በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አናባፕቲስቶች እነማን ነበሩ?

አናባፕቲስቶች እነማን ነበሩ?

አናባፕቲስቶች እነማን ነበሩ?

በጀርመን፣ ዌስትፋሊያ የምትገኘውን የሙንስተር ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጎበኙ ሰዎች ከተማው መሃል በሚገኘው የቤተ ክርስቲያን ማማ ላይ የተንጠለጠሉትን ሦስት ከሽቦ የተሠሩ ቤቶች ቆመው በአንክሮ ሲመለከቱ ማየት የተለመደ ነው። እነዚህ የሽቦ ቤቶች ከጥቂት ዓመታት በስተቀር ከዚያ ሳይነሱ ወደ 500 የሚጠጉ ዓመታት አስቆጥረዋል። በመጀመሪያ፣ በሕዝብ ፊት ተሰቃይተው የተገደሉ የሦስት ሰዎች አስከሬን ይገኝባቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች አናባፕቲስቶች ሲሆኑ የሽቦ ቤቶቹ ደግሞ የእነርሱ መንግሥት የሚዘከርበት ቅርስ ነው።

አናባፕቲስቶች እነማን ነበሩ? ቡድኑ የተቋቋመው እንዴት ነበር? ዋና ዋናዎቹ ትምህርቶቻቸው ምንድን ናቸው? ሰዎቹ የተገደሉትስ ለምንድን ነው? እንዲሁም ሦስቱ የሽቦ ቤቶች ከመንግሥት ጋር ምን ግንኙነት አላቸው?

ቤተ ክርስቲያኗ ተሐድሶ ያስፈልጋታል—ግን እንዴት?

በ15ኛው መቶ ዘመን መገባደጃና በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና በቀሳውስቱ ላይ የሚሰነዘረው ተቃውሞ እያየለ መጣ። የሥልጣንና የሥነ ምግባር ብልግና በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተንሰራፍቶ ስለነበር ብዙዎች ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተሰማቸው። በ1517 ማርቲን ሉተር ተሐድሶ እንደሚያስፈልግ በይፋ ከገለጸ በኋላ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ሌሎችም ተሰባሰቡና በጥቂት ጊዜ ውስጥ የፕሮቴስታንት የተሐድሶ እንቅስቃሴ ተጀመረ።

ይሁንና ለውጥ አራማጆቹ ምን መደረግ እንዳለበት ወይም ለውጡ ምን ነገሮችን ማካተት እንዳለበት የሚገልጽ ወጥ መመሪያ አልነበራቸውም። አብዛኞቹ አምልኮን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን በጥብቅ መከተል አስፈላጊ እንደሆነ ቢያምኑም ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የሚሰጡት ማብራሪያ ለየቅል ነበር። አንዳንዶቹም የለውጥ ሂደቱ በጣም አዝጋሚ እንደሆነ ተሰማቸው። ከእነዚህ ለውጥ አራማጆች መካከል የተወሰኑት አናባፕቲስት የሚባል ቡድን አቋቋሙ።

ሐንስ ዩርገን ጎርትስ ዲ ቶይፈ—ጌሽኸተ ኡንት ዶይቱንግ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “እንደ እውነቱ ከሆነ በወቅቱ የነበረው የአናባፕቲስት ቡድን አንድ ብቻ ሳይሆን በርካታ ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። ለምሳሌ ያህል በ1521 የዝዊካው ነቢያት የተባሉ አራት ሰዎች ዊትንበርግ ውስጥ የአናባፕቲስትን እምነቶች በመስበካቸው በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ርዕስ ሆነው ነበር። በ1525 ደግሞ በዙሪክ፣ ስዊዘርላንድ ሌላ የአናባፕቲስት ቡድን ተቋቋመ። ከዚህ በተጨማሪ፣ አሁን ቼክ ሪፑብሊክ በምትባለው በቀድሞዋ ሞራቪያ እና በኔዘርላንድ የአናባፕቲስት ቡድኖች ይገኙ ነበር።

መጠመቅ ያለባቸው ሕፃናት ናቸው ወይስ አዋቂዎች?

የአናባፕቲስት ቡድኖች በአብዛኛው ጥቂት አባላት ያቀፉና በጥቅሉ ሲታይ ደግሞ በሰላማዊነታቸው የሚታወቁ ነበሩ። የእምነቱ ተከታዮች እምነታቸውን በምስጢር ከመያዝ ይልቅ ለሌሎች ይሰብኩ ነበር። የአናባፕቲስት ሃይማኖት መሠረታዊ እምነቶች በ1527 በተዘጋጀው የሽላይትሃይም ቀኖና ላይ ሠፍሯል። ከእነዚህም ውስጥ በውትድርና አለመካፈል፣ ከዓለም የተለዩ መሆንና ኃጢአት የሚሠሩ አባላትን ማስወገድ አንዳንዶቹ ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለያቸው ዋናው ነገር መጠመቅ ያለባቸው ሕፃናት ሳይሆኑ አዋቂዎች ናቸው የሚለው ጽኑ እምነታቸው ነበር። a

መጠመቅ ያለባቸው አዋቂዎች ናቸው የሚለው አወዛጋቢ ርዕስ የመሠረተ ትምህርት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከሥልጣን ጋር የተያያዘም ነበር። አንድ ሰው በእምነት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ማድረግ እንዲችል ሙሉ ሰው እስኪሆን ድረስ ሳይጠመቅ የሚቆይ ከሆነ አንዳንዶች ጭራሽ ሳይጠመቁ ሊቀሩ ይችላሉ። ይህም ያልተጠመቁ ሰዎች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከቤተ ክርስቲያን ቁጥጥር ውጪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት፣ መጠመቅ የሚኖርባቸው አዋቂዎች ብቻ ናቸው የሚለው ትምህርት ሥልጣናቸውን እንደሚያዳክምባቸው ተሰማቸው።

ስለዚህ ካቶሊኮችም ሆኑ ሉተራኖች አዋቂዎችን የማጥመቁን ተግባር ማስቆም ፈለጉ። ከ1529 በኋላ ቢያንስ በአንዳንድ አካባቢዎች፣ አዋቂዎችን ያጠመቁ ወይም በዚያ ዕድሜያቸው የተጠመቁ ሰዎች የሞት ቅጣት ሊበየንባቸው ይችል ነበር። ቶማስ ሴይፈርት የተባሉ ጋዜጠኛ አናባፕቲስቶች “የቅዱስ ሮማ ግዛት ክፍል በሆነችው ጀርመን ከባድ ስደት ደርሶባቸው” እንደነበር ገልጸዋል። ከሁሉ የከፋው ስደት የደረሰባቸው ደግሞ በሙንስተር ነበር።

በመካከለኛው ዘመን በነበረችው ሙንስተር የለውጥ ጥያቄ ተነሳ

በመካከለኛው ዘመን ሙንስተር ወደ 10,000 አካባቢ ነዋሪዎች የነበሯት ሲሆን 90 ሜትር ገደማ ስፋትና ዙሪያውን 5 ኪሎ ሜትር በሚያህል ፈጽሞ በማይደፈር ምሽግ የታጠረች ነበረች። ይሁን እንጂ በከተማዋ ውስጥ የነበረው ሁኔታ በዙሪያዋ እንዳለው ምሽግ አስተማማኝ አልነበረም። የሙንስተር ከተማ ሙዚየም ያሳተመው ዘ ኪንግደም ኦቭ አናባፕቲስትስ የተባለው ጽሑፍ “በከተማዋ አስተዳዳሪዎችና በሞያ ማኅበራት መካከል የፖለቲካ ቅራኔ” እንደነበር ጠቅሷል። ከዚህ በተጨማሪ የከተማዋ ነዋሪዎች የቀሳውስቱ ሥነ ምግባር አበሳጭቷቸው ነበር። ሙንስተር ተሐድሶውን ተቀበለች፤ ከዚህም በላይ በ1533 የካቶሊኮች ይዞታ መሆኗ አብቅቶ የሉተራኖች ከተማ ሆነች።

በችኩልነቱ የሚታወቀው ቤርሃርት ሮትማን በሙንስተር ከነበሩት ዋና ዋና የለውጥ አቀንቃኞች መካከል አንዱ ነበር። ደራሲው ፍሬድሪኸ ኦኒንገ፣ የሮትማን “አመለካከት ከአናባፕቲስቶች የተለየ አልነበረም፤ እርሱና ተባባሪዎቹ ሕፃናትን ለማጥመቅ ፈቃደኞች አልነበሩም” ሲሉ ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ ከሚያውቀው የተለየ አመለካከት መያዙ በአንዳንዶች ዘንድ እንደ ጽንፈኛ ቢያስቆጥረውም እንኳ በሙንስተር በርካታ ደጋፊዎች አግኝቷል። “የቀድሞው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ደጋፊ የሆኑ ብዙ ሰዎች ሊከተል የሚችለው ሁኔታ ጭንቀትና ስጋት ስላሳደረባቸው አንድ በአንድ ከተማዋን ለቅቀው ወጡ። አናባፕቲስቶች፣ የሚያምኑባቸው ትምህርቶች በተግባር ሲውሉ ለማየት ተስፋ በማድረግ ከተለያዩ አገሮች ወደ ሙንስተር ጎረፉ።” የእነርሱን በሙንስተር መሰባሰብ ተከትሎ አንድ አሰቃቂ ሁኔታ ተከሰተ።

አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ተከበበች

ወደ ሙንስተር የመጡ ሁለት ደቾች ማለትም ያን ማቲስ የተባለው ከሃርሌም የመጣ ዳቦ ጋጋሪና የላይደኑ ጆን በመባል የሚታወቀው ያን ቢውከልሰን ከጊዜ በኋላ በከተማዋ በሚካሄዱት እንቅስቃሴዎች ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል። ማቲስ ራሱን ነቢይ ብሎ የሰየመ ከመሆኑም ሌላ ሚያዝያ 1534 የክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እንደሚሆን ተናገረ። ከተማዋ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም እንደሆነች ተገለጸ፤ ሕዝቡም የዓለምን መጨረሻ ይጠባበቅ ጀመር። ሮትማን ማንኛውም ንብረት የጋራ ሀብት እንዲሆን ደነገገ። የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ አዋቂዎች በፈቃደኝነት የመጠመቅ አሊያም ከተማዋን ለቅቆ የመውጣት ምርጫ ተሰጣቸው። በጅምላ ከተጠመቁት መካከል አንዳንዶቹ እንዲህ ያደረጉት ቤት ንብረታቸውን ትተው ላለመሄድ ሲሉ ብቻ ነበር።

በሌሎች ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች አናባፕቲስቶች በሙንስተር ሃይማኖታዊም ሆነ ፖለቲካዊ የበላይነት ማግኘታቸውን ሲያዩ ከፍተኛ ስጋት አደረባቸው። በጀርመንኛ የተዘጋጀው የሙንስተር መጥምቃውያን የተባለው መጽሐፍ ይህ ሁኔታ “የቅዱስ ሮማ ግዛት ክፍል በሆነችው ጀርመን ሙንስተር በጠላትነት እንድትፈረጅ” አድርጓታል ሲል ገልጿል። በአካባቢው ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ልዑልና ሊቀ ጳጳስ ካውንት ፍራንትስ ፎን ቫልዴክ ሙንስተርን ለመክበብ ከሉተራኖችና ከካቶሊኮች የተውጣጣ ግዙፍ ጦር ሠራዊት አደራጁ። ከዚህ ቀደም ከተሐድሶው ጋር በተያያዘ ባላንጣዎች የነበሩትና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ በሠላሳው ዓመት ጦርነት እርስ በርስ የሚፋጁት እነዚህ ሁለት ሃይማኖቶች በአናባፕቲስቶች ላይ ግንባር ፈጥረው ተነሱ።

የአናባፕቲስቶች መንግሥት ተደመሰሰ

ነዋሪዎቹ በከተማዋ ግንብ መታመናቸው የወራሪውን ሠራዊት ጥንካሬ አቅልለው እንዲመለከቱ አደረጋቸው። ክርስቶስ ዳግመኛ ይመጣል በተባለበት በሚያዝያ 1534 ማቲስ መለኮታዊ ጥበቃ አገኛለሁ በሚል ስሜት ነጭ ፈረስ እየጋለበ ከከተማዋ ወጣ። የከተማዋ ግንብ ላይ ሆነው ሁኔታውን ይከታተሉ የነበሩት የማቲስ ደጋፊዎች ከተማዋን የከበቧት ወታደሮች ማቲስን ከቆራረጡ በኋላ ጭንቅላቱን እንጨት ላይ ሰክተው ወደ ላይ ሲያነሱት በተመለከቱ ጊዜ ምን ያህል ተደናግጠው እንደሚሆን አስብ።

በማቲስ ቦታ የላይደኑ ጆን የተተካ ሲሆን ንጉሥ ያን የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት በሙንስተር የሚኖሩ አናባፕቲስቶች መሪ ሆነ። በከተማይቱ ውስጥ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ይበዙ ስለነበር ልዩነቱን ለማጥበብ ወንዶች ያሻቸውን ያህል ብዙ ሚስቶች እንዲያገቡ ያበረታታ ጀመር። በአንድ በኩል ዝሙትና ምንዝር በሞት ሲያስቀጡ በሌላ በኩል ደግሞ ከአንድ በላይ ማግባት የሚቻል አልፎ ተርፎም የሚበረታታ መሆኑ በሙንስተር የነበረው የአናባፕቲስቶች መንግሥት እርስ በርሱ የሚቃረን መርህ እንደነበረው ያሳያል። ንጉሥ ያንን ከወሰድን 16 ሚስቶች ነበሩት። ከእነርሱ አንዷ የሆነችው ኤልዛቤት ቫንትሼረ ከከተማዋ ለመውጣት ፈቃድ ስለጠየቀችው በአደባባይ ተሰይፋለች።

ከበባው ለ14 ወራት የዘለቀ ሲሆን በመጨረሻም ሰኔ 1535 ከተማዋ ተያዘች። ሙንስተር ከዚያ በኋላ የዚያን ያህል አስከፊ ጥፋት የደረሰባት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብቻ ነው። ሮትማን ተሳክቶለት አመለጠ፤ ንጉሥ ያንና ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ሌሎች ሁለት አናባፕቲስቶች ግን ተይዘው ከባድ ሥቃይ ከደረሰባቸው በኋላ ተገደሉ። አስከሬናቸውን ከሽቦ በተሠራ ቤት ውስጥ አስቀምጠው የቅዱስ ላምበርት ቤተ ክርስቲያን ማማ ላይ አንጠለጠሉት። ሴይፈርት ይህ ቅጣት “ዓመጽ ለመቆስቆስ ለሚከጅሉ ሁሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እንዲሆናቸው ተብሎ የተደረገ” ነበር ሲሉ ገልጸዋል። አዎን፣ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባት ከባድ መዘዝ አስከትሎባቸዋል።

የሌሎች የአናባፕቲስት ቡድኖች መጨረሻስ ምን ሆነ? ስደቱ በመላው አውሮፓ ለበርካታ ዓመታት ቀጠለ። አብዛኞቹ አናባፕቲስቶች በውትድርና ረገድ ገለልተኛ አቋማቸውን ይዘው የቀጠሉ ቢሆንም ጦርነት ቆስቋሽ የሆኑ ጥቂቶች አልታጡም። በፊት ቄስ የነበረው ሜኖ ሲመንስ ከጊዜ በኋላ የአናባፕቲስቶች መሪ ሆነ፤ ቀስ በቀስም ቡድኑ ሜኖናይት በሚለው ስያሜ ወይም በሌሎች ስሞች ይጠራ ጀመር።

ሦስቱ የሽቦ ቤቶች

በመሠረቱ አናባፕቲስቶች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ ለመከተል ይጥሩ የነበሩ የሃይማኖት ሰዎች ናቸው። ሆኖም በሙንስተር የነበሩ አንዳንድ ጽንፈኞች አናባፕቲስቶች ይህን አቋማቸውን ትተው ፖለቲካ ውስጥ እንዲገቡ አደረጓቸው። ከዚህ በኋላ ቡድኑ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ። ይህም በአናባፕቲስቶችም ሆነ በመካከለኛው ዘመን በነበረችው በሙንስተር ላይ ጥፋት አስከተለ።

ከተማዋን የሚጎበኙ ሰዎች የቤተ ክርስቲያኑ ማማ ላይ የተሰቀሉትን ሦስት የሽቦ ቤቶች ሲያዩ ከ500 ዓመታት ገደማ በፊት የተፈጸመውን ይህን አሰቃቂ ሁኔታ ማስታወሳቸው አይቀርም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዚህ ርዕስ ላይ ሕፃናት መጠመቅ አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚለው ጉዳይ አይብራራም። በዚህ ረገድ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በመጋቢት 15, 1986 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ሕፃናትን ማጥመቅ ተገቢ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሥ ያንን አሰቃይተው ከገደሉት በኋላ በቅዱስ ላምበርት ቤተ ክርስቲያን ማማ ላይ ሰቀሉት