ታላቅ መሆንን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አመለካከት አዳብሩ
ታላቅ መሆንን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አመለካከት አዳብሩ
“ከእናንተ ትልቅ መሆን የሚፈልግ አገልጋያችሁ ይሁን።”—ማቴዎስ 20:26
1. ዓለም ለታላቅነት ምን አመለካከት አለው?
ከካይሮ በስተ ምዕራብ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጥንታዊቷ የግብጽ ከተማ ቲብስ (የአሁኗ ካርናክ) አቅራቢያ 18 ሜትር ቁመት ያለው የፈርኦን አሜንሆቴፕ ሣልሳዊ ሐውልት ይገኛል። አንድ ሰው ራሱን ከዚያ ግዙፍ ምስል ጋር ሲያስተያይ በጣም ኢምንት እንደሆነ ይሰማዋል። ይህ ሐውልት የአገሪቱ ገዥ በታላቅ አክብሮት እንዲታይ የቆመ እንደሆነ ግልጽ ነው። ምስሉ ዓለም ለታላቅነት ያለውን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ሲሆን ይህም በተቻለ መጠን ራስን በማክበርና በማዋደድ ሌሎች አልባሌ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ማድረግ ነው።
2. ኢየሱስ ለተከታዮቹ የተወው ምሳሌ ምንድን ነው? ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?
2 ሰዎች ታላቅ ስለ መሆን ያላቸውን ይህን አመለካከት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ታላቅነት ከሰጠው ትምህርት ጋር አስተያየው። ኢየሱስ የተከታዮቹ ‘ጌታና አስተማሪ’ የነበረ ቢሆንም እንኳ ታላቅነት የሚገኘው ሌሎችን ከማገልገል እንደሆነ አስተምሯቸዋል። በምድር ላይ በሕይወት ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ የትምህርቱን ትርጉም በተግባር አሳይቷል። በእርግጥም ትልቅ ትሕትና የሚጠይቅ ሥራ አከናውኗል! (ዮሐንስ 13:4, 5, 14) ከማገልገልና ከመገልገል የቱን ትመርጣለህ? የክርስቶስ ምሳሌ እንደ እርሱ ትሑት የመሆን ፍላጎት ያሳድርብሃል? ከሆነ ክርስቶስ ለታላቅነት የነበረውን አመለካከት በዓለም ካለው የተለመደ አመለካከት ጋር በማወዳደር ይህን ጉዳይ እንመርምር።
ዓለም ለታላቅነት ያለውን አመለካከት አትኮርጁ
3. ከሌሎች ክብር ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች አሳዛኝ ውድቀት እንደሚደርስባቸው የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ያሳያሉ?
3 ዓለም ለታላቅነት ያለው አመለካከት ለውድቀት እንደሚዳርግ የሚያሳዩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች አሉ። በአስቴርና በመርዶክዮስ ዘመን የኖረውንና በፋርስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረውን ሐማን ተመልከት። ሐማ ለክብር መቋመጡ ለውርደትና ለሞት ዳርጎታል። (አስቴር 3:5፤ 6:10-12፤ 7:9, 10) መንግሥቱ በጣም በገነነበት ዘመን አእምሮውን ስለሳተው ትዕቢተኛ ንጉሥ ናቡከደናፆርስ ምን ማለት ይቻላል? ናቡከደናፆር “በብርቱ ኀይሌ፣ ለገናናው ክብሬ ንጉሣዊ መኖሪያ ትሆን ዘንድ ያሠራኋት ታላቂቷ ባቢሎን ይህች አይደለችምን?” በማለት ከተናገራቸው ቃላት ለታላቅነት የተዛባ አመለካከት እንደነበረው ማየት ይቻላል። (ዳንኤል 4:30) ሌላው ደግሞ ለአምላክ ክብር ከመስጠት ይልቅ የማይገባውን ክብር ለራሱ የወሰደው ኩሩው ንጉሥ ቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ ሲሆን ከዚህ ባሕሪው የተነሳ ‘በትል ተበልቶ ሞቷል።’ (የሐዋርያት ሥራ 12:21-23) እነዚህ ሰዎች ይሖዋ ለታላቅነት ያለውን አመለካከት ሳይገነዘቡ በመቅረታቸው አሳፋሪ ውድቀት ደርሶባቸዋል።
4. ሰዎች የኩራት መንፈስ እንዲጠናወታቸው የሚያደርገው ማን ነው?
4 በሌሎች ዘንድ ጥሩ ግምትና አክብሮት በሚያስገኝልን መንገድ መኖር መፈለጋችን ተገቢ ነው። ሆኖም የሥልጣን ጥመኛ የሆነው ዲያብሎስ ለዓመጽ ያነሳሳውን የኩራት መንፈስ በውስጣችን በማሳደር በዚህ ምኞታችን መጠቀም ይፈልጋል። (ማቴዎስ 4:8, 9) ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” እንደሆነና በዚህ ምድር ላይ የራሱን አመለካከት ለማስፋፋት ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ፈጽሞ አትዘንጉ። (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ኤፌሶን 2:2፤ ራእይ 12:9) ክርስቲያኖች የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ምንጭ ማን መሆኑን ስለሚያውቁ ዓለም ለታላቅነት ያለውን አመለካከት ይርቃሉ።
5. ስኬት፣ ታዋቂነትና ሀብት ዘላቂ እርካታ ሊያስገኙ ይችላሉ? አብራራ።
5 ዲያብሎስ ከሚያራምደው አስተሳሰብ መካከል አንዱ በዓለም ውስጥ ታዋቂ መሆን፣ የሰዎችን ክብር ማግኘት እንዲሁም ሀብታም መሆን የደስታ ቁልፍ ነው የሚል ነው። ይህ እውነት ነው? ስኬት፣ ዝናና ሀብት እርካታ የተሞላበት ሕይወት ሊያስገኙ ይችላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ እንዳንታለል ያስጠነቅቀናል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጥረትና የሥራ መከናወን ሁሉ ሰው በባልንጀራው ላይ ካለው ቅናት እንደሚመነጭ ተመለከትሁ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።” (መክብብ 4:4) በዓለም ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ለማግኘት ብዙ የለፉ በርካታ ግለሰቦች ይህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እውነት መሆኑን ይመሰክራሉ። ሰዎች ወደ ጨረቃ የመጠቁበትን መንኮራኩር ንድፍ በማውጣት፣ በመገንባትና ሙከራ በማካሄድ የሠራ አንድ ግለሰብ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። “ሥራዬን በትጋት አከናውኛለሁ እንዲሁም በሥራው እጅግ የተዋጣልኝ ሰው ለመሆን በቅቻለሁ። ሆኖም ሥራው ዘላቂ ደስታና የአእምሮ ሰላም በማስገኘት ረገድ አንዳች የፈየደልኝ ነገር የለም” ሲል ተናግሯል። a በንግዱም ሆነ በስፖርቱ ወይም በመዝናኛው መስክ ዓለም ለታላቅነት ያለው አመለካከት ዘላቂ እርካታ ሊያስገኝ አይችልም።
በፍቅር ተነሳስቶ ሌሎችን ከማገልገል የሚገኝ ታላቅነት
6. ያዕቆብና ዮሐንስ ታላቅ ስለ መሆን የተሳሳተ አመለካከት እንደነበራቸው እንዴት እናውቃለን?
6 በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የተከሰተ አንድ ሁኔታ በእርግጥ ታላቅነት ምን ማለት እንደሆነ ያሳያል። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የማለፍን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ናቸው። መንገድ ላይ ሳሉ የኢየሱስ የአክስቱ ልጆች የሆኑት ያዕቆብና ዮሐንስ ለታላቅነት ተገቢ ያልሆነ አመለካከት አንጸባረቁ። እናታቸውን በመላክ ለኢየሱስ ‘በመንግሥትህ አንዳችን በቀኝህ አንዳችን ደግሞ በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን’ የሚል ጥያቄ አቀረቡ። (ማቴዎስ 20:21) በአይሁዳውያን ዘንድ በቀኝ ወይም በግራ በኩል መቀመጥ እንደ ትልቅ ክብር ይቆጠራል። (1 ነገሥት 2:19) ያዕቆብና ዮሐንስ በጣም ተፈላጊ የሆኑትን ሁለቱን የሥልጣን ወንበሮች ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለመያዝ ጥረት አድርገዋል። ኢየሱስ ሐሳባቸው ስለገባው ታላቅ ስለ መሆን ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ለማረም አጋጣሚውን ተጠቀመበት።
7. ኢየሱስ በክርስትና ሕይወት ትክክለኛ ታላቅነት የሚገኝበትን መንገድ የገለጸው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ የኩራት መንፈስ በነገሠበት በዚህ ዓለም ታላቅ ተደርጎ የሚታየው ሌሎችን የሚቆጣጠርና የሚያዝዝ እንዲሁም ገና ከአፉ ሳይወጣ የፈለገው ነገር ወዲያውኑ የሚደረግለት ሰው እንደሆነ ያውቃል። በኢየሱስ ተከታዮች ዘንድ ግን የታላቅነት መለኪያው ትሕትና የሚጠይቅ ሥራ ማከናወን ነው። ኢየሱስ “ከእናንተ ትልቅ መሆን የሚፈልግ አገልጋያችሁ ይሁን፤ የበላይ ለመሆን የሚሻም የእናንተ የበታች ይሁን” አላቸው።—ማቴዎስ 20:26, 27
8. አገልጋይ መሆን ምን ማለት ነው? ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?
8 መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘አገልጋይ’ ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በትጋትና በጽናት ሌሎችን ለማገልገል ጥረት የሚያደርግን ሰው ያመለክታል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ አንድ አስፈላጊ ትምህርት ሰጥቷቸዋል:- ሰውን ታላቅ የሚያስብለው ሰዎችን ማዘዝ መቻሉ ሳይሆን ከፍቅር ተነሳስቶ ሌሎችን ማገልገሉ ነው። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘እኔ በያዕቆብ ወይም በዮሐንስ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን ምላሽ እሰጥ ነበር? አንድን ሰው ታላቅ የሚያስብለው በፍቅር ተነሳስቶ ሌሎችን ማገልገሉ ነው የሚለውን ትምህርት እቀበል ነበር?’—1 ቆሮንቶስ 13:3
9. ኢየሱስ ከሌሎች ጋር በነበረው ግንኙነት ምን ምሳሌ ትቶልናል?
9 ኢየሱስ ዓለም ለታላቅነት ያለው አመለካከት እርሱ በተግባር ካሳያቸው የተለየ መሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ ገለጸላቸው። ኢየሱስ ያገለግላቸው ከነበሩ ሰዎች የበላይ እንደሆነ አልተሰማውም ወይም ደግሞ እነርሱ የበታችነት እንዲሰማቸው አላደረገም። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንዲሁም ልጆች፣ ሀብታሞችም ሆኑ ድሆች እንዲሁም ባለ ሥልጣኖች አልፎ ተርፎም በመጥፎ ምግባራቸው የሚታወቁ ሰዎች ከእርሱ ጋር ሲሆኑ አይሸማቀቁም ነበር። (ማርቆስ 10:13-16፤ ሉቃስ 7:37-50) አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች አንዳንድ የባሕርይ ጉድለት የሚታይባቸውን ግለሰቦች በትዕግሥት መያዝ ይቸግራቸዋል። ኢየሱስ ግን እንደዚያ አልነበረም። ደቀ መዛሙርቱ አንዳንድ ጊዜ አሳቢነት ይጎድላቸውና እርስ በርሳቸው ይናቆሩ የነበረ ቢሆንም ትሕትናና የዋህነት በማሳየት በትዕግሥት አስተምሯቸዋል።—ዘካርያስ 9:9፤ ማቴዎስ 11:29፤ ሉቃስ 22:24-27
10. ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት በራቀ ስሜት ሌሎችን ማገልገሉን በአኗኗሩ ያሳየው እንዴት ነው?
10 ይህ የአምላክ አንድያ ልጅ የተወው የራስን ጥቅም የመሠዋት ምሳሌ ታላቅ መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ያሳያል። ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው እንዲገለገል ሳይሆን ሰዎችን ‘ከተለያየ በሽታ’ በማዳንና ከአጋንንት ተጽዕኖ በማላቀቅ ሌሎችን ለማገልገል ነበር። አንዳንድ ጊዜ ይደክመውና ማረፍ ይፈልግ የነበረ ቢሆንም ሰዎችን ለማጽናናት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ምንጊዜም ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ጥቅም አስቀድሟል። (ማርቆስ 1:32-34፤ 6:30-34፤ ዮሐንስ 11:11, 17, 33) ለሰዎች የነበረው ፍቅር እነርሱን በመንፈሳዊ ለመርዳት እንዲነሳሳ አድርጎታል። ለዚህም ሲል የአምላክን መንግሥት ለመስበክ በአቧራማ መንገዶች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተጉዟል። (ማርቆስ 1:38, 39) ኢየሱስ ሌሎችን ማገልገል በጣም አስፈላጊ ነገር እንደሆነ አድርጎ እንደተመለከተው ግልጽ ነው።
የክርስቶስን ትሕትና ኮርጁ
11. በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካቾች ሆነው እንዲያገለግሉ የሚሾሙ ወንድሞች ምን ባሕርያት እንዲያንጸባርቁ ይጠበቅባቸዋል?
11 በ1800ዎቹ ማብቂያ ላይ ወንድሞች የአምላክን ሕዝቦች ፍላጎት ለማሟላት ተጓዥ ተወካዮች ሆነው እንዲያገለግሉ በሚመረጡበት ጊዜ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ሊያዳብሩት የሚገባ ትክክለኛ መንፈስ ተገልጾ ነበር። የጽዮን መጠበቂያ ግንብ በመስከረም 1, 1894 እትሙ ላይ ለዚህ ኃላፊነት የሚፈለጉት “የዋህ ከመሆናቸው የተነሳ የኩራት መንፈስ የማይታይባቸው . . . ራሳቸውን ሳይሆን ክርስቶስን የሚሰብኩ ትሑታን፣ የራሳቸውን እውቀት ከመግለጽ ይልቅ ግልጽና አሳማኝ የሆነውን የአምላክን ቃል የሚያስተምሩ” ወንዶች እንደሆኑ ገልጾ ነበር። እውነተኛ ክርስቲያኖች የራሳቸውን ፍላጎት ለማርካት ወይም ታዋቂነትና ሥልጣን ለማግኘት እንዲሁም ሌሎችን ለመቆጣጠር ብለው የኃላፊነት ቦታ ለመያዝ መፈለግ እንደሌለባቸው ግልጽ ነው። ትሑት የሆነ አንድ የበላይ ተመልካች የኃላፊነት ቦታው “መልካም ሥራ” ለመሥራት እንጂ ክብር እንዲያገኝ ተብሎ የተሰጠው ማዕረግ አለመሆኑን ያስታውሳል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ሌሎችን በትሕትና ለማገልገል እንዲሁም ሌሎች ሊከተሉት የሚገባ ጥሩ ምሳሌ በመተው በአገልግሎት ግንባር ቀደም ሆነው ለመገኘት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ማድርግ ይኖርባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 9:19፤ ገላትያ 5:13፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:5
12. በጉባኤ ውስጥ አንዳንድ መብቶች ለማግኘት የሚጣጣሩ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ምን ብለው መጠየቅ ይችላሉ?
12 በጉባኤ ውስጥ የአገልግሎት መብቶች ለማግኘት የሚጣጣር ማንኛውም ወንድም ራሱን እንዲህ ብሎ ሊጠይቅ ይገባል:- ‘ሌሎችን ማገልገል የምችልበት አጋጣሚ ለማግኘት እጠባበቃለሁ ወይስ በሌሎች የመገልገል ፍላጎት አለኝ? ሌሎች ባያውቁልኝም ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎች ለማከናውን ፈቃደኛ ነኝ?’ ለምሳሌ ያህል አንድ ወጣት በጉባኤ ውስጥ ንግግር ለማቅረብ ፈቃደኛ ቢሆንም አንድን አረጋዊ ክርስቲያን እንዲረዳ ሲጠየቅ ያቅማማ ይሆናል። በጉባኤ ውስጥ ካሉ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ጋር መሆን ያስደስተው ይሆናል፣ በሌላ በኩል ግን በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ደስተኛ ላይሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያለው ወጣት ራሱን እንዲህ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው:- ‘ትኩረት የማደርገው በሌሎች ዘንድ ታዋቂነትና ምስጋና በሚያስገኙልኝ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ነው? ጥረቴ በሌሎች ዘንድ ታዋቂነት ማትረፍ ነው?’ ለራስ ክብር መፈለግ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንዳልሆነ ግልጽ ነው።—ዮሐንስ 5:41
13. (ሀ) አንድ የበላይ ተመልካች በትሕትና ረገድ ምሳሌ መሆኑ በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል? (ለ) ትሕትና ወይም ራስን ዝቅ ማድረግ ለምርጫ የተተወ ጉዳይ አይደለም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
13 ክርስቶስ ያሳየውን ትሕትና ለመኮረጅ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ሌሎችን ለማገልገል እንነሳሳለን። አንድ የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮ የሥራ እንቅስቃሴ በመገምገም ላይ የነበረ የዞን የበላይ ተመልካች ያደረገውን ነገር ተመልከት። ይህ የበላይ ተመልካች በጣም ሥራ የሚበዛበትና ከፍተኛ ኃላፊነት የተሸከመ ቢሆንም የጽሑፍ መስፊያ ማሽኑ ትክክለኛ ቦታ ላይ እንዲያርፍ ለማድረግ ይታገል የነበረን ወጣት ወንድም ለመርዳት ጊዜውን ሰውቷል። ይህ ወጣት ወንድም “ሁኔታውን ማመን ነው ያቃተኝ!” በማለት የተደረገለትን ነገር ያስታውሳል። “በወጣትነት ዕድሜው በቤቴል ሲያገለግል የዚሁ ዓይነት ማሽን ላይ ይሠራ እንደነበርና ሽቦውን ትክክለኛው ቦታ ላይ ለመምታት በጣም አዳጋች እንደሆነ ነገረኝ። ሌሎች በርካታ አንገብጋቢ ሥራዎች የነበሩት ቢሆንም ረዘም ላለ ጊዜ ማሽኑ ላይ አብሮኝ ሠራ። እንዲህ ማድረጉ በጣም ነበር ያስደነቀኝ።” በአሁኑ ጊዜ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሥራ ኃላፊ ሆኖ የሚያገለግለው ይህ ወንድም የዞን የበላይ ተመልካቹ ያሳየውን ትሕትና እስካሁን ድረስ ያስታውሳል። ትሕትና የሚጠይቁ ሥራዎችን መሥራት እንደሌለብን ወይም ተራ የሚመስሉ ሥራዎች ክብራችንን እንደሚነኩ ሊሰማን አይገባም። ከዚህ ይልቅ “ትሕትና” መላበስ ይኖርብናል። ይህ ለግል ምርጫ የተተወ ጉዳይ አይደለም። ትሕትና አንድ ክርስቲያን ሊላበሰው የሚገባ ‘የአዲሱ ሰው’ ክፍል ነው።—ፊልጵስዩስ 2:3፤ ቆላስይስ 3:10, 12፤ ሮሜ 12:16
ክርስቶስ ለታላቅነት የነበረው ዓይነት አመለካከት ማዳበር
14. ከአምላክና ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ማሰላሰላችን ስለ ታላቅነት ትክክለኛ አመለካከት እንድናዳብር ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
14 ለታላቅነት ትክክለኛውን አመለካከት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ ከይሖዋ አምላክ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ማሰላሰል ነው። ክብሩ፣ ኃይሉና ጥበቡ ደካማ የሆኑ የሰው ልጆች ካሉበት ሁኔታ እጅግ የላቀ ያደርገዋል። (ኢሳይያስ 40:22) እንደ እኛ ካሉ ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ማሰላሰላችንም ትሕትና እንድናዳብር ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ መስኮች ከሌሎች የተሻልን ልንሆን እንችላለን፤ ሆኖም ክርስቲያን ወንድሞቻችን በጣም አስፈላጊ በሆኑ የሕይወት ዘርፎች ከእኛ የበለጡ ሊሆኑ ወይም እኛ የሚጎድሉን አንዳንድ ባሕርያት ሊኖሯቸው ይችላሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ በአምላክ ፊት ውድ የሆኑ በርካታ ክርስቲያኖች ልካቸውን የሚያውቁና ትሑት ከመሆናቸው የተነሳ ከሌሎች ልቀው መታየት አይፈልጉም።—ምሳሌ 3:34፤ ያዕቆብ 4:6
15. የአምላክ ሕዝቦች ያሳዩት ጽናት ማንም ሰው ቢሆን ከሌሎች እበልጣለሁ የሚልበት መሠረት እንደሌለው የሚያሳየው እንዴት ነው?
15 የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ስለደረሰባቸው ፈተና የሚገልጹ ተሞክሮዎች ይህን ነጥብ በሚገባ ያሳያሉ። በተደጋጋሚ እንደታየው ከባድ ፈተና ሲደርስባቸው ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት ሳያጎድፉ የኖሩት በዓለም ዓይን ሲታዩ ተራ ሰዎች ተደርገው የሚቆጠሩት ናቸው። እንደዚህ ባሉ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችን ትሑት እንድንሆንና ‘ከሆንነው በላይ ራሳችንን ከፍ አድርገን እንዳናስብ’ ትምህርት እንድናገኝ ያስችለናል።—ሮሜ 12:3 b
16. በጉባኤ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ሰው የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ታላቅነትን ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው?
16 ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች፣ ሁሉም ክርስቲያኖች ታላቅነትን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በጉባኤ ውስጥ መከናወን ያለባቸው የተለያዩ ዓይነት ሥራዎች አሉ። ዝቅተኛ የሚመስሉ ሥራዎችን እንድንሠራ ብንጠየቅ ቅር መሰኘት የለብንም። (1 ሳሙኤል 25:41፤ 2 ነገሥት 3:11) ወላጆች፣ ልጆቻችሁ የጉባኤ፣ የልዩ፣ የወረዳ ወይም የአውራጃ ስብሰባዎች በሚካሄዱባቸው ቦታዎች ምንም ዓይነት ሥራ ቢሰጣቸው በደስታ እንዲያከናውኑት ታበረታቷቸዋላችሁ? ትሕትና የሚጠይቁ ሥራዎችን ስትሠሩ አይተው ያውቃሉ? በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚያገለግል አንድ ወንድም የወላጆቹ ምሳሌ በደንብ ትዝ ይለዋል። እንዲህ ይላል:- “ወላጆቼ የመንግሥት አዳራሽ ወይም አውራጃ ስብሰባ የምናደርግበትን ቦታ በማጽዳት ሥራ የሚያደርጉት ተሳትፎ ሥራውን ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት እንድገነዘብ አስችሎኛል። ሥራዎቹ በጣም ዝቅተኛ ተደርገው የሚታዩ ቢሆኑም እንኳ ለጉባኤው ወይም ለወንድሞች የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለማከናወን ፈቃደኛ ነበሩ። ለሥራ ያላቸው አመለካከት ቤቴል ውስጥ ማንኛውንም ሥራ በደስታ እንድቀበል አስችሎኛል።”
17. ትሑት የሆኑ እህቶች ለጉባኤው በረከት መሆን የሚችሉት በምን መንገዶች ነው?
17 በአምስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በፋርስ ግዛት ውስጥ ንግሥት የነበረችው አስቴር ከራሳችን ይልቅ የሌሎችን ጥቅም ማስቀደምን በተመለከተ ግሩም ምሳሌ ትታልናለች። የምትኖረው ቤተ መንግሥት ውስጥ ቢሆንም እንኳ ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕዝቦቹን ለማዳን ስትል ሕይወቷን አደጋ ላይ ጥላለች። (አስቴር 1:5, 6፤ 4:14-16) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሴቶች የገንዘብ አቅማቸው ምንም ይሁን ምን ያዘኑትን በማጽናናት፣ የታመሙትን በመጠየቅ፣ በስብከቱ ሥራ በመካፈልና ከሽማግሌዎች ጋር በመተባበር የአስቴር ዓይነት መንፈስ ማንጸባረቅ ይችላሉ። እንዲህ የመሰሉ ትሑት እህቶች ለጉባኤው ትልቅ በረከት ናቸው!
ሌሎችን ማገልገል የሚያስገኛቸው በረከቶች
18. ክርስቶስ ለታላቅነት የነበረው ዓይነት አመለካከት ማዳበር ምን ጥቅሞች ያስገኛል?
18 ታላቅነትን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ካለህ ብዙ ጥቅሞች ታገኛለህ። ራስህን ሳትቆጥብ ሌሎችን ማገልገልህ ለእነርሱም ሆነ ለአንተ ደስታ ያስገኛል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ወንድሞችህን በፈቃደኝነትና በትጋት ማገልገልህ በእነርሱ ዘንድ ተወዳጅ እንድትሆን ያስችልሃል። (የሐዋርያት ሥራ 20:37) ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ ክርስቲያን ባልንጀሮችህን ለመጥቀም የምታከናውነውን አገልግሎት ለእርሱ የቀረበ አስደሳች የምስጋና መሥዋዕት አድርጎ ይመለከተዋል።—ፊልጵስዩስ 2:17
19. ክርስቶስ ስለ ታላቅነት የነበረውን አመለካከት በተመለከተ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?
19 እያንዳንዳችን ልባችንን መመርመርና ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘ክርስቶስ ስለ ታላቅነት የነበረውን አመለካከት በማዳበር ረገድ በወሬ ብቻ አቆማለሁ ወይስ በተግባር ለማዋል ትጋት የተሞላበት ጥረት አደርጋለሁ?’ ይሖዋ ለትዕቢተኞች ያለው አመለካከት ግልጽ ነው። (ምሳሌ 16:5፤ 1 ጴጥሮስ 5:5) በክርስቲያን ጉባኤም ሆነ በቤተሰብ ሕይወታችን እንዲሁም ከሌሎች ጋር ባለን ዕለታዊ ግንኙነት ማንኛውንም ነገር ለአምላክ ክብርና ውዳሴ እናድርግ። እንዲሁም ታላቅነትን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አመለካከት በማዳበር እንደምንደሰት በተግባር የምናሳይ ሰዎች ለመሆን ያብቃን።—1 ቆሮንቶስ 10:31
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የግንቦት 1, 1982 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 3-6 ላይ “ስኬት ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት” (እንግሊዝኛ) የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምሥክሮች በኢትዮጵያ—ነፃነት አፍቃሪዎች የተባለውን ብሮሹር ገጽ 38ን እና የመስከረም 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 27-31ን ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህ?
• ዓለም ለታላቅነት ያለውን አመለካከት ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?
• ኢየሱስ ለታላቅነት የነበረው አመለካከት ምንድን ነው?
• የበላይ ተመልካቾች ክርስቶስ ያሳየውን ትሕትና መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?
• ክርስቶስ ለታላቅነት የነበረውን አመለካከት እንድናዳብር ምን ሊረዳን ይችላል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ታላቅነትን በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ያለው ማን ነው?
በሌሎች መገልገል የሚፈልግ ወይስ ሌሎችን ማገልገል የሚፈልግ?
ታዋቂነት የሚያስገኝለት ሥራ የሚፈልግ ወይስ ትሕትና የሚጠይቁ ሥራዎችን የሚያከናውን?
ራሱን ከሌሎች የሚያስበልጥ ወይስ ሌሎች እንደሚበልጡት የሚያስብ?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የፈርዖን አሜንሆቴፕ ሣልሳዊ ግዙፍ ሐውልት
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሐማን ለውድቀት የዳረገው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሌሎችን ማገልገል የምትችልባቸው አጋጣሚዎች ለማግኘት ትፈልጋለህ?