በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የይሖዋን ስም ለማስታወቅ”

“የይሖዋን ስም ለማስታወቅ”

“የይሖዋን ስም ለማስታወቅ”

መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔት መንፈሳዊ እውቀት የያዙና ትምህርት ሰጪ መጽሔቶች በመሆናቸው በዓለም ዙሪያ ይደነቃሉ። በፈረንሳይ ከምትኖር አንዲት ሴት በቅርቡ የደረሰን ደብዳቤ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል:-

“ከአፍሪካ የመጣሁ ወጣት ስሆን በትምህርቴ ብዙም አልገፋሁም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጽሑፎቻችሁን ማንበብ ጀምሬያለሁ። ርዕሶቹ የሚስቡ መሆናቸው ማንበብ ያለውን ጠቀሜታ እንድገነዘብ ረድቶኛል። የቃላት ችሎታዬ የተሻሻለ ሲሆን አሁን ብዙም ስሕተት የሌለበት ደብዳቤ መጻፍ በመቻሌ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።

“ጽሑፎቻችሁ ከሰው ልጆች፣ ከምድራችንና ከፈጣሪ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ የሚዳስሱ መሆናቸው ያስገርመኛል። የምታወጧቸው ርዕሶች ለመረዳት ቀላል በመሆናቸው አንድ ሰው የማንበብ ጉጉት እንዲያድርበት ያደርጋሉ። እንደ እናንተ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች እኩል ማስተማር የሚችል ጽሑፍ የሚያወጣ የለም።

“ይህንን ሁሉ ጥረት የምታደርጉት ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን የይሖዋን ስም ለማስታወቅ መሆኑም ያስገርመኛል። ይሖዋ እንደሚደግፋችሁ አውቃለሁ፤ አመሰግናችኋለሁ። ከፈጣሪ በምታገኙት ድጋፍ ሰዎችን ለማስተማር የምታደርጉትን ጥረት እባካችሁ ግፉበት።”

የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ወቅት በ235 አገሮች መጽሐፍ ቅዱስን እያስተማሩ ነው። መጠበቂያ ግንብ በ148 ንቁ! ደግሞ በ87 ቋንቋዎች ይታተማሉ። እነዚህ መጽሔቶች ለሰው ክብር ለመስጠት ተብለው የሚዘጋጁ አይደሉም። በጽሑፎቹ ላይ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክርና ወቅታዊ ሐሳብ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ . . . ነኝ” በማለት የተናገረውን ፈጣሪ ለማክበር ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። (ኢሳይያስ 48:17) መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በሚያስችሉት በእነዚህ ጽሑፎች አማካኝነት ቅዱሳን ጽሑፎችን አዘውትረህ በማንበብ እንድትጠቀም እንጋብዝሃለን።