በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሻለ መንግሥት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

የተሻለ መንግሥት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

የተሻለ መንግሥት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

“በዓለማችን ላይ [በብሔራት] መካከል ያለው ትስስር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መሄዱ አገራት በግላቸው ሊፈቷቸው የማይችሏቸው ዓለም አቀፋዊ ችግሮች እንዲበራከቱ አድርጓል። በሰው ዘር ፊት የተጋረጡትን አደጋዎችና ችግሮች መወጣት የምንችለው ዓለም አቀፋዊ ኅብረት በመፍጠር ብቻ ነው።”—ጉላም ኡማር፣ የፓኪስታን የፖለቲካ ተንታኝ

ለማችን ግራ በሚያጋቡ ሁኔታዎች የተሞላ ነው። ቁሳዊ ነገሮች በተትረፈረፉበት ዓለም ውስጥ ብዙዎች የዕለት ጉርስ ለማግኘት ይዋትታሉ። በኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ በተራቀቀው በዚህ ዘመን ሰዎች በየትኛውም ዘመን ከነበረው ኅብረተሰብ ይልቅ ከፍተኛ የትምህርትና የእውቀት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ያም ሆኖ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሰዎች አስተማማኝ ሥራ ማግኘት አዳጋች ሆኖባቸዋል። ቀደም ካሉት ዘመናት አንጻር ሲታይ ዛሬ የሰው ልጅ የበለጠ ነጻነት ያለው ቢመስልም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፍርሃትና አለመረጋጋት በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ። በዙሪያችን ማራኪ የሆኑ በርካታ የእድገት አጋጣሚዎች ቢኖሩም ሙስናና ሕገ ወጥነት ትልቅ ትንሽ ሳይል በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተስፋፍቶ የሚገኝ መሆኑ ለብዙዎች ተስፋ አስቆራጭ ሆኖባቸዋል።

በሰው ዘር ፊት የተደቀኑት ችግሮች መጠነ ሰፊ በመሆናቸው አንድ አገር ቀርቶ በርካታ አገሮች በአንድ ላይ ቢተባበሩም ሊወጡት ከሚችሉት በላይ ነው። በመሆኑም በርካታ ታዛቢዎች ዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን ሁሉም ብሔራት በአንድ መንግሥት ሥር መታቀፍ አለባቸው ወደሚለው መደምደሚያ ደርሰዋል። ለአብነት ያህል፣ አልበርት አንስታይን ከረጅም ጊዜ በፊት የዚህ ዓይነት አመለካከት ያራምድ ነበር። በ1946 እንዲህ ብሏል “በዓለም ላይ ያለው አብዛኛው ሰው ሰላምና ደህንነት በሰፈነበት ሁኔታ መኖር እንደሚፈልግ እርግጠኛ ነኝ። . . . የሰው ልጅ ሰላም ለማግኘት ያለው ፍላጎት እውን ሊሆን የሚችለው አንድ ዓለም አቀፋዊ መንግሥት ሲቋቋም ብቻ ነው።”

አንስታይን ከላይ ያለውን ከተናገረ ከአምስት አሥርተ ዓመታት የሚበልጥ ጊዜ ቢያልፍም ይህ የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት አሁንም አልተሟላም። በ21ኛው መቶ ዘመን ያሉትን ችግሮች በተመለከተ ለ ሞንድ በተሰኘ አንድ የፈረንሳይ ጋዜጣ ላይ የወጣ አስተያየት እንዲህ ይላል “በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ቢሆን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሲካሄድ ወዲያው ጣልቃ ገብቶ እርምጃ ሊወስድ የሚችል ፍርድ ነክ፣ አስተዳደራዊና ሕገ መንግሥታዊ መዋቅር ያለው ዓለም አቀፋዊ መንግሥት ማቋቋም ያስፈልጋል። ከዚያ በኋላ ምድር በሞላ አንድ አገር እንደሆነች የመቀበል ጉዳይ ይሆናል።” የሰው ዘር ሰላም የሰፈነበት የወደፊት ሕይወት እንዲመራ ለማስቻል እንዲህ ያለ መንግሥት ለማቋቋም ኃይልና ችሎታ ያለው ማን ወይም ምንድን ነው?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መፍትሔ ያመጣ ይሆን?

ብዙዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፋዊ ሰላም እንደሚያመጣ ተስፋ አድርገው ነበር። ለዓለም እውነተኛ ሰላምና ደህንነት የሚያመጣው መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይሆን? ተስፋ ሰጪ የሚመስል ፖለቲካዊ ዲስኩር በመስጠት ረገድ የተባበሩት መንግሥታት ችግር እንደሌለበት ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጠቃላይ ጉባኤ በ2000 ባወጣው “የምዕተ ዓመቱ መግለጫ” ላይ የሚከተለውን ድምፀ ውሳኔ አሳልፎ ነበር “ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከ5 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፈው የጦርነት መቅሰፍት (በአንድ አገር ውስጥ የሚካሄድ የእርስ በርስ ግጭት ወይም በአገራት መካከል የሚፈጸም ጦርነት) ሕዝቦቻችንን ለማዳን የምንችለውን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አንልም።” እንደነዚህ ያሉት መግለጫዎች ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተለያዩ አቅጣጫዎች አድናቆትና ውዳሴ ያተረፉለት ከመሆኑም በላይ የ2001 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል። የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያደረገውን ጥረት በማድነቅ “ዓለም አቀፋዊ ሰላምና ትብብር ለማምጣት የሚቻልበት ብቸኛው ውጤታማ መንገድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው” ብሏል።

ይህ ሁሉ ቢባልም በ1945 የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዓለም እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ማምጣት ችሏል? አልቻለም፤ አባል አገራቱ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ መሞከራቸው ድርጅቱ የሚያደርጋቸው አብዛኞቹ ጥረቶች ፍሬ ቢስ እንዲሆኑ አድርጓል። የአንድ ጋዜጣ ዘጋቢ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት “በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ያላቸውን አመለካከት ከመጠቆም” ያለፈ ነገር እንዳልፈጸመ ገልጿል፤ አክሎም “ድርጅቱ የያዛቸው አጀንዳዎች ለዓመታት ውዝግብ የተካሄደባቸው ቢሆንም ወደ መፍትሔ አንድም እርምጃ ያልተራመዱ ርዕሰ ጉዳዮች ጥርቅም እንደሆነ” በመናገር የኅብረተሰቡን አስተያየት የሚያስተጋባ ሐሳብ ሰንዝሯል። የዓለም መንግሥታት ወደፊት አንድነት መፍጠር ይችሉ ይሆን? የሚለው ጥያቄ አሁንም መልስ አላገኘም።

መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ እንደዚህ ያለው አንድነት እውን እንደሚሆን ይናገራል። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ይህንን አንድነት የሚያመጣውስ የትኛው መንግሥት ነው? መልሱን ለማግኘት የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንስታይን ዓለም አቀፋዊ መንግሥት ሊቋቋም እንደሚገባ ያምን ነበር

[ምንጭ]

አንስታይን U.S. National Archives photo