በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከይሖዋ በምናገኘው ብርታት ታምነናል

ከይሖዋ በምናገኘው ብርታት ታምነናል

የሕይወት ታሪክ

ከይሖዋ በምናገኘው ብርታት ታምነናል

ኤርዛቤት ሃፍነር እንደተናገረችው

ቲቦር ሃፍነር ቼኮዝሎቫኪያን ለቅቄ እንድወጣ መታዘዜን ሲሰማ “ከአገር ሲያባርሩሽ ዝም ብዬ አላይም፤ የምትስማሚ ከሆነ አገባሽና ከእኔ ጋር ለዘላለም ትኖሪያለሽ” አለኝ።

ይህ ድንገተኛ የጋብቻ ጥያቄ ከቀረበልኝ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ጥር 29, 1938፣ ለቤተሰቤ በመጀመሪያ እውነትን የነገራቸውን ቲቦር የተባለ ክርስቲያን ወንድም አገባሁ። ይህን ውሳኔ ማድረግ ቀላል አልነበረም። ገና የ18 ዓመት ወጣት የነበርኩ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንደመሆኔ በወጣትነት ዕድሜዬ በሙሉ ልብ አምላክን ለማገልገል እፈልግ ነበር። እያነባሁ በጸሎት ይሖዋን ጠየቅኩት። ከተረጋጋሁ በኋላ ግን ቲቦር እንዳገባው የጠየቀኝ እንዲያው በደግነት ተነሳስቶ ሊረዳኝ ብቻ ሳይሆን ከልብ ስለሚወደኝ እንደሆነና ከእርሱ ጋር ለመኖር እንደምፈልግ ተገነዘብኩ።

ይሁን እንጂ በዲሞክራሲያዊ አስተዳደሩና ሃይማኖታዊ ነጻነት በመስጠቱ በሚኩራራ አገር ውስጥ እየኖርኩ ካገር ልባረር የነበረው ለምንድን ነው? ይህን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት ግን ስለ አስተዳደጌ ትንሽ ልንገራችሁ።

የተወለድኩት ታኅሣሥ 26, 1919 ከቡዳፔስት በስተ ምሥራቅ 160 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ ሻዮሰንትፒተር በምትባል ሃንጋሪ ውስጥ የምትገኝ መንደር ሲሆን ወላጆቼ የግሪክ ካቶሊኮች ነበሩ። የሚያሳዝነው አባቴ የሞተው ከመወለዴ በፊት ነበር። ብዙም ሳይቆይ እናቴ ሚስቱ የሞተችበትን የአራት ልጆች አባት አገባችና በወቅቱ በቼኮዝሎቫኪያ ግዛት ውስጥ ወደነበረችው ሉቼኔዝ የተባለች የተዋበች ከተማ ተዛወርን። በዚያ ዘመን ከእንጀራ ወላጅ ጋር መኖር ቀላል አልነበረም። የሁሉም ልጆች ታናሽ ስለነበርኩ የቤተሰቡ አባል እንዳልሆንኩ ይሰማኝ ነበር። የኑሮው ሁኔታ በጣም ከባድ ከመሆኑም በተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮቸ ብቻ ሳይሆን የወላጅ ፍቅርና እንክብካቤም ተነፍጎኝ ነበር።

ለጥያቄዎቼ መልስ መፈለግ

አሥራ ስድስት ዓመት ሲሞላኝ በርካታ ጥያቄዎች አእምሮዬን ያስጨንቁት ነበር። ስለ አንደኛው የዓለም ጦርነት በከፍተኛ ጉጉት አነብብ የነበረ ሲሆን ክርስቲያን ነን የሚሉ የሰለጠኑ ሕዝቦች ያን ያህል እርስ በርስ መገዳደላቸው ያስገርመኝ ነበር። ከዚህም በላይ በሁሉም ቦታ ለጦርነት የመዘጋጀት አዝማሚያ ይታይ ነበር። ይህ ሁሉ ባልንጀራን ስለመውደድ በቤተ ክርስቲያን ከተማርኩት ጋር ጨርሶ አልጣጣም አለኝ።

እናም ወደ አንድ የሮማ ካቶሊክ ቄስ ሄድኩና “ክርስቲያኖች ልንመራበት የሚገባው ሕግ የቱ ነው? ባልንጀሮቻችንን መውደድ ወይስ ወደ ጦርነት ዘምቶ እነርሱን መግደል?” በማለት ጠየቅዃቸው። በጥያቄዬ ተበሳጭተው የሚያስተምሩት ከበላይ የተነገራቸውን እንደሆነ ነገሩኝ። ለአንድ የካልቪኒስት አገልጋይና ለአንድ የአይሁድ ረቢም ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረብኩላቸው። እነርሱም ያልተለመደ ጥያቄ በመጠየቄ ከመገረማቸው በስተቀር ምንም መልስ አልሰጡኝም። በመጨረሻ ወደ አንድ የሉተራን አገልጋይ ሄድኩ። ጥያቄዬ አናደዳቸው፤ ሆኖም ከመሄዴ በፊት “በእርግጥ ለጥያቄሽ መልስ ለማግኘት የምትፈልጊ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮችን ጠይቂ” አሉኝ።

የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልጌ ለማግኘት ያደረግኩት ጥረት አልተሳካም። ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ከሥራ ወደ ቤት ስመለስ በሩን በከፊል ገርበብ ብሎ አገኘሁት። አንድ መልከ ቀና ወጣት ለእናቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ እያነበበላት ነበር። ‘የይሖዋ ምሥክር መሆን አለበት!’ የሚል ሐሳብ በአእምሮዬ ብልጭ አለ። ቲቦር ሃፍነር ተብሎ የሚጠራውን ይህን ወጣት ወደ ቤት እንዲገባ ጋበዝነውና የተለመደውን ጥያቄዬን ለእርሱም አቀረብኩለት። መልሱን ከራሱ ከመናገር ይልቅ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምን መሆን እንዳለበትና ስለምንኖርበት ዘመን ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየኝ።—ዮሐንስ 13:34, 35፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

ከጥቂት ወራት በኋላ ገና 17 ዓመት ሳይሞላኝ ተጠመቅኩ። በብዙ ድካም ያገኘሁትን ይህን ውድ እውነት ሁሉም ሰው መስማት እንዳለበት ስለተሰማኝ በሙሉ ጊዜዬ በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመርኩ። ሆኖም በ1930ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በቼኮዝሎቫኪያ እንዲህ ማድረግ ቀላል አልነበረም። የስብከቱ ሥራችን ሕጋዊ እውቅና ቢኖረውም በቀሳውስት ቆስቋሽነት ከፍተኛ ተቃውሞ ይሰነዘርብን ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመኝ ስደት

በ1937 ማገባደጃ አካባቢ አንድ ቀን ከአንዲት እህት ጋር ሆነን በሉቼኔዝ አቅራቢያ ባለች መንደር እያገለገልን ነበር። ብዙም ሳንቆይ ተያዝንና ወደ እስር ቤት ተወሰድን። የእስር ቤቱ ጠባቂ “እዚችው ትሞቷታላችሁ” አለና አንድ ክፍል ውስጥ አስገብቶ በሩን በኃይል ጠረቀመብን።

ምሽት ላይ ሌሎች አራት እስረኞች የተጨመሩ ሲሆን እያጽናናናቸው ምሥራቹን እንሰብክላቸው ጀመር። እነርሱም ተረጋጉና ሌሊቱን ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስንነግራቸው አደርን።

ማለዳ 12:00 ላይ ጠባቂው ካለሁበት ክፍል ጠራኝ። አብራኝ ለነበረችው እህት “በአምላክ መንግሥት ዳግመኛ እንገናኛለን” አልኳትና በሕይወት ከተረፈች ስለሁኔታው ለቤተሰቦቼ እንድትነግራቸው ጠየቅኳት። ከዚያም በልቤ ጸሎት አቀረብኩና ጠባቂውን ተከትዬ ሄድኩ። በእስር ቤቱ አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ወሰደኝ። “አንዳንድ ልጠይቅሽ የምፈልጋቸው ጥያቄዎች አሉኝ። ትላንት ማታ የአምላክ ስም ይሖዋ ነው ስትይ ሰምቼ ነበር። ከመጽሐፍ ቅዱስ ልታሳይኝ ትችያለሽ?” አለኝ። ምን ያህል እንደተገረምኩና እፎይታ እንደተሰማኝ ገምቱ! የራሱን መጽሐፍ ቅዱስ አመጣና ይሖዋ የሚለውን ስም ለእርሱና ለባለቤቱ አሳየኋቸው። ሌሊቱን ከአራቱ ሴቶች ጋር በተወያየንባቸው ርዕሶች ላይ በርካታ ጥያቄዎች ነበሩት። በሰጠሁት መልስ ስለረካ ባለቤቱ ለእኔና ለአገልግሎት ጓደኛዬ ቁርስ እንድታዘጋጅልን ነገራት።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ተለቀቅን፤ ሆኖም ዳኛው ሃንጋሪያዊ በመሆኔ ቼኮዝሎቫኪያን ለቅቄ መውጣት እንዳለብኝ ወሰኑ። በዚህ ወቅት ነበር ቲቦር ሃፍነር እንዳገባው የጠየቀኝ። ከዚያም ተጋባንና በወላጆቹ ቤት መኖር ጀመርን።

ስደቱ እየጠነከረ ሄደ

ቲቦር የስብከት እንቅስቃሴውን የማደራጀት ኃላፊነት ቢኖርበትም በጋራ ሆነን በስብከቱ ሥራ መካፈል ቀጠልን። የሃንጋሪ ወታደሮች በኅዳር 1938 ከተማችንን ከመቆጣጠራቸው ከጥቂት ቀናት በፊት ቲቦር ጁኒየር የተባለው ወንድ ልጃችን ተወለደ። በአውሮፓ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እያንዣበበ ነበር። አብዛኛው የቼኮዝሎቫኪያ ክፍል በሃንጋሪ ቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረ ሲሆን በዚያ አካባቢ በሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚደርሰው ስደትም ይበልጥ ተፋፍሞ ነበር።

ጥቅምት 10, 1942 ቲቦር ከተወሰኑ ወንድሞች ጋር ለመገናኘት ወደ ዴብሪትሰን ሄደ። ይሁን እንጂ ወደ ቤት አልተመለሰም። ከጊዜ በኋላ ያጋጠመውን ሁኔታ ነግሮኛል። ከወንድሞች ጋር በተቀጣጠሩበት ድልድይ ላይ ያገኘው ወንድሞችን ሳይሆን የሲቪል ልብስ የለበሱ ፖሊሶችን ነበር። ፖሊሶቹ በቦታው ለመድረስ የመጨረሻ የሆኑትን ባለቤቴንና ፓል ናጅፓል የተባለውን ወንድም ለመያዝ እየጠበቁ ነበር። ከዚያ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸውና ከሕመሙ የተነሳ ራሳቸውን እስኪስቱ ድረስ ውስጥ እግራቸውን በዱላ ገረፏቸው።

ከዚያ ጫማዎቻቸውን አጥልቀው እንዲቆሙ አዘዟቸውና እንደዚያ እያመማቸው ወደ ባቡር ጣቢያው በእግራቸው እንዲሄዱ አስገደዷቸው። ፖሊሶቹ ማየት እስኪያቅተው ድረስ ራሱ በፋሻ የተጠቀለለ አንድ ሌላ ሰውም ይዘው መጡ። ይህ ሰው ከወንድሞች ጋር ለመገናኘት ወደ ቀጠሮው ቦታ የመጣው ወንድም አንድራሽ ፒሊንክ ነበር። ባለቤቴ በቡዳፔስት አቅራቢያ አላግ በተባለች መንደር ወደሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ማቆያ ጣቢያ ተወሰደ። ከጠባቂዎቹ አንዱ የቲቦርን ክፉኛ የተደበደበ እግር ሲመለከት በማፌዝ “አንዳንድ ሰዎች እንዴት ጨካኝ ናቸው! አይዞህ እኛ እንፈውስሃለን” አለው። ከዚያ ሁለት ጠባቂዎች ደሙ ዙሪያውን እስኪፈናጠቅ ድረስ ውስጥ እግሩን ይገርፉት ጀመር። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ራሱን ሳተ።

በሚቀጥለው ወር ቲቦርና ሌሎች ከ60 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ለፍርድ ቀረቡ። ወንድም አንድራሽ ባርታ፣ ዴነሽ ፋሉቬጊ እና ያኖሽ ኮንራድ በስቅላት እንዲገደሉ ተፈረደባቸው። ወንድም አንድራሽ ፒሊንክ የዕድሜ ልክ እስራት የተበየነበት ሲሆን ባለቤቴ ደግሞ 12 ዓመት ተፈረደበት። የፈጸሙት ወንጀል ምን ነበር? ዐቃቤ ሕጉ ያቀረበው ክስ አገርን መክዳት፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን፣ ስለላና ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን መሳደብ የሚል ነበር። ከጊዜ በኋላ የሞት ፍርዶቹ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተለወጡ።

የባለቤቴ እጣ ገጠመኝ

ቲቦር ወደ ዴብሪትሰን ከሄደ ከሁለት ቀናት በኋላ ማለዳ ከአሥራ ሁለት ሰዓት በፊት ተነስቼ ልብሶቻችንን እየተኮስኩ ነበር። በድንገት በሩ በኃይል ተንኳኳ። ‘መጡ ማለት ነው’ ብዬ አሰብኩ። ከዚያም ስድስት ፖሊሶች ተከታትለው ገቡና ቤቱን ለመፈተሽ ፈቃድ እንዳላቸው ነገሩኝ። የሦስት ዓመት ልጃችንን ጨምሮ በቤቱ ውስጥ የነበርነው ሁሉ በቁጥጥር ሥር ውለን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድን። የዚያኑ ዕለት በፒተርቫሻራ፣ ሃንጋሪ ወደሚገኝ እስር ቤት ተዛወርን።

እዚያ ስንደርስ ትኩሳት ስለያዘኝ ከሌሎች እስረኞች ነጠሉኝ። ትኩሳቱ ተሽሎኝ ስነቃ ሁለት ወታደሮች የታሰርኩበት ክፍል ውስጥ ቆመው ይጨቃጨቁ ነበር። አንደኛው “ልንገድላት ይገባል! እኔ በጥይት እመታታለሁ!” ይላል። ሌላኛው ግን ምንም ነገር ከማድረጋቸው በፊት የጤንነቴን ሁኔታ ለማረጋገጥ ፈልጎ ነበር። እንዳይገሉኝ ተማጸንኳቸው። በመጨረሻ ከክፍሌ ወጥተው ሲሄዱ ይሖዋን ስለረዳኝ አመሰገንኩት።

ጠባቂዎቹ ልዩ የምርመራ ዘዴ ይጠቀሙ ነበር። በደረቴ መሬት ላይ እንድተኛ ያዝዙኝና እጆቼንና እግሮቼን ካሠሩ በኋላ አፌ ውስጥ ካልሲ ጠቅጥቀው ደም በደም እስክሆን ድረስ ይገርፉኛል። የሚያቆሙት አንደኛው ወታደር ደከመኝ ሲል ብቻ ነበር። ባለቤቴ በታሰረበት ዕለት ቀጠሮ የነበረው ከማን ጋር እንደሆነ ይጠይቁኛል። ምንም ስላልነገርኳቸው ድብደባው ለሦስት ቀናት ቀጠለ። በአራተኛው ቀን ልጄን ወደ እናቴ እንድወስድ ተፈቀደልኝ። አጥንት ድረስ ዘልቆ በሚሰማው ቅዝቃዜ ልጄን በቆሰለው ጀርባዬ ላይ አዝዬ እስከ ባቡር ጣቢያው ድረስ 13 ኪሎ ሜትር በእግሬ ተጓዝኩ። ከዚያም በባቡር ወደ ቤት ሄድኩ፤ ሆኖም የዚያኑ ቀን ወደ ካምፑ መመለስ ነበረብኝ።

በቡዳፔስት በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ስድስት ዓመት እንድታሰር ተረፈደብኝ። እዚያ ስደርስ ቲቦርም የታሠረው በዚያ መሆኑን አወቅኩ። በሽቦ አጥር መሃል ለጥቂት ደቂቃዎች እንድንነጋገር ሲፈቀድልን ምን ያህል እንደተደሰትን ገምቱ! ሁለታችንም ይሖዋ እንደሚወደን የተሰማን ሲሆን እንዲህ ያለ ውድ አጋጣሚ በማግኘታችን ተበረታታን። ይሁን እንጂ ዳግመኛ ከመገናኘታችን በፊት ሁለታችንም ለመግለጽ የሚያዳግቱ መከራዎች ያጋጠሙን ሲሆን በተደጋጋሚ ጊዜያት ከሞት ለጥቂት ተርፈናል።

ከወኅኒ ቤት ወደ ወኅኒ ቤት መንከራተት

በአንድ ክፍል ውስጥ የታጎርነው በግምት ወደ 80 የምንሆን እህቶች ነበርን። መንፈሳዊ ምግብ ለማግኘት እንመኝ የነበረ ቢሆንም ወደ ወኅኒ ቤቱ ምንም ነገር ማስገባት የሚቻል አይመስልም ነበር። ታዲያ ከእስር ቤቱ ውስጥ የሆነ ነገር ማግኘት እንችል ይሆን? ምን እንዳደረግን ልንገራችሁ። ለወኅኒ ቤቱ ሠራተኞች ካልሲያቸውን ልጠግንላቸው ፈቃደኛ መሆኔን ነገርኳቸው። ከዚያም በወኅኒው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስ ማውጫ ቁጥር እንዲነግሩኝ በቁራጭ ወረቀት ላይ ጻፍኩና በአንዱ ካልሲ ውስጥ አድርጌ ላክሁት። እንዳይጠራጠሩኝ ለማድረግ የሌሎች ሁለት መጻሕፍት ስሞችም አከልኩበት።

በሚቀጥለው ቀን ከሠራተኞቹ ተጨማሪ የሚጠገኑ ካልሲዎች ደረሱኝ። በአንዱ ካልሲ ውስጥ የጥያቄዬን መልስ አገኘሁ። ከዚያም ለአንድ ጠባቂ ቁጥሮቹን ሰጠሁትና መጽሐፎቹን እንዲያመጣልኝ ጠየቅኩት። መጽሐፍ ቅዱሱን ጨምሮ መጽሐፎቹን ሲያመጣልን ምን ያህል እንደተደሰትን ገምቱ! ሌሎቹን መጻሕፍት በየሳምንቱ የምንቀይራቸው ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሱን ግን ከእኛ ጋር እናቆየዋለን። ጠባቂው ስለ መጽሐፍ ቅዱሱ ሲጠይቀን “ትልቅ መጽሐፍ ነው፤ ደግሞም ሁሉም ሰው ሊያነበው ይፈልጋል” እንለዋለን። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ችለን ነበር።

አንድ ቀን አንድ መኮንን ወደ ቢሮው እንድመጣ ጋበዘኝ። ቢሮው ስገባ ያለ ወትሮው ትሑት ሆነብኝ።

“ሚስስ ሃፍነር፣ ጥሩ ዜና ልነግርሽ ነው። ነገ ወደ ቤትሽ ትሄጃለሽ። ባቡር ከተገኘ ዛሬም ልትሄጂ ትችያለሽ” አለኝ።

“ይህማ በጣም ጥሩ ነው” ስል መለስኩለት።

“ምን ጥያቄ አለው። ልጅ አለሽ፤ ልታሳድጊው እንደምትፈልጊ እርግጠኛ ነኝ” አለኝ። ከዚያም “ብቻ እዚህ ደብዳቤ ላይ ፈርሚ” አለ።

“የምን ደብዳቤ ነው?” በማለት ጠየቅኩት።

“ስለ እርሱ አትጨነቂ፤ ዝም ብለሽ ፈርሚና መሄድ ትችያለሽ” በማለት ሊያግባባኝ ሞከረ። “እቤት ከደረስሽ በኋላ የፈለግሽውን ማድረግ ትችያለሽ። ብቻ ከአሁን በኋላ የይሖዋ ምሥክር አይደለሁም ብለሽ መፈረም አለብሽ” አለኝ።

ወደ ኋላ አፈገፈግሁና እንደማልፈርም ቁርጥ አድርጌ ነገርኩት።

“እንግዲያው እዚችው ትሞቻታለሽ!” ሲል በንዴት ጮኸብኝና ወደ ክፍሌ ላከኝ።

በግንቦት 1943 በቡዳፔስት ወደሚገኝ ሌላ ወኅኒ ቤት ተዛወርኩ፤ ከዚያ ደግሞ ማሪያኖስትራ ወደተባለች መንደር ተወስደን በግምት 70 ከሚያክሉ መነኮሳት ጋር በአንድ ገዳም ውስጥ መኖር ጀመርን። ምንም እንኳን ረሃብና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩብንም ስለ ወደፊቱ ተስፋችን ለእነርሱ ለመንገር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረን። ከመነኩሲቶቹ አንዷ ለምንነግራት ነገር ልባዊ ፍላጎት እያደረባት በመሄዱ “በጣም ደስ የሚል ትምህርት ነው። እንዲህ ያለ ነገር ሰምቼ አላውቅም። እባካችሁ በደንብ ንገሩኝ” አለችን። ስለ አዲሱ ዓለምና በዚያ ስለሚኖረው አስደሳች ሕይወት እየነገርናት ሳለ የገዳሙ እመምኔት መጡ። ለምሥራቹ ፍላጎት አሳይታ የነበረችውን መነኩሲት ወዲያውኑ ይዘዋት ሄዱና ልብሷን አስወልቀው በአለንጋ ክፉኛ ገረፏት። በሌላ ጊዜ ስንገናኝ ይህች መነኩሲት “እባካችሁ ከዚህ ወጥቼ መዳን እንድችል እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ ጸልዩልኝ። እንደ እናንተ መሆን እፈልጋለሁ” አለችን።

ቀጥሎ ከቡዳፔስት 80 ኪሎ ሜትር ርቃ በዳንዩብ ወንዝ አጠገብ በምትገኝ ኮማሮም በተባለች ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ አሮጌ ወኅኒ ቤት ተወሰድን። በዚያ መኖር በጣም አስቸጋሪ ነበር። እኔና ሌሎች በርካታ እህቶች በተስቦ በሽታ የተያዘን ሲሆን ሰውነቴ በጣም ከመዳከሙም በላይ ደም ያስመልሰኝ ጀመር። ምንም መድኃኒት አልነበረንም። በቃ መሞቴ ነው ብዬ አሰብኩ። ይሁን እንጂ መኮንኖቹ የቢሮ ሥራ መሥራት የሚችል ሰው ማፈላለግ ሲጀምሩ እህቶች እኔን ጠቆሟቸው። ከዚያም መድኃኒት ተሰጠኝና ለማገገም ቻልኩ።

ከቤተሰቤ ጋር ተቀላቀልኩ

የሶቪየት ጦር ከምሥራቅ እየቀረበ ሲመጣ ወደ ምዕራብ ለመጓዝ ተገደድን። ያጋጠመንን የሚዘገንን ሁኔታ ሁሉ ዘርዝሮ ለመጨረስ ረጅም ጊዜ ይወስዳል። በብዙ አጋጣሚዎች ለሞት ተቃርቤ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ ባደረገልኝ ጥበቃ ልተርፍ ችያለሁ። ጦርነቱ ሲጠናቀቅ ከፕራግ 80 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ታቦር የተባለች የቼኮዝሎቫኪያ ከተማ ውስጥ ነበርን። እኔና ማግዳሌና የተባለችው የባለቤቴ እህት ግንቦት 30, 1945 ሉቼኔዝ ወደሚገኘው ቤታችን ለመድረስ ተጨማሪ ሦስት ሳምንታት ወሰደብን።

ከርቀት አማቴንና ውዱን ልጄን ቲቦርን ግቢያችን ውስጥ ቆመው ተመለከትኳቸው። ዓይኖቼ በእንባ ተሞልተው “ቲቢኬ!” ብዬ ጠራሁት። ሲሮጥ መጣና ተጠመጠመብኝ። “ካሁን በኋላ ትተሽኝ አትሄጂም አይደል እማማ?” አለኝ። ስንገናኝ በመጀመሪያ የተናገራቸው ቃላት እነዚህ ነበሩ፤ እናም መቼም አልረሳቸውም።

ይሖዋ ለባለቤቴ ለቲቦርም ምሕረቱን አሳይቶታል። ከሌሎች 160 የሚያህሉ ወንድሞች ጋር በቡዳፔስት ካለው ወኅኒ ቤት በቦር ወደሚገኝ የጉልበት ሥራ የሚሠራበት ካምፕ ተላኩ። ከሞት አፋፍ ደርሰው የነበሩባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አልነበሩም፤ ሆኖም በቡድን ደረጃ ለመትረፍ ችለዋል። ቲቦር ከእኔ አንድ ወር ገደማ ቀደም ብሎ ሚያዝያ 8, 1945 ወደ ቤት ተመለሰ።

ከጦርነቱ በኋላ ቼኮዝሎቫኪያ በኮሚኒስት አገዛዘ ሥር በነበረችባቸው በቀጣዮቹ 40 ዓመታት ውስጥ ያጋጠመንን ስደት ለመቋቋምም ይሖዋ የሚሰጠው ብርታት አስፈልጎን ነበር። ቲቦር ዳግመኛ የረጅም ዓመት እስር የተፈረደበት ሲሆን እኔም ያለ እርሱ ልጄን ማሳደግ ነበረብኝ። ከእስር ከተፈታ በኋላ ቲቦር ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ማገልገል ጀመረ። በኮሚኒዝም አገዛዝ ሥር በነበርንባቸው 40 ዓመታት እውነትን ለሌሎች ለማካፈል ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እንጠቀም ነበር። ብዙዎች እውነትን እንዲያውቁ መርዳት የቻልን ሲሆን መንፈሳዊ ልጆች ሆነውልናል።

በ1989 ሃይማኖታዊ ነጻነት ስናገኝ ምን ያህል እንደተደሰትን አስቡት! በቀጣዩ ዓመት ከረጅም ጊዜ በኋላ በአገራችን በተካሄደው የመጀመሪያ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘን። ለብዙ አሥርተ ዓመታት ፍጹም አቋማቸውን ጠብቀው የጸኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶችን ስንመለከት ይሖዋ ለሁሉም የብርታት ምንጭ ሆኖላቸው እንደነበር ተገንዝበናል።

ውዱ ባለቤቴ ቲቦር ጥቅምት 14, 1993 በታማኝነት የሞተ ሲሆን እኔም ከልጄ ብዙም ሳልርቅ በዚሊና፣ ስሎቫኪያ እኖራለሁ። አሁን በአካላዊ ሁኔታ ያን ያህል ጠንካራ አይደለሁም፤ ሆኖም ከይሖዋ በማገኘው ኃይል መንፈሴ ጠንካራ ነው። ከእርሱ በማገኘው ብርታት በዚህ አሮጌ ሥርዓት የሚያጋጥመኝን ማንኛውንም መከራ በጽናት ማለፍ እንደምችል አልጠራጠርም። ከዚህም በላይ ይገባናል በማንለው የይሖዋ ደግነት ለዘላለም ለመኖር የምችልበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትቼው ለመሄድ የተገደድኩት ልጄ ቲቦር ጁኒየር (በአራት ዓመቱ)

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለቤቴ ቲቦር ከሌሎች ወንድሞች ጋር በቦር

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከቲቦርና ከእህቱ ማግዳሌና ጋር በ1947፣ በበርኖ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በብዙ አጋጣሚዎች ለሞት ተቃርቤ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ ባደረገልኝ ጥበቃ ልተርፍ ችያለሁ