የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ” ብሎ ሲነግራቸው ምን ማለቱ ነበር?
ኢየሱስ 70 ደቀ መዛሙርት መረጠና “ወደሚሄድበትም ከተማና ቦታ ሁሉ እንዲቀድሙት፣ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው።” ሰባዎቹ ደቀ መዛሙርት ሲመለሱ ተልእኳቸው በመሳካቱ ተደስተው “ጌታ ሆይ፤ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ” በማለት ተናገረ።—ሉቃስ 10:1, 17, 18
ጥቅሱ እንዲያው ከላይ ሲታይ ኢየሱስ ቀደም ብሎ ስለተፈጸመ ሁኔታ የተናገረ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከላይ ያሉትን ቃላት ከተናገረ ከ60 ዓመት በኋላ አረጋዊው ሐዋርያ ዮሐንስ ተመሳሳይ አገላለጽ በመጠቀም እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።”—ራእይ 12:9
ዮሐንስ እነዚህን ቃላት በጻፈበት ወቅት ሰይጣን በሰማይ ነበር። ይህን እንዴት እናውቃለን? ምክንያቱም የራእይ መጽሐፍ የሚናገረው ስላለፈ ታሪክ ሳይሆን ወደፊት ስለሚፈጸሙ ነገሮች ነው። (ራእይ 1:1) በመሆኑም በዮሐንስ ዘመን ሰይጣን ወደ ምድር አልተጣለም ነበር። እንዲያውም ሰይጣን ከሰማይ የተባረረው ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በ1914 በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደሆነ ማስረጃዎች ያሳያሉ። a—ራእይ 12:1-10
ታዲያ ኢየሱስ የሰይጣንን ከሰማይ መውደቅ ልክ እንደተፈጸመ አድርጎ የተናገረው ለምንድን ነው? አንዳንድ ምሑራን ኢየሱስ እንዲህ ያለው ባከናወኑት ሥራ በመኩራራታቸው ደቀ መዛሙርቱን ለመገሰጽ ነው የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ። በሌላ አባባል ኢየሱስ ‘አጋንንት ስለተገዙላችሁ አትኩራሩ። ሰይጣን በመኩራራቱ ውድቀቱን አፋጠነ’ እያለ ነበር ይላሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ሆኖም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ባቀረቡለት ሪፖርት ተደስቶ ሰይጣን ወደፊት ስለሚያጋጥመው ውድቀት እየተናገረ ነበር የሚለው ሐሳብ ይበልጥ አሳማኝ ይመስላል። ኢየሱስ የዲያብሎስን የከረረ ጥላቻ ከደቀ መዛሙርቱ ይበልጥ ያውቃል። ኃያል የሆኑት አጋንንት ፍጹም ላልሆኑት ደቀ መዛሙርቱ እንደተገዙላቸው ሲሰማ ምን ያህል እንደተደሰተ ገምት! አጋንንት ለደቀ መዛሙርቱ መገዛታቸው ወደፊት የመላእክት አለቃ ሚካኤል ማለትም ኢየሱስ ከሰይጣን ጋር ተዋግቶ ከሰማይ ወደ ምድር እንደሚወረውረው የሚያሳይ ነበር።
ኢየሱስ ሰይጣን “ሲወድቅ” አየሁ ሲል የሰይጣን መውደቅ የማያጠራጥር መሆኑን አስረግጦ መናገሩ እንደነበር ግልጽ ነው። ይህ ወደፊት የሚፈጸሙ ክንውኖችን ኃላፊ ግስ በመጠቀም ልክ እንደተፈጸሙ አድርገው በሚናገሩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም ላይ ይታያል። ለምሳሌ ያህል፣ በኢሳይያስ 52:13 እስከ 53:12 ላይ መሲሑን አስመልክቶ የሚናገረው ትንቢት በከፊል ልክ እንደተፈጸመ ተደርጎ መገለጹን ልብ በል። በተመሳሳይም ኢየሱስ በአባቱ እቅድ መሠረት ሰይጣን ከሰማይ መጣሉ እንደማይቀር ያለውን ጠንካራ እምነት መግለጹ ሳይሆን አይቀርም። ከዚህም በላይ ኢየሱስ፣ አምላክ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ጥልቁ እንደሚጣሉና ከጊዜ በኋላም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚጠፉ ሙሉ እምነት ነበረው።—ሮሜ 16:20፤ ዕብራውያን 2:14፤ ራእይ 20:1-3, 7-10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የታተሙትን ወደ ዘላላም ሕይወት የሚመራ እውቀት ምዕራፍ 10 እና ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! ምዕራፍ 27 ተመልከት።