትያ 3:19) በተመሳሳይም ጳውሎስ “ሕጉ ወደ ፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው እንጂ፣ እውነተኛው አካል አይደለም” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 10:1

12. አምላክ ደምን በሚመለከት ያለውን ዓላማ ደረጃ በደረጃ የገለጠልን እንዴት ነው?

12 ለማጠቃለል ያህል፣ በኖኅ ዘመን ሰዎች ሕይወታቸውን ለማቆየት የእንስሳ ሥጋ መብላት ተፈቅዶላቸዋል፤ ሆኖም ደም እንዳይበሉ ታዝዘው እንደነበር አስታውስ። ከጊዜ በኋላ አምላክ “የፍጡር ሕይወት በደሙ ውስጥ” መሆኑን ገለጸ። አዎን፣ ደም ሕይወትን ስለሚወክል “በመሠዊያ ላይ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ደሙን ሰጥቻችኋለሁ” በማለት ተናግሯል። ይሁን እንጂ የአምላክን ዓላማ በሚመለከት ወደፊት የሚገለጥ ተጨማሪ ነገር አለ። ሕጉ ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነበር። እነዚህ መልካም ነገሮች ምንድን ናቸው?

13. የኢየሱስ ሞት ከፍተኛ ትርጉም ያዘለው እንዴት ነው?

13 በዕብራውያን 10:1 ላይ የተጠቀሰው እውነተኛው አካል በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ላይ ያተኮረ ነበር። ኢየሱስ ሥቃይ እንደደረሰበትና እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ተቸንክሮ እንደተገደለ ታውቃለህ። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል “ገና ደካሞች ሳለን፣ ልክ ጊዜው ሲደርስ፣ ክርስቶስ ስለ ኀጢአተኞች ሞቶአልና። . . . ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል።” (ሮሜ 5:6, 8) ክርስቶስ ለእኛ በመሞት ኀጢአታችንን ለማስተስረይ ቤዛ አቅርቦልናል። ይህ ቤዛ የክርስትና ትምህርት መሠረት ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16፤ 1 ቆሮንቶስ 15:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:6) ታዲያ ቤዛው ከደምና ከሕይወት ጋር ምን ግንኙነት አለው? የአንተን ሕይወት የሚነካውስ እንዴት ነው?

14, 15. (ሀ) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በኤፌሶን 1:7 ላይ ለኢየሱስ ሞት አጽንኦት የሰጡት እንዴት ነው? (ለ) በኤፌሶን 1:7 ላይ ችላ ተብሎ የታለፈው ነጥብ የትኛው ነው?

14 አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ለኢየሱስ ሞት ከፍተኛ ቦታ ይሰጣሉ፤ ምእመኖቻቸውም “ኢየሱስ ሞቶልኛል” ብለው ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው። እስቲ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ኤፌሶን 1:7ን ምን ብለው እንደተረጎሙት ተመልከት “በእርሱና በሞቱ በኩል ቤዛነታችንን አገኘን፤ ይኸውም የበደላችን ስርየት ነው።” (በፍራንክ ሻይል ባለንታይን የተዘጋጀው ዚ አሜሪካን ባይብል፣ 1902) “በክርስቶስ ሞት ነጻ በመውጣታችን የኃጢአት ይቅርታ አግኝተናል።” (ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን፣ 1966) “ቤዛነታችንን ያገኘነው በክርስቶስ በኩል ብሎም እርሱ ሕይወቱን መሥዋዕት ስላደረገልን ነው፤ ይህም ቤዛ የኃጢአት ስርየት አስገኘልን።” (በዊልያም ባርክሌይ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት፣ 1969) “የኃጢአት ስርየት ያገኘነውና ነጻ የወጣነው በክርስቶስ ሞት አማካኝነት ነው።” (ዘ ትራንስሌተርስ ኒው ቴስታመንት፣ 1973) እነዚህ ትርጉሞች አጽንኦት የሚሰጡት ለኢየሱስ ሞት እንደሆነ መመልከት ትችላለህ። አንዳንዶች ‘የኢየሱስ ሞት በጣም አስፈላጊ ነው። ታዲያ እነዚህ ትርጉሞች ምን ጎደላቸው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል።

15 ያሉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እነዚህ ብቻ ቢሆኑ ኖሮ በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ ነጥብ ሊያመልጥህ ስለሚችል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የሚኖርህ እውቀት የተሟላ አይሆንም ነበር። ኤፌሶን 1:7 በመጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ደም” የሚል ትርጉም ያለው ግሪክኛ ቃል የያዘ ሲሆን ከላይ ያየናቸው ትርጉሞች ግን ይህን ግልጽ አያደርጉትም። በመሆኑም እንደ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ያሉ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሶች ጥቅሱን እንደሚከተለው በማለት ከጥንቱ ጽሑፍ ጋር በሚቀራረብ መንገድ አስቀምጠውታል “በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለ ጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአትን ይቅርታ አገኘን።”

16. “በደሙ” የሚለው ቃል ምን ሊያስታውሰን ይገባል?

16 “በደሙ” የሚለው ቃል ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ በመሆኑ ብዙ ነገሮችን ሊያስታውሰን ይገባል። ከአንድ ሰው ሌላው ቀርቶ ፍጹም ከነበረው ከኢየሱስ ሞት የበለጠ ነገር ያስፈልግ ነበር። ኢየሱስ ሕጉ ጥላ የሆነላቸውን በተለይ ደግሞ በስርየት ቀን ይከናወኑ የነበሩ ነገሮችን ፈጽሟል። በዚያ ልዩ ቀን ሕጉ በሚያዘው መሠረት የእንስሳት መሥዋዕት ይቀርብ ነበር። ከዚያም ሊቀ ካህናቱ በመገናኛው ድንኳን ወይም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ወደሚገኘው ቅድስተ ቅዱሳን ጥቂት ደም ይዞ በመግባት በአምላክ ፊት ያቀርባል። ሊቀ ካህኑ ይህን ማድረጉ በአምላክ ፊት እንደቀረበ ይቆጠር ነበር።—ዘፀአት 25:22፤ ዘሌዋውያን 16:2-19

17. ኢየሱስ የስርየት ቀን ጥላ የሆነለትን ነገር የፈጸመው እንዴት ነው?

17 ጳውሎስ እንደገለጸው ኢየሱስ የስርየት ቀን ጥላ የሆነለትን ነገር ፈጽሟል። በመጀመሪያ በእስራኤል የነበረው ሊቀ ካህናት “ስለ ራሱ ኀጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኀጢአት” የሚያቀርበውን ደም ይዞ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንደሚገባ ገልጿል። (ዕብራውያን 9:6, 7) ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ኢየሱስ መንፈሳዊ አካል ሆኖ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ ሄደ። መንፈሳዊ አካል እንደመሆኑ መጠን “ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት” መቅረብ ችሏል። ታዲያ ለአምላክ ያቀረበው ምን ነበር? በዓይን የሚታይ ሳይሆን ከዚያ ይበልጥ ትርጉም ያለው ነገር ነበር። ጳውሎስ ቀጥሎ እንዲህ አለ ‘ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ የገባው የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ። የውጭ አካላቸው ይነጻ ዘንድ የፍየሎችና የኮርማዎች ደም የሚቀድሳቸው ከሆነ፣ በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!’ አዎን፣ ኢየሱስ የደሙን ዋጋ ለአምላክ አቅርቧል።—ዕብራውያን 9:11-14, 24, 28፤ 10:11-14፤ 1 ጴጥሮስ 3:18

18. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም የሚናገራቸው ሐሳቦች በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች ትልቅ ትርጉም ያላቸው ለምንድን ነው?

18 አምላክ የገለጠው ይህ እውነት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም የሚናገረውን ጥልቅ ትርጉም ያለው እውቀት ይኸውም አምላክ ስለ ደም ምን አመለካከት እንዳለው፣ እኛም ምን አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባና አምላክ ስለ ደም አጠቃቀም የሰጠውን ትእዛዝ መከተል የሚኖርብን ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ያስችለናል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ስታነብ በበርካታ ቦታዎች ላይ ስለ ክርስቶስ ደም የሚናገሩ ሐሳቦችን ታገኛለህ። (ሣጥኑን ተመልከት።) ይህ ደግሞ እያንዳንዱ ክርስቲያን ‘በኢየሱስ ደም’ ማመን እንዳለበት በግልጽ ያሳያል። (ሮሜ 3:25) የኀጢአት ይቅርታ የምናገኘውም ሆነ ከአምላክ ጋር የምንታረቀው ‘በፈሰሰው የኢየሱስ ደም በኩል’ ብቻ ነው። (ቆላስይስ 1:20) ኢየሱስ ከእርሱ ጋር በሰማይ እንዲነግሱ ልዩ ቃል ኪዳን የገባላቸው ከዚህ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው። (ሉቃስ 22:20, 28-30፤ 1 ቆሮንቶስ 11:25፤ ዕብራውያን 13:20) ከመጪው ‘ታላቅ መከራ’ በሕይወት ተርፈው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት ‘እጅግ ብዙ ሰዎችም’ የኀጢአት ይቅርታ የሚያገኙትና ከአምላክ ጋር የሚታረቁት በፈሰሰው በኢየሱስ ደም አማካኝነት ነው። እነዚህ ሰዎች በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል።’—ራእይ 7:9, 14

19, 20. (ሀ) አምላክ በደም አጠቃቀም ላይ ገደብ የጣለው ለምንድን ነው? ይህን በተመለከተስ ምን ሊሰማን ይገባል? (ለ) ስለምን ነገር የማወቅ ፍላጎት ሊያድርብን ይገባል?

19 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ደም በአምላክ ፊት ልዩ ትርጉም አለው። ለእኛም እንዲሁ ሊሆን ይገባዋል። የሕይወት ጉዳይ የሚያሳስበው ፈጣሪ ሰዎች ደምን በሚጠቀሙበት መንገድ ላይ ገደብ የመጣል መብት አለው። ፈጣሪ ስለ ሕይወታችን በእጅጉ ስለሚያስብ ደምን በጣም ጠቃሚ ለሆነ አንድ ዓላማ ሊጠቀምበት ወስኗል። ሰዎች የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው። አምላክ ከደም አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ የኢየሱስን ውድ ደም የሚመለከት ነው። ይሖዋ ደምን ማለትም የኢየሱስን ደም ሕይወታችንን ሊያድን በሚችል መንገድ ጥቅም ላይ በማዋሉ ምንኛ አመስጋኞች ነን! እንዲሁም ኢየሱስ ደሙን ለእኛ መሥዋዕት አድርጎ በማፍሰሱ በእጅጉ ልናመሰግነው ይገባናል! በእርግጥም ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው ያለበትን ምክንያት መረዳት እንችላለን “ለወደደንና ከኀጢአታችንም በደሙ ነጻ ላወጣን፣ አምላኩንና አባቱን እንድናገለግልም መንግሥትና ካህናት ላደረገን፣ ለእርሱ ክብርና ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን! አሜን።”—ራእይ 1:5, 6

20 ለጥበቡ አቻ የሌለው ሕይወት ሰጪ አምላክ በደም አማካኝነት ሕይወት የማዳን የረጅም ጊዜ ዓላማ ነበረው። በመሆኑም ‘ይህ የአምላክ ዓላማ በውሳኔዎቻችንና በድርጊቶቻችን ላይ ምን ተጽእኖ ሊኖረው ይገባል?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ይሆናል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ስለ አቤል እና ስለ ኖኅ ከሚናገሩት ታሪኮች አምላክ ደምን በሚመለከት ስላለው አመለካከት ምን ልንማር እንችላለን?

• አምላክ በሕጉ ውስጥ ደምን በሚመለከት ምን እገዳ ጥሏል? ለምንስ?

• ኢየሱስ የስርየት ቀን ጥላ የሆነለትን ነገር የፈጸመው እንዴት ነበር?

• የኢየሱስ ደም ሊያድነን የሚችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሰዎችን ሕይወት የሚያድነው የማን ደም ነው?

“ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ [“በገዛ ልጁ ደም፣” NW] የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ።”—የሐዋርያት ሥራ 20:28

“አሁን በደሙ ከጸደቅን፣ ይልቁንማ በእርሱ በኩል ከእግዚአብሔር ቁጣ እንዴት አንድንም!”—ሮሜ 5:9

“በዓለም ላይ ያለ ተስፋና ያለ እግዚአብሔር እንደ ነበራችሁ አስታውሱ። አሁን ግን እናንተ ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል።”—ኤፌሶን 2:12, 13

“እግዚአብሔርም ሙላቱ ሁሉ በእርሱ ይሆን ዘንድ ወዶአልና፤ በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን በማድረግ በምድርም ሆነ በሰማይ ያለውን ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል ከራሱ ጋር አስታረቀ።”—ቆላስይስ 1:19, 20

“እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በኢየሱስ ደም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ድፍረት አግኝተናል።”—ዕብራውያን 10:19

“ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ . . . እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው።”—1 ጴጥሮስ 1:18, 19

“እርሱ በብርሃን እንዳለ፣ እኛም በብርሃን ብንመላለስ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል።”—1 ዮሐንስ 1:7

“መጽሐፉን ልትወስድ፣ ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል፤ በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።”—ራእይ 5:9

“የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና። እነርሱም በበጉ ደም፣ በምስክርነታቸውም ቃል፣ ድል ነሡት።”—ራእይ 12:10, 11

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ በሕጉ አማካኝነት ደም የኀጢአትን ይቅርታ ለማስገኘት እንደሚያገለግል በግልጽ አስታውቋል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢየሱስ ደም አማካኝነት ብዙ ሰዎች ይድናሉ