በሜክሲኮ የአገሬው ተወላጆች ምሥራቹን ሰሙ
በሜክሲኮ የአገሬው ተወላጆች ምሥራቹን ሰሙ
ኅዳር 10, 2002 በሜክሲኮ የአገሬው ተወላጅ የሆኑ ሚክ የሚባለው ጎሳ አባላት በሳን ሚጌል፣ ኬትሳልቴፔክ ተሰባስበው ነበር። ይህቺ ከተማ ውብ በሆነው ደቡባዊ የዋሃካ ግዛት ትገኛለች። እነዚህ ሰዎች በዚህ ቦታ የተሰባሰቡት በይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ነበር። በዚያን ዕለት በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ከቀረበው ፕሮግራም ድራማው የጎላ ቦታ ነበረው።
ተሰብሳቢዎቹ የድራማውን የመክፈቻ ቃላት ሲሰሙ በጣም ተደንቀው ነበር። ወዲያው ጭብጨባው ከዳር እስከ ዳር ያስተጋባ ሲሆን አብዛኞቹ ከደስታቸው የተነሳ አንብተዋል። ሕዝቡን ይህን ያህል ያስደሰተው ድራማው በሚክ ቋንቋ መቅረቡ ነበር! ድራማው ሲያበቃ ብዙዎች ለዚህ ያልተጠበቀ ዝግጅት የተሰማቸውን ጥልቅ አድናቆት ገልጸዋል። አንዲት እህት “ለመጀመሪያ ጊዜ ድራማውን መረዳት ቻልኩ። ልቤን በጥልቅ ነክቶታል” ብላለች። ሌላዋ ደግሞ “ይሖዋ በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ድራማውን እንድሰማ ስላስቻለኝ ከአሁን በኋላ ብሞትም አይቆጨኝም” በማለት ተናግራለች።
በዚያን ዕለት ጠዋት የተደረገው ይህ ዝግጅት የአገሬው ተወላጆች ምሥራቹን እንዲሰሙ ለማስቻል በሜክሲኮ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በቅርቡ እያደረጉት ያሉት ከፍተኛ ጥረት ክፍል ነው።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20
ይሖዋ ጸሎታቸውን ሰምቷል
በሜክሲኮ ከ6,000,000 በላይ የአገሬው ተወላጆች ይኖራሉ፤ የራሳቸውን መንግሥት ለመመሥረት የሚበቃ ብዛት ያላቸው እነዚህ ሕዝቦች የተለያየ ባሕል ያላቸው ሲሆን 62 ቋንቋዎች ይናገራሉ። ከእነዚህ ውስጥ አስራ አምስቱ ቋንቋዎች እያንዳንዳቸው ከ100,000 በላይ ተናጋሪ አላቸው። ከ1,000,000 የሚበልጡት የአገሬው ተወላጆች የሜክሲኮ ብሔራዊ ቋንቋ የሆነውን ስፓንኛ አይናገሩም። ስፓንኛ ከሚናገሩትም ቢሆን አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው ቋንቋ ቢማሩ በቀላሉ ይገባቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:6፤ 22:2) አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው ለዓመታት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በታማኝነት ሲገኙ የኖሩ ቢሆንም የሚረዱት የተወሰነውን ብቻ ነበር። በዚህም ምክንያት የእውነትን መልእክት በገዛ ቋንቋቸው ለመስማት እንዲችሉ ለረጅም ጊዜ ሲጸልዩ ቆይተዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ በሜክሲኮ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ከ1999 ጀምሮ በአገሬው ተወላጆች ቋንቋ የጉባኤ ስብሰባዎች ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት አደረገ። የተለያዩ የትርጉም ቡድኖችም ተቋቋሙ። በ2000 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ድራማው የቀረበው በማያ ቋንቋ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በሌሎች በርካታ ቋንቋዎችም ተዘጋጅቷል።
ቀጣዩ እርምጃ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎችን መተርጎም ነበር። በመጀመሪያ በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተሰኘው ብሮሹር ወደ ማሳቴኮ፣ ማያ፣ ቶቶናኮ፣ ዋቬ፣ ጼልታል እና ጾጺል ቋንቋዎች ተተረጎመ። ከዚያም ሌሎች ተጨማሪ ጽሑፎች የተተረጎሙ ሲሆን የመንግሥት አገልግሎታችን በማያ በቋሚነት ይታተም ጀመር። አንዳንድ ጽሑፎችም በካሴት ተዘጋጁ። የአገሬውን ተወላጆች በራሳቸው ቋንቋ ማንበብና መጻፍ ለማስተማር ማንበብና መጻፍ መማር (እንግሊዝኛ) የተባለው ብሮሹር ከአካባቢው ሁኔታ ጋር እንዲስማማ ተደርጎ በመዘጋጀት ላይ ነው። በአሁኑ ወቅት የአገሬው ተወላጆች ከሚናገሯቸው ቋንቋዎች በ15ቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ
ጽሑፎች የሚዘጋጁ ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ ጽሑፎችም በቅርቡ ይወጣሉ።‘የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል’
የትርጉም ሥራው ቀላል አልነበረም። አንደኛ ነገር፣ በሜክሲኮ በአገሬው ተወላጆች ቋንቋ የተዘጋጁ ዓለማዊ ጽሑፎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ መዝገበ ቃላት ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። አንዳንዶቹ ቋንቋዎች በርካታ ቀበልኛ ያላቸው መሆኑ ደግሞ ሌላው ችግር ነው። ለምሳሌ ያህል የሳፖቴክ ቋንቋ በትንሹ አምስት ያህል ቀበልኛዎች አሉት። እነዚህ ቀበልኛዎች በጣም የተለያዩ ከመሆናቸው የተነሳ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የሳፖቴክ ጎሣ አባላት እርስ በርስ መግባባት አዳጋች ይሆንባቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ቋንቋው የራሱ ሥርዓት በማይኖረው ጊዜ ተርጓሚዎቹ ራሳቸው ለቋንቋው ሕግጋት ማዘጋጀት አስፈልጓቸዋል። ይህም ብዙ ምርምርና ሌሎችን ማማከር የሚጠይቅ ሥራ ነው። መጀመሪያ ላይ አብዛኞቹ ተርጓሚዎች የዋቭ ቋንቋ ተርጓሚ እንደሆነችው እንደ ኢሊዳ ተሰምቷቸው የነበረ መሆኑ አያስገርምም! “ለትርጉም ሥራ በሜክሲኮ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ስጠራ በአንድ በኩል ደስ ቢለኝም በሌላ በኩል ግን ፍርሃት አድሮብኝ ነበር” በማለት ታስታውሳለች።
ተርጓሚዎቹ የኮምፒውተር ሥልጠና መውሰድ እንዲሁም ሥራቸውን በፕሮግራም መሥራትንና የአተረጓጎም ዘዴዎችን መማርም አስፈልጓቸው ነበር። በእርግጥም ሥራው ተፈታታኝ ሆኖባቸው ነበር። ስለሚያከናውኑት ሥራ ምን ይሰማቸዋል? የማያ ቋንቋ ተርጓሚ የሆነችው ግሎሪያ እንዲህ በማለት ትመልሳለች፦ “የአፍ መፍቻ ቋንቋችን ወደሆነው ወደ ማያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመተርጎሙ ሥራ በመካፈላችን በቃላት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ተደስተናል።” የትርጉም ሥራው የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም ስለ ተርጓሚዎቹ ሲናገር “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በራሳቸው ቋንቋ ለማግኘት አጥብቀው ስለሚፈልጉ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ለመወጣት የሚቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው” ብሏል። ጥረታቸው ፍሬ አስገኝቶ ይሆን?
“ይሖዋ አመሰግንሃለሁ”
ይሖዋ ለአገሬው ተወላጆች ምሥራቹን ለማካፈል የሚደረገውን ጥረት እንደባረከው በግልጽ እየታየ ነው። በጉባኤ ስብሰባዎችና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር በብዙ እጥፍ ጨምሯል። ለምሳሌ፣ በ2001 የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር 223 የሚያህሉት የሚክ ቋንቋ ተናጋሪ የይሖዋ ምሥክሮች ተሰብስበው የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ በበዓሉ ላይ የተገኙት ግን 1,674 ነበሩ፤ ይህም ከአጠቃላዩ የወንድሞች ቁጥር ከሰባት እጥፍ በላይ ማለት ነው!
በአሁኑ ጊዜ እውነትን የሚማሩ ሰዎች ገና ከመሠረቱ ጥሩ ግንዛቤ ማግኘት ችለዋል። ሚርና በማያ ቋንቋ ስብሰባ መካሄድ ከመጀመሩ በፊት ያጋጠማትን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ትላለች፦ “የተጠመቅሁት መጽሐፍ ቅዱስን ለሦስት ወራት ካጠናሁ በኋላ ነበር። መጠመቅ እንዳለብኝ ባውቅም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መረዳት የሚገባኝን ያህል እንዳልተረዳሁ አልክድም። ለዚህም ምክንያቱ አፌን የፈታሁት በማያ ቋንቋ መሆኑና ስፓንኛ በደንብ አለመቻሌ ይመስለኛል። እውነትን በሚገባ ለመረዳት ጊዜ ወስዶብኛል።” በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቷ ጋር በማያ የትርጉም ክፍል ውስጥ በደስታ ያገለግላሉ።
በራሳቸው ቋንቋ ጽሑፎች ማግኘት በመቻላቸው በጉባኤ ውስጥ ያሉት በሙሉ ተደስተዋል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመረች አንዲት ሴት በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው ብሮሹር በጾጺል ቋንቋ ተተርጉሞ ሲወጣ ብሮሹሩን ደረቷ ላይ ልጥፍ አድርጋ
“ይሖዋ አመሰግንሃለሁ!” በማለት በደስታ ተናገረች። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ፈጣን እድገት አድርገው መጠመቅ እንደቻሉ፣ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያቸውን አቁመው የነበሩ አስፋፊዎች እንደገና እንደተበረታቱና ብዙ ክርስቲያን ወንድሞች አሁን በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ እንደሆኑ እንደሚሰማቸው ሪፖርቶች ያሳያሉ። በአገልግሎት ላይም አንዳንዶች በራሳቸው ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ ሲቀርብላቸው ለመቀበልና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ይበልጥ ፈቃደኞች ሆነዋል።በአንድ ወቅት አንዲት የይሖዋ ምሥክር ወደ ጥናቷ ቤት ስትሄድ ጥናቷን ታጣታለች። የሴትየዋ ባል ሊያነጋግራት ወደ በሩ ሲመጣ ከአንድ ብሮሹር ላይ ልታነብለት ትችል እንደሆነ ጠየቀችው። “ምንም ነገር አልፈልግም” ሲል መለሰላት። እህታችን ብሮሹሩ የተዘጋጀው በእነርሱ ቋንቋ መሆኑን በቶቶናኮ ነገረችው። ሰውየው ይህን ሲሰማ ወንበር ስቦ ተቀመጠና ስታነብለት ያዳምጥ ጀመር። እያነበበችለት እያለ እየደጋገመ “እውነት ነው። አዎን፣ ትክክል ነው” ይል ነበር። አሁን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛል።
በዩካታን ግዛት የአንዲት የይሖዋ ምሥክር ባል እውነትን የሚቃወም ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ጊዜ ከስብሰባ ወደ ቤት ስትመለስ ይደበድባት ነበር። በማያ ቋንቋ ስብሰባ መካሄድ ሲጀምር እህት በስብሰባው ላይ እንዲገኝ ጋበዘችው። ይህ ሰው ስብሰባውን ከተመለከተ በኋላ በጣም ወደደው። አሁን በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ያጠናል፤ ሚስቱን መደብደብም አቁሟል።
የቶቶናኮ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ አንድ ሰው የካቶሊኩ ቄስ አምላክ የሚሰማው በስፓንኛ የሚቀርቡ ጸሎቶችን ብቻ እንደሆነ ስለነገሩት ጸልዮ እንደማያውቅ ለሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ነገራቸው። እንዲያውም ቶቶናኮ ተናጋሪ የሆኑ 2 ዜና መዋዕል 6:32, 33፤ መዝሙር 65:2
ሰዎችን ወክለው ጸሎት እንዲያቀርቡ ለቄሱ ይከፍላቸው ነበር። ምሥክሮቹ አምላክ በሁሉም ቋንቋ የሚቀርቡ ጸሎቶችን እንደሚሰማ ከነገሩት በኋላ በቶቶናኮ የተዘጋጀ ብሮሹር ሲሰጡት በደስታ ተቀበላቸው።—“ኩኣልጺን ታክቶኣ”
እነዚህ እድገቶች ያስደሰቷቸው በርካታ የመንግሥቱ አስፋፊዎች የአገሬው ተወላጆች ከሚናገሯቸው ቋንቋዎች አንዱን ለመማር ወይም ችሎታቸውን ለማሳደግ እየጣሩ ነው። በሰሜናዊ ፕዌብላ ግዛት የናዋተል ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ አምስት ጉባኤዎች የሚያገለግል አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንደዚህ እያደረገ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ያንቀላፉ የነበሩ ልጆች አሁን በናዋተል ቋንቋ ስናገር ንቁ ሆነው በትኩረት ያዳምጣሉ። አንድ ቀን ከስብሰባው በኋላ አንድ የአራት ዓመት ልጅ ወደ እኔ መጣና ‘ኩኣልጺን ታክቶኣ ’ (ጥሩ አድርገህ ትናገራለህ) አለኝ። ይህን ስሰማ ጥረቴ ከንቱ እንዳልሆነ ተገነዘብሁ።”
በእርግጥም በሜክሲኮ የአገሬው ተወላጆች መስክ ‘አዝመራው ለመከር ደርሷል’፤ በዚህ የመከር ሥራ የተካፈሉት ሁሉ በጣም ተበረታተዋል። (ዮሐንስ 4:35) የትርጉም ቡድኖቹን በማደራጀቱ ሥራ የተካፈለው ሮቤርቶ እንዲህ በማለት ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል፦ “ወንድሞችና እህቶቻችን እውነትን በገዛ ቋንቋቸው ሰምተው መረዳት በመቻላቸው የደስታ እንባ ሲያነቡ መመልከቴ ፈጽሞ የማይረሳ ትዝታ ጥሎብኛል። የተከናወነውን ሥራ ሳስበው የደስታ ሲቃ ይተናነቀኛል።” ቅን ልብ ያላቸው እነዚህ ሰዎች ከመንግሥቱ ጎን እንዲቆሙ መርዳት የይሖዋንም ልብ ደስ እንደሚያሰኝ ምንም ጥርጥር የለውም።—ምሳሌ 27:11
[በገጽ 10,11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከተርጓሚዎቹ መካከል አንዳንዶቹን እንተዋወቅ
● “ወላጆቼ ማስታወስ ከምችልበት ዕድሜ አንስቶ እውነትን አስተምረውኛል። የሚያሳዝነው የ11 ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ እውነትን ተወ። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ እናቴ ጥላን ሄደች። ከአምስት ልጆች የመጀመሪያዋ ስለነበርኩ ገና ትምህርቴን ባልጨርስም እንኳ የእናቴን ኃላፊነት ለመሸከም ተገደድሁ።
“የመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍቅራዊ ድጋፍ ያልተለየን ቢሆንም ሕይወት ቀላል አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ ‘ገና በልጅነቴ ይህ ሁሉ የሚደርስብኝ ለምንድን ነው?’ ብዬ አስብ ነበር። ይሖዋ ባይረዳኝ ኖሮ ችግሩን ልቋቋመው ባልቻልኩ ነበር። የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ፤ ይህም በጣም ጠቅሞኛል። በናዋታል ቋንቋ የትርጉም ክፍል ሲቋቋም በዚህ ሥራ እንድካፈል ተጋበዝኩ።
“በአሁኑ ወቅት አባቴ ወደ እውነት ተመልሷል፤ ታናናሽ ወንድሞቼና እህቶቼም ይሖዋን እያገለገሉ ነው። ለይሖዋ ታማኝ ሆኜ ለመኖር ያደረግሁት ጥረት በከንቱ አልቀረም። ይሖዋ ቤተሰቤን አብዝቶ ባርኮታል።”—አሊስያ
● “ትምህርት ቤት እያለሁ አብራኝ የምትማር አንዲት የይሖዋ ምሥክር ስለ ሕይወት አመጣጥ በክፍል ውስጥ ንግግር አቀረበች። በዚያን ዕለት በክፍል ውስጥ ስላልነበርኩና ፈተና ላይ ምን ብዬ እንደምመልስ ስላሳሰበኝ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ እንድታብራራልኝ ጠየቅዃት። ሰዎች ለምን እንደሚሞቱ ሁልጊዜ ያሳስበኝ ነበር። ፍጥረት የተባለውን መጽሐፍ a ሰጠችኝ፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና ስትጠይቀኝም ተስማማሁ። የፈጣሪ ዓላማና ለእኛ ያለው ፍቅር ልቤን ነካው።
“ትምህርቴን ስጨርስ የስፓንኛና የጾጺል ቋንቋ መምህር የመሆን አጋጣሚ ነበረኝ። ሆኖም ሥራው ራቅ ወዳለ አካባቢ መሄድን የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ቅዳሜና እሁድ ተጨማሪ ትምህርት ለመማር ከጉባኤ መቅረት ሊኖርብኝ ነው። ስለዚህ ይህንን አጋጣሚ ተውኩና ግንበኛ ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። የይሖዋ ምሥክር ያልነበረው አባቴ በውሳኔዬ ፈጽሞ አልተደሰተም። በኋላ ላይ አቅኚ ሆኜ እያገለገልኩ እያለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ጾጺል ቋንቋ የሚተረጉም ቡድን ተቋቋመ። በዚህ ሥራ የመካፈል ፍላጎት አደረብኝ።
“ወንድሞችና እህቶች በራሳቸው ቋንቋ ጽሑፎች ማግኘታቸው እንደሚወደዱና እንደሚከበሩ እንዲሰማቸው የሚያደርግ እንደሆነ ተመልክቻለሁ። ይህ ደግሞ ከፍተኛ እርካታ ይሰጠኛል። ይህንን ሥራ የማከናወን መብት ስላገኘሁ ክብር ይሰማኛል።”—ሁምቤርቶ
● “በስድስት ዓመቴ እናቴ ትታን ሄደች። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። አንድ ቀን አንዲት እህት መጽሐፍ ቅዱስ ልታስጠናኝ ፈቃደኛ መሆኗን ነገረችኝ፤ ጥናቱ ለወጣቶች የሚሆን ምክርንም የሚጨምር ነበር። ያለ እናት ያደግሁ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምገኝ ወጣት እንደመሆኔ ይህ በጣም የሚያስፈልገኝ ነገር እንደሆነ ተሰማኝ። አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ ተጠመቅሁ።
“በ1999 አባቴ መሬቱን ሊወስዱ በፈለጉ መጥፎ ሰዎች ተገደለ። ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ። በጣም ተስፋ ስለቆረጥኩ በሕይወት መቀጠል እንደማልችል ተሰማኝ። ሆኖም ይሖዋ ኃይል እንዲሰጠኝ መጸለዬን አላቋረጥሁም። ተጓዥ የበላይ ተመልካቹና ባለቤቱ በጣም አበረታቱኝ። ብዙም ሳይቆይ የዘወትር አቅኚ ሆንኩ።
“በአንድ ወቅት በቶቶናኮ ቋንቋ የሚቀርብ የ20 ደቂቃ ንግግር ለማዳመጥ ሲሉ ለስድስት ሰዓታት በእግራቸው ተጉዘው ስብሰባ ላይ የሚገኙ ወንድሞች ተመልክቼ ነበር፤ ቀሪው የስብሰባው ክፍል የሚካሄደው በስፓንኛ ሲሆን ይህን ቋንቋ ደግሞ አይረዱትም። ስለዚህ በቶቶናኮ ቋንቋ የሚዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመተርጎሙ ሥራ እንድካፈል ስጋበዝ በጣም ተደሰትኩ።
“በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የማገልገል ፍላጎት እንዳለኝ ለአባቴ እነግረው ነበር። እርሱም በእኔ ዕድሜ ለምትገኝ ያላገባች ወጣት ይህንን ማድረግ ቀላል እንዳልሆነ ይገልጽልኝ ነበር። በትንሣኤ እንደገና ስንገናኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ቋንቋችን በመተርጎም የተመኘሁትን ማድረግ እንደቻልኩ ሲመለከት ምን ያህል ይደሰት ይሆን!”—ኢዲት
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በ1985 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? የተባለው መጽሐፍ።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጾጺል ትርጉም ቡድን አባላት ለመተርጎም አስቸጋሪ በሆነ ቃል ላይ ሲወያዩ