በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በ2 ቆሮንቶስ 6:14 ላይ ጳውሎስ ‘የማያምኑ’ ሲል ስለ እነማን መናገሩ ነበር?

ሁለተኛ ቆሮንቶስ 6:14 “ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” ይላል። በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ አባል ስላልሆኑ ሰዎች እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። ጳውሎስ ‘የማያምኑ’ የሚለውን ቃል የተጠቀመባቸውን ሌሎች ቦታዎች መመልከታችን የዚህን መደምደሚያ ትክክለኛነት ያረጋግጥልናል።

ለምሳሌ ጳውሎስ አንዳንድ ክርስቲያኖች “በማያምኑ ሰዎች ፊት” ለመቅረብ ፍርድ ቤት በመሄዳቸው ወቅሷቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:6) እዚህ ላይ የማያምኑ የተባሉት በቆሮንቶስ በነበረው ፍርድ ቤት ውስጥ የሚሠሩት ዳኞች ናቸው። ጳውሎስ በሁለተኛው ደብዳቤ ላይ ሰይጣን ‘የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሮአል’ በማለት ተናግሯል። እነዚህ የማያምኑ ሰዎች ምሥራቹን ለማስተዋል እንዳይችሉ ዓይናቸው ‘ተሸፍኗል።’ ጳውሎስ ቀደም ብሎ “አንድ ሰው ወደ ጌታ ዘወር ሲል መሸፈኛው ይወገዳል” ሲል በተናገረው መሠረት የማያምኑ የተባሉት እነዚህ ሰዎች ይሖዋን ለማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው አላሳዩም።—2 ቆሮንቶስ 3:16፤ 4:4

አንዳንድ የማያምኑ ሰዎች ሕገወጥ በሆኑ ተግባራት ወይም በጣዖት አምልኮ ይካፈላሉ። (2 ቆሮንቶስ 6:15, 16) ይሁን እንጂ የይሖዋን አገልጋዮች የሚቃወሙት ሁሉም አይደሉም። አንዳንዶች እውነትን ለመስማት ፍላጎት አላቸው። የትዳር ጓደኞቻቸው ክርስቲያን ቢሆኑም ከእነርሱ ጋር በመኖራቸው ደስተኛ የሆኑ ብዙ የማያምኑ ሰዎች አሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:12-14፤ 10:27፤ 14:22-25፤ 1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ሆኖም ጳውሎስ “የማያምኑ” የሚለውን ቃል በተጠቀመባቸው ቦታዎች ሁሉ ለማመልከት የፈለገው ከላይ እንደተጠቀሰው ‘በጌታ የሚያምኑ’ ሰዎችን ያቀፈው የክርስቲያን ጉባኤ አባል ያልሆኑ ሰዎችን ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 2:41፤ 5:14፤ 8:12, 13

በ2 ቆሮንቶስ 6:14 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ክርስቲያኖች በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፎች ሊሠሩበት የሚችሉት ጠቃሚ መመሪያ ሲሆን ብዙውን ጊዜም የትዳር ጓደኛ ለሚፈልጉ ክርስቲያኖች ምክር ለመስጠት ይጠቀሳል። (ማቴዎስ 19:4-6) የማያምኑ ሰዎች ያሏቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች፣ ግቦችና እምነቶች ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ፈጽሞ ስለሚለዩ አንድ ራሱን ለአምላክ የወሰነና የተጠመቀ ክርስቲያን ከማያምኑ ሰዎች መካከል የትዳር ጓደኛ መፈለጉ ተገቢ አይሆንም።

መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚያጠኑና ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ስለሚሰበሰቡ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ቢሆኑስ? የማያምኑ ሊባሉ ይችላሉ? በፍጹም። ምሥራቹን ተቀብለው ለመጠመቅ ደረጃ በደረጃ እድገት እያደረጉ ያሉ ሰዎች የማያምኑ ሊባሉ አይችሉም። (ሮሜ 10:10፤ 2 ቆሮንቶስ 4:13) ቆርኔሌዎስ ከመጠመቁ በፊት እንኳን “በመንፈሳዊ ነገር የተጋና እግዚአብሔርን የሚፈራ” እንደሆነ ተነግሮለታል።—የሐዋርያት ሥራ 10:2

ታዲያ በ2 ቆሮንቶስ 6:14 ላይ በሚገኘው የጳውሎስ ምክር ውስጥ ‘የማያምኑ’ የሚለው አባባል ያልተጠመቁ አስፋፊዎችን የማያመለክት ከሆነ አንድ ራሱን የወሰነ ክርስቲያን ካልተጠመቀ አስፋፊ ጋር ለጋብቻ በመተሳሰብ መጠናናት ቢጀምር ተገቢ ይሆናል? እንዲህ ማድረጉ ተገቢ አይሆንም። ለምን? ጳውሎስ ለክርስቲያን መበለቶች የሰጠው ቀጥተኛ ምክር ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሆነናል። ጳውሎስ “የፈለገችውን ሰው ለማግባት ነጻነት አላት፤ ሰውየው ግን በጌታ መሆን አለበት” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) በዚህ ምክር መሠረት ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች “በጌታ” ከሆኑት መካከል ብቻ እንዲያገቡ ተበረታተዋል።

“በጌታ” እና “በክርስቶስ” የሚሉት ተዛማጅ አባባሎች ትርጉማቸው ምንድን ነው? ጳውሎስ በሮሜ 16:8-10 እና በቆላስይስ 4:7 ላይ “በክርስቶስ” እና “በጌታ” ስለሆኑ ሰዎች ተናግሯል። ጥቅሶቹን አውጥተህ ብታነብ እነዚህ ሰዎች ‘አብሮ የሚሠራ፣’ ‘እምነቱ ተፈትኖ የተመሰገነ፣’ ‘የተወደደ ወንድም፣’ ‘ታማኝ አገልጋይና’ ‘አብሮ ባሪያ የሆነ’ [የ1954 ትርጉም] ተብለው እንደተጠሩ ትመለከታለህ።

አንድ ሰው ‘በጌታ ባሪያ’ የሚሆነው እንዴት ነው? ከአንድ ባሪያ የሚጠበቀውን ለማድረግ ራሱን በፈቃደኝነት ሲያቀርብና ራሱን ሲክድ ነው። ኢየሱስ “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ብሏል። (ማቴዎስ 16:24) አንድ ሰው ክርስቶስን መከተልና ለአምላክ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ መገዛት የሚጀምረው ራሱን ለአምላክ ሲወስን ነው። ከዚያም ራሱን ለጥምቀት ያቀርብና በይሖዋ አምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የተሾመ አገልጋይ ይሆናል። a ስለዚህ ‘በጌታ ማግባት’ ማለት “የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ” እና አማኝ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ሰው ማግባት ማለት ነው።—ያዕቆብ 1:1

አንድ ሰው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱና ጥሩ መንፈሳዊ እድገት ማድረጉ የሚያስመሰግነው ነው። ይሁን እንጂ ራሱን ለይሖዋ ያልወሰነ ከመሆኑም በላይ ማገልገልንና መሥዋዕትነት መክፈልን ለሚጠይቀው ሕይወት ራሱን አላቀረበም። አሁንም ገና አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን እያደረገ ነው። በሕይወቱ ውስጥ ትዳር እንደ መመሥረት ያለ መሠረታዊ ለውጥ ለማድረግ ከማሰቡ በፊት ራሱን የወሰነና የተጠመቀ ክርስቲያን ለመሆን የሚያደርገውን ለውጥ ማጠናቀቅ አለበት።

አንዲት ክርስቲያን እስኪጠመቅ ድረስ እጠብቃለሁ በሚል በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ጥሩ እድገት እያደረገ ካለ ግለሰብ ጋር መጠናናት መጀመሯ ተገቢ ነው? አይደለም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ራሷን የወሰነች አንዲት ክርስቲያን ልታገባው ብትፈልግም እስኪጠመቅ ድረስ እንደምትጠብቀው ካወቀ ለጥምቀት ሊያነሳሳው የሚገባውን ዓላማ ሊስት ይችላል።

አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ የሚቆየው ለተወሰነ ጊዜ ማለትም መጠመቅ ወደሚችልበት ደረጃ እስኪደርስ ብቻ ነው። በመሆኑም በጌታ ብቻ እንድናገባ የሚያዘው ከላይ ያለው መመሪያ ሐቁን ያላገናዘበ ነው ሊባል አይችልም። ክርስቲያን በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ተወልዶ ማግባት ወደሚችልበት ዕድሜ ከደረሰና በጉባኤው ውስጥ ለተወሰኑ ዓመታት በንቃት ሲንቀሳቀስ ከነበረ ያልተጠመቀ አስፋፊ ጋር መጠናናት ስለመጀመርስ ምን ማለት ይቻላል? ራሱን ለይሖዋ እንዳይወስን እንቅፋት የሆነበት ምንድን ነው? የሚያመነታው ለምንድን ነው? አንዳንድ ጥርጣሬዎች አሉት? ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ከማያምኑት ጋር ባይፈረጅም “በጌታ” ነው ሊባል ግን አይችልም።

ጳውሎስ ትዳርን በሚመለከት የሰጠው ይህ ምክር ጠቀሜታው ለእኛው ነው። (ኢሳይያስ 48:17) ለመጋባት ያሰቡት ሁለቱም ግለሰቦች ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ከሆኑ ሲጋቡ አንዳቸው ለሌላው የሚገቡት ቃል ጠንካራ የሆነ መንፈሳዊ መሠረት ይኖረዋል። ተመሳሳይ የሥነ ምግባር አቋምና ግቦች ይኖሯቸዋል። ይህም ደስተኛ የሆነ ትዳር እንዲኖራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከዚህም በላይ አንድ ሰው ‘በጌታ ማግባቱ’ ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት የሚያሳይ ሲሆን ይህም ‘ከታማኙ ጋር ታማኝ የሚሆነውን’ የይሖዋን በረከት ያስገኝለታል።።—መዝሙር 18:25

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ጳውሎስ በመጀመሪያ ለጻፈላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘በጌታ ባሪያ’ መሆን ማለት የአምላክ ልጆችና የክርስቶስ ወንድሞች ሆነው መቀባታቸውንም ይጨምራል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ይሖዋ ከታማኙ ጋር ታማኝ ይሆናል’