በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰውነታችን ቢዝልም መንፈሳችን አይደክምም

ሰውነታችን ቢዝልም መንፈሳችን አይደክምም

ሰውነታችን ቢዝልም መንፈሳችን አይደክምም

“እግዚአብሔር . . . የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው . . . ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጒልበት ይጨምራል።”—ኢሳይያስ 40:28, 29

1, 2. (ሀ) ንጹሑን አምልኮ መከተል ለሚፈልጉ ሁሉ ምን ማራኪ ግብዣ ቀርቦላቸዋል? (ለ) መንፈሳዊ አቋማችንን ከባድ አደጋ ላይ ሊጥልብን የሚችለው ምንድን ነው?

 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። . . . ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና” የሚለውን አስደሳች ግብዣ በደንብ እናውቀዋለን። (ማቴዎስ 11:28-30) ከዚህ በተጨማሪ ክርስቲያኖች ‘[ከይሖዋ] ዘንድ የመታደስ ዘመን’ እንደሚመጣላቸው ቃል ተገብቶላቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ተስፋ ማግኘትና የይሖዋን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ማዋል ከፍተኛ እረፍት የሚያስገኝ መሆኑን እንደቀመሳችሁ ግልጽ ነው።

2 ሆኖም አንዳንድ የይሖዋ አምላኪዎች አልፎ አልፎ ኃይላቸው እንደተሟጠጠ ይሰማቸዋል። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ሲሆን በሌላ ወቅት ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ሊዘልቅ ይችላል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አንዳንዶች ክርስቲያናዊ ግዴታዎቻቸው ኢየሱስ ተስፋ እንደሰጠው እረፍት የሚያስገኝ ቀላል ሸክም ከመሆን ይልቅ አድካሚ ሆነውባቸዋል። እንዲህ ያለው አፍራሽ ስሜት አንድ ክርስቲያን ከይሖዋ ጋር የመሠረተውን ዝምድና ከባድ አደጋ ላይ ሊጥልበት ይችላል።

3. ኢየሱስ በዮሐንስ 14:1 ላይ የሚገኘውን ምክር የሰጠው ለምን ነበር?

3 ኢየሱስ ተይዞ ከመገደሉ ጥቂት ቀደም ብሎ ደቀ መዛሙርቱን “ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:1) ኢየሱስ ይህን የተናገረው ሐዋርያቱ ብዙም ሳይቆይ አሳዛኝ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሟቸው ነው። ከዚያም የስደት ማዕበል ይነሳባቸዋል። ኢየሱስ ሐዋርያቱ ከሚያድርባቸው ከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት የተነሳ ሊሰናከሉ እንደሚችሉ ተገንዝቧል። (ዮሐንስ 16:1) ያደረባቸውን የሐዘን ስሜት ካልተቆጣጠሩት በመንፈሳዊ ሁኔታ ይዳከማሉ እንዲሁም በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት ያጣሉ። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊደርስባቸው ይችላል። ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለከፍተኛ ሐዘን ሊዳርገንና ልባችን ሊዝል ይችላል። (ኤርምያስ 8:18) የመንፈስ ጥንካሬ ልናጣ እንችላለን። እንዲህ ዓይነት ጫና ሲደርስብን በስሜታዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ልንሽመደመድና ይባስ ብሎም ይሖዋን የማምለክ ፍላጎታችንን ልናጣ እንችላለን።

4. ምሳሌያዊ ልባችንን ከድካም ለመጠበቅ ምን ሊረዳን ይችላል?

4 መጽሐፍ ቅዱስ “ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ነውና” ሲል የሚሰጠው ምክር በእርግጥ ትክክል ነው። (ምሳሌ 4:23) መጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌያዊ ልባችንን ከተስፋ መቁረጥ ስሜትና ከመንፈሳዊ ድካም ሊጠብቅልን የሚችል ተግባራዊ ምክር ይዟል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ የድካም ስሜት የሚያስከትልብንን ነገር ማወቅ ይኖርብናል።

የክርስትና ሕይወት ጨቋኝ አይደለም

5. የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆንን በተመለከተ እርስ በርሱ የሚጋጭ የሚመስለው ሐሳብ የትኛው ነው?

5 የክርስትና ሕይወት ተጋድሎ እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው። (ሉቃስ 13:24) እንዲያውም ኢየሱስ “የራሱንም መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 14:27) ይህን አባባል በጥሞና ካላጤንነው በስተቀር ኢየሱስ ሸክሙ ቀላልና እረፍት የሚያስገኝ እንደሆነ ከተናገረው ሐሳብ ጋር የሚቃረን ሊመስል ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሁለቱ ሐሳቦች እርስ በርስ አይጋጩም።

6, 7. አምልኮታችን አታካች አይደለም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

6 ጉልበት ሳይቆጥቡ በትጋት መሥራት አድካሚ ቢሆንም ለጥሩ ዓላማ እስከሆነ ድረስ አርኪና መንፈስ የሚያድስ ሊሆን ይችላል። (መክብብ 3:13, 22) ታዲያ አስደሳች የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለሰዎች ከማካፈል የተሻለ ምን ሥራ አለ? ከዚህ በተጨማሪ አምላክ ያወጣቸውን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደንቦች ለመጠበቅ የምናደርገውን ትግል ከምናገኘው ጥቅም ጋር ስናወዳድረው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። (ምሳሌ 2:10-20) ስደት በሚደርስብን ጊዜም እንኳ ለአምላክ መንግሥት ብለን መከራ መቀበሉን እንደ ክብር እንቆጥረዋለን።—1 ጴጥሮስ 4:14

7 በሐሰት ሃይማኖት ቀንበር ሥር ያሉ ሰዎች ከሚገኙበት መንፈሳዊ ጨለማ ጋር ካስተያየነው ደግሞ የኢየሱስ ሸክም እረፍት የሚያስገኝ ለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። አምላክ በጣም ስለሚወደን ከአቅማችን በላይ የሆነ ትእዛዝ አይሰጠንም። የይሖዋ ‘ትእዛዛት ከባዶች አይደሉም።’ (1 ዮሐንስ 5:3) በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በተገለጸው መሠረት እውነተኛ ክርስትና ጨቋኝ አይደለም። አዎን፣ አምልኮታችን እንድንዝልና ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርግ አይደለም።

‘ሸክምን ሁሉ አስወግዱ’

8. አብዛኛውን ጊዜ የመንፈሳዊ ድካም መንስኤ ምንድን ነው?

8 በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመን የማንኛውም መንፈሳዊ ድካም መንስኤ በአብዛኛው ይህ ብልሹ ሥርዓት ከሚያስከትልብን ተጨማሪ ሸክም የሚመጣ ነው። ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር ስለሆነ’ እንድንዝልና መንፈሳዊ ሚዛናችንን እንድንስት ሊያደርጉ በሚችሉ አፍራሽ ግፊቶች ተከብበናል። (1 ዮሐንስ 5:19) አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ክርስቲያናዊ ልማዳችንን ሊያበላሹብንና ሊያሳጡን ይችላሉ። እነዚህ ተጨማሪ ሸክሞች ሊያደክሙን ብሎም መንፈሳችንን ሊደቁሱት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሸክምን ሁሉ አስወግዱ’ የሚል ምክር መስጠቱ እጅግ ተገቢ ነው።—ዕብራውያን 12:1-3

9. ቁሳዊ ነገሮችን ማሳደድ ሸክም ሊሆንብን የሚችለው እንዴት ነው?

9 ለምሳሌ ያህል፣ ዓለም ለዝና፣ ለገንዘብ፣ ለመዝናኛ፣ አገር ለመጎብኘትና ለሌሎች ቁሳዊ ነገሮች የሚሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በአስተሳሰባችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። (1 ዮሐንስ 2:15-17) በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ሀብት ያሳድዱ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን በእጅጉ አወሳስበውታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ . . . ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ። ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው፤ አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጉጉት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10

10. ኢየሱስ ስለ ዘሪው ከተናገረው ምሳሌ ሀብትን በተመለከተ ምን ትምህርት እናገኛለን?

10 ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት አሰልቺና ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ከተሰማን ምናልባት ቁሳዊ ነገሮችን ማሳደዳችን በመንፈሳዊነታችን ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆን? ኢየሱስ ስለ ዘሪው የተናገረው ምሳሌ እንደሚያሳየው እንደዚህ ዓይነት አደጋ ሊደርስብን ይችላል። “የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ፣ የሀብት አጓጊነት እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ምኞት” በልባችን የተተከለውን የአምላክ ቃል ዘር ‘አንቀው የሚይዙ’ እሾኽ እንደሆኑ ገልጿል። (ማርቆስ 4:18, 19) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይመክረናል፦ “ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ ‘ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም’ ብሎአል።”—ዕብራውያን 13:5

11. ሸክም የሚሆኑብንን ነገሮች ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው?

11 አንዳንድ ጊዜ ሕይወታችንን የሚያወሳስብብን፣ ተጨማሪ ነገሮች ለማግኘት ጥረት ማድረጋችን ሳይሆን ባሉን ነገሮች የምናከናውናቸው ሥራዎች ናቸው። አንዳንዶች ካጋጠማቸው ከባድ የጤና እክል፣ የሚያፈቅሯቸውን ሰዎች በሞት ከማጣታቸው ወይም ካጋጠሟቸው ሌሎች አስጨናቂ ሁኔታዎች የተነሳ ሐሞታቸው ሊፈስስ ይችላል። በዚህም ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝበዋል። ለምሳሌ ያህል አንድ ባልና ሚስት ጊዜ ለማሳለፍ የሚያደርጓቸውን አንዳንድ ነገሮች ለማስወገድና አስፈላጊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችንም ለመተው ወስነዋል። ዕቃዎቻቸውን አንድ በአንድ ከፈተሹ በኋላ ከእነዚያ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ አንድ ላይ ሰብስበው ከዓይናቸው አስወገዱ። እኛም አልፎ አልፎ ልማዶቻችንንና ያሉንን ዕቃዎች አንድ በአንድ አይተን አላስፈላጊ የሆኑ ሸክሞችን በሙሉ በማስወገድ ከድካምና በነፍሳችን ከመዛል እንድናለን።

ምክንያታዊነትና አቅምን ማወቅ አስፈላጊ ባሕርያት ናቸው

12. የምንፈጽማቸውን ስህተቶች በተመለከተ ምን ነገር መገንዘብ አለብን?

12 ትንንሽ በሚመስሉ ጉዳዮች እንኳ የምንፈጽማቸው ስህተቶች ቀስ በቀስ በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ። “በደሌ ውጦኛል፤ እንደ ከባድ ሸክምም ተጭኖኛል” በማለት ዳዊት የተናገረው ሐሳብ በጣም ትክክል ነው። (መዝሙር 38:4) አብዛኛውን ጊዜ የተወሰኑ ጠቃሚ ማስተካከያዎች ማድረጋችን ከከባድ ሸክም ይገላግለናል።

13. ምክንያታዊነት አገልግሎታችንን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንድንይዝ የሚረዳን እንዴት ነው?

13 መጽሐፍ ቅዱስ ‘መልካም ጥበብና ጥንቃቄ’ እንድናዳብር ያበረታታናል። (ምሳሌ 3:21, 22 የ1954 ትርጉም) በተጨማሪም “ከሰማይ የሆነችው ጥበብ . . . እሺ ባይ” ማለትም ምክንያታዊ እንደሆነች ይናገራል። (ያዕቆብ 3:17) አንዳንዶች ሌሎች በክርስቲያናዊ አገልግሎት የሚያከናውኑትን ያህል ለመሥራት ጥረት በማድረግ በራሳቸው ላይ ጫና ፈጥረዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ምክር ይሰጠናል፦ “እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ ከሌላ ሰው ጋር ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል፤ እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ሊሸከም ይገባዋልና።” (ገላትያ 6:4, 5) በእርግጥም የክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጥሩ ምሳሌነት ይሖዋን በሙሉ ልባችን እንድናገለግል ሊያበረታታን ይችላል። ሆኖም ጥበብና ምክንያታዊነት ሁኔታችን በሚፈቅድልን መጠን ልንደርስባቸው የምንችል ግቦች እንድናወጣ ይረዱናል።

14, 15. አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ፍላጎቶቻችንን ለማሟላት መልካም ጥበብ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 ተራ በሚመስሉ ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር ምክንያታዊ መሆናችን የድካም ስሜትን እንድናስወግድ ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ጥሩ ጤንነት እንዲኖረን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሚዛናዊ ልማዶች አሉን? በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግሉ የአንድ ባልና ሚስት ሁኔታ ተመልከት። አካላዊ ድካምን ለማስወገድ በጥበብ መኖር ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝበዋል። ሚስትየዋ እንዲህ ትላለች፦ “ምንም ያህል ሥራ ቢበዛብን ማታ ማታ በለመድነው ሰዓት ላይ ለመተኛት ጥረት እናደርጋለን። ከዚህ በተጨማሪ በየጊዜው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እናደርጋለን። ይህ በጣም ጠቅሞናል። አቅማችንን ስለምናውቅ ከገደባችን አናልፍም። ድካም የሚባል ነገር ከማያውቁ ሰዎች ጋር ከመፎካከር እንቆጠባለን።” እኛስ ጥሩ የአመጋገብ ልማድ አለን? በቂ እረፍትስ እናደርጋለን? በጥቅሉ ሲታይ ለጤንነታችን ተገቢውን ትኩረት መስጠታችን ስሜታዊም ሆነ መንፈሳዊ ድካም ሊቀንስልን ይችላል።

15 አንዳንዶቻችን ለየት ያሉ ፍላጎቶች ይኖሩን ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አንዲት እህት ከባድ በሆኑ በርካታ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች ተካፍላለች። ከካንሰር በተጨማሪ ሌሎች ሥር የሰደዱ የጤና እክሎች አሉባት። አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንድትቋቋም የሚረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ትላለች፦ “ጸጥታ በሰፈነበት ቦታ ብቻዬን የምሆንበት ጊዜ የግድ ያስፈልገኛል። በውስጤ የውጥረትና የድካም ስሜት እያየለ ሲመጣ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብቻዬን ሆኜ የማነብበትና የማርፍበት ጊዜ እፈልጋለሁ።” መልካም ጥበብና ጥንቃቄ ማዳበራችን በግለሰብ ደረጃ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለመገንዘብና ለማሟላት እንዲሁም መንፈሳዊ ድካም ለማስወገድ ይረዳናል።

ይሖዋ አምላክ ኃይል ይሰጠናል

16, 17. (ሀ) ለመንፈሳዊ ጤንነታችን መጠንቀቃችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዕለታዊ ፕሮግራማችን ውስጥ ምን ነገሮች ማካተት ይኖርብናል?

16 መንፈሳዊ ጤንነታችንን መንከባከብ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ከይሖዋ አምላክ ጋር የቅርብ ወዳጅነት እያለንም እንኳ ሰውነታችን ሊዝል ቢችልም እርሱን ማምለክ ፈጽሞ አድካሚ አይሆንብንም። ይሖዋ “ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጉልበት ይጨምራል።” (ኢሳይያስ 40:28, 29) የዚህን እውነተኝነት በሕይወቱ የተመለከተው ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ፣ ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል።”—2 ቆሮንቶስ 4:16

17 “ዕለት ዕለት” የሚለውን አባባል ተመልከት። ይህ አባባል ይሖዋ ካደረገልን ዝግጅቶች በየዕለቱ መጠቀም እንዳለብን ያሳያል። ለ43 ዓመታት በታማኝነት ያገለገለች አንዲት ሚስዮናዊ አካላዊ ድካምና ተስፋ መቁረጥ የተሰማት ወቅት ነበር። ይሁን እንጂ መንፈሷ ደክሞ አያውቅም። እንዲህ ትላለች፦ “የዕለቱ እንቅስቃሴዬን ከመጀመሬ በፊት ወደ ይሖዋ የምጸልይበትና ቃሉን የማነብበት ጊዜ ማግኘት እንድችል በማለዳ የመነሳት ልማድ አለኝ። በየዕለቱ የምከተለው ይህ ልማድ እስካሁን ድረስ እንድጸና ረድቶኛል።” ያለማቋረጥ አዎን፣ “ዕለት ዕለት” ወደ ይሖዋ የምንጸልይና ግሩም በሆኑት ባሕርያቱና በሰጠን ተስፋዎች ላይ የምናሰላስል ከሆነ ችግሮችን ተቋቁመን የምናሳልፍበት ኃይል እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

18. መጽሐፍ ቅዱስ በዕድሜ ለገፉ ወይም ታማሚ ለሆኑ ታማኝ ክርስቲያኖች ምን ማጽናኛ ይዟል?

18 በተለይ በዕድሜ መግፋትና በጤና ዕጦት የተነሳ ተስፋ መቁረጥ ለሚሰማቸው ክርስቲያኖች ከይሖዋ የሚገኝ ኃይል በጣም ይረዳቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ባያወዳድሩም እንኳ ከዚህ በፊት ያደርጉ የነበረውን ያህል መሥራት ባለመቻላቸው ልባቸው ይሰበር ይሆናል። ይሖዋ አረጋውያንን በአክብሮት እንደሚያያቸው ማወቁ በጣም ያጽናናል! መጽሐፍ ቅዱስ “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” ይላል። (ምሳሌ 16:31) ይሖዋ ያለብንን የአቅም ውስንነት ያውቃል እንዲሁም ደካማ ብንሆንም በሙሉ ልብ የምናቀርበውን አምልኮ በከፍተኛ አድናቆት ይመለከታል። ከዚህም በላይ እስካሁን ድረስ ያከናወንናቸውን መልካም ሥራዎች ፈጽሞ አይረሳም። ቅዱሳን ጽሑፎች ይህን ዋስትና ይሰጡናል፦ “እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም።” (ዕብራውያን 6:10) ይሖዋን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉ ክርስቲያኖች በመካከላችን የሚገኙ በመሆናቸው ሁላችንም እጅግ ደስ ይለናል!

ተስፋ አትቁረጡ

19. መልካም ነገር በማድረግ መጠመዳችን እንዴት ይጠቅመናል?

19 ብዙዎች ዘወትር ጥሩ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ የድካም ስሜትን ሊያቃልል እንደሚችል ያምናሉ። በተመሳሳይ አዘውትሮ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ማንኛውንም ስሜታዊም ሆነ መንፈሳዊ ድካም ለማቃለል ሊረዳ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት፤ ተስፋ ካልቈረጥን ጊዜው ሲደርስ መከሩን እናጭዳለን። ስለዚህ ዕድሉ ካለን ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ።” (ገላትያ 6:9, 10) ‘በጎ ነገር ማድረግ’ እና “መልካም እናድርግ” የሚሉትን አባባሎች ልብ በሉ። እነዚህ ቃላት ተግባር አስፈላጊ መሆኑን ያሳያሉ። ለሌሎች መልካም ነገሮች ማድረግ ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት እንዳንታክት ይረዳናል።

20. የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለመዋጋት ከምን ዓይነት ሰዎች መራቅ ይኖርብናል?

20 በአንጻሩ ደግሞ የአምላክን ሕግ ችላ ከሚሉ ሰዎች ጋር መቀራረብና ከእነርሱ ጋር በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ አድካሚ ሸክም ሊሆንብን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል፦ “ድንጋይ ይከብዳል፤ አሸዋም ሸክም ነው፤ የተላላ ሰው ጉነጣ ግን ከሁለቱም ይከብዳል።” (ምሳሌ 27:3) የተስፋ መቁረጥና የድካም ስሜትን ለመዋጋት አፍራሽ በሆኑ ነገሮች ላይ ከሚያውጠነጥኑ እንዲሁም ስህተት የመለቃቀምና ሌሎችን የመንቀፍ ዝንባሌ ካላቸው ሰዎች መራቅ ይኖርብናል።

21. በጉባኤ ስብሰባ ላይ ሌሎችን ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?

21 የጉባኤ ስብሰባ መንፈሳዊ ኃይል የምናገኝበት የይሖዋ ዝግጅት ነው። በስብሰባ ላይ መንፈስ በሚያድስ ትምህርትና በመካከላችን ባለው ወዳጅነት አማካኝነት አንዳችን ሌላውን የማበረታታት ግሩም አጋጣሚ አለን። (ዕብራውያን 10:25) በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ሲሰጡ ወይም መድረክ ላይ ወጥተው ክፍል ሲያቀርቡ ሌሎችን ለማነጽ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተለይ በማስተማሩ ሥራ ግንባር ቀደም የሆኑ ወንድሞች ሌሎችን የማበረታታት ኃላፊነት አለባቸው። (ኢሳይያስ 32:1, 2) ጉባኤውን በጥብቅ ማሳሰብ ወይም መውቀስ በሚያስፈልግበት ጊዜም እንኳ ምክሩ በሚያበረታታ መንገድ መቅረብ ይኖርበታል። (ገላትያ 6:1, 2) በእርግጥም ለሌሎች ያለን ፍቅር ይሖዋን ያለመታከት እንድናገለግለው ይረዳናል።—መዝሙር 133:1፤ ዮሐንስ 13:35

22. ፍጽምና የሚጎድለን ቢሆንም ልበ ሙሉ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

22 በዚህ የፍጻሜ ዘመን ይሖዋን ማምለክ በተግባር የሚታይ ነገር ማከናወን ይጠይቃል። ደግሞም ክርስቲያኖች የአእምሮ ውጥረት፣ የስሜት መቃወስና ሌሎች አስጨናቂ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ፍጽምና የሚጎድለው ሥጋችን እንደ ሸክላ ዕቃ ተሰባሪ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ይህ እጅግ ታላቅ ኀይል ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ አለመሆኑን ለማሳየት፣ ይህ የከበረ ነገር በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) አዎን፣ ሰውነታችን ሊዝል ቢችልም መንፈሳችን እንዳይደክም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲያውም “በሙሉ ልብ፣ ‘ጌታ ረዳቴ ነው’” እንበል።—ዕብራውያን 13:6

አጭር ክለሣ

• አንዳንድ ልናስወግዳቸው የምንችል ከባድ ሸክሞች ምንድን ናቸው?

• ለእምነት ባልንጀሮቻችን ‘መልካም ነገር ማድረግ’ የምንችለው እንዴት ነው?

• ሰውነታችን ሲዝል ወይም ተስፋ ስንቆርጥ ይሖዋ ብርታት የሚሰጠን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሐዋርያቱ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንደሚያጋጥማቸው አውቋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ክርስቲያኖች የተወሰኑ ጊዜ ማሳለፊያ ልማዶችንና አላስፈላጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን አስወግደዋል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአቅም ውስንነት ቢኖርብንም ይሖዋ በሙሉ ልብ የምናቀርበውን አምልኮ በከፍተኛ አድናቆት ይመለከታል