በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው’

‘ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው’

‘ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው’

“ስለዚህ ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።”—ማቴዎስ 28:19, 20

1. ደቀ መዝሙሩ ፊልጶስና ከኢትዮጵያ የመጣው ሰው ምን ውይይት አደረጉ?

 ሰውየው ከኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣት ረጅም መንገድ ተጉዟል። እዚያም ለሚወድደው አምላክ ለይሖዋ አምልኮ አቀረበ። ይህ ሰው በመንፈስ አነሳሽነት ለተጻፈው ለአምላክ ቃልም ፍቅር እንዳለው ከሁኔታው ማየት ይቻላል። በሰረገላው ወደ አገሩ በሚመለስበት ጊዜ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ እያነበበ ነበር፤ በዚህ ወቅት የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነው ፊልጶስ ተገናኘው። ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን “ለመሆኑ፣ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” የሚል ጥያቄ አቀረበለት። ሰውየውም “የሚያስረዳኝ ሰው [“የሚመራኝ፣” የ1954 ትርጉም] ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውላለሁ” ሲል መለሰለት። ከዚህ በኋላ ፊልጶስ ይህን ልበ ቅን የቅዱሳን መጻሕፍት ተማሪ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን ረዳው።—የሐዋርያት ሥራ 8:26-39

2. (ሀ) ኢትዮጵያዊው የሰጠው መልስ ትርጉም ያዘለ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ ከሰጠን ተልእኮ ጋር በተያያዘ የሚነሱትን የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 ኢትዮጵያዊው ‘የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውላለሁ’ በማለት የሰጠው መልስ ትልቅ ትርጉም ያዘለ ነው። አዎን፣ የሚመራው ሰው ማለትም መንገዱን የሚያሳየው ሰው ማግኘት ፈልጓል። ይህ አባባል በራሱ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አድርጉ ሲል በሰጠው ተልእኮ ውስጥ የተካተተ አንድ መመሪያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል። መመሪያው ምንድን ነው? መልሱን ለማግኘት ማቴዎስ ምዕራፍ 28 ላይ የሚገኙትን ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት መመርመራችንን እንቀጥል። ከዚህ በፊት በነበረው ርዕስ ላይ ለምን? እና የት? የሚሉት ጥያቄዎች ተብራርተዋል። አሁን ደግሞ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አድርጉ ሲል ከሰጠው ትእዛዝ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ምን? እና መቼ? የሚሉትን ሁለት ተጨማሪ ጥያቄዎች እንመረምራለን።

“ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው”

3. (ሀ) አንድ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሚሆነው እንዴት ነው? (ለ) ደቀ መዛሙርት ማድረግ ምን ማስተማርን ይጨምራል?

3 ሌሎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ማስተማር ያለብን ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ ሲል አዟቸዋል “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።” (ማቴዎስ 28:19, 20) በመሆኑም ክርስቶስ ያዘዘንን ነገሮች ማስተማር አለብን። a ይሁንና የኢየሱስን ትእዛዛት የተማረ አንድ ግለሰብ ደቀ መዝሙር ከመሆንም አልፎ እስከ መጨረሻው እንዲጸና ለመርዳት ምን ማድረግ ይቻላል? ኢየሱስ ትእዛዙን ከተናገረበት መንገድ አንድ ቁልፍ ነጥብ እናገኛለን። ‘ያዘዝኋችሁን ሁሉ አስተምሯቸው’ ብቻ እንዳላለ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ‘ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው’ ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:17) ይህ ምን ማለት ነው?

4. (ሀ) ትእዛዝ መጠበቅ ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) አንድ ሰው የክርስቶስን ትእዛዛት እንዲጠብቅ ማስተማር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

4 አንድን ትእዛዝ መጠበቅ ሲባል ከተሰጠው ትእዛዝ ጋር “ተስማምቶ መኖር” ይኸውም ትእዛዙን ማክበር ወይም መፈጸም ማለት ነው። ታዲያ አንድ ሰው ክርስቶስ ያዘዘንን ነገሮች እንዲጠብቅ ወይም እንዲያከብር ማስተማር የምንችለው እንዴት ነው? አንድ የመኪና አለማማጅ ተማሪው የትራፊክ ሕጎችን እንዲያከብር እንዴት እንደሚያስተምረው እንመልከት። አለማማጁ ለተማሪው የትራፊክ ደንቦችን በቃል ሊያስተምረው ይችላል። ይሁን እንጂ የትራፊክ ደንቦቹን ተከትሎ እንዴት እንደሚነዳ ለማስተማር ለማጁ ከተማ ወጥቶ ሲያሽከረክርና የተማራቸውን ነገሮች በሥራ ለማዋል ሲጥር አለማማጁ አጠገቡ ተቀምጦ መመሪያ መስጠት አለበት። በተመሳሳይ እኛም ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና የክርስቶስን ትእዛዛት እናስተምራቸዋለን። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን የክርስቶስን መመሪያዎች በዕለታዊ ሕይወታቸውና በስብከቱ ሥራ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ሲጥሩ መመሪያ ልንሰጣቸውም ይገባል። (ዮሐንስ 14:15፤ 1 ዮሐንስ 2:3) ስለዚህ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠንን ትእዛዝ ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ትእዛዛቱን ማስተማርንና እንዴት በሥራ ማዋል እንደሚቻል መመሪያ መስጠትን ይጠይቃል። አስተማሪም መሪም በመሆን ኢየሱስና ይሖዋ የተዉልንን ምሳሌ መኮረጅ እንችላለን።—መዝሙር 48:14፤ ራእይ 7:17

5. መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናው ሰው ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አድርጉ ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ከማክበር ወደኋላ የሚለው ለምን ሊሆን ይችላል?

5 የኢየሱስን ትእዛዛት እንዲጠብቁ ሌሎችን ማስተማር ደቀ መዛሙርት አድርጉ የሚለውን ትእዛዝ እንዲያከብሩ መርዳትንም ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናቸው አንዳንድ ሰዎች በዚህ ሥራ መሳተፍ ያሳፍራቸው ይሆናል። ከዚህ በፊት በአንድ የሕዝበ ክርስትና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ቢሆኑም እንኳ የበፊቶቹ መንፈሳዊ አስተማሪዎቻቸው ሄደው ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ አስተምረዋቸዋል ማለት ዘበት ነው። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ምዕመኖቻቸው ወንጌላውያን እንዲሆኑ ማስተማርን በተመለከተ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ምንም ያደረጉት ነገር እንደሌለ በግልጽ ይናገራሉ። ኢየሱስ ወደ ዓለም ሄደን ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠንን ትእዛዝ በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ጆን ስቶት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል “የዚህን መመሪያ መንፈስ ማክበር አለመቻላችን ወንጌላውያን የሆኑ ክርስቲያኖች በዛሬው ጊዜ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ እንቅስቃሴ ረገድ የታየባቸው ጉልህ ድክመት ነው።” አክለውም እንዲህ ብለዋል “ወንጌሉን ከሩቅ ቆሞ ማወጅ ይቀናናል። ወንዝ ዳር ቆመው ውሃ ውስጥ እየሰጠሙ ላሉ ሰዎች መመሪያ ከሚሰጡ ሰዎች ተለይተን አንታይም። እነርሱን ለማዳን ውሃው ውስጥ ለመግባት አልደፈርንም። በውሃ እንዳንበሰብስ ፈርተናል።”

6. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችንን ስንረዳ የፊልጶስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን በስብከቱ ሥራ መሳተፍ ሲጀምር አሳቢነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

6 መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናው ሰው ከዚህ ቀደም የነበረበት ሃይማኖት ‘በውሃ መበስበስ የሚያስፈራቸው’ አባላትን ያቀፈ ከነበረ፣ ሰውየው በምሳሌያዊ አባባል ለውሃ ያለውን ፍርሃት አስወግዶ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አድርጉ ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ማክበር በጣም ሊከብደው ይችላል። ይህ ሰው እርዳታ ያስፈልገዋል። ፊልጶስ የሰጠው ትምህርት የኢትዮጵያዊውን ግንዛቤ እንዳሰፋለትና ለመጠመቅ እንዲነሳሳ እንዳደረገው ሁሉ እኛም የግለሰቡን እውቀት የሚያሳድግና ለተግባር የሚያነሳሳ ትምህርትና መመሪያ ስንሰጥ ትዕግሥተኞች መሆን ያስፈልገናል። (ዮሐንስ 16:13፤ የሐዋርያት ሥራ 8:35-38) ከዚህ በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ የሚለውን ትእዛዝ እንዲጠብቁ ለማስተማር ያለን ፍላጎት የመንግሥቱን ምስራች መስበክ በሚጀምሩበት ጊዜ መመሪያ ለመስጠት አብረናቸው እንድናገለግል ያነሳሳናል።—መክብብ 4:9, 10፤ ሉቃስ 6:40

“ያዘዝኋችሁንም ሁሉ”

7. ትእዛዛቱን ‘ሁሉ እንዲጠብቁ’ ሌሎችን ማስተማር የትኞቹን ትእዛዛት ማስተማርን ይጨምራል?

7 አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን እነርሱም ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ በማስተማር ብቻ አናበቃም። ኢየሱስ፣ ያዘዘውን “ሁሉ እንዲጠብቁ” ሌሎችን እንድናስተምር መመሪያ ሰጥቶናል። ይህም አምላክንና ባልንጀራህን ውደድ የሚሉትን ሁለት ታላላቅ ትእዛዛት እንደሚጨምር ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 22:37-39) አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር እነዚህን ትእዛዛት እንዲጠብቅ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?

8. አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር ፍቅር እንድናሳይ የተሰጠንን ትእዛዝ እንዴት ሊማር እንደሚችል በምሳሌ አስረዳ።

8 መኪና መንዳት ስለሚማረው ሰው የሚናገረውን ምሳሌ እስቲ በድጋሚ እናንሳ። ለማጁ አስተማሪው አጠገቡ ተቀምጦ በሚያሽከረክርበት ጊዜ ሥልጠና የሚያገኘው አለማማጁ የሚነግረውን በማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አሽከርካሪዎችን በማየትም ነው። ለምሳሌ ያህል አስተማሪው መኪና በተጨናነቀበት ቦታ ሌላ መኪና ከፊቱ እንዲገባ በደግነት ቅድሚያ የሚሰጥን ሹፌር ወይም ከፊት ለፊቱ የሚመጣ አሽከርካሪ ማየት እንዳይቸገር በአሳቢነት መብራቱን የሚቀንስን ሹፌር ሊያሳየው ይችላል። በተጨማሪም መኪና ተበላሽቶበት የቆመን አንድ የሚያውቀውን ሰው በፈቃደኝነት ለመርዳት ከመኪናው የወረደን ሹፌር እንዲመለከት ይነግረው ይሆናል። ለማጁ እነዚህን በማየት ወደፊት መኪና ሲነዳ በተግባር የሚያውለው ጠቃሚ ትምህርት ያገኛል። በተመሳሳይ ወደ ሕይወት በሚያመራው መንገድ ላይ የሚጓዝ አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር ትምህርት የሚቀስመው ከአስተማሪው ብቻ ሳይሆን ጉባኤ ውስጥ ከሚያያቸው ግሩም ምሳሌዎችም ነው።—ማቴዎስ 7:13, 14

9. አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር ፍቅር እንድናሳይ የተሰጠንን ትእዛዝ መጠበቅ ምን ማለት እንደሆነ መማር የሚችለው እንዴት ነው?

9 ለምሳሌ ያህል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አንዲት ነጠላ ወላጅ ልጆቿን ይዛ ወደ መንግሥት አዳራሽ ለመምጣት ከፍተኛ ጥረት እንደምታደርግ ያስተውል ይሆናል። የመንፈስ ጭንቀት ቢኖርባትም በታማኝነት ወደ ጉባኤ የምትመጣ እህት፤ በዕድሜ የገፉ ሌሎች ክርስቲያኖች ወደ ጉባኤ ስብሰባ እንዲመጡ የሚረዱ አንዲት አረጋዊ መበለት ወይም አዳራሹን በማጽዳት ሥራ የሚሳተፍ አንድ ወጣት ይመለከት ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው፣ በርካታ የጉባኤ ኀላፊነቶች ቢኖሩበትም በመስክ አገልግሎት በታማኝነት ግንባር ቀደም ሆኖ የሚያገለግልን አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ይመለከት ይሆናል። የአካል ጉዳተኛ በመሆኑ ከቤት መውጣት የማይችል ቢሆንም ሊጠይቁት ለሚመጡ ሁሉ የብርታት ምንጭ ከሆነ የይሖዋ ምሥክር ጋር ይተዋወቅ ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን ለመንከባከብ ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ በማድረግ ላይ ያሉ ባልና ሚስት መኖራቸውን ይገነዘብ ይሆናል። ይህ አዲስ ደቀ መዝሙር እነዚህን የመሳሰሉ ደግ፣ ተባባሪና እምነት የሚጣልባቸው ክርስቲያኖች በማየት አምላክንና ሰዎችን፣ በተለይ የእምነት ጓደኞቻችንን እንድንወድ የሚያዝዘውን የክርስቶስን ትእዛዝ ማክበር ምን ማለት እንደሆነ በተግባር ይማራል። (ምሳሌ 24:32፤ ዮሐንስ 13:35፤ ገላትያ 6:10፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3) በዚህ መንገድ እያንዳንዱ የክርስቲያን ጉባኤ አባል አስተማሪና መሪ መሆን ይችላል፤ እንዲሆንም ይጠበቅበታል።—ማቴዎስ 5:16

“እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ”

10. (ሀ) ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ለምን ያህል ጊዜ እንቀጥላለን? (ለ) የተሰጠውን ተልእኮ መፈጸምን በተመለከተ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

10 ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ መቀጠል ያለብን እስከ መቼ ድረስ ነው? እስከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ ነው። (ማቴዎስ 28:20) ይህን የተልእኮውን ገጽታ መፈጸም እንችል ይሆን? በቡድን ደረጃ ተልእኮውን ለመፈጸም ቆርጠን ተነስተናል። ባለፉት ዓመታት ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ’ ሰዎችን ለማግኘት ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ገንዘባችንን በደስታ ሰውተናል። (የሐዋርያት ሥራ 13:48) በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የአምላክን መንግሥት በማወጅና ደቀ መዛሙርት በማድረግ በዓመቱ ውስጥ በእያንዳንዱ ቀን በአማካይ ከሦስት ሚሊዮን ሰዓት በላይ ያሳልፋሉ። እንዲህ የምናደርገው የኢየሱስን ምሳሌ ስለምንከተል ነው። ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:34) የእኛም ልባዊ ፍላጎት ይኸው ነው። (ዮሐንስ 20:21) በአደራ የተሰጠንን ሥራ መጀመር ብቻ ሳይሆን መፈጸምም እንፈልጋለን።—ማቴዎስ 24:13፤ ዮሐንስ 17:4

11. አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምን ዓይነት ሁኔታ ደርሶባቸዋል? ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

11 ይሁን እንጂ አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን በመንፈሳዊ ሁኔታ ከመዳከማቸው የተነሳ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አድርጉ ሲል የሰጠንን ትእዛዝ በመፈጸም ረገድ ተሳትፏቸውን ሲቀንሱ ወይም ሲያቆሙ ማየታችን በጣም ያሳዝነናል። ከጉባኤው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያድሱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉ መርዳት የምንችልበት መንገድ ይኖራል? (ሮሜ 15:1፤ ዕብራውያን 12:12) ኢየሱስ ሐዋርያቱ ለጥቂት ጊዜ ተዳክመው በነበረበት ወቅት እነርሱን የረዳበት መንገድ እኛም በዛሬው ጊዜ ምን ማድረግ እንደምንችል ፍንጭ ይሰጠናል።

አሳቢነት አሳዩ

12. (ሀ) ኢየሱስ ተይዞ ከመገደሉ በፊት ሐዋርያቱ ምን አደረጉ? (ለ) ሐዋርያቱ ከባድ ድክመት ቢታይባቸውም ኢየሱስ ምን ብሏቸዋል?

12 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ማብቂያ የሚገደልበት ጊዜ በጣም ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ሐዋርያቱ “ትተውት ሸሹ።” ኢየሱስ አስቀድሞ ተናግሮ እንደነበረው ‘ሁሉም በየፊናቸው ተበታተኑ።’ (ማርቆስ 14:50፤ ዮሐንስ 16:32) ኢየሱስ በመንፈሳዊ ለተዳከሙት ወዳጆቹ ምን አደረገላቸው? ከሞት ከተነሣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከተከታዮቹ መካከል ለአንዳንዶቹ “አትፍሩ፤ ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ በዚያ ያዩኛል” አላቸው። (ማቴዎስ 28:10) ምንም እንኳ ሐዋርያቱ ከባድ ድክመት ቢታይባቸውም ኢየሱስ “ወንድሞቼ” ብሎ መጥራቱን አላቆመም። (ማቴዎስ 12:49) ተስፋ አልቆረጠባቸውም። ይሖዋ መሐሪና ይቅር ባይ እንደሆነ ሁሉ ኢየሱስም መሐሪና ይቅር ባይ መሆኑን በዚህ መንገድ አሳይቷል። (2 ነገሥት 13:23) ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

13. በመንፈሳዊ ለደከሙ ወንድሞቻችን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

13 በአገልግሎት የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለቀነሱ ወይም ላቆሙ ክርስቲያኖች ጥልቅ አሳቢነት ልናሳያቸው ይገባል። እነዚህ የእምነት ባልንጀሮቻችን ከዚህ ቀደም በፍቅር ተነሳስተው ያከናወኑት ሥራ (አንዳንዶቹም ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሊሆን ይችላል) እስካሁን ድረስ ትዝ ይለናል። (ዕብራውያን 6:10) ከአጠገባችን መራቃቸው በጣም አጉድሎብናል። (ሉቃስ 15:4-7፤ 1 ተሰሎንቄ 2:17) ይሁንና እንደምናስብላቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14. የኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ የደከሙ ክርስቲያኖችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ በጣም አዝነው የነበሩትን ሐዋርያት ወደ ገሊላ እንዲሄዱና እርሱንም በዚያ እንደሚያገኙት ነገራቸው። በሌላ አባባል ኢየሱስ በአንድ ልዩ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:10) በተመሳሳይ በዛሬው ጊዜ በመንፈሳዊ የደከሙትን ክርስቲያኖች ወደ ጉባኤ ስብሰባ እንዲመጡ እናበረታታቸዋለን። ደጋግመን መጋበዝ ሊያስፈልገንም ይችል ይሆናል። ‘ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በገሊላ ወዳለው ኢየሱስ ወዳመለከታቸው ተራራ ስለሄዱ’ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ መልእክት መላኩ ጠቃሚ እንደነበር ታይቷል። (ማቴዎስ 28:16) በተመሳሳይ በመንፈሳዊ የደከሙ ክርስቲያኖች ያቀረብንላቸውን ሞቅ ያለ ግብዣ ተቀብለው ወደ ጉባኤ ስብሰባ መምጣት ሲጀምሩ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል!—ሉቃስ 15:6

15. ወደ ጉባኤ ለሚመጡ በመንፈሳዊ ለደከሙ ክርስቲያኖች ጥሩ አቀባበል በማድረግ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

15 በመንፈሳዊ የደከመ አንድ ክርስቲያን ወደ መንግሥት አዳራሽ ሲመጣ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ኢየሱስ ለተወሰነ ጊዜ እምነታቸው ተዳክሞ የነበረውን ሐዋርያቱን በነገራቸው ቦታ ላይ ባገኛቸው ጊዜ ምን አደረገ? “ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ” አነጋገራቸው። (ማቴዎስ 28:18) ከሩቅ ቆሞ በትዝብት ዓይን አልተመለከታቸውም፤ ከዚህ ይልቅ እነርሱ ወዳሉበት ሄዷል። ኢየሱስ ቅድሚያውን ወስዶ እነርሱ ወዳሉበት በመምጣቱ ሐዋርያቱ ምንኛ እፎይታ ተሰምቷቸው ይሆን! እኛም ወደ ጉባኤ ለመመለስ ጥረት የሚያደርጉ በመንፈሳዊ የደከሙ ክርስቲያኖችን ቀርበን በማነጋገር ሞቅ ያለ አቀባበል እናድርግላቸው።

16. (ሀ) ኢየሱስ ተከታዮቹን ሲያገኛቸው ካደረገላቸው ነገር ምን መማር እንችላለን? (ለ) ኢየሱስ ለደከሙ ክርስቲያኖች የነበረውን አመለካከት መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

16 ኢየሱስ ሌላ ምን ያደረገው ነገር አለ? በመጀመሪያ ‘ሥልጣን ሁሉ ተሰጥቶኛል’ በማለት አሳወቃቸው። ከዚያም ‘ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ በማለት ተልእኮ ሰጣቸው። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ “ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ሲል ቃል ገባላቸው። ሆኖም ኢየሱስ ያላደረገው አንድ ነገር እንዳለ ልብ በል። ደቀ መዛሙርቱ ድክመት ስላሳዩና ጥርጣሬ ስላደረባቸው አልነቀፋቸውም። (ማቴዎስ 28:17) ይህ አቀራረቡ ውጤታማ ነበር? አዎን። ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያቱ ‘ማስተማራቸውንና መስበካቸውን’ ቀጥለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:42) ለደከሙ ክርስቲያኖች ምን አመለካከት ሊኖረንና ምን ልናደርግላቸው እንደሚገባ ኢየሱስ ከተወልን ምሳሌ ትምህርት በመውሰድ እኛም በጉባኤያችን ውስጥ አስደሳች ውጤቶች ልናገኝ እንችላለን። bየሐዋርያት ሥራ 20:35

“ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ”

17, 18. ኢየሱስ “ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ሲል የተናገራቸው ቃላት ምን የሚያበረታታ ሐሳብ ይዘዋል?

17 ኢየሱስ ለተከታዮቹ በሰጣቸው ተልእኮ ውስጥ የሚገኙት “ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚሉት መጨረሻ ላይ የተናገራቸው ቃላት ደቀ መዛሙርት አድርጉ የሚለውን የክርስቶስን ትእዛዝ ለመፈጸም ጥረት ለሚያደርጉ ሁሉ ማበረታቻ ይዘዋል። ጠላቶቻችን በስብከቱ ሥራችን ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ቢሰነዝሩ እንዲሁም በእኛ ላይ ምንም ዓይነት ስም የማጥፋት ዘመቻ ቢያካሂዱ የምንፈራበት አንዳች ምክንያት የለም። ለምን? “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” የያዘው መሪያችን ኢየሱስ እኛን ለመርዳት ከጎናችን ነው!

18 ኢየሱስ “ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ሲል የገባልን ቃል ከፍተኛ የመጽናኛ ምንጭ ይሆነናል። ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ ክርስቶስ የሰጠንን ትእዛዝ ለመፈጸም ጥረት ስናደርግ አስደሳች ጊዜያት ብቻ ሳይሆን አሳዛኝ ወቅቶችም ያጋጥሙናል። (2 ዜና መዋዕል 6:29) አንዳንዶቻችን በጣም የምንወድደውን ሰው በሞት በማጣታችን ለሐዘን የምንዳረግበት ጊዜ ያጋጥመናል። (ዘፍጥረት 23:2፤ ዮሐንስ 11:33-36) ሌሎች ጤንነትና ብርታት የሚያጡበትን የእርጅና ዘመን ተቋቁመው ለመኖር ይገደዳሉ። (መክብብ 12:1-6) ሌሎች ደግሞ በመንፈስ ጭንቀት የሚዋጡባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) አብዛኞቻችን ደግሞ በከባድ የኢኮኖሚ ችግር ሥር ለመኖር እንገደዳለን። ይሁንና እነዚህን የመሳሰሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢደርሱብንም ኢየሱስ በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን አስከፊ ጊዜያት ጨምሮ “ሁልጊዜ” ከእኛ ጋር ስለሆነ አገልግሎታችንን ማከናወን እንችላለን።—ማቴዎስ 11:28-30

19. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠን ተልእኮ ምን መመሪያዎች ይዟል? (ለ) ክርስቶስ የሰጠንን ተልእኮ እንድንፈጽም የሚያስችለን ምንድን ነው?

19 በዚህና በፊተኛው ርዕስ እንደተመለከትነው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠን ተልእኮ የአገልግሎቱን የተለያዩ ገጽታዎች አካትቶ የያዘ ነው። ኢየሱስ የሰጠንን ትእዛዝ ማከናወን ያለብን ለምንና የት እንደሆነ ነግሮናል። ከዚህ በተጨማሪ ምን ማስተማር እንዳለብንና እስከ መቼ ድረስ መቀጠል እንዳለብን ነግሮናል። ይህን ታላቅ ተልእኮ መፈጸም ከባድ እንደሆነ አይካድም። ሆኖም ክርስቶስ ስለሚደግፈንና ከጎናችን ስላለ ሥራውን ዳር ማድረስ እንችላለን! በዚህ አትስማማም?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ኢየሱስ “እያጠመቃችኋቸው . . . አስተምሯቸው” እንጂ ‘እያጠመቃችኋቸው እና እያስተማራችኋቸው’ እንዳላለ ልብ ሊባል እንደሚገባው ገልጿል። ስለዚህ አጥምቁና አስተምሩ የሚለው ትእዛዝ “የግድ በቅደም ተከተል መምጣት ያለባቸው . . . ሁለት ተከታታይ እርምጃዎች አይደሉም።” ከዚህ ይልቅ “ማስተማር በተወሰነ መጠን ከጥምቀት በፊት . . . በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ከጥምቀት በኋላ የሚከናወን ቀጣይ ሂደት ነው።”

b በመንፈሳዊ ለደከሙ ክርስቲያኖች ሊኖረን የሚገባውን አመለካከትና መርዳት የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ በየካቲት 1, 2003 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 15-18 ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ይቻላል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ሌሎች የኢየሱስን ትእዛዝ እንዲጠብቁ ማስተማር የምንችለው እንዴት ነው?

• አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር በጉባኤ ውስጥ ካሉ ከሌሎች ምን መማር ይችላል?

• በመንፈሳዊ የደከሙትን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?

• ኢየሱስ “ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት ከገባልን ቃል ምን ማበረታቻና ማጽናኛ እናገኛለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስተማሪም መሪም መሆን ያስፈልገናል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር ከሌሎች ምሳሌ ጠቃሚ ትምህርቶች መቅሰም ይችላል