የአምላክ መንግሥት እውን የሆነ መስተዳድር
የአምላክ መንግሥት እውን የሆነ መስተዳድር
“ሰፊ የባህል ልዩነት ያላቸውና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙት እነዚህ ሁሉ አገሮች እንዴት ሊስማሙ ይችላሉ? የሰውን ዘር አንድ ሊያደርገው የሚችለው ከሌላ ፕላኔት የተሰነዘረ ጥቃት ብቻ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል።” —ዚ ኤጅ የተሰኘ የአውስትራሊያ ጋዜጣ
ከሌላ ፕላኔት የተሰነዘረ ጥቃት አንድነት ያስገኝ ይሆን? እንዲህ ያለው ጥቃት የምድር ብሔራት ሕብረት እንዲፈጥሩ ያድርጋቸው አያድርጋቸው ባናውቅም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የዓለም መንግሥታት አንድነት እንዲፈጥሩ ስለሚያደርግ እየቀረበ ስላለ ጥፋት ይናገራል። ይህ ጥፋት የሚሰነዘረው ደግሞ ከፕላኔታችን ውጪ ባሉ ኃይሎች ነው።
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ዳዊት በዓለም ላይ ስለሚፈጸመው ስለዚህ ሁኔታ በትንቢት ተናግሮ ነበር። በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ ገዦችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ፣ ሊመክሩ ተሰበሰቡ፤ ‘ሰንሰለታቸውን እንበጥስ፣ የእግር ብረታቸውንም አውልቀን እንጣል’ አሉ።” (መዝሙር 2:2, 3፤ የሐዋርያት ሥራ 4:25, 26) የዓለም መንግሥታት አንድ ግንባር ፈጥረው በአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ በይሖዋ ላይ እንዲሁም እርሱ በቀባውና ንጉሥ አድርጎ በሾመው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደሚነሱ ልብ በል። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው?
a በዚያን ጊዜ የዓለም ብሔራት አንድ የጋራ ሐሳብ ነበራቸው። አዲስ ለተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ሉዓላዊነት ከመገዛት ይልቅ በአንደኛው የዓለም ጦርነት የበላይነት ለማግኘት በተደረገው ፍልሚያ ተጠምደው ነበር።
በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት አቆጣጠርና ፍጻሜያቸውን ባገኙ ትንቢቶች መሠረት በ1914 ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ የሆነለት የአምላክ መንግሥት በሰማይ ተቋቁሟል።አምላክ ሰብዓዊ መሪዎች የሰጡትን ምላሽ እንዴት ይመለከተዋል? “በሰማይ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ይሥቃል፤ ጌታም ይሣለቅባቸዋል። ከዚያም በቁጣው ይናገራቸዋል፤ በመዓቱም ያስደነግጣቸዋል።” ከዚያም ይሖዋ የመንግሥቱ ንጉሥ ሆኖ ለተቀባው ለልጁ እንዲህ ይለዋል:- “ለምነኝ፤ መንግሥታትን ርስት አድርጌ፣ የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንህ እሰጥሃለሁ። አንተም በብረት በትር ትቀጠቅጣቸዋለህ፤ እንደ ሸክላ ዕቃ ታደቃቸዋለህ።”—መዝሙር 2:4, 5, 8, 9
እነዚህ ተቃዋሚ መንግሥታት በአርማጌዶን ወይም ሃርማጌዶን በብረት በትር ድምጥማጣቸው ይጠፋል። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ የሆነው የዮሐንስ ራእይ ይህንን ታላቅ ክንውን “[የ]ዓለም ሁሉ ነገሥታት” የሚሰበሰቡበት ‘ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን የሚሆን ጦርነት’ በማለት ይገልጸዋል። (ራእይ 16:14, 16) የምድር ነገሥታት በአጋንንት እየተነዱ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ለመዋጋት በማሰብ አንድነት ይፈጥራሉ።
የሰው ልጆች የአምላክን ሉዓላዊነት በመቃወም ለጦርነት የሚሰባሰቡበት ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ ነው። የሚያሳዝነው ይህ “አንድነታቸው” ምንም ጥቅም የማያስገኝላቸው መሆኑ ነው። በተቃራኒው የሚወስዱት እርምጃ ለዘመናት ሲጠበቅ የነበረው ዓለም አቀፋዊ ሰላም እንደቀረበ የሚያሳይ ይሆናል። እንዴት? በዚህ የመጨረሻ ጦርነት ላይ የአምላክ መንግሥት “እነዚያን [የዓለም] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (ዳንኤል 2:44) የሰው ዘር ዓለም አቀፋዊ ሰላም ለማግኘት ያለውን ፍላጎት የሚያሟላው የትኛውም ሰብዓዊ ድርጅት ሳይሆን የአምላክ መንግሥት ነው።
የአምላክ መንግሥት ዋና አስተዳዳሪ
የአምላክ መንግሥት ቅን ልብ ያላቸው ብዙዎች “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” እያሉ ሲጸልዩለት የነበረው መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:10) የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ የሚገኝ የማይጨበጥ ነገር ሳይሆን እውን የሆነ መስተዳድር ነው። ይህ መንግሥት በ1914 በሰማይ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አስደናቂ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል። የአምላክ መንግሥት በዛሬው ጊዜ እየገዛ ያለ እውን መስተዳድር መሆኑን የሚያረጋግጡ አንዳንድ ጎላ ብለው የሚታዩ ነጥቦችን እንመርምር።
በመጀመሪያ ደረጃ፣ ዙፋን ላይ በተቀመጠው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራ ብቃትና ኃይል ያለው ሥራ አስፈጻሚ አካል አለው። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ይሖዋ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን የክርስቲያን ጉባኤ ራስ አድርጎ ሾመው። (ኤፌሶን 1:22) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ የራስነት ሥልጣኑን በመጠቀም የማስተዳደር ብቃት እንዳለው አሳይቷል። ለአብነት ያህል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ከባድ ረሃብ ሲከሰት የክርስቲያን ጉባኤ አባላቱን ለመርዳት ፈጣን እርምጃ ወስዷል። የተቸገሩትን ለመርዳት የሚያስፈልገው ዝግጅት ከተደረገ በኋላ በርናባስና ሳውል ከአንጾኪያ የእርዳታ ቁሳቁስ ይዘው ሄዱ።—የሐዋርያት ሥራ 11:27-30
በዛሬው ጊዜም መንግሥቱ እየገዛ በመሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ ያነሰ አያደርግም። እንደ መሬት መንቀጥቀጥ፣ ረሃብ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ዓውሎ ንፋስ ወይም የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ያሉ አደጋዎች ሲደርሱ የይሖዋ ምሥክሮች
አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቻቸውና ሌሎች ሰዎችም የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በጥርና የካቲት 2001 ኤል ሳልቫዶር አውዳሚ በሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ በተመታች ጊዜ በአገሪቱ በጠቅላላ እርዳታ ለመስጠት ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ከካናዳ፣ ከጓቲማላና ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በሥራው ተካፍለዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሦስት የመሰብሰቢያ ቦታዎቻቸውንና ከ500 በላይ ቤቶችን መልሰው ሠርተዋል።የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች
የአምላክ መንግሥት በ1914 በሰማይ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ተገዢዎቹን ከመላው ዓለም ሲያሰባስብና ሲያደራጅ ቆይቷል። ይህም ኢሳይያስ የተናገረው አስደናቂ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል:- “በዘመኑም ፍጻሜ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ [የላቀው እውነተኛ አምልኮው] ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ . . . ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ።” ትንቢቱ “ብዙ ሕዝቦች” ወደዚያ ተራራ በመውጣት የይሖዋን መመሪያዎችና ሕግጋት እንደሚቀበሉ ያሳያል።—ኢሳይያስ 2:2, 3
በዛሬው ጊዜ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎቹን ለማሰባሰብ የሚያከናውነው ይህ እንቅስቃሴ በምድር ዙሪያ ከ230 በሚበልጡ አገሮች የሚኖሩ ከ6,000,000 በላይ ክርስቲያኖችን ያቀፈ ታላቅ ድርጅት እንዲቋቋም አድርጓል። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ በርካታ ሰዎች በመካከላቸው የብሔር፣ የባሕልና የቋንቋ ልዩነት ቢኖርም ይህ ሳይገድባቸው በፍቅር፣ በሰላምና በአንድነት አብረው መሆናቸው አብዛኛውን ጊዜ ታዛቢዎችን ያስገርማል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) አንድ መንግሥት በመቶዎች የሚቆጠር የተለያየ ብሔር ያላቸው ዜጎቹ በሰላምና በስምምነት እንዲኖሩ ለማድረግ ብቃት ያለውና አስተማማኝ እንዲሁም እውን መስተዳድር ሊሆን ይገባል ቢባል አትስማማም?
የአምላክ መንግሥት የትምህርት መርሐ ግብር
ሁሉም መንግሥታት ዜጎቻቸው እንዲያሟሉት የሚፈልጉት ብቃት አለ፤ የአንድ መንግሥት ዜጋ መሆን የፈለገ ሰው ይህንን ብቃት እንዲያሟላ ይፈለግበታል። በተመሳሳይ የአምላክ መንግሥት ዜጎች ለመሆን ብቃቱን ያሟሉ ሁሉ የሚጠበቅባቸው መሥፈርት አለ። ይሁን እንጂ በጣም የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው በርካታ ሰዎች አንድ ዓይነት መሥፈርቶችን እንዲቀበሉና ከእነዚህም ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ማድረግ ቀላል ሥራ አይደለም። ይህ ደግሞ የአምላክ መንግሥት እውን መስተዳድር መሆኑን የሚያረጋግጥልን ሌላው ማስረጃ ነው፤ ይህ መንግሥት የሰዎችን አእምሮ ብቻ ሳይሆን ልባቸውንም ጭምር የሚነካና ለውጥ እንዲያደርጉ የሚገፋፋ ውጤታማ የትምህርት መርሐ ግብር አለው።
የአምላክ መንግሥት ይህን ከባድ ሥራ የሚያከናውነው እንዴት ነው? ሐዋርያት ያደርጉ እንደነበረው “በየቤቱ” በመስበክና የአምላክን ቃል በግለሰብ ደረጃ በማስተማር ነው። (የሐዋርያት ሥራ 5:42፤ 20:20) እንደዚህ ያለው የትምህርት መርሐ ግብር ምን ያህል ውጤታማ ነው? ዣክ ጆንሰን የተባሉ አንድ የካቶሊክ ቄስ አንዲት ሴት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናቷን እንድታቆም ለማግባባት ስላደረጉት ሙከራ በካናዳ በሚታተም ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ ጽፈው ነበር። “የማደርገው ጥረት እንዳልተሳካ ስመለከት በሁኔታው ግራ ተጋብቼ ነበር” ብለዋል። “የይሖዋ ምሥክር የሆኑት እነዚህ ሴቶች ከቤት ከማትወጣው ከዚህች ወጣት ሴት ጋር ባሳለፏቸው በርካታ ወራት የጠበቀ ግንኙነት እንደመሠረቱ ተገነዘብሁ። እርሷን በመርዳት፣ ጓደኛዋ በመሆንና ጠንካራ ወዳጅነት በመመሥረት ከዚህች ሴት ጋር ልብ ለልብ ተግባብተዋል። ብዙም ሳይቆይ በሃይማኖታቸው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ የጀመረች ሲሆን ይህ እንዳይሆን ለመከላከል ላደርገው የምችለው ነገር አልነበረም።” ቀድሞ ካቶሊክ እንደነበረችው እንደዚህች እናት ሁሉ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም የይሖዋ ምሥክሮች በሚሰጡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርትና በክርስቲያናዊ ምግባራቸው ልባቸው ተነክቷል።
የአምላክን መንግሥት አስመልክቶ የሚሰጠው እንደዚህ ያለው ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያተኮረ ሲሆን ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን ያጎላል። ሁሉንም ሰዎች እንዲወድዱና እንዲያከብሩ ያስተምራል። (ዮሐንስ 13:34, 35) ከዚህም በላይ ሰዎች “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያበረታታል። (ሮሜ 12:2) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የቀድሞ አኗኗራቸውን ትተው ከአምላክ መንግሥት ሕግጋትና መመሪያዎች ጋር ተስማምተው በመኖር በአሁኑ ጊዜ ሰላምና ደስታ ለወደፊቱ ደግሞ ብሩሕ ተስፋ ማግኘት ችለዋል።—ቆላስይስ 3:9-11
ይህን የመሰለ ዓለም አቀፋዊ አንድነት በማስገኘት ረገድ መጠበቂያ ግንብ የተሰኘው ይህ መጽሔት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። የተቀናጀ የትርጉም ሥራ በማከናወንና በበርካታ ቋንቋዎች ለማተም በሚያስችል መሣሪያ በመጠቀም በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጡት ዋና ዋና ርዕሶች በአንድ ጊዜ በ135 ቋንቋዎች የሚታተሙ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ካሉት የዚህ መጽሔት አንባቢዎች ውስጥ ከ95 በመቶ የሚበልጡት በየራሳቸው ቋንቋ እኩል ሊያጠኑት ይችላሉ።
የሞርሞን ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ አንድ ጸሐፊ የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን ሳይጨምሩ ከሁሉ የላቀ የሚስዮናዊነት ሥራ አከናውነዋል ያሏቸውን አብያተ ክርስቲያናት ዝርዝር አውጥተው ነበር። በይሖዋ ምሥክሮች የሚታተሙት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! የላቀ የወንጌላዊነት ሥራ ያከናወኑ መጽሔቶች መሆናቸውን ከገለጹ በኋላ እንዲህ አሉ:- “መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ቸልተኝነት ያስፋፋሉ ብሎ ሊወቅሳቸው የሚችል የለም፤ ከዚህ በተቃራኒ በሌሎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ላይ እምብዛም ያላየሁትን ንቁ ሆኖ የመጠባበቅን አስፈላጊነት ያጎላሉ። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! በሐቅ ላይ የተመሠረተ፣ ጥልቅ ምርምር የተደረገበት፣ ጠቃሚና በገሃዱ ዓለም ያለውን ሁኔታ የሚያሳይ ሐሳብ ይዘው ስለሚወጡ መንፈስን ያድሳሉ።”
የአምላክ መንግሥት እውን እንደሆነና እየገዛ እንዳለ የሚጠቁሙ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ‘ይህን የመንግሥት ወንጌል’ በደስታና በቅንዓት ለሰዎች የሚያካፍሉ ሲሆን የአምላክ መንግሥት ዜጎች እንዲሆኑም ይጋብዟቸዋል። (ማቴዎስ 24:14) እንደዚህ ያለው ተስፋ አስደሳች እንደሆነ ይሰማሃል? የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን የሚያስፈልጉትን መሥፈርቶች ከሚማሩትና ከዚያ ጋር ተስማምተው ለመኖር ከሚጥሩት ሰዎች ጋር በመተባበር ከሚገኘው በረከት ተቋዳሽ መሆን ትችላለህ። ከዚያ የበለጠው ደግሞ አምላክ ቃል በገባው ‘ጽድቅ የሚኖርበት’ አዲስ ዓለም ውስጥ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የመኖር አስደሳች ተስፋ ይኖርሃል።—2 ጴጥሮስ 3:13
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከታተመው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ከተባለው መጽሐፍ “የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀምሯል” የሚለውን ምዕራፍ 10ን ገጽ 90-97 ተመልከት።
[በገጽ 4,5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በ1914 ብሔራት ዓለም አቀፋዊ በሆነ ጦርነት ተጠምደው ነበር
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ችግር የገጠማቸውን ለመርዳት በፈቃደኝነት የሚደረግ ርብርብ የክርስቲያናዊ ፍቅር መግለጫ ነው
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ማዕድ ይመገባሉ