በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ”

“በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ”

“በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ”

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ክርስቲያን ሚስዮናውያን የነበሩት ጳውሎስ፣ በርናባስና ዮሐንስ ማርቆስ በ47 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ቆጵሮስን በጎበኙበት ወቅት ስላጋጠማቸው ተሞክሮ የሚናገረውን ዘገባ የሚጀምረው በእነዚህ ቃላት ነው። (የሐዋርያት ሥራ 13:4) እንደዛሬው ሁሉ የዚያን ጊዜም ቆጵሮስ በምሥራቃዊው የሜዲትራኒያን ክፍል ቁልፍ ቦታ ነበራት።

ደሴቲቱን ለረጅም ጊዜ ይመኟት የነበሩት ሮማውያን በ58 ከክርስቶስ ልደት በፊት በቁጥጥራቸው ሥር አድርገዋት ነበር። ከዚያ በፊት ቆጵሮስ ብዙ ታሪክ ያሳለፈች ሲሆን ፊንቄያውያን፣ ግሪካውያን፣ አሦራውያን፣ ፋርሳውያንና ግብጾች በየተራ ተቆጣጥረዋታል። በመካከለኛው ዘመን ደግሞ የመስቀል ዘማቾች፣ ፍራንካውያን፣ ቬኒሺያኖችና እነርሱን ተከትለው የመጡት የኦቶማን ቱርኮች ገዝተዋታል። በ1914 እንግሊዞች ከግዛታቸው የቀላቀሏት ሲሆን ነጻነቷን እስካገኘችበት እስከ 1960 ድረስ በእነርሱ ስትተዳደር ቆይታለች።

በአሁኑ ወቅት የደሴቲቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ቱሪዝም ነው። በጳውሎስ ዘመን ግን በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች የነበረች ሲሆን ሮማውያኑ ይህን ሃብቷን እየበዘበዙ ወደ ሮም አግዘውታል። ደሴቲቱ የመዳብ ማዕድን እንዳላት የታወቀው ነዋሪዎች ከሰፈሩባት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር። በሮማውያን አገዛዝ ማብቂያ ገደማ 250,000 ቶን የሚያህል መዳብ ተቆፍሮ እንደወጣ ይገመታል። ይሁን እንጂ ይህንን መዳብ ለማቅለጥ ሲባል ጥቅጥቅ ካለው የደሴቲቷ ደን አብዛኛው ተመንጥሯል። በመሆኑም ጳውሎስ ወደ ደሴቲቱ በመጣበት ወቅት አብዛኛው የደን ሀብቷ ተመናምኖ ነበር።

ቆጵሮስ በሮም አገዛዝ ሥር

በኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ላይ የሰፈረው ዘገባ እንደሚለው መጀመሪያ ጁሊየስ ቄሳር ቆየት ብሎ ደግሞ ማርክ አንቶኒ ቆጵሮስን ለግብጽ አሳልፈው ሰጧት። ይሁን እንጂ በአውግስጦስ የግዛት ዘመን ደሴቲቱ ለሮም የተመለሰች ሲሆን የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጸሐፊ የነበረው ሉቃስ በትክክል እንደዘገበው ተጠሪነቱ ለሮም መንግሥት በሆነ አገረ ገዥ ትተዳደር ነበር። ጳውሎስ በደሴቲቱ ላይ ምሥራቹን በሰበከበት ወቅት አገረ ገዢ የነበረው ሰርግዮስ ጳውሎስ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 13:7

በሮማውያኑ አገዛዝ ወቅት የሰፈነው ፓክስ ሮማና ተብሎ የሚጠራው ዓለም አቀፋዊ ሰላም የቆጵሮስ የማዕድን ማውጫዎችና ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉና የንግዱ እንቅስቃሴ እንዲደራ አድርጓል። እንዲሁም በደሴቲቱ ከሰፈሩት የሮም ወታደሮችና የደሴቲቱ ጠባቂ የነበረችውን እንስት አምላክ አፍሮዳይትን ለመሳለም ከሚመጡት ሰዎች ተጨማሪ ገቢ ይገኝ ነበር። በዚህም የተነሳ አዳዲስ መንገዶች፣ ወደቦችና ያሸበረቁ ሕንጻዎች ተገንብተዋል። ግሪክኛ ዋነኛ መግባቢያ ቋንቋ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን ከሮማው ንጉሠ ነገሥት በተጨማሪ አፍሮዳይት፣ አፖሎ እና ዚየስ በሰፊው ይመለኩ ነበር። የተለያየ ዓይነት ማኅበራዊና ባሕላዊ የአኗኗር ዘይቤ የነበራቸው የደሴቲቱ ነዋሪዎችም የቅንጦት ኑሮ ይኖሩ ነበር።

ጳውሎስ ለሰዎች ስለ ክርስቶስ ለማስተማር በቆጵሮስ ባለፈበት ወቅት በደሴቲቱ የነበረው ሁኔታ ይህን ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ ክርስትና ጳውሎስ ከመምጣቱም በፊት በደሴቲቱ ተሰብኮ ነበር። የሐዋርያት ሥራ ዘገባ የመጀመሪያው ክርስቲያን ሰማዕት እስጢፋኖስ ከተገደለ በኋላ አንዳንድ ክርስቲያኖች ወደ ቆጵሮስ መሰደዳቸውን ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 11:19) የጳውሎስ የአገልግሎት ጓደኛ የነበረው በርናባስ የቆጵሮስ ተወላጅ እንደመሆኑ የደሴቲቱን መውጫ መግቢያ ስለሚያውቅ በስብከት ጉዞው ወቅት ለጳውሎስ ጥሩ አቅጣጫ መሪ ሆኖለት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።—የሐዋርያት ሥራ 4:36፤ 13:2

ጳውሎስ የተጓዘባቸው መንገዶች

ጳውሎስ በቆጵሮስ በነበረበት ወቅት የተጓዘባቸውን መንገዶች መገመት ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ አርኪኦሎጂስቶች በሮም አገዛዝ ወቅት ያገለግሉ ስለነበሩት ግሩም መንገዶች ደህና ግንዛቤ አግኝተዋል። በደሴቲቱ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ ዛሬ ያሉት ዘመናዊ አውራ ጎዳናዎች እንኳ የጥንቶቹ ሚስዮናውያን የተጓዙባቸውን መንገዶች ተከትለው የተሠሩ ናቸው።

መጀመሪያ ጳውሎስ፣ በርናባስና ዮሐንስ ማርቆስ በመርከብ ከሴሌውቅያ ተነስተው ወደ ስልማና ወደብ ደረሱ። የቆጵሮስ ዋና ከተማና ትልቁ ወደብ ጳፉ ሆኖ ሳለ እነ ጳውሎስ ወደ ስልማና የሄዱት ለምን ነበር? አንደኛው ምክንያት በደሴቲቱ ምሥራቃዊ ጠረፍ ያለችው ስልማና በዋናው አህጉር ከምትገኘው ከሴሌውቅያ ያላት ርቀት ከ200 ኪሎ ሜትር የማይበልጥ መሆኑ ነው። ምንም እንኳን በሮማ አገዛዝ ወቅት ስልማና ዋና ከተማ መሆኗ ቀርቶ በጳፉ ብትተካም የደሴቲቷ የባሕል፣ የትምህርትና የንግድ ማዕከል ሆና ቀጥላ ነበር። በስልማና ጥቂት የማይባሉ አይሁዳውያን ይኖሩ ስለነበር ሚስዮናውያኑ “በአይሁድ ምኩራቦች የእግዚአብሔርን ቃል [ሰብከዋል]።”—የሐዋርያት ሥራ 13:5

ዛሬ ከስልማና የቀረ ነገር ቢኖር የፍርስራሽ ክምር ብቻ ነው። ቢሆንም አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች ከተማዋ ጥንት የነበራትን ክብርና ሀብት ይመሰክራሉ። የፖለቲካና የሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ማዕከል የነበረው የገበያ ቦታዋ ምናልባት በሜዲትራኒያን አካባቢ በቁፋሮ ከተገኙት የሮማውያን የመገበያያ ሥፍራዎች ሁሉ ትልቁ ሳይሆን እንደማይቀር ይነገርለታል። ከአውግስጦስ ቄሳር የግዛት ዘመን ጀምሮ የነበረው ይህ የገበያ ቦታ በረቀቁ ንድፎች የተሠሩ የጠጠር ንጣፎች፣ ጅምናዚየሞች፣ ውብ የመታጠቢያ ቤቶች፣ ስታዲየምና አምፊቲያትር፣ ድንቅ የመቃብር ቦታዎችና 15,000 ሰዎችን ሊይዝ የሚችል ትልቅ ቲያትር ቤት እንደነበሩት ፍርስራሾቹ ይጠቁማሉ። በአቅራቢያው ደግሞ ትልቁ የዚየስ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ ይገኛል።

ሆኖም ዚየስ ከተማዋን በተደጋጋሚ ከተፈራረቁባት የመሬት መንቀጥቀጦች ሊታደጋት አልቻለም። በ15 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተከሰተ አንድ አውዳሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዳልነበረች ቢያደርጋትም አውግስጦስ በድጋሚ አስገነባት። በ77 ከክርስቶስ ልደት በኋላም በመሬት መንቀጥቀጥ ፈርሳ እንደገና ተሠርታለች። በአራተኛው ክፍለ ዘመን የተከሰቱት ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጦች ግን ዳግመኛ እንዳታንሰራራ አድርገው ያወደሟት ሲሆን ከዚያ በኋላ የቀድሞ ክብሯን መልሳ ማግኘት አልተቻላትም። በመካከለኛው ዘመን ወደቧ በደለል ተሞልቶና ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ ነበር።

የስልማና ነዋሪዎች ለጳውሎስ ስብከት ምን ምላሽ እንደሰጡ የምናውቀው ነገር የለም። ሆኖም ጳውሎስ በሌሎች ከተሞችም መስበክ ነበረበት። ሚስዮናውያኑ ከስልማና ሲነሱ ሦስት አማራጭ መንገዶች ነበሯቸው። አንደኛው የኪሬንያን የተራራ ሰንሰለት አቋርጦ ወደ ሰሜናዊው ጠረፍ የሚሄድ ሲሆን ሌላኛው በሜሳኦሪያ ሜዳማ ቦታዎች በኩል ደሴቲቱን መሃል ለመሃል ሰንጥቆ ወደ ምዕራብ የሚጓዝ ነው። ሦስተኛው መንገድ ደግሞ የደሴቲቱን ደቡባዊ ጠረፍ ተከትሎ ይሄዳል።

ጳውሎስ በሦስተኛው መንገድ እንደተጓዘ በአፈ ታሪክ ይነገራል። መንገዱ ልዩ የሆነ ቀይ አፈር ባለው ለም የእርሻ መሬት መካከል የሚያልፍ ሲሆን ወደ ደቡብ ምዕራብ 50 ኪሎ ሜትር ከተጓዘ በኋላ በስተ ሰሜን ወደ ደሴቲቱ መሃል ከመጠምዘዙ በፊት ከላርናካ ከተማ ጋር ይገናኛል።

‘ደሴቲቱን ከዳር እስከ ዳር ማቋረጥ’

ብዙም ሳይኬድ መንገዱ ሊደራ ወደተባለችው ጥንታዊ ከተማ ይደርሳል። በአሁኑ ወቅት በዚህ ቦታ ላይ የምትገኘው ዘመናዊዋ የቆጵሮስ ዋና ከተማ ኒከሲያ ስትሆን የጥንቷ ሊደራ በቦታው እንደነበረች የሚጠቁም ማስረጃ ጨርሶ የለም። ሆኖም በ16ኛው ክፍለ ዘመን በከተማዋ ማዕከል ዙሪያ በቬኒሺያኖች በተገነቡት ግንቦች መሃል ሊደራ ጎዳና ተብሎ የሚጠራ መንገደኛ የሚበዛበት ቀጭን መንገድ አለ። ጳውሎስ በሊደራ አልፎ ይሁን አይሁን የምናውቀው ነገር የለም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው “የቆጵሮስን ደሴት ከዳር እስከ ዳር” እንዳቋረጡ ብቻ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 13:6) ዘ ዋይክሊፍ ሂስቶሪካል ጂኦግራፊ ኦቭ ባይብል ላንድስ እንደሚለው ይህ አባባል “በቆጵሮስ የነበረውን የአይሁድ ማኅበረሰብ ከሞላ ጎደል ማዳረስን ሳያመለክት አይቀርም።”

ጳውሎስ በተቻለ መጠን ምሥራቹን ለብዙ ሰዎች ለመስበክ ይፈልግ እንደነበር የታወቀ ነው። በመሆኑም ከሊደራ ተነስቶ የተጓዘው በስተ ደቡብ በኩል አማተስ እና ኩርየን የሚባሉትን ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸውን ትላልቅ ከተሞች በሚያቋርጠው መንገድ ሊሆን ይችላል።

ኩርየን በባሕሩ ዳርቻ ባሉ ትላልቅ ቋጥኞች አናት ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። በ77 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ስልማናን ያወደማት የመሬት መንቀጥቀጥ የግሪክና የሮማ ባሕል የሚንጸባረቅባትን ይህቺን ውብ ከተማም አግኝቷት ነበር። በ100 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ለአፖሎ የተሠራ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ በከተማዋ የሚገኝ ሲሆን 6,000 ተመልካቾችን መያዝ የሚችል ስታዲየምም ነበራት። የግል መኖሪያ ቤቶች እንኳን ወለላቸው ዓይን በሚማርኩ የሸክላ ንጣፎች ያሸበረቁ መሆናቸው አብዛኞቹ የኩርየን ነዋሪዎች የቅንጦት ኑሮ ይኖሩ እንደነበር ይመሰክራል።

ወደ ጳፉ ማቅናት

ከኩርየን ተነስቶ ወደ ምዕራብ የሚያመራው ማራኪ መልክዓ ምድራዊ እይታ ያለው መንገድ የወይን ማምረቻ መንደሮችን አቋርጦ ቀስ በቀስ ከፍታ እየጨመረ ከሄደ በኋላ በድንገት ቁልቁል ያዘቀዝቅና በቋጥኞች መሃል እየተጠማዘዘ ወርዶ በትላልቅ ጠጠሮች ከተሸፈነ የባሕር ዳርቻ ጋር ይገናኛል። በግሪካውያን አፈ ታሪክ መሠረት ይህ የባሕር ዳርቻ እንስቷ አምላክ አፍሮዳይት ከባሕር የተወለደችበት ቦታ ነው።

አፍሮዳይት በቆጵሮስ ከሚገኙት የግሪክ አማልክቶች መካከል ትልቅ ቦታ ይሰጣት የነበረ ሲሆን እስከ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በሰፊው ትመለክ ነበር። የጸደይ ወቅት በመጣ ቁጥር የአፍሮዳይት አምልኮ ማዕከል በሆነው በጳፉ ትልቅ ክብረ በዓል ይደረግላት ነበር። ከትንሿ እስያ፣ ከግብጽ፣ ከግሪክ እንዲሁም ከፋርስ ድረስ ብዙ ሰዎች በበዓሉ ላይ ለመገኘት ይመጣሉ። የቆጵሮስ ነዋሪዎች ከፈርዖን አምልኮ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁት ደሴቲቷ ቶሎሚ ተብለው ይጠሩ በነበሩት ግብጻውያን ነገሥታት አገዛዝ ሥር በነበረችበት ወቅት ነው

ጳፉ በሮማውያን አገዛዝ ወቅት የቆጵሮስ ዋና ከተማና የአገረ ገዢው መቀመጫ የነበረች ሲሆን የመዳብ ሳንቲሞችን የመቅረጽ ሥልጣን አግኝታ ነበር። በ15 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ጳፉም አላመለጠችም። ሆኖም ስልማናን ያስገነባት አውግስጦስ ጳፉንም መልሶ ለመገንባት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ሰጥቷል። በከተማዋ የተደረጉ የአርኪኦሎጂ ቁፋሮዎች በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ሃብታም ነዋሪዎቿ የተንደላቀቀ ሕይወት ይኖሩ እንደነበር የሚጠቁሙ ከመሆናቸውም በላይ ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎች፣ የተንቆጠቆጡ የግል መኖሪያዎች፣ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች፣ ጅምናዚየሞችና አምፊቲያትር እንደነበራት ያሳያሉ።

ጳውሎስ፣ በርናባስና ዮሐንስ ማርቆስ የጎበኟት ጳፉ ይህን ትመስል የነበረ ሲሆን “አስተዋይ” የነበረው አገረ ገዢ ሰርግዮስ ጳውሎስ፣ ኤልማስ ተብሎ የሚጠራው ጠንቋይ አጥብቆ ቢቃወመውም “የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት” ልባዊ ፍላጎት ያሳየው በዚህ ነበር። አገረ ገዢው ‘በጌታ ትምህርት ተደንቆ’ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 13:6-12

ሚስዮናውያኑ በቆጵሮስ የስብከት ሥራቸውን በተሳካ ሁኔታ ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ትንሿ እስያ አመሩ። ይህ የጳውሎስ የመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞ በእውነተኛው ክርስትና መስፋፋት ረገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ክንውን ነበር። ሴይንት ፖልስ ጆርኒስ ኢን ዘ ግሪክ ኦሪየንት የተባለው መጽሐፍ “ለክርስቲያናዊው የሚስዮናዊነት ሥራም ሆነ . . . ጳውሎስ በሚስዮናዊነት ላሳለፈው ሕይወት የመጀመሪያው እርምጃ” ብሎ ጠርቶታል። አክሎም “ወደ ሶርያ፣ ትንሿ እስያና ግሪክ የሚያቀኑ የባሕር መንገዶች በሚገናኙበት ቦታ ላይ ያለችው ቆጵሮስ ማንኛውንም የሚስዮናዊ ጉዞ ለመጀመር ተስማሚ ቦታ ነች” ብሏል። ይሁን እንጂ በዚያ ወቅት ክርስቲያናዊው የስብከት ሥራ ገና መጀመሩ ነበር። ከ2,000 ዓመታት በኋላም ይህ ሥራ በሰፊው የቀጠለ ሲሆን አሁን የይሖዋ መንግሥት ምሥራች ቃል በቃል “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” ተሰብኳል ሊባል ይችላል።—የሐዋርያት ሥራ 1:8

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቆጵሮስ

ኒከሲያ (ሊደራ)

ስልማና

ጳፉ

ኩርየን

አማተስ

ላርናካ

የኪሬንያ ተራሮች

የሜሳኦሪያ ሜዳማ አካባቢ

የትሮዶስ ተራሮች

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ በጳፉ በነበረበት ወቅት በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ጠንቋዩን ኤልማስን አሳውሮታል