በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጊልያድ ተመራቂዎች በመከሩ ሥራ በቅንዓት እንዲያገለግሉ ተላኩ!

የጊልያድ ተመራቂዎች በመከሩ ሥራ በቅንዓት እንዲያገለግሉ ተላኩ!

የጊልያድ ተመራቂዎች በመከሩ ሥራ በቅንዓት እንዲያገለግሉ ተላኩ!

“መከሩ ብዙ ነው፤ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ፣ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት።” (ማቴዎስ 9:37, 38) እነዚህ ቃላት በሚስዮናዊነት ወደ ተመደቡባቸው አገሮች ለመሄድ በዝግጅት ላይ ለነበሩት ለጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 116ኛ ክፍል ተመራቂዎች ልዩ ትርጉም ነበራቸው።

ቅዳሜ መጋቢት 13, 2004 በፓተርሰን ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል እና ሥነ ሥርዓቱ በሳተላይት አማካኝነት በቴሌቪዥን በተላለፈባቸው ቦታዎች በአጠቃላይ 6,684 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ፕሮግራሙን የተከታተሉ ሲሆን በዚያ ዕለት ተመራቂዎቹ የመሰናበቻ ማሳሰቢያና ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። በመንፈሳዊ የመከር ሥራ በቅንዓት የምንካፈል ሁላችን ከዚህ ምክር ጥቅም ማግኘታችን አይቀርም።

የጊልያድ ትምህርት ቤት ሰባተኛ ክፍል ተመራቂ የነበረውና የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ወንድም ቴዎዶር ጃራዝ ያቀረበው የመክፈቻ ንግግር “ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት የሚያጎላ ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) ተመራቂዎቹ ወደ 20 አገሮች ስለሚሄዱ ያቀረበው ንግግር በእርግጥም ተስማሚ ነበር! ወንድም ጃራዝ ከአምላክ ቃል ያገኙት ትምህርት እጅግ አስፈላጊ በሆነው መንፈሳዊ የመከር ሥራ በቅንዓት እንዲካፈሉ በሚገባ እንዳስታጠቃቸው ለተማሪዎቹ ገልጾላቸዋል።—ማቴዎስ 5:16

ውጤታማ የመከር ሠራተኞች መሆን የሚቻልበት መንገድ

በፕሮግራሙ ላይ የመጀመሪያውን ንግግር ያቀረበው ለበርካታ ዓመታት ከጊልያድ ትምህርት ቤት ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበረው ሮበርት ዎለን ነበር። “ርኅራኄ—በዓይነቱ ልዩ የሆነ ባሕርይ” የሚል ጭብጥ ባለው ንግግሩ ላይ “ርኅራኄ፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ሊሰሙት ማየት የተሳናቸው ደግሞ ሊያዩት የሚችሉት ቋንቋ ነው” በማለት ለተማሪዎቹ ተናግሯል። ኢየሱስ የሰዎችን ጭንቀት በሚገባ ይረዳ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሊያጽናናቸው ይፈልግ ነበር። (ማቴዎስ 9:36) ተማሪዎቹም በስብከቱ ሥራ ላይ፣ በጉባኤ ውስጥ፣ በሚስዮናውያን ቤትና በትዳራቸው ውስጥ ይህን ባሕርይ ማሳየት የሚችሉባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ተናጋሪው እንዲህ በማለት አሳስቧቸዋል:- “ሌሎችን በምታገለግሉበት ጊዜ ማራኪ የሆነውን ርኅራኄን አንጸባርቁ። ጥሩ ባሕርይ ካላችሁ በሚስዮናውያን ቤት ውስጥ ከሌሎች ጋር ተግባብታችሁ መኖር አያቅታችሁም። በመሆኑም ርኅራኄን ለመልበስ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።”—ቆላስይስ 3:12

ቀጥሎ የጊልያድ ትምህርት ቤት 41ኛ ክፍል ምሩቅና አሁን የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጌሪት ሎሽ “የመዳን መልእክት አዋጅ ነጋሪዎች” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። (ኢሳይያስ 52:7) ሰዎች ይህ ሥርዓት ከሚደርስበት ጥፋት በሕይወት ለመትረፍ ከአምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት መቅሰም፣ ስለሚያምኑበት ነገር ለሌሎች መስበክና መጠመቅ ይኖርባቸዋል። (ሮሜ 10:10፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:15፤ 1 ጴጥሮስ 3:21) ይሁን እንጂ የመዳንን መልእክት የምንሰብክበት ዋነኛው ምክንያት ሰዎችን ለማዳን ሳይሆን ለአምላክ ክብር ለማምጣት ነው። በመሆኑም ወንድም ሎሽ እጩ ሚስዮናውያንን እንዲህ በማለት አሳሰባቸው:- “የመንግሥቱን ምሥራች እስከ ምድር ዳር ድረስ አዳርሱ፤ የመዳንን መልእክት በቅንዓት አውጁ፤ ማንኛውንም ነገር ለይሖዋ ክብር አድርጉ።”—ሮሜ 10:18

ወንድም ሎውረንስ ቦወን ያቀረበው ንግግር “መንፈሳዊ ብርሃን የምታንጸባርቁት ምን ያህል ነው?” የሚል ጥያቄ አዘል ርዕስ ነበረው። ወንድም ቦወን በማቴዎስ 6:22 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት ጠቅሶ ተመራቂዎቹ “ይሖዋን የሚያስከብርና ሰዎችን የሚጠቅም መንፈሳዊ ብርሃን ማንጸባረቅ” እንዲችሉ “ጤናማ” ዓይን እንዲኖራቸው አበረታታቸው። በዚህ ረገድ ኢየሱስ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ብቻ በማተኮር ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት አባቱ ባስተማረው ድንቅ ነገሮች ላይ ማሰላሰሉ በምድረ በዳ አጋጥሞት የነበረውን የሰይጣን ዲያብሎስን ፈተና በጽናት እንዲያልፍ ረድቶታል። (ማቴዎስ 3:16፤ 4:1-11) ኢየሱስ፣ ይሖዋ የሰጠውን ተልእኮ ከዳር ለማድረስ ሙሉ በሙሉ በእርሱ እንደሚተማመን አሳይቷል። በተመሳሳይም፣ ሚስዮናውያኑ ወደፊት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ለመቋቋም መጽሐፍ ቅዱስ የማጥናት ጥሩ ልማድ ማዳበራቸውንና ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መተማመናቸውን መቀጠል ይገባቸዋል።

በተከታታይ ከቀረቡት ንግግሮች መካከል የመጨረሻውን ያቀረበው የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪና የ77ኛው ክፍል ምሩቅ የሆነው ማርክ ኑሜር ሲሆን ንግግሩ “እነሆ በእጅህ ውስጥ ነን” የሚል ጭብጥ ነበረው። (ኢያሱ 9:25) ወንድም ኑሜር የጥንት ገባዖናውያን ያሳዩትን ዝንባሌ እንዲኮርጁ ተማሪዎቹን አበረታታቸው። ገባዖን “ታላቅ ከተማ . . . ሰዎቿም ብርቱ ተዋጊዎች” ቢሆኑም ገባዖናውያን የተለየ ክብር እንዲሰጣቸው አልፈለጉም ወይም ነገሮች እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዲከናወኑ አልጠየቁም። (ኢያሱ 10:2) ከዚህ ይልቅ የይሖዋን አምልኮ ለመደገፍ በሌዋውያን ሥር ሆነው “ዕንጨት ቆራጮችና ውሃ ቀጂዎች” በመሆን በፈቃደኝነት አገልግለዋል። (ኢያሱ 9:27) ተመራቂዎቹም ለታላቁ ኢያሱ ለኢየሱስ ክርስቶስ “እነሆ፤ . . . በእጅህ ውስጥ ነን” ብለው የተናገሩ ያህል ነው። በባዕድ አገር አገልግሎታቸውን በሚጀምሩበት ጊዜ ታላቁ ኢያሱ የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ሥራ መቀበል ይኖርባቸዋል።

ተሞክሮዎችና ቃለ ምልልሶች

“ቅዱሳት መጻሕፍትን ገልጣችሁ አስረዱ” በሚል ጭብጥ ከተወሰኑ ተማሪዎች ጋር የተደረገውን ውይይት የመራው ደግሞ የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪና የ61ኛው ክፍል ምሩቅ የሆነው ዋላስ ሊቨረንስ ነበር። ተማሪዎቹ በትምህርት ላይ በቆዩባቸው ወራት በመስክ አገልግሎት ሲካፈሉ ያገኟቸውን ተሞክሮዎች የተናገሩ ሲሆን አንዳንድ ተሞክሮዎችንም በሠርቶ ማሳያ አቅርበዋል። ተማሪዎቹ ሥልጠናውን በወሰዱባቸው አምስት ወራት ውስጥ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ባደረጉት ጥልቅ ጥናት ልባቸው እንደተነካና የተማሩትን ለሌሎች ለማካፈል እንደተገፋፉ ግልጽ ነው። (ሉቃስ 24:32) በእነዚህ ወራት አንድ ተማሪ ከትምህርት ቤቱ የሚያገኘውን ትምህርት ለሥጋ ወንድሙ ያካፍል ነበር። ይህም ወንድምየው በአካባቢው ስብሰባ የሚደረግበትን ቦታ ፈልጎ እንዲያገኝና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር አነሳስቶታል። በአሁኑ ጊዜ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

እነዚህ ተሞክሮዎች ከቀረቡ በኋላ ሪቻርድ አሽ እና ጆን ጊበርድ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን ጨምሮ ይሖዋን ለረጅም ዓመታት በታማኝነት ካገለገሉ ወንድሞች ጋር ቃለ ምልልስ አደረጉ። እነዚህ ወንድሞች በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ልዩ ሥልጠና በመውሰድ ላይ የነበሩ ሲሆን በአንድ ወቅት በጊልያድ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነበሩ። አንደኛው ወንድም በጊልያድ ትምህርት ቤት ሳለ ወንድም ኖር እንደሚከተለው ሲል የተናገረውን አስታውሷል:- “በጊልያድ ትምህርት ቤት ብዙ እውቀት ትቀስማላችሁ። ይሁንና፣ ባገኛችሁት እውቀት መኩራራት የምትጀምሩ ከሆነ ከሰርን ማለት ነው። አፍቃሪ ልብ ይዛችሁ እንድትሄዱ እንፈልጋለን።” በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት የሚያገለግሉት ወንድሞች ተማሪዎቹ ለሰዎች አሳቢ እንዲሆኑ፣ ሌሎችን ኢየሱስ በያዘበት መንገድ እንዲይዙና የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ኃላፊነት በትሕትና እንዲቀበሉ ምክር ለግሰዋል። አዲሶቹ ሚስዮናውያን ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው አያጠራጥርም።

በመከሩ ሥራ በቅንዓት ተካፈሉ!

ከዚያም የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ስቲቨን ሌት የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን ዋነኛ ንግግር ያቀረበ ሲሆን ርዕሱ “በመከሩ ሥራ በቅንዓት ተካፈሉ!” የሚል ነበር። (ማቴዎስ 9:38) ገበሬዎች እህላቸውን የሚሰበስቡበት የመከር ወቅት በጣም አጭር ነው። በመሆኑም በመከር ወቅት ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በተመሳሳይ የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በተቃረበበት በዚህ ወቅት ተግቶ መሥራቱ ይበልጥ አስፈላጊ ነው! ታላቁ መንፈሳዊ የመከር ሥራ የሰዎችን ሕይወት ከጥፋት በማዳን ላይ ያተኩራል። (ማቴዎስ 13:39) ወንድም ሌት ተመራቂዎቹ እንደገና በማይደገመው በዚህ የመከር ሥራ ‘ከመትጋት እንዳይለግሙ’ ከዚህ ይልቅ ‘በመንፈስ የጋሉ’ እንዲሆኑና ለይሖዋ እንዲገዙ አበረታቷቸዋል። (ሮሜ 12:11) ተናጋሪው “አዝመራው ለመከር እንደ ደረሰ ቀና ብላችሁ ማሳውን ተመልከቱ” የሚሉትን የኢየሱስን ቃላት ጠቀሰ። (ዮሐንስ 4:35) ከዚያም ተመራቂዎቹ ሰዎችን በሚገኙበት ጊዜና ቦታ ቀርበው ለማነጋገር ልባዊ ጥረት በማድረግና መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሏቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ በሚገባ በመጠቀም በመከሩ ሥራ ላይ በቅንዓት መካፈላቸውን እንዲቀጥሉ አበረታታ። አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ንቁ መሆን ውጤታማ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችላል። ይሖዋ ቀናተኛ አምላክ ነው፤ ሁላችንም የእርሱን ምሳሌ እንድንኮርጅና በመንፈሳዊ የመከር ሥራ በትጋት እንድንካፈል ይፈልጋል።—2 ነገሥት 19:31፤ ዮሐንስ 5:17

የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር፣ ወንድም ጃራዝ በምረቃው ሥነ ሥርዓት መደምደሚያ ላይ ከተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የተላኩ ሰላምታዎችን ካነበበ በኋላ ለተመራቂዎቹ ዲፕሎማቸውን ሰጠ። ከዚያም አንድ ተማሪ ክፍሉን በመወከል ላገኙት ሥልጠና የተሰማቸውን ከፍተኛ አድናቆት የሚገልጽ ደብዳቤ አነበበ። የ116ኛው ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት በዚያ የተገኙትን ሁሉ በመከሩ ሥራ በቅንዓት መካፈላቸውን እንዲቀጥሉ ይበልጥ እንዳበረታታቸው ግልጽ ነው።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ

የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 6

የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 20

የተማሪዎቹ ብዛት:- 46

አማካይ ዕድሜ:- 34.2

በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 17.2

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 13.9

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 116ኛ ክፍል ተመራቂዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) ሲዮንሱ ሬቸል፣ ስፓርክስ ቴማር፣ ፒንያ ክሎውዲያ፣ ተርነር ፕሮደጂ፣ ቼኒ ሊሳ፤ (2) ስዋርዲ መሪያ፣ ሾክዊስት ኦሳ፣ አማዶሪ ሊዲያ፣ ስሚዝ ናታሸ፣ ጆርዳን ኤሚ፣ ቧሳኖ ሊን፤ (3) ማትሎክ ጄይሚ፣ ሩኢት ካርመን፣ ዱላር ሎሊ፣ ቪኜሮ ማሪኤሌን፣ ሄንሪ ኪም፤ (4) ሾክዊስት ሃንስ፣ ሎክስ ጄኒፈር፣ ሩዞ ጄሲከ፣ ጉስታፍሰን ካታሪና፣ ቧሳኖ ሮበርት፣ ጆርዳን ማርክ፤ (5) ሄንሪ ዳረል፣ ተርነር ድዌይን፣ ከርዊን ስቴሲ፣ ፍሎሪት ኬቲ፣ ሲዮንሱ ሳሻ፤ (6) አማዶሪ ሴርዥ፣ ቼኒ ጆን፣ ሮዝ ሬቤካ፣ ኔልሰን ጄኒፈር፣ ሩኢት ሃዋኪን፣ ቪኜሮ ሚካኤል፤ (7) ፍሎሪት ሃዋን፣ ማትሎክ ዳረን፣ ሮዝ ብሩስ፣ ሎክስ ክሊፍ፣ ሩዞ ቶማስ፣ ዱላር ዳን፣ ከርዊን ናት፤ (8) ጉስታፍሰን አረን፣ ኔልሰን ዴቪድ፣ ስዋርዲ ዋልተር፣ ፒንያ ሚካኤል፣ ስሚዝ ክሬግ፣ ስፓርክስ ቶም።