በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ለወንጌል ሲል ብዙ የተንከራተተ” ደፋር ሰው

“ለወንጌል ሲል ብዙ የተንከራተተ” ደፋር ሰው

“ለወንጌል ሲል ብዙ የተንከራተተ” ደፋር ሰው

ጆርጅ ቦሮው በ18 ዓመቱ 12 ቋንቋዎች ይችል እንደነበር ይነገራል። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ “ብዙም ሳይቸገርና ሥነ ጽሑፋዊ ውበታቸውን በጠበቀ ሁኔታ” ጽሑፎችን በ20 ቋንቋዎች መተርጎም ይችል ነበር።

በ1833 በለንደን፣ እንግሊዝ የሚገኘው የብሪታንያና የባሕር ማዶ አገራት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ይህን ለየት ያለ ተሰጥኦ ያለው ሰው ለቃለ መጠይቅ ጋበዘው። የ30 ዓመቱ ቦሮው ለጉዞ የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን ቢያቅተውም ይህ ጥሩ አጋጣሚ እንዲያመልጠው ስላልፈለገ በኖርዊች ከሚገኘው ቤቱ ተነስቶ በ28 ሰዓት ውስጥ 180 ኪሎ ሜትር በመጓዝ በቦታው ተገኘ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበሩ ማንቹ የተሰኘውን በአንዳንድ የቻይና ግዛቶች የሚነገር ቋንቋ በስድስት ወራት ውስጥ የመማር አስቸጋሪ ሥራ ሰጠው። ቦሮው የሰዋስው መጽሐፍ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ሊያገኙለት የቻሉት በማንቹ ቋንቋ የተዘጋጀ የማቴዎስ ወንጌልና የማንቹ-ፈረንሳይኛ መዝገበ ቃላት ብቻ ነበር። ያም ሆኖ በ19 ሳምንት ጊዜ ውስጥ “የማንቹን ቋንቋ በደንብ ችያለሁ” ብሎ ወደ ለንደን ጻፈ፤ ይህንን ማድረግ የቻለው እርሱ ራሱ እንደገለጸው “በአምላክ እርዳታ” ነበር። የማንቹን ቋንቋ እየተማረ በሜክሲኮ ከሚነገሩት የአገሬው ተወላጆች ቋንቋዎች አንዱ በሆነው በናዋታል የተዘጋጀውን የሉቃስ ወንጌል ያርም የነበረ መሆኑ ደግሞ ሥራውን ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል።

በማንቹ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ

በማንቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ጽሕፈት የተጀመረው በ17ኛው መቶ ዘመን ሲሆን ሞንጎሊያን ዊጉር ከተባለው ቋንቋ በተዋሰው ፊደል በመጠቀም የቻይና ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ያገለግል ነበር። እያደር ማንቹ ጥቅም ላይ መዋሉ እየቀረ ቢመጣም የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበሩ አባላት በዚህ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ለማተምና ለማሰራጨት ይፈልጉ ነበር። በ1822 ማኅበሩ በስቴፓን ሊፖፍሰፍ የተተረጎመውን የማቴዎስ ወንጌል 550 ቅጂዎች ለማሳተም የገንዘብ ድጋፍ አደረገ። ስቴፓን በቻይና ለ20 ዓመታት የኖረ የሩስያ የውጭ ጉዳይ ቢሮ አባል ነበር። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሴንት ፒተርስበርግ ታትሞ መሰራጨት ቢጀምርም ጥቂት ቅጂዎች ብቻ እንደተሰራጩ የቀረው በጎርፍ ተበላሸ።

ብዙም ሳይቆይ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በሙሉ ተተረጎሙ። በ1834 አብዛኞቹን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የያዘ ጥንታዊ የብራና ቅጂ መገኘቱ ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ያለው ፍላጎት እንዲያድግ አደረገ። በወቅቱ የነበረውን የማንቹ መጽሐፍ ቅዱስ የማረምና የቀረውን ክፍል የመተርጎሙን ሥራ ማን ሊያከናውነው ይችላል? የብሪታንያና የባሕር ማዶ አገራት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ድርጅቱን ወክሎ ይህንን ሥራ እንዲያከናውን ጆርጅ ቦሮውን ላከው።

ወደ ሩስያ መጓዝ

ቦሮው ሴንት ፒተርስበርግ እንደደረሰ የማንቹን ቋንቋ በጥልቀት በማጥናት በጊዜው የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጥራት ባለው መንገድ ለማረም የሚያስችለው እውቀት ማካበት ጀመረ። እንደዚህም ሆኖ የተሰጠው ሥራ በጣም ከባድ ነበር፤ ከጊዜ በኋላ “በሩቅ ምሥራቅ ቋንቋ የተዘጋጀ ድንቅ ሥራ” ተብሎ ለመሰየም የበቃውን አዲስ ኪዳን ለሕትመት ለማዘጋጀት በየቀኑ 13 ሰዓት ያህል ይሠራ ነበር። በ1835 ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ሺህ ቅጂዎች ታተመ። ሆኖም ቦሮው ይህንን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ቻይና ወስዶ ለማሰራጨት የነበረው ምኞት ሳይሳካ ቀረ። የሩስያ መንግሥት የማንቹ መጽሐፍ ቅዱስ በቻይና ቢሰራጭ ድርጊቱ እንደ ሚስዮናዊ ዘመቻ ተቆጥሮ ጎረቤታቸው ከሆነችው ከቻይና ጋር ያላቸውን ወዳጃዊ ግንኙነት አደጋ ላይ እንዳይጥለው ፈራ፤ በመሆኑም ቦሮው “አንድም የማንቹ መጽሐፍ ቅዱስ” ይዞ ወደ ቻይና እንዳይገባ ተከለከለ።

ከአሥር ዓመታት ገደማ በኋላ ጥቂት ቅጂዎች የተሰራጩ ሲሆን በ1859 የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌሎች በማንቹና በቻይንኛ ቋንቋ በአንድ ገጽ ላይ ጎን ለጎን የሰፈሩበት ትርጉም ተዘጋጀ። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት ማንቹ ማንበብ የሚችሉት አብዛኞቹ ሰዎች ቻይንኛን ማንበብ ይመርጡ የነበረ በመሆኑ መላው መጽሐፍ ቅዱስ በማንቹ ቋንቋ የመታተሙ ተስፋ ተመናመነ። ለነገሩ ማንቹ እየጠፋ ያለና ብዙም ሳይቆይ በቻይንኛ የሚተካ ቋንቋ ነበር። በ1912 ቻይና ሪፑብሊክ ስትሆን ማንቹ ሙሉ በሙሉ በቻይንኛ ተተካ።

በአይቢሪያን ባሕረገብ መሬት

ጆርጅ ቦሮው ወደ ለንደን ሲመለስ ባከናወነው ሥራ ተበረታቶ ነበር። በ1835 በፖርቹጋልና በስፔይን ሌላ ምድብ የተሰጠው ሲሆን በኋላ ላይ እንደገለጸው ወደዚያ የተላከው “የሕዝቡ አእምሮ የክርስትናን እውነት ለመቀበል የቱን ያህል ዝግጁ እንደሆነ ለመመልከት” ነበር። በወቅቱ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አለመረጋጋት ሰፍኖ ስለነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበሩ በእነዚህ ሁለት አገሮች እምብዛም እንቅስቃሴ አላደረገም። ቦሮው በፖርቹጋል ገጠራማ አካባቢ ከሚኖረው ሕዝብ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ያስደስተው ነበር። ሆኖም ማኅበረሰቡ ለሃይማኖት ግዴለሽ መሆኑን ሲመለከት ብዙም ሳይቆይ ወደ ስፔይን አመራ።

በስፔይን ደግሞ ሙያውን የሚፈታተን ሌላ ሥራ ገጠመው፤ ቦሮው የጂፕሲዎቹን ቋንቋ መናገር ይችል ስለነበረ እዚያ ከሄደ ብዙም ሳይቆይ ከእነርሱ ጋር ተቀራረበ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ “አዲስ ኪዳንን” ኪታኖ ተብሎ በሚጠራው የስፔይን ጂፕሲዎች ቋንቋ መተርጎም ጀመረ። ይህን ሥራ በሚያከናውንበት ወቅት ሁለት የጂፕሲ ሴቶች በተወሰነ መጠን ይረዱት ነበር። ቦሮው የስፓንኛውን ትርጉም ያነብላቸውና እንዲተረጉሙለት ይጠይቃቸዋል። በዚህ መንገድ የጂፕሲ ፈሊጣዊ አነጋገሮችን ትክክለኛ አጠቃቀም መማር ቻለ። ይህ ሁሉ ጥረቱ ፍሬ አስገኘና በ1838 የፀደይ ወቅት የሉቃስን ወንጌል አሳተመ፤ ይህን የተመለከቱ አንድ ቄስ “በጂፕሲዎች ቋንቋ በመጠቀም መላዋን ስፔይን [ወደ ክርስትና] ይለውጣታል” ሲሉ ተናግረዋል።

ጆርጅ ቦሮው “ቅዱሳን ጽሑፎችን በባስክ ቋንቋ የመተርጎም ብቃት ያለው ሰው” እንዲፈልግ ታዝዞ ነበር። ይህ ኃላፊነት ዶክተር ኦታሳ ለተባለ አንድ ሐኪም ተሰጠ፤ ቦሮው ስለዚህ ግለሰብ ሲገልጽ “እኔ ራሴ በመጠኑ የማውቀውን ይህን ቀበልኛ አጣርቶ [ይችላል]” በማለት ጽፏል። በስፔይን ባስክ ቋንቋ ከተዘጋጁት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የመጀመሪያው የሆነው የሉቃስ ወንጌል በ1838 ታተመ።

ቦሮው ተራውን ሕዝብ ለማስተማር ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረው ረዥምና አብዛኛውን ጊዜም በጣም አደገኛ የሆነ ጉዞ በማድረግ በገጠሩ አካባቢ ለሚኖረው ድሀ ኅብረተሰብ መጽሐፍ ቅዱስን አሰራጭቷል። ሕዝቡን ከሃይማኖታዊ ድንቁርናና አጉል እምነት ነጻ ለማውጣት ይፈልግ ነበር። በገንዘብ የሚገዙት ስርየት ዋጋ እንደሌለው ሲያጋልጥ “ቸር የሆነው አምላክ ኃጢአትን በገንዘብ ማወራረድን እንዴት ሊደግፍ ይችላል?” በማለት ይከራከር ነበር። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበሩ ሰፊ ተቀባይነት ባገኙ እምነቶች ላይ እንደዚህ ያለ ጥቃት መሰንዘሩ እንቅስቃሴውን እንዳያሳግድበት ስለፈራ ቦሮው መጽሐፍ ቅዱስን በማሰራጨቱ ሥራ ላይ ብቻ እንዲያተኩር መመሪያ ተሰጠው።

ቦሮው በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርቶች ላይ የተሰጡ ማብራሪያዎች ያልተጨመሩበት ኤል ኑኤቮ ቴስታሜንቶ የተባለ የስፓንኛ አዲስ ኪዳን ለማዘጋጀት ጥያቄ አቀረበ። መጀመሪያ ላይ የትርጉም ሥራውን አደገኛና “ተገቢ ያልሆነ መጽሐፍ” በማለት ከጠሩት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃውሞ ቢገጥመውም ይህንን መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት የቃል ፈቃድ ማግኘት ቻለ። ከዚያም ቦሮው በማድሪድ የመጻሕፍት መሸጫ መደብር ከፍቶ ይህንን በስፔይን ቋንቋ የተዘጋጀ አዲስ ኪዳን መሸጥ መጀመሩ ከሃይማኖት መሪዎቹም ሆነ ከባለ ሥልጣናቱ ጋር እንዲጋጭ አደረገው። ለ12 ቀናት ከታሰረ በኋላ የታሰረው አላግባብ እንደሆነ በመግለጽ ተቃውሞውን ሲያሰማ ባለ ሥልጣናቱ በስውር ሊፈቱት አሰቡ። ቦሮው የታሰረው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መሆኑን አሳምሮ ያውቅ ስለነበር የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ከጠቀሰ በኋላ ንጹሕ መሆኑ ተገልጾ በአግባቡ እስካልተፈታ ድረስ በዚያው ለመቆየት መረጠ።—የሐዋርያት ሥራ 16:37

የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበሩን ወክሎ ሥራውን በቅንዓት ያከናወነው ይህ ሰው በ1840 ከስፔይን ሲወጣ ማኅበሩ “ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በስፔይን ወደ 14,000 የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ተሰራጭተዋል” በማለት መናገር ችሏል። በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና የተጫወተው ቦሮው በስፔይን ያሳለፈውን ጊዜ “በሕይወቴ ውስጥ በጣም የተደሰትኩባቸው ዓመታት” በማለት ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል።

ጆርጅ ቦሮው በ1842 ለመጀመሪያ ጊዜ በታተመውና አሁንም በሕትመት ላይ በሚገኘው ዘ ባይብል ኢን ስፔይን በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ስላደረጋቸው ጉዞዎችና ገጠመኞቹን አስመልክቶ ማራኪ የሆነ ትረካ አስፍሯል። ቦሮው ገና ከመጀመሪያው ከፍተኛ ተወዳጅነት ባተረፈው በዚህ መጽሐፉ ላይ ስለ ራሱ ሲናገር “ለወንጌል ሲል ብዙ የተንከራተተ” ሰው እንደሆነ ገልጿል። “አስቸጋሪ በሆኑት ኮረብታማና ተራራማ አካባቢዎች ያሉትን ርቀው የሚገኙ ገለልተኛ ቦታዎች መጎብኘትና እንደ ክርስቶስ ሕዝቡን ማነጋገር እፈልግ ነበር” ሲል ጽፏል።

ጆርጅ ቦሮው ቅዱሳን ጽሑፎችን በቅንዓት በማሰራጨትና በመተርጎም ረገድ ለሌሎች መሠረት ጥሏል፤ ይህ በእርግጥም ታላቅ ክብር ነው።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጆርጅ ቦሮው መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎምና ለማሰራጨት ሲል (1) ከእንግሊዝ ወደ (2) ሩስያ፣ (3) ፖርቹጋልና (4) ስፔይን ተጉዟል

[ምንጭ]

Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1835 በማንቹ ቋንቋ የታተመው የዮሐንስ ወንጌል ከግራ ወደ ቀኝ ከላይ ወደታች ሲነበብ

[ምንጭ]

በ1860 ከተዘጋጀው ዘ ባይብል ኦቭ ኤቭሪ ላንድ የተባለ መጽሐፍ የተወሰደ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በ1919 በክሌመንት ሾርተር ከተዘጋጀው ዘ ላይፍ ኦቭ ጆርጅ ቦሮው የተሰኘ መጽሐፍ የተወሰደ